መጋቢት 29 ቀን 2015 ዓ/ም
ቀሲስ አስተርአየ [email protected]
ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክረስቲያን ቀሳውስት ትድረስ!
ህዝባችን ሊፈታው ሊያስወግደው ካቅሙ በላይ የሆነ ችግር ሲደርስበት “ኧረ ቄስ ጥሩ” ይላል፡፡ ይህ አባባል ለብዙ ዘመናት ስለኖረ ባሕል ይመስላል፡፡ በመለመዱ ባህል ይምሰል እንጅ “ከእናንተ የታመመ ማንም ቢኖር የቤተ ክርስቲያንን ቀሳውስት ይጥራ”(ያዕ 5፡14) ብሎ ቅዱስ ያዕቆብ ያዘዘው ሐዋርያዊ ትውፊት ነው፡፡ ጥሪውን የሚሰማ ቄስ ባይኖርም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታይ ትውፊቱን (ልማዱን ) ተከትሎ ዛሬም ቄስ ጥሩ እያለ ነው፡፡
አሁን ቀርቶ ካልሆነ በቀር በሐኪም ታክሞ ለማይድን በወጌሻ ለማይጠገን በዘመኑ አጥማቂወችና ዘይት ቀቢወች ለማይፈውስ ብሽታ የሚጠሩ ቄሶች ነበሩ፡፡ ሰው መርዘኛ ሕዋሳት ተሸካሚ ለሆኑት አይጥና እብድ ውሻ በመሳሰሉ ሕዋሳት ንክኪ ሲጋለጥ፡ የሚረግጠውም መሬቱ ረክሷልና በስማም ብሎ ጠበል የሚረጭ ቄስ ጥሩ ይባል ነበር፡፡
ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች በአይጦች ባበዱ ድመቶችና ውሾች ልክፍት በባሰ ሰበነክ ልክፍት ተለክፈዋል፡፡ የመርዛቸው ልክፍት የኢትዮጵያን ምድር የገዳይና የተገዳይ የአፈናቃይና የተፈናቃይ የተሰዳጅና ያሳዳጅ የቀባሪና የተቀባሪ ያልቃሽና ያስለቃሽ ከተማ አድርገዋት ህዝበ ክርስቲያኑ ኧረ ቄስ ጥሩ እያለ ነው፡፡
ከመርከስም አልፎ በመርዙ ልክፍት በሚሞተው በሰው ሥጋና አጽም ገጸምድሯ ተሸፍኗል፡፡ አፈሩ በሰው ደም ጨቅይቷል፡፡ የሚነፍሰው አፈር ትቢያ የሆነውን የወገንን ሥጋ ባፍንጫችን እየጋተን ነው፡፡ የምንጠጣው በወገኖቻችን ደም የተቀላቀለ ውሀ ነው፡፡ ነፋስ ከመሬት እየጠረገ በሰውነታችን ላይ የሚበትነው ትቢያ ሰወቻችንን እያለበሰው ነው፡፡ እኛ ክርስቲያኖች ሁላችንም ሙታን በመሆናችን ስርአተ ቀብር የሚፈጽም ቄስ የለም፡፡ አልቅሶ ገንዞ የሚቀብር ወገንም የለም፡፡ አፈር ትቢያ ሆኖ ነፋስ በላያችን በሚበትነው በወገን አካል እየተቀበርን ነው፡፡ ሕዝቡ “ንፍሴን ከሞት አዳንካት” የሚለውን ዳዊት ደግሞ ንጹሕ አፈር የሚበትን ቄስ ጥሩ እያለ ነው፡፡
በየሳምንቱ ዓርብ በሰላም ዘመን “ቅዱሳነ አድኅን እመራደ ካልዕ ሕዝብ”(ሊጦ ዘዓርብ) ከሰባዊ ስሜት በራቀ በአራዊታዊ ጭካኔ ስሜት ከሚወር ድንገተኛ ወራሪ ንጹሐን ወገኖቻችንን ጠብቃቸው” የምንለውን በቤተ መቀደስ እንድንደግመው ብቻ ሳይሆን በወራሪውና በተወረረው ሕዝብችን መካከል ለመቆም በክህነታዊ ቅስናችን ተጠርተን ነበር፡፡
ኢትዮጵያውያን በተለይም ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች በተናጠልና በቡድን ከመሰደድ ከመፈናቀልና ከመገደል በብልጽግና ዘመን ፋታ ያገኙበት ቅጽበት ባይኖርም፡ ከሞት ተርፈው በሕይወት ያሉት በክርስትናችን በማንነታችን ተሰደድን በአረመኔወችም ተበዘበዝን እያሉ የሚያሰሙት ጩኸት “ንሕነሰ እለ ተሰደድነ በእንተ ስምከ ወኮነ ሕብልያ እምኅቤሆሙ ለዕልዋን” እያልን የሆሣዕና ዕለት ከምናንጎራጉረውና ከምናነበው ጋራ ገጠመ፡፡ አይገርምም?
