በላይነህ አባተ ([email protected])
ዛሬም እንደ በፊቱ አሽከርና ሎሌ ሆነው አገርን ሲክዱና ሕዝብን የምድር ሲኦል ሲያሳዩ የኖሩ ጭራቆች በስልጣን ተጣልተው ያስፈጁትን በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ዜጋና ያሰደዱትን በሚሊዮኖች የሚቆጠር ሕዝብ ችላ ብለን የእርቅና የድርድር ጭፈራ መደለቅ ጀምረናል፡፡ እነዚህ ጭራቆች አስገድደው በመድፈር የወደፊት እጣ ፈንታቸውን ያጨለሙትን ወይዛዝርት ዘንግተን፤ ታለወላጅ ወይም ታለልጅ ስለቀሩ በሐዘን የተቆራመዱትን ወገኖች ረስተን፤ በዘራቸው እየተመረጡ ተቤታቸውና ተእምነት ሥፍራቸው ታርደውና ተቃጥለው ምድር በግ ኒደር እየተበረቀሰ ተጉድጓድ እንደ ቆሻሻ የተጣሉትን ወገኖች ችላ ብለን፣ ሆዳቸውን በስለት የታረደውን እርጉዞችና አይናቸው ተቆፍሮ የወጣውን ወጣቶችን ተቁብ ሳንቆጥር በደም የቆሸሸ የእርቅ ጥሩንባ በመንፋት ላይ እንገኛለን፡፡ ለዚህ ሁሉ በኢትዮጵያ ታይቶ ለማይታቅ የመከራ ቸነፈር ቀጥተኛ ተጠያቂ የሆኑንት አውሬዎች በቅጥፈት የተሞላ ድርድር የሚያዳምቅ አጃቢ በመሆን መለኮትንም፣ ህሊናንም፣ ታሪክና ትውልድንም በማስከፋት ላይ እንገኛለን፡፡
ከእነዚህ የአረመኔዎች የቅጥፈት ድርድር ጥሩንባ ነፊዎች አንዳንዶቻችን የብሔራዊ እርቅንና ይቅር ባይነትን ጠቀሜታ ለማሳየት በአፓርታይድና በደቡብ አፍሪካ ጥቁሮች የተፈፀመውን እርቅ በማስረጃነት እንደ ውዳሴ ማርያም እንደግማለን፡፡ በደቡብ አፍሪካ “እርቅ” እንደሰፈነ በምዕራባውያን አቀንቃኝነትና በእኛ ተቀባይነት ተዘፍኗል፡፡ ስለዚህ እርቅ ዘፍነን ባናባራም ፍትህ ግን እንጦሮጦስ እንደ ወረደች ደም የጎረሱት የደቡብ አፍሪካ ወንዞች፣ የሕዝብን ጩኸት ያስተጋቡት የደቡብ አፍሪካ ተራሮች፣ የታጋዮችን ስቃይ ያዳመጡት የደቡብ አፍሪካ ከርቸሌዎች ብቻ ሳይሆኑ የአፓርታይድ መሪዎችም ያውቁታል፡፡ በዚህ ፍትህ እንደ ጭቃ ተረግጣ እርቅ እንደ ጎርፍ ወረደበት በሚባለው ደቡብ አፍሪካ ዛሬም ገዳይና የገዳይ ወገን እንደ ሥጋጃ ተንፈላሶ፣ የተገዳይ ወገን ግን እንደ ቆርበት ተቆራምዶ ይኖራል፡፡ ይህ ፍትህ አልባው የደቡብ አፍሪካ እርቅ ገዳዮችን ጠቅሟል፤ የተገደሉትን ግን ከመቃብርም በጦር ወግቷል፡፡ ከመቃብር በጦር የተወጉትን ዜጎች እንደ ውቃቢ ዶሮዎች ለኢፍትሐዊ እርቅ ገብረው የሟች ወገኖች እርምን እየጠሸቀሙ መኖርን ቀጥለዋል፡፡ እንደ ዓባይ የፈሰሰው ደም ፏፏቴ ግን ዛሬም “የፍትህ ያለህ!” እያለ ይጮኻል፡፡
