“ሃገራዊ የምክክር መድረክ ግጭቶችን የመፍቻ ታላቅ ቁልፍ መሳሪያ ነው “ “National Dialogues: A Tool for Conflict Transformation” የተባበሩት መንግስታት /UN/ ኢትዮጵያ ሃገራችን ታሪካዊና በህላዊ የሆኑ የግጭት የመፍቻ ቁልፍ መቸቶች ባለቤት ናት። ከነዚህም መካከል አውጫጭኝ ፣ አፍርሳታ፣ ጉማ፣ የቤተሰብ ጉባኤ፣ የሽማግሌዎች ጉባኤ ወ.ዘ.ተ.። እነዚህን ዕምቅ አገራዊ የምክክር ተሞክሮዎችን ከዘመናዊው ሃገራዊ መድረክ ፅንሰ ሃሳቦች ጋር አጣምሮ መስራቱ ለውጤታማነት አስፈላጊ ነው ተብሎ ይታሰባል።
ሃገራዊ የምክክር መድረክ የሚከወነው በሥልጣን ላይ ያለው መንግስትና ተቋማት ችግሮችን፣ ግጭቶችን የመፍታት አቅም ሲሳናቸው ፣ በሕዝብ ያላቸው ተቀባይነት እያሽቆለቆል ሲሄድና ተቀባይነት እያጡ ሲመጡ ነው። ከዚህ ባሻገር ከዚህ በፊት ለረጅም ጊዜ የነበሩ ታሪካዊ፣ ሃገራዊ ኩነቶችን ሂደቶች ፣ ሰላምን፣እንድነትን እንደነበሩ መልሶ ማስጠበቅ ሲሳናቸው እንደሆነ ፅንሰ ሃሳቡ ይተነትናል። ሃገራዊ ምክክር ግጭቶችን የመፍቻና የፓለቲካ እንቅስቃሴዎች ወደ ተሻለ እምርታ እንዲያመሩ የሚያሳልጥ ቁልፍ ማሳሪያ ከሆነ ረጅም ጊዜ ያስቆጠረና ብዛት ያላቸው ሃገሮች ጠቀሞታ ላይ አውለውታል።
ሃገራዊ ምክክር ከፓለቲከኞች እሰጥ አገባና የምሁራን የለውጥ ውሳኔ ሃሳቦች ለየት ባለ መልኩ ውይይቶች ሰፋ ብለው ወደ መድረክ እንዲቀርቡ የሚያስችል ታላቅ ድጋፍ ያገኘ መርሆና መንገድ ቢሆንም መሪዎች ለስልጣናቸው ማረጋጊያና ማስቀጠያነት ሊጠቀሙበት ይችሉ ዘንድ አጋጣሚ የሚፈጥር ከመሆኑ ባሻገር ፓለቲከኞችና መሪዎች በሚፈልጉት መልኩ ሊያሾሩትና ሊዘውሩት የሚችሉበት ስልታዊ አካሄድ ሊፈጠር እንደደሚችል ተሞክሮዎች ያሳያሉ ።
ከዚህ ባሻገር መንግስት የህዝብን ትኩሳት፣ ተቃውሞና እምቢ ባይነት ለማብረድ ሊጠቀምበት እንደሚችል የሃገራት ተሞክሮ ያሳያል ። አስመሳይ ፓለቲከኞችና አደርባይ ምሁራን ሕዝብን በማምታትና በማባበል በሥልጣን እንዲቀጥሉና ጥቅማቸው እንዲራዘም ይህን ታላቅ የሃገራዊ ምክክር መርሆ እንደመሳሪያ ሊጠቀሙበት ይችላሉ ተብሎ ይታሰባል።
ይህን ካልን ዘንዳ አገራዊ የምክክር መድረክን በአመሪቂ ሁኔታ ለመተግበርና ለማሳለጥ አንድ ወጥ የሆኑ ስልታዊ መንገዶች ፣ ደንቦችና ሙሪያዎችን ለማስቀመጥ አዳጋች ቢሆንም የሚከተሉትን መርሆዎች ተከትሎ ሃገራዊ ምክክርን መከወን ስኬታማና በውጤት የታጀበ እንዲሆን ያደርገዋል። እነሱም :
- አካታችነት /inclusion/
