ግርማ በላይ – ኢትዮጵያ ፤ አዲስ አበባ ([email protected])
አውቃለሁ – ይህ አጭር ደብዳቤየ ደርሶት የማያስተናግደኝ ድረ-ገፅ ሞልቷል፡፡ እናም ከልቤ እንዲህ እላለሁ – ሆን ብሎ በትዕቢትም ይሁን በዕብሪት ወይም በሌላ ማንኛውም ምክንያት ይህን ጭንቀቴን መረዳት የማይፈልግ ኢትዮጵያዊ ነኝ ባይ ሁሉ ጥቁር ውሻ ይውለድ፡፡ እምራገመው ከአንጀቴ ነው፡፡ በአሁኒቷ ቅጽት ማለትም በአቤቶኪቻው ድረገፅ አነሳሽነት የዚህን የተረገመ ሰውዬ ጽሑፍ ካነበብኩ በኋላ ስሜቴን መቆጣጠር ባቃተኝ ደረጃ ተናድጃለሁ፡፡ ይህን ጭንቀቴን ተረድቶ ሊያስታምመኝ የማይፈልግ ወገን – ማንም ይሁን ማን – የእምዬ ኢትዮጵያ አምላክ ከጊዜ መዝገብ በአጭርነቱ በሚታወቅ ቅጽበት ውስጥ የዶጋ ዐመድ ያድርገው – በቃ፡፡ ተስፋ ስትቆርጥ አይደለም መራገምና መሳደብ ያገኘኸውን ነገር አንስተህ በመወርወር በእጅህ ሰው ታጠፋለህ፡፡ የዚህ ነቀርሣ ሰውዬ መርዝ ማርከሻ ካልተገኘ በጣም አደገኛ ሁኔታ ሊከሰት እንደሚችል የምንረዳ ሰዎች በአሁኑ ወቅት እንይዘውንና እንጨብጠውን አጥተን የታሪክንና የፈጣሪን ፍርድ ብቻ በከፍተኛ ጉጉት መጠባበቅ ላይ ነን፡፡
ከአሣታሚው ድርጅት ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ምክንያት ብዙ ገንዘብ እንደሚያገኝበት የጠበቀውን መጽሐፍ ክፍያውን እኛ በዓይነት እንድንከፍልለት ወስኖ በነጻ አድሎናል – ያ የዓይነት ክፍያም የኢትዮጵያውያን በተለይም የአማራና የኦሮሞ እርስ በርስ መጨራረስ ነው – ቸሩ መድሓኔዓለም ይህን የመከራ ድግስ ለራሱና ለመሰሎቹ ያዙርለት፡፡ መርዝ በነጻ ታደለ፤ እኛም ያገኘን መስሎን ተገኘን! ርህራሄ በሌለው ዱላም ተስፋዬ ለመቶኛ ጊዜ ይዠልጠን ገባ፡፡ ተባባሪዎችን እስካገኘ ድረስ ደግሞ እሱ ምን ቆርጦት ገና ብዙ ያዳክረናል፡፡ ከሚያገኘው ገንዘብ ይልቅ የተስፋዬ ቅርሻት በሕዝቡ ዘንድ የሚፈጥረው ግማትና ቀጣዩ ሁከት በልጦበት በነጻ አሰራጨው – የኛ altruist የ”ኪነ ጥበብ ሰው”፡፡
እንደሚታወቀው ይህ የሰባት አጋንንት ውላጅ ገብረ ዲያብሎስ የበጎ አድራጎት ድርጅት የከፈተ አይመስለኝም፤ በተፈጥሮውም ከነሂትለርና ሙሶሊኒ የከፋ አረመኔ እንጂ ለሰው አዛኝና ሩህሩህ አይደለም፤ ከመያዶች(NGOs) ድጎማ ስለመሰጠቱ እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡ የኤርትራ መንግሥት ወጪውን ሸፍኖለትም ከሆነ አላውቅም፡፡ ስለዚህ ይህን ብዙ የደከመበትን አርቲ ቡርቲ በነጻ በድረገፅ መልቀቁ ከመነሻው የእልህና ኢትዮጵያን የማውደም ዓላማ አንግቦ እንጂ ለደግ ተግባር እንዳልሆነ መታወቅ ነበረበት፡፡ ቄንጥ እየመሰለን ብዙዎቻችን በምንሠራው አጉል ሥራ ይህን ሰውዬ የልብ ልብ እዬሰጠን በላያችን ላይ እንዲጸዳዳ እያደረግነው ነው ፡፡(ደግሞም “የሥነ ጽሑፍ አድባር