እንደ ደቡብ አፍሪካ ሕዝብ እኛም አራጅና ታራጅ ሆነን አራጆች ደማችንን እንደ ፋሲካ በግ ሲያፈሱት ታራጆችም እንደ ፍሪዳ ስንሰዋና ስንበላ ኖረናል፡፡ የሰማእታት ወገኖችም የደቡብ አፍሪካን እርቅ እየጠቀስን አራጆችን ነፃ እሚያወጣውን የእርቅ ዘፈን ከሰማእታትን አስከሬኖች በተሰራ ደረጃ መዝፈንና መደለቅ ቀጥለናል፡፡ ከድለቃው በስተጀርባም ካራጆች ጋር ውል አስረን የታረዱትን እርም ለመብላት የቋመጥን ሆነናል፡፡ ይህንን ለመብላት የቋመጥነውን እርም የተባረከ ጮማ ለማስመሰልና የእርቅ ሐዋርያ ለመባልም መጽሐፍ ቅዱስ መጥቀሱን ቀጥለናል፡፡
“የእርቅ” ሐዋርያት ሆይ! መጽሐፍ ቅዱስ ከየትኛው ምዕራፉ እርቅን ከፍትህ ነጥሉ ሲል ያስተምራል? “ኢፍትሐዊ እርቅን ፈጥሙ!” የሚልን ምዕራፍ የትኛው መጋቢ ብሉይና መጋቢ ሐዲስ ሊጠቅስ ይችላል? ቅዱሱ መጥሐፍ እርቅን ከፍትህ ነጥሉ ካላለስ ካራጆቻቸው ውል አስረን ኢፍትሀዊ እርቅን እንድንፈጥም የታረዱት ሰማእታት መቼ ፈርመውልናል? አራጆች ከነነፍሳቸው ገደል የወረወሯቸው፣ የአራጆችን ካራ ሲሸሹ አውሬ የበላቸው፣ በአረመኔዎች ብትር ማሰብ የተሳናቸውና ሌሎችም ያካል ጉዳተኞች በእነሱ ስም ፍትህን ረግጠን “የእርቅ” ውል እንድናስር መቼ ቃላቸውን ሰጥተውናል? በማን ህይወት ማን ከአራጆች ኢፍትሐዊ ውል አስሮ ሰላሙን ይተኛል? በማን የስቃይ ማገዶ ማን ከአረመኔዎች እርሾ ተበድሮ እንጀራውን ይጋግራል?
የእርቅ ጥሩንባ ነፊዎች ሆይ! በግፍ የረገፉት ሚሊዮን ዜጎች እንኳን ለናንተ ለወላጆቻቸው፣ ለልጆቻቸው፣ ለወንድሞቻቸውና ለእህቶቻቸውስ ኢፍትሐዊ እርቅ እንዲፈጸምብቻው ባውራ ጣታቸው ፈርመው አልፈዋል ወይ? የፍትህ መብታቸውን እንደ ገዳዮቻቸው እንድትገፉ ለናንተ መብቱን ማን አስረክቧል? “በሽግግር ውስጥ ሰው ይሞታል” በሚል አረመኔአዊ ፈሊጥ በ “እርቅ” ከረጢት ቋጥራችሁ እንደ ፍሪዳ ፈርስ ከወረወራችኋቸው እናንተስ ካራጆቻቸው ትሻላላችሁ ወይ? “ያለፈው አልፏል! የሞተ ሞቷል” በሚል ኢሞራላዊና ድውይ አስተሳሰብ እስራኤላውያን ዜጎቻቸውን እንደ ፍሪዳ ፈርስ በእርቅ ቋጥረው ቢወረውሩ የሂትለር ጀኔራሎች ዛሬም እየታደኑ ለፍትህ ይቀርቡ ነበር ወይ? የተቀሩት አይሁዳውያንስ እንደገና ተመጨፍጨፍ ይድኑ ነበር ውይ?
