የዐማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በየትኛውም ዘመን፤ በማንኛውም የዓለማችን ሀገራት ሕዝቦች እና ማንኛውም አይነት የብሔር፣ ሃይማኖትም ሆነ የቆዳ ቀለም ባለው ሰብአዊ ፍጡር ላይ የተፈጸሙ በማንኛውም ደረጃ የሚገለጹ ሁሉንም አይነት የመብት ጥሰቶችን ይቃወማል፡፡
ማንኛውም አይነት የተቃርኖ ምክንያቶችን ተገን በማድረግ በሰው ልጅ ላይ የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን፤ የዘር ማጥፋትም ሆነ የጦር ወንጀሎችንም ያወግዛል፡፡ ይህን መሰል እኩይ ድርጊቶችን ለመከላከልም ሆነ ጥፋተኞችን ለሕግ ለማቅረብ የሚደረጉ ምርመራዎችን ያደንቃል፤ ያበረታታልም፡፡
የክልሉ መንግሥት ለሰብአዊ መብቶች መከበር ያለው ውግንና የሚመነጨው ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሰብአዊ መብቶችን ለማስጠበቅ ላጸደቃቸው ሕጋዊ ድንጋጌዎች ተፈጻሚነት ባለን ቀናዒነት ብቻ ሳይሆን የዐማራ ሕዝብ ቀደምት ሁለንተናዊ የሥልጣኔ ትሩፋቶቹን ተመርኩዞ ማኅበረሰባዊ ሰብእናውን የቀረጸባቸው የባህል፣ የሞራል፣ የእሴቶቹ እና የመለኮታዊ አስተምህሮቶቹ ስለማይፈቅዱለትም ጭምር ነው፡፡ ለሰብአዊ መብቶች መከበር ሲባል የጸደቁና ሀገራችን የተቀበለቻቸው የሕግ ማዕቀፎችና ድንጋጌዎች ሁሉ በክልሉ ውስጥም ሆነ ከክልሉ ውጭ ባልተሸራረፈ መልኩ ተፈጻሚነታቸው እንዲረጋገጥ ያላሰለሰ ጥረት እያደረግን የምንገኝበት ዐቢይ ምክንያትም ይኸው ነው፡፡
ይሁን እንጂ ‹ሰብዓዊ መብቶችን ለማስከበር ጥብቅና ቆመናል› የሚሉ አንዳንድ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ አሸባሪ እና ወራሪው የህወሓት ቡድን የዐማራ ህዝብን ሕልውና ለማክሰምና የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለመናድ አልሞ የከፈተውን ጦርነት ተከትሎ የተከሰተው ቀውስ ላይ ተመስርተው የዐማራ ክልል መንግሥትን እና ሕዝብን ‹‹የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፤ የዘር ማጥፋትና የጦር ወንጀሎችን›› ፈጽመዋል የሚሉ ገለልተኛነት፤ ሚዛናዊነት እና ተዓማኒነት በሌላቸው ሪፖርቶች ላይ የተመሰረቱ፤ በጦርነቱ የተፈጠሩ ሰብአዊ ቀውሶችን ለማከምም ሆነ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ለመከላከል አጎልባችና አዎናታዊ ሚና የሌላቸው ሐሰተኛ ክሶችን በተደጋጋሚ ሲያሰሙ ተስተውለዋል፡፡
እነዚሁ አካላት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ኤፕሪል 6/2022 በሂዩማን ራይትስ ዎች እና በአምነስቲ ኢንተርናሽናል ጥምረት የተዘጋጀውና በሰብዓዊ መብት ላይ የሚፈፀሙ ከባድ ጥሰቶችን በማስታከክ ‹‹የጦር ወንጀል›› እና ‹‹የዘር ማጽዳት›› ክሶችን ሽፋን አድርጎ በዋነኛነት በዐማራ ክልል የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ላይ የሚያጠነጥን ሪፖርት ይፋ ማድረጋቸውን የዐማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ታዝቧል፡፡
