May 1, 2019
57 mins read

“እንዴት ይረሳል…ተረሳሽ ወይ?” – ሰሎሞን ዳኞ

ሰሎሞን ዳኞ – ዘብሔረ ዓባይ
(sent to Reporter on Friday, April 19, 2019)

 

ከአንድ ዓመት በፊት አገራችን የነበረችበትን ቀውስ አልፋ እዚህ መድረሷን ሳስብ ታምር መስሎ ይታየኛል፡፡ በአስከፊ ማዕበል ውስጥ እንደምትናወጥ መርከብ የማያባራ ሕዝባዊ አመጽ ወዲያና ወዲህ ያላጋት ነበር፡፡ በሰላም ወጥቶ መግባት ብርቅ ሆኖ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ ስንቱ በሽብርተኛ ስም እየታፈሰ እስር ቤት ተወረወረ? ስንቱስ ኢሰብአዊ ድርጊት ተፈጸመበት? የስንት ኢንቨስተሮች ንብረት በእሳት ጋዬ? ስንቱ መንገደኛ በመንገድ መዘጋት ተጉላላ? ስንቱ እንደ ወጣ ቀረ? ስንቱ በሙሰኞች አበሳውን አዬ? ስንቱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተጨነቀ? … ቤቱ ይቁጠረው፡፡ ከሁሉም በላይ ሕዝቡን ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ከትቶት የነበረው የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝ ድንገት ሥልጣን መልቀቃቸው ነበር፡፡ ማነው የሚተካቸው? በሚል ከፍተኛ ሥጋት ነበር፡፡ ኢሕአዴግ ቀጣዩን ጠቅላይ ሚንስትር ለመምረጥ ዝግ ስብሰባ ባደረገበት ወቅት በሕዝቡ ዘንድ የነበረው ምጥ የሚረሳ አይደለም፡፡ ስጋቱም በአብዛኛው ኅብረተሰብ ዘንድ ተቀባይነት ያለው መሪ ተገኝቶ አገሪቱን ያረጋጋትና ከመፍረስ ይታደጋት ይሆን? ከሚል ነበር፡፡ ጊዜው ደረሰና ባልተጠበቀ ሁኔታ ዶ/ር ዓብይ አሕመድ ቀጣዩ መሪ መሆናቸው ተበሰረ፡፡ እሳቸውም ከባዕለ ሹመታቸው ቀን ጀምሮ በሚያሰሟቸው አጥንትን ዘልቀው በሚገቡ መሳጭ ንግግሮችና በሚያከናውኗቸው ተግባሮች ሰፊ ተቀባይነትን አገኙ፡፡ “ከሰማይ የተላከ ስጦታ” ተባሉ፡፡ ይዘውት በመጡት የፍቅር፣ የይቅርታና የመደመር ፍልስፍና ሁሉን እየማረኩ ከጎናቸው እንዲሰለፍ አደረጉት፡፡ ብሩህ ተስፋ መታየት ጀመረ፡፡ አገሪቱ ተረጋጋች፡፡ በደስታ ማዕበል ተጥለቀለቀች፡፡ በዕልልታ ቀለጠች፡፡ በመቃወም ብቻ የሚታወቀው በውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ሳይቀር ብርቱ መስተፋቅር እንደተደረገባት ኮረዳ በዓብይ ፍቅር አበደ፡፡ አፋፍ ላይ ደርሶ የነበረው የመበታተን አደጋም እንደ ጉም ተንኖ ጠፋ፡፡ ዓለም ተደነቀ፡፡

 

ዓብይ ምን አከናወኑ?

አብዛኛው ሰው በደንብ የሚያውቀውን ነገር በመደጋገም እንዳላሰለች እንጅ ዓብይ በብዙ ዓመታት ሊሰሩ የማይችሉትን በአንድ ዓመት ውስጥ አከናውነዋል፡፡ ኢትዮጵያዊነትን ከተቀበረበት ማውጣታቸው፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማንሳታቸው፣ በጫካ የነበሩት ተቃዋሚዎች በሰላማዊ መንገድ እንዲታገሉ በር መክፈታቸው፣ በሕዝቡ መካከል እየተገኙ የልቡን ትርታ ለማዳመጥና ለማረጋጋት መድከማቸው፣ ሙት በቃ የተፈረደባቸውን ጨምሮ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞችን መፍታታቸው፣ በተለያዩ አገሮች ወህኒ ቤቶች ሲማቅቁ የነበሩ ዜጎችን ነጻ ማውጣታቸው፣ አያሌ ሴቶችን በካቢኔአቸው ውስጥ ማካተታቸው፣ በደህንነትና በመከላከያ ተቋማት ውስጥ ከፍተኛ ለውጥ (ሪፎርም) ማምጣታቸው፣ የሚቀጥለውን ብሔራዊ ምርጫ ነጻና ፍትሃዊ ለማድረግ ቃል ከመግባት አልፈው ተጨባጭ ርምጃዎችን መውሰዳቸው፣ የፍትህ ሥርዓቱ ነጻና ተአማኒ እንዲሆን የማይናቁ ሥራዎችን መሥራታቸው፣ በኦርዶክስ ቤ/ክ አባቶች መካከል ለረጅም ዓመታት የቆየውን ከፍተኛ ቅራኔ መፍታታቸው፣ በሙስሊሙ ኅብረተሰብ ዘንድ የነበረው አለመግባባት እዲቋጭ ማድረጋቸው፣ ከኤርትራ ጋር ዕርቀ ሰላም ማውረዳቸው፣ በሙስና ላይ ከፍተኛ ምንጠራ ማካሄዳቸው፣ እንደ ሽብርተኝነት ያሉት አፋኝ አዋጆችንና ሕጎችን ማሻሻላቸው፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለመቅረፍና የአገሪቱን የዕዳ ጫና ለመቀነስ መጣራቸው፣ ከፍተኛ መጓተት የነበረባቸውን ትላልቅ የመስኖ ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁ ማድረጋቸው፣ አዲስ አበባን ውብና ማራኪ ለማድረግ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን መጀመራቸው፣ እንደ አየር መንገድና ቴሌኮሙኒኬሽን የመሳሰሉትን ግዙፍ ተቋማት ለግሉ ዘርፍ ክፍት ማድረጋቸው፣ የወሰንና የዕርቀ ሰላም ኮሚሽኖችን ማቋቋማቸው፣ መገናኛ ብዙኃን በነጻነት እንዲሰሩ በር መክፈታቸው፣ የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋታቸው፣ ታግደው የነበሩ በርካታ ድረ-ገጾችና የግል የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ መፍቀዳቸው ከሠሯቸው ውስጥ ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ ደግሜ እላለሁ ይህ ሁሉ የተደረገው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ነው፡፡

 

ይህ ማለት ግን ገና መሠራት ያለባቸው ነገሮች የሉም ማለት አይደለም፡፡ ምኑ ተነካና! ለዓመታት የተዘሩት እንክርዳዶችና የተተከሉት መርዛማ እሾኾች እንዴት በአንድ ዓመት ውስጥ ተነቅለው ያልቃሉ? ሥር የሰደደ ድህነት፣ ረሃብና ሥራ አጥነት እንዴት በ12 ወራት ይወገዳሉ? በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከዚህ በላይ እንዲሰሩ መጠበቅ ግን “ለተቀማጭ ሰማይ ቅርቡ” መሆን ይመስለኛል፡፡ የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታም ማገናዘብ ያስፈልጋል፡፡ ሁሉ ነገር በአንድ ጀንበር ሊሰራ አይችልም፡፡ “ሮም በአንድ ሌሊት አልተገነባችም” ይባል የለ ከነተረቱ!

