የ“ዓለም አቀፍ አማራ ተራድኦ ድርጅት” ምሥረታ አስፈላጊነትን በሚመለከት – ለውይይት የቀረበ

November 23, 2016
18 mins read

(ዮፍታሔ)

ባለፈው 40 ዓመት፣ ይልቁንም ባለፉት 26 ዓመታት አማራውን ያጋጠሙትና አሁንም እንደቀጠሉ ያሉት ችግሮች ከፍ ያሉና ዘርፈ ብዙ ናቸው። ከፍ ያለ ችግር ከፍ ያለ መፍትሔ ያስፈልገዋል።

አማራው በአገር ቤት የደረሰበትና እየደረሰበት ያለው ዘርፈ ብዙ ጥቃት፣ ችግርና መከራ የታወቀ፣ እየታወቀ ያለ፤ በአብዛኛው የተመዘገበና እየተመዘገበም ያለ ነው። ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል።

ይህን ዘርፈ ብዙ ጥቃትና ችግር በማያዳግም መንገድ ለመፍታት የፖለቲካና የሲቪክ ድርጅቶችን ማቋቋም እየተከናወነ ቢሆንም እነዚህ ድርጅቶች የሚንቀሳቀሱበትንና ሥራቸውን በአጥጋቢ ሁኔታ ለማከናወን የሚያስችላቸውን የገንዘብ አቅም ለማግኘት በየራሳቸው ብቻ የሚያደርጉት ጥረት በቂ አይሆንም። የሕዝቡ ይልቁንም በውጭ የሚኖረው አማራ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል። ከድርጅቶቹ ቁጥር መብዛት ጋር ለረጂዎቻቸው አንድ ወጥ መንገድ ማመቻቸትም ተገቢ ነው። ይህ አንዱ ነው።

አማራው ከአገሩ ውጭ እየደረሰበት ያለውም ቀላል አይደለም። በ Human trafficking ከአገራቸው እየወጡ ሴቶች ከባርነት በሚስተካከል ግርድና ወንዶች በእረኝነት ኑሮአቸውን የሚገፉና አካላቸው በቀዶ ጥገና እየወጣ የሚገደሉም አብዛኞቹ የአማራው ልጆች መሆናቸው የአደባባይ ምስጢር ነው። የመረረውን ሕይወትና የሕወሐትን አፈና በመሸሽ በባሕር ሲጓዙ ውኃ ከሚበላቸው መካከል በርካታ የአማራ ተወላጆችም ይገኙበታል። በየዓመቱ በማደጎ ከኢትዮጵያ ከሚወጡ በብዙ ሺ ሕፃናት መካከል የአማራ ሕፃናት መኖራቸውን ከምንኖርባቸው የውጭ ከተሞችና ከማኅበራዊ ሚዲያ ፍንጮች ለመገንዘብ ይቻላል። ኢትዮጵያዊ ሕፃናት በማደጎ የሚወጡት በአብዛኛው ወደአሜሪካ፣ አውሮፓና አውስትራሊያ ቢሆንም በነዚህ አገራት እስከሞት የሚያደርስ ብዙ በደል እንደሚፈጸምባቸው በየጊዜው በዓለም አቀፍ መገናኛ ከሚወጡ ዘገባዎች መረዳት ይቻላል። በነዚህ የውጭ አገራት በአንጻራዊ ሰላም የሚኖሩት ሕፃናት ደግሞ ከአገራቸውና ከማንነታቸው ተነቅለው በባዕድ አገርና የነርሱ ባልሆነ ባሕል፣ ማንነትና አኗኗር ውስጥ ያልፋሉ። ይህ ለአሁኑና ለቀጣዩ የአማራ ትውልድና ሕዝብ ጉዳት አለው። በሳውዲ አረቢያ፣ በሊባኖስ፣ በሊቢያና ባልተረጋጋው መካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ ከሞቱትና ከሚሞቱት ኢትዮጵያውያን መካከል አማሮች መኖራቸው የሚታወቅ ነው። እነዚህ ከችግሮች በጣም ጥቂቶች ናቸው። ተቆርቋሪ መንግሥትም ሆነ ማንም ረዳት በሌለበት እነዚህንና መሰል ችግሮች ከሥራቸው ማድረቅና ዘለቄታዊ መፍትሔ መስጠት በአማራው ትከሻ ላይ የወደቀ ነው። ይልቁንም በውጭ አገር ከምንኖር አማሮች ብዙ ይጠበቃል። ሁለተኛው ይህ ነው።

