ለቸኮለ! ዓርብ ጥቅምት 12/2014 ዓ.ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

1፤ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዛሬ በመቀሌ ከተማ ለአራተኛ ቀን የአየር ድብደባ እንደፈጸመ የወቅታዊ መረጃዎች ማጣሪያ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል። የድብደባው ዒላማ የሕወሃት ወታደራዊ ማሰልጠኛና የውጊያ ግንኙነት ኔትዎርኮች ያለበት የቀድሞው የመከላከያ ሠራዊት ማሰልጠኛ ማዕከል እንደሆነ መረጃ ማጣሪያው አክሎ ገልጧል። የሕወሃት ዜና ምንጮች በበኩላቸው፣ ድብደባው የተፈጸመው መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ አቅራቢያ እንደሆነና በጥቃቱ 11 ሰዎች እንደቆሰሉ ዘግበዋል።

2፤ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዛሬ በመቀሌ ድብደባ በመፈጸሙ የዓለም ምግብ ድርጅት ዕርዳታ ጫኝ አውሮፕላን መቀሌ የማረፍ እቅዱን እንደሰረዘ ሰምቻለሁ ሲል ሮይተርስ ዘግቧል። ሮይተርስ መረጃውን ሰማሁ ያለው ከረድዔት ድርጅቶች ሁለት ምንጮች ነው። የድርጅቱ አውሮፕላን ዕቅዱን የሰረዘው፣ ትግራይ ክልል ገብቶ ወደ መቀሌ ከተቃረበ በኋላ ወይንስ ገና ከአዲስ አበባ ሳይነሳ ይሁን አይሁን ዘገባው አላብራራም።

3፤ ፌስቡክ ኩባንያ በኢትዮጵያ መንግሥት በአሸባሪነት የተፈረጀውን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን ወይም ኦነግ ሸኔን ከፌስቡክ ማኅበራዊ ትስስር ገጽ ማገዱን ቢቢሲ አማርኛ ዘግቧል። ፌስቡክ ቡድኑን ያገደው አደገኛ ድርጅቶችንመድረክ ላለመስጠት በሚከተለው መመሪያ መሠረት እንደሆነ ገልጧል። ከእንግዲህ በቡድኑ ወይም ቡድኑን ወክለው የሚከፈቱ የፌስቡክ ገጾች እንዲኖሩ እንደማይፈቅድ እና ለቡድኑ ድጋፍ የሚሰጡ መልዕክቶችንም እንደሚያጠፋ ኩባንያው ገልጧል።

4፤ ሩሲያ የሰሜኑ ኢትዮጵያ ጦርነት ተፋላሚ ኃይሎች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ተኩስ አቁም እንዲያደርጉ ጠይቃለች። ሩሲያ የአፍሪካ ኅብረት መልዕክተኛ ኦሌሴጎን ኦባሳንጆ ችግሩን ለመፍታት እያደረጉት ያለውን ጥረት እንደምትደግፍም የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ማሪያ ዛካሮቫ መናገራቸውን ሚንስቴሩ በትዊተር ገጹ ገልጧል። የኢትዮጵያን አንድነትና የግዛት ሉዓላዊነት ማስጠበቅ፣ ውስጣዊውን የትግራይ ግጭት ጨምሮ ሁሉንም ውዝግቦች ለመፍታት እና ማኅበራዊና ሰብዓዊ ቀውሱን ለማረጋጋት ቁልፉ መሠረት እንደሆነ ሩሲያ ጠቁማለች።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የቫንኩቨር ኢትዮጵያዊያን ተደስተዋል - ቤተክርስቲያናቸው ቋሚ ቤተመቅደስ አግኝታለች

5፤ ትናንት በባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ አመራሮች ችሎት ላይ በፖሊስ የታሠሩ 42 የችሎቱ ታዳሚዎች ዛሬ ፍርድ ቤት እንደቀረቡ ዶይቸቨለ ዘግቧል። ፍርድ ቤቱ ሁለቱ በዋስ እንዲለቀቁ ያዘዘ ሲሆን፣ 40ዎቹ ታዳሚዎች ግን በመጭው ሰኞ ችሎት እንዲቀርቡ አዟል። ፖሊስ ታዳሚዎቹን ያሰራቸው ችሎቱን በመረባሻቸው እና ሁከት በመፍጠራቸው እንደሆነ አብራርቷል። የፓርቲው ጠበቃ ግን በወቅቱ ታዳሚዎቹ ተከሳሽ እስክንድር ነጋ ወህኒ ቤት ውስጥ መደብደቡን ሲሰሙ፣ ከችሎቱ ለመውጣት የሞከሩና ችሎቱም በሰላም እንዲወጡ የፈቀደላቸው ታዳሚዎች መሆናቸውን በመጥቀስ የፖሊስ እስር ሕገወጥ መሆኑን ተናግረዋል።

