October 13, 2019
ጠገናው ጎሹ
እንደ መግቢያ የሚከተለውን ልበል
አልፎ አልፎ ግለሰቦች በሚያቀርቧቸው የፖለቲካ አስተሳሰቦች ፣ አስተያየቶች ፣ ትንታኔዎችና ድምዳሜዎች ላይ አስተያየት የምሰጠው ከግለሰቦች የግል ባህሪ (ሰብእና)፣ ህይወት (አኗኗር) እና ከአገር ጉዳይ ጋር ባልተያያዘ ጉዳይ ላይ ከሚኖራቸው አስተሳሰብ ጋር ጉዳይ ስላለኝ ፈፅሞ አይደለም ። የሚያቀርቧቸውን ጉዳዮች የሚያቀርቡበት ፣ የሚያዩበትና የሚደርሱበት ድምዳሜ ገና በቅጡ ካልተጀመረው ከመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግርና ምሥረታ አንፃር ሲታይ አነጋጋሪነት ስለሚኖረውና ይህንንም በግልፅና በቀጥታ ማሄስ (መተቸት) ተገቢ ወይም አስፈላጊ ነው የሚል ፅዕኑ እምነት ስላለኝ ብቻ ነው ።አዎ! አስፈላጊ ወይም ተገቢ ሆኖ ሲገኝ አካፋን አካፋ ማለት ትክክል ነውና።
እንደ አንድ የአገሩ ጉዳይ እንደሚያሳስበው ተራ ኢትዮጵያዊ በህዝብ የሚታወቁ ፖለቲከኞችንና አክቲቪስቶችን ንግግሮች በአዳራሽ ውስጥና በአደባባይ ህዛባዊ ስብሰባዎች በአካል በመገኘት የሚነሷቸውን ጉዳዮች ለመረዳት ሞክሪያለሁ /እሞክራለሁም ።
ብዙዎችን ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች ደግሞ የፖለቲካ አስተሳሰባቸውንና አስተያየታቸውን በልዩ ልዩ መገናኛ ብዙን ሲያቀርቡ ፣ በፅሁ አስፍረው ሲያስነብቡ ፣ እና በተለያዩ ፖለቲካዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ሲሳተፉ በቅርብና በጥሞና ተከታትያለሁ /እከታተላለሁም።
ወደ ዋናው ጉዳዬ ልለፍ +የኦሮሚያው ገዥ ፣ በተረኝነት ስሜት ህወሃትን የተካው ኦዴፓ ከፍተኛ አመራር አባል እና ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ታማኝ ጓዶች አንዱ የሆነው አቶ ሽመልስ አብዲሳ የፖለቲካ ጨዋታ መድረክ ባደረገው የኢሬቻ በዓል ላይ የተናገረውን ሃላፊነት የጎደለውና አደገኛ ንግግር አስመልክቶ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በቀጥታም ባይሆን አጠቃላይ (ደምሳሳ) በሆነ አቀራረብ “እያረምን ወይስ እያበድን እንሂድ” በሚል ተረታዊ ምሳሌነት ርዕስ ጀምሮ “እያረምን እንጅ እያበድን አንሄድም” በሚል የቋጫትን ፅሁፍ አነበብኳት ። በአንድ የቴሌቪዥን መስኮት በኩልም ከተናጋሪው በላይ ተናጋሪውን ተከላካይ በመሆን የሰጠውን አስተየት ሁሉንም ባይሆን ሊያስተላልፍ የፈለገውን የተከላካይነት ዋና መልእክት አዳመጥኩት ።
ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ካለው ንቁና የማያቋርጥ (active and continuous) ተሳትፎ አንፃር ትኩረቴን ከሚስቡ ወገኖች መካከል አንዱ ነው። በግል/በአካል (in person) አላውቀውም። አብዛኛዎቹን የሚፅፋቸውን ፅሁፎቹንና በልዩ ልዩ መድረኮች የሚያደርጋቸውን ዲስኩሮቹን (ንግግሮቹን) ተከታትያለሁ አሁንም እከታተላለሁ ።
ከለውጥ ብልጭታው ወዲህ ደግሞ ከፅሁፍና ከንግግር አልፎ በሚገርም ፍጥነትና አኳኋን የለውጥ አራማጅ ከምንላቸው ፖለቲከኞች ጋር ሽርጉድ በማለት የየሚዲያውን ካሜራ ትኩረት ለመሳብ መቻሉን ታዝቤያለሁ ። ሽር ጉዱ ነውር ነው የሚል ደምሳሳና ደንቆሮ አስተያየት የለኝም ። የሽር ጉዱ መነሻና መዳረሻ መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግርና ምሥረታ ነው ወይ? ከሆነስ ሽር ጉዱ እውን ይህን የተቀደሰ ተልእኮና ተግባር ለማገዝ የሚያስችል ባህሪ የተላበሰ ነው ወይ? ብሎ መጠየቅ ግን በእጅጉ ተገቢ (ትክክል) ነው ብየ አምናለሁ። ምክንያቱም የእልፍኝ ወይም የአዳራሽ ወይም የአደባባይ ሽር ጉድ እና እፁብ ድንቅ ዲስኩር መሬት ላይ ወርዶ መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግርና ምሥረታ እውን እንዲሆን ለማድረግ እስካላስቻለ ድረስ ከፋይዳ ቢስነቱ በላይ ማታለያነቱ (ማዘናጊያነቱ) አስከፊ ነው ።
