አክሎግ ቢራራ (ዶር)
“ኢትዮጵያ የቃልኪዳን አገር ናት፤ የሚገነቧት ይገነባሉ
ሊያፈርሷት የሚያስቡ ግን ይፈርሳሉ”
አባታችን አቡነ መልከ ጸዲቅ
ክፍል አንድ
የኢትዮጵያ መሰረታዊ ተግዳሮት ህወሓት/ትህነግና ፈረስ ሆኖ የሚጋልባቸው ሌሎች የዘውግ ሽብርተኛ ቡድኖች ብቻ አይደሉም። እነሱ ብቻ ቢሆኑ ኖሮ የዛሬ ዓመት በህወሓት የተጀመረው የሚዘገንን እልቂትና ውድመት ያስከተለው ጦርነት እስካሁን ይገባደድ ነበር። ምንም እንኳን ህወሓት “አንድ ሚሊየን ተዋጊ ኃይል አሰልፌ ሂሳብ አወራርዳለሁ” ብሎ ቢፎክርም፤ የዘረፈውና ለአስርት ዓመታት በተምቤን፤ በጉናና በሌሎች ተራራዎች የደበቀው መሳሪያ ግዙፍ ቢሆንም፤ ዙሮ ዙሮ የራስህ ቤትም አብሮ ይወድማል ብሎ የተነሳው አገር ወዳዱ የኢትዮጵያ ኃይል አጥፊውን፤ ከጨጃኝ በላይ ጨካኝ የሆነውን፤ የንጹሃንን ህይወት ከእንስሳ ህይወት በታች ነው ብሎ በእልቂት ላይ እልቂት የሚያካሂደውን ህወሓትን እስካሁን ይደመስሰው ነበር። የረሳነው አንድ አስኳል ነገር አለ።
ይኼውም፤ ኢትዮጵያን ልክ እንደ ዩጎስላቭያ ለመበታተን የተሰለፉ ኃያላን መኖራቸውን ነው።
የተግዳሮቱ መንስኤ
መጀመሪያ፤ በችግሩ እምብርት ላይ እንስማማ። የኢትዮጵያ የዘውግ ልሂቃን፤ ፓርቲዎችና ምሁራን በህወሓት/ትህነግ መሪነትና አቀነባባሪነት፤ በውጭ መንግሥታት ድጋፍ በዘውግና በቋንቋ የማይታረቁ ልዩነቶች ላይ የተዋቀረ ዘውግ-ተኮር ሕገመንግሥት አወጁ። ሰብሳቢውን ምሰሶ “እኛ ብሄር፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች” በሚል ሃረግ ጀመሩት። ማንኛውም ብሄር፤ ብሄረሰብ ወይንም ሕዝብ የመገንጠል መብቱ የተከበረ ነው (አንቀጽ 39) በሚል ማንም አገር የማይቀበለውን ውሳኔ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ጫኑበት።
የኢትዮጵያ መአከላዊ መንግሥት እየደከመ፤ የክልል መንግሥታት እየጠነከሩ ሄዱ፤ በተለይ ህወሓት የሚመራው ትግራይ ክልል። ራስን በራስ ማስተዳደር የሚለውን ለጥጠው (stretching ethnic regionalism to the breaking point) የራሳቸውን ልዩ ኃይል አጠናከሩ። የዘውግ ማንነት ስር እየሰደደ ኢትዮጵያዊነት እየመነመነ ሄደ።
ይህንን የዘውግና የቋንቋ ልዩነት የውጭ ኃይሎች እየተጠቀሙበት ነው። ላሰምርበት የምፈልገው አስኳል ጉዳይ የኢትዮጵያን ችግር መሰረት የፈጠርነው ራሳችን መሆናችን ነው።
ህወሓትና የምእራብ አገር ባለሥልጣናት– በተለይ የባይደን መንግሥት– እየተናበቡ “ጥፋቱ” የኢትዮጵያ መንግሥት አመራር እንጅ የህወሓት አይደለም የሚሉበት መሰረታዊ ምክንያት የራሳችሁ ሕገመንግሥት እንደሚለው ራስን በራስ ማስተዳደር በሕግ የተከበረ ነው። ሌላው ቀርቶ መገንጠልንም ይደግፋል ይላሉ።
ለአንድ ዓመት ሲካሄድ የቆየው የእርስ በእርስ ጦርነት መሰረቱ ራሱ ሕገመንግሥቱና የአስተዳደር መዋቅሩ መሆኑን ለመካድ አይችልም።
እኔን የሚያሳስበኝ፤ ይህ ሁሉ በዘውግ ጥላቻ ላይ የተመሰረተና የሚካሄድ የእርስ በእርስ ጦርነት ቢያልቅም እንኳን ከዚያ ባሻገር “የቃልኪዳኗ” ኢትዮጵያ ምን አይነት አገር ትሆናለች? ህወሓት ተወግዶ ሌላ ህወሓት ይፈጠራል?
