ሕዝባዊ ንቅናቄው መቀጠል አለበት – አንዱዓለም ተፈራ

ለውጥ ስለተመኘነው ብቻ ዱብ የሚል ክስተት አይደለም። ለረጅም ጊዜ የሕዝብን ልብ ሲያቆስል የኖረ መንግሥት፤ በሕዝቡ ላይ የሚደርሰው የበደል ክምችት ከቋቱ ሞልቶ ሲፈስ፤ ሕዝቡ ሆ! ብሎ ይነሳል። ያን ማዕበል የሚያግደው ወታደራዊ ኃይል የለም። በርግጥ በሞት ቋፍ ላይ ያለ ባለሥልጣን፤ ሥልጣኑን ላለመልቀቅ፤ ብዙ ይገድላል፣ ብዙ ያስራል፣ ብዙ ያሰድዳል። የብዙ ሰዎችን ንብረት ያጠፋል። የሀገርን ሀብት ያጋፍፍና ወደ ራሱ ጓዳ ያዛውራል። አይቀሬው ሲመጣና ሕዝቡ በቃኝ ብሎ ሲነሳ ደግሞ፤ አሳሪው ባስፋፋው እስርቤት፤ ራሱ ይታጎራል። ይህ ነው የለውጥ ሂደት። አዎ! በዚህ ሂደት የሚገኘው የኅብረተሰብ ለውጥ፤ በአንድ ቀን ሀገር አያለብስም። ሟች አልሞትም፣ የነበረ ሥርዓት በቀላሉ አልፈርስም፣ ሌባ የሠረቀውን ንብረት አልመልስም፣ ሌላም . . . ሌላም . . . ሁሉ የትንቅንቅ ትግል አለበት። ይህ በየትም ቦታ የታዬና የተተረከ የኅብረተሰብ ሀቅ ነው። የኛዎቹም ገዥዎች ከዚህ የተለዩ አይደሉም፤ ሊሆኑም አይችሉም። ይሄን ሁሉ አልፎ የዘለቄታ መፍትሔ የሚገኘው፤ ሕዝባዊ ንቅናቄው ትክክለኛ ግቡን እስኪመታ ድረስ፤ በተወሰኑ ለውጥ አምጭዎች ለውጡ እየተመራ ሳይሆን፤ በትክክል በሕዝቡ እየተመራ የቀጠለ እንደሆነ ብቻ ነው። ይህ ማለት፤ ትክክለኛ መፍትሔው ከሕዝቡ ጋር ነው ማለት ነው።