ቄሶች ቢችሉ ከኛ ጩኸት በፊት ቀድመው፡ የመቅደም እድሉን ቢያጡት ጩኸታችንን ተቀብለው “ረዐየነ በሣሕልከ ከመ ንሐድፍ ለመሃይምናኒከ” (ቅ አ ቁ 138) በፊታችን የተደቀነውን መከራ ለመጋፈጥ ኃይሉን ስጠን የሚሉ ቀሳውስት ይጠሩ እያለ ሕዝቡ ድምጹን እያስተጋባ ነው፡፡
“ወያብጥሎ ለዘያሜክረነ ወስድዶ እምኔነ ወገሥጽ ሁከታቲሁ ዘተከለ ዲቤነ ውብትክ እምኔነ ምክክንያተ እንተ ትወስደነ ውስተ ኃጢአት ወባልሐነ በኃይለ ቅዱስ በኢየሱስ ክርስቶስ እግዚእነ”(ቅ ጎ ቁ 85) ለሕይወታችን አስጊ በሆነ
ተግዳሮት ላይ የጣለንን አጥፊ ኃይል አርቅልን፡፡ መናብርት በመካከላችን የተከሉትን እርስ በርስ መገዳደያ አመራር አፍርስልን የሚለውን በቃል እያሰማን በተግባር እንድንተረጉመው የሚያስገድደንን የሆሣዕናውን ቅዳሴ በቤተ መቅደሱ ብናፍነውም፡ ሕዝባችን ግን ድምጹን እያሰማበትና የሚተባበረንን ቄስ ጥሩልን እያለ ነው፡፡ አቤት! አቤት! አቤት ! እንዲህ ያለ ክፉ ዘመን ህዝባችንን ገጥሞት አያውቅም፡፡
እርስ በርስ በሚያገዳድል አመራር ላይ የወደቀው ህዝባችን “ናሁ ለደቂቅክሙ በልዐተነ
ኃጢአት ከመ ዘእሳት ወአውያተነ ፍትወት አኮ ፍትወት ዘነፍስ አላ ፍትወት ዘሥጋ ዘውእቱ ማኅጎሊሃ ለነፍስ”(አት ቁ 34)፡፡
ማለትም፦እኛ ልጆቻችሁ ተቃጠልን፡፡ ሥጋችንን ብቻ ሳይሆን ውስጣችንን መንፈሳችንንና ትውልድ የሚያጠፋ ከቀድሞው የከፋ መከራ ስለወደቀብን “የእግዚአብሔርን ቃል ማካፈል ብቻ ሳይሆን የገዛ ነሳቸንን ደግሞ እናክፋላችሁ ዘንድ በጎ ፈቃዳችን ነበረ፡፡ ለእኛ የተወደዳችሁ ሆናችሁ ነበር ”(1 ተሰ 2፡8) የሚሉ ቄሶችን ጥሩ እያለ ነው፡፡
“ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል”(1ኛ ዮሐን 2፡17) የሚለውን ተረድተው ከዓለምና ከምኞቱ የተላቀቁትን “ሞት ፈርሀ ወዲያብሎስ ወድቀ ወሲኦል ሖረት ምስለ እሊኣሃ ኅቡረ ለቀበላ አምላክ ግሩም”(ቁ 44)
የሚለውን የሆሣዕናውን ቅዳሴ ለመቀደስ የበቁትን ቄሶች ጥሩ የሚል ዋይታ እየተሰማ ነው፡፡