የወረደችለት ዘመናዊ ደራሲ” እየተባለ ይሞካሽልኛል፡፡ የቱ ነው የተስፋዬ ሥነ ጽሑፍ? ሥነ ጽሑፍን ከአርቲ ቡርቲ የመንደር ወሬ መለየት የሚችል ሰው ከናካቴው ጠፋ ማለት ነው? እንዲያ ከሆነ አሳሳቢ ነው! ለምሳሌ የዚህ የ‹ስደተኛው ማስታወሻ› የሚል ዝባዝንኬ ጽሑፍ ታሪኩ የታል? ሤራው የታል? ግጭቱ የታል? ጭብጡ የታል? ጡዘት ልቀቱ የታል? ለመሆኑ ልቦለድና ኢ-ልቦለድ ምንድነው አንድነታቸውና ልዩነታቸው? ለምን በሥነ ጽሑፍ ይቀለዳል? ተስፋዬን በአዲስ ጃነር “ጸሓፌ-መስተፃልዕ ወጸላኤ ፍቅር” ብሎ መፈረጅ ይቻል እንደሆነ እንጂ ከጽሑፎቹ የአማርኛ ሥነ ጽሑፋዊ ውበት ውጪ የተዋጣለት ደራሲ የሚል ቅጥያ ትከሻውን ያጎብጥበታልና ይቅርበት – ‹ባናርስ አጣምደናል› እባክህን!) በነጻ የለቀቀውን መርዝ በነጻነት እየተጎነጨን ልናብድ የደረስን ዜጎች ሞልተናልና የሚመለከታችሁ ወገኖች የእሪታ ድምጻችንን ስሙልን ፤ አሰሙልንም፡፡ እምቢ ብትሉ አሁንም ዕጣ-ፋንታችሁ የተስፋዬ እንዲሆን ከመጸለይ ውጪ ለጊዜው ምንም የምንለው ነገር የለም፡፡ ከአዲሱ የተስፋዬ መጽሐፍ ገጽ 89 ላይ የሚከተለውን ተመልከቱ፡፡ እያንዳንዷን ዐረፍተ ነገር ልብ ብላችሁ አስቧት፡፡ ልክ እንደቡርቃ ዝምታ መጽሀፉ ሆን ብሎና በዕቅድ አማራንና ኦሮሞን ለማጋጨት ያጠነጠነው የተንኮል ክር ነው፡፡ ይህ ጽሑፍ ከአርባና አምሳ ዓመታት በፊት ቢጻፍ ምናልባት ትርጉም ሊኖረው ይችል ነበር – አስተማሪነትም ላይጠፋበት ይችላል – አንዳንድ ደናቁርት አማሮችም አልነበሩም አይባልምና፡፡ አሁን ግን ላም ባልዋለበት ግጭት ለቀማ ካልሆነ ኩበት የለም፡፡ (ይህ የመጽሐፉ ክፍል የመጽሐፉ አንኳር ተልእኮ የሚተላለፍበት ዋና ቁም-ነገሩ ነው – ለተስፋዬ፡፡ የተቀረው ባብዛኛው ለዚህ በ‹ማን አባት ገደል ገባ› የልጆች ጨዋታ ዓይነት የማጣያ ድግምታዊ አንደርብ እንደመናጆ የሚውል ነው፡፡)
ክፍላቸው ውስጥ ቶለሳ መገርሳ የሚባል ተማሪ ነበር። ስሙ በመምህሩ ሲጠራ ወይም እሱ ስሙን ሲናገር ተማሪዎቹ ይስቃሉ። ተማሪዎቹ በሳቁ ቁጥር ጫልቱ ኪሎዋ ይቀንሳል። ሄለን አለመሆኗ፣ ጫልቱ ሚደቅሳ መሆኗ የሚታወቅ እየመሰላት ላብ ያጠምቃታል። ቶለሳ በተመሳሳይ ሲሰቃይ ታየዋለች። ራቁቱን የሆነ ያህል እጁን የሚያስቀምጥበት ቦታ ይቸግረዋል። ጫልቱ አንድም ቀን ግን አዋርታው አታውቅም። በአጋጣሚ እንኳ ሲጠጋጉ ፈጥና ዘወር ትላለች። በስሙና በአማርኛው ቶለሳ ላይ ሲሳቅበት አብራ ስቃ አታውቅም። አቀርቅራ ዝም ትላለች። በተመሳሳይ ኤልሳ አበበ ጫላ የምትባል ሌላ ተማሪ ነበረች። አዲስ አበባ የተወለደች ናት። አማርኛዋ ችግር አልነበረበትም። ንቅሳትም የለባትም። የአያቷ ስም ጫላ በመሆኑ ብቻ የቀልድ ኢላማ ሆና ነበር። ተማሪዎቹ “ጫላ” እያሉ ይጠሯታል። ይህም ጫልቱን በጣም አስደንቆአት ነበር። ያልተመለሱ ጥያቄዎች እንደ ቢንቢ ይወሯታል…
……..
