ማን ቢስምሽ ታሞጠሙጫለሽ? ፖለቲከኞችና እበላ ባይ ተከታዮች ማን መረጣችሁና ነገር የምታምሱ፤ታሪክ የምታረክሱ፤ ሕዝብ የምታናክሱ ሀገር የምታፈርሱ? ኧረ በፈጠራችሁ ወደ ቀልባችሁ ተመለሱ!

በገ/ክርስቶስ ዓባይ
ነሐሴ 24 ቀን 2011 ዓ/ም

ፖለቲካ ማለት የሕዝብ አስተዳደር እንደሆነ ምሁራን ይናገራሉ። እንግዲህ ፖለቲከኛ ደግሞ ሕዝብ አስተዳዳሪ ማለት እንደሆነ አድርገን ልንወስደው እንችላለን። ፖለቲከኞች የሚለውን ቃል ስንጠቀም ደግሞ ሕዝብ አስተዳዳሪዎች ማለት እንደሆነ እንገነዘባለን። ነገር ግን እነዚህ ፖለቲከኞች ‘ከየትኛው ዩኒቨርሲቲ ወይም ልዩ የማሠልጠኛ ተቋም ተመርቀው ነው እንዲህ ያለውን የመጠሪያ ማዕረግ ያገኙት?’ ብለን ስንጠይቅ የምናገኘው መልስ ሁሉ የሚያረካ አይሆንም። የትኛውም ታዋቂ ፖለቲከኛ ተብዬ እንዲህ ያለውን ማዕረግ የሚያገኘው ከማንም ሳይሆን ከራሡ ከግለሰቡ በመሆኑ ሁሌም ሚዛናዊና ሐቀኛ ስያሜ ሊሆን አይችልም።

በዘመናዊው ትርጉምና አመለካከት ፖለቲከኛ ማለት ውሸታም ወይም ከሐዲ የሚል ትርጉም ቢሰጠው የሚያስገርም አይደለም። አንዳንዶቹም አታላይና አጭበርባሪ የሚል ቅጽል ስም ይጨምሩለታል። ሌሎችም ሥልጣን ፈላጊ፤ ዘራፊና ጨካኝ ሲሉ ይኮንኑታል። አንዳንዶቹም ‘ከእኔ በላይ አዋቂ የለም ባይ፤ እኔን ስሙኝ የሚል እንጂ ማዳመጥን የማይፈልግ’ በማለት ይገልጹታል። ጥቂቶቹም ‘ሰላምን የማይወድ ደም አፋሳሽ ከፋፋይ የሰይጣን ቁራጭ’ በማለት ያወግዙታል።

እንግዲህ ልብ ያለው ልብ ይበል! ከዚህ በላይ በአጭሩ የተዘረዘሩት የፖለቲከኛ መገለጫዎች ናችው። ታዲያ ሕዝብ እንደነዚህ ያሉትን ሰዎች በምን መስፈርትና ሚዛን ቢመረምር የተሻሉ ፖለቲከኞችን መምረጥ ይችላል? እጅግ በጣም አስቸጋሪ ነው። ምክንያቱም እነዚህ ፖለቲከኞች ምንጊዜም ‘እበላ ባይ’ ተከታዮች አሏቸው። የፖለቲከኛ አጫፋሪዎች በራሳቸው ኅሊና የማይመሩ፤ የአእምሮ ድሁር ናቸው። በፖለቲካ አጠራር ‘ካድሬ’ በመባል ይታወቃሉ። ካድሬዎች ፖለቲከኛው ሊተገብር ያቀደውን ፕሮግራም አጥንተው ለሕዝብ የሚያስተጋቡ በቀቀኖች ሲሆኑ የዕውቀት አድማሳቸውን ለማስፋት በሚያስችል፤ የግል ተነሳሽነት ተገፋፍተው መማርና መለወጥ የሚፈልጉ አይደሉም።

ይልቁንም ካድሬዎች እንደ ለማዳ ውሻ ጭራቸውን እየቆሉና እነርሱ የሚሰግዱለትን ፖለቲከኛ ሌላውም ሕዝብ እንደ ልዩ ፍጡር እንዲያመልከው ቀን ከሌት ተግተው ይሰብካሉ። ስለሆነም በሕዝብ ዘንድ ፍቅርን፤ ሰላምን፤ ተግባብቶና ተሳስቦ በአንድነት መኖርን ሳይሆን፤ ጥላቻን፤ መጠራጠርንና አለመተማመንን በመዝራት የቂም በቀልንና የአለመግባባትን ችግኝ በመትከል፤ ለአለው ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ለቀጣዩ ትውልድም የሚተርፍ ዘላቂ ጠብን ይኮተኩታሉ። እንዲህ ካላደረጉ ሕዝቡ እርስ በእርስ መወያየትና መደማመጥ ስለሚጀምር ዕድሜያቸው እንዳያጥር ይፈራሉና!

