07/09/2021
የአንድት ፈትል ውሉ ከተወሳሰበ፣ ሊቃቂቱ ተጎልጉሎ ከጥቅም ውጭ ይሆናል። ውሉ ከተገኘ ደግሞ ቋጠሮው ተፍትቶ ልቃቂቱ ድርና ማግ ይሆናል። የአገራችንም ጉዳይ ውሉ እንደ ጠፋ ሊቃቂት ተወሳስቧል። ለችግሮቻችን መፍቻ ናቸው ተብለው እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችም በውስጣቸው ሌላ ቅራኔ ያረገዙ በመሆናቸው፣ ይበልጡኑ ነገሮችን እያወሳሰቡ ናቸው።መቼም ቢሆን ስንኮፉ ካልወጣ ቁስል አይድንምና፣ የችግሮቻችን ሰንኮፉ ምንድነው? ብለን ብንጠይቅ፣ መልሱ የቅራኔዎች አያያዝና አፈታት ችግር ነው ለማለት ይቻላል። ቅራኔዎቹ ደግሞ ደርጃና የአፈታት ቀደም ተከተል አሉአቸው።
ቅራኔን በሚመለከት ከሁሉም የከረረው ጭቁን ሕዝቦች፣ከወራሪ የፋሺሽት ፓርቲዎች፣ከአክራሪ እምነት ተከታዮችና ከብሔር ትምክህተኞች ጋር ለነጻነታቸው የሚያደርግት ትግል ነው ይባላል።የዚህ ዓይነቱ ቅራኔ ሁሉንም መደብ የሚያስተባብር፣ የብሔር ቅራኔንም ለጊዜው የሚያለዝብ፣ መሠረታዊ ቅራኔ ነው።
ስለዚህም ነው የሕዳሴ ግድባችን ጉዳይ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን የእግር እሳት የሆነው። የብሔር፣ የክልልና የወስን ጉዳይም እንዲሁ፣ ሁሉንም መደብ አስተባብርሮ በአንድ ግምባር እያሰለፈ ነው ያለው።ከዚህ የተነሳም ነው የትግራይ ገበሬና ካህናቱ ሳይቀሩ ሁሉም በጅምላ ከሕወሐት ጎን የተሰለፉት።በአንጻሩ የመደብ ትግል የአንድ ብሔር አባላትን፣የአንድ እምነት ተከታዮችን በያመዳባቸው ይከፋፍላል። ከተመሳሳይ የመደብ አባላት ጋር ደግሞ ያስተባብራል።
ከዚህ አንጻር የብልጽግና ፓርቲ ሲታይ ከብሔር አንጻር የተሰባሰበ አይደለም።ሁሉንም ብሔር ያቀፈ ነውና።ከመደብ አንጻርም የተሰባሰበ አይደልም። ብሔራዊ ከበርቴውን፣ አቀባባይ ከበርቴውን ፣የንዐስ ከበርቴ አባል የሆኑትን፣ ምሁር፣ ተማሪና ገበሬውን፣ዓላም አቀፋዊ ርዕዮተ ዓለም ያለውን የፋብሪካ ሰራተኞችን በአንድነት አጭቆ ይዟልና።
ስለሆነም ይህን ሁሉ በአንድነት አቅፎ የየትኛውን መደብ ጥቅም ሊያስከብር፣ የመንን ርዕዮት ዓለም ሊያራምድ ነው? የአሐዳዊያንን ጥያቄ ሲያራምድ የፌድራሊስቶች ፈቃድ ይደፈጠጣል።የሠራተኛውን መደብ ጥቅም ሲያስከብር፣ የብሔራዊ ከበርቴው ጥቅም ይጎዳል።ከሶሻሊስቶች ጎራ ሲሰለፍ የካፒታሊስቱ ጎራ ያኮርፋል።ታዲያ ለዚህ ምን ይሻላል። የኃይል ሚዛኑ ወዴት ያመዝናል።ይህንና መስለ ችግሮችን በማመዛዘን ስህተትን አርሞ የጎደለውን አሟልቶ፣ የተጣመመውን አቃንቶ ፣የብሔር ብሔረሰብን መብት አክብሮ፣ቅራኔዎችን በማለዘብ አገሪቱን ከጥፋት፣ ኅብረተሰቡ ከርስ በርስ ጥላቻ በመታደግ፣ ተስማምተው፣በእኩልነትና በነፃነት ጎን ለጎን የሚኖሩበትን ሠለማዊ ሁኔታ ማመቻቸት ይገባል።
ይህ ችግር ጊዜያዊ ነውና ያልፋል።ነገር ግ ን የማያልፈው የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክ፣ ነገ እንዳይወቅስን፣ በሚያልፍ ሥልጣን፣ የማያልፍ ታሪክ ማስመዝገብ ይገባናል።ከዚህም በለይ ልብና ኩላልትን የሚመርምር አምላካችን ከእኛ ጋር ነውና እርሱም የታዘበናል፣ስለሆነም እርሱንም የሚያስደስት መልካም ነገር ፈጽመን ለመገኘት መጣር ይኖርብናል። ሰላም ነፃነትና እኩልነት ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ!!!
ጆቢር ሔይኢ፣ ከሁስተን ቴክሳስ።