በገ/ክርስቶስ ዓባይ
ሐምሌ 27 ቀን 2011 ዓ/ም
ዓለማችንን ሲያስጨንቃት የነበረው የቀዝቃዛው ጦርነት እ.ኤ.አ በ1991 ዓም በደካማው የሶቪየት ፕሬዚዳንት በሚሃኤል ጎርባቾቭ ተሸናፊነት ከተጠናቀቀ በኋላ እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ የሦስትኛው ዓለም አገሮች ለከፍተኛ ችግር ማለትም ለዕድገታቸው መገታት፤ ለኢኮኖሚ ብዝበዛ፤ ለአገር ሉዓላዊነት አደጋና ለፖለቲካ ቀውስ ተዳርገዋል። የኢኮኖሚው ብዝበዛ በአሜሪካ በሚዘወረው የዓለም ባንክ እና ዓለም አቀፍ የገንዘብ አቅርቦት ተቋም (IMF) ቀጥተኛና ስውር ሴራ አማካይነት ነው። ይህንን በተመለከተ ወደፊት እራሱን ችሎ ማብራሪያ እንስጥበታለን።
ለአሁኑ ጉዳያችን ግን ኢራቅን፤ሶሪያን፤አፍጋሃኒስታንን፤ ሊቢያን የመንን፤ኩየትን፤ ሶማሊያን እና አገራችንን ኢትዮጵያን ማየቱ ብቻ ይበቃል። ከላይ የተገለጹት አብዛኛው አገሮች መንግሥታቸው ፈርሶ ከተሞቻቸው ተደምስሶ፤መሠረታዊ ልማቶቻቸው ተደቁሶ፤ ሕዝቦች ለረሃብ፤ ለበሽታ አልፎ ተርፎም ለከፍተኛ ሰቆቃና ስደት ሰለባ ሆነዋል።
በእርግጥ የዚህ ሁሉ ጣጣ ሕዝቦች ከፈጣሪ አምላካቸው ሕግጋትና ትዕዛዝ ፈቀቅ በማለታቸውና ሁሉንም ነገር በትዕቢት ተወጥረው በራሳቸው ጥበበና መንገድ እንፈጽማለን በማለት ሲታገሉ ረድኤተ እግዚአብሔር ስለሚለያቸውና የርኩስ መንፈስ አስተሳሰብ ሁለመናቸውን ሲቆጣጠረው፤ ዕቅዳቸውና ተግባራቸው አልጣጣም እያለ እርባና ቢስ ሆነዋል ማለት ይቻላል።
በመሠረቱ የማርክሲዝም ሌኒንዝም አስተሳሰብ ከሕግጋተ እግዚአብሔር የሚጣላ ሳይሆን እንዲያውም የሚያጠናክርና የሰውን ልጅ እኩልነትና አንድነት የሚሰብክ ‘ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው ፤ለሁሉም እንደ ፍላጎቱ’ የሚል ዓይነተኛ መርህ አለው። ይህ አስተሳሰብ ከፈጣሪ ትዕዛዝ የሚቃረን አልነበረም። ነገር ግን ሰዎች ስንባል በተፈጥሯችን ስግብግቦች ስለሆን ለእኛ ከማለት ይልቅ ለእኔ በሚል ግለኝነት የተተበተብን በመሆናችን፤ የማርክሲዝም ሌኒንዝም ፍልስፍና በትክክል በተግባር ሊተረጎም አልቻለም።
የዚህ ፍልስፍና አንደኛው ድክመት የዲያሌክቲካል ማተሪያሊዝም ወይም የቁስ አካል ታሪካዊ ክስተት የሚለው ትንተና ሲሆን ይህም የእግዚአብሔርን ዘለዓለማዊ አምላክነትና ፈጣሪነት በመካድ ያንን የመሰለ ታላቅ አስተሳሰብ በዚህ ሰይጣናዊ ብረዛ እንዲሰናከል ሆኗል።
ይኸውም ሰማይና ምድርን የፈጠረውን ኃያል አምላክ ለመካድ በሚፈትን መልኩ በሰዎች ልብ ውስጥ ጥርጣሬን በመዝራት አልፋና ኦሜጋ ዘለዓለማዊነቱን ለማስካድ፤ እንደ በካይ መርዝ ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል። በዚህም ምክንያት የሰዎችን እኩልነትና ነፃነት የማይቀበለው የምዕራባዊያን ፍልስፍና አሸናፊ ሆኖ የበላይነቱን አረጋግጧል።