ሃገራዊ የምክክር መድረክ የተዋጣለት እንዲሆን በተነሳው አጀንዳ የመለከታቸዋል የሚባሉ አካላት ወይም ቡድኖች በሙሉ ተሳታፊ መሆን ይኖርባቸዋል። ሃገራዊ ምክክሩን ሰፋ ለማድርግና ትክክለኛነቱንና ተቀባይነቱን ለማስረገጥ የግጭቶች ገፈት ቀማሽ የሆኑት የተለያዮ ፍላጎቱ ያላቸው ማህበረሰቦች ማለትም የሃይማኖት አባቶች፣ ሴቶች፣ወጣቶችና በባህላዊ ተፅህኖ ተግለዋል ተብለው የሚታሰቡ ቡድኖች ሁሉ ይታደሙ ዘንድ ጥረት ማድረጉ የግድ ይላል።
- ግልፅነትtransparency /
ሃገራዊ ምክክር ከመጀመሩ በፉት አካታችና ግልፅ የሆነ፣ በባለሙያ አማካሪወች የተደገፈ አካሄድ እንዲኖረው ጥረት ከማድረግ ባሻገር ሂደቱ ደረጃ በደረጃ ከተከናወነ ሃቀኛና ቅቡልነትን የተላበሰ አካሄድ አለው ተብሎ ይታሰባል።
- የሕዝብ ተሳትፎ/publicparticipation/
ሃገራዊ ምክክር ከመጀመሩ በፊት እነማን ይሳተፉ፣ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ የማህበረሰቡ ክፍሎች /Civic Associations/ , የፓርቲ አባላት፣ የህዝብ ተመራጮች ወ.ዘ.ተ. ተመርጠው ሊካተቱ ይገባል። በተቻለ መጠን መላ ህብረተሰቡን ማሳተፍ ይቻል ዘንድ ስልቶች ሊቀየሱ የግድ ይላል። የማህበረሰቡን ተሳትፎ ተግባራዊ ለማድረግ የክልል ውይይቶችን ከዋናው ሃገራዊው ምክክር መድረክ ጋር በማቀናጀትና በማጣመር የክልል ማህበረሰቦችን በማማከር፣ ቀርቦ በማነጋገርና በመገናኛ ብዙሃን የ የእለት ተእለት ውይይቱን በሃገር አቀፍ ደረጃ በማስተላለፍ አመርቂ ስራ መስራት ይቻላል። በአንድ አንድ ሃገሮች እንደታየው ውጭ ሃገር ነዋሪ የሆኑትን ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን ማሳተፉ ሃገራዊ ምክክሩን የተዋጣለት ያደርገዋል ተብሎ ይታሰባል።
- ትኩረት የሚሹና ሊጨበጡ የሚችሉ አጀንዳዎችa /far-reaching agendas/
በሃገራዊ ምክክር መድረክ እንደ አጀንዳ ተይዘው ሕዝብ ሊወያዮባቸው ይችላሉ ከተባሉ ጉዳዩች መካከል የሚከተሉትን ማንሳት ይችላል። ለምክክርና ለሽምግልና ቀርበው በሃገር ደረጃ መግባባት ያልተደረሰባቸው ጉዳዮች፣ ለዘመናት እየተከባለሉ የመጡ ችግሮችና ሰንኮች፣ መንግስት በሃይማኖት ላይ ሊኖረው ስለሚገባው ግንኙነቶች ፣ ፓለቲካዊ መብትና ነፃነት፣ የተቋማት የለውጥ አስፈላጊነት፣ ሰለምርጫ አካሄድ፣ ስለ መንግስት አወቃቀር፣ ሰለፌደራል መንግስታት አወቃቀር ወ.ዘ.ተ. ባሉ አጀንዳወች ላይ ሃገራዊ የውይይት መድረክ ማካሄድ ይቻላል። ነገር ግን የህዝብ ሮሮንና ብሶት በተመለከተ መንግስት እራሱን ካሻ ሻለ ወይም ከጠቀየር ይፋታሉ ተብሎ ስለሚታሰብ በሃገራዊ ምክክር እንደመወያያ አጀንዳ ይዞ መወያየቱ አላስፈላጊ እንዳልሆነ ተሞክሮዎች ያመለክታሉ ።
- በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነትና ቅቡልነት ያላቸው መማክርታን ስለመሾም፣ /a credible convener/
የሃገራዊ መማክርት ጉባኤ አባላት ግለሰቦች ፣ የህዝብ ስብስብ ና ድርጅቶች ሊሆኑ ይችላሉ። በሃገር አቀፍ ደረጃ ቅቡልነት ያላቸውና አክብሮት የተቸራቸው የመማክርት ጉባሄው አባላት መኖራቸው በጣም አስፈላጊና ትኩረት ሊሰጥበት ይገባል። የፓለቲካ ግብ የሌላቸው፣ ከፓለቲካ ወገንተኝነት የፀድ ፣ የራቁና በሂደቱ የጎንዮሽ ተጠቃሚ ያልሆኑ / Conflict of interest/ የሌላቸው ሊሆኑ ይገባል።
- ግልፅና አግባብነት ያላቸው ደንቦች፣ መመሪያዎችና የምክክር ውጤቶችን ወደ ተግባር ማስቀየር የሚያስችሉ ዕቅዶች ማካተት /Agreed mechanism for implementation of outcomes.
ሃገራዊ ምክክር መድረኩን በውጤት እንዲከናወን መተዳደሪያ ደንቦችና መርሆች በአንክሮ ታስቦበት የአማካሪ ፣ የባለሙያዎች ጥናቶች ተከውኖ ቢካሄድ ሃገራዊ ምክክሩን ዘላቂ ፣ አመርቂ ፣ ተቀባይነትና ውጤታማም ሊሆን ያስችለዋል ተብሎ ይታሰባል። መተዳደሪያ ደንብና አካሄዶች ለውሳኔ አሰጣጥ ትልቅ ግብአት ስለሚሆኑ ግልፅና በጥንቃቄ መንደፍ አለባቸው።
የምክክር መድረኩ ያለ ጋራ ስምምነት ቢቋጭ እንኳ የችግሩን መፍቻ አንጥሮ ፣ በሕግና የሚልመለከታቸው የበላይ አካላት ውሳኔ እንዲሰጡበት ያስችል ዘንድ መንገዶችን፣ ጠቋሚ ሃሳቦችን ሊያስቀምጥ በሚያስችል መልኩ ሊነደፉ የግድ ይሏል።
አገራዊው የምክክር መድረኩ የደረሰበትን የውሳኔ ሃሳቦች ተግባራዊና ተፈፃሚ ይሆኑ ዘንድ በሕገ-መንግስት፣ በሕግና በፓሊሲ ደረጃ ሰፍረው እንዲወጡና ይካተቱ ዘንድ መንገዶችና አካሄዶች ወጥና ተቀባይነት ያላቸው ሆነው መቀመጥ ይኖርባቸዋል። በዚህ መልክ ካልተካሄደ ውጤት አልባ ፣ ለብዙ ወጭ የሚዳርግ ጊዜም የሚያባክን ይሆናል።
- የአለም አቀፍ ድርጅቶች ተሳትፎን በተመለከተ
አለም አቀፍ ድርጅቶች አስፈላጊ የሆኑ የገንዘብ ድጋፎች፣ ሃገራዊ ምክክሩ አካታች፣ አሳታፊና ወጥ በሆነ መልኩ እንዲከወን መግለጫዎችን፣ ማበረታቻወን ማድረግ ይችላሉ። ምክክሩ ከመጀመሩ በፊት ልምዳቸውን ቢያካፍሉ አይከፋም። ቢሆንም ለምክክር ከቀረቡት ቡድኖች ከአንዱ ወይም ከሌላኛው ጋር እንዲወግኑ ቦታና መድረክ ሊሰጣቸው አያስፈልግም። ስለዚህ ሃገራዊ የምክክር መድረኩ ከማንም ጣልቃ ገብነት ተጠብቆና በነፁህ አዕምሮ ሃገራዊ ሆኖ ሊከወን የግድ የሚል መሆኑ ሊታወቅ ይገባ