ታዲያ ወገኔ ንቃ! ማንኛችንም ወደንና ፈቅደን ወይም መርጠን ከአንድ ዘር አልተፈጠርንምና ከልብ ልናስተውል ይገባናል። ማንኛችንም ኦሮሞ፤ ትግሬ፤ አማራ፤ ጉራጌ፤ አፋር፤ሱማሌ፤ሲዳማ፤ ወላይታ ወይንም ኑዌርና አኝዋክ መሆን ፈልገን አልተወለድንም። ከእኛ ቁጥጥር ውጭ በሆነ የአምላክ ረቂቅ ምሥጢር ግን ከአለመኖር ወደ መኖር መጥተናል። የመኖሪያ ቀያችንንም ብንመለከት ማንኛችንም ብንሆን እንዲሁ መርጠን አልተወለድንበትም። የአፍ መፍቻ ቋንቋችንም ቢሆን እንዲሁ ነው። ሌላው ቀርቶ ኢትዮጵያዊ፤ ወይም አፍሪካዊ መሆንም ፈልገን አልተፈጠርንም። የሁላችንም ታሪክ ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ነው ፡ ሁለመናችን ከእኛ ፈቃድና ቁጥጥር ውጭ የተከናወነ መሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል። ከሁሉም በላይ ደግሞ እንድንተባበርና እንድንረዳዳ ሰው መሆናችን ብቻ በቂ ነው። ይህንንም የሚያጠናክርልን ኢትዮጵያ የምትባል ታላቅ አገርና አረንጓዴ ቢጫ ቀይ የሆነ መለያ ሰንደቅ ዓላማ አለን።

ይህችን አገራችንን አምላክ ነፍሳቸውን ይማርና አያት ቅድመ አያቶቻችን በአንድነት ሆነው ደማቸውን አፍስሰው፤ አጥንታቸውን ከስክሰው፤ ታሪኳን ጽፈው፤ ሉዓላዊነቷን አስከብረው ለእኛ ለልጆቻቸው አቆይተውናል። ይህ ሊሆን የቻለው ሁሉንም ሕዝብ በአንድነት የሚያስተሳስረውና የሚያስተባብረው የዘውድ አስተዳደር መሆኑ ነበር። ነገር ግን በኢትዮጵያ ታሪክ በሚቀኑ የውጭ መሠሪ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት ለብዙ ም ዕተ ዓመታት በገናናነት የዘለቀው የአንድነት አርማ የሆነው የዘውድ አስተዳደር በ1967 ዓ/ም ከተወገደ በኋላ፤ ሁሉም ፖለቲከኛ፤ ሁሉም መሪ፤ የመሆን ፍላጎት አደረበት። ከዚህም የተነሣ አገራችን ለረጅም ዘመናት ያስተማረቻቸውን ብዙ የተከበሩ ምሁራንን በእርስ በእርስ ሽኩቻ አጥታለች። ብዙዎቹ ሐቀኞች ለህልፈተ ሕይወት ተዳርገዋል ፤ ፈጣሪ አምላክ ነፍሳቸውን ይማር!

እበላ ባይ ደካሞች፤ተንኮለኞችና ነፍሰ ገዳዮች ግን አሁንም አሉ። እነዚህን የአገር ጠንቆች በዕድሜ እርጅና ምክንያት ልንገላገላቸው የቀሩን ጥቂት ዓመታት ነበሩ። ምናልባት እግዚአብሔርም ምንጊዜም መሐሪ ነውና ዕድሜያቸውን ያንዘላዘለው በአጠፉት ጥፋት አዝነው ንስሐ እንዲገቡ ሳይሆን አይቀርም። ነገር ግን በዚች በቀረችው ጊዜያቸው እንኳ ተጸጽተው ሕዝብን ይቅርታ መጠየቅ ሲገባቸው፤ እንዲያውም መርዛቸውን ለአዲሱም ትውልድ በማስተላለፍ በእኩይ ተግባር ላይ ተጠምደው ይታያሉ። በዚህም ወጣቱ ትውልድ በዘር በቋንቋና በክልል ተለያይቶ ወንድሙን እንዲፈራውና እንደጠላት እንዲመለከተው መስበኩን ቀጥለውበታል። እንግዲህ ሐቁ ይህ ሆኖ ሳለ፤ የአገራችንን ውድቀት የማንፈልግ ሁሉ እያየን ዝም ማለት የለብንም።

