February 13, 2013
85 mins read

ቤተ ክርስቲያን ከፓትርያርክ ምርጫና ከአንድነት የትኛውን ልታስቀድም ይገባታል? ስለምን?

/ውሉደ አበው ዘተዋሕዶ/

ቤተ ክርስቲያን ከፓትርያርክ ምርጫና ከአንድነት የትኛውን ልታስቀድም ይገባታል? ስለምን?

ክፍል አንድ

ለሺህ ፍልጥ ማሰሪያው ልጥ የሚለውን የቆየ ብሂል ስንሰማው ወይም ስንናገረው የኖርነው ነውና አዲስ አይሆንብንም። ለፍልጥ ብቻ ሳይሆን ተበታትነው ላሉ የተለያዩ ነገሮች ሁሉ ልጥም ባይሆን በመልክ በመልካቸው አንድነት እንዲቆሙ ለማድረግ የሚያስችል አንድ ማሰሪያ አይጠፋም። የማሰሪያው መኖር አንድነቱን ያጸናዋል። አንድ የሆነ አካል ወርዱም ስፋቱም ርዝመቱም ይታወቃል። ቅርጽና ጠባዩም ይለያል። የአንዱ መኖር የሌላውም የሕልውና መሠረቱ ነውና አንዱ ሌላውን እንደ ዐይኑ ብሌን ይጠብቀዋል። አንዱ ለሌላው ውበቱም ጥንካሬውም ማንነቱም ሥልጣኑም ነው። ከሺሁ መካከል አንድ ስትጎድል የታሰረው ፍልጥ ይላላል። አንዲት ስትጎድል አንድነት አደጋ ላይ ይወድቃል። ስለሆነም አንዲትም ስንኳ እንዳትሾልክ የሁሉም ፍልጦች ሓላፊነት ነው። ካመለጠችና ከሾለከች ግን ሌሎቹም ጠብ ጠብ እያሉ መሹለካቸው አይቀርም። ሰለሆነም አንዷን ማጣት ሁሉንም ከማጣት አይተናነስም። በመሆኑም አንዷ እንዳትነጠል ወይም እንዳትባዝን የሚከፈለው መሥዋዕትነት ሰለሁሉም ተደርጎ ይወሰዳል።

ለዚሀም ነው ጌታችን መድኃኒታችን አምላካችን ኢየሱሰ ክርስቶስ ከመቶ በጎች አንዲት ብትጎድልበት ዘጠና ዘጠኙን ትቶ የባዘነችውን ወይም የጠፋችውን አንዲት በግ ለመፈለግ ከሰማያዊ መንበሩ ከየማነ አብ ከዘባነ ኪሩብወደዚሀ ዓለም የመጣው። መምጣት ብቻ አይደለም ሊነገር የማይችል ግፍ የደረሰበት። የተበደለ እርሱ የካሠም እርሱ በፍቅር ማሰሪያ የተበተኑት ልጆቹን አንድ ለማድረግ ከቤተልሔም እስከ ቀራንዮ የሄደም እርሱ! ክብር እና ምስጋና ይግባውና ከልደቱ እስከ ትንሣኤው የሰበከው ”እነዚህን የሰጠኸኝን እንደ እኛ አንድ እንዲሆኑ በስምህ ጠብቃቸው።” ያለውን ነው። ዮሐ ፲፯፥፲፩። ከጌታችን ጸሎት የምንረዳው ዐቢይ ቁም ነገር አንድነትን መግፋት ከጌታ ፈቃድ ውጪ መሆን ማለት መሆኑን ነው።አንድነት ካለ ሰላም አለ ሰላምም ካለ አንድነት አለ። ሁለቱ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው። በምድር ያሉ የሰው ልጆች ያጡት ይኽንን ሰላም ነበረና ከቤተልሔም እስከ ቀራንዮ ከዚያም እስከ ትንሣኤ በጌታችን የተሰበከው እርሱ ነው።

+ ገና በትንቢት ሲነገርለት የሰላም አለቃ ተብሎ ተጠርቷል። ኢሳ ፱፥፮።

+ በተወለደም ጊዜ የሰማይ መላእክት በምድር ካሉ አረኞች ጋር “ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ስምረቱ ለሰብእ-በሰማይ ለአግዚአብሔር ምስጋና፣ በምድርም ሰላም፣ ለሰው ልጆችም በጎ ፈቃድ” ብለው ዘምረዋል። ሉቃ ፪፥፲፬።

+ የመጣው ሰላሙን ሊተውልን ሰላሙን ሊሰጠን መሆኑንም ነግሮናል። ዮሐ ፲፬፥፳፯።

+ በቀራንዮ አደባባይ እንደ ብራና ተወጥሮ በመልእልተ መሰቀል ላይ ሆኖም ያደረገው ታርቆ በማሰታረቅ ሰላምን መስጠት ሰላምን ማድረግ እንደሆነ ተነግሮናል። ገብረ ሰላመ በደመ መስቀሉ እንዲል። ቆላ ፩፥፳።

+ መግነዝ ፍቱልኝ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል በገዛ ሥልጣኑ ሞትን በሞቱ ሽሮ ለቅዱሳን ሐዋርያት ሲገለጥላቸው “ሰላም ለሁላችሁ ይሁን” እያለ ነው። ዮሐ ፳፥፲፱።

በጥቂቱ ከአነዚህ የመጽሐፍ ክፍሎች ስንነሣ ጌታችን ከቤተልሔም እስከ ቀራንዮ የሰበከው ሰላምን ተፋቅሮን እርቅን መሆኑን ማበል አይቻልም። የቤተ ክርስቲያን የአንድነት ልጥ ሰላም ነውና። ሰላም ስንል በቤተ ክርስቲያን አባቶች አና አባቶች፣ ወንድሞች እና እኅቶች፣ አባቶች እና ልጆች መካከል ሊኖር ስለሚገባውማለታችን መሆኑን ማስገንዘብ እንወዳለን።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አባቶች መካከል ለሃያ አንድ ዓመታት የኖረው መቋሰል እና መቆራቆስ አሁንም አነጋጋሪ አንደሆነ ይገኛል። በዚህ ወቅት እነማን ለቤተ ክርስቲያን አንድነትና ክብር እንደቆሙ፣ እነማን ደግሞ ከቤተ ክርሰቲያን ይልቅ ለሆዳቸው፣ ለፍቅረ ሢመታቸውና ለግትርነታቸው ዘብ እንደሆኑ ለማየትም ለመታዘብም ችለናል። የመጀመሪያዎቹ በቁጥር የሌሉ እስኪመሰሉ ድረስ ትንፋሻቸውን እንኳ ጆሯቸው እንዳይሰማባቸው የሚጠነቀቁ፣ በፍርሃት የተሸበቡ ሲሆኑ ሁለተኛዎቹ ደግሞ ከቁጥራቸው በላይ አብጠውና ገንነው ጥቅማቸውን ለማርካት ጠብ ርግፍ እያሉ ናቸው።

የሁለተኞቹ መልካቸው ብዙ ሲሆን የተወሰኑት መለካውያን ወይም ፈጻምያነ ፈቃደ መኳንንት ሲሆኑ ውለው ባደሩ ቁጥር አለቆቻቸውን ምን ደባ በመፈጸም እንደሚያሰደስቱ የሚጨነቁ ናቸው። ወንድሞቻቸውን አንኳ ሰውተው ቢሆን አለቆቻቸውን በማስደሰት ተደላድለው ለመኖር የሚቋምጡ በየሥራ ቦታቸው ያለባቸውን የሥራ ድክመት እና ሌላ የጉድ ጅራት ለማለባበስ ስተው በማሳሳት የተሰማሩ ናቸው። የተቀሩት ደግሞ በፍርሃታቸው እምነታቸውን አስጨንቀው አስረው ወደሞቀበት እየደነበሩ አቧራ የሚያስነሱ ገላግልት ናቸው። ሌሎቹ ደግሞ በዐይነ ስውር ቤት አንድ ዐይና ብርቅ ነው እንዲሉ ጥቂት የማንቆለጳጰስ ሥራ እንዲሠሩ የተመደቡ በቻሉት አጋጣሚ የእርቁ ሂደት ወማ እንዲበላው የሚጋረፉ የስድብ አፍ የተሰጣቸው ናቸው። ሌሎቹ ደግሞ ፈርተው የሚያስፈሩ ደንግጠው የሚያስደነግጡ ደንብረው የሚያስደነብሩ የፍርሃት መንፈስን የተቀቡ የአበው በረከት የተለያቸው እንደ እሽኮኮ ዘወትር በስጋት የተወጠሩ ናቸው።

እንዲህ እና እንዲያ እያልን ብንፈነካክታቸው ብዙ ቁርጥራጮች ይወጣቸዋል እንጂ ወጥነት አይገኝባቸውም። እነርሱን ግን አንድ ነገር አገናኛቸው እንጂ ስምምነት እንደሌላቸው ሩቅ ሳንሄድ የተንገበገቡለት ምርጫ ደርሶ ብትንትን ብለው ዞረው የእርስ በእርስ የጦር ዐውድማ ላይ ሲተጋተጉ ማየታችን አይቀርም። ሌቦች ሲሰርቁ ተስማምተው ሲከፋፈሉ ተጣልተው ይላል የአገራችን ሰው።

