የብሔር ጽንፈኝነት በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር

ነሐሴ 26 ቀን 2011 ዓ.ም.

ነሐሴ 19/2011 ዓ.ም በአዳማ ከተማ በሚገኘው አዩ ኢንተርናሽነል ሆቴል ከ300 በላይ የሚሆኑ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሠራተኞች የተገኙበት ዓመታዊ ስብሰባ ተከናውኗል ፤ በስብሰባው ላይ ዋናዋ ሚኒስትር እና የቱሪዝም ዘርፍ ሚኒስተር ዴኤታዋ አልተገኙም ነበር፡፡ ስብሰባው የ2011 በጀት ዘመን ሥራ አፈጻጸምን ለመገምገምና የ2012 በጀት ዘመን እቅድ ላይ ለመነጋገር የታሰበ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በስብሰባው ላይ በስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታው የቀረበው ጉዳይ ሕገ መንግስትን የተመለከተ ነበር ፡፡ ሚኒስትር ዴኤታው በመ/ቤቱ በቁዩባቸው አጭር ወራት የሚኒስቴር መ/ቤቱ ሠራተኞች ሙሉ በሙሉ የሀገሪቱን ሕገ መንግሥት የማያውቁ መሆኑን መገምገማቸውን ተናግረው ፤ ይህንን ሥልጠና ለመስጠት ተዘጋጅቼ መጥቻለሁ በማለት ተሰብሳቢውን ስለ ሕገ መንግሥቱ አስተምረዋል፡፡ ሚኒስትር ዴኤታው በየአንቀጹ ሕገ-መንግስቱን እየተነተኑ ያስረዱ ከመሆኑም በላይ በገለጻቸው መሓል ካነሷቸው ሃሳቦች ውስጥ፡- እስከ ዛሬ ድረስ በሚ/መ/ቤቱ አንድ ብሔር የበላይነት የሚታይበት በመሆኑ ሕገ መንግሥቱ የፈቀደው የብሔረሰቦች ምጣኔ አለመኖሩን አውስተዋል፡፡ በሌላ በኩልም በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚከናወኑ ባህላዊና የቱሪዝም ዝግጅቶች፣ የቅርስ ጥገና፣ የቋንቋ ማበልጸግ ሥራዎች እንዲሁም ከደብዳቤዎች አጻጻፍ ጀምሮ ሕገ መንግሥቱን  የሚጋፉ  አሠራሮች መኖራቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ከገለጸቸው በኋላም ጥያቄ እና አስተያየት ያቀረቡ የሚ/መ/ቤቱ ሠራተኞች የ2011 በጀት ዘመን ሥራ አፈጻጸምን ለመገምገምና የ2012 በጀት ዘመን እቅድ ላይ ለመነጋገር በተጠራው ስብሰባ ላይ ዓላማውን በሳተ መንገድ አሁን ሀገሪቱ በብሔር ጉዳይና በሕገ መንግስቱ ምክንያት ከየአቅጣጫው ችግሮች በተጋጋሉበት ወቅት ጠብ ጫሪ የሆነና የጽንፈኝነት ስሜት የተሞላበት ማብራሪያ ማቅረብ ተገቢ አለመሆኑን በከፍተኛ ተቃውሞ ድምጽ አሰምተዋል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የአባይ ግድብና የአገዛዙ ተቃርኖዎቹ

በእርግጥ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ኅብረ ብሔራዊ መልክ ሊኖረው ቢገባም አሁን ያሉት ሠራተኞች በተለያዩ ዓመታት በውድድር የተቀጠሩና በሚቀጠሩበት ወቅትም የብሔር ተዋጽኦ መጠበቅ ያለበት ጉዳዩ የሚመለከተው ቀጣሪ ሆኖ ሳለ ምስኪኑ ሰራተኛ በዚህ ወቅት ለምን ከዚህ ብሔር መጣህ ለምንስ ቁጥርህ በዛ ተብሎ እንዴት ይጠየቃል?  እንዴትስ ሊወቀስ ይችላል? የሚሉ አቤቱታዎች ተነስተዋል፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚከናወኑ ባህላዊ  ዝግጅቶች፣ የቅርስ ጥገና፣ የቋንቋ ማበልጸግ ሥራዎች እንዲሁም ከደብዳቤዎች አጻጻፍ ጀምሮ ክልሎችን ያማከሉ አይደሉም ሲባልስ እነዚህ ግድፈቶች መቼ ተፈጸሙ? ተጠያቂውስ መቼ የነበረው ሚኒስትር ነው? ተብሎ በዝርዝር ሳይገመገም እንዴት በጅምላ ያለፉት የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሥራዎች  ሁሉ ትላንት በመጡ ሰው ይጠለሻሉ? የሚሉ ጉርምርምታዎች ተደምጠዋል፡፡