ዲያቆን ዳንኤል በፅሁፍና በንግግር ያለውን የአቀነባበርና የአቀራረብ (articulation and presentation) ችሎታ አሳንሶ ለማየትና ለማሳየት አልፈልግም ። ትክክል አይሆንምና ። አንፃራዊነት እንደ ተጠበቀ ሆኖ በዚህ ረገድ ያለው ችሎታ የሚታማ አይመስለኝም። ፅሁፎቹም ሆኑ ዲስኩሮቹ ጨርሶ እውነትና ጠቀሜታ የላቸውም የሚል የድንቁርና ግንዛቤና ግምገማም የለኝም ።
እነዚህን ችሎታዎቹን ለምንና እንዴት ነው የሚጠቀምባቸው? የሚለውን ጥያቄ የማንሳቱ አስፈላጊነትና ትክክለኝነት ግን ነገሮችን በጥሞና ለሚያይና ሚዛናዊ አስተሳሰብ ላለው የአገሬ ሰው አጠያያቂ አይመስለኝም።
ቀደም ብሎ (ከለውጥ ብልጭታው በፊት) በታዳሚዎቹ ዘንድ ከነበረው በስሜታዊነት የተሳከረ አድናቆት ላይ በዚህ ብልጭና ድርግም እያለ እያስቸገረን ባለው የለውጥ ብልጭታ ውስጥ የሚያሳየው ሽር ጉድ ሲጨመርበት ሊያስከትል የሚችለውን ይበልጥ መሳከር መገመት አያስቸግርም። “የለውጥ አራማጅ ሃይሎች ጥፋትም ሆነ ልማት ለእኔ ስለሚታየኝና ስለምንመካከር ሃሳብ አይግባችሁ” የሚል አይነት የለየለት ግብዝነትን ሊያስከትል ይችላል። ይህም ከሰሞኑ ከአዝማሚያነት አልፎ በግልፅ የሚታይ ሆኗል ።
የኦሮሚያው ገዥና ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩት ድርጅት ከፍተኛ አባል አቶ ሽመልስ አብዲሳ በአደባባይ የተናገረውን ወይም ያወጀውን “የድል አድራጊነት” አዋጅ “ባይነገር ጥሩ ነበር ፤ ቢሆንም ግን ታስቦበት የተነገረ ነው ብየ አላምንም … ” በሚል አይነት እጅግ የወረደ አስተሳሰብ ከዲያቆን ዳንኤል ክብረት ሰምተናል ። የአያሌ ንፁሃን ዜጎችን ትእግሥት በከፍተኛ ሁኔታ የተፈታተነውን የፖለቲካ እብደት ተራ የምላስ ግድፈት (ወለምታ) አስመስሎ ለማሳመን ከመሞከር የበለጠ ግብዝነትንና እውነትን ከወሸት ጋር የማምታት ( hypocritical and delusional ) አስተሳሰብንና ባህሪን የሚያሳይ ዋቢ የለም።
ዲያንቆን ዳንኤል ይህን ለምን እንደሚል ቢጠየቅ ያው የፈረደበትን የክርስቶስ አስተምህሮት እና ከየመፃህፍቱና ከየማህበረሰቡ የሚቃርማቸውን ትርክቶች በሚመቸው መንገድ በመተርጎም “ለአገር መረጋጋት ፣ ለለውጡ በድል መገስገስ ፣ ለሰላምና ለፍቅር ሲባል ነገሮችን በቀላሉ ማየት …” የሚል አይነት ምላሽ ሊሰጥ እንደሚችል መገመት አያስቸግርም ። ይህ ግን የክርስቶስን አስተምህሮት ይበልጥ ማበላሸት ነው የሚሆነው ። ምክንያቱም ነገሮችን ከስሜታዊነት በፀዳና በትዕሥት የማስተናገድ አስፈላጊነት እንደተጠበቀ ሆኖ በአገራዊ የጋራ ጉዳዮች ዙሪያ በእውነት ስለእውነት ሳይናገሩና ሳይመሰክሩ ዘላቂ ሰላምና ፍቅር ከቶ የሚታሰብ አይደለም። ክርስቶስም እውነትና ግልፅነት በሌሉበት እንኳን ሰማያዊው ምድራዊ ዓለምም የሚመች እንደማይሆን አስተማረ እንጅ ለጊዜያዊ ሰላምና መረጋጋት ስትሉ እውነትንና ግልፅነትን መስዋዕት አድርጉ ብሎ እንዳላስተማረ የቲዎሎጅ ምሁር ወይም ተማሪ መሆንን ጨርሶ አይጠይቅም። ዲያቆን ዳንኤል ግን ይህን መሠረታዊ ሃቅ ነው አንሻፎ ለማለፍ የሞከረው። ዲያቆን ዳንኤል እኮ የሚለን “በአደባባይና ቀጥሎም በውጭ ሚዲያና ቋንቋ መልሶ መላልሶ ያረጋገጠውን ሰውየ ቃል ሳይሆን “በእኔ ይሁንባችሁ እኔን እመኑኝ” ነው። እንዲህ አይነት ልክ የሌለው ግብዝነት ለዛሬው አገራዊ ፈተናችን ተጨማሪ እራስ ምታት እንጅ ከቶውንም የመፍትሄነት ሽታ የለውም ።
ዲያቆን ዳንኤል አስተያየቱን ከብልሁ የአገሬ ገበሬ ተረታዊ ምሳሌ እና አገርን አገር አድርገውና ለትውልድ አስተላልፈው ካለፉ አባቶቻችንና እናቶቻችን ተጋድሎ ጋር እያገናኘ ለመግለፅ የሞከረበት አቀራረብ መልካም ነው። የውጭ ጠላትን ለመመከት የቻልንበትን ምክንያት በማስታወስ ነፃነት ምን ያህል የጋራ መስዋእትነት እንደሚጠይቅና አሁን ኩሩ ባላገሮች (የአገር ባለቤቶች) ለመሆን የቻልነውም በዚሁ መስዋእትነት እንደሆነ ለመዘንጋዘብ በእጅጉ ይጠቅማል ። በሌላ በኩል ግን ይህ ለአጠቃላይ እውነታ እንጅ የውጭ ጠላትን መመከት እና ከውጭ ጠላት ባልተናነሰ የመከራና የውርደት ቀንበርን የሚያሸክሙንን ጨካኝ አምባገነን ገዥ ቡድኖችን አስወግደን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመመሥረት የምናደርገው ትግል ተመሳሳይ ባህሪና የአተገባበር ሥልት የሌላቸው በመሆኑ ንፅፅራችን ደምሳሳና አሳሳች እንዳይሆን ተገቢውን ትኩረት መስጠት ይኖርብናል ። እንደ አጠቃላይ አተያየት ግን የዲያቆን ዳንኤል አቀራረብ መልካም ነው።
