በሃብታሙ አያሌው (የአንድነት ፓርቲ ምክትል የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ)
እንደ መግቢያ
የፀረ ሽብረ አዋጅና የፓርቲዎች አቋም ሲል ወይም ኢ.ቲ.ቪ በላከው ደብዳቤ መስረት የሶስት ሰዓታት በእጅጉ የተጋጋለ ውይይት ከተካሔደ በኋላ ውይይቱ በዜና እንኳን ሳይዘገብ ከሳምንት በላይ ለሆነ ግዜ በመራዘሙ ተወያይ ፓርቲዎች በተለያየ መንገድ ቅሬታቸውን ሲገልጹ የግል ኘሬስና ማህበራዊ ገፆችም የፓርቲዎቹን ክርክር ኢቲቪ የውሀ ሽታ ሊያደርገው ይችላል ከሚለው መላምት ባሻገር በተለያየ መንገድ አገኘን ያሉትን መረጃም ሲለቅቁ ሰንብተዋል፡፡ አንዳንዶች ተቃዋሚዎች ውኃ የሚቋጥር ኃሣብ ማንሳት እንዳልቻሉ የውስጥ መረጃ አገኘን ሲሉ ሌሎችም በተከራካሪዎች ላይ አለ የሚሉትን የአቅም ማነስ ሳይቀር በመዘርዘር ኢህአዴግ ከውይይቱ ትርማማ ይሆናል ሲሉ ተነበዩ ከዚህ አስተሳሰብ በመጠኑ እንለያለን የሚሉም ውይይቱ ፋይዳ የለውም ኢቲቪ ቆራርጦ መቅኖ ያሳጣዋል ሲሉ ስጋታቸውን ሲገልፁ ስንብተዋል፡፡ ለፓለቲካ ነፅሮት ልዬ ተስጦ ያላቸወ በሳል ተንታኞች በበኩላቸው ኢህአዴግ ውይይት ማድረጉን ለምን መረጠ? ለምን ይህንን ወቅት መረጠ? ውይይቱ ለተቃዋማው ያለው ፋይዳ ምንድነው? አዋጁ እንዲሰረዝና በዚህም ምክንያት የታሰሩ እንዲፈቱ ከማድረግ ባሻገር ይህ አፋኝ ስርአት እንዲለወጥ የትግሉ አቅጣጫ ምን ያህል የተጠና ነው? የሚሉ በርካታ ጥያቄዎችን በማንሳትና መፍትሔዎችን በማመላከት የበኩላቸወን ጥረዋል፡፡ በጥቅሉ በፀረ ሽብር አዋጁ ዙሪያ የተደረገው ክርክር ለህዝብ እይታ ከመቅረቡ አስቀድሞ አጓጊ ሆኖ ሰንብቷል፡፡ የብዙዎቹ የሆነው የጋራ ስጋት የሚመነጨው ኢቲቪ በህዝብ እነት ያጣ ድርጅት ከመሆኑ ጋር በቀጥታ የሚያያዝ በመሆኑ ውይይተ በስርጭት ላይ ውሎ የብዙሀኑን ቀልብ የሳበ ቢሆንም ኢቲቪ ቆርጦባችኋል? የሚለው ጥያቄ ግን አሁንም አላቋረጠም እና ኢቲቪ የሽራረፋቸውን የኢትዮ ምህዳር ጋዜጣ በኩል ላቀብላችሁ ወደድኩ፡፡
ከመሸራረፍ ባህሪው ያልታረመ ቢሆንም ኢቴቪ ገለታ ይደረሰው ለማለት ግን አልሰስትም፡፡ ስለ ሽብር ያወያየን አሸብር ፊሽካ ይዞ ለመዳኘት ስንፈቅድለት ያንን ክብር ትቶ ኳስ አቀባይነት፣ ሲያኘው አጥቂና ተከላካይ እየሆነ ምላስ ቦታ በመርገጡ የተሰማኝን ቅሬታ መግለፁም እውነታ ነውና ነውር የለውም፡፡
አንድ ጋዜጣና ሚዛን አልባ ሆኖ ለሚደግፈው ካራገበ፣ የማይፈልገውን ሃሳብ ከጨቆነና አንዳንዴም ሀሳብን በፈለገው መንገድ ከቆረጠ ጋዜጣኛ ሊባል የሚችልበት ምንም ምክንያት የሌለ ሲሆን በመስኩ ሊገኝ የሚገባውን ጤናማ ውጤት ሁሉ የሚያበላሽ ይሆናል፡፡
