ህወሓት የትግራይን ሕዝብ ወደ ጦርነት የሚያስገቡ  እንቅስቃሴዎች እያደረገ መሆኑ ተነገረ

በቅርቡ የመቀሌ ዩኒቨርስቲ ባዘጋጀው ስብሰባ ሀሳባቸውን ሳይጨርሱ በጭብጨባ ንግግራቸው የተቋረጠባቸው አቶ አምዶም ገብረስላሴ ‹‹ህወሓት የትግራይን ሕዝብ ወደ ጦርነት የሚያስገቡ  እንቅስቃሴዎች እያደረገ ነው›› አሉ፡፡ 

የአረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ለሉአላዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ የሆኑት አቶ አምዶም ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሰጡት ቃለምልልስ በወቅቱ ያነሱት ሃሳብ ምን እንደሆነ ተጠይቀው ‹‹አቶ በረከት ስምዖን ኢህአዴግ የሕግ የበላይነትን እያስከበረ አይደለም፤  የሀገሪቱ አካሄድም አደገኛ ነው የሚል አስተያየት አቅርበዋል፡፡ እኔ ደግሞ ኢሕአዴግ የለም፣ ሊጠፋ ተቃርቧል የሚል አስተያየት ሰጥቻለሁ፡፡›› ብለዋል፡፡

 

ጨምረውም ‹‹ህወሓትና የትግራይ ሕዝብ አንድ ናቸው የሚል የተለመደና የተሳሳተ ፕሮፓጋንዳ አለ፡፡ ይሄ ትክክል እንዳልሆነና ያለው በጣም አምባገነን መንግሥት በመሆኑ ከጭቁኑ ሕዝብ ጋር እንደ አንድ መታየት እንደሌለበት ማብራሪያ ለመስጠት ሞክሬ ነበር፡፡ በመካከል በጭብጨባ አቋርጠውኛል፡፡›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡ በዋነኝነት የአቶ አምዶምን ንግግር በጭብጨባ ያቋረጡት አዛውንቱ አቦይ ስብሀት ነጋ ሲሆኑ ንግግራቸውን ባይቋረጥ ምን ይናገሩ እንደነበርም ተጠይቀው ነበር፡፡ አቶ አምዶም ሲናገሩ ‹‹ኤፈርትን በኃላፊነት ያገለገሉት አቶ ስብሀት ነጋ መድረኩ ላይ ስለነበሩ ባያቋርጡኝ ድርጅቱን በተመለከተ ለመናገር ነበር ያሰብኩት፡፡ ከኤፈርት ጋር በተያያዘ የትግራይ ሕዝብ ተጠቃሚ እንደሆነ ተደርጎ ይወራል፡፡

ህወሓት ድርጅቱን ለራሱ ነው መጠቀሚያ ያደረገው፡፡ ይሄ ድርጅት ለትግራይ ሕዝብ ጠቅሞ እንደማያውቅ፤ በትግራይ ላይ ያለው  አፈና፤ የዴሞክራሲና የፍትህ እጦት፤ የፖለቲካ ምሕዳሩ ጠባብ መሆን፤ በሀገሪቱ ያለው ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታም ጥንቃቄ ሊደረግበት እንደሚገባ ለመግለጽ  አስቤ ነበር፡፡›› በማለት ገልፀዋል፡፡ መድረኩ ሀሳብን የመግለጽና የመናገር ሕገ መንግሥታዊ መብት በትግራይ በጣም የማይቻል መሆኑን፤ ከትላልቅ መሪዎች እስከ ተራው ካድሬ ሕዝቡን አፍነውት እንደነበረ ያሳየ መሆኑን ያስረዱት አቶ አምዶም ‹‹ህወሓት ከፍተኛ ኔትወርክ አለው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ‹‹ተሸንፈናል!!››ከጃዋር እስከ አንዷለም አራጌ! የባከኑት! | የፕ/ር አስራት ወልደየስ ብርጌድ ፋኖ አዛዡ |

እዚያ የሚገኘው ሚዲያ  ከእነርሱ አመለካከት ውጭ ሌላ ነገር አያስተናግድም፡፡ እነዚህና ሌሎችም ተጨምረው ነው አፈና የሚደረገው፡፡›› ብለዋል፡፡ ድርጅታቸው አረና በአሁኑ ወቅት ያለውን የህወሓት አቋም እንዴት እንደሚገመግመው ተጠይቀው ሲመልሱ ደግሞ ‹‹ህወሓት ከፌዴራል ተሸንፎ ነው የመጣው፤ በጣም ችግር ላይ ነው ያለው፡፡  የቆየው በጠመንጃ፣ በደህንነት፣ በፖሊስ እና በገንዘብ ኃይል ሲሆን፤ የትግራይን ሕዝብ ፍላጎት የማያሟላና ለማስተዳደር የማይበቃ ድርጅት ነው፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ተጋልጦ ከፍተኛ አደጋ ላይ ነው ያለው፡፡ ህወሓት የትግራይን ሕዝብ ወደ ጦርነት የሚያስገቡ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እያደረገ ነው፡፡

በአማራው ክልል አዴፓ እና በህወሓት መካከል ያለው የሥልጣን ሽኩቻ  የሁለቱን ክልሎች  ሕዝቦች ያጋጫል፤ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል ብለን እንገምታለን፡፡›› ማለታቸውን ከቃለምልልሱ አንብበናል፡፡

https://www.youtube.com/watch?v=rcbWeNfbu_o&t=32s

Share