ጥያቄ የሚያስነሳው በአሁኑ ወቅት አደባባይ ወጥቶ አገር ያወቀውን፣ ፀሐይ የሞቀውንና የመንግሥቱንና የገዥ ፓርቲነት ዙፋኑን ተቆጠጥረናል በሚሉ የዘመናዊ ፖለቲካ ጨዋታ ድሃዎች (የጎሳ/የዘውግ ጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ልክፍተኞች) እየታወጀ ያለውን የእብደት አዋጅ አቃሎ ለማየት የሄደበት እጅግ መሠሪና አሳሳች አካሄድ ነው። ዲያቆን ዳንኤል የጎሳ/የዘውግ ፖለቲካ የሥልጣን ተረኝነት አገዛዝ ፍላጎታቸውን በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባር እያሳዩን ያሉትን ወገኖች ከእነርሱ በላይ ሊያስተባብል ወይም ተራ ነገር አስመስሎ ሊያሳየን ነው የሚሞክረው ። ይህን ሲያደርግ ግን ጉዳዩ እጅግ አሳሳቢ መሆኑን ተረድተው በአጭሩ እንዲታረም የሚጠይቁ የሚሊዮኖች ቅን አሳቢ ዜጎችን ህሊና ምን ያህል እያቆሰለ እንደሆነ ጨርሶ ትዝም አላለውም ወይም ደንታ አልሰጠውም።
የጎሳ/የዘር/የቋንቋ ፖለቲካ አጥንት እየቆጠሩ “ሁሉንም በበላይነት ጠቅልሎ የመግዛቱ ተረኝነት የእኛ ነው” የሚሉ ወገኖች በለየለትና አደገኛ በሆነ ቅዠት ውስጥ የመገኘታቸው መሪር ሃቅ ከበቂ በላይ ግልፅና ግልፅ ሆኖ መሬት ላይ እየታየ ነው ። ታዲያ እነዚህን ወገኖች በግልፅ ፣ በቀጥታና ገንቢነት ባለው አኳኋን ተያይዞ ወደ መጠፋፋት እየወሰደን ከሚገኘው ክፉ ልክፍትና እብደት ተመለሱ ከማለት ይልቅ ጉዳዩን እንደተራ ጉዳይ ለማሳየት ተረት መተረትና የማጣጣያ ቃላትን መደርደርን ምን ይሉታል ?
ዲያቆን ዳንኤል በአፍ ወለምታ ሳይሆን ከለውጡ ብልጭታ ጥንሰሳና መከሰት ጀምሮ ስላሰቡትና ስላቀዱት ከህወሃት የከፋ (የባሰ) የተረኝነት ፖለቲካ ጨዋታ አንዴና በተወሰነ አጋጣሚ ብቻ ሳይሆን በተደጋጋሚና በበርካታ አጋጣሚዎች በግልፅና በቀጥታ እያሳወቁን ያሉትን ወገኖች በዚህች ፅሁፉ አንድም ቦታ ላይ ቢያንስ ከሞራል አንፃር “እባካችሁ ወደ መልካሙ መንገድ ተመለሱ” ለማለት አልፈለገም (ወኔ አላገኘም)። ፅሁፏን ያዘጋጃት የትኛውንም ወገን ለይቶ በማይነካ (ደምሳሳ ወይም ጅምላ) በሆነ እና ከተረትና ምሳሌ እና ከታሪክ ማጣቀሻ በሚነሳ እሳቤ ሲሆን አሁን ካለው እጅግ አሳሳቢ ወቅታዊ ሁኔታ ጋር የደመደመበት ሃሳብም ያው ደምሳሳ (ጅምላ) ነው። ይህ ደግሞ ክፉ የአድርባይነት ፖለቲካ ባህሪ ወይም ሰብእና መሆኑን ለመገንዘብ የተለየ እውቀት አይጠይቅም ።
ይበልጥ ግልፅ ለመሆን የፅሁፉን ዋና መልክት የያዙትን ነጥቦች እየጠቀስኩ አስተያየቴን በአጭር ባጭሩ ልግለፅ፦
“መቆጨት እንጅ መናደድ መፍትሄ አይደለም” ማለት በአጠቃላይ ማሳየት ያለብን ጠቃሚ ባህሪ ቢሆንም ለከት የሌለው የባለጌ ፖለቲከኞች አደገኛ አካሄድ በዴሞክራሲያዊት አገር በአብሮነትና በእኩልነት ለመኖር አጥብቆ የሚፈልገውን ህዝብ ሊያናድድ እንደሚችል እውቅና ሳይሰጡ በደፈናው “አትናደዱ” ማለት ግን ላለንበት መሪር ሃቅም ሆነ ከገሃዱ ዓለም የፖለቲካ መስተጋብር ጋር ሁልጊዜና በማነኛውም ሁኔታ አብሮ የሚሄድ እውነት አይደለም።
ዲያቀቆን ዳንኤል “አንደ ጥግ ይዞ ፀጉር መንጨት እንደማይጠቅም” ብሎ ሲነግረን ማን ፀጉር አስነጭ ወይም ፀጉር ነጭ እንደሆነ ለመናገር ቢያንስ የሞራል ድፍረት (ጥሩውን ጥሩ መጥፎውን መጥፎ ) የማለትን ደፋርነት አላሳየንም ።
አሁን ላለንበት ሁኔታ ትምህርት ይሆን ዘንድ ለማስገንዘብ ይመስለኛል የአርበኞች አባቶቻችንና እናቶቻችን ፀረ ቅኝ ግዛትና ፀረ ወረራ ትግል “ከተናጠል ወደ ህብረት ፣ ከህብረት ወደ ትብብር ፣ ከትብብር ወደ ግንባር ፣ ወዘተ እያደገ መጣ” ይለናል። በአሁኑ ሁኔታችን ወስጥ ግን ይህ እንዳይሆን ጠንክረው እየሰሩ ያሉትና ይህንንም በአደባባይ እየነገሩንና በመሬት ላይም እያሳዩን ያሉት እራሱ ዲያቆን ዳንኤል ሽር ጉድ የሚልላቸው የቤተመንግሥት ፖለቲከኞች የሚመሩትና ህወሃትን የተካው ኦዴፓና ፅንፈኛ ተባባሪዎቹ አይደሉም እንዴ? ታዲያ በቀጥታ ለመግለፅ ፍርሃትና አድርባይነት ቢያስቸግሩት እንኳ በቁልምጫ ወይም በተማፅኖ መልክ ለመግለፅ ወኔ ያጣ ሰው አስቀያሚ የፖለቲካ አረምን ለማረምና እብደትን አደብ ለማስገዛት የሚደረገውን እልህ አስጨራሽ ትግል ትርጉም ባለው አኳኋን ለማገዝ እንዴት ይቻለዋል ?