 

በዓብይ ላይ እየተካሄዱ ያሉ ማጥላላቶች

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ለማመን በሚከብድ ሁኔታ የነበረው ፌሽታና ፈንጠዝያ ወረቱ እያለፈና የጫጉላው ጊዜ እያበቃ ያለ ይመስላል፡፡ በብዙ መስዋዕትነት የተገኘውን ውጤት የሚያጣጥሉና ጥላሸት የሚቀቡ ሰዎች ብቅ ብቅ እያሉ ነው፡፡ እንደገና እያገረሹ ያሉትን የአገሪቱን ችግሮች በሙሉ በዓብይ ላይ ለማላከክ እየሞከሩ ነው፡፡ ዓብይን እያብጠለጠሏቸው ነው፡፡ ወሬ ብቻ ነው፣ አድሎአዊ ሆኖአል፣ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ እያለ እያጭበረበረን ነው፣ አገሪቱን እያፈራረሳት ነው፣ የኦሮሞን የበላይነት ለማረጋገጥ እየሠራ ነው፣ በፕሮቲስታንት ካቢኔና አማካሪዎች የተከበበ ሆኗል፣ እወደድ ባይና ራሱን ከመጠን በላይ የሚክብ ነው፣ ምክር አይሰማም፣ ሕገ መንግሥቱን ማስከበርም ሆነ መለወጥ አልቻለም፣ ችግሮችን አቅሎ ያያል፣ ሕግ እንዲላላ ስላደረገ ሥርዓት አልበኝነት እንዲስፋፋ አድርጓል፣ እጅግ በመለሳለሱ በአጥፊዎች ላይ ርምጃ መውሰድ አልቻለም፣ በእሱ ዘመን የብሔር ግጭትና መፈናቀል በዛ፣ የክልልነት  ጥያቄ ተበራከተ፣ ለውጡ እንዲፈጥን አላደረገም፣ ወዘተ እያሉ እየከሰሷቸው ነው፡፡ ራሳቸውን የኢትዮጵያዊነት መታወቂያ ሰጭና ከልካይ አድርገው የሾሙ እነዚህ ስም አጥፊዎች እነዓብይ የኢትዮጵያዊነትን መመዘኛ አያሟሉም ለማለት እየዳዳቸውም ነው፡፡ ይባስ ብለው ስብዕናቸውን የሚነኩ ስድቦችንም እየወረወሩባቸው ነው፡፡ በአጭሩ “መፈንቅለ መንግሥት” ለማድረግ እየዶለቱባቸው ነው ቢባል ይቀላል፡፡ አብያችን፣ ማንዴላችን፣ ሳሳንልህ፣ የእኛ ማር፣ ወዘተ ሲሏቸው እንዳልነበሩ ሁሉ በዚያው አፋቸው ሌላ ታርጋ እየለጠፉባቸው ነው፡፡ የለውጡ ሞተር እየተባሉ ሲሞካሹ የነበሩት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳም ከውርጅብኙ አላመለጡም፡፡ ነገሩ ሁሉ የእምቧይ ካብ እየሆነ ያለ ይመስላል፡፡ አዎ ምድራችንን ከጉድ ያወጧት እነ ዶ/ር ዓብይ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች መሆናቸው እየተዘነጋ ነው፡፡ ለማመን ቢያስቸግርም በእርግጥ ውለታቸው እየተረሳ ነው፡፡ “እንዴት ይረሳል? እንዴት ይረሳል? ተረሳሽ ወይ?” አለ ተወዳጁ ድምጻዊ ሙሐሙድ አሕመድ ቢቸግረው!

 

እየሆነ ያለውን ነገር ሳስብ አንድ ተረት ትዝ አለኝ፡፡ ተረቱ ከሞላ ጎደል እንዲህ ነው፡፡ በድሮ ጊዜ አንድ ሰው በክረምት ወራት ወደ አንድ አገር ለመሄድ ይነሳል፡፡ ጥቂት ከተጓዘ በኋላ በአካባቢው የሚገኝ አንድ ወንዝ ከአፍ እስከ ገደፉ ሞልቶ ያገኘዋል፡፡ ወንዙን በዋና ለመሻገር እየተዘጋጀ እያለ አንድ እባብ መሻገር አቅቶት ከቦታ ቦታ ሲቅበዘበዝ አገኘ፡፡ እባቡም ወደ ሰውዬው ተጠጋና “እባክህ ወንዙን መሻገር አቅቶኛልና አሻግረኝ” ሲል ይለምነዋል፡፡ ሰውዬውም “እጅ የለህ፣ እግር የለህ ምንህን ይዤ ነው የማሻግርህ?” ሲል ይመልስለታል፡፡ እባቡም “ብቻ አንተ ፈቃደኛ ሁን እንጅ ዘዴው ቀላል ነው፤ በራስህ ላይ መጠምጠም እችላለሁ” ይለዋል፡፡ ሰውዬውም ራራለትና እባቡን በራሱ ላይ ጠምጥሞ አሻገረው፡፡ እባቡንም “በል እንግዲህ በሰላም አሻግሬሃለሁና ውረድልኝ፤ እኔም ወደ መንገዴ አንተም ወደ ፈለግኸው ቦታ ሂድ” ይለዋል፡፡ እባቡ ግን አልወርድም ይላል፡፡ ሰውዬውም ግራ ስለገባው በአካባቢው ወደሚገኝ ጫካ ሄዶ የደረሰበትን በደል ለተለያዩ አራዊት ነገራቸው፡፡ እንስሳቱም መጀመሪያውኑ አንተ ምን ዓይነት ሞኝ ብትሆን ነው እባብ በጭንቅላትህ ላይ የጠመጠምከው? ጥፋቱ የራስህ ነው እያሉ ጥለውት ሄዱ፡፡ በመጨረሻም ወደ ቀበሮ ሄደና እንድትፈርድለት ተማጸናት፡፡ ቀበሮም ጉዳዩን በጥሞና ካዳመጠች በኋላ “ይህ የተባለው ነገር እውነት ነውን?” ስትል እባቡን ጠየቀችው፡፡ እባቡም ገና መናገር ሊጀምር ሲል “አይ እንዲህማ አይሆንም፣ ወርደህ ነው መከራከር ያለብህ” ስትለው መሬት ላይ ዱብ አለ፡፡ በዚህን ጊዜ ቀበሮ ወደ ሰውዬው ዘወር አለችና “እንዴት ነው ነገሩ በእናንተ አገር ዱላ ለመደገፊያ ብቻ ነው እንዴ የሚያገለግለው?” ስትለው ወዲያው ነገሩ ገባውና በያዘው ዱላ እባቡን ቀጥቅጦ ገደለው፡፡ ሰውዬውም በቀበሮ ጥበብና ፍርድ ተደነቀ፡፡ ስለዋለችለት ውለታም አመሰገናት፡፡ ቀበሮንም “የበግ ስጦታ ላመጣልሽ እፈልጋለሁና እባክሽ አድራሻሽን ንገሪኝ” አላት፡፡ አድራሻዋን ነገረችውና ቀጠሮ ይዘው ተለያዩ፡፡ ቀበሮም ስለሚመጣላት የበግ ስጦታ እያሰላሰለች በጉጉት ስትጠብቅ ሰነበተች፡፡ በቀጠሮው ቀንም ስጦታዋን ልትቀበል ከጉድጓዷ ቸኩላ ወጣች፡፡ ሰውዬው ግን በግ ሳይሆን የቀበሮ ቀንደኛ ጠላት የሆነውን ኃይለኛ ውሻ ነበርና አስከትሎ የሄደው “ያችን ቀበሮ አሳደህ ያዝ” ሲል ውሻውን አዘዘው፡፡ ቀበሮም ባለ በሌለ ኃይሏ ሮጣ አመለጠች፡፡ ሰውዬው ባደረገባት ነገር በመገረምም “ለሰው ሞት አነሰው” ብላ ተናገረች ይባላል፡፡ ተረቱ የሰው ልጅ ማፍቀርና በጎ ነገር ማድረግ እንደሚችል ሁሉ ቃሉን የማይጠብቅ፣ የተደረገለትን ውለታ የሚረሳና ተንኮለኛ ፍጥረት መሆኑንም ያሳያል፡፡ በእነዓብይ ላይ እየሆነ ያለው ነገር በቀበሮዋ ላይ ከተደረገባት ጋር ተመሳሳይ ሆነብኝ፡፡