ርግጥ ነው፣ በሁለተኛ ቋንቋ ስሜትን መግለፅ ያስቸግራል።በመሆኑም ጫልቱ ይህን መሰል ችግር ውስጥ መግባቷ ግድ ነበር።የዘመድ መርዶ መጥቶ በተነገራቸው ጊዜ ይህ ችግር ገጥሞአታል። በኦሮምኛ ማልቀስ በመጀመሯ፣ ከሳሎኑ ተነጥላ ጓዳ ገብታ እንድታለቅስ ተደረገች። አክስቷ፣ “አኒበዴ” የሚለው ቃል በጓደኞቿ እና በጎረቤቶቿ ፊት እንዲሰማ ሳትፈልግ ቀረች።
አሁን ወደ ጥያቄዎቼ ልሂድ፡፡
- ተስፋዬ የተባልከው ሰይጣን አማራንና ኦሮሞን ለማበጣበጥ ቆርጠህ መነሳትህ ግልጽ ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ምን አነሳሳህ? ሀሰትም ይሁን እውነት ያለፈን መጥፎ ታሪክ አሁን ከተቀበረበት እያወሱ አንዱን በአንዱ ላይ በማነሳሳት ሊፈጠር በሚችል ጠብና ሁከት ምን ዓይነት እርካታስ ነው የምታገኝ? ከዚህ የተሻለ የምትሠራው ነገር አጥተህ ነው ወይንስ የተፈጥሮ ጥሪህ የጥፋትና የጥፋት ብቻ ሆኖብህ አንተም ተቸግረህ ነው? እንዲህ ከሆነ ለምን ሀኪም አታማክርም ወይም ክፍልና ኮከብህን አስቆጥረህ ወደጠበል አትሄድም? ኢትዮጵያና ኤርትራ የሚጠቀሙት አማራ ሲጠፋ ብቻ ነው ብለህ ለማመን የተገደድከው በምን አመክንዮ ይሆን? ብንፋቀር እንጠቀማለን ወይንስ ብንጣላ? ተለያይተን ሞከርነው – ውጤቱ አንተም እንደምታውቀው ነው – ዛሩ እንዳልሰከነለት ባለውቃቢ ከሀገር ሀገር የሚያንከራትትህና ዜግነትህን ሳይቀር እንደሸሚዝ የሚያለዋውጥህ፣ ትዳርም ይዘህ የተረጋጋ ማኅበረሰብኣዊና ኢኮኖሚያዊ ሕይወት እንዳይኖርህ ያደረገኽ ይሄው የእናትና ልጅ በመሠሪዎች ተገነጣጥነው ለየብቻቸው መኖር ነው፡፡ ታዲያ ዛሬ በ21ኛ መቶ ክፍለ ዘመን የሥልጣኔና የሰው ልጅ ከፍተኛ የዕድገት ደረጃ ላይ የደረሰበት የግሎባላይዜሽን ዘመን ላይ ሆነህ እንደጥነቱ የመንደርተኝነትና ጠጎጠኝነት አስጠሊታ ዘመን ‹የአባት ሀገር፤ የእናት ሀገር› እያልክ የምትቀባዥረው ይህ አስከፊ ሁኔታ እስከዘላለሙ እንዲቀጥል ትፈልጋለህ ማለት ነው? ከጥፋት መንገድህ በአፋጣኝ የማትመለስ ከሆነ እግዚአብሔር በጀመረህ መንገድ ሲያንቀዠቅዥህ ይኑር – በአንተ ቤት ሁሉን ነገር ዐውቀህና ከሁለንተናዊነት ይልቅ ጎጠኝነቱ ይሻለኛል ብለህ ሞተሃል፡፡ ይታይህ – አንድ ሰው ተነስቶ – በቃ ከመሬት ተነስቶ ልበልህ – “የኤርትራ ዜጎች ከምድረ ገፅ ካልጠፉ መካከለኛው ምሥራቅም