እንደነዚህ ያሉ ማሽንክ አስተሳሰብ ያላቸው መንፈሳውያን መሳይ ያሉትን ያኽል ደግሞ እስከ መጨረሻው ለማተባቸው የታገሉ መኖራቸውን አንክድም። በዚህ ጎራ ያሉት በሁለት መልክ የሚታዩ ናቸው። እስከመጨረሻዋ ሰዓት ለእርቀ ሰላሙ ቅድሚያ ይሰጥ በሚለው የጸኑ፣ ቁጥራቸው ቢያንስም መዓዛቸው ከሩቅ የሚጣራ ዉሉደ ሰላም ናቸው። ባልተሸራረፈ ጽናታቸው ትውልዱም ታሪክም በወርቅ ቀለም የጻፋቸው በረከተ አበው የደረሳቸው ጀግኖች ናቸው። በሌላ በኩል ያሉት ደግሞ መጋፈጡን ችላ ብለው ግን እርቀ ሰላሙ ይቅደም የሚለውን ከመደገፍ የማያባሩ አባቶች ናቸው። እንደ መጀመሪያዎቹ ፊት ለፊት ሲታገሉ አልታዩ ወይ አልተሰሙ ይሆናል እንጂ ድምፃቸውን ለቤተ ክርስቲያን አንድነት የገበሩ በመሆናቸው ሳናመሰግናቸው አናልፍም። ስለነዚህ አባቶች ስንናገር ግን እንዲያ ወይም እንዲህ ማለት ወይም ማድረግ ነበረባቸው እያልን አንገት እንዳናስደፋ ልንጠነቀቅላቸው ይገባል። በዙሪያቸው ያለውን እንቅስቃሴም መረዳት ግድ ይላልና።

ማንም በአንድ ቀን የታጠበ አና የጸዳ ሊሆን ከባድ ነውና ከነባራዊው ሁኔታ ተነሥተን የደረሱበትን ተረድተን ከጎናቸው ልንቆምላቸው ይገባል። የፍጹማንን ሥራ ከእነርሱ በመጠበቅ ብቻ የድርሻችንን ሳንወጣ እንዳንቀር ደጋግመን ማሰብ ይጠበቅብናል። ሳኦል እያለ ብላቴናውን ዳዊትን ያሰነሣውን አምላክ የምናምን ነንና። ብርቱዎቹ እያሉ በደካሞቹ ሥራ መሥራት ልማዱ የሆነ ጌታ በተናቁት የሚሠራውን ማን ያውቃል? ስለሆነም የምናውቀውን አምላክ እንደማናውቀው ሁሉ በአመክንዮአዊ አካሄድ ተስበን አባቶች ዝም ያሉትን እኛ ምን ልናደርግ እንችላለን? በማለት ተስፋ አንቁረጥ።

ነቢዩ ዳንኤል እያለ በሠለስቱ ደቂቅ ሥራውን የሠራ ፈጣሪ፣ ባርቅ፥ ዛብሎንና ንፍታሌም እያሉ ዲቦራን ያሥነሳ እግዚአብሔር፣ ቅድስት እየሉጣ ሳለች በሕፃኑ ቂርቆስ ሰማዕትነት የተመሰገነ ጌታ፣ ሊቃውንቱ እያሉ ዓሣ አጥማጆችን የጠራ መድኃኔዓለም በማን አድሮ ምን እንደሚያደርግ ማን ያውቃል? በእርሱ ዘንድ የተናቀው ልቡ የደነደነ እያወቀ የማያውቀው እንጂ የልብ ንጽሕና ካላቸው ዘንድ መቼ ርቆ ያውቅና።

እውን ዛሬ ለምናያት ቤተ ክርስቲያን የሚያስፈልጋት የትኛው ነው? የፓትርያርክ ምርጫ ወይስ ዕርቅ

አባቶቻችንን እንዲህ ከፋፍለን እንድናያቸው ያደረግን ሌላ ሳይሆን ለእናት ቤተክርስቲያናችን አንገብጋቢ እና ጊዜ የማይሰጥ ችግሯ እየሰጡት ያሉት ምላሽ እንደሆነ ግልጽ ነው ብለን እናምናለን፡፡ሰው ያልበላውን ቢያኩለት እንዴት መፍትሔ ሊሆነው ይችላል? እንዲያውም ያልበላውን ያከኩ ጊዜ ሌላ ሕማም ወይም ስቃይ ጨመሩለት እንጂ እንዴት መድኃኒቱ ይሆናል? እግሩ ቆስሎ ሐኪም ቤት የሄደን ሰው እጁን ቢዳስሱለት ምን ይበጀዋል? ወይስ ዐይኑን ለታመመ ወገቡን ቢያክሙት ምን ይጠቅመዋል? ይህንን ጌታችን በወንጌል እንዲህ ሲል ገልጦታል። አባት ከሆናችሁ ከእናንተ ከማንኛችሁም ልጁ እንጀራ ቢለምነው፥ እርሱም ድንጋይ ይሰጠዋልን? ዓሣ ደግሞ ቢለምነው በዓሣ ፋንታ እባብ ይሰጠዋልን? ሉቃ ፲፩፥፲፩። የሚያስፈልገው ሌላ የተሰጠው ሌላ። መፍትሔው ሌላ በመፍትሔነት የቀረበው ደግሞ ሌላ። ዓሣ መፍትሔው ሲሆን የሚሰጠው እባብ ከሆነ ሰጪውስ ሰጪ ነውን?

ቅድስት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ያዘነችበት የተጎዳችበት ዋና ጉዳይ እያለ እርሱን ሁለተኛ ወይም መጨረሻ አድርጎ በመመልከት ቤተ ክርስቲያን እፎይታ ልታገኝ አትችልም። ዓሣ ስትጠይቅ እንዴት እባብ እንሰጣታለን? ባጎረሰች እንዴት ትነከሳለች። ለመሆኑ ለወቅታዊው የቤተ ክርስያን ችግር ትክክለኛው መፍትሔ የቱ ነበር? ምንም እንኳ ሂደቱ ከፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት ነጻ ነው ለማለት ባይቻልም ከላይ እንደገለጽነው የአባቶቻችን ልዩነት ጎልቶ የወጣው ለዓሣው ጥያቄ ምላሹ እባብ ሆኖ በቀረበው የፓትርያሪክ ምርጫ ጉዳይ ነው፡፡ በአንደኛ ወገን ያሰቀመጥናቸው ወገኖች እርቀ ሰላሙ እየቀጠለ ነገር ግን ያለምንም መዘግየት የፓትርያሪክ ምርጫ መካሄድ አለበት ሲሉ ሁለተኞቹ ምናልባትም ድምፃቸው ባልፈለጉት መንገድ የታፈነባቸው ደግሞ ያልታረቀች ቤተ ክርስቲያን እንዴት ለሹመት ትጣደፋለች በማለት ልዩነታቸውን ቢያስቀምጡም ለጊዜውም ቢሆን የመጀመሪያዎቹ ያሸነፉ በሚመስል መልኩ የብዙዎቹን ፍላጎት እነደረመጥ በማዳፈን የምርጫ ሽርጉዱ ተጀምሯል፡፡

ለመሆኑ የየትኛው ወገን አስተሳሰብ ሊደገፍ ይገባዋል?
ሁለቱም አማራጮች በአንድ ጊዜ ሊደገፉ የማይችሉ ነገር ግን እውነት ስፍራ ያገኘች ጊዜ አንዱ በሌላው ላይ ተደጋግፈው የሚቆሙ እንጂ ተነፃፃሪ ባሕርይ የላቸውም። ይህም ልክ እንደ ቤት መሠረት እና እንደ ጣሪያና ግድግዳ ያደርጋቸዋል። ከቅዱስ ላሊበላ አብያተ መቅድስ በስተቀር መሠረቱን የቀደመ ጣሪያ ኖሮ አያውቅምና ሁሉም ቅደም ተከተሉን ሥርዓቱን ጠብቆ ሊመጣ ግድ ነው። ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በታሪክ ሂደትም ሆነ በመጽሐፋዊ መመሪያ የምታሰቀድመው አንድነትን መሆኑ በማያሻማ ሁኔታ የታየ እና የተገለጠ ነው።

ታሪክ

የመጀመሪያው ሲኖዶስ ወደ አገልግሎት የመጣው በ፶ዓም አካባቢ ቅዱሳን ሐዋርያት በኢየሩሳሌም ሲሰበሰቡ ሲሆን የቤተ ክርስቲያን አንድነት ግን የተመሠረተው ጸጋ መንፈስ ቅዱስ በጽርሐ ጽዮን ለመቶ ሃያው ቤተሰብ በተሰጠ ጊዜ ነው። ሥራ፪፥፩−፣ ፲፭፥፩−፳፱። ታላቁ የቤተ ክርስቲያን ሊቅ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በዓለ ጰራቅሊጦስን የቤተ ክርስቲያን ልደት ብሎ የጠራው ለዚህ አብነት ይሆናል።ይህ አስተሳሰብ ዓለማቀፋዊ ተቀባይነት ያለው እንደመሆኑ መጠን ሌሎች የሚጠቀሱ ዘመናት ቢኖሩም በዚህ ርእሰ ጉዳይ መነሣታቸው ያን ያህል አስፈላጊ አይደለም። በዓለ ጰራቅሊጦስ ወይንም በዓለ ጰንጠቆስጤ የተከበረው ጌታችን ሞትን ድል አድርጎ ከተነሣ በ፶ኛው ቀን ወይንም በክበበ ትስብእት በይባቤ መላእክት ወደ የማነ አብ ዘባነ ኪሩብ ባረገ በ፲ኛው ቀን ነው። ይህም ከጉባኤ ሲኖዶስ ፲፮ ዓመት ቅድሚያ እንዲኖረው ያደርገዋል።