 

በእርግጥ እንዲህ ዓይነት ክህደት በአገራችን ሲፈጸም ይኼ የመጀመሪያ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ በሥልጣኔ ጎዳና ወደፊት እንድትራመድ እጅግ የደከሙላትና ባንዲራዋ በዓለም አደባባይ ከፍ ብላ እንድትውለበለብ ያደረጉት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ (ጃንሆይ) እንደ ሸንኮራ አገዳ ተመጥጠው ተጥለዋል፡፡ የእነዓብይን የተለየ የሚያደርገው ለውጡን ከጀመሩ ገና ዓመት ሳይሞላቸው መሆኑና ለተጨማሪ ድሎች ሳይታክቱ እየሰሩ ባሉበት ወቅት መሆኑ ነው፡፡ ለመሆኑ የአገራችን ጉዞ እንደ ግመል ሽንት ወደ ኋላ የሚሆንበት ሚስጥር ምን ይሆን? የተጀመሩ መልካም ነገሮች ብዙ ርቀት ሳይሄዱ ለምን ይጨነግፋሉ? መሪዎቻችንን እንድናዋርድ የተደረገብን አንዳች አዚም ይኖር ይሆን? እስከ መቼ በቅንነት ሊሰሩ የሚነሱ ሁሉ በሚደርስባቸው ውርጅብኝ “ለዚች አገር ያሰበ ኢትዮጵያዊ ወዮለት” እያሉ እየረገሙን ይሄዳሉ? ይህን መርገም የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ ቦታ ላይ ካልተሰበረው ለመጭው ትውልድም መትረፉ የሚቀር አይመስልም፡፡

 

ዓብይ አላጠፉምን? መወቀስስ የለባቸውምን?

ዓብይ ፍጹም ናቸው ብሎ የሚከራከር የለም፡፡ ሊሆኑም አይችሉም፡፡ አንዳንድ ስህተቶችን መፈጸማቸውም የሚካድ አይደለም፡፡ ለምሳሌ በጫካ ውስጥ አዕምሮው ሲመረዝ (brainwashed ሲደረግ) የኖረውን የአንዳንድ ተቃዋሚዎች “ሠራዊት” ቢያንስ ቢያንስ ትጥቅ ሳያስፈቱ ማስገባታቸው ከፈጸሟቸው ጉልህ ስህተቶች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ሥርዓተ አልበኝነትን ለመግታት ተጨባጭ ርምጃ አለመወሰዱም ሌላው ስህተት ነው፡፡ ይህ ችግር አገሪቱን ወደ እርስ በእርስ ጦርነት አልፎ ተርፎም ወደ ዘመነ መሣፍንት ሥርዓት እንዳይከታት ያሰጋል፡፡ እስካሁን በአጥፊዎች ላይ የማያዳግም ርምጃ እንወስዳለን ሲባል እንጅ በተግባር የታየ ነገር የለም፡፡ መንግሥት ጥርስ የሌለው አንበሳ መስሏል፡፡

 

መሪዎቻችን መወቀስ በሚገባቸው መወቀሳቸው ተገቢ ነው፡፡ ዲሞክራሲን እናሰፍናለን እያሉ ትችትን ወይም ወቀሳን ሊሸሹ አይችሉም፡፡ ነገር ግን ትችቶች አፍራሽ መሆን የለባቸውም፡፡ የስነ ልቡና ሊቃውንት “የምትተቸውን ሰው አክብረው፤ ተግባሩንም ሆነ ንግግሩን ለመተቼት ስትነሳ እንዲለወጥ የምትፈልገው ጉዳይ ላይ አተኩር” ይላሉ፡፡ ትቺት በይሆናልና በጭፍን ጥላቻ ላይ የተመሰረተ መሆን አይገባውም፡፡ በስድብ ተጀምሮ በስድብ የሚያልቅ መሆን የለበትም፡፡

 