አሁንም ትምህርት ይሁነን በሚል ይመስላል አርበኞች አባቶቻችንና እናቶቻችን “እገሌ እንዲህ አለ፣ እዚህ ቦታ እንዲህ ተዘፈነ፣ እገሌ ለጣሊያን ገባ፣ እነገሌም በመሣሪያ ተደራጅተው ሊዘምቱብን ነው ፣ ወዘተ የሚለውን ሐሞት አፍሳሽ ወሬ መስማት ተው” ይለናል ። በመጀመሪያ ደረጃ ወሬን ወይም ኢንፎርሜሽንን (ይጥቀምም አይጥቀምም) መስማት እርግፍ አድርገው እንደተውና ይህም ትክክል እንደነበር እመኑኝ ማለት ከሃዱ ዓለም ጋር ጨርሶ አብሮ አይሄድም። በሁለተኛ ደረጃ በተቻለ መጠን በአላስፈላጊ ወሬ መጠመደን ቀንሰው ወይም ተቆጣጥረው ትኩረታቸውን በሥራ ላይ አድርገው ነበርና እኛም ካለንበት ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር እንዲሁ ለማድረግ እንሞክር ለማለት ካልሆነ በስተቀር አገር በማፍረስ ቅዠት የተለከፉ ፖለቲከኞችና በእፁብ ድንቅ ዲስኩር ህዝብን የሚደልሉ መሪዎች በሚቆጣጠሩት የፖለቲካ አውድ ውስጥ የምትሰሙት ሁሉ ተራ ወሬ ነውና ጀሯችሁን ድፈኑ የሚል አይነት ሰበካ ጨርሶ ስሜት አይሰጥም። ይህ አይነቱ አጠቃላይ (ድምሳሳ) አባባል ለስሜታችን የሚቀል ወይም የሚመች መስሎ ስለሚሰማን ለሁሉም ዘመንና ተጨባጭ ሁኔታ መሥራት እንዳለበት እያደረግን ማቅረብ ወይ ባለ ጊዜ ፖለቲከኞችን ላለማስቀይም ነው ወይም ደግሞ የፖለቲካ እምቦቃቅላነት ( political neivity ) ነው።
“በትንሽ በትልቁ በማለቃቀስና በማበድ ጉልበታችንን ሁሉ ለለቅሶና ለእብደት ከምናውለው ስህተቱን እያረምን ፣ ሰውን እያተረፍን መጓዝ … ” ይለናል ዲያቆን ዳንኤል ። ይህ አባባሉ ከአገራችን መሪር ሃቅ አንፃር ሲታይ በእጅጉ የኮሰመነ ነው ። የለውጥ ብልጭታው ወጋገን እንኳን አድማስ ሊያቋርጥ ብልጭ ካለበት ቤተ መንግሥት ብዙም ሳይርቅ መሬት ላይ የሆነውንና በአሁኑ ወቅት ደግሞ እጅግ በሚያሳፍርና በሚያሳስብ ሁኔታ እየሆነ ያለውን በቅን ልቦና እና በመልካም ዜግነት ህሊና ለመረዳት ለሚፈልቅ የአገሬ ሰው ይህ አይነት አስተሳሰብ ከመሪሩ ሃቅ ሳይሆን ለከት ከሌለው ስሜታዊነት ወይም የአድርባይነት ልክፍት የሚመነጭ መሆኑን የሚያጣው አይመስለኝም። አዎ! እውነተኛ ለውጥ እውን እንዲሆን ከፈለግን ገዥዎችንና አጋሮቻቸውን ከማማረርና ከመራገም አልፎ በተደራጀና በተቀነባበረ ትግል ለመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግርና ምሥረታ መታገል ያስፈልጋል ማለት በጣም ትክክል ነው። እጅግ ለማመን ከሚያስቸግረው የእለት ኑሮን ለማሸነፍ ያለመቻል ፈተና በተጨማሪ እየተካሄደ ላለው ፖለቲካ ወለድ ሰቆቃና አፈና ከሁሉም በፊት ገዥዎችና አደገኛ ፅንኞች ሃላፊነትና ተጠያቂነት እንዳለባቸው በግልፅና በቀጥታ መንገር ተገቢ ነበር (ነው) ። ዲያቆን ዳንኤል ግን የራሳቸው ድክመት እንደተጠበቀ ሆኖ በዚህ ሰቆቃና አፈና ውስጥ የሚማቅቁትን ነፃነትና ፍትህ ፈላጊ ዜጎች ነው “በትንሹም በትልቁም አታለቃቅሱ” የሚላቸው። ከዚህ የበለጠ የእራስን አረምና እብደት አዙሮ ያለማየት ኮስማናነት (ውድቀት) የት አለ?
