December 18, 2019
13 mins read

የአገሪቱን ሀብት ሲበዘብዙ የነበሩ ኃይሎች ዛሬ ደርሰው ለፌዴራሊዝም ጠበቃ ነን ሲሉ ለእኔ የሚመስለኝ ኢትዮጵያውያን ላይ ማሾፍ ነው” – ዶክተር ዓለሙ ስሜ በጠ/ሚ ጽ/ቤት ሚኒስትር

index 300x204 1

ክልሎችን እኛ እናውቅልሃለን በማለትና የአገሪቱን ሀብት ሲበዘብዙ የነበሩ ኃይሎች ዛሬ ደርሰው ለፌዴራሊዝም ጠበቃ ነን ሲሉ ለእኔ የሚመስለኝ ኢትዮጵያውያን ላይ ማሾፍ ነው”

ዶክተር ዓለሙ ስሜ በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ግንባታ ማዕከላት አስተባባሪ

• ለፌዴራሊዝም ጠበቃ ለመቆም የሚጥረው ኃይል ትላንት እዚህ አገር እውነተኛ ፌዴራሊዝም እንዳይሰፍን ሲያደርጉ ከነበሩት ውስጥ ግንባር ቀደም ሚና ሲጫወት የነበረው ሀይል ነው፤

• የኢትዮጵያ ህዝብ የጠየቀው እውነተኛ ፌዴራሊዝምን እንጂ ፌዴራሊዝም አልጠቀመኝምና ወደኋላ ይመለስ አላለም። በመሆኑም አዲሱ ፓርቲ ፌዴራሊዝምን ወደኋላ የሚተው ጅላጅል ፓርቲ አይደለም፤

• የብልፅግናን ፓርቲን የተቀላቀልነው እውነተኛ የፌዴራሊዝም አቀንቃኞች ነን። ሶስቱ በኢህአዴግ ውስጥ የነበሩና አምስት አጋር የነበሩ ድርጅቶች ናቸው፣

• በኢህአዴግ የተዛባውን የፌዴራሊዝም ስርዓት ለማስተካከል የታገሉ፣ ለውጡን በማምጣት ግንባር ቀደም ሚና የተጫወቱ በመሆናቸው ፌዴራሊዝምን ለማስተካከል ይሰራሉ።

• ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ ፌዴራሊዝምን ሳይቀበል የሚንቀሳቀስ ግለሰብም ይሁን ፓርቲ ራሱን በራሱ የሚያጠፋ ነው። ህዝቡ አይከተለውም።

• አሁን ያለው የለውጥ አመራር ፌዴራሊዝምን ለማፍረስ ነው የሚሰራው የሚለው ክስ ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ ይመስለኛል።

• ባለፉት 28 ዓመታት በፓርቲ ማዕከላዊነት የተጠረነፈ፣ ክልሎች ነፃነት የሌላቸው፣ የራሳቸውን የክልል መስተዳድር፣ ካብኔ ነፃና ህገ መንግስታዊ በሆነ መንገድ ማዋቀር የማይችሉበት ፌዴራሊዝም ነበር፣

• በፌዴራል ደረጃ እኩል የመወሰን እድል የተነፈገበት ስርአት ነበር፤ ብዙ ቋንቋ ተናጋሪ እያለን እንኳን በፌዴራል ደረጃ አንድ ቋንቋ ብቻ ነው ስራ ላይ የዋለው፤

• ችግሮች ከፈጠሩት መካከል ግንባር ቀደሙ በአሁኑ ወቅት የፌዴራሊዝም ጠበቃ እኔ ነኝ የሚለው። ይህ ጠበቃ ነኝ ባይ የፌዴራሊስት ኃይሎች በሚልም ደጋፊ ለማሰባሰብ ጥረት እያደረገ ነው፤

• ከዚህ አንፃር ጠበቃ ነኝ ባዩ የሞራል ብቃት የለውም። በጥቅሉ የፌዴራሊዝም ጠበቃ እኔ ነኝ የሚለው አካል ግንባር ቀደም ችግር ፈጣሪ ነበር።

• አጋር ፓርቲዎች ሲባሉ የነበሩት ከማንም በላይ እውነተኛ ፌዴራሊዝም ባለመኖሩ የተጎዱት ናቸው፤ እውነተኛ ፌዴራሊዝምን ፍለጋ ውህድ ፓርቲውን ፍለጋ እየተንቀሳቀሱ ያሉት።

• ስለዚህም በአሁኑ ወቅት አዲሱን ፓርቲ የመሰረቱት ለእውነተኛ ፌዴራሊዝም የታገሉ ናቸው።

• ፌዴራሊዝም በኢትዮጵያ ህገ መንግስታዊ ነው። ማንም ተነስቶ ፌዴራሊዝምን በማፍረስ አሃዳዊ መንግስት ሊመሰርት አይችልም፤ህገ መንግስቱ በፍፁም አይፈቅድም።