በውጭ የምንኖር አማሮች ቁጥር በሰሜን አሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በአውስትራሊያ፣ በእስያ፣ በአረብ አገራትና በእስራኤል በትንሹ ከ 1 – 2 ሚሊዮን ሊሆን እንደሚችል ከወጡ አንዳንድ ጠቋሚ መረጃዎች ግምት መውሰድ ይቻላል።

በዓለማችን 2 ሚሊዮን አካባቢና ከዚያ በታች የሕዝብ ቁጥር የሚኖርባቸው አገሮች እጅግ በርካታ ናቸው። ባህሬን፣ ኳታር፣ ስሎቬንያ፣ ላቲቪያ፣ ጊኒ ቢሳዎ፣ ቦትስዋና፣ ጋቦን፣ ስዋዚላንድ፣ ትሪኒዳድና ቶቤጎ፣ ሞሪሽየስ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ጋቦን ጥቂቶቹ ናቸው።

ስለዚህ በውጭ የምንኖር አማሮች ቁጥራችን የአንድ ትንሽ አገር ሕዝብ ያህል ሆኗል ማለት ነው።

ይህ ከሆነ እንኳን ይህን ያህል ችግር እያለብን ባይኖርብን እንኳን በውጭ የምንኖር አማሮች እንደ አንድ ሕዝብ የሚያገለግሉን ተቋማት ያስፈልጉናል ማለት ነው። ይህ ደግሞ ሦስተኛው ነው።

ከነዚህ ተቋማት መካከል “ዓለም አቀፍ የአማራ ተራድዖ ድርጅትን ማቋቋም” አንዱ መንገድ ሊሆን ይችላል በሚል በመላው ዓለም የሚገኙ አማራ ኢትዮጵያውያን ሀሳብ እንዲሰጡበትና እንዲወያዩበት ይህ ሀሳብ ቀርቧል።

ይህን የመሰሉ በአንድ ሕዝብ ላይ የሚያተኩሩ ነገር ግን አደረጃጀታቸው ዓለም አቀፋዊ የሆኑ ድርጅቶች በየጊዜው ነበሩ አሁንም ይኖራሉ።

እሥራኤል እ. ኤ. አ በ 1948 እንደአገር ከመመሥረቱ አስቀድሞ በተለያዩ አገሮች ተበትነው ይኖሩ የነበሩትን እስራኤላውያን የሚመዘግብ፣ የሚያሰባስብና ከራሳቸው ከእሥስራኤላውያንና ከበጎ አድራጊዎች ገንዘብ በመሰብሰብ እስራኤላውያንን በያሉበት ይረዳና በኋላም ወደአገራቸው እንዲመለሱና እሥራኤልን እንዲመሠርቱ ያደረገ ድርጅት ነበራቸው። ይህ ድርጅት በመጀመሪያ Jews Agency በመባል ይታወቅ ነበር። በኋላ ደግሞ World Zionist Organization በሚል ስም እንዲጠራ ሆኗል።

ዓለም አቀፍ የአማራ ተራድኦ ድርጅት ቋሚ ድርጅት ነው። የዓለም አቀፍ የአማራ ተራድኦ ድርጅት በአገር ቤትም ሆነ በውጭ አገር አማራውና ሌሎችም ኢትዮጵያውያን የሚደርስባቸውን ጥቃት፣ በደልና፣ ችግር በማያዳግም ሁኔታ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ ይሠራል። ለአማራው እንደአንድ ጃንጥላ ድርጅት (Umbrella Organization) ሆኖ ሌሎችንም የአማራውን ድርጅቶችና ተቋማት በጠቅላላ በውጭ አገርና በአገር ቤት በገንዘብና በቁሳቁስ የሚደግፍ ይሆናል። ከዚሁ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ሌሎችን አስፈላጊ ድርጅቶች ያቋቁማል፣ እንዲቋቋሙ ሁኔታዎችን ያመቻቻል፤ የተቋቋሙትንና በመቋቋም ላይ ያሉትን ይደግፋል።

