ኤርትራን በአቋራጭ (ከኤፍሬም እሸቴ)

በሰሜን ምዕራቧ የአሜሪካ ከተማ በሲያትል ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን የሚርመሰመሱበት አንድ ሰፈር አለ። ንግድ ቤቶቹ፣ ጋራዦቹ፣ ሬስቶራንቶቹ እና እዚያ አካባቢ የሚቆሙት መኪናዎች አብዛኛው የኛ ሰዎች ንብረት ናቸው። ከመንገዱ አንዱ ኮርነር ላይ “ስታርባክስ” ቡናመጠጫ ደረቱን ሰጥቶ መንገዱን ቁልቁል ይመለከታል። ወደ ውስጥ ሲገባ አንዱ ጥግ “የኢትዮጵያውያን ጥግ” ነው፤ ሌላው ደግሞ “የኤርትራውያን ጥግ”።

 

አንድ ኢትዮጵያዊ ሲገባ እግሩ የሚመራው ወደራሱ አገር ጥግ ነው። መቀመጫ ባይኖርና በኤርትራው ጥግ በኩል ባዶ ቦታ ቢገኝ፣ ወደዚያ ለመሔድ አይሞክርም። ድንበር አይሻገርም። አንድ ኤርትራዊም እንዲሁ ወንበር ቢሞላበት ወደ ኢትዮጵያው ጥግ ለመሔድ አይሞክርም። ይህንን የሚነግረኝ ወዳጄ እየሳቀ ነው። ስታርባክሱ የባድመ ግንባር (ጦርነት የሌለበት፣ ነገር ግን ወታደሮቹ የተፋጠጡበት) አሊያም የአሰብ ቡሬ ግንባር መሰለኝ። ለመግባት አልፈለግኹም።

 

ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን በየሄዱበት ድንበርተኛ ሆነው መኖር ይፈልጋሉ ልበል? የተለያየን አገሮች ነን ብለው እንደሚለፍፉት ሳይሆን ተለያይተውና ተቆራርጠው ለመኖር አይፈልጉም።  ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ። የሚገርመው ግን ድንበርተኛ መሆን ሲፈልጉ ባድመ ግንባርንም አብረው እየገነቡ ነው። ጦራቸውን ሰድረው። የአበባ መስክ ያለበት ድንበር አይመቻቸውም – ሁለቱም። “አብረው ለመኖር የማይችሉ፣ ተለያይተው ለመኖርም የማይችሉ” የተባለው ለእነርሱ ሳይሆን አይቀርም። ይህንን የሚያፈርስ ገጠኤርትራን በአቋራጭ

መኝ ያገኘኹት ደግሞ ከሰሞኑ ወደ ሰሜን ካሊፎርኒያ ጠቅላይ ግዛት ሳን-ሖዜ ከተማ በሔድኩበት ወቅት ነውና ገጠመኙን በደስታ (ከልቤ ደስስስስ እያለኝ) ላጫውታችሁ።

 

በሰሜን አሜሪካ የተለያዩ ስብብሰቦች አሉ። ከሰፈር ልጅና ዕድር ጉባኤ እስከ ሃይማኖትና ፖለቲካ፣ ከብሔረሰብ ስብስብ እስከ ስፖርት ቡድኖች ድረስ። ከነዚህ ውስጥ በአሜሪካ የሚገኙ ወጣቶች ያቋቋሙትና ባለፈው ሳምንት 13ኛ ዓመቱን ያከበረው “የሰሜን አሜሪካ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባኤ” አንዱ ነው። ከመላው አገሪቱ የሚሰባሰቡ ወጣቶች የሚካፈሉበት የሦስት ቀናት ኮንፈረንስ አካሂዷል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ኦሮ-ትርያ - አስቻለው ከበደ አበበ _ሜትሮ ቫነኩቨር ካናዳ

 

ዝግጅቱን ያዘጋጁት በሳንሆዜ እና በአካባቢው የሚገኙ ወጣቶች እና እነርሱ የሚያገለግሉባቸው አብያተ ክርስቲያናት ናቸው። ኋላ ግን እንደሰማኹት ዝግጅቱን አብረው ያከናወኑት ከሳንሆዜ ወጣ ብለው ከሚገኙት ከተሞች (ለምሳሌ ከኦክላንድ) የመጡ ኤርትራውያን ወጣቶች ጭምር መሆናቸውን ተረዳኹ። ለካስ አለማወቄ ነው እንጂ እዚያው አብረውኝ ከሚውሉት መካከል አንዳንዶቹ ኤርትራውያን ነበሩ። አንዱ ወጣት መልከ መልካም ልጅ ራሱን አስተዋውቆ እስኪነግረኝ ድረስ አላወቅኹም ነበር።

 

አማርኛው ለክፉ አይሰጥም። በእጁ የያዘው መጽሐፍ የአማርኛ ነው።

“የት ለመድክ አማርኛ” አልኩት።

“እዚሁ ነው የለመድኩ”።

“ስንት ጊዜ ፈጀብህ?”