እጅግ በጣም የሚገርም ሌላም ጉዳይ አለ። መሬትን በተመለከተ እኛ ሰዎች ፍጹም ጨካኝና አረመኔ ስለሆን ከምድረ ገጽ አጠፋናቸው እንጂ፤ አንስሳትም እኰ በዚህ ዓለም የመኖር መብት ነበራቸው። ምክንያቱም የተፈጠሩት በዚህ ዓለም እስከሆነ ድረስ መሬት የእነርሱም ድርሻ ጭምር ነበረች። ነገር ግን እንደሰው ስለማይናገሩና፤ ኃይሉም ስለሌላቸው መጠለያቸው የሆነው ጫካና ዱር በሰው ልጅ ተመንጥሮ ብዙዎች እንስሳት ከምድረ ገጽ የጠፉ ሲሆን አንዳንዶችም ሊጠፉ የተቃረቡ በመሆናቸው፤ በተቻለ መጠን አስፈላጊው እንክብካቤ እንዲደረግላቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ በጸጸት ይመከራል። እንዲያውም በበለጸጉ ሀገሮች የእንስሳት መብት ተከራካሪ ድርጅቶች ተቋቁመው ሽንጣቸውን ገትረው ይከራከሩላቸዋል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ዓባይ እንደ ዋዛ--ኢትዮጵያዊነትን አጥፍቶ ዓባይን ለመታደግ ይቻላልን? - አክሎግ ቢራራ (ዶ/ር) - 2

እንዲያው የውጩን አነሳሁ እንጂ በእኛም አገር የተሠራ ድንቅ ነገር አለ። ፃድቁ ዮሐንስ በመባል የሚታወቁት ንጉሠ ነገሥት ጎንደር ከሚገኘው ቤተ መንግሥታቸው አቅራቢያ ድንገተኛ ችግር የአጋጠመው ሰው አቤቱታውን የሚያሰማበት ደወል አዘጋጅተው እንደነበር ይነገራል። ታዲያ ከዕለታት አንድ ቀን ይህ ደወል ይደወላል። ንጉሡም ሰምተው ከባለሟሎቻቸው አንዱን ጠርተው ሂድ ይህን ሰው ጥራ ይሉታል። መልክተኛውም ተመልሶ ኧረ ማንም የለም ጃንሆይ ይላል። ተንሽ ቆይቶም እንደገና ይደወላል፤ ንጉሡ አሁንም መልከተኛ ይልካሉ፤ እሱም አንድ አህያ ናት እየታከከች የምትደውለው እንጂ ሰው የለም ይላቸዋል።

እርሳቸውም ጻድቅ ናቸውና ቶሎ ብልከህ አህያይቱን አምጣት በምማለት ያዛሉ። አህያይቱ ስትመጣ  ጀርባዋ በጭነት ብዛት ተገጥቦ በቁስል እየተሰቃየች ኖሯል። ንጉሡም ይህንን እንደተረዱ ባለቤቱን አስጠርተው ሳትድን ምንም ዓይነት ጭነት እንዳይጭንባት ከማዘዛቸውም በላይ፤ ማንኛውም ቁስል ያለበት እንስሳ ለጭነት እንዳይውል በአዋጅ ማገዳቸው ይነገራል።

በተጨማሪም በዚሁ በጎንደር ከአብዮቱ በፊት የነበሩ ከንቲባ ማሞ ወልደሰንበት፤ በጎንደር ከተማ ያገለግሉ የነበሩ ጋሪዎች፤ ቀንጃ ፈረስ ያላቸው መሆኑን በማረጋገጥ የንግድ ፈቃድ እንዲታደስ ያደርጉ እንደነበር ይታወቃል። ምክንያቱም አንዳንድ ሰዎች በአንድ ፈረስ ብቻ ቀኑን ሙሉ ሊሠሩ ስለሚችሉ እንስሳውን በጭካኔ እንዳይጎዱት ለማድረግ ታስቦ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል።