ይህ ድርጅት በውጭ ለሚኖሩ አማሮች እንደወኪልና ተሟጋች ሆኖ የሚያገለግል፣ እንደ ቀይ መስቀልና UNHCR ለአማሮችና ለኢትዮጵያውያን ፈጥኖ ደራሽ የሆነ፣ እንደኢንሹራንስና እንደዓለም ዓቀፍ አበዳሪ ባንኮች ለበጎ ሥራና ለአማራው የፖለቲካ፣ የሲቪክ፣ (መረጃ፣ ሚዲያ፣ ባሕል፣ ታሪክ፣ ቋንቋ፣ ትምህርት፣ ጤና፣ ዲፕሎማሲ ወዘተ) ተቋማትና ድርጅቶች ረዳትና ዋስትና የሚሆን፣ ለችግሮች መፍትሔ መስጠት የሚችልና የችግሮችን ምንጭ እስከማድረቅ ድረስ የሚሠራ ድርጅት መሆን ይኖርበታል።

Steering committee (tink tank) መጀመሪያ ከተቋቋመ በኋላ ያ ኮሚቴ የድርጅቱን ዓላማዎች፣ ራዕይ፣ ዝርዝር ተግባራት ረቂቅ ያዘጋጃል፣ ድርጅቱ የሚመሠረትበትን ቦታ ይወስናል፣ የሚመለከታቸውን የአማራውና ኢትዮጵያውያን፣ ተቋማት፣ የፖለቲካና የሲቪክ ድርጅቶች ይጋብዛል። በዚያ ስብሰባ ላይ ድርጅቱ ይመሠረታል። እንደሲያትሉ የአማራ ግብረኃይል ዓይነት ማኅበር ይህንን ኃላፊነት ሊወስድ ይችላል።

አደረጃጀት

ዓለም አቀፍ የአማራ ተራድኦ ድርጅት በመላው ዓለም ለሚገኙ አማሮችና ኢትዮጵያውያን የሚሠራ በመሆኑ አደረጃጀቱ ዓለም አቀፋዊ ይሆናል።

ማዕከላዊ የድርጅቱ አስተዳደር (የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ) በአንድ በተመረጠ የውጭ ከተማ ይቋቋማል። ድርጅቱ ቅልብጭ ያለ የቢሮክራሲ ውስብስብነት የሌለው መሆን ይኖርበታል። ይህ እንዲሆን በየአገሩ ኢትዮጵያውያን በጠቅላላ በሚገኙባቸው ከተሞች ንዑስ ኮሚቴዎች (chapters) ይኖሩታል። እነዚህ ኮሚቴዎች ከዋናው ሥራ አስፈጻሚ ጋር በመነጋገር በአካባቢያቸው ስላለው እና መከናዎን ስላለበት ሁሉ የተሰሚነትና የወሳኝነት ቦታ ይኖራቸዋል። በአካባቢያቸው ስለደረሰ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ሁሉ ለድርጅቱ ዋና የመረጃ ምንጭ በመሆንም ያገለግላሉ።

ምንም እንኳን በግንባር ቀደምነት በአማራው ላይ የሚሠራ ድርጅት ቢሆንም እንደሌሎችም ዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅቶች በሥራው እውቅና እንዲያገኝ በአንድ አገር መመዝገብ ካለበት የድርጅቱ ዋና ጽ/ቤት በሚገኝበት አገር ያለዚያም በዓለም አቀፍ ደረጃ ይህን የሚመዘግብና እንደተባበሩት መንግሥታት እውቅና የሚሰጥ (World Red cross, UNICEF, UNHCR, etc) ድርጅት ካለ በዓለም አቀፍ ደረጃ መመዝገብ ይችላል። ይህን ማጣራትና ለዚህ መንገድ ማግኘት ለዚህ ድርጅት ቀዳሚ ከሆኑት ዓላማዎች አንዱ ነው።