ትችቶች ሚዛናዊ መሆንም ይኖርባቸዋል፡፡ ዓብይ ከሚወቀሱባቸው ችግሮች ውስጥ አንዳንዶቹ ከእሳቸውም በፊት የነበሩና ሲንከባለሉ የመጡ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ ለምሳሌ የመፈናቀልን ጉዳይ ያነሳን እንደሆነ ምናልባት የአንዳንዶቻችን ዓይን የበራው ገና አሁን ካልሆነ በቀር ኢሕአዴግ ከመጣ ጀምሮ መፈናቀል ያልነበረበት ዓመት የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ይህን የደረሰበት ያውቀዋል፡፡ አሁን ከተፈናቀሉት ውስጥ አንዳንዶቹ “ከክልሌ ውጣልኝ” በሚል ሌሎችን ሲያፈናቅሉና ሲገድሉ የነበሩ ናቸው፡፡ እጁ ንጹህ የሆነ የለም ለማለት ነው፡፡ ለዚህም ዋና ተጠያቂው ሕዝቡ ሳይሆን የኢሕአዴግ የብሔር ፖለቲካ ነው፡፡ ሕዝቡማ ለዘመናት በፍቅር አብሮ ሲኖር የነበረ ነው፡፡ ብዙዎች እንደሚስማሙበት ለዚህ ችግር ዘላቂ እልባት የሚያመጣው በጎሳ ላይ የተመሰረተውን አከላለል ማሻሻል ነው፡፡ ይህንንም የሚያጠናና መፍትሄ የሚያመላክት ኮሚሽን ዓብይ አቋቁመዋል፡፡ መልካም ጅምር ነው፡፡ ውጤቱን በትዕግሥት መጠበቅ ነው፡፡ የክልልነት ጥያቄም ድሮም የነበረ ነው፡፡ ዘረኝነትም ቢሆን ዓብይ የፈጠሩት አዲስ ችግር እንዳልሆነ ማንም የሚያውቀው ነው፡፡ በፕሮቲስታንት ተከበዋል ስለሚባለው ጉዳይም ምናልባት ነገሩ እውነት ከሆነም ሰው መመዘን ያለበት በሚሰራው ሥራ እንጅ በእምነቱ መሆን ያለበት አይመስለኝም፡፡ ትችቱ አንዳንድ እምነቶችን አገር በቀል ሌሎችን ደግሞ መጤ አደርጎ ከማሰብ የመነጭ ከሆነም እንዲህ ዓይነቱ ኋላቀር አስተሳሰብ አሁን ባለንበት ክፍለ ዘመን ተቀባይነት የለውም፡፡

 

ሌላው ልንዘነጋው የማይገባን ዓብይ ለያዙት ከባድ ኃላፊነት አዲስ መሆናቸውንና ወጣትነታቸውን ነው፡፡ ወደፊት ልምድ እያካበቱና ዕድሜአቸውም እየበሰለ ሲሄድ የተሻሉ ድሎች እንደሚያስመዘግቡ አይጠረጠርም፡፡

 

ተጠያቂው ዓብይ ብቻ ናቸውን?

አገራችን አሁን ለገጠሟት ችግሮች ሁሉ ዓብይን ብቻ ተጠያቂ ለማድረግ መሞከር ፍርደ ገምድልነት መስሎ ይታየኛል፡፡ እያንዳንዱ ዜጋ በኃላፊነት ስሜት የድርሻውን ካልተወጣ በቀር ዓብይ ብቻቸውን አገር ሊገነቡ አይችሉም፡፡ በጠመንጃ ዘላቂ ድል እንደማይገኝም የቅርብ ታሪካችን ምስክር ነው፡፡ እሳቸው ወደፊት ሲስቡ ሌላው ወደኋላ የሚጎትት ከሆነ፣ እሳቸው ሲገነቡ ሌላው የሚንድ ከሆነ የታሰበው ውጤት እንደ ሰማይ እየራቀ ይሄዳል፡፡ ክፉኛ እየተፈታተናቸው ያለው ችግርም ይኼ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ሰሚ ያገኙ አይመስሉም እንጅ ሕዝቡ ከጎናቸው እንዲቆምና አርቆ እንዲያስብ ከመምከርና ከመለመን ተቆጥበው አያውቁም፡፡ የታያቸውን የሚያይላቸው መገኘቱ ያጠራጥራል፡፡ አዲስ ወይን ጠጅን በአሮጌ አቁማዳ ውስጥ ማስቀመጥ እንደሚከብድ የተገለጠላቸውን ነገር በሕዝቡ ውስጥ ማስረጽ የተሳናቸው ይመስላል፡፡ ከሁለት ወራት በፊት አንድ ሕዝባዊ ስብሰባ ላይ “ይኸው አሥር ወር ሙሉ አንድ ቀን ረፍት የለኝም፣ እያመመኝ ሕክምና መሄድ አልቻልኩም፣ … ኢትዮጵያን ማልማት እፈልጋለሁ ግን እናንተ ግብር አትከፍሉም፣ ሥራዬን እንዳልሠራ በየቦታው ክላሽ እየተኮሳችሁ ሰው እየገደላችሁ ትበጠብጣላችሁ፣ እናንተን እያረጋጋሁ ሥራ ልሠራ አልቻልኩም፡፡” ሲሉ የተናገሩትን ልብ ይሏል፡፡

 

የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል ከዶ/ር ዓብይና ከመንግሥታቸው ምን ይጠበቃል?

  • ዓብይ ሥልጣን መልቀቅ የለባቸውም

ዓብይ አልፎ አልፎ ከሥልጣን መውረድ ናፈቀኝ ወይም ፖለቲካንና ኮረንቲን በሩቁ ነው ዓይነት የተስፋ መቁረጥ ንግግሮችን ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡ መጀመሪያ ስሰማቸው ቀልዳቸውን ይመስለኝ ነበር፡፡ ሲደጋግሙት ግን “ድንገት በቃኝ ሊሉ ነው እንዴ?” እላለሁ፡፡ ለመሆኑ ይህ “የስንፍና” ንግግራቸው የደጋፊዎቻቸውን ስነ ልቡና እንደሚጎዳ ለጠላቶቻቸው ደግሞ የልብ ልብ እንደሚሰጣቸው አስተውለውት ይሆን? እንደ እሳቸው ካለ ከፍተኛ የሕዝብ ድጋፍ ካለው መሪ የሚጠበቅ አይመስለኝም፡፡ መቼም የተረከቡት ኃላፊነት ከባድ መሆኑን ሳይረዱት ወደ ሥልጣን የመጡ አይመስለኝም፡፡ ሁሉ ነገር አልጋ ባልጋ ይሆናል ብለው እንደማይጠብቁ እገምታለሁ፡፡ ደግሞስ ለዚህ ሥልጣን ዕድሜ ልካቸውን ሲዘጋጁ መኖራቸውን በአደባባይ ነግረውናል አይደል! የተናገሩትን በተግባር ማሳየት አለባቸው፡፡ ታሪክ የሚሰራው እኮ በእንዲህ ዓይነት የጭንቅ ወቅት ነው፡፡ አይበለውና ድንገት ሆድ ብሷቸው ሥልጣን ቢለቁ ማነው የሚተካቸው? እጅግ አሳሳቢና ከባድ ነገር ነው፡፡ እናም በሕዝብ ለተመረጠ መንግሥት ሳያስረክቡ በምንም መንገድ ሥልጣን መልቀቅ የለባቸውም፡፡ ቢያደርጉት ግን በተፋፋመ ጦርነት ውስጥ ያሉትን ወታደሮቹን እንደ ከዳ ጀኔራል ይቆጠራሉ፡፡

 

