በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት 60 በመቶ ቡና አብቃይ አካባቢዎች ከአምራችነት ውጭ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተመራማሪዎች ይፋ አደረጉ

ብርሃኑ ፈቃደ
ሐረር ከነጭራሹ ቡና ማብቀል ልታቆም እንድምትችል ተንብየዋል
የእንግሊዝ ተመራማሪዎች ከኢትዮጵያውያን አቻዎቻቸው ጋር ሆነው ባጠኑት መሠረት፣ እስከ 60 በመቶ የሚገመተው የኢትዮጵያ ቡና አብቃይ አካባቢ፣ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ለቡና አብቃይነት ያለውን ተስማሚነት ሊያጣ እንደሚችል ይፋ ከማድረጋቸውም በላይ በቡና ላይ ሊመጣ የሚችለው አስከፊ የጣዕም ለውጥም አገሪቱን እንደሚጎዳት በጥናታቸው ይፋ አደረጉ፡፡
ኢትዮጵያውያን ምሁራን የተሳተፉበትና የእንግሊዙ ሮያል ቦታኒክ ጋርደንስ፣ ኪው የተባለው ተቋም ለንባብ ያበቁትና ‹‹ሬዚሊየንስ ፖቴንሺያል ኦፍ ዚ ኢትዮጵያን ኮፊ ሴክተር አንደር ክላይሜት ቼንጅ፤›› በሚል ርዕስ ይፋ የተደረገው ጥናት እንደሚያሳው፣ በየጊዜው እየጨመረ የመጣው የሙቀት መጠን ለቡና ማሳዎች ህልውና ሥጋት እየሆነ በመምጣቱ የአራት በመቶ ዲግሪ ሴልሺየስ የሙቀት ጭማሪ ታሳቢ በማድረግ ዋና ዋና የቡና አብቃይ የሆኑ የአገሪቱ አካባቢዎች የቡና አብቃይነታቸው በአስጊ ደረጃ እየቀነሰ እንደሚሔድ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
በዚህም መሠረት ከ39 እስከ 59 በመቶ ድረስ የሚገመቱ 16ቱ ዋና ዋና የኢትዮጵያ ቡና አምራች አካባቢዎች ቡና አብቃይነታቸው ሊቀንስ ብሎም ሊጠፋ እንደሚችል በጥናት አሳይተዋል፡፡ በመሆኑም ቡና አብቃይ በሆኑ ወይናደጋና ጫካ ገብ አካባቢዎች ላይ ተገቢው የሙቀት መጨመርን ሊከላከሉ የሚችሉ ዕርምጃዎች ካልተወሰዱ የቡና ምርት ወደፊት፣ ምናልባትም የተያዘው ክፍለ ዘመን ከመገባደዱ ቀድሞ የኢትዮጵያ ታላቅ የአራቢካ ቡና ዝርያ አምራችነት ሊያከትም እንደሚችል አጥኚዎቹ አስጠንቅቀዋል፡፡
ይሁንና በተገላቢጦሹ የአየር ንብረት ለውጥ በቡና ላይ እያሳደረ የሚገኘውን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመከላከልና የቡና ምርትን ለመጨመር፣ ከዚህ ቀደም ቡና አምራች ወዳልነበሩ ሥፍራዎች ቡናን ማስፋፋት እስከ አራት እጅ የሚገመቱ ለቡና ምርት ተስማሚ አካባቢዎች እንዲፈጠሩ ለማድረግ እንደሚያግዝ ተጠቁሟል፡፡ ይህ የቡና አብቃይ አካባቢዎችን ከመሠረቱ የሚቀይር አካሔድ እንደሆነ የሚገልፁት አጥኚዎቹ፣ ለቡና በአብዛኛው ተስማሚ የሚባሉት ከፍተኛ ሥፍራዎች ሲሆኑ በእነዚህ አካባቢዎች የሚታየው የሙቀት መጠንም ዝቅተኛ እንደሚሆን ስለሚታመን ለቡና ምርት ተስማሚ እንደሚሆኑ ይታመናል ብለዋል፡፡ ቡና በባህሪው ቀዝቃዛ አካባቢ የሚፈልግ በመሆኑ እንዲህ ያሉ አካባቢዎች ተመራጭ ስለሆኑ የቡና እርሻዎችም ወደእነዚህ አካባቢዎች እንዲስፋፉ ይመከራል ብለዋል፡፡
ምንም እንኳ በሙቀት መጨመር ምክንያት የቡና ምርትና የአምራች አካባቢዎች ምርታማነት በየጊዜው እየቀነሰ እንደመጣ ከገበሬዎች የተገኙ ግብረ መልሶች እንዲሁም በመስክ ወደ እርሻ ማሳያዎች በመሔድ የተደረጉ ጥናቶች ማረጋገጣቸውን ጥናቱን በጋራ የመሩት፣ በሮያል ቦታኒክ ካርደንስ ተመራማሪ የሆኑት አሮን ዳቪስ (ዶ/ር) አስታውቀዋል፡፡
ይሁንና የአየር ንብረት ለውጦች በቡና ላይ ያመጡት ለውጥ አዝጋሚ በሆነ ሒደት፣ በበርካታ አሥርታት ውስጥ የተከሰተ እንደሆነም ሚስተር ዳቪስ ያብራራሉ፡፡ ‹‹ይህ ጥናት ለበርካታ ዓመታት የተደረገ የምርምር ሥራ ውጤት ነው፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ በኢትዮጵያ ቡና ምርት ሒደት ላይ የሚያደርሰውን ተፅዕኖ በዝርዝር ለመረዳት ሞክረናል፡፡ እንዳረጋገጥነው ከሆነም እስካሁን ሲሠራበት በነበረው አኳኋን መቀጠል፣ በኢትዮጵያ የቡና ዘርፍ ላይ ለወደፊቱ ከባድ አደጋ እንደሚያስከትል ነው፡፡ በመሆኑም በመጪዎቹ ዓመታት ውስጥ ወቅታዊ፣ ተገቢና ሳይንስ ተኮር ውሳኔዎችን በማስተላለፍ የቡናውን ቀጣይነትና ለአየር ንብረት ለውጦች አይበገሬነት ማረጋገጥ የግድ ይላል፡፡››