“ኢትዮጵያ መድረስ ወዳለባት ሰገነት ለማድረስ የማንም ቡራኬና ፈቃድ አያስፈልገንም።” ይለናል ዲያቆን ዳንኤል ። ይህ እኮ ሲባል የኖረና ወደ ፊትም የሚኖር አጠቃላይ እውነትን የሚገልፅ አባባል እንጅ የእኛን ሁለንተናዊ መሪር እውነት የሚገልፅ አይደለም። ይህ መፈክር እኮ ከማንም በፊት መነገር ያለበት ተግባራዊ እንዳይሆን በግልፅና በሸፍጥ መሰናክል ለሚፈጥሩ የቤተ መንግሥት ፖለቲከኞችና ፅንፈኛ የጎሳ ፖለቲካ አራማጅ ሸሪኮቻቸው ነው። በቤተ መንግሥታቸው ሽር ጉድ ለሚል እንደ ዲያቆን ዳንኤል ያለ ሰው ደግሞ ድፍረቱ ካለው ወይም በዚያ ክፉ የአድርባይነት ልክፍት ካልተያዘ በስተቀር ይህን ማድረግ ይቻለዋል ። ይህን አድርጎ መገኘት ነው “እናርማለን እንጅ አናብድም” የሚለውን ሃይለ ቃል ህይወት ያለው ትርጉም የሚያጎናፅፈው ።
በታዳሚ ፊት ሃሳብን በጥሩ ሁኔታ በተቀነባበረ ፅሁፍ ወይም በአንደበተ ርዕቱነት (articulation) የመግለፅ ችሎታ ለመልካም ነገር እስከዋለ ድረስ ተፈላጊና መበረታታት ያለበት ተሰጥኦና ችሎታ ነው ። ችግር የሚሆነው ይህ ተሰጥኦና ችሎታ ለሸፍጥ ፣ ለሴራና ለቅሌት ፖለቲካ መስዋእትነት ሲቀርብ ነው። አዎ! የለውጥ ብልጭታ ታየ በተባለ ቁጥር ምን? ለምን? እንዴት? ከየት ወደ የት? ለነማን? በነማን? መቸና እስከመቸ? የሚሉ እውነትን ፈልጎ የማግኛ ጥያቄዎች ሳይጠይቁ የለውጥ መሪዎች ነን ከሚሉ ፖለቲከኞች ጋር በስሜት መክነፍ ብቻ ሳይሆን እጅግ አሳሳች በሆነ አንደበትና ድርሰት የህዝብ መከራና ውርደት እንዲራዘም ከማድረጉ ላይ ነው ችግሩ ። ይህ ደግሞ የመንፈሳዊውንና የዓለማዊውን ምንነትና እንዴትነት ለመረዳት የሚያስችል እውቀት አለኝ ከሚል ሰው ሲመጣ አስቀያሚነቱ አስከፊ ነው።
ለነገሩ እውቀት በትክክለኛ የህሊና ዳኝነት ካልተገራ ፋይዳው ኑሮን የተመቸ ከማድረግ የእንስሳዊነት ባህሪ አያልፍም። በአገራችን የመከራና የውርደት ሥርዓተ ፖለቲካ እድሜን አሳጥረን ወደ የምንመኘው የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግርና ምሥረታ መራመድ ካልቻልንባቸው ምክንያቶች አንዱ የሚመነጨው ከዚሁ እጅግ አስቀያሚ አስተሳሰባችንና አካሄዳችን ነው።
አዎ! ለዚህ ነው አያሌ ቁጥር ያላቸው ተማርንና ተመራመርን ወይም እየተማርንና እየተመራመርን ነው የሚሉ ዜጎች የሚኖሩባት አገር ከመከራና ከውርደት ለመገላገል ተስኗት በደስታ ኖሮ በሰላም የሚቀበሩባት ሳይሆን በቁም ሲሞቱ ኖሮ ወደ ከርሰ ምድሯ የሚወርዱባት ሆና የቀጠለችው።
አዎ! ለዚህ ነው ከኑሮው አስከፊነትና ከገዥዎች የመከራ ቀንበር ጋር እየታገለ ልጀቹን ፊደል አስተምሮ ለቁም ነገር ያበቃ/ች ወላጅ የወላድ መካን መሆኑ/ኗ በእጅጉ እየረበሸው/ሻት የደም እንባ የሚያነበው/የምታነባው።
አዎ! ለዚህ ነው በአብሮነትና በመከባበር የሚኖርባትን አገር ለትውልድ አስረክበው ያለፉ አባትና እናት መቃብር ውስጥ ሆነው የዛሬውን ትውልድ የለየለት ተያይዞ የመጠፋፋት እንስሳዊ ባህሪና አካሄድ እየታዘቡ እንዲህ አይነቱን የወላድ መካንነት እንኳንም ቆይተን አላየን በሚል ምርር ብለው የሚያዝኑት ።
አዎ! ለዚህ ነው የደጋግ አባቶቻችንንና እናቶቻችንን ጩኸት እየሰማ ፈጥኖ ይታደጋቸው የነበረው ፈጣሪም እነ ዳንኤል ክብረት እንደሚነግሩን የተለየን ኅጢአተኞች በመሆናችን ሊቀጣን ፈልጎ ሳይሆን እግዚኦታችን ትርጉም አልሰጠው ብሎ ዝም ብሎ የሚታዘበን ።
የለውጥ ብልጭታዋን በአግባቡ ተጠቅመው ለዜጎቿ ሁሉ የምትመች ኢትዮጵያን እውን ከማድረግ ይልቅ “ጠቅልሎ የመግዛት ተራው የእኛ ነው” የሚሉትን የፖለቲካ እብዶች በግልፅና በቀጥታ ነግሮና አነጋግሮ ወደ የሰውነት ቀልባቸው እንዲመለሱ ከማድረግ ይልቅ “በፀባይ ካልቀረብናቸው ይዘውን ይጠፋሉ” የሚል እጅግ የወረደ አስተሳሰብና አካሄድ የት እንደሚያደርስ ለማሰብ በእጅጉ ይጨንቃል ።
በእውነት ከተነጋገርን አገራችን ለዘመናት ከቆየችበት በእጅጉ አስከፊ የሆነ የዴሞክራሲ፣ የኢኮኖሚ ፣የማህበራዊ ፣ የህግ የበላይነት ፣የሞራልና የሥነ ምግባር ድህነት ለመውጣት ካልቻለችባቸው እና አሁንም ከድጡ ወደ ማጡ በሆነ ሁኔታ ውስጥ እንድትገኝ ካደረጓት ምክንያቶች አንዱ በህዝብ መሠረታዊ ፍላጎትና ጥቅም ላይ የተመሠረተ መርህ የሌላቸው ወገኖች ጥሩ አንደበታቸውንና ፀሃፊነታቸውን ተጠቅመው የህዝብን ሥነ ልቦና ሲያነሆልሉ (ሲያሽመደምዱ) በቃችሁ! አለመባላቸው ነው ።