አትናቴወስ “ናሁ ለደቂቅክሙ በልዐተነ ኃጢአት ከመ ዘእሳት ወአውያተነ ፍትወት አኮ ፍትወት ዘነፍስ አላ ፍትወት ዘሥጋ ዘውእቱ ማኅጎሊሃ ለነፍስ”(አት ቁ 34)፡፡ ብሎ የተናገረውን ማለትም “ትውልድ በሚያመክን እልቂት እኛ ልጆቻችሁ ተቃጠልን ሥጋችን ተበላ ውስጣችንን መንፈሳችንና ሁለመናችን ሁሉ ከሰለ” የሚለውን በሹክሹክታ ከመድገም ተላቀው በቃላቸው እየተናገሩ በተግባር የሚተርጉም ቄሶችን ጥሩ እያለ ነው፡፡ “ኢትፍራህ ተጋነዮ በእንተ ኃጢአትከ ወኢትወስክ ኃጢአተ በዲበ ኃጢአት” (ሲራ 5፡5) የሚለውን ተረድተው ከአሸማቃቂ ነውር ራሳቸውን በንስሀ በኑዛዜ አጸድተው ባካባቢው የተፈጸመውን ኃጢአት እየገለጹ ኃጢአተኛውንና በህዝብ ላይ ያመጸውን ከማውገዝ የማያፈገፍጉ ቄሶች ይጠሩ እየተባለ ነው፡፡
በቤተ መቅደስ ውስጥ ተደብቆ “ንሕነሰ እለ ተሰደድነ በእንተ ስምከ ወኮነ ሕብልያ እምኅቤሆሙ ለዕልዋን” እያለ የሚቀድሰውን ቄስ አርቅልን፡፡ ከቤተ መቅደስ ውጭ ድምጹን አስምቶ ለዓለም የሚጮኽልንን ቄስ አቅርብልን አያለ ነው፡፡ “አብጥሎ ለዘያሜክረነ ወስድዶ እምኔነ ወገሥጽ ሁከታቲ ዘተከለ ዲቤነ ወብትክ እምኔነ ምክንያተ እንተ ትወስደነ ውስተ ኃጢአት” ”(ጎርጎ ቁ 85) የሚፈታተነንን አስወግድልን በመካከላችን አለመረጋጋትን የሚሰብከውን ገስጸው ወደጥፋት የምንጎተትባቸውን ሰንሰለቶች ሁሉ በጣጥስልን የሚለውን በቤተመቅደስ ተደብቆ የሚደግመውን፤ በተግባር ለመግለጽ የፈራውን ቄስ አርቅልን እያለ ነው፡፡
“ናንቀዐዱ ኀቤከ አዕይንተ አልባቢነ ወናደንን ለከ ቀፈተ ልብነ ግናይ ለከ ለመንግሥትከ “(ጎር 15)፡፡ ማለትም
ወደ መንግሥት ከማንጋጠጥና ክሣደ ልቡናን በምንግሥት ከማስረገጥ አላቀው ዓይነ ልቡናቸውን ወደ እግዚአብሔር ያንጋጥጡትን ክሣደ ልቡናቸውን ወደ እግዚአብሔር ያዘነበሉትን ቄሶች ጥሩ እያለ ነው፡፡
“ከኃጢአተኛው ጋራ ስትታገሉ ገና ደማችሁን እስከ ማፍሰስ ድረስ አልተቃወማችሁም”(ዕብ 12፡4) የሚለውን ሐዋሪያዊ ትውፊት ለሰረዙትና ለረሱት ጳጳሳት “ከመ ዐቂበ ይዕቀቦ ለነ ልብዙህ ዓመታት ዘተአመኖ ለሢመተ ክህነት ዘብዑለ ጸጋሁ ይጼጉ”(ሥ ቅ ቁ 15_18 ) ማለትም፦“ለረዥም ዘመናት ለብዙ አመታት ጠብቃቸው” እያሉ የሚቀድሱትን ቄሶች ከመቅደሳችን አርቅልን እያለ ነው፡፡
“ነሳዕናሆሙ በመዋዕሊነ አስተብቋዕያነ ለነ ለኀበ እግዚአብሔር”(ቅ ማ ቁ 10)፡፡ “ወደን አክብረን አባትነታችሁን ተቀበለነዋል” እየተባለ ለህዝባቸው ተላልፈው ለሚሰውት አባቶች የሚጸለየውን ህዝብ ላልመረጣቸውና ለሕዝብ በዝባዦች፡ በምቾት እንቅልፍ ላይ ላሉት ጳጳሳት የሚጸልዩትን አድርብዮችን ቄሶች ከመንበሩ አርቅልን እያለ ነው፡፡
“አሌ ሎሙ ለእለ ይጽሕፉ መጽሐፈ እኩየ ወይመይጡ ፍትሐ ነዳይ ወምስኪን ሕዝብየ ወአይቴ የሐደጉ ትርሲቶሙ ከመ ኢይደቁ ውስተ ሀሳር፡፡ ወበእንተዝ ኩሉ ኢተመይጠት መአቱ” (ኢሳይያስ 10 ፡2 ) ህዝብ የሚለያይበትን ሰው
የሚጎዳዳበትን ሕግ የሚቀርጹ ሰወች ወዮላቸው የሚለውን መለኮታዊ ማስጠንቀቂያ በሙሉ ልብ የሚናገሩ ቄሶችን ጥሩ እያለ ነው፡፡
አብዶ ሰው እየነከሰ መርዙን ወደ ሌላ እንዳያሳልፍ ለማስቆም በርብርብ አይነት ዘመቻ የሚገደል ውሻ ደሙ ተጠያቂ አልባ ነው፡፡ የእብድ ውሻ ደም ብድራት ከፋይ የለውም፡፡ ገዳዩ በሐላፊነት አይጠየቅም ፡፡ የክርስቲያን ወገኖቻችን ደም፤ ተጠያቂ አልባ ደመከልብ በሆነበት ዘመን የሚጠራ ቄስ አጣን እያለ ሕዝብ እየጮኸ ነው፡፡ “ወላሂ ከዛሬ ጀምሮ አማራ አይደለሁም” እያለች የተገደለችው ሙስሊሟ ወገናችን ሼክ ጥሩ እያለች ነው፡፡
በመዋዕለ ጾማችን መጨረሻ “የአምላክ ውዳሴ በአንደበታቸው ነው፡፡ባለ ሁለት ልሳን ሰይፍም በጃቸው ይሁን ህዝቦችን የሚበቀሉበት ሰወችንም ይቀጣሉ ነገሥታቶቻቸውን በሰንሰለት መኳንንቶቻቸውን በእግር ብረት ያስራሉ፡፡ በነሱ ላይ
የተጻፈውን ፍርድ ይፈጽማሉ”(መዝ 149፤ 6_9) እያልን ምናስተዛዝለው ዳዊት “ የአምላክን ውዳሴ ከከንቱ ድጋም ተላቀው ሁለት ልሳን ካለው ሰይፍ በሰላ አንደበታቸው እንደነ መምህር ገብረ ኢየሱስ የሚመሰክሩትንና በተግባራዊ ትርጓሜያቸው የወራሪን እጅና እግር ማሰር መፍታት ብቃት ያላቸውን ቄሶች ጥሩ ማለት ነው፡፡
ህዝባችን ይህንን ጥሪ በሚያሰማበት ወቅት ገዳዮቹ እየተሳሳሙና እየተስማሙ እየተሳሳቁና እየተሳለቁ ለበለጠ እርክሰት ተመልሰው በህዝብ ላይ