“አንድ ስድስቲ ምናምን ወር ይሆናል”።

 

ዲያቆን ነው። የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ይማር ነበረው ከአንድ ኢትዮጵያዊ መሪጌታ ኖሯል። እሳቸውን ሁል ጊዜ “ደህና ነሽ” ይላቸው እንደነበር “ነሽ ለሴት፣ ነህ ለወንድ” እያሉ እንደሚያርሙት እየሳቀ ነገረኝ። ገና ለጋ ወጣት። 19 ዓመቱ ነው። በዚህ ዓመት የመጀመሪያ ዓመት ትምህርቱን ተከታትሏል። ወደ ሁለተኛው ተሸጋግሯል። በዕድሜ እኩያ ከሚሆኑት ኢትዮጵያውያኑ ጋር ቶሎ ተላምዷል። ወጣት አይደል?

 

ሌላው ወጣት ወደ ሃያዎቹ አጋማሽ ነው። እዚሁ አሜሪካ ያደገ ሳይሆን የስደትን መከራ ቀምሶ የመጣ ስክን ያለ ልጅ ነው። እንደ ሌሎቹ ስደተኛ ወገኖቹ በሱዳንና የመን አልተጓዘም። በከባዱ የኢትዮ-ኤርትራ ድንበር አልፎ ኢትዮጵያ በሰላም ለመግባት የቻለ “ዕድለኛ ልጅ”። ቃሉን ተውሼ እንጂ “ዕድለኛ ልጅ” ያለው ራሱ ነው። አማርኛ ጥሩ አድርጎ ይናገራል። “መጻፍ ነው ችግሬ”  ብሎኛል። ታሪኩ ደግሞ ልብ ይነካል።

 

ወጣቱ ብሔራዊ ውትድርናውን ጨርሷል። ከአንዱ የጦር ግንባር ወደ ሌላው ጦር ግንባር ሲዟዟር አሳልፏል። ጦርነት ባይኖርም። “ዓይንህን ለአፍታ እንኳን ከምሽጉ እንድትነቅል አይፈቀድም” ብሎኛል። “አንድ ቦታ አያስቆዩንም። መቀያየር ነው። አንዴ ቡሬ፣ አንድ ባድመ፣ አንዴ ….”። ከዚያ ሲመርረው አገሩን ጥሎ ለመሰደድ ወሰነ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ነፍሴ ቸኩላለች !!

 

“አገሩ ውስጥ ወጣት የሚባል የለም’ኮ። አንድ ልጅ 16፤ 17፣ 18 ዓመት ከሆነ የሚያስበው መጥፋት ነው። አባት ከሆንክ ግን የት ትሔዳለህ። መማረር ብቻ። ሰዉ አይናገርም። ዝ…..ም ብቻ”። (‘ም’ን ላላ አድርጎ እየጠራት።)

 

ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ ሽሬ አካባቢ ወደሚገኝ የስደተኞች ካምፕ እንዲገባ ተደረገ። እርሱ ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ብዙ የአገሩ ሰዎች ጋር። ለአራት ዓመታት ኖረ።

 

“ምን ታደርግ ነበር?” ጠየቁት።

“ለእኔ ስኮላርሺፕ ማለት ነበር። አማርኛ ተማርኩ። መጻሕፍት ማንበብ ቻልኩ። የሚገርምህ ወደ አሜሪካ ስመጣ ሻንጣዬ 50ኪሎ ይመዝናል። 48ቱ ኪሎ መጽሐፍ ነው።”

“ሌሎቹስ ጓደኞችህ ምን ይሠሩ ነበር?”

“ሌሎቹም ዝም ብለው አልተቀመጡም። ቅኔ፣ ዜማ፣ መጻሕፍት ለመማር ወደ ጎጃም፣ ወደ ጎንደር፣ ወደ ሸዋ ሄዱ።”

“ኢትዮጵያ መጥተህ አታውቅም አይደል ከዚያ በፊት?”