የውሸት እርቅ ጥሩንባ ነፊዎች ድርድርና ሽምግልናን የማምታት አባዜ፦
የምዕራባውያን ሰው ከተፈጠረበት ዘመን ጀምሮ የነበረውን የኢትዮጵያውያን እምነትና ባህል ተሸቀጣቸውና ተእርጥባናቸው ጋር በሚልኩት እንደ ጥንዚዛ በሚያፈናጥር የዳንስ ባህል ከተፈታተኑት በከፋ ሁኔታ የኢትዮጵያን የሽምግልና ሥርዓት ተፈታትነውታል፡፡ ሽምግልናን ድርድር በሚባል ተበዳይን ከበዳይ እግር አስወድቆ ይቅርታ በሚያስጠይቅ ኤፍሬም ይሳቃዊ ወለፈንዲና ኢመለኮታዊ ተግባር ክፉኛ አጥቅተውታል፡፡ የኢትዮጵያን ሽምግልና መለኮታዊ ሚዛንን፣ ፍርድንና ፍትህን ያካትታል፡፡ በአንፃሩ ኤፍሬም ይሳቅ እንደ ወረርሽኝ ጎትቶ ያስገባው ሳጥናኤላዊ ድርድር መለኮታዊ ሚዛንን፣ ትክክለኛ ፍርድንና ፍትህን በመዳመጫ ደፍጥጦ የተጎዳውን ደካማ ተጎጂው ጉልበታም በደም የከረፋ እግር ሥር ወድቆ ይቅርታ እንዲጠይቅ ያደርጋል፡፡
የውሸት እርቅ ጥሩንባ ነፊዎች ፍርድና ፍትህን የማምታት አባዜ፦
ፍትህን ያልተላበሰ ፍርድ የሳጥናኤል ግብር ነው፡፡ ይህ የሳጥናኤል ግብር የሆነው ኢፍትሐዊ ፍርድ ተውጪ እንደ ሸቀጥ ተሸምቶ የገባ ነው፡፡ ማንም ማየት እንደሚችለው ዲሞክራሲ ደንድኖባቸዋል በሚባሉት ምዕራባውያን አገሮች ሳይቀር በፍርድ ቤት አሸንፎ የሚገባው ገንዘብ ያለውና ነገርን ፈቶ እንደገና መግጠም የሚችል ወይም ነገሮችን አንከረባብሶ ማደናበር የሚችል የሕግ ባለሙያ መቅጠር የሚችል ብቻ ነው፡፡ ገንዘብና ሥልጣን ያለው ነፍስ ቢያጠፋ እንኳን ነፃ ሊወጣ ይችላል፤ ከተፈረደበትም ትንሿን ቅጣት ብቻ ያገኛል፡፡ እንደዚህ ዓይነቱ ብይን ኢፍትሐዊ ፍርድ ይባላል፡፡ ኢፍትሐዊ ፍርድ ከመለኮት ስለማይመጣ የሳጥናኤል ግብር ይባላል፡፡ ኢፍትሐዊ ፍርድ ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ እንዲያውም የጪራቅ ቀንድ አውጥቶ እርጉሙ ቅዱሱን ከሶ ፍርድ ቤት ገትሮና አስሮ መከራውን ያበላዋል፡፡ እርጉሙ ከሳሽ ምስክር ገዝቶ ወይም አስፈራርቶና አሰልጥኖ አይኑን በጨው ታጥቦ በቅዱሱ እንዲመሰክርበት ያደርጋል፡፡
በእምነታችን፣በታሪካችንና በባህላችን እንደዚህ ዓይነቱ ኢፍትሐዊ ፍርድ እንኳን በአዋቂዎች ዘንድ በልጆች ሳይቀር እንደ መቅሰፍትና እንደ ኩነኔ የሚታይ እጅግ ፀያፍ ተግባር ነበር፡፡ በመለኮት ሚዛን የተለካ ፍትሃዊ ፍርድና እርቅ ለብዙ ሺህ ዘመናት እምነታችንና ባህላችን ሆኖ ቆይቷል፡፡ ልጅ ሳለሁ ሁለት ጎረምሳ ወንድማማች ያጎቴ ልጆች መንገድ ገፍተው የተከሉትን ተክላቸውን የረገጠ አንድ ሰው ፈነከቱ፡፡ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ፈንካቾችና ተፈንካቹ ለእርቅ ተስማሙ፡፡ የፈንካቾቹ አባትና ሌሎች አጎቶቼ ሽማግሌ የመምረጡን ዕድል ሙሉ በሙሉ ለተፈንካቹ ሰጡ፡፡ ይህንን ሽማግሌ የመምረጡን እድል የተረከበው ተፈንካችም የፈንካቾችን አባት፣ አጎታቸውንና