ይህ ድርጅት በየመስኩ የተለያዬ ሥራ ከሚሠሩ እንደ ቀይ መስቀል፣ UNHCR, UNESCO, USAID, World Vision, Medicine san frontier ካሉ፣ የማደጎ ልጆችን ከሚመለምሉና አሳዳጊ ከሚያገናኙ ድርጅቶች፣ ከዓለም አቀፍ በጎ አድራጎት ድርጅቶችና በየትኛውም መስክ ከተሠማሩ ሕጋዊ ድርጅቶች ጋር በመቀራረብ ይሠራል።

የገንዘብ ምንጭ እና አያያዝ

የድርጅቱ ዋና የገቢ ምንጭ በመላው ዓለም ከሚገኙ አማሮችና ደጋፊዎቻቸው ይሆናል። ይህ ድርጅት በውጭ ለሚገኙ አማሮች በሙሉ እንደ ወኪል፣ እንደድንገተኛ ደራሽ፣ እንደእድር፣ እንደኢንሹራንስ ዋስትና እና እንደ ባንክ ሆኖ ስለሚያገለግላቸው ሁሉም አማራ ሊመዘገብና አባል ሊሆን ይገባል።

ድርጅቱ ድጋፍ በማድረግና ችግሮችን በመፍታት ላይ ትኩረት የሚያደርግ ከመሆኑ በተጨማሪ በደሎችና ችግሮች እንዳይደርሱ የበደሎችንና የችግሮችን ምንጭ በማድረቅ ላይ ስለሚሠራ በአገር ቤት ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ አማራውን ከሚረዱ መንግሥታትና ድርጅቶች ጋራ በመነጋገርና እውቅናውንም ለማጎልበት ከነርሱ ጋር በመቀራረብ ይሠራል። ስለዚህ ኢትዮጵያን በድህነት መቅረፍ፣ በረኃብ፣ በመልሶ ማቋቋም፣ በጤና፣ በሥራ ፈጠራ፣ በመሠረተ ልማት፣ በእርሻ፣ በትምህርት፣ በባህል ወዘተ የሚረዱ መንግሥታትና ድርጅቶች የዓለም አቀፍ የአማራው ተራድዖ ድርጅት ተጨማሪ የገንዘብ ምንጭ ይሆናሉ።

ከዚህ ቀደም ከተገኘው ልምድ በውጭ የሚኖረውን አማራም ሆነ ሌላውን ኢትዮጵያዊ በአንድ ጊዜ ከፍተኛ ገንዘብ (lump sum) እንዲያዋጣ ከማድረግ ይልቅ ትናንሽ ወርኃዊ መዋጮዎች የተሻለ ውጤት ያስገኛሉ።

መዋጮው በአረብ አገራትና በአፍሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንንም የሚያሳትፍ እንዲሆንና በሌሎችም አገሮች የሚገኘው ኢትዮጵያዊ ደስ እያለው ከወር ወር መዋጮውን መክፈል እንዲችል እጅግ ዝቅተኛ መሆን ይኖርበታል።

እንደማንኛቸውም መሰል ድርጅቶች ገንዘቡ የሚጠራቀምበት (Maturity period) ይኖረዋል።

የገንዘቡ አስተዳዳር ሙሉ በሙሉ ጉዳዩ በቀጥታ በሚመለከታቸው የገንዘብ አስተዳደር ድርጅቶች (Financial Institutions) ይከናወናል። ይህ ለገንዘቡ ሙያዊ አያያዝ ከሚጠቅመው በተጨማሪ በአባላት አማሮች ዘንድ ድርጅቱ ታማኝነት እንዲኖረው ከፍ ያለ አስተዋጾኦ አለው። ይህ ደግሞ ዞሮ ድርጅቱ ዘላቂ እንዲሆን ያደርገዋል።