• የውሸት ምርጫና መድብለ ፓርቲ ነበር ያለው። በአሁኑ ወቅት ለውጡ ከሌሎች ጥያቄዎች ጎን ለጎን በዋነኝነት ምላሽ የሰጠው ለዴሞክራሲ ጥያቄ ነው።

• ዴሞክራሲ እንደሚታወቀው በሂደት የሚመጣ ነው። ባህሉን ገና አላጎለበትንምና ብስለትና ቁርጠኝነት ከሁሉም ዜጎች ይጠበቃል።

• መንግስት ዴሞክራሲን ተገን በማድረግ የሚፈጸሙ ወጣ ያሉ ነገሮችን በትዕግስት በማለፉ ትዕግስቱ ወሰን እንዳጣ አድርገው የተናገሩ አሉ፤

• መንግስት ወደ ድሮ ማንነቱ ማለትም አስሮ ገራፊነት እንዲመለስ የሚገፋፉም አልታጡም።ጉዳዩ የህዝብንና የመንግስትን ማስተዋል ይጠይቃል።

• የሃይማኖት መሪዎች፣ ምሁራን፣ ህዝቡ ሁሉ ከለውጡ ጎን ቢቆሙ መልካም ነው።

• ኢትዮጵያ ውስጥ በተደጋጋሚ የለውጥ እድሎች መጥተዋል፤ ግን አልተጠቀምንባቸውም። ሁሉም የለውጥእድሎች በአግባቡ ስላልተመሩ ለውጦቹ አልጠቀሙንም፤ እንዲያውም ከመፍረስ አፋፍ እየተመለስን ተርፈናል ማለት ያስደፍራል።

• አብዮታዊ ዴሞክራሲ ያጎደለው አንዱ ህብረተሰብን በጎራ መለየቱ ነው። ለምሳሌ ባለሀብትን ብንወስድ ልማታዊ ባለሀብት ይላል፤ ኪራይ ሰብሳቢ ባለሀብትም ይላል። ሁለቱ የተለዩበት ግልፅ የሆነ መስፈርት የለም።

• ነገር ግን ልማታዊ የተባለው በላቡና በድካሙ ያገኘ የሚመስል ሲሆን፣ ኪራይ ሰበብሳቢው ደግሞ አጭበርባሪውን ለማለት ሊሆን ይችላል።

• ይሁንና በተጨባጭ ሲታይ ግን ልማታዊዎቹ ወደኢህአዴግ የተጠጉ ሲሆኑ፣ ኪራይ ሰብሳቢ የሚባሉት ደግሞ ኢህአዴግን ያልተጠጉት ናቸው።

• ከለውጡ በኋላም ሆነ ወደ ለውጡ ስንሄድ እውነታው ግን ሌባ በመሆን የበዛው መንግስትን የተጠጋው ነው።

• ልማታዊ ባለሀብቱ ከመንግስት ሹማምንት ጋር የተጠጋው ነው። በማጭበርበርና በመስረቅም ይታወቃል።

• አብዮታዊ ዴሞክራሲ ምሁራንንም ተራማጅ እና ወላዋይ በማለት ይጠራቸዋል። ይህም ከኢህአዴግ ጋር ካለው ቅርበትና ርቀት ይነሳል። ምንም መስፈርት የለውም፤

• ኢህአዴግን የተጠጋው ምሁር አልምጥም ይሁን ለአገር አሳቢም ይሁን ተራማጅ ይባላል፤ ከኢህአዴግ የራቀው ደግሞ የቱንም ያህል ታታሪ ይሁን እንደጠላት ተቆጥሮ ወላዋይ ይባላል።

• የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አግላይነት ነው። አርብቶ አደሩ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ማህበራዊ መሰረት ሊሆን አይችልም የሚል ነው።

• እንዲህም ሲባል አርብቶ አደሮች ገና ያልነቁና በጎሳም የሚተተዳደሩ ስለሆኑ ማህበራዊ መሰረትን ሊሸከሙ አይችሉም በሚል ነው።

• ይሁንና አርብቶ አደሮች በኦሮሚያም ሆነ በደቡብ ክልል አሉ፤ እነዚህ ግን አልተገለሉም።

• አርብቶ አደሮች የደኢህዴን የኦዲፒ ማዕከላዊ ኮሚቴ አልፎ ተርፎ የኢህአዴግ ምክር ቤት አባል ሆነው ሲያገለግሉ ይስተዋላል።

• ሐረሪን ብንወስድ እንኳን አርብቶ አደር ቀርቶ አርሶ አደር እንኳ የሌላትና በንቃተ ህሊና ከተባለ ከሌሎች ተሽላ የምትገኝ ናትና የሚሰራ አይደለም፤ ስለዚህ አርብቶ አደር ስለሆኑ ነው የተውኳቸው የሚለው አመክንዮ አይሰራም።