ዋናዋ ሚኒስትር በስብሰባው ላይ ባይገኙም የስብሰባው ሪፖርት እንደሚደርሳቸው ስለሚታመን ይህንን መላ ሠራተኛውን ያሳዘነና ያሰከፋ ጉዳይ እስከ አሁን ለምን ተድበስብሶ ይቀራል? ለምንስ ሰራተኛውን በግልጽ አወያይተው ጽንፈኞቹ ይቅርታ እንዲጠይቁ አላደረጉም? ከወራት በፊት የሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ አዲስ የአደረጃጀት መዋቅር ተግባራዊ ሲሆን እኚሁ ሚኒስተር የሠራተኞችን ድልድል በተጽእኖ በራሳቸው ፍላጎት እንዲሰራ አድርገዋል፡፡ ይህንንም ተፈጻሚ ለማድረግ በለውጡ ደስተኛ አለመሆናቸውን በግልጽ የሚናገሩት ሁለቱም የባህልና ቱሪዝም ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታዎች እና የእርስዎ ጽቤ/ት ሃላፊ ሙሉ ተባባሪ መኆናቸው ግልጽ ነው፡፡ ድልድሉ ከላይ እንደተጠቀሰው የወቅቱን የጽንፈኝነት ስሜታዊ አሰራር  የሞላበት ሲሆን ለማሳያነት ያህልም በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በድልድሉ ከተሰጡት 16 የዳይሬክተርነት ሥራ መደቦች ውስጥ 11 መደቦች በቋሚነትና በተጠባባቂነት የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታው ለመጡበት ክልል አባላት እንዲሰጥ ተደርጓል፡፡ ይህም በሲቪል ሰርቪስ የተፈቀደውን የሜሪት አሠራር በሴራ ፖለቲካ በመጥለፍ የተደረገ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:   ለቤት ቀጋ ለውጭ አልጋ - አገሬ አዲስ   

ክፍት በነበሩት ወይም በሌላ ብሔር አባላት በተጠባባቂነት ከተያዘው የዳይሬክተርነት ሥራ መደብ  ደግሞ በቅርቡ ከሰላሌ ፍቼ  ዞን ባ/ቱ በዝውውር የመጡ ሰው እንዲመደቡበት ተደርጓል፡፡ በሌሎች መደቦችም ተገቢው ሰው ከመ/ቤቱ አለመገኘቱ ከተረጋገጠ ለውጭ ተወዳዳሪዎች  ክፍት ማድረግ ሲገባ የሚቀርቧቸውን ሰዎች በዝውውር በማምጣት ላይ ይገኛሉ፡፡

ሚኒስተር ዴኤታው ይህንን የለየለት የአንድ ብሔር የበላይነት በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ውስጥ ለማስፈን በዳይሬክተሮች ምደባ የጀመሩትን ስራ እስከ ታችኛው ሰራተኛ ድረስ የሚገፉበት መሆኑን በስብሰባ ላይ ማረጋገጣቸው የሚታወቅ ሲሆን ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ የእርሳቸው ብሔር አባል የሆኑት እና የሚኒስትር ጽ/ቤት ሃላፊው እየፈጸሙላቸው ይገኛሉ፡፡

ከላይ የተጠቀሱትና የመ/ቤቱን ሠራተኞች መብት በግልጽ የሚጋፉ ብሔር ተኮር አሠራሮች ሲፈጸሙ ክብርት ዋና ሚንስትሯ እንዳላየ በመሆን መቀመጣቸው አሳዛኝም አስገራሚም ነው፡፡ በመሆኑም ክብርት ሂሩት ካሰው፤  የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር፣ ይህንን ገሀድ የወጣ የብሔር ጽንፈኝነትን እንዲያስቆሙ፣ የዘረኞችን ብልሹ አሠራርንም በግልጽ እንዲቃወሙ፣ የተፈጸሙት ሕገወጥ ምደባዎች  እና ዝውውሮች እንዲሠርዙ፣ ሚኒስተር ዴኤታዎቹም በአስቸኳይ ተነስተው በምትካቸው የዘረኝነት ሳይሆን የዘርፍ እውቀትና ልምድ ያላቸው ዴኤታዎች እንዲመደቡ እንዲያደርጉ እያሳሰብን ይህንን ካላደረጉ ግን በጽንፈኞች ተከበውና ተጠርንፈው ያለዎትን የዘርፍ ልምድና የትምህርት ዝግጅት በአግባቡ ተጠቅመው ዘርፉን ለመምራት  የሚቸገሩ በመሆኑ ሃላፊነትዎን በፈቃድዎ ቢለቁ እንደሚሻልዎት እንመክራለን፡፡

ከሠላምታ ጋር

ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሠራተኞች

 

Share