አሁን በርግጥ ሞገደኛው የትግራይ ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ቦታውን አጥቷል። ለውጡ የመጣው በገዥው የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ላይ ነው። ስለ መፍትሔ በምንነጋገርበት ወቅት፤ ድብቅ የሆነ ጉዳይ አይኖርም። ቅልን ቅል፤ ዱባን ዱባ ማለት መቻል አለብን። ያለበለዚያ የእሬያ መታጠብ ይሆንብናል። ታጥቦ ጭቃ! የገዥዎች መቸነፍና ከሥልጣናቸው መራቅ ብቻውን፤ የነበረውን ሥርዓት ማክተም አያረጋግጥም። ለነገሩ አሁንም የትግራይ ነፃ አውጪ ግንባር የገዥው ክፍል አካል ነው። ያን እያደባበስን መሄዳችን የትም አያደርሰንም። የነበረው ሥርዓት ደግሞ፤ በገዥ ግለሰቦቹ ብቻ ሳይሆን፣ በአስቻዮቹ፣ በርዕዩተ ዓለሙና በተከላቸው መርዛማ የአስተዳደር መመሪያዎቹ ጭምር ነው ሕልውናውን ያረጋገጠው። እናም ጊዜያዊ ግለሰቦቹ የለቀቁ ቢመስለንም (አንዘንጋ አልለቀቁም!)፤ ቢለቁም ሥርዓቱን መሰሶ ሆነው ይዘውት ያቆዩት ሌሎቹ አካሎቹ በቦታው እስካሉ ድረስ፤ ሥርዓቱ ይቀጥላል። በሀገራችን እየታየ ያለው ሀቅ ይሄው ነው። ለምን እርስ በርስ ግጭቱ አሁንም ቀጠለ? ለምን ተበዳዮች አሁንም በጩኸት ላይ ናቸው? ለምን ሰላምና ዕድገት መልክ አልያዙም? መልሱ የሥርዓቱ ርዝራዥ ኅብረተሰቡን ፈጥርቆ ይዞ፤ አሁንም እያመረቀዘ ስለሆነ ነው። አሁንም ሀገራችን የምትመራው በትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ግንባር ሕገ-መንግሥት፤ የምትተዳደረው በትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ግንባር መተዳደሪያ ደንብ ነው። አሁንም ራያ፣ ጠለምት፣ ወልቃይት፤ እንደቅኝ ግዛት በትግሬዎቹ ቁጥጥር ሥር ነው ያሉት። አሁንም የትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ግንባር የአዲሱ አስተዳደር አንድ አራተኛ ባለቤት ነው! የተወሰኑ ሰዎችን በተወሰነ ጥፋት ተጠያቂ አድርጎ በቁጥጥር ሥር በማዋል፤ ሥርዓቱ ተወግዷል ማለት፤ ዓይናችሁን ጨፍኑ ላሞኛችሁ ከማለት የተለየ አይደለም። አሁንም በዘር በተከፋፈለ የአስተዳደር ፍልስፍና ሥር እያለን፤ አሁንም ዐማራው ዐማራነቱ ወንጀል ሆኖ፤ እንደ ከብት እየታረደ፤ ለውጡ በትክክል እየተካሄደ ነው! ማለት ትክክል አይደለም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ለመላው የክርስትና ኃይማኖት ተከታይ ኢትዮጵያውያን በሙሉ፥ - ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት

አዎ! በሕዝቡ ከፍተኛ መስዋዕነት መክፈል የተገኘው ለውጥ አሁን ያለንበትን የሽግግር ወቅት አስገኝቶልናል። የሽግግር ወቅት ብዙ የተወሳሰቡ ጉዳዮችን በውስጡ ያቀፈ ቢሆንም፤ መሠረታዊ ማጠንጠኛው፤ የነበረው ሥርዓት ፈርሶ አዲስ ሥርዓት በቦታው መተካቱ ነው። በሀገራችን እየተካሄደ ያለውን ይሄን ለውጥ ሂደት እየመራ ያለው፤ ባሁኑ ሰዓት መንግሥታዊ ሥልጣን የያዘው አካል ነው። በዚህ የሽግግር ሂደት፤ ብዙ ግጭቶች በተለያዩ ቦታዎች ተከስተዋል፤ እየተካሄዱም ነው። በነኚህ ግጭቶች ዕንቁ የሆኑ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። በቦታው በመገኘታቸው ብቻ፤ ያለምንም ምክንያት ሰዎች ተገድለዋል። ለምን? እውነት ሕዝባዊ የሆነ የለውጥ ሂደት፤ የለውጥ ፈላጊ ንፁህ ሰዎችን ሕይወት መጥፋት ግድ ይላል? አለመረጋጋቱስ ለምንድን ነው? ብዙ ጥያቄዎችን ማስቀመጥ ይቻላል።