የአደጉ አገሮች ከእኛ እጅግ በጣም ብዙ እርቀው ሄደዋል። ይህ ብቻም ሳይሆን የእንስሳት ሆቴል አላቸው። ድመት እና ውሻ ያላቸው ቤተስቦች ወደ ሌላ ሀገር ሲሄዱ (በአብዛኛው ይዘዋቸው ይሄዳሉ) እንስሳቱን አብረው መውሰድ ካልቻሉ ግን ወደ ሆቴል ያስገቧቸውና በዚያ ሆነው እስኪመለሱ በእንክብካቤ ይቆያሉ። ለምሳሌም ከታመሙ ገብተው የሚታከሙበት የእንስሳት ሆስፒታል አላቸው። ክሊኒኩ ግን በየቦታው ነው። ድንገት ከቤታቸው ወጥተው የባዘኑ (ቤታቸው የጠፋባቸው) እንስሳትን ተቀብሎ ባለቤቶቹ ጋር የማገናኘት አገልግሎት የሚሰጥ ድርጅትም አላቸው። የእንስሳት ምግብ ቤትና የመዋቢያ ቦታ አላቸው፤ ታዲያ የእንስሳቱ ባለቤቶች ቢያንስ በሳምንት አንድ ቀን ወደ ምግብ ቤት በመውሰድ ይመግቧቸዋል።

‘ከሩቅ ዘመድ የቅርብ ጎረቤት’ እንዲሉ፤ አጠገባችን ያለውን ወንድማችንን እንድንጠላ የሚሰብከንን የፖለቲከኛ አፈቀላጤ ተቀብለን የምናስተናግድ ከሆነ፤ በመሬት በዕድሜ ልክ የሕሊና ወቀሳ ስንሰቃይ እንኖራለን፤ በሰማይም ወንድማችንን እንደ እራሳችን አላየንምና የሚጠብቀን የዘለዓለም ፍርድ ይሆናል።

የፖለቲከኛ ካድሬ ድንጉል ማለት ነው።  አሁን በአገራችን ያለው ሁኔታም ተመሳሳይ ነው። የዘር ፖለቲካ ለኢትዮጵያውያን እንደማይሠራ በተደጋጋሚ ተነግሯል። ይሁን እንጂ የሐሳብ ልዕልና የሌላቸው ደካሞች በዘር አጥር ተከልለው የዕለት ኑሯቸውን ለመኖር የሚያስችል እንደ ሥራ ፈጠራ አድርገው ይመለከቱታል።

ፖለቲከኞች፤ እኛ እንወክላችኋለንና ገንዘብ አዋጡ በማለት የየዋሁን ሕዝብ ኪስ እጥብ እያደረጉ፤ ለሕዝብ የሚጠቅም ሥራ መሥራት ሲገባቸው እንዲያውም የሐሰት ትርክት በመፍጠር በሕዝብ መካከል የልዩነት ግድግዳ መገንባትን ሥራዬ ብለው ይዘውታል። ሕዝብ ከተፋቀረና ከተስማማ የፖለቲከኞች ሚና ዜሮ ይገባል። ሁሌም ድንጉላን ሕዝብን በማታለልና በማማለል እኩይ ተግባራቸውን ያከናውናሉ።

በተለይ የዘር ፖለቲካ የዋሁን ሕዝብ ከወገኑ በመለየት በጥርጣሬ እንዲኖር ማድረግ ነው። እንዲህ ያለው የፖለቲካ አካሄድ የአስተሳሰብ ድሁር የሆኑትና በበታችነት ስሜት እየተሠቃዩ ያሉት የሚጠቀሙበት ዘዴ ነው። ነገር ግን ሕዝብ ሊገዛው የሚችል ምጡቅ አስተሳሰብ ቢኖራቸው፤ በዘር ጉሮኖ ሳይታጠሩ ስለአገር አቀፍ፤ አልፎም አህጉር አቀፍ፤ ላቅ ሲልም ዓለም አቀፍ አጀንዳ ይዘው በኩራት ይቀርቡ ነበር።

ደካሞች ስለሆኑ ግን፤ ሌላው ቀርቶ በአንድ ሐሳብ እንኳ ጸንተው ለመቆም የሚያስችል ጥንካሬ የላቸውም። በየጊዜው እንደ እስስት ይለዋወጣሉ፤ ድርጅታቸውንም እንዲሁ ይቀያይራሉ። ዓላማቸውና ዕቅዳቸው አንድና አንድ ብቻ ነው፤ ሥልጣን ላይ መውጣት ብቻ! እንጂ ለሕዝብ የሚሆን አንዳች ለውጥ እናመጣለን ወይም ዲሞክራሲ እና ፍትህ እናሰፍናለን ብለው እንዳልሆነ መጠርጠር ተገቢ ነው።