ሐቁ ይህ ሆኖ እያለ፤ የሰዎች ነፃነት እየተከበረ ያለው በዚሁ በምዕራብያኑ የካፒታሊስት ሥርዓተ መንግሥት እንደሆነ አድርገው ሕዝብን ያታልላሉ። በካፒታሊስት ሥርዓት የሰው ልጅ ጉልበት እንደሸቀጥ ይቆጠራል። ከዚህም የተነሳ ሰዎች እኩል ናቸው ለማለት አያስደፍርም። ስለሆነም ቤሳ ቤስቲን የሌላቸው ሰዎች መጠለያ አልባ ሆነው በየበረንዳው ይወድቃሉ። ድኆች የአደረባቸውን በሽታ የሚታከሙበት ገንዘብ አጥተው ያለዕድሜያቸው ለህልፈተ ሕይወት ይዳረጋሉ።
በአንፃሩም የጨቀዩ ሀብታሞች ባለብዙ ቢሊዮን ዶላር ቱጃሮች ሆነው ምድር ጠቧቸው ይንደላቀቃሉ። የሚገርመው ደግሞ በዚያው በአላቸው ላይ ተጨማሪ ሀብት ለማጋበስ እጃቸውን አስረዝመው ሲዘርፉ የሚገድባቸው የሕግ መስፈርት የለም። እንዲህ ያለውን እኩልነት መቀበል እራስን ለማታለል ካልሆነ በስተቀር ጸሐፊው ግን ፈጽሞ አይቀበለውም።
እዚህ ላይ በቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት የነበረውን የኢትዮጵያን ሁኔታ ብንመለከት ለአሁኑ ትውልድ እንደ መንግሥተ ሰማያት ሊቆጠር የሚችል ነው። በቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ኢትዮጵያችን፤ የባዕድ አስተሳሰብ ሰለባ የሆኑት ጥራዝ ነጠቅ ፖለቲከኞች አሁን እንደሚያወሩት ሳይሆን ከየትኛውም የዓለም ሀገሮች እጅግ በጣም የታፈረችና የተከበረች ነበረች። ክብር ምስጋና ለዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስና ለዳግማዊ አፄ ምኒልክ ይሁንና ክብራችንን እና ነፃነታችንን አውጀውልን አልፈዋል።
በቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥትም እስከ ዘመነ ደርግ ድረስ ይኸው ባህል በተደራጀ መልኩ ቀጥሎ ነበር። ይኸውም የአፍሪካ የዳቦ ቅርጫት፤ የአፍሪካ የውሀ ማማ፤ በመባል ትታወቅ ነበር። አፄ ኃይለ ሥላሴም በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የነበራቸው ከብርና ዝና እንዲህ በቀላሉ የሚገለጽ አልነበረም። የሰላም አምባሳደር፤ የነፃነት አባትና የፍሪካ መሥራች በመባልም ይታወቃሉ።
ንጉሡ ምዕራባዊያንን በቅኝ ገዥነት ከያዟቸው የአፍሪካና ሌሎችም ታዳጊ ሀገሮች ለቀው እንዲወጡ እልህ አስጨራሽ የሆነ ከፍተኛ ትግል አድርገው በመጨረሻም ተሳክቶላቸዋል። የዚህን አጀንዳ እ.ኤ.አ. በ1949 ዓ/ም ለዓለም መንግሥታት ማኅበር ጀኔቫ አስገብተው፤ ፋይሉ ሲገፋ ሲገፋ ቆይቶ እ.ኤ.አ በ1954 ዓ/ም ለውይይት እንደቀረበና ተቀባይነት ማግኘቱ ሲታወቅ እንግሊዝና ፈረንሣይ በመመሳጠር ሐሳቡን ተግባራዊ ለማድረግ ያፈሰስነውን መዋዕለ ንዋይና የተለያዩ ቁሳቁሶች ለማንሳት የ15 ዓመት ጊዜ ይሰጠን በሚል ሂደቱን በማራዘም የቅኝ ገዥዎች ዕድሜ ማብቂያ እ.ኤ.አ. በ1969 ዓ/ም በኦፊሴል ተግባራዊ መሆኑ በዓለም ታሪክ ሲታወስ ይኖራል።