ሪፖርቱ የዐማራ ክልል የመንግሥት ኃላፊዎችን፣ የልዩ ኃይል ፖሊስ አባላትን፣ ሚሊሻዎችን እና በሕግ ማስከበርና የህልውና ዘመቻ ላይ የተሳተፉ የፋኖ አደረጃጀትን ‹‹በንብረት ዝርፊያ››፤‹‹በአፈናቃይነት››፤ ‹‹በአስገድዶ መድፈርና የወሲብ ባርነት ፈጻሚነት››፤ ‹‹በጾታዊ ጥቃት››፤ ‹‹በዘር ማጥፋት››፤ ‹‹በጦር ወንጀልና እና በከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰት›› ፈጻሚነት ይወነጅላል፡፡
መሬት ላይ ያለውን ሐቅ ለሚያውቁ ገለልተኛ አካላት፤ ለክልላችን ሕዝብም ሆነ ለመላው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የሪፖርቱ ፋይዳ ከሦስት ግቦች አይዘልም፡፡
አንደኛ፡- የሕዝባችንን ጩኸት ለመቀማትና የሀገራቸውን ሉዓላዊነትና ህልውናቸውን ለማስከበር ብሔራዊ ግዴታቸውን በተወጡት የመንግሥት ኃላፊዎች፣ የጸጥታ መዋቅር አባላትና በሐቀኛ ፋኖዎች መካከል ያለውን ጠንካራ ትስስር በመስበር ወደፊትም በሉአላዊነታችን ላይ የሚጋረጥ አደጋ ቢመጣ በአንድነት መታገል የማይችል አቅመ ቢስ ኅብረት እንዲኖር የማድረግን ዓላማ ያነገበ ነው።
ሁለተኛ፡- በአሸባሪና ወራሪው የህወሓት ቡድን ከላይ የተዘረዘሩት ሁሉም አይነት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፤ የዘር ማጥፋትና የጦር ወንጀል ሰለባ በሆነው የዐማራ ሕዝብ ቁስል ላይ እንጨት በመስደድ የዐማራ ሕዝብን እንደ ሕዝብ ፍትህ በመንፈግ በኢትዮጵያዊነቱ እና በዓለም አቀፍ የፍትህ፤ የሰብአዊ መብት ተከራካሪና የዴሞክራሲ እሴት ግንባታ ባለድርሻ አካላት ላይ ተስፋ ቆርጦ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ እና የሕዝብና የግዛት አንድነትን ለማስከበር ያለውን ቁርጠኝነት በማሟሟት በብሔራዊ የእርቅና የምክክር መድረኮች ሰላምን ለማስፈንና ወንድማማችነትንና እህትማማችነትን ለመገንባት የሚኖረውን ሚና ለማምከን ታስቦ የተዘጋጀ ደባ ነው።
ሦስተኛ፡- የማዕከላዊውም ሆነ የክልላችን መንግሥት ወታደራዊ ግጭትን በማቆም ለሰላምና ለሰብአዊ ድጋፎች ተደራሽነት በሙሉ አቅሙ እየተጋ በሚገኝበት ወቅት ይህ ሚዛናዊነት፤ገለልተኛነት እና ተዓማኒነት የሌለው ሪፖርት ይፋ መደረጉ መንግሥት በአፍሪካ ህብረት የህዝቦች መብት ጥበቃ ኮሚሽን (ACHPR)፣ በተባበሩት መንግሥታት ጽህፈት ቤት የሰብአዊ መብትቶች ጥበቃ ከፍተኛ ኮሚሽን (OHCHR) እና በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (EHRC) የጋራ ጥምረት የተከናወኑ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ምርመራ ጥረቶችን ዋጋ የሚያሳጡና በሰብአዊ መብቶች ጠበቃነት ካባ ተሸፍኖ በሰብአዊነት ላይ በገሀድ የተፈጸመ ኢ-ሞራላዊ ጥቃት ሆኖ እንዲታይ ያደርገዋል፡፡