ከዚህ እረገድ የኢትቪው አሸብር ጌትነት እራሱን መፈተሽ እና ለሙያው መታመንን መምረጥ ተቀዳሚ ተግባሩ ሊያደርግ የሚገባው ይመስለኛል ይህም በማሳሰብ ሳይሆን ይልቁንም በመምከር ነው፡፡
ሽርፍራፊዎች
ኢቲቪ ለአየር ያበቃው የውይይቱ ክፍል የተቆራረጠ ሀሳብ እና የማጠቃለያ ቅደም ተከተል መዛባት ቢኖረውም ገለታ ይድረስው ለማለት አልሳሳም ያልኩበት ምክንያት አንባቢ እንደሚገነዘበው ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ይህውም ቢሆን ከእባብ እንቁላል እርግብ እንደማግኘት የሚያስገርም በመሆኑ ነው፡፡
1. በአቶ ሸመልስ ከማል የቀረበ አስተያየት
ፍርድ ቤትን ፓሊስን እያጣጣላችሁ በማስረጃ ተረጋግጦ ቦንብ ሊያፈነው የመንግስትን ተቋማት ሊያወድሙ ሲሉ ተይዘው በማስረጃ የተረጋገቀባቸውን ሰዎች ይፈቱ እያላችሁ፣ እንደሰማዕት ከየአደባባዩ ከመጥራትም አልፋችሁ እዚህ ሳይቀር እየደገማችሁበት ባለችሁበት ሁኔታ እናንተ እንዴት ሰላማዊ ታጋይ ልትሆኑ ትችላላችሁ፡፡
የተቆረጠብኝ ምላሽ እነዚህን አሸባሪዎችን ሰማዕት ማስመሰልና ማበረታታት በሙሉ አሸባሪነት ነው፡፡
እናንተ ያስራችኋቸው እኛ ጀግና ሠላማዊ የነፃነት ታጋይ የምንላቸው እና አንዷለም አራጌ፣ በቀለ ገርባ፣ ሌሊሳ ኣልባና ናትናኤል መኮንን፣ አንዱአለም አያሌው አለም አቀፍ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ጋዜጠኛ ርዮት ዓለሙና የመሳሰሉትን የታሰሩት ነፃነት የሌላው የፓርቲ አገልጋይ ነው ይሞግቱት በነበረው ፍ/ቤት ነው፡፡ እንደፓርቲ ፍ/ቤት ነጻ እንዳልሆነ እናምናለን ይህም ከእኛ በላይ በመንግስት ተቋም በተደረገ ጥናት የተረጋገጠ ነው፡፡ በዚህ ታማኝና ነጻ ባልሆነ ፍ/ቤት አሸባሪ ስለታባሉ እኛ አሸባሪ አንላቸውም፡፡ ለእኛ ጀግኖች ናቸው፡፡
እነዚህ ጀግኖች ፈንጂ ሊያፈነዱ ነበር ተቋማት ሊያወድሙ ነበር የተባሉት በኢቲቪ አኬልዳማ ዶክመንተሪና በኢህአዲግ ባለስልጣናት እንጂ በፍ/ቤት የቀረበባቸው የክስ ቻርጅ እና መረጃ ይህ አይደለም ዛሬም እንደትናንቱ ህዝብ አታታሉ፡፡ በቃ የሚል ጽሁፍ ያለበት ወረቀት ፎቶ አነሳሽ፣ የወንድምህን ደህንነት፣ በስልክ አወራህ፣ ኢሚል ተጻጻፍክ ወዘተ በሚል ተልካሸ ምክንያት ከኢህአዴግ የተለየ አስተሳሰብ በመያዛቸው ምክንያት ብቻ የህሊና እስረኞች ናቸው፡፡
ይህንን ሀቅ መናገር አሸባሪነትን ማበረታታት ነው ብላችሁ ለማሸማቀቅ የምታደርጉት ሙከራ ተቀባይነት የለውም፡፡ ዛሬም ነገም በየአደባባዩ ስማቸውን እንዘክራንለ ነጻ እስኪወጡም እንታገላለን፡፡