እንኳንስ ፊደል ለመቁጠርና በቆጠረው ፊደል መሣሪያነት ክፉውንና ደጉን ያለምንም ገደብ (በነፃነት) የማወቅ መሠረታዊ መብቱን በእኩይ ገዥ ቡድኖችና ተባባሪዎቻቸው ተነፍጎ ለኖረና አሁንም እንደተነፈገ ላለ ህዝብ በአንፃራዊነት የተሻለ ደረጃ ላይ ለሚገኝ ህዝብም እንደ ዲያቆን ዳንኤል በመሰሉ እጅግ አሳሳች አድርባዮች ዕፁብ ድንቅ ዲስኩር (oratory/rhetoric) እና የፅሁፍ ትርክት ሰለባ ቢሆን ከቶ አይገርምም።
ለዚህ ነው ይህ አይነቱ አስቀያሚ ባህሪ የተጠናወታቸው ወገኖች የህዝብን ሥነ ልቦና ለማዳከም ያላቸው ወይም የሚኖራቸው አሉታዊ ተፅኖ በእጅጉ ሊያሳስበን የሚገባው። አዎ! እነዚህ ከታሪክና ከተሞክሮ ተምረው ህዝብን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ባለቤት እንዲሆን ከማገዝ ይልቅ እየተተካኩ የህዝብን መከራና ውርደት ከሚያራዝሙ ፖለቲከኞች ጫማ ሥር ጭራቸውን እየቆሉ (እየተሻሹ) ስለ ዴሞክራሲ አጥብቀው ሲሰብኩንና ሲዘምሩብን አደብ ግዙ ካላልናቸው በስተቀር የገዥዎች ጦር አልባ መሣሪያነታቸው ማቆሚያ የለውም ።
አዎ! የለውጥ ብልጭታ ታየ በተባለ ቁጥር ከህዝብ ጋር ሆነው የብልጭታው ወቅት ወደ ተሟላና ዘላቂነት ወደአለው የብርሃን ዘመን እንዲሸጋገር ከማገዝ ይልቅ ከቤተ መንግሥት ባለሟልነት እስከ አደባባይ ተዋናይነት ለማገልገል እራሳቸውን የሚያዘጋጁ ወይም ለርካሽ ሽያጭ የሚያቀርቡ ወገኖችን በግልፅ፣ በቀጥታና በገንቢነት አደብ ማስገዛት ካልተቻለ ስለ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግርና ምሥረታ ማውራት ጨርሶ ስሜት አይሰጥም።
የእንዲህ አይነት ባህሪና አስተሳሰብ ልክፍተኞችን በግልፅ፣ በቀጥታና ገንቢነት ባለው አቀራረብ ደፍሮ ለማሄስ (ለመተቸት) እና ወደ ትክክለኛው መስመር እንዲገቡ ለማድረግ የሚሽኮረመም ወይም እኔ ምን አገባኝ የሚል ትውልድ እንኳን ለትልቁ የዴሞክራሲ ሥርዓት እውን መሆን ለሌላ መለስተኛ ተልእኮም ከቶ ሊመጥን አይችልም።አዎ! የደረስንበት ሁለንተናዊ ውድቀት እዚህ ድረስ መሆኑን እየመረረንም ቢሆን አምነን ተቀብለን የሚበጀውን ካላደረግን በስተቀር ሸፍጠኛ ገዥ ቡድኖችና የጎሳ/የዘር አጥንት ቆጠራ ፖለቲከኞች እንደ ዲያቆን ዳንኤል በመሳሰሉ እጅግ አሳሳች (disigenious and deceitful) እፁብ ድንቅ ዲስኩር (rhetoric) እና ድርሰት እየታጀቡ ከድጡ ወደ ማጡ ይዘውን ይወርዳሉ ።
ለውጥ ታየ በተባለ ቁጥር ከባለጊዜ ፖለቲከኞች ጋር ሽር ጉድ በማለት ክፉ ደዌ የተለከፉ ወገኖች የሚሉን እኮ “የኦዴፓ/ኢህአዴግ የተሃድሶ ፍርፋሪ ለኢትዮጵያ ህዝብ ምን አነሰው? “ ነው ። “ህሊናችን ሸጠን ያመጣንላችሁን ርካሽ ገፀ በረከት አሜን ብላችሁ ተቀበሉን” እኮ ነው የሚሉን ። እናም “በቃችሁ! ሲሆን ለእራሳችሁም ስትሉ ወደ ትክክለኛው ምንነትና ማንነት ሳይውል ሳያድር ተመለሱ፤ ካልሆነ ደግሞ የመከረኛውን ህዝብ መከራና ውርደት የዲስኩራችሁ መራቀቂያ እና የድርሰታችሁ ብቃት ማሳያ አታድርጉት” መባል አለባቸው።
መናገር (መደስኮር) መብታቸው ነው ። ለሩብ ምዕተ ዓመት በፖለቲካ ወለድ ወንጀል የበሰበሰውንና የከረፋውን ሥርዓተ ኢህአዴጋዊን ከራሱ በወጡ ተሃድሷዊያን አድሶ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እውን ማድረግ ይቻላልና ዝም ብላችሁ በእኛ የመደመር ባቡር ተሳፈሩ ብለው ሊያሳምኑ ሲሞክሩ ነው ችግር የሚሆነው።
በእውነት ከተነጋገርን በእንዲህ አይነት ሾካካ (disingenuous/deceitful) የፖለቲካ ባህሪ (ሰብእና) ምክንያት ነው የፖለቲካችን ታሪክ የከሸፉ የለውጥ እንቅስቃሴዎች ታሪክ እየሆነብን የተቸገርነው። ከግማሽ ምዕተ ዓመት የመከራና የውርደት ተሞክሮ ለመማር ፈቃደኞችና ዝግጁዎች ባለመሆናችን ዛሬም አዙሪቱን ሰብሮ ከመውጣት ይልቅ ይበልጥ እያወሳሰብነውና ጥልቀት እየሰጠነው ቀጥለናል ።
ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ታዳሚን (ህዝብን) በተግባር የሚፈትንና አዳዲስ አስተሳሰቦችንና የችግር መፍቻ ዘዴዎችን አምጦ እንዲወልድ የሚያስችል የአነሳሽነት አቅም (ችሎታ) ያላቸው ተናጋሪዎችን (motivational/inspirational speakers) ከማፍራትና ከማበረታት ይልቅ የአድርባይነት ወይም ልክ የሌለው የስሜታዊነት መንፈስ የተጠናወታቸውን ተናጋሪዎች (mere orators/rhetoricians) በየአዳራሹና በየአደባባዩ ድርጊት አልባና እጅግ አሰልች ትርክታቸውን እንዲያዥጎደጉዱ በማድረግ መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ለውጥን እውን ማድረግ እንኳን ሊቻል የሚታሰብም አይደለም ።
