ጀግና ተፈጠረ ወጣ አደገ ሲባል!
ስልጣንና ሆዱ ደፍቆት እርፉቅ ይላል፡፡
ቀንበር እምቢኝ የሚል ኮርማ ሆነ ሲባል፣
ተአህያ ፈስ ኮራጅ ጊደር ሆኖ ያርፋል፡፡
መቃብር ውስጥ ገብቶ ነገ ምስጥ ሊበላው፣
ሞልቶ እማይመርጉት ሆድ ስንቱን አስከነዳው!
ሆድ!
እስር የለህ ማፈኛ፣
ልጥጥ እንደ ፊኛ፣
ሌሊት አታስተኛ፣
ቀንም ቀበጠኛ፣
ስትጮህ ሞገደኛ፣
አመልህ ቀበኛ፣
ቀጪ የለህ ዳኛ፣
አይ ሆድ ወንጀለኛ!
ራስን ታስፎክት፣
አንገትን ታስቀትት፣
አይንንም ታስፈጥጥ፣
ማተብን ታስቆርጥ፡፡
አይ ሆድ አዋራጁ፣
ሁሌ እንደጎመጁ፣
በልተው አያፈጁ፣
ኖረው አያረጁ፣
ብለህ ታስጠራቸው
ሁል ጊዜ ያ ልጁ፣
ለትልተው ቢጃጁ፣
እንደ ኤፍሬም ይሳቅ
ጭራን ቢያወራጩ፡፡
እንደውሻ አስነካሽ፣
እንደ ጅብ አስቦዳሽ፣
እንደ ድመት አስላሽ፣
አንደ አሳማ አሳፋሽ፣
ስንቱን አንበረከክ
ሆድ የሚሉህ አሳች!
አይ ከርስ በጥራቄ፣
ለጭራ አያስበቄ፣
ቆብን አስወልቄ፣
ቀበቶ አስፈልቅቄ፡፡
እንደ አህያ ጫኙ፣
እንደ በሬ አፋኙ፣
እንደ ሙቅ አቅጣኙ፣
እንደ ሙት ከፋኙ፣
አይ ሆድ ብላሽ ከንቱ!
አይ ሆድ መተተኛ፣
ከእግር ሥር ታስተኛ፣
ታሳጥብ ክርነኛ፣
ታስም ጉልበተኛ፡፡
ከርስ ሰለክላካ!
እንደ ሊጥ ታስቦካ፣
ታዝቅ እንደ አሙካ፣
እንደ አተር ታስከካ፣
ታስርድ እንደ ቡርካ!
ጆሮን ያንሰራራህ፣
አይንን ያቅነዘነዝህ፣
ምላስን ያስተባህ፣
አፍንጫን ያሰፋህ፣
ህሊናንም ያሳትህ፤
አይ ሆድ ወንጀለኛ
ተነግሮ አያልቅ ግፍህ፣
ማነው የሚዳኝህ?
ማን ይሆን አለቃህ?
ዓለምን ወጥረህ፣
በካስማ ሰቅዘህ፣
በጭንቅ እያጣበብህ፣
እያመስካት ያለህ፤
አቅሙን ማን ዳረገህ?
ስልጣኑን ማን ሰጠህ?
ምን ቆሌ ብታመልክ፣
ምን ጋኔን ቢደቃህ፣
ስንቱን አስከድተህ፣
ይሁዳንም ያስናክ?
ለጓሚ ህሊና
ቀጭ ዳኛ የለህ፣
እውነትን ያስቀለህ፣
ዲናርን ሲያስዩህ፣
እግዚኦ ምመሀርነ!
ሆድ ስንቱን አስከዳ፡፡
በላይነህ አባተ
*ቁዘማ ከሚለው መጽሐፍ በማሻሻል የተወሰደ
ተጻፈ ታህሳስ ፲፱፻፺ ዓ.ም.