2. አቶ ሸመልስ ከማል በሀገር ውስጥ ተከውኖአል ያሉትን የሽብር ተግባር ሲዘረዝሩ የበደኖን ጭፍጨፋ በማንሳን ኦነግ ጨፍጭፎአል ሲሉ ላቀረቡት መከራከሪያ
የተቆረጠው የእኔ ምላሽ
ብዙዎቹ የኢህአዴግ ባለሥልጣናት ደፍረው የማያነሱትን የበደኖ ጭፍጨፋ በማንሳትዎ አቶ ሸመልስን አመስግናለሁ፡፡ የበደኖን ጭፍጨፋ ለኦነግ በማቀበል ዘወር ማለት ግን አይቻልም፡፡ ኦነግ ከሀገር ሳይወጣ አሸባሪም ብላችሁ ሳትፈርጁት በሽግግር መንግስትነት ከህወሀት ኢህአዴግ ጋር ሀገር እየመሩ ባሉበት ወቅት የተፈፀመ ጭፍጨፋ መሆኑ ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ ሌላው ይህንን የበደኖ ጭፍጨፋ እርስዎ በመሰሎት መንገድ ሲናገሩት ወንጀል አይደለም ከፖርቲዎ ሞራል ያሰጥዎታል፡፡ ይህንን የበደኖ ጭፍጨፋ ዘርዝሮ በመጻፍ ለእውነት በመትጋቱ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሣለኝ ክስ ተመስርቶበት ፍ/ቤት እየተመላለሰ ነው፡፡ እንግዲህ ህግ አለ የምትሉት ይህንን ነው፡፡ ለዜጋ ሳይሆን ለካድሪ የሚፈርደውን የእናንተን ህግ የምንሟገተውም ይህ ብልሹ አሰራር እንዲቀየር የህግ የበላይነት እንዲከበርና የስርአት ለውጥ እንዲመጣ እንጂ እናንተ እንደምትፈርጁን ለሁከት አይደለም፡፡
3. አቶ ጌታቸው እረዳ በአንድ ወቅት አስታውሳለሁ ሀብታሙ የማደራጃ አዋጅን ከእኔ በተሻለ ብቃት ይተነትን ነበር አሁን መንገዳችን ለየቅል ቢሆንም ሲሉ ለሰነዘሩት የትናንት አብረን ነበርን ሾርኒ …
የተቆረጠው የእኔ ምላሽ
የኢህአዴግ ባለስልጣናት ለተቃዋሚ እውቅና መስጠትና ይበልጠኛል ማለት ሞታቸው ነው፡፡ አቶ ጌታቸው በዚህ መድረክ ከእኔ በተሻለ የመተንተን ብቃት አለህ ብለው ምስክርነት በመስጠትዎ አከብራለሁ አመሰግናለሁ፡፡
ነገር ግን “በእኔ እምነት ከስህተቱ የማይማረው ፈንጂ አምካኝ ብቻ ነው” ሲያመክን ከተሳሳተ ይሞታል የመማሪያ እድል የለውም እርስዎና የኢህአዴግ ባለስልጣናት እንደእኔ ከስህተት ለመማር አልረፈደባችሁም፡፡ አሰላለፋችሁም እንደእኔ ከህዝብ ጋር በማድረግ እንድትማሩ እመክራለሁ፡፡
4. አቶ ሸመልስ ከማል መንግስት ደጋግሞ ቢያሳስባችሁም ከስህተታችሁ ለመማር አልፈለጋችሁም እናንተ ህገ ወጦች ናችሁ፡፡ በማለት ቁጣ ቀላቅለው ለሰነዘሩት ዛቻ
የተቆረጠው የእኔ ምላሽ