6፤ በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ከምትገኘው ኮምቦልቻ ከተማ ወደ አዲስ አበባ ለመጓዝ የሚከፈለው መደበኛው የሕዝብ መጓጓዣ ተመን ሰሞኑን በአምስት እጥፍ መጨመሩን ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ዘግቧል። የመጓጓዣ ተመኑ የጨመረው በአካባቢው ከሕወሃት ኃይሎች ጋር በሚደረገው ውጊያ ሳቢያ የተሽከርካሪዎች እጥረት በመፈጠሩ እንደሆነ የተናገሩት ተጓዦች፣ ቀደም ሲል 200 ብር የነበረው የአንድ ጉዞ ዋጋ ተመን አሁን ወደ 1 ሺህ ብር ማሻቀቡን ገልጠዋል። ሌላኛው የመጓጓዣ አማራጭ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ካለፈው ሰኞ ጀምሮ ከአዲስ አበባ ወደ ኮምቦልቻ የሚያደርገውን በረራ አቋርጧል።

7፤ በአማራ ክልል አራት ዞኖች አደገኛው የፖሊዮ ቫይረስ እንደገና እንዳገረሸ የክልሉ ኮምንኬሽን ቢሮ የክልሉን ጤና ቢሮ ጠቅሶ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባሰራጨው መረጃ አመልክቷል። የፖሊዮ ቫይረስ የተከሰተው በሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ወሎ፣ ምዕራብ ጎጃም ዞኖች እና በኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር እንደሆነ የገለጠው ጤና ቢሮው፣ የቫይረሱን ሥርጭት ለመከላከል በአራቱም ዞኖች ለአራት ቀናት የሚቆይ የጸረፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ዛሬ እንደጀመረ ገልጧል። ባሁኑ ዙር ዕድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች የሆኑ 2.5 ሚሊዮን የክልሉን ሕጻናት ለመከተብ የታቀደ ሲሆን፣ ሁለተኛው ዙር ክትባት ከአንድ ወር በኋላ ይጀመራል። ሰሜን ወሎ እና ደቡብ ወሎ ዞኖች ግን ባሁኑ ሰዓት በከፊል የጦርነት ቀጠና ናቸው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  Sport: የተጨዋቾች ዝውውር ዋጋ ንረት ምክንያቱ ምን ይሆን?

8፤ ዛሬ የመክፈቻ ጉባዔውን ያካሄደው አዲሱ የሐረሬ ክልል ምክር ቤት አርዲን በድሪን በድጋሚ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አድርጎ እንደሾመ የመንግሥት ዜና አውታሮች ዘግበዋል። አርዲን ክልሉን ላለፉት 3 ዓመታት በርዕሰ መስተዳድርነት የመሩ ናቸው። ምክር ቤቱ አፈ ጉባዔውን እና ርዕሰ መስተዳድሩ የሚያቀርቧቸውን የክልሉን ካቢኔ አባላትም ይሾማል። መስከረም 20 በተደረገው ምርጫ መሠረት ከክልሉ ምክር ቤት በተጨማሪ በመላ ሀገሪቱ በሚኖሩ የሐረሬ ብሄረሰብ አባላት የተመረጠው የብሄረሰቡ ምክር ቤት ይቋቋማል።

9፤ የፌደራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ የሁለት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞችን ያለመከሰስ መብት እንዳነሳ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዛሬ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባሰራጨው መረጃ አስታውቋል። የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ይህን ውሳኔ ያሳለፈው፣ ፍትህ ሚንስቴር ዳኞቹ በወንጀል እንደሚጠረጠሩ እና ምርመራ ለማድረግ እንዲመች ያለመከሰስ መብታቸው እንዲነሳ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት ነው። ያለመከሰስ መብታቸው የተነሳባቸውን ዳኞች ማንነት ግን መረጃው አልጠቀሰም።

[ዋዜማ ራዲዮ]

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share