ከዚህ በተቃራኒ በእንዲህ አይነት እጅግ ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ በምንገኝበት በዚህ ወቅት እውቀትንና ፅዕኑ የአርበኝነት ስሜትን በተላበሰ ሰብእና ወስላታ ፖለቲከኞችን፣ አክቪስቶች ነን ባዮችን እና ህዝብን እጅግ አሳሳች በሆነ ንግግራቸው (oratory/rhetoric) የሚያደነዝዙትን አድርባዮች የሚሞግቱ እንደ አቶ ታየ ቦጋለ የመሰሉ እጅግ ብርቅየ ኢትዮጵያውያንን ስናይ ተስፋና ኩራት ሊሰማን ይገባል። አዎ! “ለካስ አገራችን ዛሬም ዜጎቿ ሁሉ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሥር በአብሮነት ፣ በእኩልነት ፣በፍቅር፣ በሰላምና በጋራ ብልፅግና ይኖሩ ዘንድ በየትግሉ መድረክና አደባባይ ለህዝብ ስሜት የሚመቸውን የፕሮፓጋንዳ ንግግር ሳይሆን መሪሩን ሃቅ በመጋፈጥ ለትክክለኛና ዘላቂ መፍትሄ ፍለጋ ፋና ወጊ የሆኑ ልጆች አሏት” የሚል ግዙፍና ጥልቅ የሆነ የተስፋና የኩራት ስሜት ሊሰማን ይገባል ።
ልቀጥል
ለሩብ ምእተ ዓመት በጎሳ/በዘውግ አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ላይ በተመሠረተው ሥርዓት ላይ የሰላ ሂስና ተቃውሞ የሰነዙሩና በፅዕናት የቆሙ አያሌ ንፁሃን ዜጎች ከቁም ስቃይ እስከ የህይወት በከፈሉት መስዋእትነት ህወሃት ፍፁማዊ የበላይነቱን አጥቶ አንፃራዊ የሆነ የለውጥ ብልጭታ ፈነጠቀ በሚል የለውጥ አራማጅ የምንላቸውን የኢህአዴግ ፖለቲከኞች “የዘመናችን ሙሴዎች” ብለን ከተቀበልን ይኸውና የሁለተኛ ዓመቱን ሁለተኛ አጋማሽ ይዘናል ።
የለውጥ አራማጅ የምንላቸው ፖለቲከኞች ሚናቸውን በቅጡ በመለየት ተገቢውን የመሪነት ሚና ለመጫወት ባለመቻላቸው ወይም በጎሳ/በዘውግ አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ነጋዴዎች እና በዜግነት ላይ በተመሠረተ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሥር በፍቅርና በሰላም ለመኖር በሚፈልገው አብዛኛው ህዝብ መካከል ክፉኛ በመዋዠቃቸው የለውጥ ብልጭታው ከፈነጠቀ ብዙም ወራት ሳይቆጠሩ ከተስፋ ይልቅ እጅግ አደገኛ ሥጋት እየተንሰራፋ መጥቷል ። እነዚህ የለውጥ አራማጅ ተብይ ኦዴፓ/ኢህአዴጋዊያን የፖለቲካ እብደታቸው የሚያስከትለውን ተያይዞ የመውደቅ አስከፊነት ያልተረዱ ወይም ቢረዱም ጨርሶ ደንታ የሌላቸውን የጎሳ/የመንደር ፖለቲካ ልክፍተኞች በፖለቲካና በህግ አግባብ አደብ ከማስገዛት ይልቅ ይባስ ብለው የይዘቱ ምንነት ለህዝብ ያልተገለፀ “የአጋርነትና የፍቅር ስምምነት” እየተፈራረሙ መከረኛውን ህዝብ “የተትረፈረፈው የሰላማችን ቡራኬ ይድረስህ ” በሚል ይሳለቁበታል።
የተረኝነትን የፖለቲካ ጨዋታ በሸፍጥና በሴራ ለማለማመድና አጠናክሮ ለማስኬድ ያላሳለሰ ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኙ ኦዴፓዎች አደገኛ የፖለቲካ ፅንፍ ከረገጡ ወገኖች (የኦሮሞ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች ነን ባዮች) ጋር ከአደባባይ በስተጀርባ የነበራቸውን ሁሉን የመጠቅለል ቅዥት ይኸውና ዛሬ የፖለቲካ ተውኔት መተወኛ ባደረጉት የኢሬቻ በዓል ላይ ለኢትዮጵያ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ለዓለምም ግልፅና ግልፅ አድርገዋል።
ሰበረን የሚሉትን ነፍጠኛ ( አማራ ማለታችን አይደለም የሚለው ስላቃቸው እንዳለ ሆኖ) ሰባብረው ለዘመናት በመላው ዜጎች የህይወት ፣ የእውቀት ፣የጉልበት፣ የገንዘብ ፣ ወዘተ መስዋእትነት የተመሠረተችውንና ለዛሬ እድገቷ የበቃችውን እና የአገር ርእሰ ከተማ ብቻ ሳይሆን አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የሆነችውን አዲስ አበባን እንደተቆጠጠሯትም በማያሻማ ብቻ ሳይሆን እጅግ አደገኛ በሆነ አገላለፅ አውጀዋል ። “የአዲስ አበባ ባለቤቶች እኛና እኛ ብቻ መሆናችንን ለማረጋገጥ ጠንክረን እየሠራን ነው” በሚል ከብዙ ወራት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚመራው ገዥ ድርጅታቸው (ኦህዴድ/ኦዴፓ) መግለጫ ያሳወቁንን ሃላፊነት የጎደለው የፖለቲካ አካሄዳቸውን ነው በአደባባይ ያወጁት።