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ዕፅዋት ሳይንቲስት የሆኑትና በጥናቱ ከተሳፉ ኢትዮጵያውያን አንዱ የሆኑት ፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሰው እንደገለጹት፣ ‹‹የአራቢካ ቡና በኢትዮጵያ ደጋማ አካባቢዎች የሚበቅልና ኢትዮጵያ ለዓለም ያበረከተችው ስጦታ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የአራቢካ ቡና የጂን ብዝኃነት ተፈጥሯዊ መገኛ እንደመሆኗ መጠን፣ በኢትዮጵያ የሚከሰተው ማንኛውም ነገር ሁሉ ወደፊት በዓለም የቡና አምራቾች ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል ብለዋል፡፡
በዚህ ደረጃ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖዎችን በቡና ዘርፍ ላይ ያሳዩት ምሁራኑ፣ በሙቀት አማጪ ጋዞች አማካይነት በየጊዜው እየጨመረ በመጣው የዓለም የሙቀት መጨመር ሳቢያ ወደፊት ቡና አምራች የሆኑ አካባቢዎች እየተመናመኑ እንደሚመጡ ሥጋታቸው ሲገልጹ፣ ዋቢ ካደረጓቸው መካከል ሐረር ተጠቅሳለች፡፡ በዓለም የንግድ ምልክትና ስያሜቸው ከተረጋገጠላቸው ሦስቱ ዋና ዋና የልዩ ጣዕም ቡናዎች ማለትም የይርጋጨፌና የሲዳማ ቡናዎች ተርታ የሚመደበው የሐረር ቡና፣ ከ1997 ዓ.ም. ጀምሮ በዚሁ መሠረት ለዓለም ገበያ ቀርቦ እየተሸጠ የሚገኝ ቡና ነው፡፡
ሐረር የኢትዮጵያ ምርጥ የቡና ዝርያ አብቃይ የመሆኗን ያህል፣ ተገቢው የመከላከል ዕርምጃ እንኳ ተወስዶ ቡና አብቃይነቱ በዚህ ክፍለ ዘመን ውስጥ ሊያካትም የሚችልበት ዕድል ሰፊ እንደሆነ አጥኚዎቹ ይተነብያሉ፡፡ ለዚህም አስተዋጽኦ የሚያደርገው ሐረር የምትገኝበት የከፍታ መጠን እንደሆነ ያብራሩት ምሁራኑ፣ ለቡና ተስማሚ የሚባለው የከፍታ መጠን ከባህር ወለል በላይ ከ1,200 እስከ 2,200 ሜትር ድረስ እንደሚገመት አስፍረዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ለቡና ተስማሚ የሚባለው ዓመታዊ የዝናብ መጠንም ከ1,300 ሚሊ ሊትር መሆን እንዳለበት ተጠቅሷል፡፡
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የሚታየው ዓመታዊ አማካይ የሙቀት መጠን ጭማሪ ከ50 ዓመታት በኋላ ማለትም እ.ኤ.አ. በ2060 ከ1.1 ወደ 3.1 ዲግሪ ሴልሺየስ እንደሚጨምር ይገመታል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2090 ደግሞ እስከ 5.1 ዲግሪ ሴልሺየስ ሊጨምር እንደሚችል ሣይንሳዊ ትንበያዎች እያመላከቱ ይገኛሉ፡፡ በዚህ አግባብ መሠረት በኢትዮጵያ የሚታየው የሙቀት መጠን ጭማሪ ለቡና ማሳያዎች የሥጋት ደውል እየተስተጋባበት ይገኛል፡፡ ዘ ጋርዲያንን ጨምሮ የአገር ውስጥና የውጭ መገናኛ ብዙኃን ያሰራጩትን ይህንን የጥናት ውጤት አጥኝዎቹ ይፋ ያደረጉት ‹‹ኔቸር ፕላንትስ›› በተባለው የሳይንስ ጆርናል አማካይነት ነው፡፡
ዓምና ለውጭ ገበያ ከቀረበው 180 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ቡና ከ800 ሚሊዮን ዶላር በመገኘቱ የአገሪቱን ሲሦ የውጭ ምንዛሪ ድርሻ የያዘው ቡና እንደሆነ አጥኚዎቹ ዘክረዋል፡፡ አራት ሚሊዮን ቡና አምራቾችን ጨምሮ 15 ሚሊዮን ሕዝብ የሚተዳደርበት የቡና እርሻ ላይ የተደቀነው አደጋ ወለል ብሎ የሚታይ በመሆኑ፣ የመንግሥትና የሚመለከታቸውን አትኩሮት እንደሚሻ ተጠቅሷል፡፡
ተጨማሪ ያንብቡ:  የፍረጃ ፖለቲካ አይጠቅመንም!  መልስ ለሁኔ አቢሲኒያ ( ግሬስ አባተ)
Share