በተለይም ሪፖርቱን ያዘጋጁት ተቋማት ከተመሰረቱበት ዓላማ ባፈነገጠ ሁኔታ በሪፖርታቸው ላይ የሀገር ውስጣዊ የፖለቲካ ለውጦችን የማስተጓጎል፣ በክልሎች መካከል የሚገኙ የወሰን ጉዳዮች ላይ ብያኔ የመስጠት እንዲሁም በአንድ ሉዓላዊ ሀገር የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ገብቶ ሕዝብን ከሕዝብ የማጋጨት ጥረቶች መስተዋሉ አሸባሪው የህወሃት ቡድን ጦርነቱን በከፈተበት የመጀመሪያዎቹ ወራት ላይ አንዳንድ ኃያላን ሀገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ሲሰነዝሩት የነበረውን ለአንድ ወገን ያደላ ሀሳብ በሪፖርታቸው ላይ አጭቀው ማቅረባቸው የክልላችን መንግሥት በሪፖርቱ ላይ ብቻ ሳይሆን ሪፖርቱን ባዘጋጁት ተቋማት ላይም ጭምር በገላልተኛነታቸው፣ በሚዛናዊነታቸውና በተዓማኒነታቸው ላይም ጭምር ጥርጣሬ እንዲኖረው አድርጓል፡፡
የተቋማቱ ዋና መቀመጫ መሥሪያ ቤት በእንግሊዝ ለንደን እና በአሜሪካ ኒውዮርክ የሆነውና በሱዳን ምድር ሆነን 427 ተጠቂዎችን በአካልና በስልክ ቃለ መጠይቅ በማድረግ ሪፖርቱን አዘጋጅተነዋል ያሉት የድርጅቶቹ ባለሙያዎች በስልክ ቃለ መጠይቅ አደረግንላቸው ያሏቸው አንዳንዶቹ ‹‹የዘር ማጥፋት ወንጀል ሰለባ ናቸው›› የተባሉ የህብረተሰብ ክፍሎች በዐማራ ክልል ውስጥ የሚኖሩ በመሆናቸው በስልክ ለማግኘት መቻላቸውን መግለጻቸው እርስ በእርሱ ይጣረሳል፡፡
ሱዳን ከሚገኙ ስደተኞች ሰበሰብነው ያሉት መረጃም ቢሆን የጥቅምት 30/2013 ዓ.ም. የማይካድራ ጭፍጨፋን ከትግራይ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ጋር ሆኖ ከመራውና ‹ሳምሪ› ከተሰኘው ኢ-መደበኛ አደረጃጀት ላይ እንደሆነ እናምናለን፡፡
ከዓለማቀፍ ሕግ በሚቃረን መልኩ በሱዳን የስደተኛ ካምፖች ውስጥ አሸባሪው ህወሃት ንጹሃን የዐማራ ተወላጆችን ለመጨፍጨፍ የተጠቀመባቸው የትግራይ ልዩ ኃይል፣ የሚሊሻና የኢ-መደበኛ አደረጃጀት አባላት በስደተኛ ስም እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡ በሱዳን በኩል ስደተኛ ካምፕ ያሉትን እነዚህን ኃይሎች የሽብር ስልጠና በመስጠት በዐማራ ክልል በቋራ እና በቤንሻንጉል ጉሙዝ በኩል በንጹሃን፣ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እና በመሰረተ ልማት ላይ ጥቃት እንዲከፍቱ ስምሪት ሲሰጥ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ የስደተኞች ካፕም ውስጥ ገብተው መታወቂያ (Refugee ID Card)
የተሰጣቸው ነገር ግን አሸባሪው ህወሓት ለጥፋት ተልዕኮ ወደ ኢትዮጵያ አስርጎ አስገብቷቸው በውጊያ የተማረኩ ምርኮኞች እንዳሉም ይታወቃል፡፡
በተጨማሪም “በአፈናቃይነት” የተወነጀለው የዐማራ ክልል መንግሥት በሚያስተዳድረው ክልል ውስጥ በርካታ የትግራይ ክልል ተወላጆች በንግድ ሥራ፣ በመንግሥት ሠራተኝነት፣… ወዘተ በተጨባጭ የሚኖሩ መሆኑን ዘንግቷል፤ አልያም ክዷል፡፡ ዛሬም ‹ሥርዓት ይመጣል፣ ይሄዳል፣… ይቀያየራል የሕዝብ ግንኙነት ግን ቋሚና ዘላቂ ነው› በሚል እምነት ከዐማራ ወንድሞቻቸው ጋር በሰላምና በፍቅር የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች በክልላችን ውስጥ መኖራቸው የዐማራ ሕዝብን አቃፊነት የሚያሳይ በመሆኑ የክልሉን መንግሥት ያኮራዋል፡፡