የሰብአዊና የዜግነት መብቱ በሚከበርበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሥር በእኩልነት አብሮ ለመኖር ጨርሶ ችግር በሌለበት ህዝብ ላይ እጅግ ሃላፊነት በጎደለው በሰባሪነትና በተሰባሪነት ትርክት ላይ የተመሠረተ አዋጅ ማወጅ ጨርሶ የጤናማ ፖለቲከኝነት ባህሪ አይደለምና በእንጭጩ እንዲታረም ማድረግ የግድ ነው። ተያይዞ ከመዳን ተያይዞ መጥፋት በምንም አይነት ሁኔታ ተመራጭነት የለውምና ።
ኦህዴድ/ ኦዴፓ ይህን እጅግ ሃላፊነት የጎደለውን እወጃ አስመልክቶ ያዘጋጀውን ፅሁፍ “በነፃ ሚዲያዎቹ (ዋልታና ፋና)” በኩል አሰራጭቶ አስነብቦናል። እጅግ አደገኛ ውጤት ሊያስከትል ከሚችለው “የሰባብረን ተቆጣጠርነው” ዲስኩር አንፃር የመግለጫ ተብየውን ቅኝትና ይዘት በጥሞና ላነበበ ሰው እነዚህ ኦዴፓ/ኢህአዴጋዊያን ምን ያህል የህዝብን የመረዳት አቅም በእነሱ የድንቁርና ፖለቲካ አስተሳሰብ ልክ እንደሚለኩት ለመገንዘብ አይከብደውም።
በሁለቱም ቤተ መንግሥቶች (በመንፈሳዊውና በዓለማዊው) መካከል እያሸረገዱ እና የትርክታቸውን ይዘትና ቅርፅ እንደ የሁኔታው እየቀያየሩ (እያስማሙ) የሚራመዱ ግለሰቦችን አካፋን አካፋ እስከ ማለት በሚደርስ ግልፅነትና ቀጥተኝነት አደብ እንዲገዙ ማድረግ ተገቢ ነው ። ምክንያቱም እውነተኛ (መሠረታዊ) ለውጥ የእንዲህ አይነት ሰዎችን አስተሳሰብና አካሄድ መቀነስንና በአንፃሩ ከቅንነትና ከእውነተኝነት የሚመነጭ የሞራልና የፖለቲካ ሰብዕና ያላቸውን ማበረታታትና ማብዛትን የግድ ይላልና።
አዎ! ሸፍጠኛ ፖለቲከኞችንና ፅንፈኛ የጎሳ/የዘውግ አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ልክፍተኞችን በአግባቡና ትርጉም ባለው አኳኋን ለመተቸት የሞራልና የዜግነት ወኔው ሲከዳን የመከረኛውን ህዝብ መከራና ውርደት በየአዳራሹና ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ እየተረክን የንግግራችን ወይም የትርክታችን እፁብ ድንቅነት ማሳያ ከማድረግ ክፉ ልማድ መውጣት ይኖርበናል ። አካፋን አካፋ ለማለት ካልተቸገርን በስተቀር በዚህ ረገድ ከራሳቸው ጋር ታግለው ነፃ መውጣት ካለባቸው ብዙ ወገኖች መካከል ዲያቆን ዳንኤል ክብረት አንዱ ነው።
የመከረኛውን ህዝብ ቁስል በዘላቂነት ለማዳን በሚያችል አኳኋን ሳይሆን እያከኩ (እያሻሹ) በሚያዘናጋ የሰላ አንደበት መከራውን ለማራዘም አስተዋፅኦ ማድረግ የለየለት ሸፍጠኝነት (hypocracy) ብቻ ሳይሆን ወንጀልም ነውና ልብ ያለው ልብ ይበል ።ለዚህም ነው “እያረሙ እንጅ እያበዱ ላለመሄድ” ከራስ መጀመር የሚያስፈልገው ።
ግሩም ዕይታ ነው፤ጽሑፉ ሣያልቅ ተንጠልጥሎ ቀረ እንጂ። አካፋን አካፋ ማለት ደግ ነው። በይሉኝታ ሸፋፍነው የሚተውት ነገር ለባሰ ምርቀዛ ያጋልጣል።
የ”ዲያቆን” ዳንኤልን ጽሑፍ አንብቤዋለሁ። ባንድ ምሣሌ ግለጠው ብባል “ሣቢውን ግረፈው”ዓይነት ነው።ይህ ሰው በሁለት ቤቶች ውሥጥ በአንድ ቀን ማደር ይፈልጋል። እውነቱን ተናግሮ ዛሬን ባለማስቀየም የነገም ሰው መሆንን ይመኛል፤ይህን ለማሣካትም ዕውቀቱንና “ሞኝነታችን”ን መጠቀም ይፈልጋል። የሁለት አገር ሰው መሆን ያለውን ችግር በቅጡ የተረዳ አይመሥልም። He seems to be beating around the bush. He wants to hide the crimes of his friends in high positions of both the so called federal and regional structures specifically Abiy and Shimelis Abdissa. ይህ ሰው እንደሚያሣየው ልፋትና ድካም ያሣዝነኛል፤ ሁሉንም ለማሥደሰት በሚያደርገው አድሮ የመገኘት ለራሥ ያደላ ጥረት ግን ከሁሉም ሣይሆን እንዳይቀር እፈራለታለሁ።
እንጂ ዳኒ የነሽሜንና አቢይን የጭቡ አካሄድ አይረዳም ማለት የዋህነት ነው። ከሁሉም ደግሞ ትዝብት ውሥጥ ከሚገባ ዝም ቢልም ብልኅነት ነው።እነሱን ለማሥደሰት እኛን “አትናደዱ፤ ዝም ብላችሁ እንደፈረሥ ተጋለቡ …”ብሎ መምከር በትንሹ እንደ ጠገናው አባባል አድርባይነት ነው።ለነገሩ ዳኒ የሚለው ነገር የጊዜው አንገብጋቢ ችግራችን አይደለም፦ልፋ ቢለው እንጂ። አገር በሠገጤ አክራሪ ኦሮሞ በግላጭ እየተወረረና መንገዶች ሣይቀሩ እየተዘጉ “አትበሣጩ” ብሎ መምከር “ግፉ ገና ይጨመርላችኋል” እንደማለት የሚቆጠር እንጂ የርሱ ባማርኛ የመድረክ መራቀቅ ችግራችንን አይፈታም፤ ግን ግን እርሱ ራሱ ሥራ ፈትቶ እኛንም ሥራ አስፈታን – ዳኒ የኔ ማር።