የእኔን አባት ለሽምግልና መረጣቸው፡፡ ተፈንካቹ ለሽምግልና የመረጣቸው የፈንካቾች አባት፣ ሌላው አጎታችንና አባቴ የተጣለባቸው አደራ ከሰማይ የወረደ ያህል ተሰማቸው፡፡ ይህ አደራ የከበዳቸው እነዚህ ሽማግሌዎች ባንድ ድምፅ በልጆቻቸው ፈርደው ከዚያ በፊት በዚያ ዘመን ለእንደዚህ ዓይነት እርቅ ተከፍሎ የማይታወቅ ገንዘብ እንዲከፍሉና ድንጋይ ተሸክመው እግሩ ስር ወድቀው ተፈንካቹን ከልብ ይቅርታ እንዲጠይቁ አድርገው አስታረቁ፡፡ በእርቁ ወቅት ተፈንካቹና ፈንካቾች ተቃቅፈው በእንባ ተራጩ፡፡ ግፉና ብሶቱ ከእንባው ጋር ከልባቸውና አይምሯቸው ወጣና በንፁህ ልብና መንፈስ መለኮትን አስደሰቱ፡፡ በሽማግሌዎች ፍትሐዊ እርቅ የረካው ተፈንካችም “ፍትህ ይበቃኛል” በሚል መንፈስ የሰጡትን ገንዘብ አልቀበልም ብሎ መለሰው፡፡ ፈንካቾችም ገንዘቡን አንቀብለም ብለው ትተውለት ሲሄዱ ሌላ ጊዜ ሳያዩት ከደጃፋቸው ጣለለቻው፡፡ ሽምግልናው እርቅን ወለደ እርቅም ፍትህን አነገሰ፡፡ ፍትህን ያነገሰው እርቅም ሰላምና ፍቅርን እስከ መጨረሻው አሰፈነ፡፡
ይኸንን የመሰለ ሰላምና ፍቅር የሚያነግሱ የእርቅ እሴቶቻችን በውጪ ኃይሎች እሽኮኮ ወንበር በተጎለቱት ገዳይ ገዥዎች፣ እነዚህ ገዳዮች እንደ ችግኝ በተከሏቸው የሃይማኖት መሪዎችና ገዳዮችን በሚላላኩ ሽማግሌዎች ጥቅሙ እንዳለቀ ድሪቶ ተወርውረዋል፡፡ በእነዚህ እሴቶች ምትክም ጉልበተኛ እንዲያሸንፍበት ፈረንጅ የሸመነውን የድርድር (ሚዴሽን) ሸማ እነ ኤፍሬም ይስሃቅ ሸምተው ዘርግተዋል፡፡ ይህንን ከምዕራባውያን የሸመቱትን የድርድር ሸማ እየጎተቱም ወንጀልን መሸፋፈን ከጀመሩ ውለው አድረዋል፡፡ እነ ኤፍሬም ይስሃቅ በግፍ የተገደሉትን ወገኖቻችንን ፍትህ ነፍገው ከምዕራባውያን በሸመቱት የድርድር እራፊ አጥንታቸውን እንደ ችቦ አስረው፣ እንደ ጎርፍ የወረደውን ደማቸውን እንደ ስፖንጅ መጠው እንደ ወጥ ቤታቸው ቆሻሻ ጥለውታል፡፡ ይኸንን ፍትህን የገደለ ድርድራቸውንም ብሔራው እርቅ ብለው ሰይመው ሽምግልናንና እርቅን እስተንፋሳቸውን አፍነው ሰውተዋቸዋል፡፡ እነ ኤፍሬም ይስሃቅ እንደ እኔ አባትና አጎቶች ጥጋበኛ ፈንካቾችን በግፍ ከተፈነከተው እግር እንዲወድቁ ሳይሆን በግፍ የተፈነከቱትን ከአረመኔ ፈንካቾች እግር ወድቀው ይቅርታ እንዲጠይቁ አድርገዋል፡፡ በዚህ ኢሰብአዊና ኢሞራላዊ ድርጊታቸውም በሞቱት ነፍስ፣ በተጎዱት ህይወት፣ በእኛ ህሊናና በመለኮት ኃይል ቀልደዋል፡፡
ሄሮድተስና ነቢዩ መሐመድ ሳይቀር የፍትህ መንደር ባሏት ኢትዮጵያ ሽምግልና ታሞ ተኝቶ ሽምግልናን ተምዕራባውያንና እስከ ትናንት ድረስ የእነሱ ቅኝ ተገዥ ተነበሩት ተናይጀሪና ተኬንያ መማር፤ ሽማግሌዎችንም ተእንሱ መምረጥ ቀጥለናል፡፡ የራሳችንን ሥር እየነቀለን የሌሎችን አረም መትከል ጀምረናል፡፡ ሽምግልናን በድርድር መዶሻ እየፈነከትን እየሰባበርነው ይገኛል፡፡ በዚህም ምክንያት