ከዚህ የምንረዳው እግዚአብሔር በመጀመሪያ የቤተ ክርስቲያንን አንድነት መመሥረቱን፤ ቀጥሎም አስተዳደራዊ መዋቅሩን በቅዱስ ሲኖዶስ አማካይነት አዘጋጀ፤ ከቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ በፊት የመቶ ሃያውን ቤተሰብእ አንድነት ማጠናከሩንነው። “በዓለ ኀምሳ የተባለውም ቀን በደረሰ ጊዜ፥ ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው አብረው ሳሉ” የሚለው ቃል መቶሀያው ቤተሰብእ የነበራቸውን ፍጹም አንድነት ወይም አኗኗር ያሳያል። ሥራ ፪፥፩። ምንም እንኳ በዚህ ጉባኤ ፊት ቅዱስ ጴጥሮስ መመሪያ ይሰጥ የነበረ ቢሆንም ጉባኤ ሲኖዶስ ስለተመሠረተ አይደለም። ቅዱስ ሲኖዶስ በተመሠረተ እና ሥራውን በጀመረ ጊዜ የመቶ ሀያው ቤተሰብእ አባላት ወደ ስብሰባው እንዳልገቡ ከመጽሐፉ ቃል መረዳት ይቻላል። “ሐዋርያትና ሽማግሌዎችም ስለዚህ ነገር ለመማከር ተሰበሰቡ።” እንዲል። ሥራ ፲፭፥፮። በመቶ ሀያው ቤተሰብእ ጉባኤ ውስጥ ፴፮ቱ ቅዱሳት አንእስት የሚገኙ ሲሆን በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ላይ ግን የተገኙት ወንድሞች የተባሉ ሐዋርያት እና ሽማግሌዎች ብቻ ናቸው። (ምንም እንኳ ጥንት ከመሠረቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ከሐዋርያት ወይም ከጳጳሳት በተጨማሪ ሽማግሌዎች የተባሉ ከካህናትም ይሁን ከምእመናን የተመረጡ እንደሚገኙበት ቢታወቅም ቅሉ ዛሬ ግን ችላ የተባለ ይመስላል፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሔር ፈቃዱ የሚያስረዳን በመጀመሪያ የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ማጽናት ተቀዳሚ የሌለው ተግባር መሆኑን ነው።

“ያመኑትም ሁሉ አብረው ነበሩ፤ያላቸውንም ሁሉ አንድነት አደረጉ። መሬታቸውንና ጥሪታቸውንም እየሸጡ፥ ማንኛውም እንደሚፈልግ ለሁሉ ያካፍሉት ነበር።በየቀኑም በአንድ ልብ ሆነው በመቅደስ እየተጉ በቤታቸውም እንጀራ እየቈረሱ፥ በደስታና በጥሩ ልብምግባቸውን ይመገቡ ነበር፤እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ በሕዝብ ሁሉ ፊት ሞገስ ነበራቸው። ጌታም የሚድኑትን ዕለት ዕለት በእነርሱ ላይ ይጨምር ነበር።” የሚለው መጽሐፋዊ ቃል የሚያስረግጠው ቀዳሚው ጉዳይ የምእመናን አንድነት መሆኑን ነው። ሥራ ፪፥፵፬−፵፯።እንዲሁም በሌላ ስፍራ ቅዱስ ሉቃስ የነበረውን ሁኔታ ሲገልጥ እንዲህ በማለት ተናግሮ እናገኘዋለን። “ያመኑትም ሕዝብ አንድ ልብ አንዲትም ነፍስ ነበሩአቸው፥ ገንዘባቸውም ሁሉ በአንድነት ነበረ እንጂ ካለው አንድ ነገር ስንኳ የራሱ እንደ ሆነ ማንም አልተናገረም።” ሥራ ፬፥፴፪። ይህ ሁሉ የተገለጠው ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ጉባኤ ሲኖዶስ ሳይመሠረት አንዲት ቤተ ክርስቲያን በምልአት በአንድነት እና በፍጹም ፍቅር ዓላማዋን እያስፈጸመች እንዴት እንደቆየች ለማሳየት ነው።

ቅዱስ ሲኖዶስ እንዲመሠረት ያደረገውም ሌላ ነገር ሳይሆን የቤተ ክርስቲያን አንድነት ተጠብቆ እንዲቀጥል ለማድረግ እንጂ ለሌላ አልነበረም። ምከንያቱም የመጀመሪያው ሲኖዶስ በኢየሩሳሌም እንዲሰበሰብ ያስገደደው ከይሁዲነት ወደ ክርስትና በገቡት እና ከአሕዛብነትወደ ክርስትና በመጡት መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት ሲባል ነው። ከይሁዲነት ወደ ክርስትና የመጡት ከአሕዛብነት የመጡትን ካልተገረዛችሁ አትድኑም የሚል ተቃውሞ ያሰሙባቸው ስለነበር ይህንን ልዩነት ለመፍታት እና የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ለማጽናት ሲባል ቅዱሳን ሐዋርያት ተሰብስበው “መገረዝ ወይም አለመገረዝ አይጠቅምም” በማለት የሚያስታርቅ ውሳኔ ወስነው፣ ማኅበራቸውን የሚያጸና ግሩም መንፈሳዊ ውሳኔ አስተላልፈው ቤተ ክርስቲያንን ከመከፋፈል ታድገዋታል።

የዛሬዋ ቤተ ክርስቲያን አባቶችም ቅድሚያ ሊሰጡ የሚገባቸው የአባቶቻቸውን አሠረ ፍኖት የተከተለ፤ ቤተ ክርስቲያንን ከሚከፍል አጀንዳ ይልቅ አንድ የምትሆንበትን በመምከር ሊሆን እንደሚገባው ከዚህ መረዳት ለማንም አይከብድም፤ የልብ ክፋት እና ጥመት ከሌለ በቀር። ከታሪክ የምንማር ከሆነና በትውፊተ አበው የምንመራ ከሆነ የቅድሚያ ሁሉ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው የቤተ ክርስቲያን አንድ መሆን ብቻ ነው። ይህንን መፈጸም የሚያቅተው ቢኖር እንኳ ወደ አፍራሽ እንቅስቃሴ ከሚገባ ራሱን ማግለል ይጠበቅበታል።

ታሪክ ይህንን ይላል። መጽሓፉም እንዲህ ይነበባል። ሌላ መጽሐፍ አለን ያሉ እስካልመጡ ድረስ በቃለ እግዚአብሔር ተፀንሳ በቃለ እግዚአብሔር የተወለደችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሌላ መመሪያ ታመጣለች ብለን እንዴት ልንጠብቅ እንችላለን? ማምጣቱንስ እርሷ አታመጣም እንደ መዥገር የተጣበቁባትን መለካውያኑን ማለታችን እንጂ። ጥቂት የቆየን ጊዜ ሌላ አዲስ የታሪክ ጠባሳ መድበል “ሸልመውን” ወደ ሥጋ ገበያቸው ሽው ይላሉ።

መጽሐፍ

በመጽሐፍ ቅዱስ አንደበት መነጋገር ስንጀምርም ታላቁ መጽሐፋችን አጉልቶ አና አምልቶ የሚያሳየን አንድነትን ማጽናት የቤ ክርስቲያን ተቀዳሚ ተልእኮ መሆኑን ነው። መሪ የሚሾመው መንጋው ሲኖር ነው። የተበተነን መንጋ ለመሰብሰብ ቅድሚያ ያልሰጠ መሪ በምን ምከንያት የትኛውንስ መንጋ ወክሎ ሊመረጥ ይችላል? የተበተኑት መንጋዎችንስ ድምጽ ማን ሰማቸው? በእነማንስ ተወከሉ ወይም እነማን ይወክሏቸዋል? ለምንስ አይወከሉም? እንዲህ ያለው ሩጫ በመጽሐፍ ይደገፋልን?

ከቅዱሳት መጻሕፍት ምልከታ ምን መረዳት ይቻላል? የሚለው የሁላችንም ጥያቄ ነውና መጽሐፍ ቅዱስ ለየትኛው ቅድሚያ ይሰጥ እንደሆነ መመልከቱ ተገቢውን ምላሽ እንድናገኝ ስለሚያደርገን ከእርሱ ጋር መነጋገሩ እጅግ የተሻለ አና ተወዳዳሪ የሌለው አማራጭ ይሆናል።ወደሌሎች ዝርዝር የመጽሐፍ ሀሳቦች ከመግባታችን በፊት ከፍ ብለን ከታሪክ ምልከታ አንፃር ያነሳነው ሀሳብ ከዚያው ከመጽሐፉ የተገኘ መሆኑን ለማውሳት እንገደዳለን።

ከነዚህም ሌላከብሉያት እስከ ሀዲሳት ሰንመለከት እርቅ፣ ሰላም፣ ፍቅር አና አንድነት የሚሉት የጭብጣቸን አርእስት በየቦታው የተሰጣቸው ልዕልና ከፍ ብሎ ይታያል። ከተጻፈው አትለፉ የሚለውን ቃለ እግዚአብሔር ደጋግመው ሲመለከቱ ለኖሩ አባቶች ይህንን መናገር እጅግ አሳዛኝ እነደሆነ ብንረዳም ሐቅ ያንቃልና ዝምታን እንመርጥ ዘንድ አልተቻለንም። የመጻሕፍቱ ኁባሬ በአንድ ላይ ተጠቅልሎ ሲታይ መልእክቱ አንድ እና አንድ መሆኑን እንደሚከተለው በመዳሰስ እናሳያለን፡፡

አንባቢው እስኪ በጥሞና የሚከተሉትን መጽሐፋዊ ኃይለ ቃላት ይመልከታቸው።

“በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሽዋሽዋ ጸናጽል ሆኜአለሁ። ትንቢትም ቢኖረኝ ምሥጢርንም ሁሉና እውቀትን ሁሉ ባውቅ፥ ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ።ድሆችንም ልመግብ ያለኝን ሁሉ ባካፍል፥ ሥጋዬንም ለእሳት መቃጠል አሳልፌ ብሰጥ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም።” ፩ቆሮ ፲፫፥፩−፫።