  • የሕዝቡን ንቃተ ኅሊና ደረጃ ግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል

አንዳንድ ጊዜ የኅብረተሰባችንን ንቃተ ኅሊና ዝቅተኛነት ስንመለከት ዲሞክራሲ ለአገራችን ቅንጦት የሚመስልበት ሁኔታ አለ፡፡ ከጠቅላላው ሕዝብ ውስጥ በግምት ከ80% በላይ የሚሆነውን የገጠር ነዋሪ እንተወውና ፖለቲካውን የሚዘውረው ጥቂቱ ከተሜ እንኳ ከዘመኑ ሥልጣኔ ጋር ለመራመድ ብዙ ይቀረዋል፡፡ ባሎች ሚስቶቻቸውን ካልደበደቧቸው አይወዷቸውም ብለው የሚያምኑ ብዙ ናቸው፡፡ ጠንክሮ በመሥራት ፋንታ የሌላው ሰው ሀብትና ዕድል ወደ ራሱ እንዲገለበጥለት ጨለማን ተገን በማድረግ ጎረቤቱ በር ላይ ሟርት ሲቀብር  የሚያድረው ዜጋ ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ ስለሆነም የፖለቲካ ባህላችን ደካማ ቢሆንና መጠላለፉ ቢበዛ የሚገርም አይደለም፡፡ መፍትሄውን ሚሼል ኦባማ በአንድ ወቅት ተናግራዋለች – “እነሱ ሲወርዱ እኛ ከፍ እንላለን” (When they go low, we go high)፡፡ መቻልና ንቆ መተው ነው፡፡

 

  • በሚያደርጉት ነገር ሁሉንም ሰው ማስደሰት እንደማይችሉ ማወቅ አለባቸው

በምንሠራቸው ሥራዎች ሁሉንም ሰው ማስደሰት ቢቻል ጥሩ ነበር፡፡ ግን አይቻልም፡፡ ሰዎች የሚሉትን ሁሉ ለማድረግ የምንሞክር ከሆነ ገደል ልንገባ እንችላለን፡፡ ከሰዎች አስተያየትና ምክር መቀበል መልካም ቢሆንም የራሳችን አቋም ደግሞ አስፈላጊ ነው፡፡ አንድ የኤዞፕን ተረት እዚህ ላይ ማንሳቱ ጠቃሚ ነው፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን አባትና ልጅ አህያቸውን እየነዱ ወደ ገበያ ለመሄድ ጉዞ ይጀምራሉ፡፡ ጥቂት እንደተጓዙ ሌሎች መንገደኞችን ያገኛሉ፡፡ መንገደኞቹም አባትና ልጅን በመገረም እየተመለከቱ “ባዶ አህያ እየነዱ የሚሄዱት ምን ዓይነት ጅሎች ቢሆኑ ነው? አንዳቸው እንኳ ለምን አይቀመጡበትም?” ይላሉ፡፡ ይህን የሰሙ አባትና ልጅ ተመካከሩና አባት አህያው ላይ ተቀመጠበትና መጓዝ ጀመሩ፡፡ ጥቂት እልፍ እንዳሉ ሌሎች መንገደኞችን ደግሞ አገኙ፡፡ ሰዎቹም አባትየውን በአግራሞት ተመለከቱና “ምን ዓይነት ጨካኝ አባት ቢሆን ነው ልጁ በእግሩ እየሄደ እሱ አህያው ላይ የተቀመጠው?” እያሉ ሲያወሩ ያዳምጣሉ፡፡ ወዲያው አባት ወረደና ልጁ በተራው አህያው ላይ ተቀምጦ ጉዞ ቀጠሉ፡፡ አሁንም ሌሎች መንገደኞችን ያገኛሉ፡፡ “ምን ዓይነት ባለጌ ልጅ ቢሆን ነው አባቱ በእግር እየሄደ እሱ አህያው ላይ የተቀመጠው?” እያሉ ሲነጋገሩ ይሰማሉ፡፡ አባትና ልጅ ጥቂት ከአሰቡ በኋላ ሁለቱም አህያው ላይ ይቀመጡና ጉዞ ይጀምራሉ፡፡ የተወሰነ ርቀት ከሄዱ በኋላ ሌሎች መንገደኞች ደግሞ ተገናኟቸው፡፡ “ምን ዓይነት ጨካኝ ሰዎች ቢሆኑ ነው ሁለቱም የተቀመጡበት? ይህን አህያ ገደሉት እኮ! ቢያንስ አንዳቸው እንኳ በእግራቸው ቢሄዱ ምን አለበት” እያሉ ሲነጋገሩ ያዳምጣሉ፡፡ ሁለቱም ከአህያው ወረዱና አጠገባቸው ከሚገኝ ጫካ እንጨት ቆረጡ፡፡ የአህያውን እግሮች በገመድ ጠፍረው አሰሩ፡፡ አህያውን በቆረጡት እንጨት ላይ አንጠለጠሉና በትክሻቸው ተሸክመው ገበያው ቦታ ደረሱ፡፡ ገበያተኛው በሙሉ ጉድ አለ፡፡ መሳቂያ መሳለቂያ ሆኑ፡፡ አህያውም ብዙ እንግልት ስለደረሰበት ሞቶ ተገኘ፡፡

 

  • የሕግ የበላይነት ሊከበር ይገባል

በዓለም ላይ ካሉ ፍጥረቶች ሁሉ ያለሕግና ቁጥጥር መኖር የማይችል የሰው ልጅ ብቻ ነው፡፡ አስቸጋሪ ፍጥረት ስለሆነ ነው፡፡ ፈጣሪስ ሰውን በመፍጠሩ የተጸጸተው የሰውን የልብ ክፋት ስላዬ አይደል (ዘፍጥ. 6፡6)! አቤት ሰውን ለመቆጣጠር ያለው የሕግ ብዛት! የፈጣሪ ሕግ፣ የዕድር ሕግ፣ የትራፊክ ሕግ፣ የሆቴል ሕግ፣ የስፖርታዊ ጨዋታ ሕግ፣ የሆስፒታል ሕግ፣ የመሥሪያ ቤት ሕግ፣ የት/ቤት ሕግ፣ የቤተ ክርስቲያን ሕግ፣ የመስጅድ ሕግ፣ የጋብቻ ሕግ፣ የቤተሰብ ሕግ፣ የሠፈር ሕግ፣ የቀበሌ ሕግ፣ የወረዳ ሕግ፣ የዞን ሕግ፣ የክልል ሕግ፣ የፌዴራል ሕግ፣ የአሕጉር ሕግ፣ ዓለም አቀፍ ሕግ፡፡ እነዚህ ሁሉ ሕጎች እያሉ ግን የሰው ልጅ አልተቻለም፡፡ የሰውን ተፈጥሮ መቀየር ስለማይቻል ያለው ተመራጭ ዘዴ ሕግን ማጥበቅ ነው፡፡ የሰው ልጅ ቅጣትን እንደሚፈራ ደግሞ የታወቀ ነው፡፡ በአደጉት አገሮች ሰው አደብ ገዝቶ እንዲኖር ከሚያደርጉ ቁልፍ ምክንያቶች አንዱ ሕጋቸው ጥብቅ ስለሆነ ነው እንጅ ዲሞክራሲያቸው እንከን የለሽ ስለሆነ አይደለም፡፡ ሕግን ለጣሰ የሚሰጡት ቅጣት አይጣል ነው፡፡ “እኔን ያየህ ተቀጣ” ነው የሚያሰኙት፡፡ አቤት ፖሊስ ሲፈራ! አቤት ሕግ ሲፈራ! በእኛ አገር 3 ወራትና 6 ወራት እስራት የሚያስቀጣ ወንጀል እነሱ ጋ 20 እና 30 ዓመታት ሊያሳስር ይችላል፡፡ በአጠቃላይ ከሕጋቸው ጋር መጋጨት “ነብር አየኝ በል” ነው፡፡