በመሠረታዊ ዕውነትነቱ፤ ለውጡ መብላት ያለበት፤ ለውጡ የመጣበትን ክፍል ነው። ጉዳቱ እየደረሰ ያለው ግን፤ ለውጡን ክፍተኛ መስዋዕትነት ከፍሎ ባስገኘው ሕዝብ ላይ ነው። ላለንበት ሁኔታ ምክንያት በሆኑት ጉዳዮች፤ አስፈላጊውን ሀገራዊ ውይይት በማካሄድ፤ መፍትሔ ላይ መድረስ ግዴታ ነው። ምኞት ፈረስ ሆኖ የትም አያደርስም። ያለንበት ዘመ፤ እከሌ ደግ ሰው ነውና ጥሎ አይጥለንም የሚባልበት ዘመን አይደለም። ትክክለኛ ዕቅድና አሰራር ያለበት ሂደት ብቻ ነው ወደፊት የሚያስኬደን። ዋና ዋና የሆኑትን የለውጡ ሂደት ጉዳዮችን በመመልከት፤ ሀገራዊ ውይይቱ መፍትሔ ለማግኘት ማትኮር አለበት። እኒህም፤ ለውጡን እየመራ ያለው ክፍል ማነው? ይህ ክፍል ከለውጡ ጋር ምን ዓይነት ግንኙነት አለው? ለውጡ ምን ዓይነት አመራር አለው? ለውጡና ሕዝቡ እንዲደረግለት የሚፈልገው ጉዳይ ተጣጥመዋል ወይ? ለምን በዚህ ምስቅልቅል ሂደት ውስጥ እንዳሽቃለን? ሕዝባዊ ለውጡ የሚፈልገው ዕርምጃ እየተወሰደ ነው ወይ?

ተጨማሪ ያንብቡ:  ኦሪት ዘፍጥረት ኦሮሞ ከውሃ ነው የመጣው! የእርግማን ትውልድ! - ሰርፀ ደስታ

እኒህ ጥያቄዎች ወደፊት የመጡት፤ አሁን ከፊታችን የተደቀነብን ምስቅልቅል የትርምስ ሂደት፤ ከሀገራዊ አመራሩ ጋር በቀጥታ የተያያዙ በመሆናቸው ነው። ለውጡ እየተመራ ያለው እንዴት ነው? ለውጡ፤ ተበዳዩን ክፍል ማዕከል አድርጎ፣ ተጠያቂ ክፍሉን በቁጥጥር ሥር አውሎ፣ ጉዳዩን በመመርመር፤ ወደ ትክክለኛ መፍትሔ መሄድ አለበት። ይህ የለውጥ ሂደቱ ማዕከላዊ መመሪያ ካልሆነ፤ ትክክለኛ ለውጥ እየተካሄደ አይደለም።

አንደኛ ተግባር፤ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው ክፍል፤ የለውጡን ራዕይ በትክክል ቀርጾ ማቅረብ ነው። ይህ ራዕይ፤ የነበርንበትን ፈትሾ፣ ጠያቂና ተጠያቂን ለይቶ፣ ለደረሰው ጥፋት ፍትኅ አቅርቦ፤ ሰላምና መረጋጋትን አስፍኖ፤ ወደፊት የሚወስድ መሆን አለበት።

ሁለተኛው ተግባር፤ ሕዝባዊ የሆኑ ማኅበራትና ያካባቢ ቡድኖች የተዋቀሩበትን ክፍል፤ በየቦታው ማቋቋም ነው። ይህ ሥልጣን ላይ ባለው ክፍል ሳይሆን፤ በራሱ በሕዝቡ መደረግ ያለበት ነው። ሕዝቡ አጥፊዎችን ለይቶ ያውቃል። ሕዝቡ የሚፈልገውን ያውቃል። መንግሥት ለዚህ ሕዝባዊ መዋቅር እውቅና ሠጥቶ፤ ደጋፊ መሆን አለበት።