- በኢትዮጵያ ሃገራዊ ምክክር መድረክ ሊነሱ የሚገቡ አጀንዳዎች፣ከላይ
እንደተጠቀሰው ሃገራዊ የምክክር መድረኮች ሃቀኛና ቅቡልነት ይኖራቸው ዘንድ ውሳኔ ሳያገኙ እየተጠለጠሉ የመጡ ጉዳዮችን እንደ አጀንዳ ይዞ መወያየት አንዱና ዋነኛው ተግባር ነው። ስለዚህ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሳይፈልግ ፣ ሳያማክሩትና ሳይወድ በኃይል እንደቀንበር ከተጫኑበት ጉዳዮች መካከል በሃገራዊ ምክክር መደርክ ሊታዮ የሚገቡ አጀንዳዎች የሚከተሉት ናቸው ተብሎ ይታሰባል :
- የባንዴራ ጉዳይ
- የሕገ-መንግስት መሻሻል ጉዳይ
- የአዲስ አበባ ከተማ የባለቤትነት ጉዳይ
- የመሬት የይገባኝል ጥያቄዎች
- የመንግስት ባለስልጣናት አሿሿም ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል የአማከለ ይሆን ዘንድ የማሳሰብ ጉዳይ
- በሃገረችን የሚከሰቱ ግጭቶችን በዘላቂነት የመፍታት ጉዳይ
- ሃገረ ኢትዮጵያን በብሄር ፣ በቋንቋና በጆግራፊያዊ አቀማመጥ በየትኛው ቢሆን ይሻላል ብሎ የማካለል ጉዳይ
ማጠቃለያ
ከሃገራት ልምድ አንፃር ሲታይ ሃገራዊ የምክክር መድረክ ማከናወኑ እሰየው የሚያሰኝ ጉዳይ ቢሆንም የመካክርት ጉባሄው ከላይ የተጠቀሱትን መስፈርቶች አሟልቶ ነው የተዋቀረው የሚለውን ጉዳይ ሕዝብ ሊነጋገርበትና ሊተቸው የሚገባ ኩነት ነው። በታሪክ እንደሚታወቀው ብዙ ሃገራዊ የምክክር መድረኮች ተካሂደዋል እነሱም ለምሳሌ ያህል የደርግና የሕውሃት ፣ የኦነግና የሕውሃት፣ የኢህአፓ፣ ኢዲዩና የሕወሃት ወ.ዘ.ተ. የሚጠቀሱ ሁነው እነዚህ የውይይት መድረኮች አንዱ አንዱን የመሰልቀጫ መድረክ ሆነው እንዳለፉ ታሪክ ልብ ይሏል። ስለዚህ የአሁኑ ሃገራዊ የምክክር መድረክ ይህ አይነት ክሳቴ እንዳያጋጥመው እናሳስባለን።
ይህ ሃገራዊ የምክክር መድረክ ከውጭ ሃገራት ተፅህኖ የፅዳ ፣ የአንድ ቡድን ፍላጎት የተነፀባረቀበት አለመሆኑን ፣ የመንግስትና የፓለቲከኞችን አጀንዳ ለማስፈፀም የተጎነጎነ ስላለመሆኑ ክትትል የሚሻው ይሆናል። ከዚህ ባሻገር ሃገራዊ የምክክር መድረኩን ለመፈፀም የሚያስችሉ ቅድመ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል ወይ
- የሚለው ጥያቄ ምላሽ ይሻል። ሕዝብ መነጋገርና መ መካከር ከማይፈልጋቸው አካላትና ቡድኖች ጋር መመካር መሞከሩ ሊያመጣው የሚችለው አሉታዊ ተፅህኖ ሊታሰብበት የሚገባና ለአገር ጠንቅ የሆኑ ቡድኖችን ለዘለቄታ አደብ ማስገዛት እንደሚገባ ግንዛቤ ሊወሰድበት የሚገባ ጉዳይ ነው እንላለን።
ተዘራ አሰጉ ከምድረ እንግሊዝ።