መለኮታዊ ፍርድና ፍትህ እንደ ሰማይ እርቀውናል፡፡ ጭራቆች ለሰላሳ ዓመታት ለፈጁትና በኮረቲ ለጠበሱት ብዙ ሚሊዮን ህፃን፣ አሮጊት፣ ወጣትና አዛውት፣ ሆዷን በስለት ለተሰነጠቀች ነፍሰ ጡር ጀርባ ሰጥተን ታርቀው ነገ ተመሳሳይ አረመኔአዊ ድርጊት የሚፈጥሙትን ጭራቆች ሳጥናኤላዊ ድርድር እርቅ ብለን ስንቧርቅና ስንጨፍር እርቅን ከመለኮታዊ ሚዛንና ፍትህ የማይነጥለው አምላክ ይከፋል፡፡ አምላክ ሲከፋ እንኳን እውነተኛ እርቅ አንጣራዊ ሰላምም እንደ ሰማይ ይርቃል፡፡
ፍትሐዊ እርቅ ብቀላን አስወግዶ በፍቅርና በሰላም ስለሚያስኖር ልንፈፅመው ይገባል፡፡ ፍትህን ያገለለ እርቅ ግን ገዳዩን አድኖ ተገዳዩን ደጋግሞ ስለሚገድል የህሊና እረፍትና ሰላምን ይነሳል፡፡ ስለዚህ ዛሬ በእኛ ባቅመ ቢሶች ባይሳካም አቅም ያለው ሲፈጠር ሰማእታት የዛሬ ሚሊዮን ዓመትም ቢሆን ፍትህ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ወንጀለኞች ከፍትህ ችሎት ለመቅረብ በሰው ደም እንደ ቅንቡርስ ያበጡት ሥጋዎቻቸው ቆመው መሄድ አይኖርባቸውም፡፡ ወንጀለኞች ከመቃብር ምስጥ እየበላቸውም ስማቸውና ሰይጣናዊ ግብሮቻቸው እየተዘረዘሩ ከፍትህ ችሎት መቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ ፍትህ ከፍትህ ችሎት ስትገኝ የፍትህ አባት መለኮትና ፍትህ ናፋቂ ሕዝብም ይደሰታል፡፡ መለኮትና ሕዝብ ሲደሰቱም ፍቅር እንደ አበባ ይፈካል፤ ሰላምም እንደ መንፈስ ይሰፍናል፡፡
ፍቅርን እንደ አበባ የሚያፈካና ሰላምን እንደ መንፈስ የሚያሰፍን እውነተኛ እርቅ ከመለኮታዊ የፍርድ ሚዛንና ከፍትህ ይመነጫል፡፡ ይኸንን ፈር ስተን በኢፍትሐዊ እርቅ ገደል እንደ ነፋስ ከነጎድን “እዘጭ እምቦጭ” ብቻ ሳይሆን እንደ ልማዳችን መንደባለልም ይቀጥላል፡፡ ልግመኛነታችንን፣ አቅመ ቢስነታችንን፣ ፍርሀታችንን፣ መሐል ሰፋሪነታችንን፣ አድርባይነታችንንና ከርሳምነታችንን ለመሸፋፈን የሰማእታትን አፅም በእርቅ እራፊ ጠቅልለን እንደ ማድ ቤት ቆሻሻ ለመጣል መንፈራገጡን ማቆም ይኖርብናል፡፡ ይኸንን መንፈራገጥ ካላቆምን እንደ ቆሻሻ የጣልነው የሰማእት ህይወትና ታሪክ በጥኑ ይወቅሰናል፡፡ በአሰመሳይ ሃይማኖተኛነት፣ በአጉል ሽምግልና፣ በስመ ምሁርነት፣ በእታይ እታይ የአገር አውራነት ወይም ከእውነት በሚያላትም ይሉኝታ ወገባችን አደግድገን የኢፍትሀዊ እርቅን ዘፈን በከበሮ ከደልቅን የሰማእታት ነፍስ በምድርም በሰማይም ይፋረደናል፡፡
እውነተኛ እምነት ከሥራ ውቂያኖስ እንደሚቀዳው እውነተኛ እርቅ ከፍትህ ባህር ይጨለፋል፡፡ ይህ ካልሆነ ያዕቆብ በመልክቱ “ሥራ የሌለው እምነት … የሞተ … (፪፡፲፯) እንዳለው ፍትህ የሌለው እርቅም አሁንም የሞተ ይሆናል፡፡
አመሰግናለሁ፡፡
መጀመርያ ታህሳስ ሁለት ሺ አስር ዓ.ም. እንደገና ህዳር ሁለት ሺ አስራ አምስት ዓ.ም.