 

በዲሞክራሲ ስም ማንም እንዳሻው እንዲፋንን በር መክፈት አደገኛ ነገር ነው፡፡ ከአገር የሚበልጥ የለምና እሹሩሩው ገደብ ሊበጅለት ይገባል፡፡ በፍቅር ብቻ አገርን እናስተዳድራለን የሚባለው ነገር በገሐዱ ዓለም የሌለ ነገር ነው፡፡ ፈጣሪም ቢሆን ፍቅር ብቻ ሳይሆን የሚባላ እሳትም ነው፡፡ የእሱ ቅጣትማ ምኑ ይነገራል! አይድረስ ማለት ነው የሚሻለው፡፡ እንደዚያማ ባይሆን ሰውን ይችለው ነበር? በፍጹም፡፡

 

  • ልጽነትን (transparency) ማስፈን ያስፈልጋል

በየጊዜው ለሚሰነዘሩ ትችቶች ሁሉ አጸፋዊ መልስ መስጠት አስቸጋሪ ቢሆንም በተለይ በሕዝቡ ዘንድ ጉልህ የሆኑ ብዥታዎች ሲፈጠሩ መንግሥት አፋጣኝ ማብራሪያ ቢሰጥ ብዙ ችግሮችን ይቀርፋል፡፡ አሉቧልታዎችን በአጭሩ ከመቅጨትም አልፎ ለለውጡ ደጋፊዎች ብርታት ይሰጣል፡፡ ለምሳሌ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ላይ ስለተነሳው የባለቤትነት ውዝግብ ዶ/ር ዓብይና አቶ ለማ መገርሳ የሰጧቸው መሳጭ ማብራሪያዎች ብዙዎችን አረጋግቷል፡፡ መንግሥት የተቸገረበት ነገር ሲኖርም ለሕዝቡ ግልጽ የማድረግ ባህል ቢለመድ የተጀመረውን ዲሞክራሲ የበለጠ ያጎለብተዋል፡፡ በአጭሩ ከሕዝቡ የሚደበቅ ነገር መኖር የለበትም፡፡

 

  • ትግራይ ቸል መባል የለባትም

በኢትዮጵያዊነቱ ኩሩ የሆነው የትግራይ ሕዝብ ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር ከተኮራረፈ ይኼው አንድ ዓመት ደፈነ፡፡ ለቤተሰብ በጣም ረጅም ጊዜ ነው፡፡ ሆዳም እንዳልባል እንጅ በተለይ እንደ እኔ ከደጉ የትግራይ ገበሬ እጅ ነጭ ማር ልሶና ከጓሮው እሸት በልቶ ለሚያውቅ ሰው የሺህ ዓመት ያህል ይረዝማል፡፡ ትግራይን በጭፍን የሚጠሉ አንዳንድ ሰዎችን ስመለከት አይ ሕዝቡን ቀርባችሁ አለማወቃችሁ? እላለሁ፡፡ የኩርፊያው ምክንያት ምንም ይሁን ምን ቀዳዳን ከተቻለ ሙሉ በሙሉ መድፈን ካልሆነም ማጥበብ እንጅ እያሰፉ መሄድ ደግ አይደለም፡፡ በጣልያን ወረራ ወቅት ባንዳ እየሆኑ አገር ሲያደሙ ከነበሩት ሰዎች ውስጥ ብዙዎቹ በመንግሥት ላይ አኩርፈው የነበሩ ናቸው፡፡ ችግሩ በሽምግልናም ይሁን በሌላ መንገድ መፈታት ይኖርበታል እንጅ ትግራይ “ምን ታመጣለች?” በሚል በቸልታ ሊታለፍ አይገባውም፡፡ ጉዳዩ እልባት ቢያገኝ የተጀመረውን ለውጥ ወደፊት ለመግፋት ብዙ አወንታዊ ጎኖች ይኖሩታል፡፡ በሌላ በኩል “ሜዳ ሲቃጠል ተራራ ይስቃል” እንደሚባለው ምናልባት የትግራይ መሪዎች በሌላው የአገሪቱ ክፍል ያለው “እሳት” እኛን አይመለከተንም ብለው ተኩራርተው ከሆነ ተሳስተዋል፡፡ ሜዳ ላይ የተነሳ እሳት ቀስ በቀስ ተራራውንም ማጋየቱ እንደማይቀር ምርምር አያስፈልግም፡፡ ዳር ቆሞ ከማየት ይልቅ በአርቆ አሳቢነት የሁላችንም እናት የሆነችውን መተኪያ የሌላት አገር ከጥፋት መታደግና ልማቷን ማፋጠን ነው የሚያዋጣው፡፡

 

  • መሪዎቻችን ጽኑና እልኸኛ ሊሆኑ ይገባል

የምዕራባውያን አገሮች ፖለቲከኞች በጣም ያስቀኑኛል፡፡ ጽኑዎች ወይም እልኸኞች (determined) ናቸው፡፡ ድል በትግል እንጅ በአስማትና በዕድል እንደማይገኝ ያውቃሉ፡፡ ለጠላቶቻቸው በቀላሉ እጃቸውን አይሰጡም፡፡ ከይቻላል ውጭ የሽንፈት ቃል ከአፋቸው አይወጣም፡፡ ተሰደብን ብለው ማለቃቀስ የሚባል ነገር እነሱ ጋ አይሰራም፡፡ ላመኑበት ነገር ሽንጣቸውን ገትረው እስከመጨረሻው ይፋለማሉ፡፡ ተቀናቃኞቻቸው የጓዳ ገበናቸውን ሳይቀር አደባባይ እያወጡ ሲዘከዝኩባቸውና ሲያዋርዷቸው ከመንገዳቸው ፍንክች አይሉም፡፡ በመጨረሻ የሚዳኛቸው ሕዝቡ ነው፡፡ ግራና ቀኙን አመዛዝኖ ላመነበት ድምጹን ይሰጣል፡፡ በቃ፡፡ ከፖለቲካው ውጭም ቢሆን ዓለምን የለወጡ እልኸኛ ሰዎች ናቸው፡፡ ዓብይም ሆኑ ሌሎች ፖለቲከኞቻችን እንዲህ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ለሕዝብ መብት እንታገላለን ብለው እስከተነሱ ድረስ ተዋጊዎች መሆን አለባቸው፡፡ ለምን ተነካሁ ብሎ ነገር አይሰራም፡፡ የጀመሩትን ጉዞ መቀጠል እንጅ ውሾች ለምን ይጮሃሉ በማለት ጊዜ ማጥፋት አያስፈልግም፡፡