ሆነ የአፍሪካ ቀንድ ሰላም አያገኙም!” ቢልና ኤርትራ እንደኢራን በማዕቀብ ተወጥራ ልትፈነዳ ብትደርስ ወይም ኤርትራ እንደሦርያ የጦር ዐውድማ ብትሆን ትደሰታለህ ወይ? ይከፋሃል፤ ታለቅሳለህም – አውቃለሁ፡፡ አንተ የዲያብሎስ ውላጅ ሽል መንጣሪ ነህ፡፡ የበላህበትንም ወጪት የምትሰብር፣ የጠጣህበትንም ዋንጫ ወደገደል የምትወረውር ልዩ ፍጡር ነህ፡፡ ዋጋህን እግዜር ይክፈልህ፡፡ አንተ በኤርትራ መጎሰቆልና የጥቃት ዒላማ ውስጥ መግባት ከተከፋህና ካዘንህ ለእኛ ለምሥኪን ኢትዮጵያውያንስ ዕልቂት ለምን ትደግስልናለህ? አንተም ሆንክ አባትህ ሻዕቢያና አጎትህ ወያኔ እስካሁን የምታሰቃዩን አነሰን ወይ? እምነትህ ዋቄፈታ መሆኑንና የእሬቻ ባህላዊ ወግና ልማድ ደጋፊ መሆንክን በአዲሱ ጽሑፍህ በቀጥታም ባይሆን በተዛዋሪ ነግረኸናል፡፡ ስለዚህ ሃይማኖትህን አልጠይቅም፡፡ እንደኔ ግምት ግን ኤቲይስት መሆን አለብህ፡፡ ምክንያቱም በእሬቻም ሆነ በተለያዩ ሰማያዊም ይሁኑ ምድራዊ አማልክት የሚያምኑ ሰዎች እንዳንተ ጨካኝ አይደሉም፤ ምንም ይሁን ምን ሃይማኖት ያለው አንድ ሰው ያንተን ያህል ቀርቶ የሩብ እሩብህንም ያህል እንኳን በሰዎች ስቃይ አይደሰትም፡፡ብዙ የደጋግ መርህ ሰዎች የሆኑ ኤቲይስት ጓደኞች አሉኝ፡፡ አንተ ግን እንዲያውም ሴቴኒስት ሳትሆን አትቀርም፡፡
ስለዚህ አንተ ወይም አንተን በተልእኮ አስፈጻሚነት የላከ አካል ችግር አለባችሁ ማለት ነው፡፡ ያ ችግር የሚፈታው ደግሞ እናንተ ስትጠፉ ወይም አስተሳሰባችሁን ስትቀይሩ ነው፡፡ በመሠረቱ ሰውን ‘በማጥፋት ለውጥ ስለማይመጣ የአመለካከታችሁን መለወጥ ለብዙ ጊዜ ስንጠብቀው የነበረ ጉዳይ ነው – ግን አልተሳካልንም፡፡ የነገውን አላውቅም፡፡
- ግንቦት ሰባት ከዚህ ሰውዬ ምን አላችሁ? ከዚህ ሰውዬ ጋር አብራችሁ እየሠራችሁ ከሆነ ፈጣሪ “የልጅነት ጊዜያችሁን አያስጨርሳችሁ” ብዬ እንዳልረግማችሁ በውነት ለምን እንደሆነ … አይ … ንዴቴ ከመነሻው አሁን በረድ ስላለልኝ ይቅርብኝ፤ በአንድ ተስፋዬ ሳቢያ የብዙዎችን ቀና ልፋት ማጠየም ያለብኝ አይመስለኝምና እርግማኔን ለሌላ ጊዜ አስተላለፍኩት ፡፡ ጅምሩ ያላማረ መጨረሻውም አያምርምና ከዚህ ከሰይጣን ሰውዬ ለኢትዮጵያ ነጻነት የሚመጣ ነገር ባፍንጫችን ይውጣ፡፡ ይህ ሰው መጠቀሚያ እያደረጋችሁ እንደሆነ መገመት ይቻላል – ባለፈው የሰጠውን አንድ ቃለ ምልልስ ወደጽሑፍ ተገልብጦ ዘሀበሻ ድረገፅ ላይ አንብቤያለሁ፡፡ ወደሰውነት የሚገባና ከሰውነት የሚወጣ አንድ አይደሉም፡፡ ለምንም ዓይነት ሥልት ይሁን ተስፋዬ ያለበት የነጻነት ትግል ለኢትዮጵያ ቀርቶ ለማንም አይጠቅምምና ግንቦት ሰባት ከዚህ ሰውዬ ጋር ግንኙነት ካለው ቁርጡን ነግሮን እሱን አንጋጠን መጠበቃችንን እናቁም ዘንድ ይርዳን፤ ይህም ብቻም አይደለም ተስፋዬ ያለበትን ስብስብ ሕዝብ እንዲረዳውና የራሱን መውጫ ቀዳዳ እንዲያፈላልግ የበኩላችንን ጥረት እናድርግ – ሞኝነት ለእንዶድም አልበጃትምና ከዚህ አኳያ ሁሉም ይነጋገርበት፤ ይወቃቀስበት፤ መፍትሔም ይፈልግበት፡፡ ትግሉ ፈር እየያዘ የሚሄደው ጠላትንና ወዳጅን ለይቶ ከማወቅ ሲጀመር ነው፡፡ አማራን ለማስጨረስ ቆርጦ ከተነሣ ሰው ጋር ተባብሮ አማራንም ሆነ ሌላውን ወደሌላ የጭቆና አዙሪት ለመክተት ካልሆነ በስተቀር ለነጻነት የሚደረግ ትግል የለም፡፡ ስለዚህ ግንቦት ሰባትና ይህ ሰው ያላቸውን ግንኙነት አስረዱን – በኢትዮጵያ አምላክ እንለምናለን፡፡ እንዴ? የሰው ጭንቀት አይገባችሁም? ዝም ባለ አፍ ተስፋዬ ሲገባበት ማየት ለማንወድ ዜጎች የግንቦት ሰባትን አጭር መልስ እንፈልጋለን፡፡
- ኢሳት ስለዚህ ሰውዬ ተንፍሶ አያውቅም፤ አለመተንፈሱ መብቱ ነው – “ለምን”ን ማስከተሉንና ለዚያ ተገቢ “ለምን” በምን ምክንት መልስ እንደተነፈገ የማስረዳት ግዴታ ግን አለበት – ኢሳት፡፡ (‹ማንም እንደፈለገው ይጩህ እኛ ግን ሥራችንን በርትተን እንሠራለን› ማለቱም በመሠረተ ሃሳቡ ትክክል ሆኖ እንዳካሄድ ግን የተወሰነ ህፀፅ አለበት – ‹ግመሎቹ ይጓዛሉ -ውሾቹም ይጮኻሉ› ከሚለው ነባር የወያኔ አሠራር ለመሻል ከአነጋገር ጀምሮ መጠንቀቅ ይገባልና፡፡ ‹በየት ዞረሽ ቀደምሽኝ?› አልነበር ያሉት አለቃ ገ/ሃና እቤታቸው አስጠልቷቸው ጓደኛቸው ቤት ምሣ ሊበሉ ሲሄዱ ለቀረበላቸው ሽሮ ይሁን ጎመን?) ወያኔን ሰርክ የሚያወግዝ የሕዝብ እስትንፋስ ለምንድነው ይህ ሰውዬ ላይ ሲደርስ ብዕሩና አንደበቱ የሚልፈሰፈሰው? ምን ዓይነት ሥልት ነው? የኤርትራ መንግሥት ኢትዮጵያውውን ታጣቂዎችን መርዳቱ እስከተገለጠና ተስፋ እንዳለም እስከተገለጠ ድረስ የዚህ ሰውዬ እኩይ ተግባር የኤርትራው መንግሥት ሃይ እንዲለው “ወንድሞች! ይህ ሰውዬኣቺሁ ጥረታችንን አመኔታ በማሳጣት እያጠየመው ነው፤ ለተወሰነ ጊዜ አደብ እንዲገዛ ይደረግልን፡፡ ታጥቦ ጭቃ ሊያደርገን ነው፡፡” ብሎ ማሳሰብ አይቻልም ነበር ወይ? የምን መደባበቅ ነው? የምንስ ዕንቆቅልሽ ነው?