ከቅዱስ ጳውሎስ አባባል የምንረዳው ከየትኛውም ዓይነት መንፈሳዊ ብቃት አና አገልግሎት ይልቅ ፍቅር ከፍተኛውን ደረጃ መያዙን ነው። ታዲያ እንዴት ፍቅር ይገፋል? ፍቅር እኮ ራሱ እግዚአብሔር ነው። አባቶች ስለቤተ ክርስቲያን የትኛውንም መከራ ተቀብለው ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ከሰማዕትነቱም ፍቅር ይበልጣል። ፍቅርን መመሥረት ሃይማኖትን ለዘላለሙ መመሥረት ነው። ሰለዚህም ደግሞ “ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም፤ ትንቢት ቢሆን ግን ይሻራል፤ ልሳኖች ቢሆኑ ይቀራሉ፤ እውቀትም ቢሆን ይሻራል።”ይለናል። ፩ቆሮ ፲፫፥፰።ለማያልፈው መንግሥት ብለው አስኬማ የጫኑ አባቶች እንዴት ፍቅርን ሲሸሹ ልናይ እንችላለን? የምናየውን ማመን የምንሰማውንም መቀበል እየከበደን መጥቷል። ከዚህ የሐዋርያው አባባል አስከትለን ሥልጣንም ቢሆን አለቅነትም ቢሆን ወድሶ ሰብእም ቢሆን ይቀራል የሚልም እንዳለበት መካድ አይቻልም።ፍቅር ከእምነትም ከተስፋም ብልጫ ያለው የክርስትና ማዕከላዊ መዘውር ነው። ታዲያ እንዴት ከአስተዳደር፣ ከሥልጣን፣ ከሲመተ ፓትርያርክና ከግትርነት ሊበልጥ አይችልም ብሎ ማሰብ ይቻላል? በውኑ ፓትርያርክ መሾም እና ወደ መንበር መመለስ ከፍቅር ሊበልጡ ይችላሉን? ፍቅር እምነትንም ተስፋንም ያስከነዳ ኃያል ወልድን ከመንበሩ ስቦ ያመጣ ልዩ መግነጢሳዊ ኃይል ነውና ቅድሚያ ለፍቅር መስጠት ይገባል። መጻሕፍቱ የትብብር ድምጻቸውን ለፍቅር ቅድሚያ በመስጠት እያሰሙ ነው። “እምነት ተስፋ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ፤ ከእነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው።” ፩ቆሮ ፲፫፥፲፫።የምናደርገው ነገር ሁሉ ፍቅር የገባበት ፍቅር የተሞላበት እንዲሆንም ታዝዘናል። “በእናንተ ዘንድ ሁሉ በፍቅር ይሁን።” ፩ቆሮ ፲፮፥፲፬። በአባቶች መካከል ያለው ልዩነት ፍቅር መጉደሉን እያሳየን እንዴት ወደሌላ እርምጃ ልቡናችን ይሳባል። መምህራችን ቅዱስ ጳውሎስ ለፍቅር የሰጠነው ቦታ የተዛባ እንዳይሆን በተደጋጋሚ አሳስቦናል። ለኤፌሶን ሰዎች በላከው ክታብም “በመንፈሱ በውስጥ ሰውነታችሁ በኃይል እንድትጠነክሩ ክርስቶስም በልባችሁ በእምነት እንዲኖር እንደ ክብሩ ባለ ጠግነት መጠን ይስጣችሁ፤ የእናንተ ሥርና መሠረት በፍቅር ይጸና ዘንድ።”በማለት ፍቅር ማለት ምን ያኽል አስፈላጊ እንደሆነ አስረድቷል። ኤፌ ፫፥፲፮። ሥርና መሠረታችሁ በፍቅር ይጽና ማለቱ የየትኛውም መንፈሳዊነት መነሻው ፍቅር መሆኑን ሲያጠይቅ ነው። ፍቅር ሥር ከሆነ ሌላ ሥር የለምና ፍቅር መሠረት ከሆነ ሌላ መሠረት አይኖርምና።

ሌላው ሁሉ እንደ ግንድ እና እንደ ቅርንጫፍ ፍቅርን ተከትሎ የሚመጣ መሆኑን እያመለከተን በመሆኑ ከቃሉ ፈቀቅ እንዳንል ሰውነታችንን እንገስጸው። ክርስቶስ በልባችን የሚኖረው ሥርና መሠረታችን በፍቅር የታነጸ ጊዜ መሆኑን ሐዋርያው አስረድቶናል። ታዲያ ለዚህ የምጽሐፍ ቃል ተገዢዎች ከሆንዘንድ እንደምን ከእርቀ ሰላም በፊት ሌላ ርምጃ በምን ምክንያት ሊመጣ ይችላል? እርቀ ሰላሙ አልተሳካም ተብሎ ሳይደመደም እንዳያማህ ጥራው እንዳይበላ ግፋው ዓይነት አካሄድ ለምን ይታሰባል? እርቀ ሰላሙ አልተሳካም ለማለትም በቂ የሆነ እርምጃ አሳማኝ የሆነ ድካም ከተደከመ ወዲያ እንጂ ገንዘብ ባከነ፣ ለምን የድርድር ቦታው ከአሜሪካ ውጭ አይሆንም በሚል ከፍቅር ያልመነጨ አሉቧልታ በማስወራት አይደለም።

ለፍቅር ሲባል አይደለም ገንዘብ እና ጉልበት ቤተ ክርስቲያን የከፈለችው የክርስቶስን ደም መሆኑን መዘንጋት አይገባም። አይደለም አንድ መንፈሳዊ ክርስቲያን ሊሸፍነው የሚችለውን ወጪ ቀርቶ ሌላም ቢያስወጣ ለፍቅር እንዴት በዛ ይባላል? አንዳንዶች በጠበበ መከራከሪያ ዋናውን ቁም ነገር ለማስረሳት ሲሞክሩ ዐይተናል። አይደለም ከአዲስ አበባ አሜሪካ ፍቅር ከመንበረ ጸባኦት ወደ ምድር ጌታችንን ስባለች። የመንበረ ጸባኦትን ርቀት ለኩልን እንዳይሉን እንጂ ከሚታየውም ከማይታየውም በላይ ያለ እግዚአብሔር የከፈለውን መሥዋዕትነት የሚያውቅ ሰው ይህንን መከራከሪያ ብሎ ያውም እርቁን ለማስታጎል ማቅረብ የጨነገፈ ምልከታ ነው። ወንድምህ አንድ ምእራፍ እንድትሄድለት ቢፈልግ ሁለተኛ ደግሞ ጨምርለት የሚለውን የፍቅር ሕግ ማን ሰወረባቸው?

ፍቅራችን አረአያ ክርስቶስን ያነሳ እንዲሆን ተነግሮናልና የመንገድ ርቀት የሚፈታው ልብ ይዘን እንታረቅ የምንልም ከሆነ ስህተቱ ከእኛ ነው። “ክርስቶስም ደግሞ እንደ ወደዳችሁ ለእግዚአብሔርም የመዓዛ ሽታ የሚሆንን መባንና መሥዋዕትን አድርጎ ስለ እናንተ ራሱን አሳልፎ እንደ ሰጠ በፍቅር ተመላለሱ።” በማለት መጽሐፍ እንደተናገረ ፍኖቱን ተከትለን የሰነፈ ምክንያትን ትተን ለእርቀ ሰላም ልንጋደል ይገባል። ኤፌ ፭፥፪።

የቤተ ክርስቲያን የሆነ ሁሉ ሊያስበው የሚገባው ፍቅር ያለበትን ነገር ነው። መጽሐፍ “በቀረውስ፥ ወንድሞች ሆይ፥ እውነተኛ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ጭምትነት ያለበትን ነገር ሁሉ፥ ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ፥ መልካም ወሬ ያለበትን ነገር ሁሉ፥ በጎነት ቢሆን ምስጋናም ቢሆን፥ እነዚህን አስቡ።” እንዲል። ፊል ፬፥፰።

ፍቅር እግዚአብሔርን የማወቅ መስፈርት መሆኑን ከመጽሐፍ እንማራለን። ቅዱስ ዮሐንስ “ፍቅር የሌለው እግዚአብሔርን አያውቅም፥ እግዚአብሔር ፍቅር ነውና።”ሲል እንደጻፈ። ፩ዮሐ ፬፥፰። ሰዎች አኛ እየወደድናቸው ቢጠሉን እንኳ የአኛ ፍቅር የሚቆም ሊሆን አይገባውም። የጠፋውን ልጅ ለመቀበል የአባቱ ቤት ሁል ጊዜ ለምሕረት እና ልጄ ብሎ በቀደመ ክብሩ ለማስገባት የተከፈተ ሊሆን ይገባዋል። ፍቅር እንዲህ ነውና። ምናልባትም በእርቀ ሰላሙ ሂደት ከምንሰማቸው ማስተባበያዎች አንዱ “እነርሱ እኮ አይፈልጉም” የሚል ነው። ነገሩ አይደለም እንጂ ቢሆን እንኳ የእኛ እነርሱን ለመቀበል ያለን ፍላጎት በእነርሱ አለመፈለግ የሚዘጋ እና የሚከፈት ሳይሆን ምን ጊዜም ለፍቅር ያደላ ሊሆን ይገባል።

ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ስለመጨረሻው ዘመን ልጁን ቅዱስ ጢሞቴዎስን ሲያስገነዝበው “ነገር ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ።ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፥ ገንዘብን የሚወዱ፥ ትምክህተኞች፥ ትዕቢተኞች፥ ተሳዳቢዎች፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ የማያመሰግኑ፥ቅድስና የሌላቸው፥ ፍቅር የሌላቸው፥ ዕርቅን የማይሰሙ፥ ሐሜተኞች፥ ራሳቸውን የማይገዙ፥ ጨካኞች፥ መልካም የሆነውን የማይወዱ፥ከዳተኞች፥ ችኩሎች፥ በትዕቢት የተነፉ፥ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ።” ብሎት ነበር ። ፪ ጢሞ ፫፥፩−፬።ምናልባትም የዚህ ትንቢት መፈጸሚያ እንዳንሆን በሃይማኖት ልንቀሳቀስ ያስፈልገናል።

