መሰረት ተስፉ ([email protected])
እንደሚታወቀው የዩጎዝላቪያ ፈዴራላዊ ስርዓት አወቃቀር ማንነትንና ታሪካዊ ትስስርን መሰረት ያደረገ ነበር። የኢትዮጲያ የፌዴራል ስርዓትም በሸፍጥና በሴራ የተተበተበ ቢሆንም ከዩጎዝላቪያ ጋር ተመሳሳይ ሊባል በሚችል መልኩ ከሞላ ጎደል ማንነትን፣ ቋንቋንና ታሪካዊ ትስስርን መሰረት አድርጎ የተዋቀረ ስርዓት ነው።
በሁለተኛ ደረጃ ዩጎዝላቪያን ሲያስተዳድራት የነበረው ዮጎዝላቪያ ኮምዩኒስት ሊግ (League of Communists of Yugoslavia) ተብሎ የሚታወቅ ፖለቲካ ፓርቲ ነው። ይህ ፓርቲ በስድስቱም የዩጎዝላቪያ ክልሎች ቅርንጫፍ ፅ/ቤቶች ነበሩት። ኢትዮጵያም በየክልሎቹ አባል ወይም አጋር ድርጅቶችን ባቀፈው ኢህአዴግ ስትተዳደር ቆይታለች።
በሶስተኛ ደረጃ ሁለቱም ሃገሮች በአንድ ወቅት ጠንካራ ናቸው ተብለው በሚታወቁ ሰዎች ተመርተዋል። በዚህም መሰረት ዩጎዝላቪያ ስልጣን ላይ እንዳሉ ህይወታቸው ባለፈው “አምባገነኑ” ግን ደግሞ “ተወዳጁ” ፕረዚደንት ጆሲፕ ብሮዝ ቲቶ (Josip Broz Tito) ስትመራ ነበር። ኢትዮጵያም እንዲሁ ስልጣን ላይ እያሉ ህይወታቸው ባለፈው “ብሩህ” ግን ደግሞ “ከፋፋይ” ፣ “ብልጣብልጥና” “አምባገነን” ተብለው በብዙ ሰወች ዘንድ በሚታወቁት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ስትመራ ቆይታለች። እነዚህ የሁለት ሃገር መሪዎች ፀረ-ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ቢሆንም በየሃገሮቻቸው ተነፃፃሪ የሆነ ሰላምና የኢኮኖሚ እድገት በማስፈን ይታወቃሉ።
ከሁለቱም ሃገራት መሪዎች ህልፈተ-ህይወት በኋላ ግን ይህ በየሃገራቱ የነበረው ተነፃፃሪ ሰላምና የኢኮኖሚ እድገት ፈተና እንደገጠመው ይታውቃል። በዮጎዝላቪያ ሁኔታ ከፕሬዚደንቱ ህልፈት በኋላ (በየክልሎቹ ይነሱ የነበሩ የመገንጠል ፍላጎቶችን ጨምሮ) ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄቀችን መፍታታት አዳጋች እየሆነ ሄደ። ይህን ሁኔታ ያባባሰው ደግሞ በስሎቮዳን ሚሎሶቪች (Slobodan Milošević) ይመራ የነበረው የሰርቢያ (Serbia) ሃይሎች የበላይነት ዝንባሌና የሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን ጥያቄወች የማፈን አቅጣጫ ነበር። እነዚህና ሌሎች መሰል ችግሮች ተደማምረው ሃገር አቀፍ ፓርቲ የነበረውን የዮጎዝላቪያ ኮሙዩኒስት ሊግ እንዲፈርስ አደረጉት። ይህ አገር አቀፍ ፓርቲ ከፈረሰ በኋላ ማንነትን ማዓዕከል አድርገው በየቅርንጫፍ ፅ/ቤቱ የተደራጁት የየክልሉ ኮሙዩኒስት ድርጅቶች ራስ ራሳቸዉን ችለው ሶሻሊስት ፓርቲ ሆነው ቀጠሉ። በመጨረሻም ሁኔታው እየተባባሰ ሄዶ ከብዙ በማንነት ላይ ያተኮረ የእርስ በእርስ ግጭት በኋላ ዩጎዝላቪያ ከአለም ካርታ ላይ ጠፋች።
ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ ከአቶ መለስ ህልፈት በኋላ አቶ ሃይለማሪያም አቀናጅተው መምራት ባለማቻላቸው ምክንያት ሃገራችን ዘጠኝና ከዚያ በላይ ትንንሽ ሃገራት ልትሆን ተቃርባ እንደነበር ሁላችንም እናውቃለን። የዚህ ችግር ዋነኛ ምክንያቶች ደግሞ የህወሃት ሰዎች ረጃጅም እጆች እንደነበሩ ግልፅ ነው። በአጋጣሚ ግን ዶ/ር አብይ ወደስልጣን መጥተው የኢትዮያን ስም ከፍ ከፍ አድርገው በመጥራታቸው ምክንያት በጣም ተመናምኖ የነበረው የአንድነት መንፈስ ነብስ መዝራት ጀምሮ እንደነበር ሁላችንም እንረዳለን ብየ እገምታለሁ። በተጨማሪም የብሄር ድርጅቶች ግንባር የሆነው ኢህአዴግ ከስሞ በምትኩ ብልፅግና የሚባል “ሃገራዊ ፓርቲ” ሲቋቋምም ተስፋው የበለጠ ጨምሮ ነበር። በነገራችን ላይ የዚህ ፓርቲ አወቃቀር ልክ እንደዮጎዝላቪያው ሁሉ ሃገራዊ ሆኖ በአስሩ ክልሎችና በሁለቱ ከተማ መስተዳድሮች ቅርንጫፍ ፅ/ቤቶች አሉት።
በዚህ ፅሁፍ ውስጥ ከፍ ብሎ ከተገለፁት ነጥቦች መረዳት የሚቻለው በኢትዮጵያና በዮጎዝላቪያ ስርዓታዊ አወቃቀር ዙሪያ ተመሳሳይነት ያለ መሆኑን ነው። እዚህ ላይ ሊነሳ የሚችለው ጥያቄ ከስርዓታዊ አወቃቀር በመለስ ባሉ ጉዳዮችስ በሁለቱ ሃገሮች እጣ ፋንታ ዙሪያ መመሳሰል ሊኖር ይችላል ወይ የሚል ነው። የዚህን ጥያቄ መልስ የሚወስነው ደግሞ አሁናዊዩ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ሁኔታ ነው። የፖለቲካ ሂደቱ ተቋማዊ አሰራርን አዳብሮ፣ ፍትሃዊና ግልፅ በሆኑ ህጎች እየተመራ፣ ሙስናንና አድሎን በመፀየፍ፣ የሁሉንም ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች መብትና ጥቅም በእኩልነትና ዕኩል ተጠቃሚነት መንፈስ ማስከበር የሚችል ከሆነ ኢትዮጵያ ውስጣዊ አንድነቷን አጠናክራ ለውጭ ጥቃት የማትቀመስ ሆና መቀጠል የምትችልበት እድሏ ሰፊ ነው።
ነገር ግን አሁን እንደሚታየው ፖለቲከኞች በባለጊዜነት አዙሪት ውስጥ ገብተው በስውርም ሆነ በግልፅ የየራሳቸውን ቡድን ጥቅም ብቻ ለማስከበር ያሻቸውን እየፈፀሙ ሌሎችን ለመድፈቅ የሚሞክሩ ከሆነ የአብሮነት ስሜት መሻከሩ አይቀርም። በተለይ ደግሞ የፖለቲካ ስልጣኑ ውስጥ ረጃጅም እጆች ያሉት ቡድን በጥሎ ማለፍ አረንቋ ውስጥ ተዘፍቆ የሌሎችን እኩልነት፣ እኩል ተጠቃሚነት፣ ነፃነት እና የመሳሰሉ መብቶችን በመድፈቅ አገዛዜን አስቀጥላለሁ የሚል ከሆነ የተገፊነት ስሜት የሚያድርባቸው ክልላዊ ቅርንጫፍ ፅ/ቤቶ ሳይወዱ በግድ ሌሎች አማራጮችን ወደማማተር መግባታቸው አይቀርም። ከአማራጮች ውስጥ አንዱ ደግሞ ክልሎች የየራሳቸውን ፖለቲካ ፓርቲ አቋቁመው አገር ለመመሰረት መንቀሳቀስ ይሆናል። በዚህ ሂደት ጫናንና አፈናን እንደምርጫ አድርጎ የሚወስድ ሃይል ካለ ደግሞ የዮጎዝላቪያው አይነት ቀውስ መፈጠሩ አይቀርም።
ስለዚህ ኢትዮጵያንና ዮጎዝላቪያን በማነፃፀር የሚቀርቡ ስጋቶችን በሟርትነት ከመፈረጅ ይልቅ እንደ ማንቂያ ደውል አድርጎ በመውሰድ ምርጫንና መንገድን ማስተካከል ጠቃሚ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ።