መግብያ
እኛ !
መቃብር እስክንገባ
መቃብር የምናሥገባ!
…………………. እኛ !
ራቁታችንን ተወልደን
ገላ ሰውነታችንን ጠልተን።
ተመሳሳይ ቆዳችንን አዋደን
በቋንቋችን ተመጻድቀን
ሰው ፣ ንቀን ተናንንቀን
ነገር ግን ፣ ስው ተብለን
እሥከጊዜው እንኖራለን።
……………………… እኛ !
ትወራ፣ሲበዛ እንኳን ፖለቲካ፣ኃይማኖትም ይሰለቻል።
“ትወራ ያለድርጊት እምነትም ያለሥራ ከንቱ ነው። ” የሚባለውም ለዚህ ነው ምን በወሬ ወይም በትወራ ወይም በቢሆናል ሃሳብ የማትገምጠው ዳቦ ቢበዛ እንደ ተጨባጩ ዳቦ አያጠግብህም።ዳቦ የድርጊት ውጤት ነው ና ዳቦ ዝም ብሎ አይገኝም።ዳቦ ፣ ዳቦ ለመባል ይበቃ ዘንድ በብዙ ድርጊቶች ውስጥ ስንዴ ማለፍ ይጠበቅበታል።
የገበሬውን ልፋት ትተን ፣ሥንዴ የተባለው ፣ ምርት፣
በብዙ ድርጊት ተፈትኖ በማለፍ ነው፣ “ለአንባሻ” “ለድፎ” እና “ለፉርኖ” ዳቦነት የሚበቃው።
ሲፈተግ -ሲከካ
ሲፈጭ -ሲቦካ
በእሳት ሲጋገር..
ሊበላ መሆኑን
ወይ ያለማወቁ
የጥሬ ነገር።
(ድንገቴ ግጥም ይሉሃል ይህ ነው።ግጥም እንዲህ ግጥም ሲል ፣ ውበቱ ይጎላል።መልዕክቱም እልፍ ይሆናል።)
በዛሬ ግዜ በየሠፈር ሱቅ የሚሸጠው፣ ባለ ሁለት ብር ዳቦ ና የቀድሞው ጊዜ ባለ አምስት ሣንቲም ዳቦ ሚዛን ላይ ቢወጡ እኩል ናቸው። እኔን ይህ ማነፃፀሪያ አይደንቀኝም። እኔን ድንቅ የሚለኝ አምስት ሳንቲም ዛሬ እንደገንዘብ ተቆጥራ ብቻዋን አንዳችም የምትገዛው ያለመኖሩ ነው። …
የአምስት ሣንቲሞ ዳቦ ትዝ የሚለው፣ ዕድሜ ሰጥቶት ለዚህ የበቃው ኢትዮጵያዊ ዜጋ ፣ ኑሮ በአርባ ዓመት ውስጥ ጣራ መንካት ሣይሆን ጣራ ቀዶ ወጥቶ ሰማይ ላይ መሰቀሉን እያየ ፣በጥላሁን ገሠሠ ዘፈን”ያሳለፍነው ጊዜ ደሥታን ያየንበት ተመልሶ ቢገኝ አሁን ምንአለበት ።”እያለ ይቆዝማል። ሱቅ ተልኮ ሲገዛ በነፃ ከረሜላ ሲመረቅለት በእዝን ልቦናው እያሥታወሰ።
ዛሬ ዘይት እንኳን በዝግታ የሚገድልህ የኬሚካል ጦር መሣሪያ ሆኗል።ዘይት ብለህ የምትበላው ኮለሥትሮል ነው።ደም ሠርህ ላይ እየተጋገረ ለድንገተኛ ሞት የሚዳርግህ። ያኔ እኮ የሀገርህን ንፁህ፣ የተልባ፣የኑግ ፣የሱፍ ዘይት በፈለገህ ጊዜ በሣንቲም ቤት ትገዛለህ።ዋጋም ነጋዴ እንደፈለገ በየዓመቱ አይጨምርብህም። ዛሬ እኮ አሥቦበት በዕውቀት ተደግፎ ነጋዴው ወጪውን ያገናዘበ ጭማሪ አይደረግም።
ብዙ ጊዜ እንደተሥተዋለውም በኢትዮጵያ አንዴ ዋጋ ከተሰቀለ በተአምር እንደማይወርድ ይታወቃል። ምክንያቱም ፣ ጨማሪዎቹ የነፃ ገበያን ምንነት ያልተረዱ በመሆናቸው “ነፃ ገብያ “ሲባል ዘረፋ ይመሥላቸዋል።አንዳንድ የኢትዮጵያ ነጋዴዎች ፣ጀሶ በዱቄት ውስጥ፣ ቀይ ሸክላ በበርበሬ ፣ሙዝ በቅቤ ፣በቆሎውን በማሽን ከክተው ከሩዝ ጋር ቀላቅለው የሚሸጡ…ምርታቸውን ከግራሙ በታች በማምረት ሆኖም በግራሙ ዋጋ አምርተናል ብለው የሚሸጡ ፣ በዚህ ማጭበርበርም ስንጥቅ እንደሚያተርፉ እየታወቀ ለምን የነጋዴ ሥም ይሰጣቸዋል ??? ለምን ነጋዴ ይባላሉ ??? እነዚህ ሰዎች እኮ አጭበርባሪዎች ናቸው። እናም “ዘራፊ” ወይም “ማጅራት መቺ” ነው። መባል የነበረባቸው። በአሥተሳሰብ ደረጃ።
በአሥተሳሰብ ደረጃ፣ ሥል ምን ትዝ አለኝ መሰላችሁ? “ምን ትዝ አለህ ?” አትሉኝም ! አላችሁኝ? ወሬ የሚደምቀው እንዲህ ዓይነት አድማጭ ሲኖር ነው።አንዳንዱ እኮ ያለማዳመጥ አባዜ የተጠናወተው ነው።ጉንጫቹሁን በእጁ ወደፊት ለፊቱ እያዞረ፣ ምራቁን እያፈነጠቀባችሁ ፣ ካልሰማችሁኝ ሞቼ እገኛለሁ እያለ ” የቆጥ ና የጉሮነውን” ካወራላችሁ በኋላ፣እናንተ ቁምነገር ልታወሩት አፋችሁን ከመክፈታችሁ። “ቻው!!ቻው!! … እቸኩላለሁ” ብሏችሁ ፈትለክ ይላል።እናንተም “ያአድማጭ ያለህ ያሰኝህ !የሚሰማህ እጣ ! እኔማ ከእንግዲህ አንተን ቁምነገረኛ ብዬ አፌን አልከፍትም። “በማለት ላታዋሩት ለራሳችሁ ቃል ትገባላችሁ። “ወደትዝታዬ” (በእርግጥ የኔ ትዝታ ብቻ አይደለም።የሀገርም ትዝታ ነው። ) ልመልሳችሁ።
አንድ ጊዜ የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ በ2002 ዓ/ም ምርጫ ጊዜ በፓርላማ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ላነሱት ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ ” የምርጫ መቀሥቀሻ ፖሥተር የሚቀድ የኢህአዴግ ዓባል ካለ እሱ የኢህአዴግ አባል አይደለም።ወራዳ ነው !!እደግመዋለሁ ወራዳ ነው!! ወራዳ በመሆኑም እጁ መቆረጥ አለበት።ማለቴ በተግባር ሳይሆን በአስተሳሰብ ደረጃ።” ብለው ነበር።
እናም እኔ እንዲህ እላለሁ። ” የዛሬ ጊዜ የኑሮ ውድነት ከገብያው አንፃር ሲታይ፣ ለብዙዎቻችን ተራራ ሳይሆን ሰማይ ላይ የተሰቀለ ሆኖብናል።ሥለዚህም ፣ ይህንን የመሥቀል ድርጊት ምክንያት አልባ በሆነ ፣እጅግ በተጋነነ አድማ በሚመሥል ጭማሬ የሚፈፅሙ የነፃ ገብያን ምንነት ያልተገነዘቡ ደንቆሮዎች ናቸው ። እደግመዋለሁ ደንቆሮዎች ናቸው። ሥለዚህም መሰቀል አለባቸው ማለቴ በአሥተሣሠብ ደረጃ።”
በእውነትና ስለእውነት ከምር እንነጋገር ከተባለ፣ በሀገራችን ከበቆሎ የረከሰ እህል አልነበረም።ዝቅተኛ ገቢ ያለው እንኳ እንደልቡ በርካሽ ዋጋ ያገኘው ነበር። ዛሬ ግን መካከለኛ ገቢ ያለውም ተወዶበታል። እናም የኑሮ ውድነት በአሥተሳሰብ ሳይሆን በተጨባጭ ከጣራ በላይ ሆኗል።ከጣራ በላይ ደግሞ ሰማይ ነው።
እናም በደሃ ላይ ያው ሰማይ ተደፍቶበታል።በአሥተሳሰብ ሳይሆን በተጨባጭ።ይህም ሆኖ በደሃ ላይ ይሾፍበታል።ርካሹን ዘይት “ለጤና ጠንቅ ነውና ሽሮህን ሰርተህበት አትብላ ይባላል።” ይህ በሰው ቁሥል ላይ እንጨት መሥደድ ነው። የጠላ ቂጣ ያረረበትን ፣ በርገር ለምን ገዝተህ አትበላም ማለትም ነው።እንዲህ ማለት ደግሞ በእሳት ላይ ቤንዚን መርጨት ነው። ማናደድ ነው። በርሃብ ላይ ንዴት ሲደመር ደግሞ ህይወትን ያሳጥራል።ይህንን ደግሞ ኢትዮጵያዊው ምንዱባን ሥለሚገነዘብ
“ምንም ቢቸግራት ፈረሥ ቀንድ የላትም
ተናዳጅ ይሞታል፣አናዳጅ አይሞትም። ” በማለት
በቂም፣በብሥጭት ና በንዴት ነጋ ጠባ መብሰክሰክ ና ዕድሜንም ማሣጠር የተናዳጅ እጣ ፈንታ መሆኑን አሣምሬ ሥለማውቅ ፣ለድህነቴ ያደረከውን አሥተዋፆ አውቃለሁና በማይረባ ቀልድህ አታሹፍብኝ ይልሃል።
ይልቁንስ በሁለትሺ አሥራሁለት ፣ አዲሥ ዓመት “አሮጌውን ሥግብግብ ሰው አውልቀህ አዲሱን ለጋሱን እና ለህዝብና ለሀገር አሳቢውን ሰው ልበሥ።” በማለትም ይመክርሃል።
ነፍሥ ያወቀ ኢትዮጵያዊ ዜጋ በዚህ አዲሥ ዓመት፣ በግሉ ከራሱ ጋር ስብሰባ ተቀምጦ በፅሞና መነጋገር ፣መወያየት ካልቻለ በዚህ ሀገር ተጨባጭ ለውጥ አይመጣም።
ሰዎች ሆይ ! ከራሳችሁ ጋር በወጉ መሰብሰብ ካልቻላችሁ በሥተቀር ከሌሎች ጋር ቁጭ ብላችሁ በትዕግሥት መወያየት አትችሉም።ራሳችሁን ማዳመጥ ካልቻላችሁም ሌሎችን በወጉ ማዳመጥ አትችሉም።
ከራሳችን ጋር በወጉ ተሰብስበን በወጉ በአእምሯችን ውስጥ ያሉትን መልካም ነገሮች ለማዳመጥ ትዕግሥቱ ካለን ራሳችንን ያለአንዳች መካሪ ታላቅ ማድረግ እንችላለን።ሆኖም፣ አእምሯችን ውስጥ የተከማቹትን መጥፎ ና ክፉ ባህርያትን ተግተን በማዳምጥ እነሱን ለመተግበር ሣንታክት የምንተጋ ከሆነ ሁሌም ከውድቀት ና ከጥፋት ጎዳና ልንወጣ ከቶም አንችልም።
የሰው ጎዳና ፣የሰው መንገድ መንታ ነው።አንደኛው መንገድ መልካም እና ደሥ የሚል ህይወትን የምናገኝበት ሲሆን ፣ሌላኛው መንገድ ደሞ የጥፋትና የሞት መንገድ ነው።እናም የምትጓዙበትን መንገድ ለመፈተሽ
ወደ ግል ህይወታችሁ የሥብሰባ አዳራሽ መግባትን ሁሌም መርሳት የለባችሁም።ይህንን ጠቃሚ ድርጊት ሳታክቱ ሁሌም ስታደርጉ፣የሚያጋጥማችሁን ጥቅምና ጉዳት ፣ትርፍ ና ኪሳራ በቀላሉ ለማወቅ ትችላላችሁ።
ህይወት እንደሆነ ሁልጊዜም ስብሰባ ላይ ናት።ህይወትን ያለሥብሰባ ለማሰለጥ አይቻለም።
ከወተት ተሸጋግሮ፣ጥሬ መቆርጠም የጀመረ ሰው ሁሉ ከራሱ ጋር ሁሌም ሥብሰባ ያደርጋል።ይጨቃጨቃል።ይነታረካል።ራሱን ይወቅሳል።ይኮንናል።ራሱንም ያደንቃል።ያሞግሣል።ይሸልማል።ብራቮ!ብራቮ! ይላል።
በገሃዱ ዓለምም ሰው፣ለተለያየ ዓለማዊ ና መንፈሳዊ ጉዳይ ፀሐይ ሞቆትም ሆነ በምሥጢር ሁለት እና ከዛ በላይ ሆኖ ይሰበሰባል። ሁለትና ከሁለት በላይ በጠረጴዛ ዙርያ ከተወያየህ ተስብስበሃል ማለት ነው።ላጤ ካልሆንክም ማታ ማታ ከሚሥትህ ጋር ትሰበሰባለህ።
ስብሰባ የሰዎች ባህል ከሆነ ቆይቷል።በቅርቡ የዳቦን፣አቅርቦትና ጥራት በተመለከተ ፣ በሸማቾች ማህበር በኩል ሥብሰባ የተጠራ ወዳጄ ፣ ዳቦን በተመለከተ ሰብሰባው ላይ የተነገረውን ቀልድ ነግሮኝ ተገርሜያለሁ።
“በዚህ ኑሮ እንደ እሳት በሚያቃጥልበት ወቅት ዳቦን በተመለከተ ሥብሰባ አለ ተብዬ ተጠራውና ወደስብሰባው ሄድኩ።” በማለት ታሪኩን ጀመረልኝ።
“በስብሰባው የሚባለው ከመድረኩ ተባለና አበቃ።
‘….እሺ ጥያቄ ካለ እቀበላለሁ።’ በማለት
ሰብሳቢው ለተሰብሳቢው መድረኩን ክፍት አደረጉ።በመቀጠልም ‘አንተ እዛ ጥግ ነጭ ኮፍያ ያደረከው። ‘ በማለት እንዲናገር ዕድል ሰጡ።ሰውዩውም ከመቀመጫው ተነሳና መናገር ጀመረ።
‘የኔ ጥያቄ በዋነኝነት የሚያነጣጥረው ዳቦ ላይ ነው። ተኩስ ካሉኝ መተኮሴ ነው።ክብሩ ሰብሳቢ
።’ በማለት ፍቃድ ጠየቀ።
‘ተኩስ! የሚፈራ የለም።’ አሉት ፈገግ ብለው ሰብሳቢው።
‘ ለምንድነው በድፍን ኢትዮጵያ በሁለት ብር የሚገዛው ዳቦ ድንገት እንደኪኒን የሚዋጥ የሆነው?……..”
በማለት እጁን እያወናጨፈ ተቀመጠ።
ሰብሳቢው በቁጣ አይናቸው ፈጠጠ። በሪፖርታቸው የዳቦ ግራም ላይ በቂ ቁጥጥር እንደተደረገ ጠቁመው ነበር።
‘ዳቦ ኪኒን ሆኖ በሁለት ብር ህዝብ እየገዛ ይውጣል ነው የምትለኝ?? ይህ ፈፅሞ በኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ አይፈጠርም። እንዲህ ዓይነት የተራቀቀ ሣይንሣዊ ዘዴ ታላቋ አሜሪካ እንኳ የላትም። ‘ በማለት የሰውየውን ተኩስ ወደአሜሪካ አዞሩ። በመቀጠልም ‘ሆኖም እንዲህ ዓይነት ገላጋይ ፣ ሆድ አጥጋቢ ኪኒን አሜሪካ አትፈጥርም ማለት አይቻልም። ለምን በኪኒን መልክ የሚዋጥ ዳቦ አሜሪካን ማምረቷን የሚያረጋግጥ መልስ እንዲሰጠን የአሜሪካውን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራፕን በደብዳቤ አንጠይቀውም?? ሥንዴ በዶላር ገዝተን ከሟብኳት ኪኒኑን መዋጥ ይሻለናል። ‘ አሉ።
ይህ ከተረት ተረት ነፃ የወጣ በእውነታ ላይ የተመሰረተ ወግ ነው።
አሪፍም ትወራ ነው።ትወራ ብሎ ዝም ነው። በእውነታ ላይ የተሰነዘረ ትችትም ነው።
በእርግጥ በሀገራችን ትወራ በዝቷል። ነባራዊው እውነታ እና የብዙሃኑ የደሃ ህዝብ ኑሮ ተዘንግቷል። መላ ቴሌቪዢኑ ጉድለቶቻችንን፣እድፎቻችንን፣ጭቅቅቶቻችንን፣ቅማል፣ ቁንጫ ና ትኋኖቻችንን ዘንግቷዋል።የበቆሎ ቆሎ ያረረበት ነጭ ደሃ ዜጋ እንደሌለ ተቆጥሯል።
የዘፈን ክሊፖቻችን፣ድራማዎቻችን ወዘተ ሁሉ ሣይቀሩ ከድህነት እንድንወጣ የማያደርጉ፣ፈጽሞ እንድንቆጭ የማይጎተጉቱ ናቸው።ቱልቱላ ነው የሚያሥጮሁት።ባዶ ጩኸት ነው የሚያሰሙት።አይናችን እያየ በሃሳብ ቂቤ ያጠጡናል። ዓይን ተከፍቶ ህልም የሚታለምበት ዓለም ውስጥ ያሥዳክሩናል።(…።)
የእኛሥ የከተሞቹ ይሁን፣ሰማኒያ ፐርሰቱን ገጠሬ መርሳት ምን ይባላል??? “ቂጥ ገልቦ ክንብንብ” ይሉሃል ይሄ ነው።
ሰዎች፣ ከትወራ በኋላ ድርጊት ካልተከተለ ምን ፋይዳ አለው?? “ወደፊት እንቡጡ የበዛ የሚያጠግብ ዳቦ ትበላለህ ።” ሣይሆን ፣”በህግ መሠረት ዛሬውኑ ፣እንቡጡ የበዛ ዳቦ ፣ዳቦ የመጋገር ፍቃድ ያወጡ፣አምራቾች ለተጠቃሚው ያቅርቡ ።”የሚል ህጋዊ ትዕዛዝና ቁጥጥርን ነው ፤ ዜጋው የሚፈልገው የሚዋጥ ሳይሆን የሚበላ ዳቦ ነው።የስንዴ አቅርቦትን እና ውድነትን ምክንያት እያደረጉ እንደኪኒን የሚዋጥ ዳቦ ፣ያውም ዋጋ ጨምረው መሸጥ አግባብ አይደለም።” ባይ መንግሥት ዜጎች ይሻሉ።
በሁለት ሺ አሥራሁለት ፣ ዜጎች በግለሰብ ደረጃ እንዲያሥቡ ና የቡድን ወይም የመንጋ አሥተሳሰብን እርግፍ አድርገው እንዲተው መንግሥት ራሱ ከመንጋ አሥተሳሰብ መላቀቅ ይኖርበታል።
በስድስቱ የጳጉሜ ቀናት እየተቀነቀኑ ያሉት ሃሳቦች ፣ መንግሥት የቆመበትን ችካል የሚነቅሉ ናቸው።መንግሥት ግን ዛሬም ሰው ፣ሰው መሆንን ፣ ሁሉም ዜጋ በህግ ፊት አንድ ዓይነት ሰው መሆኑን አይሰብክም። ችካሎቹ ፣ የቋንቋ አጥሮቹ ይፈረሱ አይልም።ቢያንስ ከኤርትራ ለመማር እንኳ ዝግጁ አይደለም።በኤርትራ ዘጠኝ ቋንቋ ተናጋሪ ብሔረሰቦች አሉ ፣ሆኖም ፖርቲ ና ክልል የላቸውም። ከቶስ በዓለም እንደእኛ ዓይነት የሀገር ፍቅርን የሚሸረሽር መንግሥታዊ አደረጃጀት አለ ወይ?? እርግጥ ነው፣በቲዎሪ ደረጃ ሀገር አለን ።በተግባር ግን ሚሊዮኖች ሀገር አልባ ነን።
ቀጥተኛ ተሳትፎ የማታደርግበት ፣ በትወራ የጦዘ ኢትዮጵያዊነት ብቻውን ዋጋ የለውም። “ከሰሜን እስከደቡብ፣ከምስራቅ እሥከምዕራብ በሀገሬ ፖለቲካ ካልተሳተፍኩ ና ዜጎች ወደው ና ፈቅደው መርጠውኝ፣ ካላገለገልኳቸው፣ዜግነቴ ምኑ ላይ ነወ።” የሚል የሀገር ፍቅር የሚያንገበግበው ቋንቋን የማያመልክ ፣በሚሊዮን የሚቆጠር በጥበብና በእውቀት የዳበረ በሰውነቱ ብቻ የሚኮራ ዜጋ የቋንቋ ፖሊቲካችን አግሎ የትም አይደርስም። ለነገው ሀገር ተረካቢ ትውልድ ኢትዮጵያ የምተባለዋን ሀገር ለማውረስ ፣ ብቻችንን ለመብላት ሥንል ከፈጠርነው የቋንቋ ፖለቲካ ወጥተን የዜግነት ፖለቲካን ማራመድም የሚበጀን ሁሉንም ዜጋ አሣታፊ ለማድረግ እንደሆነ መገንዘብ አለብን።
ደጋፊያችን ቻይናም ሆነች ፣ወዳጆቻችን የበለፀጉት ሀገሮች የሚያራምዱት የዜግነት ፖለቲካ እንጂ የቋንቋ ፖለቲካ አይደለም።እናም በአዲሱ ዓመት ትወራው ይብቃ።በተግባር ኢትዮጵያን ለማሥቀደም እንጣር።ደሞም ወደትክክለኛው የሰው መሥመር ከገባን ሀገራችንን ታላቅ ማድረግ አያዳግተንም።
በመጨረሻም ከሦሥት ዓመት በፊት ፕሬዝዳንት ኦባማ ትራምፕ እንደተመረጡ፣ በቺካጎ ያደረጉትን የሥንብት ንግግር እንድታዳምጡ በመጋበዝ ፅሑፊን እቋጫለሁ።
መልካም አዲስ ዓመት
አሜን