አባቶቻችን እርቅን የማይሰሙ ከሆነ እንግዲህ ምን እንበላቸው? እጅግ ግራ አጋብተውናል። በውጭም ይሁን በውስጥ ካሉት አንዳንዶች ከሌላ ጋር የቆረቡ ይመስላሉ። አንጥረን አንጠርጥረን እንወቃቸው እና በእነርሱ ላይ እርምጃ እንውሰድ ማለት ጠፍቶን አይደለም። ጥፋት በሌላ ጥፋት አይታረምምና በትዕግስት ቁመናቸውን እስኪያስተካክሉ እንጠብቃቸዋለን። ያቺ የትዕግስት ጊዜ ያለቀች (ንግራ ለቤተ ክርስቲያንን ያልሰሙ) እንደሆነ ግን ቀጣዩ እርምጃ ምን እንደሚሆን እነርሱም አይጠፋቸውም። በአንድ ራስ ሁለት ምላስ የሆኑት እርቅን የማይወዱት እነርሱ ናቸው። በቆብ እና በካድሬነት ቤተ ክርስቲያንን ማመስ ሊቆም ይገባዋል። አባቶችማ ቢሆኑ እርቅን ይሰሙ ነበራ።

ከምንም በላይ የአባቶች የዘወትር ጸሎት የክህነት አገልግሎት በሚሰጡበት ስፍራ ሁሉ ሳይሉት ሳይጸልዩት የማይውሉት ደግሞም የልመናቸው ሁሉ ማሳረጊያ የሆነው ጸሎት አቡነዘበሰማያት “እኛም ደግሞ የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን ይቅር በለን።” የሚል ከፍተኛ የይቅርታ ቃለ አሚን ወይም ቃለ መሓላ ያለው መሆኑን እንዴት አድርገን እንናገር? ማቴ ፮፥፲፪። አቤቱ ጌታ ሆይ አውቃለሁ ለሚል ሰው የሚያውቀውን መልሶ መንገር እንዴት ከባድ ነው?

ቅዳሴ ቢቀደስ፤ ምሕላ ቢደርስ፤ ሱባኤ ቢገባ፤ ጾም ሰጊድ ቢበዛ ይቅር ለመባል አይደለምን? አቡነ ዘበሰማያት የምንለው ይቅርታ ለማግኘት አይደለምን? ይቅር ለመባል ቀዳሚው እኮ ይቅርታ ያውም ለበደልናቸው ሳይሆን ለበደሉን መሆኑን እየጸለይን ከቶ ማንን ልናታልል እንችላለን? ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ጸልዩ ብሎ በማሰሪያ አንቀጽ የሰጠንን ጸሎት የት ልንደብቀው እንችላላን?

በዚህም ሆነ በዚያ ያሉት ሁሉ ይመለከታቸዋል። ሁሉም የተበደሉት ነገር ቢኖር እንኳ ይቅር የማለት ግዴታ መግባታቸውን ማሳየት ይጠበቅባቸዋል። ለስንቱ ነፍስ ተጠያቂዎች እንደሆናችሁ አስቡ። ይቅር ሳትሉ የምታጸኑት ሥልጣንም መንበርም አይኖርም እኮ። እስኪ መሳሳቡን እና መጓተቱን ተውት እና በፍቅር እንባ እንራጭ። በቁማችን ሥጋችንን እንቅበረው እና በነፍሳችን እልል እንበል። እባካችሁ ተለመኑን። ስለ አዛኝቱ ማርያም ስለ ወላላይቱ ብላችሁ በፍቅር ስትዋደቁ እንያችሁ።

መጻሕፍትም ታሪክም እንዲህ ተባብረውባችኋል። ማምለጫ ለሌለው የክርስቶስ ፍቅር መገዛት ቅድመ ሁኔታ አይቀመጥለትም። አባቶቻቸን ይህን ሁሉ የምንላችሁ ለቅድስት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እንድታደሉ መንጋውን ከመበተን እንድትታደጉ እንጂ አንዳች የጎደለብን የሥጋ ጥቅም ኖሮ አይደለም። ማኅቶተ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ጳውሎስ “አገልግሎታችንም እንዳይነቀፍ በአንዳች ነገር ማሰናከያ ከቶ አንሰጥም።” ሲል እንደተናገረው ያንን የእርሱን ጥንቃቄ ዛሬም ስትደግሙት ለማየት ከፍተኛ ጉጉት አለን። ፪ ቆሮ ፮፥፫። በሁለቱም ወገን ያለው የሚያሰነቅፍ አካሄድ ሌላ ሦስተኛ እና አራተኛ አካል ይዞብን እንዳይመጣ ተጨንቀናልና በዚሁ ቅጩት።

እናንተ የቀራችሁ ዘመን ጥቂት ሊሆን ይችላል። እኛም እንደዚያው። ቀጣዩ ትውልድ በማን ዕዳ ይግባበት? እርግጥ መንፈሳዊነት ከማንኛውም ምድራዊ ተጽዕኖ ነፃ መውጣት ነው። ነገር ግን ነፃነቱም በገደብ ነው። “ወንድሞች ሆይ፥ እናንተ ለአርነት ተጠርታችኋልና፤ ብቻ አርነታችሁ ለሥጋ ምክንያትን አይስጥ፥ ነገር ግን በፍቅር እርስ በርሳችሁ እንደ ባሪያዎች ሁኑ።” ገላ ፭፥፲፫። አርነቱ ፍቅር ከሌለበት ወደ አጥፊነት ይሻገራል። ለአርነቱ አጥር እና ቅጥሩ ፍቅር ነው። ፍቅር የሌለበት አርነት ትርጉም የለውም። ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ የዚህ አርነት ባለቤት በመሆኑ ገራፊውን ከደረሰበት መቅሰፍት ፈውሶታል። የታባቱ ብሎ አልተወውም። ቅዱስ እስጢፋኖስም ይቅርታ ለምኖላቸዋል። አርነት መውጣት እንዲህ እንጂ የፈለጉትን ለማድረግ አይደለም።

በፍቅር የወዛ እና የወረዛ አርነት ስትሰብኩ ለመደመጥ ይህ ጊዜ ቀርቦላችኋል። ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው ሰላም የአንድነት ማሰሪያ ልጥ ነውና ለእርሱ እንትጋ። “በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ።” ኤፌ ፬፥፫። ትጋታችን በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ማጽናት መሆኑ ቀርቶ እንዴት ለመበታተን ይሆናል? ከቶ እነዚህ የማን ልጆች ናቸው? የመንፈስ አንድነት የሚጸናው በሰላም መሆኑን በማያሻማ ቃል የዘመኑ ሰው ሳይሆን ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ከተናገረ ቆየ። ቅድሚያ የሚሰጠው ሰላም መሆኑን መሰከረ። አንድነትን የሚያጸናው ሰላም መሆኑ ተሰበከ። እንበለ ሰላም አንድነት ማምጣት አይቻልም።
መጽሐፋችን በተደጋጋሚ የሚያስተላልፈው መልእክት የአበውን፣ የምእመናንን ተፋቅሮ፤ በአንድነት አና በስምምነት በሰላም መኖርን ነው። ከዚህ በተቃራኒው ለመቆም አይደለም ለመሰነባበት ወይም ለመከራረም ወይም ውሎ ማደር ወይም ለሰከንድ ቀርቶ ለሳልሲት እንኳ አይፈቅድም። የማይፈቀድ ከሆነ ደግሞ ባልተፈቀደው ባልተወደደው ጎዳና ለመንጎድ ምን ያነቃናል?

ብኂለ አበውም ቅድሚያ ለእርቅ ይላል

የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ወደ ማኅበረሰቡ ዘልቆ ከመግባቱ የተነሣ የአበው ብኂል ሳይቀር በመጽሐፋዊው አባባል የተቃኘ ሆኖ እናገኘዋለን። በተለይም “ሳል ይዞ ስርቆት ቂም ይዞ ጸሎት የለም” የሚለው አባባል ሊደረግ ከታሰበው ጉዳይ በፊት ሊሟላ የሚገባውን ቅድመ ሁኔታ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፤ እናም ከታሪክ እና ከመጻሕፍት በተጨማሪ ብኂለ አበውም ሌላ ማስረጃ ሆኖ ቀርቧል።

የሌባውን ቅድመ ሁናቴ እንተወውና ወደ ጸሎቱ ስንገባ ሰው መቼም የሚጸልየው ፈጣሪው እንዲማለደው ነው። ይሁን እንጂ ጸሎቱ ውስተነዋ ሰማይ አንዲያርግ፣ ከደመና በታች እንዳይቀር፣ እግዚአብሔር እንዲለመነው ከፈለገ አስቀድሞ ቂም በቀል በልቡናው አለመኖሩን ካረጋገጠ ወዲያ እንዲሆን ያስፈልጋል ማለት ነው። ቂም መኖሩን ካወቀ ደግሞ አስቀድሞ ከተጣላው ጋር እርቅ መፈጸም ይኖርበታል። ከታረቀ በኋላ ቅድመ እግዚአብሔር ለመድረስ የማይከለከል ጸሎት እና ልመና ሊያቀርብ እንደሚችል ከአበው ምሳሌያዊ አነጋገር እንረዳለን። ማኅበረሰቡ እንደነዚህ በመሳሰሉ ወርቃማ ብኂሎች ሃይማኖቱን እንዲያስረዳ እስከማስቻል ድረስ ትምህርቷ ዘልቆ እንዲታወቅ በኑሮም እንዲገለጥ ያበቃች ቤተ ክርስቲያን ዛሬ ልጆቿ ማንንም በማያሳምኑ ጠባብ ምክንያቶች መለየትን ሲሰብኩ መስማት እንዴት ያሳምማት ይሆን?