 

በእኔ እምነት አገራችን አሁን የገጠሟት ችግሮች በፋሽሽት ጣሊያን ወረራ ወቅት ገጥመዋት ከነበሩት አይበልጡም፡፡ አጠገቡም አይደርሱም፡፡ በዚያ የጨለማና የስቃይ ዘመን ኢትዮጵያ አልቆላት ነበር፡፡ ለአምስት ዓመታት መንግሥት አልባ ነበረች፡፡ ሽፍታና ሥርዓት አልበኝነት ሕዝቡን ቁም ስቅሉን አሳይቶት ነበር፡፡ ሁሉ በውጊያ ላይ ተጠምዶ ስለነበር የአገሪቱ ኢኮኖሚ መቀመቅ ወርዶ ነበር፡፡ በርካቶች ተጨፍጭፈዋል፡፡ በየቦታው የሚሰማው ዋይታ ብቻ ነበር፡፡ ጠላት ሕዝቡን በዘርና በቋንቋ ለመከፋፈል ሞክሮ ነበር፡፡ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ እንደ አሸን ፈልተው የነበሩት ባንዳዎች ከጠላት ጋር ወግነው እናት አገራቸውን ይወጉ ነበር፡፡ ሆኖም በጃንሆይ ጽናትና በአርበኞች ብርታት ኢትዮጵያ እንደገና በእግሯ ለመቆምና እንደ አገር ለመቀጠል በቃች፡፡ ያንን ድል ለመድገም ዛሬም አልረፈደም፡፡ ይቻላል የሚልና ሕዝቡን ከዳር እስከ ዳር የሚያንቀሳቅስ መሪ ግን ወሳኝ ነው፡፡

 

ለውጡን ለማስቀጠል ከደጋፊዎች ወይም ከሕዝቡ ምን ይጠበቃል?

  • ብይን ልናምናቸው ያስፈልጋል

ዶ/ር ዓብይ የሚወዷት ኢትዮጵያን ለመለወጥ እስከ ሕይዎት መስዋዕትነት ለመክፈል መዘጋጀታቸውን በተደጋጋሚ ቃል ሲገቡ ሰምተናል፡፡ እየወሰዷቸው ያሉት እርምጃዎችም ይህን የሚመሰክሩ ናቸው፡፡ ስለዚህ ልናምናቸው ይገባል፡፡ በሆነ ባልሆነው በተጠራጠርናቸው ቁጥር ቅንነታቸውን እያጠፋነው ልንሄድ እንችላን፡፡ “ሰውን ክፉ የሚያደርገው ሰው ነው” ይበላል አይደል? የአገሪቱን ቁልፍ ሚስጥሮች ሳይቀር በእጃቸው የያዙትን ሰው ዝቅ አድርጎ መገመት ተገቢ አይመስለኝም፡፡ ሌላው ቢቀር እሳቸውም እኮ የሚወዷቸው ልጆች፣ ሚስት፣ ዘመድ አላቸው፡፡ የራሳቸውን ቤተሰቦች የሚጎዳ ነገር ያደርጋሉ ብሎ ለማመን ይከብዳል፡፡ አንዳንዴ በእሳቸው ጫማ ውስጥ ሆነን ነገሮችን ማመዛዘን ያስፈልጋል፡፡ ጠቅላይ ሚንስትር ስለሆኑ ሁሉን ነገር ብቻቸውን ይወስናሉ ብዬ አላስብም፡፡ በኢሕአዴግ አሠራር ዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት የሚባል ነገር አለ፡፡ ለአብላጫ ድምጽ ተገዥ መሆን ማለት ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ መንግሥት አንዳንዴ ተገቢ የማይመስሉ ነገሮችን ሲያደርግ ብንመለከት እንኳን ለመሳደብ ከመጣደፍ ይልቅ ቅሬታችንን በተገቢው መንገድ ማቅረብ ብንችል የተሻለ ውጤት ሊያመጣ ይችላል፡፡

 

  • የዓብይ ጉልበታቸው ደጋፊዎቻቸው መሆናቸውን አንዘንጋ

ፖለቲከኛ ያለደጋፊ ዋጋ የለውም፡፡ ዜሮ ነው፡፡ የደጋፊ ጉዳይ ሲነሳ ትዝ የሚለኝ ዶናልድ ትራምፕ ነው፡፡ ገና ለምርጫ እወዳደራለሁ ካለበት ጊዜ ጀምሮ ከተቀናቃኞቹ የሚደርስበት ፈተና ለጉድ ነው፡፡ እሱን ለማዋረድና ለመጣል የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡ ምን አለ አርፎ ንግዱን ቢነግድ ኖሮ ያሰኛል፡፡ ሆኖም ሁሉንም ድል ነስቶ 45ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ለመሆን በቃ፡፡ ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? የራሱ ጽናት እንደተጠበቀ ሆኖ አይዞህ የሚሉትና የማይነጥፍ ድጋፍ የሚሰጡት እሳት የላሱ ደጋፊዎች ስላሉት ነው፡፡ ትራምፕ አንዳንዴ የዋሽንግተን ዲሲ ፖለቲካ ሲታክተው ጓዙን ጠቅልሎ ወደ ደጋፊዎቹ ይሄዳል፡፡ እሳት ለብሶ እሳት ጎርሶ፣ ኃይልን ተቀብሎ ይመለሳል፡፡ መሪዎቻችን ሰው ናቸውና “በርቱ፣ ከጎናችሁ ነን” ልንላቸው ያስፈልጋል፡፡

 

  • የተፈጠሩትን መልካም ዕድሎች እንጠቀምባቸው

“በእጅ የያዙት ወርቅ ከመዳብ ይቆጠራል” እንዳይሆንብን እንጅ ለውጡን ተከትሎ የተገኙ በርካታ መልካም ዕድሎች አሉ፡፡ የመሪዎቻችን ቅንነት፣ አገር ወዳድነታቸው፣ ለለውጥ ያላቸው ቁርጠኝነት፣ በመካከላቸው ያለው መግባባት፣ ሌብነትን የሚጸየፉ መሆናቸውና ከሕዝቡ ጋር እየፈጠሩት ያለው ቅርርቦሽ የሚደነቅ ነው (በትግራይ ያለው ችግር እንዳለ ሆኖ)፡፡ ኢትዮጵያዊነት ዳግም እያንሰራራ መሆኑ ተስፋ ሰጭ ነው፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ ከመቼውም ጊዜ በላይ ከሌሎች ወገኖቹ ጋር በመሆን ሁሉም ዜጋ የሚኮራባት ኢትዮጵያን ለመፍጠርና እሴቶቿ እንዲጎለብቱ ለማድረግ እያደረገ ያለው ጥረትም ሊበረታታ የሚገባው ነው፡፡ እኔ ከተወለድሁ ጀምሮ እንደ አሁኑ ኦሮሞ በአደባባይ አፉን ሞልቶ “ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው” ሲል አልሰማሁም፡፡ “ስንኖር ኢትዮጵያዊ፣ ስንሞት ኢትዮጵያዊ” ሲል አዳምጨ አላውቅም፡፡ ኦሮሞ ለአገራዊ አንድነት ልቡን ሙሉ በሙሉ የከፈተበት ጊዜ ቢኖር አሁን ነው ቢባል ሐሰት አይደለም (የጥቂቶች አፍራሽ ተግባር ሳይዘነጋ)፡፡ ትንሽ ከርዕሱ ወጣ ቢልም ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን በተመለከተ ከማንም በላይ የተፈጸመባቸውን አሳፋሪ ግድያ በአደባባይ የኮነኑትና ላበረከቱት አስተዋጽኦ ዕውቅና የሰጡት የኦሮሞ ልጆች ሟቹ ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ፣ ቄስ ዶ/ር ቶሎሳ ጉዲና እና አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ናቸው፡፡ እነዚህን መልካም የታሪክ አጋጣሚዎች በመጠቀም አገራችንን ወደ ላቀ ደረጃ ማድረስ አለብን፡፡