በዚህም ሁሉም የአውሮፓ ቅኝ ገዥዎች በተለይም እንግሊዝ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በንጉሡ ጥርስ እንደ ነከሱባቸው አይዘነጋም። “የጥበብ መጀመሪያው እግዚአብሔርን መፍራት ነው” እንዲሉ፤ ንጉሠ ነገሥቱ ለዚህ ሁሉ ሞገስና ክብር የበቁት ፈጣሪያቸውን የሚፈሩና ለሕዝባቸውም የሚራሩ መሪ እንደ ነበሩ በግልጽ ይታወቃል። ጠላቶቻቸው ግን ‘ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ’ እንዲሉ በምዕራባዊያን አስተሳሰብ ተቃኝተው ስማቸውን ሲያጎድፉ ኖረዋል። በተለይ የዚያ ትውልድ ወጣቶች ዓይነተኛ ተጠያቂ ሲሆኑ አብዛኛዎቹ ያለዕድሚያቸው ተቀስፈዋል፤ አሁንም አገራችንን እየበጠበጡ ያሉት የዚያው ትውልድ ቅሪቶች ናቸው።
ሌላው ቀርቶ ንጉሡ የሚበሉትና የሚጠጡት የተመጠነ ከመሆኑም በላይ ፈጣሪያቸውን በጾምና በስግደት ያስቡ እንደነበር የቅርብ አገልጋዮቻቸው ይመሰክራሉ። ከዚህም የተነሣ በዚያችው ለኢትዮጵያ በታሪካዊ ጠላትነት በምትታወቀዋ እንግሊዝ፤ እጅግ የረቀቀ ሴራ ሲሸረብባቸው ቆይቷል። ለምሳሌም የዓባይን ወንዝ ለመገደብና ጠንካራ የሆነ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት የሚያስችል የመሠረተ ልማት ለመገንባት ከአሜሪካ መንግሥት ጋር ከ1925-27 ዓ/ም ድረስ የተከናወነው የቅየሳ ሥራ የሚዘነጋ አይሆንም።
በቀጣዩ ዓመት ማለትም በ1928 ዓ/ም የግንባታ ሥራ ከመጀመሩ በፊት በዚችው ተንከሲስ የእንግሊዝ መንግሥት ሴራና ተንኰል አሜሪካኖች ኢትዮጵያን ለቀው እንዲወጡ፤ ጣሊያን ደግሞ ከአርባ ዓመታት በፊት በዳግማዊ አፄ ምኒልክ አድዋ ላይ በ1988 ዓ/ም የደረሰባቸውን አሳፋሪ ሽንፈት እንዲበቀሉ በምክርና በማቴሪያልም እንደሚደግፉ በመገፋፋት አገራችን እንድትወረር ታላቁን ሚና ተጫውተዋል።
ከታሪክ እንደተማርነው በዳግማዊ አፄ ምኒልክ መሪነት የተከናወነው የ1988 ዓ/ም የአድዋ ድል እንዲህ በቀላሉ የተገኘ አልነበረም። በወቅቱ ንጉሡም ሆነ ተከታዮቻቸው ለፈጣሪያቸው ቅርብ ነበሩ። አምላካቸውን በጾምና በጸሎት እንዲሁም በስግደት ያመሰግኑ ነበር። ሁለመናቸውንም ለፈጣሪያቸው አሳልፈው የሰጡ በመሆኑ የጣሊያን የጦር ሠራዊት በጊዜው የነበረውን ዘመናዊ የጦር መሣሪያ ታጥቆ ቢመጣም “ኃይል የተዕቢተኛ ሳይሆን ኃይል የእግዚአብሔር ነውና” ዓለምን በአስደመመ ሁኔታ አሳፍረው መልሰውታል።
ከሁሉም በላይ የሚገርመውና የሚደንቀው ደግሞ የቆሰሉትን የጠላት ወታደሮች በማከምና፤ የተማረኩትንም ለቤተሰቦቻቸው ኀዘንና ሥቃይ መሆኑን በመገንዘብ ልብን በሚነካ ርህራኄና ይቅርታ በሰላም ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ መፍቀዳቸው ነው። እንዲህ ያለው ከሰው አእምሮ በላይ የሆነ ውሳኔያቸው ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ታላቅ ሀገር እንድትሆን አድርጓታል። በመሆኑም አገራችን በዓለም አቀፍ በተቋቋሙ ድርጅቶች በመሥራች ዓባልነት እንድትመዘገብ ምክንያት ሆኗል። ይሁን እንጂ እነመልስ ዜናዊና እንደ ኦነግ ያሉ ደቀመዝሙሮቹ ስማቸውን ለማጠልሸት የፈጠራ ታሪክ ደርሰው የአኖሌ ሐውልትን አቁመዋል። ዋናው ተዋናኝ አሁን በሕይወት የለም፤ ተባባሪዎችም እንዲሁ ዕድሜያቸው አጭር መሆኑ አያጠራጥርም።