እውነታው ይህ ሆኖ እያለ በሪፖርቱ ላይ የቀረበው ክስና ውንጀላ የተቋማቱን ፖለቲካዊ ወገንተኝነት የሚያሳብቅ ነው፡፡ ሌላኛው አሳዛኝ ሁነት ጥናቱን ለማከናወን በመረጃ ምንጭነት የተጠቀማቸው ግለሰቦች የአንዱን ማኅበረሰብ ወገን ብቻ መሆኑ ሪፖርቱ በመረጃ አሰባሰብ ሥነ-ዘዴው ደካማ መሆኑን ከማረጋገጡ ባሻገር በውጤቱም ሚዛናዊነት የጎደለው፣ ለአንድ ወገን ያደላ እና ተዓማኒነት የሌለው እንዲሆን አድርጎታል፡፡
በዚህም ምክንያት ተቋማቱ አንድ ዓመት እንደፈጀባቸው የገለጹት የጥናት ውጤት ለሰብዓዊ መብቶች መከበር አዎንታዊ ሚና ከመጫወት ይልቅ ችግሮችን የበለጠ የሚያወሳስቡ፣ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን የሚደረጉ ጥረቶችን የሚያጨናግፉ፣ በተፈጠሩ ግጭቶች ምክንያት በቀጥተኛም ሆነ በተዘዋዋሪ መልኩ ሰለባ የሆኑ ዜጎች ፍትህና ርትዕን ለማረጋገጥ የሚቻልባቸውን ዕድሎች የሚያጠቡ ሆነው አግኝተናቸዋል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የጥናት ቡድን ለአስራ ስድስት ወራት ባደረገው ጥናት መሰረት በወልቃይት ጠገዴ በርካታ የጅምላ መቃብሮችን አግንቷል፡፡ “ገሃነም” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኙ በርካታ የህወሓት የጉድጓድና የዋሻ ድብቅ እስር ቤቶች ላይ ጥናት ያደረገው ዩኒቨርሲቲው በአካባቢው የአገር ሽማግሌዎችና የዓይን እማኞች በኩል ከተጠቆሙት የጅምላ መቃብሮች መካከል ለሙከራ አምስቱን አስቆፍሮ ጭካኔ በተሞላበት ግፍ የተረሸኑ ንጹሃንን አፅም አስወጥቷል።
በዚህ አሰቃቂ እስር ቤት የታሰሩ ንጹሃን በሚደርስባቸው ሰቆቃ ምክንያት ራሳቸውን ማጥፋታቸውን፣ የህወሃት ታጣቂዎች በየቀኑ ታሳሪዎችን እየወሰዱ ይገድሉ እንደነበርና የብዙዎቹ አስከሬን በአካባቢው የሚገኝ ቃሌማ ወንዝ ላይ ይጣል እንደነበር ከሞት የተረፉት አዛውንቶች ለጥናት ቡድኑ ቃላቸውን ሰጥተዋል። እልፍ የዐማራ ተወላጆች ባለቁበት በዚህ ‹የኢትዮጵያው ኦሽዊዝ› ሦስት አሰርታትን ለሚሻገሩ ዓመታት ዓለም ያላስተዋለው የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈፅሟል፡፡
የድብቅ እስር ቤቱ ውስጥ በበሽታና በርሃብ፣ በድብደባ ተሰቃይተው እንዲሁም በህወሓት ታጣቂዎች ለሚገደሉት እስረኞች ቀብር ይቆፍሩ የነበሩት እስረኞች እንደነበሩም በጥናቱ መሰረት ለማወቅ ተችሏል። ከዚህ ጥናት ባሻገር ዓለም የሚያውቀውና ድርጊቱን በሚገባው ልክ ባይሆንም ያወገዘው ጥቅምት 30/2013 በማይካድራ ከተማ በዐማራ ተወላጆች ላይ የደረሰው ዘርን መሰረት ያደረገ ጭፍጨፋ በህወሓት መሪነት የተፈፀመ ነበር፡፡ ጭፍጨፋው በትግራይ ልዩ ኃይልና ሚሊሻዎች እንዲሁም የሩዋንዳ ኢንተር ሃሞይ (Interahamw) ሞዴል የሆነው የሳምረ ኢ-መደበኛ ኃይል (Tigrians paramilitary Force) በህወሓት መሪነት መፈፀሙ፣ በጭፍጨፋውም ከ1600 በላይ የዐማራ ተወላጆች መሞታቸው አይዘነጋም፡፡