ከአሁን ቀደም በዚሁ የማታለያ ዘዴያቸው የሕዝብን ቀልብ ስበው የነበሩት አንዳንድ ታዋቂ ፖለቲከኛ ተብየዎች፤ በእስር ቤት ሲማቅቁ በነበረበት ወቅት በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በአንድነት በመሆን እንዲፈቱ ድምፅ ሆነውላቸው እንደነበርም አይዘነጋም። እንዲህ ያለው አንድነት በሕዝብ ሲካሄድ በኢትዮጵያዊነታቸው እንጂ ዘርን መሠረት አድርጎ አልነበረም። ለምሳሌም ብንጠቅስ ለጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፤ለጋዜጠኛ ተመስገን ደሣለኝ፤ለወ/ት ብርቱካን ሚዴቅሣ፤ ለወ/ት ርዕዮት ዓለሙ፤ ለዶ/ር መራራ ጉዲና፤ ለአቶ አንዱ ዓለም አራጌ፤ለአቶ ሀብታሙ አያሌው፤ ለአቶ አንዳርጋቸው ጽጌና ለአቶ በቀለ ገርባ፤ ወዘተ. ጥቂቶቹ ናቸው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሰውእየው(አንድ ሁለት) (አጭርልብወለድ) በመኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

የአምላክም ፈቃድ ሆኖ እነዚህና ሌሎችም በሰላም የመፈታት ዕድል አጋጥሟቸዋል። ነገር ግን ከጥቂቶቹ በስተቀር አብዛኛዎቹ በተለይ ፖለቲከኞች፤ እንዲፈቱ የጮኸላቸውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ውለታ እረስተው ጭካኔ የተሞላበት ክኅደት እየፈጸሙበት ይገኛሉ። እጅግ በጣም አሳዛኝ ቅሌት ውስጥ ዘው ብለው ገብተዋል። አንዳንዶችም ምነው ባልተወለደ እንደሚባል የተረገመ ልጅ፤ ምነው ከእሥር ባልወጡ የሚያስብል ደረጃም የደረሱ ጨካኝ ከሐዲዎች አሉበት።

ከቋንቋ ጀምሮ የአንድን ማኅበረሰብ እስከመኖር ጭምር በድፍረት የካዱ ናቸው። እንዲህ ያለው ጉዞ ይብላኝ ለእነርሱ ለተዋረዱት እንጂ የኢትዮጵያ ሕዝብማ ንቋቸዋል። የአላቸውን የዘር ጥላቻ፤ ምንም ነፍስ በሌለው ቋንቋ አሳበው በልባቸው ያለውን ጥልቅ ጥላቻ ገልጸውበታል። መስሏቸው ነው እንጂ ወንዝ አይሻገሩም፤ ሲቋምጡለት የነበረውን ሥልጣንም ሲያምራቸው ይቀራል እንጂ አያገኙትም። ይህንን እርግጠኛ ሆኖ መናገር ይቻላል።

ወገኔ ንቃ! እንደ አባት አያቶቻችን ጥበበኛ የምንሆንበት ጊዜ ቢኖር አሁን ነው። አባቶቻችንን የአውሮፓ ቅኝ ገዥዎች ለማታለል ሞክረው ነበር። ነገር ግን ፈሪሃ እግዚአብሔር ያላቸውና ጥበበኞችም ስለነበሩ አብዛኛዎቹ በጊዜያዊ ጥቅም አልተታለሉም። ባላምባራስ አዋሎምን ማስታወስ ተገቢ ነው። ባላምባራስ አዋሎም ኅሊናቸውን ለጥቅም ቢሸጡ ኖሮ የአድዋ ታሪክ ሊቀየር ይችል ነበር። ጀግናው ዘርዓይ ደረስ በሮም አደባባይ ላይ እንኳ ሆኖ የወገኑን ስቃይና ውርደት ማየት ኅሊናው አልፈቀደለትም። የጀግናው አብዲሳ አጋን ተጋድሎ (በኢጣልያ በርሃዎች)ን ይመልከቱ፤ አብርሃ ደቦጭ፤ ሞገስ አስገዶምና ስምዖን አደፍርስ በግራዚያኒ ላይ የወሰዱትን ቆራጥ እርምጃ አሁን ላይ ሆነን ስንመረምረው ለሀገራቸው ክብርና ለወገናቸው የነበራቸው ወኔና ፍቅር ከአምእሮ በላይ ነው። የደጃዝማች በላይ ዘለቀን፤የአብቹን የውጊያ ስልትና የማጥቃት ጥበብ (የሐበሻ ጀብዱ)ን ይመልከቱ፤ በምዕናባችን ስንቃኘው እንዲህ ዓይነት ታላቅነት፤ ለሀገር ነፃነትና ለወገን አንድነት የመቆርቆር ልዕልና ከአሁኑ ትውልድ መጠበቅ ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ መገንዘብ አያዳግትም።