እየሰለጠኑ ናቸው፡፡ “ወለኩሎሙ እለ ይትቃረንዋ ለሕግነ ሠሩ እምድር ዝክሮሙ ወኢትጽሐፍ ስሞሙ ውስተ መጽሐፈ ሕይወት”(ቅ አ ቁ 135) ማለትም ከነገረ መለኮት ሁሉ በላይ የሆነውን ሰው ያስጠፉትን ሕጋችንን የሚቃረኑትን ቄሶች ወይም ጳጳሳት ከክህነተዊ ተልእኮ ሰርዟቸው የሚለው ሕገ ቤተ ክርስቲያን ተሽሮ በመርገማቸው እንዲቀጥሉ ወደ ቤተ መቀድሰ እየተመለሱ ናቸው፡፡ ይህን ስህተት በግልጽ የሚቃወሙትን ቄሶች ጥሩልን እየተባለ ነው፡፡
ህዝቡ የቅዳሴውን ይዘት ባለመረዳት ይሁን እግዚአብሔር ዋጋችሁን ይክፈላችሁ በሚል ትግስቱና ትሕትናው ከቤተ መቅደሱ ባያባርረንም፡ ጥሪውን
ሳንቀበል የሆሣዕናውን ቅዳሴ ቀድሰን “በዘኀለፈ ይምሐርክሙ ወበዘይመጽ ይዕቀብክሙ በእንተ ሥጋሁ ሥጋ መለኮት ወበእንተ ደሙ ደመ ሕግ ወሥርአት ኢየሱስ ክርስቶስ” (ቅ ሐ ቁ 161) ከዚህ ቀደም ንስሀ ለገባችሁለት
በደላችሁና ኃጢአታችሁ እግዚአብሔር ይቅር ይበላችሁ ወደፊት ተመሳሳይ በደል ከመፈጸም ይጠብቃችሁ ለማለት በሕዝብ ፊት ስንቆም ድፍረት አይሆንብንምን?
በጻሕል የሚሰየመው መለኮታዊ ሥጋው በጽዋዕ የሚቀዳው ደሙ የሕግና የሥርአት መነሻና መድረሻ ነው፡፡ በሕግ ደባ ተስርቶበት ፍርድና ስርአት ተነፍጎት ቄስ ጥሩ እያለ በሚጮኸው ህዝብ ፊት የአምላክን ሕግና ስርአት መነሻና መድረሻነቱን በቃላችን ሳንመሰክር በተግባራችን ስናረጋግጥ የዘንድሮውን የሆሣዕናውን ቅዳሴ መቀደስ ኧረ ቄስ ጥሩ የሚለውን ህዝብን ንቆ መርገጥ በአግዚአብሄር ላይም መሳለቅ መሰለኝ፡፡
ኧረ ቄስ ጥሩ ሲባል እየሰማን ጥሪውን ሳንቀበል ድምጣችንን አጥፍተን ቅዳሴውን እንቀጥል? ወይስ ጥለን እንጥፋ? ምን እናድረግ ? አሁንስ እኔን ግራ ገባኝ፡፡ የሆሣዕናውን ዐመታዊውን ቅዳሴ የምትቀድሱ የኔ ቢጤ የዘመኔ ቀሳውስትስ ተመሳሳይ ስሜት ይሰማችሁ ይሆን! ከተሰማችሁ በጋራ ምን እናድረግ?
በተረፈ ኧረ ቄስ ጥሩ የሚለውን ሕዝባዊ ጥሪ ሰምተው በመቀበል “አብጥሎ ስድዶ ገሥጾ ብትኮ” (ጎርጎ ቁ 85) እያሉ የሆሣዕናውን ቅዳሴ የሚያቀርቡ ንጹሐን ቀሳውስት ጨርሰው አይጠፉምና እግዚአብሔር ቅዳሴያቸውን ይቀበልላቸው፡፡