ከረጂም ዓመታት የኢትዮጵያ ምስቅልቅል ዘመናት ጀምሮ ያለፈዉን እና የነበረዉን በማዉገዝ እና በመደለዝ ፍሬ ቢስ የጥላቻ ስብከት አገሪቷን እና ህዝቧን ከድጡ አዲስ ጎጂ ሠሪ በማድረግ በተመሰቃቀለ የማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ወጥመድ ዉስጥ አስገብቷል፡፡
ከአራት ዓመት( ፬) ዓመት በፊት የነበረዉ ቀዳሚ ኢህአዴግ አገሪቷን እና ህዝቧን ከቀደሙት ስርዓቶች ጋር ፍርኃት እና የበታችነት ስሜት የወለደዉ ጥላቻ መንፈስ ለሰላሳ ዓመታት ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያዉያን እና የቀደሙት መንግስታት ወቃሽነት ተጠምዶ ስለነበር ኢህአዴግ በአገር እና ህዝብ ላይ ያደረሰዉ ወደር የለሽ ግፍ እና መድሎ ሊታየዉ አልቻለም ነበር ፡፡
አበዉ “ራስ ሲመለጥ ፤ ቃል ሲያመልጥ አይታወቅም ” እንዲሉ የነበረዉ የዓመታት ድርብርብ ብሄራዊ በደል በኢህአዴግ በጥላቻ የማናገር እንጂ በተጠያቂነት እና በኃላፊነት ህዝብን የመስማት ጠባይም ሆነ ልምድ ስላልነበረዉ በጥላቻ ተፀንሾ በጥላቻ ፈራርሶ ግን አሁንም በማንአለብኝነት ተኮፍሶ የሚገኝ ነዉ ፡፡
ይህም የሆነዉ ለዛሬዋ ኢትዮጵያ በመከራ አዉድማ ላይ መገኘት ችግሩም ሆነ መንስዔዉ ብቸኛዉ እና ዋነኛዉ ኢህአዴግ መሆኑ በተለያየ መንገድ በሽፍንፍን መታለፉ ነዉ፡፡
ዛሬ ላይ ኢህአዴግ ካለፉት ረጂም ዓመታት ከሰራዉ የአገር እና ህዝብ በደል አዲስ እና የተለየ ነገር የለም ፡፡ የሚለይ ነገር ቢኖር ቀደም ሲል በህዝብ እና ሠባዊ ክብር ላይ የሚደርሰዉ አድሎ እና መድሎ እንዲሁም በአገር ሉዓላዊነት ላይ የሚያሳስበዉ አደጋ በግለጭ እና በማን አህሎኝነት ከዉስጥ እና ዉጭ ጠላቶች ጋር የሚከወን መሆኑ ነዉ ፡፡
ዛሬ በኢትዮጵያዉያን ላይ በማንነት ላይ ያተኮረ የዘር ማጥፋት፣ ስደት ፣ ዕንግልት እና ዉርደት ፣ በኢትዮጵያ የግዛት አንድነት ላይ የሚደረግ ክህደት እና ቅርምት …. ላለፉት ፴ ዓመታት ከነበረዉ የሚለይበት ቢኖር ይህን ያህል በአገር እና በህዝብ ላይ የሠባዊ እና ብሄራዊ ጥፋት እና ክህደት የፈፀሙት በወንጀላቸዉ ሳይጠየቁ ዛሬም በድርጊታቸዉ እንዲገፉበት በራሱ በኢህአዴግ ፈቃድ ያገኙ መሆናቸዉ ነዉ ፡፡
ለዓመታት ኢትዮጵያዊነት ደመኛነት ፣ ኢትዮጵያዊ ማንነቶች ወንጀሎች ፣ የኢትዮጵያን ግዛት እና የባህር በር ኣሳልፎ ለጠላት መስጠት እና ህዝብን ጋት በማይሞላ መሬት ማጋደል ፣ ኢትዮጵያዊነት ባይተዋርነት …..በማድረግ ኢትዮጵያ በታሪክ ገጥሟት የማይታወቅ የዜጎች ሞት እና መፈናቀል፣ የመልካም አስተዳደር ዕጦት ፣ድህነት የመሳሰሉት የተከሰቱት በኢህአዴግ የአመራር ድክመት እንጂ በኢትዮጵያዉያን ኃጢያት አለመሆኑ ይታወቃል ፡፡