ነገር ግን አገራችን ኢትዮጵያ አሁንም የወላድ መካን አይደለችም። እነዚህ ከሐዲ ካድሬዎች በተለያየ መንገድ የወጣቱን ወኔ ሰልበውት ነው እንጂ፤ ለሕዝብ አንድነትና ለሀገር ሉዓላዊነት የሚቆረቆሩ እውነተኛ ዜጎች በየቦታው ሞልተዋል። በእርግጥ አሁንም ቢሆን ጀግኖች አልጠፉም ነገር ግን እንደ ጃዋር መሐመድ ያሉ በምላሳቸው ጥሬ የሚቆሉ፤ የወጣቱን ትግል በመስለብ ለግል አጀንዳቸው መጠቀሚያ አውለውታል። የኦሮሞ ልጅ የሆነ አማርኛ እንዳይማር ሲወስኑ ምን አስበው እንደሆነ የኦሮሞ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን በጥሞና ሊያጤኑት ይገባል። ምስጢሩ እሩቅ አይደለም፤ እነርሱ ባለሥልጣን፤ የኦሮሞ ሕዝብ ደግሞ ዕድሜ ልኩን የእነርሱ አገልጋይ እንዲሆን በማሰብ ለመሆኑ መጠራጠር አያስፈልግም። በቀለ ገርባም ሆነ ፕሮፌሰር ተብየው ሕዝቅኤል ገቢሳ ለኦሮሞ ሕዝብ አስበው እንዳልሆነ መታወቅ አለበት።

እስኪ ማን ይሙት፤ ቋንቋ በምን መስፈርት ነው አንድን ወገን ነጥሎ የሚጠቅም። ቋንቋ አገር፤ ወገንና ዘር የለውም። የአወቀውንና የአከበረውን ግን ይጠቅመዋል.፤ ያገለግለዋል። በበታችነት ስሜት እየተናጠ የሚገኘው ስግብግቡና ጠባቡ፤ የጋን መብራት የሆነው ሕዝቄል ገቢሳ በኦሮምኛ ቋንቋ ተምሮ ነው የፕሮፌስርነት ማዕረግ አለኝ እያለ የሚደነፋው? እንግሊዝኛ ቋንቋ በእኔ መጠቀም አትችልም በማለት የዘር መድሎ አድርጎበታል? በፍጹም አይደለም። እንግዲህ ሕዝቄል ገቢሳ እንግሊዝኛ በመማሩ እንዲህ ያለ ደረጃ ላይ ያደረሰው ከሆነ፤ ሌላው የኦሮሞ ሕዝብ የራሱን ቋንቋ የሆነውን አማርኛ እንዳይማር የሚከላከሉበት ምክንያት ምን ሊሆን ይችላል?

ጃዋር መሐመድም ሆነ በቀለ ገርባና ሕዝቄል ገቢሳ አማርኛ ይናገራሉ፤ ነገር ግን አማርኛ በመናገራቸው ተጠቀሙ እንጂ የተጎዱት ነገር የለም። አለ የሚሉ ከሆነ በግልጽ መናገር አለባቸው። የለም የሚሉ ከሆነም ደግሞ ሌላው የኦሮሞ ሕዝብ እንዳይማር ማዕቀብ የሚጥሉበትና የሚያስፈራሩበት ምክንያት ምንድን ነው? በደንብ ለሚያሰላስለው ግን፤ ለኦሮሞ ሕዝብ ተቆርቁረው እንዳልሆነ መረዳት አይከብድም። እነርሱ መሳፍንት ሆነው የኦሮሞ ሕዝብ ደግሞ ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ወገኖቻቸው ጋር ሳይገናኙ እንደ ከብት በዘር በረት ታጉረው የእነርሱ የዕድሜ ልክ ሎሌ ሆነው እንዲኖሩ የሚታትሩ መሆናቸውን መገመት፤ ብልህነት ባይሆን እንኳ ድክመት ሆኖ መታየት የለበትም። በተለይ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ትንሽ ላቅ ያለ ደረጃ ላይ ስለሆኑ የጉዳዩን አሳሳቢነት ተረድተው በጥልቀት በመመርመር ወገናቸው ለሆነው ሠፊው የኦሮሞ ሕዝብ ማስተማር አለባቸው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ዛሬም በሱስና መደመር ተጠምደህ ፋኖን የማትደግፍ ካለህ! ተሱስህ ተላቀህ ወደ ጎበዝ አለቃህ!