ተስፋዬ እግዜር መሆኑ ነው እንዴ? ‹ስንት ሰዓት ነው እንዴ?› ይለኛል አንድ ትግሬ ጓደኛየ፡፡ ያልገባኝ ብዙ ነገር አለ፤ አውቃለሁ፡፡ ተስፋዬ በኢሳት እንዲፏልል መድረክ ያልተሰጠውን ያህል – ይህን ያህል ስለእርሱ መጥፎ ዕቅድ አንዳችም ያለመወራቱ ምክንያት ግን ላውቅ ይገባኛል፤ ከመብቶቼ ትንሹ ነው፡፡
- በመጨረሻም ከዚህ ሰውዬ ጋር – በኢትዮጵያ የኤርትራ ጉዳይ አስፈጻሚና በኢትዮጵያ የናዚ ኦሽትዊዝ ኢንደፈጠር ሌት ከቀን ከሚጥር ከዚህ በላኤሰብዕ ጋር ወግናችሁ የምትገኙ ወገኖች ሁሉ በቶሎ ከዚህ እርኩስ መንፈስ ካልተለያችሁ እናንተም ጥቁር ውሻ ውለዱ፡፡ ለየትኛውም የትግል ሥልት ይሁን ከዚህ ሰው ጋር ለኢትዮጵያ ብሎ የሚሠራ የተረገመ ይሁን፡፡ ሰይጣን የትኛውንም ሀገር ነጻ አውጥቶና ከጭቆናና ከመሪር አገዛዝ አላቅቆ አያውቅም፡፡ መጽሐፉን አንብቡና ተለዩት – በቃ፡፡ “በቃ!” ለተስፋዬ ሲሆን መስነፍ የለበትም – ገኣስ! የአክልና ተስፋዬ! ከአሁን በኋላ በተስፋዬ ፍቅር እንደተነደፈ የሚጸና ቢኖር እርሱ የኢትዮጵያ “ሕዝቦች” ቀንደኛ ጠላት ነው፡፡ ክፋትን ለማውገዝ በግድ ክህነት እንዲኖረን አይጠበቅብንም፡፡
- በሕዝብ ዘንድ ታዋቂነትና ሕዝባዊነትን ያተረፋችሁና እያተረፋችሁ የምትገኙ ዜጎች – እነታማኝ በየነ፣ እነገብረ መድህን አርአያ፣ እነአበበ ገላውና በለው፣ እነብርሃኑ ዳምጤ፣ እነእንትናና እነእንቶኔ ሁሉ — ስንቱ ተዘርዝሮ —- ብቻ ሁሉም የታወቀም ያልታወቀም ኢትዮጵያዊ ሁሉ የዚህን ሰው ብልግናና መሠሪ ተንኮል እያወቃችሁ በሆነ ምክንያት የማታጋልጡ ከሆነ እናንተም ሀገራችን ሁለንተናዊ ችግሮች እየተባባሰ መሄድ (ዐውቃችሁም ሆነ ሳታውቁ – ምናልባትም ሳታውቁና በ‹ትግስት›ም) ቢያንስ ከኔ በበለጠ አስተዋፅዖ እያደረጋችሁ ነውና እግዚአብሔር የሚገባችሁን ፍርድ አይንሳችሁ፡፡ ለሀገር ሲባል ልጭና አፍሮ የለም፡፡ ለሀገር ሲባል ጥሬና ብስል የለም፡፡ ትግል በተፈጥሮው መራራ ነው፡፡ እውነት በተፈጥሮዋ መራራ ናት፡፡ አንድ ነገር ለማግኘት ብለህ አንድ እንዲኖርህ የማትፈልገው ነገር እንዲኖርህ ከፈለግህ ምንም ነገር እንዳይኖርህ ብትሆን ይሻላል ( ቀላል ምሳሌ፤ -5+5= 