ኢትዮጵያ የዓለም ቴለኤኮሙኒኬሽን መሥራች ዓባል፤ የዓለም ኑክሌር ኢነርጂ መሥራች ዓባል፤የዓለም ሜትሮሎጂ መሥራች ዓባል እንደሆነች ይታወቃል። እንደሚታወቀው ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ከታላቁ መሪ ከአፄ ቴዎድሮስ የወረሱትን አገራቸውን የማዘመን ራዕይ ተግባራዊ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸው ታሪክ ምስክር ነው። ነገር ግን የዳግማዊ አፄ ምኒልክን ራዕይ የተገነዘቡት እነዚሁ የኢትዮጵያ ጠላቶች የሆኑት እንግሊዞች፤ ‘ዕቅዴን ያስቀጥልልኛል’ በማለት ከሕፃንነቱ ጀምሮ በሥነ መንግሥት ዕውቀትና በታላቅ እንክብካቤ ያሳደጉትን ልጅ ኢያሱን በእሳቸው ዙፋን እንዲነግሥ መኳንቶቻቸውን አስምለው ተናዘው ማለፋቸውን በመረዳት ኑዛዜያቸው ተግባራዊ እንዳይሆን በከፍተኛ ሴራ እንዲከሽፍ አድርገዋል።
ልጅ ኢያሱ የአያቱን ራዕይ ለማስፈጸም እንዲረዳው ገና የግዛት አንድነቱን ለማጠንከር በመላ አገሪቱ እየተዘዋወረ በመጎብኘት ላይ እንዳለ ሁኔታውና አካሄዱ ያልጣማቸው እንግሊዞች በወቅቱ ሲያስተዳድሩት በነበሩት የግብጻዊው አቡን አማካይነት በመጀመሪያ ቀሳውስቱን ቀጥሎም መኳንንቱን በማሳመጽ የልጅ ኢያሱ መንግሥት በእንጭጩ እንዲቀር ከፍተኛ ተንኰል ፈጽመዋል።
የሆነው ሆኖ እንደ እንግሊዞች ቢሆን ኖሮ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር እንደ ዩጎዝላቪያ ከዓለም ካርታ ትጠፋ ነበር። ከአሁን ቀደምም እንዲሁ ኢትዮጵያ የሚለውን ስም ለማጥፋት ‘አቢሲኒያ’ የሚል ስም ሰጥተዋት እንደነበርና በተለይ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታዮችና አማራው ኢትዮጵያ የሚለው ስም ጥንታዊ በመሆኑ አዲሱን ስያሜ ሊቀበሉ ባለመፍቀዳቸው ሊጸናላቸው አልቻለም።
ምዕራባዊያን ግን የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታይ ሀገሮችን እያሳደዱ ማዳከምና ማጥፋት ስውር ፖሊሲ አድርገው እየተገበሩት ይገኛሉ። ለምሳሌ ጥንታዊ ባቢሎናዊያን በመባል የሚታወቁት የአሲርያን ሕዝቦች፤ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታይ በመሆናቸው አገር አልባ ሆነው በዓለም ላይ ተበትነው ይገኛሉ። እነዚህ ሕዝቦች እንደ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ታሪካቸውን መዝግበውና ከትበው የያዙ ስለሆኑ በስደት ዓለም እየኖሩ እንኳ በሃይማኖታቸው እጅግ የጸኑ ናቸው።
ከአሁን ቀደም እንግሊዞች ጀኔራል ናፒርን ከሕንድ በማዝመት በአፄ ዮሐንስ አራተኛ መሪነት ለአፄ ቴዎድሮስ ህልፈትና ኢትዮጵያ ከቀረው ዓለም ጋር እንዳትገናኝ በማድረግ የማዕከላዊ መንግሥት መዳከም ምክንያት ሆነው መቆየታቸው አይዘነጋም። ቀጥሎም ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን እንድትወር ድጋፍ ማድረጋቸው ይታወሳል። በመጨረሻም ከአሜሪካ ጋር በመሻረክ የደርግን መንግሥት ለመጣል በሚል ዕቅድ በኸርማን ኮህን አማካይነት አናሳው የወያኔ መንግሥት ሥልጣኑን በሞኖፖል ተቆጣጥሮ እንደፈለገ እንዲፈነጭና አገሪቱን ለማፍረስ ከፍተኛ እርብርብ እያደረገ ይገኛል።