ይህንን ጉዳይ በተለይ ከሠላሳ ዓመት በታች ያለው የኦሮሞ ወጣት የአማርኛ ቋንቋ እንዳይማር በሕወሃትና ጃሻ አጃግሬ በሆነው ኦሕዴድ፤ ታላቅ ደባ የተፈጸመበት መሆኑን የሚዘነጉ አረጋውያን ወላጆች አይገኙም። ይህንን እኩይ አስተሳሰብ ያለውን ክፍተትና በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ሆነ ተብሎ የተጫነውን የኋልዮሽ ጉዞና ከሌላው የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ የመነጠል አዝማሚያ እየተረዱት ስለሆነ የማነቆውን ሴራ ጠንክረው መታገልና ማክሸፍ ይጠበቅባቸዋል።

ብዙ የኦሮሞ ምሁራንም ይኼ ጉዳይ ትክክል አለመሆኑ ጠፍቷቸው አይደለም። ነገር ግን ‘አፍ ያለው ያግባሽ ከብት ያለው?’ እንዲሉ ጥቂት ምላሳሞች በሚያሰሙት ጩኸት ድምፃቸው ስለታፈነ በግርምት እየታዘቡ መሆኑ አይካድም። ይሁን እንጂ ዝም ብለው ከሚቆዝሙ አንድ እርምጃ ወደፊት ተራምደው ሐቁን በማፍረጥረጥ ለኦሮሞ ሕዝብ የሚጠቅመውን ማስተማር አለባቸው።

ወያኔ ሥልጣን እንደያዘ፤ ሕወሃቶች ‘ለኦሮሞ ሕዝብ የአንድ መቶ ዓመት የቤት ሥራ ሰጥተነዋል’ በማለት ይስቁና ይሳለቁ እንደነበር አይረሳም። ከዚህ ውስጥ አንደኛው የግእዝን ፊደል በላቲን እንዲለውጡ ማስደረጋቸው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከሌላው የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ጋር እንዳይግባቡ የአማርኛን ቋንቋ እንዳይማሩ የሚያግድ ደንብ መደንገጋቸው ነው።

እንዲህ ዓይነቱን መሠሪ ተግባር የኦሮሞ ልሂቃን አያውቁትም ማለት ዘበት ነው፤ ነገር ግን በጊዜያዊ ጥቅም ተታለው  የወገናቸውን ዘለቄታዊ እሴት ሊያስጠብቁለት አልቻሉም። አብዛኛዎቹ እበላ ባይ (opportunists) ናቸው። ጥቂት ቢኖሩም በጣት የሚቆጠሩ ሲሆኑ ከእነዚህ ውስጥ ፕሮፌስር መራራ ጉዲና፤ መምህር ታዬ ቦጋለ፤ወጣት ቶለሳ ኢብሳ እና ወጣት ዳዊት አርአያ ተጠቃሽ ናቸው። ሆኖም ግን ፕሮፌሰር መራራ ጉዲና አንድም የፖለቲካ ምሁር ስለሆኑ ተንኮሉንና ምስጢሩን አብጠርጥረው ስለሚያውቁ ሊሆን ይችላል እንደሌሎቹ እበላ ባዮች ማለትም ጃዋር ሞሐመድ፤ፕሮፌሰር ሕዝቄል ገቢሣ፤ በቀለ ገርባ እና ፀጋዬ አራርሣ እንደልብ የሜዲያ ሽፋን ሊያገኙ ስላልቻሉ አቋማቸውን ለሠፊው የኦሮሞ ሕዝብ ለማስተላለፍ አልታደሉም። በዚህም ምክንያት ከላይ በተጠቀሱት ጊዜያዊ ጥቅም ፈላጊዎች ጩኸትና የአፈና ስብከት እውነቱን እንዳያስተላልፉና እንዳያስተምሩ ታግደዋል ግን ማለት አይቻልም።