ሶስተኛ ተግባር፤ በየአካባቢው ለሚነሱ ማናቸውም ጉዳዮች፤ ከመንግሥትና ከሕዝቡ የተውጣጣ ክፍል ነው መፍትሔ ፈላጊና ተግባሪ መሆን ያለበት። አሁን ባለንበት የሽግግር ወቅት፤ መንግሥት ከሕዝቡ ተገንጥሎ አድራጊ ፈጣሪ ከሆነ፤ ተመልሶ እምቦጭ ይሆናል። አንገብጋቢ ለሆኑት፤ የተፈናቀሉትን ወደ ቦታቸው መመለስ፣ የተዘረፉትን ንብረታቸውን ማስመለስ፣ ወደ ውጪ የተበተኑትን ማስባሰብ፣ የሀገሪቱን ንብረት ተቆጣጥሮ ወደቦታው ማስገባት፣ እና ሌሎች ጉዳዮች፤ ሕዝቡ እንዲረዳው በየአካባቢው የሚቋቋሙት ሕዝባዊ ክፍሎች፤ ሕዝቡን እያሰባሰቡ ከሕዝቡ መማርና ሕዝቡን ማስተማር ይችላሉ። የተሻረውን ራዕይና አዲሱን ራዕይ በግልጽ ልዩነታቸውን ለሕዝብ ለማስረዳት፣ ይህ ክፍል ወሳኝ ነው። ሽግግሩም ሆነ ለወደፊቱ የሚሆኑ የኢኮኖሚ፣ የትምህርት፣ የሕክምና፣ የሀገር ሕልውናና የደንበር ጥበቃ፣ የሀገር ውስጥ ደህንነትና ቁጥጥር፣ የሰላምና መረጋጋት ሂደቶች፣ የዴሞክራሲያዊ መብቶችና ግዴታዎች ምንነት፣ ሀገራዊ አንድነት ባለው መልክ መነደፍና ለሕዝብ መቅረብ አለባቸው። ያን ጊዜ ነው፤ በኢትዮጵያዊነት ላይ የተመረኮዘ የሀገር አስተዳደር መገንባት የሚቻለው። ያን ጊዜ ነው በዜግነት ላይ የተመረኮዘ የፖለቲካ ተሳትፎ የሚታነጸው። ከዚያ በፊት የሚደረገው ትርምስምስ፤ ያው ትርምስምስ ነው። ትርምስምስ ደግሞ ለሌባ ብቻ ነው የሚመቸው። የነበርንበትን እና ያለንበትን ሀቅ ሳይረዱ፤ ከመሬት ተነስቶ ሀገራዊ ፓርቲ እና የፖለቲካ ተስትፎ ቢሉ፤ ትርምስምስሩን ከማባባስ ያለፈ ፋይዳ የለውም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ስለ ኮሎኔል ታደሰ ጥቂት ልበል፡ ከፍል1 በይታያል የሩቅሰው

በርግጥ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው ክፍል፤ ተገቢ የሚላቸውን ዕርምጃዎች ሊወስድ እየጣረ ነው። ነገር ግን በምን ላይ ተመርኩዞ ነው? ሕዝቡንስ በምን ደረጃ እያሳተፈ ነው? ደርግ ሕዝቡ አርፎ ይቀመጥ፤ እኔ ሁሉን አደርጋለሁ አለ። እናም አደረገ! ሕዝቡን አንድ በአንድ፣ በመነጣጠል ፈጀ! የትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ግንባርም ያንኑ በሰላ መንገድ ቀጠለበት። ከዚያ ትምህርት መውሰድ አለብን። ይህ የችግሩ አካል ነው። ሕዝባዊ የሆኑ ማኅበራትና የአካባቢ ቡድኖች በጎኑ ካልቆሙ፤ በሥልጣን ላይ ያለው ክፍል ቀፎ ነው። አሁን በመንግሥት ሥልጣን ላይ ካሉት ይልቅ፤ በየቦታው የየራሳቸው አጀንዳ የሚያራምዱትና ሕዝቡን የሚያፋጁት፤ ሀገራዊ አጀንዳውን እየተቆጣጠሩት ነው። ከላይ የተዘረዘሩት በተግባር ላይ ከዋሉ፤ ይሄንን ማጠፉ ጊዜ አይወስድም።

 

2 Comments

  1. Religious churches are considering not to hold religious services and ceremonies with any other languages except in the national language of the entire country, using only Amharic language in church settings is hoped to bring an end to the current ever growing ethnic tensions and divisions in the Ethiopian society.

  2. What’s Taking place i am new to this, I stumbled upon this I have discovered It positively helpful and
    it has aided me out loads. I hope to give a contribution & assist different users like its helped me.
    Good job.

Comments are closed.

Share