ሆኖም ኢህአዴግ ራሱ የዚህች አገር ችግር እና የችግር ምንጭ መሆኑን የሚነግረዉም ሆነ የሚነገረዉን አስቀድሞ በጠላትነት ፍረጃ ባለዉ ፍርኃት ወለድ ጥላቻ ከኔ በላይ ላሳር በሚል ልክፍት ዛሬም በዚህች አገር እና ህዝብ ላይ ለሚደርሰዉ የመከራ በረዶ ችግር እና ምንጭ ወደ ኋላ እና ወደ ዉጭ ይልጥፋል ፡፡
የምንም ነገር በሽታ እና መንስዔ የሚነሳዉ ከዉስጥ እንጂ ከዉጭ ሆኖ አያዉቅም ፡፡ በከብቶች በረት የሚገኙ ዕንስሶች ጥቃት የሚጀምረዉ ከዉስጣቸዉ በሚከሰት የአብሮነት ትስስር ሲሰረሰር ብቻ ነዉ ፡፡ ለዚህ ነዉ አህአዴግ ትናንት ኢትዮጵያን በደም እና በአጥንት መስርተዉ እና ጠብቀዉ ያቆዩትን ኢትዮጵያን ሲኮንን ጨልሞበት ዛሬ “ሌባሲሰርቅ ይስማማል ሲከፋፈል ይጣላል ” እንዲሉ አባት እና ልጂ የሚያስጨንቃቸዉ የዚህች አገር የግዛት አንድነት እና የህዝቦች ሉዓላዊነት ሳይሆን የስልጣን እና የጥቅም ግጭት መሆኑን በማዳፈን ረመጡ በሚያቃጥላት አገር በጭለማ ዉስጥ ሆነዉ በህዝብ እና አገር መስዋዕትነት የራሳቸዉን ብርኃን ይናፍቃሉ ፡፡
ለሁላችንም እንደ ህዝብ አገር በጋራ ጎጆነቷ እንድትቀጥል ይህችን አገር ለዘመናት በጥፋት ቋያ ረመጥ ዉስጥ እንድትነድ ምክነያት የሆነዉ ኢህአዴግ በአገር እና በህዝብ ላይ ላደረሰዉ መጠነ ሰፊ ጥቃት እና ክህደት ይቅርታ እንዲጠይቅ ፣ በጥፋቱም እንዲጠየቅ እስካልሆነ ጊዜ ድረስ ችግርን ወደ ሌላ መግፋት እና ዕዉነትን በማክፋፋት ማለባበስ እና መድበስበስ ለተዉልድ እና ለአገር ፋይዳ ሳይሆን ባልበላዉ እና ባልኖረበት ከፋይ እንዲሆን ዕዳ ማስተላለፍ ነዉ ፡፡
የአገራችንን ጥንታዊ ብሂል“ ነገርን ከስሩ ፤ ዉኃን ከምንጩ ” መሆኑን ተገንዝበን እንደ አገር ችግራችንን ፣ ምንጩን እና መድኃኒቱን ከእኛ በላይ ሠማይ ብቻ መሆኑን በመረዳት እና በመረዳዳት መርህ ካለፈዉ ተምረን ፤ዛሬ ተባብረን ፤ በዓላማ እና በግልፅ መኖርን የኢትዮጵያዊነትን ህማም መከተል ይኖርብናል ፡፡ እንደ አገር ለዘመናት ከተጣባን ፈርጀ ብዙ ችግር እና መከራ የምንፋታዉ ችግሩን ከመነስዔዉ በመንቀስ ፣መዉቀስ እና መደምሰስ እንጂ ወደሌላ በመግፋት እና በማጥላላት ማለፍ ብሶት እንጂ ትሩፋት አያስገኝም ፡፡
“የአገር አንድነት፣ሉዓላዊነት እና ነጻነት ያለህዝባዊ ተሳትፎ ህልም ነዉ ፡፡”
“አንድነት ኃይል ነዉ” !!!
NEILLOSS Amber