December 10, 2020
2 mins read

ጊዜው (ዘ-ጌርሣም)

ጊዜ ማለት ዛሬ
የትናንቱ ወሬ
የነገው ተስፋ ነው
መንገድ የሚጠርገው
ፅፎ ያልፋል
ይናገራል
ያስነግራል
ያስተርታል
ያሳድማል
ያስዶልታል
ያሳስራል
ያስገርፋል
ይገላል
ያስገድላል
ያንገላታል
ያሰድዳል
ያዋርዳል
ይከዳል
ያስከዳል
ከፍታ ላይ ያወጣል
ጠብቆ ይጥላል
አመድ ትቢያ ያለብሳል
ጊዜ ንጉሥ ነው
ራሱን ነው የሚሾመው
ህግና ደንብ አለው
የፈለገ ኃይል ቢነሣ
እያገሳ እንዳንበሳ
ማንም አይደፍረኝ ብሎ
ተገዝቶና ምሎ
በዕብሪት
በትቢት
በባዶነት
ተኩራርቶ
በጉልበት ተመክቶ
በአውሬነት
በአርመኔነት
እንደ ድብልብል ድንጋይ
የሚንደባለል መውደቂያውን ሳያይ
ጊዜው !
ጥሩ መምህር ነው
ጎበዝ ተማሪ ከገጠመው
ከትናንቱ ተምሮ
የዛሬውን መርምሮ
የነገውን ለማየት
ክፉና ደጉን በመለየት
ስለ አለፉት አወዳደቅ
ቆም ብሎ በመጠየቅ
ዛሬን በጥበብ አልፎ
ስብራቱን አስደግፎ
በመጠገን አስተቃቅፎ
መጭውን ያዘጋጃል
የሰላም ቅብብሉን ያመቻቻል
ጊዜ ወርቅ ነው
ላወቀበት ማጌጫው
ለማይገባው መውደቂያው
የመጨረሻ መጥፊያው
ያውም እስከ ወዲያኛው
ጊዜ ፍትሐዊ ዳኛው
የእጅን የማይነሳው
የማያዳላ ሚዛን ነው
ትናንት ሌሎች ሲወድቁ
የሕዝብ አስተያየት እየናቁ
ከእኛ በላይ ማን ኑሮ
አውቆና ተመራምሮ
የማንስ ጉልበት ሊቋቋመን
አሽንፋለሁ የሚለን
በማለት ሲምሉ ሲገዘቱ
ጊዜው ደርሶ ሲረቱ
ምን ያተርፋል ቢፀፀቱ
ጊዜ እንደሁ አይመለስ
በደል በፀፀት ለመካስ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop