አዴፓ ከዳተኝነት፣ ከለዘብተኝነትና  ከይሉኝታ ፖለቲካ ወጥቼ በቁርጠኝነት የህዝባችንን ጥቅም ለማረጋገጥ እየተንቀሳቀስኩ መሆኑ ይታወቅልኝ አለ

የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፖርቲ (አዴፓ) ማዕከላዊ ኮሚቴ ከጥር 13-15/2011 ዓ.ም ድረስ  ያደረገውን መደበኛ ስብሰባ ካጠናቀቀ በኋላ ባወጣው መግለጫው  ድርጅታችን ከዳተኝነትና ለዘብተኝነት እንዲሁም ከይሉኝታ ፖለቲካ ወጥቼ በቁርጠኝነት የህዝባችንን ጥቅም ለማረጋገጥ እየተንቀስቀስኩ መሆኑን ተገንዘቡልኝ አለ:: 

https://www.youtube.com/watch?v=pJpzsue5H3c&t=917s

 “ለዚህ ተልዕኮ መሳካት ወሳኙ ቀዳሚ ጉዳይ በክልላችን ህግ የማስከበርና ሰላም የማረጋገጥ ተልዕኳችን በተሣካ ሁኔታ መፈፀም የሚገባን መሆኑን ማዕከላዊ ኮሚቴው ትኩረት ሰጥቶ ገምግሟል፡፡ ይህ ካልሆነ ማየት የጀመርነው የለውጥ ጭላንጭል መልሶ ሊጠፋ እንደሚችል ተገንዝበን መላው ህብረተሰብ በተለይም ወጣቶች የጀመራችሁትን ህግ የማስከበር ተግባር አጠናክራችሁ ከአመራራችንና ከፀጥታ አስከባሪዎቻችን ጎን በመሰለፍ ለውጡን በጋራ ከማንኛውም ጥቃት እንድንከላከል ማዕከላዊ ኮሚቴው ጥሪውን ያስተላልፋል ፡፡” ያለው መግለጫው ባለ8 ነጥብ አቋሙን ይፋ አድርጓል::

የተወሰነውን ነጥብ እናካፍላችሁ:

ድርጅቱ አቶ በረከት ስም ዖን እና ታደሰ ካሳ ጥንቅሹ ከታሰሩ ከአንድ ቀን በኋላ ባወጣው መግለጫው “  ሙስና እና ብልሹ አሰራር የስርአቱ መገለጫ ሆኖ እንደመቆየቱ መጠን የለውጡ ጉዟችንንም እያደናቀፈ አብሮን እንዲይኖር ሁለት ስለት ያለው ሰይፍ ይዞ መታገል እንደሚገባ ማዕከላዊ ኮሚቴው መክሯል፡፡ ከዚህ አኳያ የክልሉን ህዝብ ሃብት ያለምህረት ሲመዘብሩ በቆዩ አካላት ላይ በሰከነና በበሰለ መንገድ፤ ማስረጃዎችን መሰረት በማድረግ የፀረ-ሙስና ትግልና ህጋዊ እርምጃ መወሰድ የተጀመረ ሲሆን እርምጃው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ባደረሱ አካላትም ተጠናክሮ የሚቀጥልና በድርጊቱ ተሳታፊና ተባባሪ የነበሩ ቡድኖችና ግለሰቦችም በተመሳሳይ ለህግ እንዲቀርቡ ድርጅታችን የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ከመቼውም ጊዜ በላይ ትግሉን አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡ ስለሆነም መላው ህዝባችን ከአማራ ዴሞክራሲያዊ ፖርቲና ከክልሉ መንግስት ጎን በመሰለፍ የተጀመረው የፀረ-ሙስና ትግል ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማዕከላዊ ኮሚቴው ጥሪ አቅርቧል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የካቲት 12 በኢትዮጵያ ታሪክ ልዩ ስፍራ ያለዉ ዕለት ነዉ

“በምዕራብ ጎንደርና በማዕከላዊ ጎንደር የተፈጠረውን የዜጎቻችን ሞት፤ ንብረት መውደምና ከቀያቸው መፈናቀልን በተመለከተ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ በዝርዝር ገምግሟል፡፡ በተፈጠረው ችግርም ከልብ አዝኗል፡፡ ለተፈጠረው ችግር መነሻ ለሆነው የሱር ኮንስትራክሽን ድርጅትና በዜጎቻችን ላይ ያልተገባ እርምጃ በወሰዱ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ የተጀመረውን የማጣራት ስራ በፍጥነት በማጠናቀቅና ህጋዊ እርምጃ በመውሰድ ለህዝባችን እንዲገለፅ ውስኗል፡፡ በሌላም በኩል በቀጠናው የሚታየው ባዕድ ጦርነትና ግጭት እንዲያበቃና ከዚህ በኋላ በአካባቢው ሰላም እንዲሰፍን፤ ዜጎቻችን እንደዚህ ቀደሙ ሁሉ ኑሮአቸውን ተረጋግተው እንዲመሩ፤ በደረሰው ጉዳት የተፈናቀሉ እንዲቋቋሙ፤ አካላዊም ሆነ ሞራላዊ ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖቻችን ትኩረት ሰጥቶ በመደገፍ በቁርጠኝነት እንዲሰራ ማዕከላዊ ኮሚቴው ውሳኔ አሳልፏል፡፡”

የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ 12ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ ውሳኔ ያስተላለፈበትን የወሰንና የማንነት ጉዳይ “ሌሎች ይሰሩታል፤ በህገ-መንግስቱ ይፈታል” ከሚሉ ለዘብተኛ አቋሞች በመውጣት በትኩረትና የአካባቢውን ታሪካዊ ዳራ ጭምር ታሳቢ ባደረገ ሁኔታ ጥያቄው እንዲፈታ ቀጣይነት ያለው ትግልና ክትትል እንደሚደረግ፤ በአገር አቀፍ ደረጃ የማንነትና የወሰን ጥያቄዎችን በዘላቂነት ለመፍታት የተቋቋመው የወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን በፍጥነት ወደ ስራ እንዲገባ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ በማድረግ የጉባዔያችን ውሳኔ ዳር ለማድረስ ማዕከላዊ ኮሚቴያችን በቁርጠኝነት ስራውን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን በድጋሜ አረጋግጧል፡፡

የአማራ ህዝብ በታሪክ አጋጣሚ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በስፋት ተሰባጥሮና ተዋህዶ እንደሚኖር የሚታወቅ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት ቁጥራቸው ቀላል ያልሆነ ህዝባችን ከየሚኖሩበት አካባቢ በተለያየ ምክንያት ተፈናቅለው በየአካባቢው በጊዜያዊ መጠለያዎች በችግር ውስጥ ህይወት በመግፋት ላይ እንደሚገኙ ማዕከላዊ ኮሚቴያችን በዝርዝር ገምግሟል፡፡ በመሆኑም ለተፈናቀሉ ወገኖቻችን የዕለት ቀለብ የማቅረብና መጠለያ የማመቻቸት ስራ የሚቀጥል ሲሆን ጎን ለጎንም ችግሩ በዘላቂነት የሚፈታበት አግባብ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ ለተግባራዊነቱም ሌት ከቀን ስራዎች እንዲሰሩ ተወስኗል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ህውሀት የልብ ልብ የተሰማው ከመንግስት አቅመ ቢስነት የተነሳ ነው ገዳዩ የሟቾች ቤተሰብ ባሉበት በአደባባይ ካልተሰቀለ እርምጃ ተወስዷል አልልም ታዴዎስ ታንቱ

የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ቀጣይነቱ እንዲረጋገጥ ከአስፈለገ በኢኮኖሚ አቅሙ ጠንካራ የሆነ ህዝብ መፍጠርን ዓላማ ያደረገ አመራር ማረጋገጥ እንደሚገባ ድርጅታችን የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በፅኑ ያምናል፡፡ ድህነት ሁለንተናዊ አቅምን እንደሚሰልብ ጥርጥር የለውም፡፡ ስለሆነም የክልላችንን ኢኮኖሚ የማሣደግ ጉዳይ ተኪ የማይገኝለት ተልዕኮ ነው፡፡

መላው የክልላችን ህዝቦች፤ ወጣቶች፤ ሴቶች፤ ባለሃብቶች፤ የመንግስት ሰራተኞች፤ አርሶ አደሮች፤ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ ሲቪክ ማህበራት፤ የፖለቲካና የሚዲያ አክቲቪስቶች በሙሉ፡- አሁን የምንገኝበት ወቅት የሽግግር ወቅት በመሆኑ ሁኔታዎችን በጥንቃቄ፤ በመቻቻልና በመተባበር መንፈስ መስራት፤ መደማመጥ የሚገባን ወቅት ነው፡፡ ይህን ሂደት አውቆም ይሁን ሳይረዳው የሚያደናቅፍ ቁጥሩ ቀላል ያልሆነ ሃይል አለ፡፡ በሂደቱም በክልላችን እያጋጠሙ ያሉ ህገ-ወጥ ድርጊቶች በዝርዝር ተለይተዋል፡፡ ክልላችን ሙሉ በሙሉ ሰላም የሰፈነበት መሆን አለበት፡፡ በዜጎቻችን ላይ ጥቃት እንዳይደረስ፤ ህገ-ወጥ ድርጊቶች እንዲታረሙ ህዝባችንን በማደራጀትና በማብቃት የምንቀሳቀስ ይሆናል፡፡ ከዚህ አልፎ ለሚመጣ ህገ-ወጥነት ህጋዊ እርምጃም የሚወሰድ መሆኑ ተሰምሮበታል፡፡ በመሆኑም ለአማራ ህዝብ ጥቅም ቆሜያለሁ የሚል ሃይል ሁሉ ለዚህ አቋም ተፈፃሚነት ከህዝባችን፤ ከፓርቲያችንና ከመንግስታችን ጋር በትብብር መንቀሳቀስ ይኖርብናል፡፡

ወቅቱ መላ የአገራችን ህዝቦች አጋርና እህት ድርጅቶች ተደጋግፈንና አጥፊውን እያረምን እንድነታችንን አጠናክረን የምንቀጥልበት እንደሆነ ፓርቲያችን የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ያምናል፡፡ በተለይም ለረጁም ጊዜ የጉርብትና ብቻ ሣይሆን የተሣሰረ የደም ግንኙነት ከአለን የትግራይና የኦሮሞ ህዝብ ጋር በተባበረ ክንድ በመሥራት ለውጡን ቀጣይ የምናደርግ ሲሆን የአማራ ህዝብ ከነዚህ ህዝቦች ጋር እንዲነጠልና በጥላቻ መንፈስ እንዲተያዩ ለማድረግ የሚሰበከውን ዘመን ያለፈበት የጥላቻ ትርክት የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እንደማያምነበትና በፅኑም እንደሚታገለው ማእከላዊ ኮሚቴው ገምግሟል ፡፡ ይህ ብቻ ሣይሆን የአማራ ህዝብ ወንድሞና ጎረቤት ከሆኑት ከአፋርና ቤኒሻንጉል ጉምዝ ህዝቦችና ከሌሎችም የሃገራችን ህዝቦች ጋር በመተባበር ህብረ ብሔራዊነትና ዴሞክሲያዊ ኢትዮጵያን ለመገንባት በሚካሄደው ትግል ታሪካዊ ኃላፊነቱን እንደሚወጣ ቃል በመግባት ጭምር ማእከላዊ ኮሚቴው ስብሰባውን አጠናቋል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የመኢአድ ም/ፕሬዝደንት አቶ ዘመነ ምህረት ከፍተኛ ድብደባ እንደተፈፀመባቸው ፓርቲው ገለፀ
Share