• ብልፅግና ፓርቲ አካታች ነው ሲባል የሚቀር የለም ለማለት ነው። ለሁሉም በሩ ክፍት ነው። በጥቅሉ ይህንን አያቅፍም ተብሎ የሚገለል የለም።

• መደመር የዜጎችን ጤና እንደ አንድ ግብ የሚይዝ ሲሆን፣ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ግን የዜጎችን ጤና የምጠብቀው እንዲያመርቱ ነው ይላል። በዚህም ነው ብልፅግና ሁሉን አቀፍ ነው የሚባለው።

• መደመር ከዴሞክራሲ አኳያ የዜጎች፣ የቡድንና የግለሰብ መብቶች እኩል መከበር አለባቸው ይላል። መደመር ከሰው ማንነት ይጀምራል።

• ብልፅግና ፓርቲ ስልጣን ላይ ለመቆየት የሚያስችለው ህጋዊ ምክንያት አለው። የመጀመሪያው ብልፅግና ፓርቲ የኢህአዴግ ወራሽ ነው። ይህን የመረጠው ኢህአዴግ ራሱ ነው። በውስጡ ያሉ ከሞላ ጎደል የኢህአዴግ አባላት ናቸው።

• በሐዋሳ በተካሄደው 11ኛው የኢህአዴግ ጉባኤም የኢህአዴግ ምክር ቤት አዲሱን ፓርቲ እንዲመሰርት ውክልና ሰጥቶታል።

• ውህደት ምክር ቤቱ ኢህአዴግ ያለው መብትና ግዴታ በሙሉ ወደ አዲሱ ፓርቲ እንዲዞር ስላደረገ ህጋዊም ፖለቲካዊም ስልጣን አለው ማለት ነው።

• የአገሪቱን ሰላምና ህልውና ለአደጋ ለሚዳርግ ሁኔታ ያበቃው አንዱ ችግር የሌሎች መብቶች አለመከበር ነው፤ይህ እንዳለ ሆኖ በልዩነት ላይ የተሰራው ስራም ዛሬ እያየን ያለነውን በጎ ያልሆነ ነገር አስከትሏል።

• በ27 ዓመት ውስጥ በሰራናቸው ልዩነቶች ሳቢያ በሁለት ግለሰቦች መካከል ግጭት ሲፈጠር ወይ ወደ ሃይማኖት አሊያም ወደ ብሄር ግጭት እንዲለወጥ የሚያደርጉ ነገሮች እየተፈጠሩ ነው።

• ሙስሊም ከክርስቲያን ፣ ኦሮሞው ከአማራው እንዲሁም ትግራዩ ከሌላው ጋር ተጋብቷል። አንዱ ብሄር ከሌላው ብሄር ጋር በመጋባት ተሰናስሏል። በዚህም ሁሉም ተጋምዷል ማለት ይቻላል።

• ብቻውን እንደ ደሴት የተገነጠለ ዘር የለም። ከመተሳሰሩም የተነሳ የአንዱን ሃይማኖት በዓል የሌላ ሃይማኖት ተከታይ ያከብረዋል።

• አብዮታዊ ዴሞክራሲ ያጎደላቸውንና መደመር የሞላቸውን በመያዝ ልዩነቱን ለማሳየት ያህል የመደመር ሐሳብ ያለፈውን በጎ ነገር በማስቀጠል ስህተቶችን ያለማወላወል በማረም ለመጪው ትውልድ ጥቅምና ፍላጎት አሟልቶ አቅርቧል።

ምንጭ አዲስ ዘመን

1 Comment

  1. ወይ ጉድ! ደግሞ አለሙ ስሜ የትህነግ ወቃሽ ይሁን??? የኦሮሞ አርሶ አደሮችን ከቀዬአቸው በማፈናቀል መሬቱን ሲቸበችብ የነበረው ቀንደኛው ጅብ ማን ሆነና ነው እዚህ የሚያላግጥብን?? የአቢይ መንግስት በስም እንጂ በአሰራሩ ያልተቀየረ የድሮው ኢህአደግ መሆኑን ዋናው አመላካች እንደ አለሙ ስሜ ያሉ ገዳይና ዘራፊዎች ” !! በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ግንባታ ማዕከላት አስተባባሪ !! ” ይታያችሁ ያውም “የዴሞክራሲ ግንባታ አስተባብባሪ” ተብለው መቀመጣቸው ነው!!

Comments are closed.

Previous Story

ሱሰኛ አማራ ሆይ! ተሱስህ ተላቀህ ወደ ጎበዝ አለቃህ! – በላይነህ አባተ

Next Story

ይብላኝ ወንድሜ፣ ላንተ ይብላኝ! – ወለላዬ ከስዊድን

Latest from Blog

አስቸኳይ ህዝባዊ ጥሪ

July 24, 2024 ዓለማቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት Global alliance for the Rights of Ethiopians (GARE) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሳቻ ጎዝዲ ቀበሌ በደረሰው የመሬት መንሸራተት የብዙ ወገኖቻችንን ህይዎት ማለፉን
Go toTop