በጦርነት የተጎሳቆለው፤ ዘመድ አዝማዱን ያጣው፤ መኖሪያ ቤቱ የተቃጠለበት፤ የትምህርትና የጤና አገልግሎት መሰረተ ልማቱ የወደመበት ወዘተ የአፋሩና የአማራው ሕዝብ እንዴት ባለ ተዓምር ነው የትግራይን ሕዝብ አምኖና አክብሮ ሊኖር የሚችለው? ብሎ መጠየቅ አስፈላጊ ነው። እኔ እንደ ህወሓት ያለ ርህራሄ የሚባል እሴት የሌለው፤ አገርን የሚከዳ፤ ከኢትዮጵያ የውጭ ጠላቶች ጋር የሚያሴር፤ የሃሰት መረጃዎችን ፈብርኮና ለውጭ ተቋማት አሰራጭቶ ድረሱልኝ የሚል፤ የከሃዲ ከሃዲ ቡድን አይቸ ወይንም ሰምቸ አላውቅም። ግን፤ ይህ ሁሉ ሆኖ ህወሓት የውጭ ደጋፊዎች አሉት። ከእነዚህ መካከል የአሜሪካ መንግሥትና የተባበሩት መንግሥታት መስሪያ ቤት ዋናዎቹ ናቸው።
የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት አመራር በሕዝብ ግንኙነትና በዲፕሎማሲ በኩል ሁኔታዎችን አመዛዝኖ፤ ፍኖተ ካርታ አውጥቶ፤ ብቃት ያላቸውን ባለሞያዎች ቦታ አስይዞ ከንትርክ ይልቅ ተጽእኖ ፈጣሪ ከሆነው ከአሜሪካ መንግሥት ጋር በቀጥታ ሆነ በድብቅ፤ ውይይትና ድርድር አለማድረጉ ያሳዝነኛል። መሰረታዊ ጥያቄ አለ። ይኼውም አሜሪካና ኢትዮጵያ የ118 ዓመታት ወዳጅነት አላቸው። ይህንን ወዳጅነት ለምን ታፈርሱታላችሁ? የኢትዮጵያ መንግሥት የኢትዮጵያን ግዛታዊ አንድነት፤ ሉዐላዊ መብትና ብሄራዊ ጥቅም ለማስከበር የሚያደርገው ትግል ለምን አሳሰባችሁ? እኛ የምናደርገው እናንተ የአሜሪካን ደህንነት ለመታደግ ከምታደርጉት እንዴት ይለያል? የሚሉ ጥያቄዎችን ማቅረብ አስፈላጊ ነበር፤ ነው።
የአሜሪካ ባለሥልጣናት ይህንን ይቀበሉ አይቀበሉ የማውቀው ነገር የለም። ግን ክፍተቱን መካድ አይቻልም።
ከዚህ ጋር አብሮ የሚሄድ ክስተት አለ። ለመጀመሪያ ጊዜ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፤ በተለይ፤ ሴኩሪቲ ካውንስል ተብሎ የተቋቋመው ድርጅት በተከታታይና በሚያሳፍር ደረጃ፤ በማያገባው በኢትዮጵያ የአገር ጉዳይ ውስጥ ገብቶ አይን ያወጣ ወገንተኛነት ሲያሳይ ኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ አገር ናት። የሊግ ኦፍ ኔሽንስ የፈጸመውን ስህተት በዋናው ጸሃፊ በአንቶኒዮ ጉተሬዝ የሚመራው ድርጅት (ተመድ) እየፈጸመው ነው። ይህ ተቋም የችግሩ አካልና መጋቢ ሆኗል።
ዋናው ጸሃፊና የእሳቸው ታዛዢዎች ህወሓት የሚፈጽማቸውን ወንጀሎች ልክ እንዳልሰሟቸውና እንደማያምንቧቸው ችላ ይሏቸዋል። የአፋርና የአማራ ወጣቶች፤ እናቶች፤ አባቶች፤ ህጻናት፤ እርጉዞች፤ አዛውንቶች ወዘተ ህይወት እልቂትና ብሶት ተንቀዋል ለማለት እችላለሁ።