0)፡፡ መጽሐፉ -“ቀኝ ዐይንህ ብታስትህ ካንተ አውልቀህ ጣላት፤ ከሁለት ዐይኖችህ ጋር ወደሲዖል ከምትወርድ አንድ ዐይና ሆነህ ወደገነት ብትገባ ይሻልሃል፡፡” ይላል፡፡ ከተስፋዬ ጋር አራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ለመግባት የሚመኝ ቢኖር ካለተስፋዬ በለመደው ባርነት ቢኖር ይቀለዋል፡፡ አንድ ሞትና ዘጠኝ ሞት ያው ነው – ይህ የኔ እውነት፣ ውሸት መሆኑን የሚያስረዳኝ ሰው ባገኝ ግን እጅግ ደስ ይለኛል፡፡ ፈራሁ…. በጣም ያስፈራል፡፡ ነገሩ እንዲህ አስፈሪ ከሆነ ዘንዳ አዋጪ አማራጭ መፈለግ ሊኖርብን ነው፡፡ ሰውን እንደትንኝና እንደትቢያ ከምትቆጥሩ ወገኖች ምንም አልጠብቅም፡፡ የአንድ ዜጋችን ጭንቀት የኛም ጭንቀት ነው ከምትሉ ወገኖቼ ግን ብዙ አጽናኝ ቃላትን በጉጉት እጠብቃለሁ፡፡ በውነቱ ተስፋዬ ብዙ አስደንግጦኛል – ተወን ስል እንደአዲስ በመጀመሩ ፈራሁ፡፡
ልጨርስ ነው፡፡ ከአንዲት አክስቴ እውነተኛ ግለ-ታሪክ እንማር፡፡ አንዲት የጎረቤት ሴት ወደቤቷ ትመጣለች፡፡ አክስቴ ደግና የዋህ ነበረች፡፡ ብረት ምጣዷን ጎተት ታደርግና ቡና ልታፈላላት መንደፋደፍ ትይዛለች፡፡ እሳቱ እስኪጋጋምና ቡናው እስኪቆላም ከማጀቱ ሞሰብ እንጀራ ዘንጠፍ አድርጋ በሌማት ላይ አድርጋ ታቀርባለች – ጊዜው እንዳሁኑ ሙትቻ አልነበረም፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ እንደዳቦ የሚገመጥ እርጎ ከላጋው አውጥታ አዋዜ እላዩ ላይ ጣል ታደርግበትና እንድትበላ ፈገግታ በተሞላበት ፊቷ ትጋብዛታለች፡፡ የሃሜት ሱሰኛ የነበረችው ያቺ ሴት እጇን ወደቀረበው ማዕድ ከመሰንዘሯ ጎን ለጎን፣ “አይ ወ/ሮ እገሊት፣ አንቺስ ጥሩ ሚስት ነበርሽ፤ ባልሽ ግን …” ብላ የነገር ኮረጆዋን ከፍታ የሃሜት ጥይት እሩምታዋን ለማስወንጨፍ ከመጀመሯ ቆፍጣናዋ አክስቴ ወደማዕዱ የተዘረጋውን የዚች ሴትዮ እጅ በንዴት እየከላች “አንቺ ሆድሽን በኔ እርጎ ልታርሽ፣ እኔ ባንቺ ሃሜት አንጀቴን ልበጥስ፤ እ… ? ይሄማ በጭራሽ አይደረግም! በይ ውጪልኝ አንቺ ሾካካ፤ የማን ናት አጓምዳ በዝጊሃር!” ብላ ቀልቧን ገፍፋ አስወጣቻት፡፡ አዎ፣ እኛም እነተስፋዬን እንደዚህች ሴት ነው ቆሌያቸውን እዬገፈፍን በመካከላችን እንደወተት ዝምብ ጥልቅ እያሉ እንዳያውኩን መጠንቀቅ ያለብን፡፡