ካነሣነው አባባል በቀላሉ የምንረዳው ቂም ካለ ምንም ቢጸልዩ፣ ምንም ቢጾሙ፣ ምንም ቢሰግዱ፣ ምንም ቢመጸውቱ፣ የቱንም ያኽል ቢደክሙ፣የወደዱትን ያክል ምህላ ቢያውጁ ግዳጁ የማይፈጽም ከደመና በታች የሚቀር መሆኑን እንማራለን። ታዲያ አባቶቻችን ከወዴት አመጡት አና እምቢኝ አንታረቅም ይላሉሳ? በየትኛው መንገድ ሄደን ሀሳባቸውን ልናደምጥ እንደምንችል ቢነግሩን ምንኛ ባመሰገናቸው። የቀደሙት አበው ያስተማሩት ማኅበረሰብ ትምህርቱ እንዳይረሳ በአባባል ደረጃ ፈርጅ አስይዞ ለእኛም ገላጭ ንግግር ሆኖ እንጠቀምበታለን። እነዚያ እውነተኛውን ትምህርት አስተምረው ሲያልፉ የአሁኖቹ ደግሞ መጠቋቆሚያ የሚያደርግ ትተው እንዳያልፉ ያሰጋል።

ምንም ይሁን ምን ጋሪ ከፈረሱ አይቀድምም። ከቀደመ ደግሞ ውጤቱ ለማንም ግልጥ ነው። ፈረሱ ቂምን ማስወገድ ጥላቻን ማጥፋት እርቅን መመሥረት ሰላምን ማጽናት ፍቅርን እንደሸማ መልበስ ሲሆን ጋሪው ከእርቅ በኋላ እግዚአብሔር ባለበት አበው በአንድ መንፈስ ለአንድ ዓላማ ተሰብስበው እግዚአብሔርን በመካከላቸው አድርገው የሚወስኑት ወሣኔ ነው። ቅዱስ ዳዊት “ናሁ ሰናይ ወናሁ አዳም ሶበ ይኄሉ አኃው ኅቡረ – ወንድሞች በኅብረት ቢቀመጡ መልካም ነው እነሆም ያማረ ነው” ሲል እንደተናገረው አባቶች ተስማምተው አንድነት ሆነው ለመቀመጥ ያብቃቸው እንጂ ያን ጊዜ ምንም ወሠኑ ምን የማይስማማ ይኖራል ብለን አንገምትም። መዝ ፻፴፫፥፩። እነርሱ ከተስማሙ መንፈስ ቅዱስ በመካከላቸው በስፍራው ይቀመጣል። እርሱ ከተቀመጠ ደግሞ ውሣኔው ሁሉ በእርሱ የተቃኘ ይሆናል። ያም ውሣኔ ሁሉንም ያስማማል። እነርሱም እንደ አባቶቻቸው እንደ ሐዋርያት እኛ እና መንፈስ ቅዱስ ይህንን አዝዘናል የማለት ሥልጣን ይኖራቸዋል። ከመንፈስቅዱስ ይልቅ ሌላ አማካሪ እየያዙ የሚወሥኑት ውሣኔ ግን ለማንም የማይዋጥ አሳፋሪ የክስረት ታሪክ ይሆናል።

ስለዚህም ጋሪው እንዳይቀድም አስፈላጊው ጥንቃቄ ከአሁኑ ሊደረግ ይገባል። አሁንም አንረፍቅም አሁንም አልመሸም። ጋሪው ከፈረሱ ቀድሞ በሚመጣው አደጋ ተጠያቂ ከመሆን ለመዳን አሁንም ጊዜ አለ። “ብርሃን ሳለላችሁ በብርሃን ተመላለሱ” መባላችንን እያሰብን እንመለስ። ታሪካዊ ስህተት በመሥራት ቤተ ክርስቲያንን እና ልጆቿን ከመበተን እንታደግ። ያለበለዚያ በትሩ የሚቻል አይሆንም።

አበው እርስ በእርስ ቢፋቀሩ፦

፩̣ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት መሆናቸው ይታወቃል

መጽሐፍ ስለዚህ ምስክርነቱን ሲሰጥ እንዲህ ይላል። “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፥ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ።” ዮሐ ፲፫፥፴፭።እውነተኛ የክርስቶስ አገልጋዮች የሚሆኑትም የሚባሉትም ከምንም በላይ በፍቅር ለመኖር የሚችሉ ከሆነ ብቻ ነው። ፍቅር በምንም ምክንያት የማይገፋ ታላቅ በረከት ነውና። በተቃራኒው የሚቆሙ ከሆነ ደግሞ የክርስቶስ ነን ለማለት ምንም ዓይነት ሥልጣንም የሞራል ብቃትም አይኖራቸውም። ታዲያ አንታረቅም ወይም ለመታረቅ እንቅፋት የሚሆነውን ማሰናከያ የሚያስቀምጡትን በየትኛውም ወገን የሚገኙትን አባቶች ምን እንበላቸው? ብዙ ታግሰናቸዋል እና ከእንግዲህ ጥቂት ታግሰን ወደ ሰላሙ እና ወደፍቅሩ የማያዘነብሉ እንደሆነ “እናንተ የክርስቶስ አይደላችሁም” ማለታችን አይቀርም። የማን እንደሆኑ በተለያየ መንገድ እየነገሩን ሰነባብተዋልና።

ደቀመዛሙርት ከሆኑ የሚወድዱት እውነትን እና ሰላምን በሆነ ። በነቢዩ “እውነትንና ሰላምን ውደዱ።” ተብሎ እንደተነገረ። ዘካ ፰፥፲፱። እንዲሁም አይደለም በዐይን ጥቀሻ በከንፈር ንክሻ ሊግባቡ ከሚችሉት ከመሰል ወንድሞቻቸው ጋር ቀርቶ ከሌሎችም ጋር ቢሆን በሰላም እንዲኖሩ ታዝዘዋል። “ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ።”ሲል ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረው። ሮሜ ፲፪፥፲፰።

የክርስቶስ ደቀመዛሙርት ሥራቸው ሰላም ለሚቆምበት ወይም ለሚጸናበት መታገል እንጂ ለምድራዊ ድሎት እና ምቾት መትጋት ባለመሆኑ በየትኛውም መስፈርት ሰላምን ይገፋሉ ተብሎ አይጠበቅም። ሐዋርያው “የእግዚአብሔር መንግሥት ጽድቅና ሰላም በመንፈስ ቅዱስም የሆነ ደስታ ናት እንጂ መብልና መጠጥ አይደለችምና። ∙∙∙ እንግዲያስ ሰላም የሚቆምበትን እርስ በርሳችንም የምንታነጽበትን እንከተል።” ሲል የተናገረው ይህንን ያመለክታል። ሮሜ ፲፬፥፲፯−፲፱። ደግሞም “እግዚአብሔርስ የሰላም አምላክ ነው እንጂ የሁከት አምላክ አይደለምና፤ በቅዱሳንም አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እንዲህ ነው።” የሚለው የመጽሐፍ ቃል ያንኑ የሚያጠናክር ነው። ፩ቆሮ፲፬፥፴፫።

ሕዝባችን የሰለቸው ጉዳይ ቢኖር ሁከት መስማት ሁከት ማየት እና ስለሁከት ማሰብ ነው። የሰላሙን አምላክ መከተል ትተን ወደ ሁከት የምናመራ ከሆነ አሰላለፋችን በተሳሳተ ጎራ ነውና በፍጥነት ለመስተካከል እንዘጋጅ። በሰላም ወንጌል እንዲቆሙ የተጠሩት የክርስቶስ ተከታዮች ናቸው። ለሰላም ቁሙ ሲባሉ ለጠብ የሚከራከሩ ከሆነ ጎራቸውን ለይተዋል እና በምንም መስፈርት የክርስቶስ ነን ቢሉም ልንቀበላቸው አንችልም። ቅዱስ ጳውሎስ ለሰላም በጽናት መቆም እንዳለብን ሲያጠይቅ “እንግዲህ ወገባችሁን በእውነት ታጥቃችሁ፥ የጽድቅንም ጥሩር ለብሳችሁ፥ በሰላም ወንጌልም በመዘጋጀት እግሮቻችሁ ተጫምተው ቁሙ።”በማለት ነግሮናል። ኤፌ ፮፥፲፬−፲፭። እንግዲህ አባቶቻችን የምንላቸው በመጽሐፉ ቃል የሚመሩትን ብቻ ነው።

፪̣ ውሉደ ብርሃን (የብርሃን ልጆች) ይባላሉ

ጌታቸን በወንጌል “የብርሃን ልጆች እንድትሆኑ ብርሃን ሳለላችሁ በብርሃኑ እመኑ አላቸው።” ሲል መናገሩ ተጽፏል። ዮሐ፲፪፥፴፮። በብርሃን የሚያምኑ በብርሃን የሚኖሩ ደግሞ ወንድሞቻቸውን ይወድዳሉ እንጂ አይጠሉም። ወንድሞችን የሚጠሉ ከሆኑ ደግሞ ውሉደ ብርሃን መባላቸው ቀርቶ ውሉደ ጽልመት ይሆናሉ። “በብርሃን አለሁ የሚል ወንድሙንም የሚጠላ እስከ አሁን በጨለማ አለ።” እንዲል መጽሐፍ። ፩ዮሐ ፪፥፱።

