የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን በትላንትናው ዕለት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንን ጨምሮ ከሶስት ከፍተኛ የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ጋር መወያየታቸውን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቃል አቃባይ ገለጹ። ልዩ መልዕክተኛው በዛሬው ዕለትም ከሌሎች የኢትዮጵያ ባለስልጣናትን አግኝተው እንደሚነጋገሩ ገልጸዋል።
ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ልዩ መልዕከተኛ ጋር ትላንት ተገናኝተው ከተወያዩ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት መካከል፤ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን አንዱ እንደሆኑ ኔድ ፕራይስ ተናግረዋል። ፌልትማን ባለፈው ነሐሴ ወር ወደ አዲስ አበባ በመጡበት ወቅት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጋር ተገናኝተው መነጋገራቸው ይታወሳል።
አሜሪካዊው ዲፕሎማት፤ ከአቶ ደመቀ በተጨማሪ ከመከላከያ ሚኒስትሩ ዶ/ር አብርሃም በላይ እና ከገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ ጋር ተገናኝተው መወያየታቸውን የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቃል አቃባይ ለጋዜጠኞች ገልጸዋል።
የሽዋስ አለምነህ ወንድም