ይህ ሁሉ ሴራና ተንኮል እየተሸረበ ሐሳባቸው ሙሉ በሙሉ ሊሳካ አልቻለም። ለዚህ ሁሉ ዋናው ምክንያት ኢትዮጵያ ባላት የጦር መሣሪያ ጥራትና ብቃት ሳይሆን አብዛኛው ሕዝብ እስላምም ይሁን ክርስቲያን በሃይማኖቱ የጸና፤ ፈሪሀ እግዚአብሔር ያለው በመሆኑ በሚያደርገው ጾም ፤ጸሎትና ስግደት እንደሆነ የሚያጠራጥር አይሆንም። በተለይ በገዳም ያሉ አባቶች ለአገራችን ብቻ ሳይሆን አንጀታቸውን በገመድ አስረው ለዓለም ፍቅር እና ሰላም ስለሚጸልዩ ነው። በነገራችን ላይ በዓለም ከፍተኛ የኦርቶዶክስ ኮሙዩኒቲ የሚገኝባት ሀገር ኢትዮጵያ መሆኗ መረሳት የለበትም።
ወያኔ እንደ ጉም ተኖ እንደጢስ በኖ መቀሌ መሽጎ ዕለተ ሞቱን የሚጠባበቀው፤ አባቶች በሚያደርጉት ጸሎት እንጂ በጦር ኃይል እንዳልሆነ ሊሰመርበት ይገባል። አሁንም ቢሆን ‘ገርድመው ብትሄድ ሸርድመው መጣች!’ እንዲሉ አገራችን ወደ ባሰና ከመቼውም ጊዜ በላይ የከፋ ክኅደትና አረመኔነት እያስተናገደች ለመሆኗ ምስክር የሚያሻ አይደለም።
ስለዚህ በአገራችን ላይ ያንዣበበው መከራ እጅግ በጣም የሚያሳስብና የሚያስጨንቅ ስለሆነ የኢትዮጵያ የግዛት ሉዓላዊነትና የሕዝቦች አንድነት የሚያሳስበውና ኃላፊነትም የሚሰማው ዜጋ ሁሉ በተለይ ደግሞ አማራው መጭውን የፍልሰታ ጾም በታላቅ ንጽሕና እና ሱባኤ ሆኖ ፈጣሪውን እንዲለምን ማስገንዘብ እወዳለሁ። እንደሚታወቀው የፍልሰታ ጾም ከሰባት ዓመት ዕድሜ ጀምሮ ልጅ አዋቂው የሚጾማት፤ በሕይወት ዘመን መፍትሔ የምታጎናጽፍ፤ ታላቅ ጾም ናትና የአገራችን ወቅታዊ ሁኔታ የሚያሳስባቸው ኢትዮጵያውያን ሁሉ በጽናት እየጾሙ ፈጣሪያቸውን መማጸን አለባቸው። የአድዋው ጦርነት ድል የተገኘው በመሣሪያ ጋጋታና ጥራት ሳይሆን በዘመኑ በነበሩ ሰዎች የጾምና ጸሎት ወጤት መሆኑን ማመን ይገባናል።
አሁንም ቢሆን ኦነጋውያን እና ጁሀራዊያን በወያኔ አማራ ጠል ፖለቲካ ተበክለው የዋሁን የኦሮሞ ሕዝብ ደም ለማፍሰስ በፈጠራና የሐሰት ትርክት እየቀሰቀሱት ይገኛሉ። የሰይጣን መላክተኛው መለስ ዜናዊ አማራውን ስለሚጠላ ብቻ በበጀት ምደባ እና የተወካዩን ብዛት ለመቀነስ ሲል የሕዝቡን ቁጥር እጅግ በማሳነስ ሲጫወት ቆይቷል። ሐቁ ከዚህ የተለየ እንደሆነ ለምሁራን የተሰወረ አይደለም። የኦሮሞ ሕዝብ ቁጥር የአማራውን ሕዝብ ቁጥር ግማሽ እንኳ አይሆንም። ነገር ግን የመለስ ጥፍጥፎች የኦሮሞው ሕዝብ ቁጥር ከአማራው የላቀ እንደሆነ አድርገው የሐሰት ፕሮፓጋንዳቸውን እየነዙ ሕዝብን ለዕልቂት እያነሳሱ መሆናቸው ያሳዝናል።
ይሁን እንጂ አማራው ፈሪሀ አግዚአብሔር ስላለው በትዕግሥትና በአርምሞ እየተመለከተ ይገኛል። ምክንያቱም አማራው በወንድሙ ላይ የጥፋት እጁን ማንሳት አይፈልግም። የሆነው ሆኖ የትዕግሥትም ልክ አለውና እንደ ሩዋንዳ ወደ የማያስፈልግ መጠፋፋት እንዳይኬድ ከአሁኑ ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ነው።