በተለያየ መንገድ እንደምንሰማው በውጭ ሀገር ካሉትም በሀገር ቤት ካሉትም ለቃላቸው ብቻ እርቀ ሰላሙን እንፈልገዋለን ይላሉ። ቃል ሌላ ሥራ ሌላ ሲሆን እያየን እንደ ቂል አየተሞኘን እሰከማዕዜኑ እንሰማቸዋለን። ድርጊታቸው ፓትርያርክ ለመምረጥ ከሸማኔ መወርወሪያ ይልቅ አየፈጠነ እያየነው ዕርቀ ሰላሙን እንፈልጋለን እያሉ ዶሮን ሲያታልሏት በመጫኛ ጣሏት ዓይነት ሥራ ይሠራሉ። የፓትርያርክ ምርጫ ሂደቱ ከፍተኛው የእርቀ ሰላም ማደናቀፊያ እንደሆነ ስላወቁ በሚያቆላምጥ አፋቸው እኛ መቼ እርቁን ገፋን እያሉ በግብራቸው ግን የጨለማውን ሥራ ይሠራሉ። በብርሃን ይዘምራሉ በጨለማ ይዘፍናሉ። ክርስትና ግን በብርሃንም በጨለማም መዘመር ነው። በሚያፍሩአቸው ወይም በአፍም በመጣፍም በሚሞግቷቸው ፊት ክርስቲያን፤ ዘወር ብለው ደግሞ የሚያሳፍር ሥራ ውስጥ ለሚዘፈቁት እናዝናለን። ሃይማኖት በሰው ፊትም፣ ሰው በሌለበትም፣ በብርሃንም፣ በጨለማም የምትሠራ የምትፈጸም እንጂ እንደ ጊዜ ግብሩ የሚገለባበጡባት የጅምናስቲክ መድረክ አይደለችም።

ሌሎቹ ደግሞ የመከራከሪያ ነጥባቸው ላይ ሙዝዝ ብለው በመቆም የሚያሰላች እና ተስፋ የሚያስቆርጥ አካሄድ መከተላቸውን እስካልተው ድረስ ለብርሃን ልጅነት የሚያበቃ ሥራ እየሠሩ ነው ለማለት አይቻልም። መደራደሪያው ሁሉ ለቤተ ክርስቲያን ጥቅም ሲባል የሚቀርብ እንጂ ለግል ዝናና ክብር የሚጨነቅ መሆን የለበትም። በጋራ ያጠፋናትን ቤተ ክርስቲያን በጋራ እናልማ የሚል መሆን ሲኖርበት ድሮ በቆሙበት መቅረት ጨርሶ ወደ መረሳት እንደሚያደርስ ሊታወቅ ይገባል። ለመታረቅ ቅድመ ሁኔታ በጭራሽ ሊኖር አይገባውም። እንዲህማ ቢሆን ጌታችን እኛን ላለመታረቅ ሺህ ጊዜ አእላፍ ወትእልፊት ምክንያቶች ነበሩት።

በውስጣቸው ሌላ ይዘው መድረክ ለማሳመር ብቻ ከልባቸው የማይገኘውን እየነገሩን እንዲቀጥሉ አንሻም። ቅዱስ ዳዊት ከእነዚህ ጋር እንዳይቀላቅለው ሲናገር “ክፋትም በልባቸው እያለ ከባልንጀራቸው ጋር ሰላም ከሚናገሩት ጋር አትጣለኝ።” ይላል። መዝ ፳፰፥፫። እንዲሁም ጠቢቡ ሰሎሞን በተመሳሳይ “ክፋት በልቡ ሳለ ፍቅርን የሚናገር ከንፈር በብር ዝገት እንደ ተለበጠ የሸክላ ዕቅ ነው።” በማለት ይህንን የተጠላ ተንኮለኛነት ያወግዛል። ምሳ ፳፮፥፳፫።ጉዳዩ የፕሮቶኮል አይደለም። የልብን ቅንነት የልብን ንጽሕና የሚጠይቅ በመሆኑ በሁሉም ወገን ያሉት እየተመዘኑበት መሆኑን አይዘንጉ። መጻሕፍቱ ተባብረው ሊሆን የሚገባውን ነግረውናልና ሰላምን አስቀድመን ሃይማኖታችንን እናጸና ዘንድ ይጠበቅብናል። “ከክፉ ሽሽ መልካምንም አድርግ ሰላምን እሻ ተከተላትም። መዝ ፴፬፥፲፬።ከክፉ ፈቀቅ ይበል፥ መልካምንም ያድርግ፥ ሰላምን ይሻ ይከተለውም።” ፩ጴጥ፫፥፲፩።

፫̣ የሰላም ተከታዮች ይባላሉ

ቅዱሳት መጻሕፈት ከሚያስተላልፏቸው ዐበይት መንፈሳዊ ቁም ነገሮች መካከል አንዱ አማንያን ሁሉ የሰላም ተከታዮች እንዲሆኑ ነው። ለአብነትም ያህል የሚከተሉትን ኃይለ ቃላት እንመልከት። “ከክፉ የጎልማሳነት ምኞት ግን ሽሽ፥ በንጹሕም ልብ ጌታን ከሚጠሩ ጋር ጽድቅን እምነትን ፍቅርን ሰላምን አጥብቀህ ተከተል።” ፪ጢሞ ፪፥፳፪። ሰላምን ለመከተል የጎልማሳነት ምኞትን መተው ይፈልጋል። ሁሉን በእጄ ሁሉን በደጄ ላድርግ ይሄንንም ያንንም ለእኔ ላድርግ እያሉ ከሚቋምጡበት የጎልማሳነት ስሜት ያልወጡ ሰዎች ለራሳቸው የፍላጎት ስካር (ego) ብቻ እንጂ ለቤተ ክርስቲያን ጥቅም ከቶውኑ ሲያስቡ አይገኙም።

አባቶቻችን ከዚህ የጎልማሳነት ስሜት ነፃ መሆናቸውን ሊያሳዩን የሚችሉት ሰላምን ሲከቱ ካየናቸው ብቻ ነው። የጎልማሳነት ምኞት ለሥልጣንና ለፍቅረ ሲመት መትከንከን ነው። የጎልማሳነት ምኞት ሌላውን መናቅ እና ማንጓጠጥ እንዲሁም ምን ያመጣል? እያሉ መዛት ነው። የጎልማሳነት ምኞት በእጅ ጭብጥ በእግር እርግጥ አድርጎ ስለመግዛት ማለም ነው። ለጠብ እና ለክርክር እንጂ ለሰከነ ሃይማኖታዊ ኑሮ ግድየለሽ መሆን ጎልማሳነት ነው። የጎልማሳነት ስሜት እኔ ብቻ ልደመጥ፤ እኔ ያላቦካሁት አይጋገርም ማለት ነው። አባቶቻቸን ከዚህ መሰል ድርጊት እስካልታቀቡ ድረስ እንዴት የሰላም ተከታዮች ይባላሉ? ሠራንላቸው እያሉ ለሰላሙ የታገሉ አባቶች ላይ ማፌዝ የጎልማሳነት ስሜት ነውና ፈጥነው ከዚህ ውዱቅ አሠራር ቢወጡ ምንኛ ያማረ በሆነ?

የተቀበሉት ሥልጣን፣ የጫኑት አስኬማ የሰላም ማጽኛ፣የሰላም መስበኪያ በመሆኑ ሐዋርያው “ከሰው ሁሉ ጋር ሰላምን ተከታተሉ ትቀደሱም ዘንድ ፈልጉ፥ ያለ እርሱ ጌታን ሊያይ የሚችል የለምና።” እያለ መክሮአቸዋል። ዕብ ፲፪፥፲፬። ከቅዱስ ጳውሎስ አባባል የምንረዳው ጌታችንን ማየት የሚቻለው እንደ እርሱ ሰላምን የምንከታተል ከሆነ ብቻ ነው። በዚህ ረገድ መጻሕፍቱ ሁሉ ድምጻቸው ተመሳሳይ ነው። መቼም ሌላ መጽሓፍ ካላመጡ በቀር እርቀ ሰላምን ከማስቀደም ሌላ አማራጭ በመጽሐፍ ቅዱስ በኩል አያገኙም።

፬̣ መሥዋዕታቸው ቅድመ እግዚአብሔር ይደርሳል

የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን አባቶች አንዱ መለያ ጸሎታቸው፣ አምሀ ሰግደታቸው ቅድመ እግዚአብሔር ደርሳ ግዳጅ የምትፈጽም በመሆኗ ነው። መሥዋዕታቸው ቅድመ እግዚአብሔር የምትደርሰው አስቀድመው መደረግ የሚገባውን ሁሉ አድርገው ነጽተው እና ጸድተው በሚገባ በእግዚአብሔር ፊት ስለሚቆሙ ነው። ይልቁንም ቅር ያሰኙት ሰው እያለ እርሱን የራሱ ጉዳይ ብሎ በጎን የፈለጉትን ያኽል አምሀ እና ስጦታ ይዘው ቢቀርቡ ተቀባይነት እንደሌለው ጌታችን በወንጌል ተናግሮታል እና በዚህ በኩል ያለ ነውር እና ያለነቀፋ መገኘት አማራጭ የማይገኝለት ዐቢይ ተግባር ይሆናል።

“እንግዲህ መባህን በመሠዊያው ላይ ብታቀርብ፥ በዚያም ወንድምህ አንዳች በአንተ ላይ እንዳለው ብታስብ፥ በዚያ በመሠዊያው ፊት መባህን ትተህ ሂድ፥ አስቀድመህም ከወንድምህ ጋር ታረቅ፥ በኋላም መጥተህ መባህን አቅርብ።” በማለት አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አጽንዖት ሰጥቶ የተናገረው የማንኛውም ክርስቲያን ዘለዓለማዊ መመሪያ ነው። ማቴ ፭፥፳፫−፳፬።