የህወሓትን አረመኔነት ተመልከቱት። ከዚህ ጽሁፍ ጋር አባሪ ያደረግሁት ቪዲዮ እንደሚያሳየው፤ በቅርቡ በተካሄደው ጦርነት፤ ህወሓት ልክ ማይ ካድራ ላይ እንዳደረገው ሁሉ 28 ወጣቶችን ዐማራ መሆናቸውን ለይቶ፤ ወጣቶቹን የፊጥኝ አስሮ በአንድ ቤት አጎራቸው። ካጎራቸው በኋላ አንድም እንዳይተርፍ ስሌት አድርጎ፤ የታጎሩበትን ቤት በቤንዚን ረጨው። እነዚህን የአማራ ወጣቶች እንዳይተርፉ ቤቱን አቃጥሎ ጨፈጨፋቸው። ይህንን ወንጀል ከሚፈጽም አረመኔ ቡድን ጋር እርቅ አይታሰብም፤ አይቻልም። ይቻላል የምትሉት ኢትዮጵያዊያን እስኪ ሂዳችሁ ልጆቻቸው የሞቱባቸውን እናቶች አነጋግሩ እላለሁ። ይህም ሆኖ ግን የአሜሪካ መንግሥት ባለሥልጣናት ጥፋቱን የጫኑት በዐብይ መንግሥት ላይ ነው።
በእኔ እምነት፤ ከህወሓት ጋር እየተናበቡ የሚሰሩ የውጭ ተቋማት ህሊና ቢሶች ናቸው።
ህወሓት ይህንን የሚዘገንን ድርጊት ፈጽሞ ግን የምእራብ አገር ጋዜጦች፤ ለምሳሌ የህወሓት አፈ-ቀላጤ የሆነው ሮይተርስ፤ ባለሥልጣናትና የተባበሩት መንግሥታት ህወሓትን አላወገዙም። በተጻራሪው ዋና ዜና ሆኖ የቀረበው የኢትዮጵያ መከካለክያ ኃይል በመቀሌ ለይቶ ማጥቃት በሆነ ስልት ሽብርተኛው ህወሓት የሚጠቀምባቸውን የመገናኛ ስርጭት ሰንሰለቶች የያዙ ህንጻዎችን በአየር ኃይል ሲደበድብ ልክ የትግራይን ንጹሃን ደበደበ ብለው ይከሳሉ።
እኔን ያሳሰበኝ የህወሓትን መሳሪያ ክምችት ለይቶ መምታቱ አይደለም። ህወሓት ከትግራይ አልፎ በአፋርና በአማራ ክልሎች የሚቆጣጠራቸውን አካባቢዎች ለማስለቀቅ የወታደራዊ አመራር ብቃት አለመኖሩ ነው። ወጣቱ በገፍ ለመዋጋት ተሰልፎ፤ ህይወቱን ለአደጋ አጋልጦ፤ መሳሪያ “ስጡኝ፤ አስታጥቁኝ፤ በዱላ ለመዋጋት አልችልም” እያለ ቢጮህም ሰሚ አለማግኘቱ አስደንግጦኛል። ይህ የአመራር ድክመት በአጭር ጊዜ ካልተፈታ መቀሌን ቦምብ ማድረጉ በሕዝብ ግኑነትና በዲፕሎማሲ በኩል የሚደግፈውና የሚያጠናክረው ህወሓትን ነው። በአፋርና በዐማራው ክልል የሚደረገውን ማንኛውንም የማጥቃት እርምጃ የአሜሪካ መንግሥት ባለሥልጣናትና የተባበሩት መንግሥት ጽህፈት ቤት ለማውገዝ አይችሉም።
የሁለቱም አካላት ትኩረት ከትግራይ ክልልና ከትግራይ ሕዝብ ላይ ነው። ሕገመንግሥቱ ተጥሷል በሚል ሰበብ፤ አላማቸው ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን መንግሥት ማዳከምና ማጋለጥ ነው። ሚዛናዊና ፍትሃዊ መርህ ቢከተሉ ኖሮ፤ ህወሓት በአፋርና በአማራ ሕዝብ ላይ የሚያካሂደውን ጭካኔ የተሞላበት እልቂትና ውድመት ያወግዙ ነበር።