አቶ ሸመልስ ሳይቀር መንግስትን የተለየ አካል አድርገው አሳስበናችኋል፣ አደጋ አለው፣ታግሰናችኋል በማለት ለማስፈራራት መሞከር እና ዛቻ መምረጥዎ ያሳዝናል በእርግጠኛነት የምነግርዎ እናንተና እኛ በህግ ፊት እኩል ነን እናንተ ከእኛ የምትለዩት የመንግስት ስልጣን በመያዛችሁ እኛ ደግሞ ነገ መንግስት ለመሆን የምንወዳደር ፓርቲ ነን ሁለታችንም ሊዳኘን የሚገባው ሰርአትና ህግ እንጂ እናንተን አሳሳቢና አስፈራሪ ያደረጋችሁ ማነው? ትልቁ ችግራችሁ ከእዚህ ይመነጫል የተቃወማችሁን ሁሉ ለማጥፋት አሸባሪ የምትለውን ታርጋ መጠቀም የመረጣችሁትም ከዚህ ባህርይ በመነሳት በመሆኑ ሊታረም ይገባል፡፡
ጥቅል ቆረጣ የተካሄደበት
ውይይቱ የተላለፈው በሶስት ክፍል ሲሆን ክፍል አንድ በኢህአዴግ ተጀመረ የመጨረሻ ሰፊ ሀተታ በኢህአዴግ ከቀረበ በኋላ የተቃዎሚዎች ምላሽ ሳይቀጥል ክፍል ሁለት ይቀጥላላ ተባለና ክፍል ሁለትን በአዲስ ጥያቄ በመጀመር የተቃዎሚውን መልስ ሙሉ በሙሉ አስቀረ ክፍል ሁለት ሲጠናቀቅ እንዲሁ በተመሳሳይ ከኢህአዴግ ማብራሪያ በኋላ ያለው የተቃዎሚዎች ማብራሪያ ተቆርጦ በአዲስ ጥያቄ ተጀመረ፡፡ የክፍል ሶስት ማጠቃለያም በኢህአዴግ ማብራሪያ እንዲጠናቀቅ ተደረገ፡፡
የማጠቃለያው ሀሳብ
ውይይቱ ሲጠቃለል የመጨረሻው ተናጋሪ አቶ ሸመልስ ከማል ሆነው ማብራሪያ ሲሰጡ አንቀጽ በአንቀጽ መረጃ ማቅረብ አልቻላችሁም በማለት መከራከሪያ ሀሳብ እንደአጠረንና አንቀጽ ለመጥቀስ እንደተቸገርን በማስመሰል መደምደሚያ አድርገው ሊያጠናቅቁ ሲል የተቃውሞ ሀሳቤን ሰነዘርኩ፡፡ አንቀጽ በአንቀጽ እንወያይ ብለን ስናነሳ አወያዩ የፓለቲካ አቋም ላይ ተወያይተን በአንቀጹ በኋላ እንመለስበታለን በማለት ካቆየ በኋላ ሰአት አልቋል አለን፡፡ ባልተወያየንበት ጉዳይ መረጃ አላቀረባችሁም ብለው መደምደሚያ መስጠቱ ስህተት ነው፡፡ አቶ ጌታቸው ሀብታሙ ትክክል ነው ይህ ያልተወያየንበት በመሆኑ ሁለተኛ ቀጠሮ ተይዞ ውይይት ይጠራ የሚለው ሀሳብ ማጠቃለያ ሆነ፡፡ ለኢቲቪ ሲተላለፍ ግን ይህ ማጠቃለያ ውይይት ተቆርጦ የአቶ ሸመልስ ሀሳብ ወደ መሀል ተወስዶ መሀል ላይ ለማደናገሪያ ገባና ከመሀል የአቶ ጌታቸው ንግግር ተቆርጦ ማጠቃለያ እንዲሆን በማድረግ ኢቲቪ በኤዲንግ ጥበቡ አጠቃለለው፡፡
የግል አስተያየት
የተቆረጡ ሀሳቦች በሚል የማስታውሳቸውን ስጽፍ የሌሎች ተከራካሪዎች ሀሳብ አልተቆረጠም በማለት ሳይሆን በራሳቸው አገላለጽ እንደሚጽፋት በማሰብ ንግግራቸውን እንዳላበላሽ በመስጋት የተውኩት ነው፡፡ የተቆረጡ ሀሳቦችን መጻፍ ያስፈለገውም በርካታ ህዝብ የተቆረጡ ሀሳቦችን ለማወቅ ከአቀረበው ጥያቄ በመነሳት እና ኢቲቪ በጐውን እንዲቀጥልበት እኩይ ተግባሩንም እንዲተው ለመቃወምና ለማስጠንቀቅ እንዲረዳ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር
Part 2
Part 2