“አላውቅም። ናጽነት ከመጣ በኋላ ደግሞ ችግር ሆነ። ኢትዮጵያ ማለት ሰይጣን ማለት ነበር የሚመስለኝ።”

ገታ አደረገና አንገቱን ነቀነቀ። እኔም “ለምን እንደዛ አሰብክ ምናምን” ወደሚል ጥያቄ ውስጥ መግባት አልፈለግኹም። ከሚናገረው ይልቅ በአካላዊ እንቅስቃሴው የሚያሳየው ብዙ ይናገር ነበር።

 

ወጋችንን ሳናጠናቅቅ የራት ሰዓት ደረሰና ወደ ማዕዱ ታደምን። ቀስ በቀስ ጠረጴዛችን ሞላች። ሁሉም ኤርትራውያን ናቸው። ወንዶችም ሴቶችም። ገና ወጣቶች። ሁሉም አማርኛ ይሰማሉ፣ ይናገራሉ። የተማሩት ግን በቅርብ ነው። አንዲቱ ልጅ ብቻ ገና አማርኛ አልተማረችም። አንዱ ኢትዮጵያዊ እየሳቀ “ጆሮሽን ቢቆርጡሽ አትሰሚም ማለት ነው?” አላት። ሌሎቹ የአገሯ ልጆች ሳቁ። ትርጉሙ ሲነገራት እሷም ሳቀች። የዛሬ ዓመት እሷም አማርኛ የምትችል ይመስለኛል።

 

“አማርኛ መማር ይሄን ያህል ቀላል ነው ማለት ነው?” አልኳቸው። አዎንታዊ መልስ አገኘኹ። በውስጤ “ለምን ትግርኛ አልተማርኩም ነበር? የመማር ዕድል ነበረኝ? ልማረው የምችለው ሌላ የአገራችን ቋንቋ  ነበር?” እያልኩ አሰላሰልኩ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የዩክሬን ወረራ (በአንድ ኢትዮጵያዊ ዕይታ) - አንዱ ዓለም ተፈራ 

 

“አስመራ፤ ቤት ሙዚቃ ውስጥ አማርኛ ዘፈን እኮ መክፈት አይቻልም” አለኝ ቅድም ታሪኩን ያጫወተኝ ልጅ። ለካስ ክልከላው ጠንከር ያለ ኖሯል። ግን አልሰራም። ወጣቶቹ የፖለቲካ ድንበርን በፍቅር እየተሻገሩት ነው። ለብዙ ዘመናት ሲዘራ የነበረው የጥላቻ ዘር በጥቂት ግንኙነቶች ሲመክን ማየት እጅግ ያስደስታል። ወጣቱ በትግራይ ስላጋጠመው መልካም ነገር ሁሉ ተናግሮ አይበቃውም።

 

“አዲስ አበባ የቆየኹት አንድ ሳምንት ብቻ ነው። አሜሪካ ልመጣ ስል።” . . . ትንሽ ቆየት ብሎ ቢያየው ተመኘኹ። አዲስ አበባ የብሔረሰቦች ሁሉ መናኸሪያ፣ የኢትዮጵያዊነት ናሙና ማሳያ። ክትፎውን ቢበላ፣ ጠጁን ቢጠጣ፣ ከወያላው ጋር ቢላከፍ፣ ቆጮውን ቢሞክር፣ ቡላውን፣ ጨጨብሳውን፣ ዶሮ ወጡን …። “አብሮ የበላን ቅዱስ ዮሐንስ አይሽረውም” ይሉ የለ አባቶቻችን?

 

የሄድንበት ኮንፍረንስ እሑድ ማታ ሲጠናቀቅ ከሲያትል በመጡ ወጣቶች እና በሳንሆዜ አካባቢ በሚገኙበት መካከል ትልቅ የጨረታ ፉክክር ተጀምሮ ነበር። የሳንሆዜዎቹ ቁጥራቸው አነስተኛ በመሆኑ ውድድሩ ሲከብዳቸው ኤርትራውያኑ ወጣቶች ያግዟቸው ጀመር። በዚያ ውስጥ የምመለከተው የተለያዩና ለጦርነት የሚፈላለጉ ድንበርተኛ አገሮች ሳይሆን ወጣትነትና ፍቅር ያስተሳሰራቸው ፍጡራንን ነበር። ጠቢቡ ሰሎሞን እንዳለው ሆነ፤ “የጐመን ወጥ በፍቅር መብላት የሰባ ፍሪዳን ጥል ባለበት ዘንድ ከመብላት ይሻላል።” (መጽሐፈ ምሳሌ 15፥17)

ይቆየን – ያቆየን

7 Comments

  1. ተባረክ እግዚአብሔር ይስጥህ ዲያቆን ኤፍሬም። ያኔ ስምዐ ጽድቅ ላይ ታወጣቸው የነበሩ ዓይነት ጽሑፍ ነው ዛሬ ያስነበብከን። እግዚአብሔር እጅህን ይባርከው! እንዲህ ዓይነት ጽሑፎች ሰውን ማነጽ ብቻ ሳይሆን አገር ያንጻሉ። የጻፍከው አጭር ጽሑፍ ጊዜን የሚሻገር ነው። ተስፋ አለን ብዙ ነገር ይለወጣል፣ አንድ የሆነውን ሕዝብ ለመለየት የተገነባው ግንብ እንደባቢሎን ይፈርሳል። እንደ አንድ አገር ባንሆን እንደወንድማማች መኖራችን አይቀርም። ሁሉም የእግዚአብሔር ሥራ ነው። ከእኛ ግን ብዙ ድርሻ ይጠበቃል – ለእኛ ባይሆን ለልጆቻችን ስንል።

  2. መልካም መጣጥፍ ። ባሁኑ ግዜ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ያለውን የጠብ ግድግዳ ለማፍረስ የሚጥሩ ኤርትራውያን ብቅ ብቅ እያሉ ነው ። ኢትዮጵያና ኤርትራ እንደግና ቢዋሃዱ ሁለቱም ህዝቦች ተጠቃሚ ይሆናሉ ። ኤርትራ ውስጥ ለነጻነት ተብሎ የተካሄደው ትግል ትክክል አልነበረም ። አሁንም ሁለቱ ህዝቦች እንደገና መዋሃድ አለባቸው ብለው በግንባር ቀደምትነት በዌብ ሳይቶች ላይ (አስማሪኖ.ኮም እና ባሕረነጋሽ.ኮም) ተከታታይ ጽሁፎች በማውጣት የሚታወቁ ሁለት ግለሰቦች አሉ ። አቶ ግርማይ የእብዮ እና አቶ ዮሴፍ ገብረ ሕይወት ይባላሉ ። ሁለቱም ኤርትራውያን ናቸው ። በዋነኛነት የኢትዮጵያውያን የሆኑ ዌብሳይቶች የእነዚህን ሰዎች ጽሁፎች ለአንባብያን ቢያቀርቡዋቸው መልካም ነው እላለሁ ። ሊበረታቱና ሊደገፉ የሚገባቸው ሰዎች ናቸውና ።

  3. እግዚያብሔር ይባርክህ ኤፍሬም።
    ያንተንም ጽሁፍ አንብቤ ሳልጠግብ አለቀብኝ። ምነው ጃል ብትጨምርበት። ለዛና የቃል አጠቃቅቀም ከውብ እይታ ጋር። አወ በዛሬው ጠዋት አንድ ከአስማሪኖ ድህረ ገጽ ያነበብሁት የእንግሊዘኛ ጥናታዊ ጽሁፍ ነበር። እሱ የሰጠኝን የመንፈስ ደስታ ሳልጨርስ ያንተንም አገኘሁ። እግዜር መልካሙን ያሰማን

  4. wonderful, it’s rare to see this kind of article on ZeHabesha. We should aspire to pass on such good things to the next generation instead of writing about separation of our two nations and things that make us clash. God bless you

  5. ለብስራት – ካልተሳሳትኩ በቅርቡ አዲስ የኢትዮ ታሪክ ፅፈሃል:: ስለሁለቱ ህዝብ ይህን ያህል ከተሰማህ በሀገር ውስጥ ስላሉ ጎሳዎችም ተመሳሳይ ልብ ሊኖርህ በተገባ::

    • ለ ሳም
      የስም ሞክሼ ነው ። እኔ አይደለሁም ። ያንን የተወናበደ ታሪክ የጻፈው የኢሐዴግ አባል ነው ። ስማችን ባጋጣሚ ተመሳሳይ ሆነ እንጂ ።

  6. ለብስራት_አንተ ካልሆንክ አስተያየቴን አንስቻለሁ:: የአንተ ሃሳብም ገንቢ ስለሆነ ወደ ተግባር ቢለውጡት እጅግ መልካም ነው::

Comments are closed.

Share