ይህ የቅርብ የህወሓት ጭካኔ በማያሻማ ደረጃ የሚሰጠን መልእክት ከዚህ ከአረመኔ በላይ አረመኔ ከሆነ አጥፊ ቡድን ጋር ምንም አይነት የሰላም ድርድር የማይታሰብ መሆኑን ነው። ጭካኔውን የአማራና የአፋር ጉዳይ ነው ብሎ ማለፉ ስህተት ነው። ህወሓት ዱሮ እንደ ለመደው አፋሩንና አማራውን ካደቀቀ በኋላ ነገ ደግሞ ኦሮሞውን፤ ሶማሌውን፤ ወላይታውን፤ ጉራጌውን ወዘተ ይጨፈጭፋል። “ነግ በኔ” ይደርሳል ብሎ ማሰቡና መተባበሩ ይሻላል። ቦዝኒያ የሆነውን አንርሳ።
በጥናትና በምርምር የተደገፉ ሰነዶች የሚያሳዩት፤ ህወሓት እንደ ጠባብ ብሄርተኛ ድርጅት የጸነሰው የብሄር ጥላቻ አመለካከት፤ የመሰረተው ዘውጋዊ ሕገመንግሥትና የከፋፍለህ ግዛው አስተዳደር እስካልተገረሰሱ ድረስ ኢትዮጵያ ሰላምና እርጋታ ሊኖራት አይችልም። ዘላቂና ፍትሃዊ ልማት አይቻልም። ችግሩ መሰረታዊና ስርዓታዊ ስለሆነ ስር ነቀል ለውጥ ይጠይቃል። የምእራብ አገሮች፤ በተለይ የአሜሪካ መንግሥት የአሁኑ ኢትዮጵያን ያዳከመውና ለጦርነት የዳረጋት የብሄሮች መከፋፈል ስርዐት እንዲቀየር አይፈልጉም። የአሜሪካ መንግሥት ህወሓትን ከሚደግፍባቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ ዘውጋዊው ሕገ መንግሥት፤ ስርዓትና አስተዳደር የኢትዮጵያን ብሄራዊ/ግዛታዊ አንድነትና ሉዓላዊነት ስላዳከማቸው ነው።
ይህ የከፋፍለህ ግዛው፤ አዳክመው፤ ጥገኛ አድርገው የሚል ስርዓትና መዋቅር በታማኙ በህወሓት የበላይነት ካልቀጠለ ኢትዮጵያን መበታተን ያስፈልጋል ወደሚል ድምዳሜ የደረሱ ይመስለኛል። ትክክል ባልሆን ደስ ይለኛል። ግን እናስብበት።
የዚህ ትንተና ዋና ዓላማ የአሜሪካ፤ አጋር የሆኑ ሌሎች የምእራብ አገር መንግሥታት መሪዎች፤ በበላይነት የሚያሽከረክሩትና የሚያዙት የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሃፊ ጽህፈት ቤት፤ የምእራብ ሜድያዎች በሙሉ በሚያስብል ደረጃ ወዘተ ህወሓት የጫረው ጦርነት ከጀመረበት ቀን ጀምሮ እስካሁን የሚደግፉት ሃቁን አይደለም። የኢትዮጵያን ግዛታዊ አንድነትም አይደለም። ሰላምና እርጋታም አይደለም። የአገራችንም ዘላቂ ደህንነትና ልማት በማሰብ አይደለም። የሚመሩት በራሳቸው ብሄራዊ ጥቅም ነው።
የሚሰሩት ለፍትህ አይደለም፤ ሊሆንም አይችልም። ለሰብአዊ ደህንነትም ቢሆን ደንታ የላቸውም። ማህበረሰባዊ ወይንም ሰብአዊ ድጋፍ (Humanitarian aid) የፖለቲካ መሳሪያ ከሆነ ቆይቷል። ለህወሓት ቀጥተኛ ወይንም የድብቅ ድጋፍ የሚሰጡት የምእራብ ተቋማት ረሃብን፤ የሰብአዊ መብት መኮላሽትንና ተመሳሳይ መስፈርቶችን የሚጠቀሙበት ዋና ምክንያት ግባቸውን በሌላ መንገድ ስኬታማ ለማድረግ ስለማይችሉ ነው።
