በንጹሃን ዜጎች ላይ እየተፈጸመ ያለውን ጅምላ ግድያ በጥብቅ እናወግዛለን
ወታደራዊ ጡንቻውን እና የስለላ መረቡን መከታ በማድረግ የስልጣን ዕድሜውን ለማራዘም ቆርጦ የተነሳው የወያኔው የማፊያ ቡድን፣ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት ላይ ያነጣጠረውን የጥፋት ኢላማ እና የቀሰረውን ጣት ዛሬም አጠናክሮ ቀጥሎበታል። ብልሹው ስርዓት በፈጠረው የፍትሕ ጉድለት እና የአስተዳደር በደሎች የተነሳ ህዝባዊ ተቃውሞዎችና አመጾች መቀስቀሳቸው የግድ ነው። በማስተር ፕላን ሽፋን የአዲስ አበባ ዙሪያ ከተሞችን ለመጨፍለቅና የአርሶ አደሮችን ህልውና የሚፈታተነውን የወያኔን የጥፋት ፖሊሲ በመቃወም የምዕራብ ሸዋ የአምቦ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በሰላማዊ ሰልፍ ተቃውሟቸውን ለመግለጽ አደባባይ ቢወጡም የተማሪዎቹ የፍትሕ ጥያቄ እንደ ወንጀል ተቆጥሮ ወከባ፣ እስራት እና ግድያ በተማሪዎች ላይ ተፈጽሟል።
ሰብዓዊነት ፍጹም ያልፈጠረበት ይህ ነፍሰ ገዳይ ቡድን በእብሪትና በማን አለብኝነት የንጹሃን ተማሪዎችን ደም በከንቱ ማፍሰሱ ሳይበቃ ይባስ ብሎ የተማሪዎችን ፍትሐዊ ጥያቄ ወደ ተቃዋሚ ሀይሎች ማሳበቡ ሥርዓቱ በሕዝብ ላይ ምን ያህል ንቀት እንዳለው በገሀድ ያሳያል። የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር በኢንቨስትመንትና በማስተር ፕላን ሽፋን ዜጎችን ማፈናቀል፣ ማዋከብ እና ጅምላ ግድያን መፈጸም አሳፋሪ ወንጀል መሆኑን እየገለፀ በተማሪዎች ላይ የተወሰደውን የጭካኔ እርምጃ በጥብቅ ያወግዛል።
ይኸው እብሪተኛ ቡድን በሁሉም የሀገሪቱ ዜጎች ላይ እየፈጸመ ያለውን በደልና ሰቆቃ አጠናክሮ ቀጥሏል። የጎንደር፣ የአፋር፣ የጋምቤላና የኦጋዴን አርሶ አደር ወገኖቻችን ከእርሻ መሬታቸው ተፈናቅለው አውላላ ሜዳ ላይ ተጥለዋል፣ ታስረዋል፣ ተገድለዋል። አሸባሪው የወያኔ ቡድን የምርጫ ድራማ በተቃረበ ቁጥር እና ለተዘፈቀበት ውስጣዊ ቀውስና ውጥረት፣ ዜጎችን ማሸበር እና ማስፈራራት እንዲሁም ብቀላና ግድያን መፈጸም ወያኔ እንደ ማስታገሻ መድሀኒት እንደሚጠቀምበት ለማናችንም ቢሆን የተሰወረ ሚስጥር አይደለም። በመሆኑም ኢትዮጵያንና ዜጎቿን ከወያኔው የስጋት ቀጠና ለማውጣትም ሆነ በሀገሪቱ ምድር ስርዓቱ የቀበረውን የዘረኝነት ፈንጅ ማምከን ዛሬ ወቅቱ የጠየቀው ሀቅ ነው። ስለሆነም ወያኔ በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያዊነት ላይ ያነጣጠረውን የጥፋት ኢላማ ለማክሸፍ ከእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሞራላዊና ህሊናዊ ግዴታ የሚጠበቅ በመሆኑ መላ ኢትዮጵያዊ በተጀመረው ሕዝባዊ ተጋድሎ የበኩሉን አስተዋጾ ያደርግ ዘንድ የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ወገናዊና ሀገራዊ ጥሪውን ያቀርባል።
የህዝብ ወገናዊነቱን እና ጥቃት መላሽነቱን በድርጊት እያስመሰከረ የመጣው የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር በነፍሰ ገዳዩ የወያኔ ቡድን የፈሰሰው የወገኖቻችን ደም ከንቱ ሆኖ እንደማይቀር የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ለጠላትም ለወገንም ያስገነዝባል።
አንድነት ኃይል ነው!!!
የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር