ልክ የዛሬ 4 ዓመት ገደማ፣ በታኅሣሥ ወር 2010 አካባቢ የተጀመረውን የኢሕአዴግ ውስጠ ተሐድሶ የለውጥ ማዕበል ሁሉም ሰው በዋህነት ተቀብሎ ነበር። የኢትዮጵያ መንግሥት አሁንም ተመሳሳይ ነገር እየሞከረ ይመስላል። ነገር ግን በዚህ ጊዜ የብዙኃን እና የፖለቲካ ልኂቃኑን የዋህነት መደገም የለበትም። ያልጠረጠረ ተመነጠረ! ነገር ግን ጠርጣራነቱ ለሁሉም መሆን አለበት። የብዙኃን ጥቅም፣ የተረጋጋ አገረ መንግሥትና ሰላማዊ ማኅበረ ፖለቲካ በየትኛው ወገን በቆመ የግለሰብ ሐሳብ ልክ መሠራት የለበትም።
በእኔ አረዳድ፣ ያለፈው የተሐድሶ ማዕበል በሚከተሉት አጀንዳዎች ተለብጦ የቀረበ ነበር፦
1) የክልል አገረ-መንግሥታት ነጻነት፣
2) በማዕከላዊ መንግሥት ውስጥ የክልሎች ተመጣጣኝ ውክልና፣
3) ኢኮኖሚያዊ ፍትሕ፣ እና
4) የዜጎች ነጻነት እና ደኅንነት።
በአጠቃላይ የተሐድሶ ማዕበሉ የተቀለበሰው በዋነኝነት በሚከተሉት ምክንያቶች ነው።
1) የተከፋፈሉ የኢሕአዴግ አካላት (ሕወሓት፣ ብልፅግና እና ሌሎችም) መካከል የተነሳ የሥልጣን ሽኩቻ፣
2) የተከፋፈሉ ተቃዋሚዎችና ብሔርተኞች መካከል የተነሳ የኃይል/ትርክት ሽኩቻ፣
3) የሕግ ማሻሻያዎችን ተቋማዊ ማድረግ አለመቻል ያመጣው ክፍተት፣ እና
4) ፖለቲካዊ ነውጠኝነት።
አዲሱ የ”ተሐድሶ” ማዕበል እስረኞችን በመፍታት የጀመረው አዲስ በተቋቋመው ኮሚሽን ይመቻቻል ለተባለው የ”አገራዊ ምክክር” መንገድ እንዲጠርግ ታስቦ ይመስላል።
ይህ አገራዊ ምክክር በመንግሥት እና በዜጎች መካከል ያለውን ማኅበራዊ ውል እንደገና ለመጻፍ ይበጃል ተብሎ ይታመናል።
አገራዊ ምክክሩ በስኬትም ይሁን በውድቀት ቢጠናቀቅ፣ ውጤቱ ብዙኃን ላይ ከባድ ተፅዕኖ አለው።
ከተሳካ፣ የሚከተሉትን ሊያስከትል ይችላል፡-
1) ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎች ይከለሳሉ፣
2) የፌዴራል አወቃቀር ይቀየራል፣
3) የመንግሥት ቅርፅ ይቀየራል፣
በተጨማሪም፦
1) የሽግግር ጊዜ ፍትሕ ሊኖር ይችላል፣
2) የአገረ መንግሥቱ ትርክቶችና ትዕምርቶች ይለወጣሉ።
ካልተሳካ ደግሞ፣ የሚከተሉት ሊፈጠሩ ይችላሉ፡-
1) ሕዝባዊ ቅቡልነት የሌለው መንግሠታዊ፣ ሕገ መንግሥታዊ እና ፌዴራላዊ የመዋቅር ለውጥ ሊኖር ይችላል፣
2) የተባባሱ የእርስ በርስ ግጭቶች ይቀጥላሉ፣
3) ደካማ መንግሥት ይኖራል፣ የዜጎች ማኅበራዊ ደኅንነት የከፋ አደጋ ላይ ይወድቃል።
እነዚህ ሁሉ ከፖለቲካ ልኂቃን ይልቅ ተራ ዜጎችን ይጎዳሉ።
ከዚህ ቀደም የፖለቲካ ታዛቢዎች/ዜጎች “የእነሱ” ወገን የሚመስሏቸውን የሥልጣን ተዋናዮች ከግልና ከቡድን ጥቅማቸው በላይ የፖለቲካ አጀንዳቸውን የሚያስቀድሙ ቅዱስ ፍጡራን አድርገው ይመለከቱ ነበር። የብዙኃንን ደኅንነት እና የአገራዊ ጥቅምን በመናድ ለተራ ጥቅም ሲሉ ወደ ትርምስ ይገባሉ ብሎ ብዙ ሰው አልጠረጠረም።
የተቀለበሰው “ተሐድሶ” ዛሬ ላይ በብዙዎቹ ተዋናዮች ተከድቷል።
በማናቸውም የተሐድሶ ለውጦች በመንግሥት እና በተቃዋሚዎች ውስጥ ካሉ ሁሉም የፖለቲካ ተዋናዮች አታላይ ምላስ ራስን ማዳን ያስፈልጋል። የፖለቲካ ተዋናዮቹን ተግባራቸውን ከንግግራቸው ባለፈ ማንበብ እና የንግግራቸው ውጤት ምን እንደሆነ በምክንያታዊነት መመርመር ካለፈው ልንማረው የሚገባ እና ለሁላችንም የሚበጅ ድርጊት ነው።
ብዙኃን የፖለቲካ ተዋናዮች ፕሮፓጋንዳ መጠቀሚያ መሆን የለባቸውም።
በበኩሌ፣ ካለፈው እና ከባከነው “የተሐድሶ” ዕድል በመማር ልንከተላቸው የሚገቡ የጥንቃቄ መርሖዎችን እነሆ ብያለሁ፦
1) መሪዎችን በነሲብ በመከተል ፈንታ እርምጃቸውን መቆጣጠር፣
2) ነውጠኝነት የጭቆናም ይሁን የተቃውሞ ዘዴ በሆነ ጊዜ በጋራ መቃወም፣
3) አጀንዳ ማወቅ፤ ነገር ግን ፍፁም እርግጠኛ አለመሆን፣
4) ጀግኖችን ሳይሆን ተቋማትን መሥራት።