 

  • የመረጃ ምንጮቻችንን እንፈትሽ

በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚለቀቀው የሐሰት ወሬ (fake news) ዓለምን እየበጠበጠ ባለበት በዚህ አስቸጋሪ ዘመን የመረጃ ምንጮቻችንን ቆም ብሎ መፈተሽ ቸል ሊባል የማይገባው ተግባር ነው፡፡ እንዲሁም ባገኙት ክፍተት ሁሉ የዓዞ እንባ እያነቡና የሕዝብን ጆሮ የሚኮረኩሩ ነገሮችን በመናገር ተቀባይነት ለማግኘት የሚሯሯጡትን ፖለቲከኞች (opportunist politicians) ልንነቃባቸው ይገባል፡፡ ስህተት ካላገኙ ተደማጭነት የሚያገኙ ከማይመስላቸው በተግባር ግን በእሳት ላይ ቤንዚን ከሚያርከፈክፉ አንዳንድ የመገናኛ ብዙኃንም መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡

 

  • “ይዋጣልን” ለማንም አይጠቅምም

“ይዋጣልን” በሚል የጦርነት ነጋሪት መጎሰም ለማንም አይጠቅምም፡፡ በተለይ ባላቸው ከፍተኛ የሕዝብ ብዛት በመመካት ሌሎችን የሚንቁና የሚያስፈራሩ ብሔረሰቦችና ጎሳዎች ሊገነዘቡት የሚገባቸው ነገር ቢኖር የሕዝብ ብዛት በዲሞክራሲያዊ ምርጫ ለማሸነፍ እንጅ በጦርነት ለማሸነፍ ዋስትና አለመሆኑን ነው፡፡ ይህ ታሪክ የሚመሰክረው እውነት ነው፡፡ ዮዲት ጉዲት በዓለም ገናና የነበረውን የአክሱም መንግሥት ከሥሩ መንግላ የጣለችው ከጎኗ ያሰለፈቻቸው ፈላሻዎች ከሌላው ሕዝብ በቁጥር ስለሚበዙ አልነበረም፡፡ ዘመኑ ያለፈበትን ከንቱ ፉከራ አሽቀንጥረን በመጣል በወንድማማችነት ስሜት አገራችንን ለመገንባት በሚደረገው ርብርብ ውስጥ የድርሻችንን ልንወጣ ይገባል፡፡

 

  • እርስ በእርሳችን ስንባላ አገራችንን ለጠላት አሳልፈን እንዳንሰጥ እንጠንቀቅ

ሕዝባዊ አመጾች ለጥሩ ውጤት የሚያበቁበት ሁኔታ እንዳለ ሁሉ በጥንቃቄ ካልተያዙ ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ ሊያመሩና አገርን ሊያዳክሙ ብሎም ሊያፈራርሱ ይችላሉ፡፡ ከዛሬ አምስት ዓመታት በፊት ምሥራቅ አውሮፓዊቷ አገር ዩክሬን ክራይሚያ (Crimea) የሚባለውን እጅግ ጠቃሚ ግዛቷን ድንገት በሩሲያ የተነጠቀችው ለረጅም ጊዜ በዘለቀ ሕዝባዊ አመጽ ስለተዳከመችና በሕዝቡ መካከልም ከፍተኛ መከፋፈል ስለነበር ነው፡፡ በ1969 ዓ. ም. ጎረቤታችን ሱማሌያ ለሁለተኛ ጊዜ ድንገት የወረረችን በአብዮቱ ምክንያት መዳከማችንን ስለተረዳች ነበር፡፡ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም እነ ኩባን፣ ሶቭየት ኅብረትንና (ሩሲያ) ሌሎች ሶሻሊስት አገሮችን ከጎናቸው አሰልፈው በጽናት ባይዋጉ ኖሮ ከአዋሽ መለስ ያለው የአገራችን ክፍል ታሪክ ሆኖ ይቀር ነበር፡፡ ይህም በግምት ሶማሌ ክልል፣ ሐረርጌ፣ ባሌ፣ አርሲ፣ ከሸዋና ከአፋር ከፊሉ እንደማለት ነው፡፡ የሱማሌያ ምኞት ለጊዜው ተዳፈነ እንጅ እንዳልጠፋ አያጠያይቅም፡፡ ለፖለቲካ ፍጆታ (political correctness) ሲባል ተሸፋፍኖ ታለፈ እንጅ ከአንድ ዓመት በፊት በኦሮሚያና በሱማሌ ክልል ዜጎቻችን መካከል የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ ጎረቤታችን ሱማሌላንድ ከ3000 በላይ ኦሮሞዎችን ከሌሎች በመነጠል ከግዛቷ ማባረሯ ብዙ የሚያስተላልፈው መልዕክት አለው፡፡ “የምጣዱ እያለ የዕንቅቡ ተንጣጣ” እንደተባለው ማለት ነው፡፡ ጠላቶቻችን ለሌላው የአገራችን ክፍልም በስውር ምን እየደገሱልን እንዳሉ አይታወቅም፡፡ ስለዚህ “የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን ጣለች” እንዳይሆን በስሜት ከመነዳትና ከሚነፍሱ ሁሉ ጋር ከመንፈስ መታቀብ ብልህነት ነው፡፡

 

ቸር ያሰማን!

[email protected]

Latest from Blog

ከነፃነት ዘገዬ የአራት ኪሎው ኦነግ ሸኔ ከቁጥር ጋር እንደተጣላ ዕድሜውን አገባደደ፡፡ ኦነግ/ኦህዲድ ዛሬም ሆነ ዱሮ፣ በቤተ መንግሥትም ይሁን በጫካ ቁጥር ላይ ያለው አቋም ምን ጊዜም ያስደንቀኛል፡፡ ደግሞም እየባሰባቸው እንጂ ሲቀንሱ አይታዩም፡፡ ጥቂት

80 ቢሊዮን ብር ስንት ብር ነው?

በላይነህ አባተ ([email protected]) መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና

ሰው ሆይ!

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

Go toTop