ለሁለተኛው ዙር ጥርጊያ ተዘጋጅቶ፣
ሕዝብ ሊያደነዝዝ ሱስ ጎርፍ መጣ ደሞ፡፡
በመጀመርያው ዙር ሰውን ጥንብዝ አርጎ፣
ይጦብያ ሱስ ናት ሕዝብን አስተኝቶ፣
ወንበር አግዳሚውን ወሰደ ጠራርጎ፡፡
ሱሱን ጭልጥ አርጎ ሕዝብ ሲያንቀላፋ፣
ግንዱን አንከባሎ ተላይ ተሱሉልታ፣
ጉልት አደረገው ታዲሳባ ጫንቃ፡፡
እየዋለ ሲያደር ሱሱ ሲጠንክር፣
ያፈናቅል ጀመር ዜጋ እንደ ባይተዋር፡፡
የሱስ ማደንዘዣ አገር አስተኝቶ፣
ጋሞን አስጠረገ ሸዋ ውስጥ ቡራዮ፡፡
ሱሱ ከቡራዮ እንደ ጎርፍ ፈሶ፣
ጠቅልሎ ወሰደው “መጤን” ለገጣፎ፡፡
ስካር የነዳው ሱስ ስብተን በጥሶ፣
የእንጦጦን አቀበት ሽቅብ ተፈናጦ፣
ሱሉልታን አወከው ውሀ ሙላት ሆኖ፡፡
ይህ የሱስ ነጎድጓድ ወደ ደቡብ ነጉዶ፣
በማበል ወሰደው ጌዲኦን ጠራርጎ፡፡
ሱስ ጅረትን ሆኖ ሰውን ተጠረገው፣
ባህር ሲደርስማ ምን ነፍስ ሊተርፈው ነው?
ሕዝብ ሆይ ነቃ በል ሱሱ ማዕበል ነው፣
የዋጣትን አገር ጠርጎ ሊወስዳት ነው፡፡
የሱስ ጎርፍ ህሊና ይሉኝታ የለውም፣
በውል በምክክር ባማላጅ አይቆምም፣
ገድግዶ የሚያስቀር ያስፈልጋል ግድብ፡፡
በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)
መጋቢት ሁለት ሺ አስራ አንድ ዓ.ም.