ይህ የገንዘብ አስተዳደር ድርጅት ከዓለም አቀፍ የአማራው ተራድዖ ድርጅት ሥራ አስፈጻሚ ጋራ በመመካከር በመላው ዓለም ተበትነው ከሚገኙ አባላቱ ሳይቋረጥ ገንዘቡ የሚሰበሰብበትን አሠራር ይዘረጋል፣ ገንዘቡን በሥራ ላይ በማዋል የሚያድግበትን መንገድ ይነድፋል፣ ለእያንዳንዱ አባል እንደባንክ አካውንት በመስጠት አባላት አካውንታቸው ውስጥ በሚገቡ ጊዜ ስለሚያዋጡት ገንዘብ ኢንፎርሜሽን እንዲያገኙ ያመቻቻል፣ በየስድስት ወሩ ደግሞ አጠቃላይ ሪፓርት በቀጥታ ለአባላትና ለድርጅቱ ሥራ አስፈጻሚ ያቀርባል።

ይህ መነሻ ሀሳብ ሲሆን ውይይት ከተደረገበት በኋላ የሚለወጥ፣ የሚሻሻልና የሚዳብር ስለሚሆን መላው የአማራ ማኅበረሰብ አባላት ሀሳብ እንድትሰጡበት ትለመናላችሁ።

Previous Story

የዚህን ጨቋኝ ስረአት እድሜ እንድናሳጥር መረባረብ ይጠበቅብናል (ልኡል አለሜ)

Next Story

I went to art school

Latest from Blog

አትዮጵያ ያን ዕለት

ግም ሞት 20’ 1983 .ዓ.ም. ለህወሀት /ኢህአዴግ ልደት ለኢትዮጵያ እና ለብዙዉ ኢትዮጵያዉያን የዉድቀት ፣ጥልመት እና ሞት ዕለት መሆኑን ያ ለሁለት አሰርተ ዓመታት ከፍተኛ ዕልቂት እና ደም መፋሰስ የነበረበት ጦርነት አዲስ አበባ በደም

አቢይ አህመድ ታላቁን አሜሪካንና የተቀሩትን የምዕራብ ካፒታሊስት አገሮችን ማታለል ይችላል ወይ? የአሜሪካ “ብሄራዊ ጥቅምስ ኢትዮጵያ ውስጥ“ እንዴት ይጠበቃል? የአሜሪካ እሴቶችስ(Values) ምንድን ናቸው?

ለመሳይ መኮንና ለተጋባዡ የቀድሞ “ከፍተኛ  ኢትዮጵያዊ ዲፕሎማት” በአሁኑ ወቅት በአሜሪካን የስቴት ዴፓርትሜንት ውስጥ ተቀጥሮ ለሚስራው ኢትዮጵያዊ ሰው የተሰጠ ምላሽ!   ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር) ግንቦት 19፣ 2016(ግንቦት 27፣ 2024) መሳይ መኮንን በአ.አ በ17.05.2024 ዓ.ም አንድ እሱ  የቀድሞው “ከፍተኛ የኢትዮጵያ

ጎንደር ሞርታሩን እስከ ጄነራሉ ተማረከ | ይልማ ምስጢሩን አወጣ “ብርሃኑ ከሸ-ኔ ጋር በድብቅ ይሰራል” | ብይ ክዶናል ለፋኖ እጅ ለመስጠት ዝግጁ ነን

ይልማ ምስጢሩን አወጣ “ብርሃኑ ከሸ-ኔ ጋር በድብቅ ይሰራል” | “ፋኖ ከተማውን ቢቆ-ጣ-ጠር ይሻላል” ከንቲባው |“አብይ ክዶናል ለፋኖ እጅ ለመስጠት ዝግጁ ነን” ኮ/ሉ |“በድ-ሮን እንመ-ታችኋለን እጅ እንዳትሰጡ” ጄ/ሉ
Go toTop