tig1
በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ ስጋት የደቀነውን አሸባሪውን የህወሓት ቡድን ለመደምሰስ ማንኛውንም አይነት መስዋዕትነት እንደሚከፍሉ በአዲስ አበባ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ተናገሩ።
ተወላጆቹ ከመንግስት ከፍተኛ የአመራር አባላት ጋር በአገሪቷ ወቅታዊ ሁኔታና አገር ለማዳን እየተደረገ ላለው ዘመቻ መሰራት ባለባቸው ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።
በቀደምት አባቶች አንድነትና ትብብር ሉዓላዊነቷን አስጠብቃ የቆየችው ኢትዮጵያ፤ በአሸባሪው ህወሓትና በውጭ ሃይሎች የተደቀነባትን ፈተና በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ አቶ ዛዲግ አብርሃ አብራርተዋል።
ተወላጆቹ አሸባሪው ቡድን በአፋር ክልል በንጹሃን ዜጎች ላይ የፈጸመውን ጭፍጨፋ፣ ለትግራይ ሕጻናት ሀሺሽ እየሰጠ ለጦርነት ማሰለፉንና በሌሎች አካካቢዎች እያደረገ ያለውን የሽብር ድርጊት አውግዘዋል።
99999999999999999999999999999999 768×298
ለትግራይ ሕዝብ ቆሜያለሁ የሚለው አሸባሪ ቡድን ሕጻናትን በጦርነት በማሰለፍ እናቶች በጭንቀት እዲኖሩ በማድረግ ጠላትነቱን በግልጽ ማሳየቱን ገልጸዋል።
በመሆኑም የመላው ኢትዮጵያዊያን ጠላት የሆነውን አጥፊውን ቡድን ለመደምሰስ መከላከያ፣ የክልል ልዩ ሃይሎችና መላ ኢትዮጵያዊያን እያደረጉት ያለውን አንድነት በመደገፍ ከመንግስት ጎን እንደሚቆሙ ተናግረዋል።
ደም በመለገስ፣ ግንባር ድረስ በመሄድ፣ ከደመወዛቸው በመስጠትና ሠላማዊ ሠልፍ በመውጣት እንደግፋለን ብለዋል።
የትግራይ ተወላጆቹ አሸባሪው ቡድን ተደምስሶ በኢትዮጵያ ሠላም፣ አንድነት፣ ልማትና ብልጽግና እንዲሰፍን አስፈላጊውን መሰዋዕትነት እንደሚከፍሉም አረጋግጠዋል።
ከሽብር ቡድኑ ጋር አብረው የሚሰሩትን በማጋለጥ፣ የአቋም መግለጫዎችን በማውጣት፣ ቡድኑን የሚያወግዙ ሠልፎችን ማካሄዳቸውን እንደሚቀጥሉም ነው የተናገሩት።
ስራቸውን በተደራጀ መንገድ ለማከናወን ከሃይማኖት አባቶች፣ ከሲቪል ማኅበራትና ከፖለቲካ ፓርቲዎች የተውጣጣ ካውንስል እንዲቋቋምም ጠይቀዋል።
አቶ ዛዲግ አብርሃ ተወላጆቹ የመከላከያ ሠራዊቱን አገር የማዳን ዘመቻ ለመደገፍ የገቡትን ቃል በተግባር እንዲያሳዩ ጠይቀዋል።
የትግራይ ሕዝብ እንደ እህትና ወንድሞቹ ለኢትዮጵያ ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረከተ መሆኑን በመጥቀስ ይህም በተለያየ መልኩ የቡድኑን የሐሰት ፕሮፖጋንዳ እንደሚያከሽፍ ገልጸዋል።
በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ በልጅጌም የኢትዮጵያን አንድነት ለማስቀጠል በጋራ መቆም እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
የትግራይ ተወላጆች በተደራጀ መንገድ ሙያተኛው፣ ባለሃብቱና ሌላውም ቡድኑን ለመደምሰስ እየተደረገ ያለውን ዘመቻ እንዲያግዙ ጠይቀዋል።
ተወላጆቹ ለመከላከያ ሠራዊት ደም የመለገስ፣ የገንዘብና ሌሎች ድጋፎችን ለማድረግ የገቡት ቃል የሚበረታታ መሆኑን በማንሳት ኢትዮጵያ የገጠማትን ችግር በተባበረ ክንድ በማለፍ አዲስ ታሪክ የሚጻፍበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን አክለዋል።
በውይይቱ የትግራይ ተወላጅ አርቲስቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ ምሁራንና የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላት ተሳትፈዋል።
ሐሴ 6/2013 (ኢዜአ)