ወፈን ሆይ ስማ እንጅ ስንቴ እንስጥህ ምክር፣
የቀን ጅቦችና የጥንብ አንሳ ፍቅር፣
በምድር ጸንቶ ኖር አብሮ እንደሚቀበር፡፡
ጥንብ አንሳና ጅቦች ጉጉት አጥቅቷቸው፣
በልፋጭ ተጋፍተው የተጣሉ መስለው ፣
በመላ አገሪቱ ስንቱን አስጨርግደው፣
ይሉኝታን ህሊናና ዛሬም ፍቀው ጥለው፣
ደምን በጎረሰ ምላስ ከንፈራቸው፣
መላላስ ጀመሩ እንደ ልማዳቸው፡፡
እባክህ ወይፈን ሆይ ሁሌ አትንዘላዘል፣
እንደ ቆቆች ንቃ እንደ ንስር አተኩር፣
እንደ አንበሳ አግስተህ እምቢ አሻፈረኝ በል፡፡
አንተ ብቻ ሳትሆን ዓለም እንደሚያውቀው፣
ጅብና ጥንብ አንሳ በላም ላይ ዶልተው፣
ተካፍለው ሊበሏት ቆራርጠው ዘልዝለው፣
ለሰላሳ ዓመታት ተማክረው ተስማምተው፣
ጅቡ ባለስልጣን ጥንብ አንሳ አሽከር ሆነው፡፡
በልቶ እማይጠግብን ጅብ ግፉ ጣለውና፣
ጥንብ አንሶች አረፉት ስልጣኑን ያዙና፡፡
በስልጣን ዘመኑ ሆዱ የሰፋው ጅብ፣
እንዴት ይዋጥለት ዳረጎት መቀበል፣
ጥንብ አንሳ ተሚባል ተድሮው ጥሩ አሽከር?
ጥንብ አንሶች ተጅቡ በስልጣን ተጋፍተው፣
ስንት ወይፈን አስፈጁ ላምን አዳኝ መስለው፡፡
ጅብ ሰክሮ ሲመጣ አተላውን ቅሞ፣
ጥንብ አንሳን ሊያወረደው ተስልጣን ዠልጦ፣
ወይፈንና ኮርማ አዳነው ተዋግቶ፣
ለላሚት ጥንብ አንሳው ተጅብ ይሻል ብሎ፡፡
ነገር ግን ጥንብ አንሳ የድሮው ጅብ አሽከር፣
ለጊዜውም ቢሆን ስልጣኑን ሲስያከበር፣
ለጅብ መኖር ሲፈቅድ ተወንዙ ባሻገር፣
መናቆር ጀምሯል ተወይፈን ኮርማ ጋር፡፡
ጥንብ አንሳ እርግቦችን ጅብ በግ እንደማይሆን፣
ከሰላሳ ዓመት ውጪ ማን ይንገርህ ወይፈን?
የሰላሳ ዓመቱ ታሪክ ሲመረመር፣
ጆፌ ትርፍራፊ ጉርሻ ለመቀበል፣
ስንቱን ወይፈን ኮርማ በጅብ አስበልቷል፡፡
እባክህ ወይፈን ሆይ ዛሬ እንኳን ነቃ በል፣
ጅብና ጥንብ እንሳ የተጣሉ ቢመስል፣
እውነት አይምሰልህ እንዳትንዘላዘል፣
ለአያሌ ዘመናት በአንድ ማድ በልተዋል፣
ላሟን በጦር ወግተው ደሟን ጠጥተዋል፡፡
ዛሬም የጥንብ አንሳ ተጅብ ጋር ድርድር፣
አንተኑ ዳግመኛ በጅብ ለማስወረር፣
መሆኑን አጢነህ አካኬ ዘራፍ በል፣
አንድ ላይ ከትመህ ምከርና ዘክር፣
በቀንድህ በሻኛህ ክብርህን አስከብር፡፡
ተቂል ተአድርባዮች ተሆዳም በስተቀር፣
እንዲህ ዓይነት ተረት ድሮስ ማን ይሰማል፣
ጥንብ አንሳ ለፍትህ በጅብ ይጨክናል?
በላይነህ አባተ ((abatebelai@yahoo.com)
መጀመርያ ታህሳስ ሁለት ሺ አስራ አራት ዓ. ም.
እንደገና ጥር ሁለት ሺ አስራ አስራ አራት ዓ. ም.