በቅኝ አገዛዝ ጊዜ እንግሊዞች፤ ፈረንሳዮች፤ ቤልጅያኖች፤ ጣልያኖች ወዘተ ጥቁር አፍሪካን ለመቆጣጠር ይዘምቱ ነበር። ይህ ሁኔታ ተቀይሯል። የምግብ ድጎማ ሆነ ሌላ ሰብአዊ እርዳታ መሳሪያ ሆኖ ድሃና ኋላ-ቀር የሆኑትን አገሮች ለምእራብ አገሮች የበላይነት ያገለግላል (Humanitarian aid has become a new form of imperialism). ለማኝ ሊመርጥ አይችልም። ስለማይችል፤ ለጋሶቹ ለምግብ እርዳታ በሚጠቀሙበት መኪና የመገናኛ መሳሪያ፤ ሰላይ፤ ወዘተ ለማጓጓዝና የሚፈልጉትን ኃይል አቅም ለማጠናከር የሚጠቀሙበት እድል አላቸው ማለት ነው። እርዳት የጦር መሳሪያ ሆኗል (Humanitarian aid is weaponized) የሚባለው በዚህ ምክንያት ነው።
የተባበሩት መንግሥታት ዋና ድክመትና ክህደት የሚታየው ከዚህ ላይ ነው። አራት መቶ ሃያ ስምንት የምግብ ማጓጓዣ መኪኖዎች ወደ ትግራይ ሂደው በህወሓት አማጽያን ሲጠለፉና የወታደር ማመላለሻ ሲሆኑ ለምን ይህንን አይን ያውጣ ወንጀል ዋና ጸሃፊው አልተቹም፤ አላወገዙም፤ በፍጥነት እንዲመለሱ አላደረጉም? ይህ በራሱ ተባባሪነትን ያሳያል። ጉተሬዝና የአሜሪካው የህወሓት ደጋፊ አንቶኒ ብሊንከን በአንድ ድምጽ ጩኸት ያሰሙትና ያወገዙት፤ የኢትዮጵያ መንግሥት 7 ግለሰቦች፤ ስራቸውንና የተሰጣቸውን ሃላፊነት ወደ ጎን ትተው፤ ህወሓትን ሲደግፉ እጅ ለፍንጅ የተያዙትን ሰራተኞች የኢትዮጵያ መንግሥት ሃላፊነቱን ለመወጣት ከአገር ሲያባርራቸው ነው።
አንኳን የተባበሩት መንግሥታት ሰራተኛን አንድ አምባሳደር የአንድ አገርን ሉዓላዊ መብትና ደህንነት የሚጻረር ስራ ከሰራ፤ ሽብርተኞችን ከረዳ የማባረር መብት አለው።
የተባበሩት መንግሥታት ራሱን ዝቅ ያደረገባቸውን ብዙ ምሳሌዎችን ለመጥቀስ ይቻላል። መኪናዎቹ ምሳሌ ናቸው፤ ሰባቱ ሰራተኞች ምሳሌ ናቸው፤ በትግራይ ጦርነት ምክንያት ኢትዮጵያ እንደ አጀናዳ ሆና በተባብሩት መንግሥታት የደህንነት ካውንስል ዘጠኝ ጊዜ ስትቀርብ ሌላው ምሳሌ ነው። የህዳሴ ግድብ ጉዳይ ሊዘነጋ አይችልም። እነዚህ ሁሉ ያልተለመዱ ናችው (These are all unprecedented and precedent setting episodes against a Black African country that is fighting for its survival). በእነዚህና በተዛማጅ ምክንያቶች የተነሳ በተባበሩት መንግሥታት አመራር ላይ የኢምንት ያክል እምነት የለኝም።
ክፍል ሁለት የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ጫና የሚያደርግባቸውን ምክንያቶች ያቀርባል
October 22, 2021