በጥቅሉ ባለፉት ሠላሳ ዓመታት በህወሓት መሪነት በአካባቢው የተፈፀሙ ዓለማቀፍ ወንጀሎች፣ በዓለማቀፍ መመዘኛዎች ደረጃ ስንመለከተው በወልቃይት ጠገዴ የዐማራ ሕዝብ ላይ ዓለም ያልሰማው የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈጽሞበታል፡፡ ለዚህም ወንጀል ፈጻሚ የህወሓት አመራሮች በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ቀርበው ሊጠየቁ ይገባል።
የዓለማቀፉ ማኀበረሰብ እና ተቋማት በእነዚህ አካባቢዎች ቅድመ እና ድኀረ ነጻነት ያለውን ሁኔታ የሚያዩበትን መንገድ በተለይም የመረጃ ምንጮቻቸውን ሊፈትሹ ይገባል፡፡ አምነስቲ ኢንተርናሽናልና ሂውማንት ራይትስ ዎች በተደጋጋሚ ሪፖርቶቻቸው ሰብአዊነትን ሳይሆን ፖለቲካዊ ወገንተኝነታቸውን አሳይተዋል፡፡ ይህ የፖለቲካ ወገንተኝነታቸው የሰብዓዊ መብት ጠለፋ (hijacking human rights) በሚል የሚያስተቻቸው ከመሆኑም በላይ በአንዲት ሉዓላዊት ሀገር የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጀን ድርጅት (የህወሓትን) የፖለቲካ አቋም በሚጋራና የወልቃይት ጠገዴ የዐማራ ሕዝብን የዘመናት በደል በሚክድ ሁኔታ በሪፖርታቸው ወገንተኛ ሆነው መገኘታቸው የቆሙለትን ዓላማ እንደካዱ ይቆጠራል፡፡ ይህን አሳዛኝ ሁነት የሚያከፋው ደግሞ በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኢምባሲ በይፋዊ ገጹ ሪፖርቱን መጋራቱና የተጠያቂነት ጣቱን ተበዳይ ወደሆነው የዐማራ ክልላዊ መንግሥት ማዞሩ እጅግ አሳዝኖናል፡፡
ተለዋዋጭ ፖለቲካ አይነተኛ ባህሪው በሆነው የምስራቅ አፍሪካ ፖለቲካ ውስጥ ‹ዓለማቀፍ ድንበሮች አይገድቡኝም› በሚል ጎረቤት ሀገራትን ጭምር ለማተራመስ የሚሰራውን አሸባሪውን ሕወሓት የሚደግፍ የትኛውም ዓይነት አቋም መያዝ እንደ ክልልም ሆነ እንደ ሀገር የተያዘውን የሰላምና መረጋጋት ጉዞ የሚያደናቅፍ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ ኤምባሲው በክልላችንም ሆነ በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ የሚያይበትን መንገድ በተለይም የመረጃ ምንጮቹን ደግሞ ደጋግሞ እንዲፈትሽ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
ዓለማቀፉ ማኀበረሰብ የዐማራን ሕዝብ በተመለከተ ሊረዳው የሚገባ እውነት የዐማራ ሕዝብ ከመላ የኢትዮጵያ ብሔር ብሄረሰቦች ጋር እኩልነትን መርሁ አድርጎ በወንድማማችነት ስሜት፣ በሠላምና በፍቅር ከመኖር ውጭ የተለየ ፍላጎት የለውም፡፡
በጥቅሉ በነዚህ እና የዐማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት እየመረመራቸው በሚገኙ ሌሎች የሪፖርቱ አካል የሆኑና ለክልሉ ሕዝብ ሰላም መስፈንም ሆነ የሰብአዊ መብቶች መከበር የማይበጁ ስሁት ሀሳብና ብያኔዎች ምክንያት በሂዩማን ራይትስ ዎች እና በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የተዘጋጀውን የጋራ ሪፖርትን አንቀበለውም፡፡
የዐማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት
ሚያዚያ 02/2014 ዓ.ም.
ባህር ዳር-ኢትዮጵያ