አምልኮተ እግዚአብሔር የሚካሔድባቸውን ቤተክርስቲያናትን ማቃጠልና ምንም ዓይነት የፖለቲካ አመለካከት የሌላቸውን ካህናትንና ምዕመናንን መግድልና መዝረፍ አግባብ እንዳልሆነ ይታወቃል። በመንግሥት ወንበር ላይ ያለው አካል አስቀድሞ ሥርዓት ማስያዝ ሲገባው ‘ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ’ እንዲሉ ኃላፊነቱን በአግባቡ ካልተወጣ የሕገወጦች ዓባል ከመሆን የሚለየው የለም።
በዚህ አጋጣሚ የጠቅላይ ሚንስትር ዓቢይ ባለቤት ወ/ሮ ዝናሽ ታያቸው በቅድሚያ ከመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፈ አስቴርን አንብበው ባለቤታቸውን እንዲመክሩ ለማሳሰብ እወዳለሁ። ምክንያቱም እግዚአብሔር ፍጥረቱን ከጥፋት የሚያድንበትን ዘዴ አስቀድሞ ያዘጋጃልና ማን ያውቃል በኢትዮጵያ ላይ ያንዣበበው የእርስ በእርስ ዕልቂት በዚህ ሰበብ ሊገታ ይችላልና!
ይህም ባይሆን፤ አማራነት የነጻነትና የድል አድራጊነት መንፈስ ስለሆነ ትዝብቱ ይተርፋል እንጂ ገፍቶ ከመጣ፤ አማራው በፈጣሪው ኃይል ጠላቱን ሁሉ ድባቅ እንደሚመታ ጥርጥር የለውም።
‘ድንጋይ ቢወድቅብን ይሰብረናል ብንወድቅበትም ይጎዳናል’ አሁን አገራችን የአለችበት የተረኝነት ፖለቲካ ትርክት በተለይ ለአማራው ሥነልቦና የሚመጥን ስላልሆነ፤ በመሞትም ሆነ በመግደል አገራችን ኢትዮጵያ እንደምትጎዳ በመረዳት በቅድሚያ ሁኔታውን ለኃያሉ ፈጣሪ በትህትና ማመልከት ተገቢ ነው።
‘ኢትዮጵያ ታበጽህ እደዊሃ ኅበ እግዚአብሔር!’ ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች ሲል ታላቁ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል። ከዚህም አኳያ ይህ ሱባኤ ከኒኩሌር ቦምብ ቢበልጥ እንጂ የማይተናነስ መከላከያ እንደሆነ የማይታበል ሐቅ ነውና። ሁሉም የኦርቶዶክስ ምዕመናን በታላቅ ትጋትና በፍጹም እምነት ይችን የጾም ጊዜ በሱባኤ ከልቡ መጾም ይኖርበታል። እኛንም ያገባናል የምትሉ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮችም በዚህ ጸሎት ተባባሪ ብትሆኑ ይደገፋል።
ጸሎቱ፡“ለሀገራችን ለኢትዮጵያ ሰላምና ፍቅርን አድለን፤ ፈጣሪያችን ሆይ! አንተን የሚፈራ ለሕዝብህ የሚራራ፤ ደካሞችን የማይበድል፤ ፍርድ የማይገመድል መሪ ስጠን፤ የሕዝብን መብት የሚጥስ፤ የንጹሐንን ደም የሚያፋስሰውን በረቂቅ ጥበብህ አጥፋልን፤ በዘር የሚያስበውን ለአንድ ወገን የሚያዳላውን አንሳልን፤ ሕያው አምላካችን ሆይ!ሁሉ ይቻልሃልና!” የሚል መሆን አለበት።
ይህንን መልዕክት ለመላው ኢትዮጵያውያን በማዳረስ እንድትተባበሩ በትህትና እጠይቃለሁ! ሁሌም ኃይል የሕያው እግዚአብሔር ነውና! እንደ አረመኔዎች በጉልበት ማሰብ የለብንም።
እግዚአብሔር አገራችንን ኢትዮጵያን ይባርክ!