አሁን አነጋጋሪ የሆነብን ጉዳይ የዚህ መጽሐፍ መተርጉማን የሆኑት አባቶቻችን ይህንን የእግዚአብሔር ወልድ ቃል እየሸሹት ይሆንን? አያልን ነው። ቃሌን ሰምታችሁ ስታደርጉት በዚህ ሰዎች ደቀመዛሙርቴ መሆናችሁን ያውቃሉ ነበር ያለው። ይህንን ቃል በመፈጸም ማን እንደሆኑ ሊያሳዩን ይገባል። ጌታችን መባውን የምቀበልህ በብዛቱ ወይም በጥራቱ አይደለምበንጽሕናው እንጂ ማለቱ ግልጽ ነው። ንጽሕናው የሚመጣው ደግሞ የተጣላው ካለ አስቀድሞ ይቅር ከተዋረደ ለይቅርታ ከተጎናበሰ በኋላ መሆኑን በማያሻማ መልክ ነግሮናል።

አሁንም አባቶቻችን ጸሎታቸው እንዲሰምር መባቸው ቅድመ እግዚአብሔር እንዲደርስ እግዚአብሔርም እንዲቀበለው ጠብ የሌለበት ንጹሕ መሆኑን እንዲያረጋግጡ ይገባቸዋል። አኛ መች ተጣልተን እያሉ አግድም መሄዱን ትተው የፍቅርን ፍሪዳ ጥለው ከጎረሱት በማጉረስ እኛንም ሊፈውሱን ይገባል። የፓትርያርክ ምርጫም ሆነ ወደ መንበር የመመለስ ጥያቄ መነሣት ያለበት በመጀመሪያ መቅደም ያለበት የእርቅ ጉዳይ እልባት ሲያገኝ ብቻ መሆኑ የተሰመረበት ቃል ነውና። መስጠትም መቀበልም የሚቻለው በቅደም ተከተሉ መሠረት መሄድ ሲቻል መሆኑ ግልጽ ነው።

መታረቅ ቅድመ እግዚአብሔር ለመቅረብ ብቸኛው መንገድ እንደሆነ ከተረዳን በአቋራጭ ወይም በአማራጭ ወደ እግዚአብሔር መድረስ አይቻልም። ላለመታረቅ የሚደረገው መግደርደር እና ግብግብ በሰዎች ፊት ሰልፍ አሳምሮ ሊሆን ይችላል። በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ምን ያኽል የተጠላ እና ጸያፍ ድርጊት እንደሆነ ከዚህ እንረዳለን። ሰውን እንዲህ እና እንዲያ እያሉ በማመካኘት ማሞኘት እና መደለል ይቻላል እግዚአብሔርን ግን ምን ሊያደርጉት ይችላሉ? በእነርሱ ጠብ እና ግብግብ እየደረቅን ያለነው እኛ ነን። ደርቀናልና ሕማሙ ዘልቆ ተሰምቶናል። ምናልባትም ከጊዜ ወዲህ በምናየው ሂደት የችግሩ ገፈት ቀማሾች እየሆንን ያለነው እኛ እንጂ እነርሱ እንደ መዝናኛ የሚያዩት ይመስላል። ዝኆኖቹ በተጣሉ ቁጥር የሚደርቁት ሣሮች ናቸው።ጌታቸውን የማይሰሙ ከሆኑ እኛን እንዴት ሊሰሙን ይችላሉ? የሚለው ጥያቄ በአእምሮአችን እየተመላለሰ ነው።

ያም ሆነ ይህ መጽሐፉ ያዘዘው ከማንኛውም ተግባር በፊት መታረቅን እንደሆነ ተገንዝበናል። ስለሆነም ፓትርያርክ ለመሆን ከመሽቀዳደም ይልቅ እግዚአብሔር የወደደውን ለማድረግ መፍጠን ይሻላል። ለመሆኑ የትኛውን ምእመን ለመምራት ነው ፓትርያርክ የሚሾመው? ጌታችን የጠፋችውን አንድ በግ ለመፈለግ ከሰማያት ወርዶ ከድንግል ማርያም ተወልዶ እስከ መከራ መስቀል መሄዱን ያልሰማ ይኖር ይሆንን? በስደት ያሉትም ሆኑ በሀገር ቤት ያሉት አንዱ ለሌላው የጠፉ በጎች አይደሉምን? እነርሱን ለመፈለግ አስቀድሞ ዝቅ ማለት፣ በትሕትና መገኘት አይሻልምን?

ፓትርያርክ የሚመረጠው በሰዎች ብቻ ከሆነ ምንም ማለት አያስፈልግ ይሆናል። በእግዚአብሔር ፈቃድ መሆኑን ቢያንስ በከንፈር እንኳ የማይናገር ይኖራል ተብሎ አይጠበቅምና ይህንን ብለናል። ፓትርያርኩን አግዚአብሔር የፈቀደው ግን ያልወደደው ለማድረግ ከሆነ ግን ከእግዚአብሔር ማዕቀፍ መውጣት ያስፈልጋል። የሳኦል ሹመት እግዚአብሔር ፈቅዶታል ግን አልወደደውም። እስራኤል በጸሎት እና በትኅርምት ተጸምዶ የእግዚአብሔርን ሀሳብ ከመስማት ይልቅ እነርሱ የፈለጉትን ብቻ እንዲያደርግላቸው ስለፈለጉ ብቻ ሳይወድድ ግን ፈቅዶ ሳኦልን ሾሞላቸዋል። የተሾመውም ንጉሥ ዕደሜ ዘመኑን እንዳወካቸው እና እንደረበሻቸው ለራሱም በማይበጅ መንገድ እንደተቀሰፈ እናውቃለን። በነቢዩ ሆሴዕ “በቍጣዬ ንጉሥን ሰጠሁህ፥ በመዓቴም ሻርሁት።” የተባለው ለሳኦል መሆኑን ሊቃውንት ያስተምራሉ ። ሆሴ፲፫፥፲፩። ይህም ደግሞ በእኛም የተደገመ ነውና የሩቅ ሳይሆን የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው።

ደግሞም ለአባቶች ይህን ያኸል መናገር አስፈላጊ አይሆንም። በመጽሐፍ “እናንተ ራሳችሁ እርስ በርሳችሁ ልትዋደዱ በእግዚአብሔር ተምራችኋልና ስለ ወንድማማች መዋደድ ማንም ይጽፍላችሁ ዘንድ አያስፈልጋችሁም።”ተብለዋልና። ፩ ተሰ ፬፥፱። ይሁን እንጂ በጉዳዩ ያገባናል ብለው የሚያለቅሱት ምእመናን እና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እውነታውን ይነጋገሩበት ዘንድ ብቻ ነው። አባቶቻችን ሊቀመጡ የሚገባቸው በአባቶች ወንበር መሆን አለበት። የየራሳቸውን ወንበር እየያዙ በመምጣት ቤተ ክርስቲያንን ሊያሳዝኑ ዕድል የላቸውም። “በመጨረሻው ሁላችሁ በአንድ ልብ ሁኑ፥ የሌላው መከራ ለእናንተ እንደሚሆን አድርጉ፥ እንደወንድሞች ተዋደዱ፥ ርኅሩኆችና ትሑታን ሁኑ።” የሚለው የሚመለከተው እነርሱን ነውና። ፩ጴጥ ፫፥፰።

፭∙ በአንድ ሀሳብ ይስማማሉ

ፍቅር ሲኖር አንድነት ስምምነት ይኖራል። እነዚህ ሁለቱ የፍቅር ልጆች ናቸውና። ፍቅር ሲኖር ትዕቢት ይጠፋል፣ ትኅትና ይነግሣል፤እነዚህም የፍቅር ውጤቶች ናቸው። እነዚህ ሲመጡ ደግሞ ልሾም ልግነን የሚል የጎልማሳነት ምኞት ይጠፋል። ግለኝነት ተወግዶ ከእኔ ይልቅ የወንድሜ ሀሳብ ይሻላል የሚለው ቦታ ያገኛል። ይህ ሲሆን ደግሞ ቡድነኝነት ርቆ ለአንድ ዓላማ ለአንድ ፍላጎት በጋራ መቆም ይመጣል። ቅዱስ ጳውሎስ “እርስ በርሳችሁ በአንድ አሳብ ተስማሙ፤ የትዕቢትን ነገር አታስቡ፥ ነገር ግን የትሕትናን ነገር ለመሥራት ትጉ። ልባሞች የሆናችሁ አይምሰላችሁ።” በማለት እንደተናገረው የየግል ስሜቶች ጠፍተው የቤተ ክርስቲያንን ፍላጎት መከተል ይቻላል። ሮሜ ፲፪፥፲፮።

ለዚህም ነው መጽሐፍ በተደጋጋሚ አንድ የመሆንን አስፈላጊነት ሊያስገነዝበን የፈለገው። “በአንድ አሳብ ተስማሙ፥ አንድ ፍቅር አንድም ልብ አንድም አሳብ ይሁንላችሁ።” የሚለው ቃል የአንድነትን አስፈላጊነት የሚያስረዳ እንደ ትእዛዝም የተላለፈ ነው። ፊል ፪፥፪። ከእኛ የሚጠበቀው ለቃሉ መታዘዝ ብቻ! ጠቢቡም “የጐመን ወጥ በፍቅር መብላት የሰባ ፍሪዳን ጥል ባለበት ዘንድ ከመብላት ይሻላል።” በማለት ፍቅር ምን ያኽል አስፈላጊ እንደሆነች ይመክራል። ምሳ ፲፭፥፲፯።

ይቆየን፡፡

Go toTop