ለዘመኑ ቴክኖሎጂ ምስጋና ይግባውና ከላይ የተጠቀሱት የኦሮሞ ወጣቶች ለሕይወታቸው ሳይሳሱ ለወገናቸው በመቆርቆር ለኦሮሞ ሕዝብ የሚበጀውንና የሚጠቅመውን በድፍረት እየገለጹ ይገኛሉ። ቶሎሳ ኢብሳም ሆነ ዳዊት አርአያ ዘረኝነትንና ጠባብነትን የሚጠየፉ፤ ነገር ግን በሰብአዊ መብት፤ እኩልነትና በአገር አንድነት የሚያምኑ፤ ለዚህም ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ጠንክረው የሚሠሩ ወጣቶች መሆናቸውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ያውቃል። በአንፃሩም እነጁሀር መሐመድ፤ሕዝቄል ገቢሣ፤ በቀለ ገርባ እና ጸጋዬ አራርሣን የመሳሰሉ የጋን መብራቶች ግን የኦሮሞን ሕዝብ ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለመነጠል የሚያስችለውን የኦነግ አጀንዳ ይዘው በማቀንቀን ላይ መሆናቸው እጅግ በጣም ያሳዝናል። እነዚህ ግለሰቦች ምንጊዜም ግባቸው የግል ጥቅም እንጂ ለሠፊው የኦሮሞ ሕዝብ አስበው እንዳልሆነ መታወቅ አለበት።

ኦነግም በአንድ ወቅት ማለትም ከሽግግር መንግሥቱ ማዕድ እንዳይቋደስ እርህራሄ በሌለው ጭካኔ፤ በጠመንጃ አፈሙዝ ብዙ ታጋዮቹን አስገድሎና አሳስሮ ሲያሰቃይ ቆይቶ፤የታጋዮችን መስዋዕትነትና ቃል ኪዳን ከምንም ባለመቁጠር፤ በኃይል ገፍተሮ ያስወገደውን የሕወሃት ወያኔን የመገንጠል አጀንዳ ለማስፈጸም በትጋት እየሠራ መገኘቱ እጅግ አሳፋሪ ተግባር ነው። ኦነግ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የኦሮሞ ታጋዮችን ለወያኔ ገብሮ ሲያበቃ ከእነርሱ ደመኛ ጋር በመቆም ስውር ወኪል ሆኖ የመቅረቡ ምልክት ራስ ወዳድና የጊዜያዊ ጥቅም ተገዥ መሆኑን ከማረጋገጥ ያለፈ፤ ለኦሮሞ ሕዝብ የሚበጅ ሌላ የሠራው የሚያኮራ ጀግንነት የለውም።

እራሳቸውን ቄሮ አድርገው የሚቆጥሩ ምሁር የኦሮሞ ወጣቶች መከተል ያለባቸው፤ ቶሎሳ ኢብሳንና ዳዊት አርአያን እና ምንም ዓይነት የበታችነት ስሜት በሌለው በሙሉ ልብ ለሐቅ የቆመውን የመምህር ታዬ ቦጋለን አቋም መሆን እንዳለበት በድፍረት መናገር ይቻላል። ቋንቋ አገርም ሆነ ዘርና ጎሣ የለውም። የተማረውንና ያወቀውን ጥሎ የማይጥል እውነተኛና ሐቀኛ የሕይወት ጓደኛና የኅልውና ቁልፍ መሆኑ እየታወቀ፤ የኦሮሞ ሕዝብ ተለይቶ ሌላ ቋንቋ እንዳይማር የሚገደድበት ምክንያት ግልጽ አይደለም። ቋንቋ መማር ሕይወትን ያተርፋል እንጂ አይገድልም፤ ያበለጽጋል እንጂ አያከስርም፤ ዕውቀትን ያዳብራል እንጂ አያደነቁርም። እዚህ ላይ ‘Life’ ሕይወት ከተባለ የቼኮዝሎቫኪያ መጽሔት ባገኘሁት ጥቅስ ጽሑፌን ላጠናቅ። ‘The more languages you know the most of a man you are!’ ‘ብዙ ቋንቋ መናገር በቻልክ ቁጥር ስብዕናህ የላቀ ይሆናል።’

-//-

 

1 Comment

  1. Yezemenu Partiwoch ye hodam Tirikim new..hodam partewoch hizb yegodalu..Ende Ayele chamiso yalut partewoch be 1997 Ye hizbin Dil le weyane shetewal…Hizbu hodamochin yekir malet yelebetim.

Comments are closed.

Share