እሁድ፣ መስከረም ፩ ቀን፣ ፳፻፱ ዓመተ ምህረት
የያዝነው የሁለት ሺ ዘጠኝ ዓመተ ምህረት አዲስ ዓመት፤ በኢትዮጵያ ሕዝብ የተጀመረው የየካቲት ሺ ዘጠኝ መቶ ስድሳ ስድስቱ መነሳሳት፤ ከግቡ የሚደርስበት ዓመት ይሆን ዘንድ፤ ምኞቴን እገልጻለሁ። ምኞት ብቻውን የትም አያደርስምና፤ መሠረታዊ መግባባት በሕዝቡ ወገን ታጋዮች መካከል ይኖር ዘንድ፤ የሃሳብ አንድነት ኖሮን፤ በድርድር ዙሪያ በሚሽከረከረው ሃሳብ ላይ፤ ሊኖረን የሚገባንን ግንዛቤና ቅድመ ተግባራችን ምን መሆነ እንዳለበት ማስመር እወዳለሁ።
በመጀመሪያ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከማን ጋር ነው የሚደራደረው? መንግሥት የማን ሆነና ነው፤ ሕዝቡ ልደራደርህ የሚለው? ከዚህ መሠረታዊ ሀቅ ተነስተን፤ ድርድሩ በማንና በማን መካከል እንደሚሆን ማረጋገጥ አለብን። በርግጥ አሁን የሕዝብ የሆነ መንግሥት ቀርቶ፤ መንግሥትና ሕዝብ ያላቸውን ዝምድና የማያውቅ አካል በሥልጣን ላይ ያለ ስለሆነ፤ ሕዝቡ በርግጥ በመንግሥቱ ስላልተወከለ፤ ሕዝብና መንግሥት የሚባሉ አካሎችን ለይቶ ማስቀመጡ ይረዳል። በርግጥ የኢትዮጵያ ሕዝብ ባንድነት ቁጭ ብሎ የሚደራደር አካል አይደለም፤ ተወክሎ የሚደራደርለትም የለውም። እናም እንግዲህ፤ ተደራዳሪ የምንላቸው፤ በአካል ተቀምጠው የሚደራደሩ ክፍሎች በሌሉበት እውነታ፤ ድርድር የለም። ሆኖም ግን፤ በኢትዮጵያ ባለው የፖለቲካ እውነታ፤ በሕዝቡ ላይ ከፍተኛ አረመኔ ተግባር እያደረሰ ያለ አካል አለ። በሌላው በኩል ደግሞ፤ ይህንን አረመኔ ተግባር በመከላከል ላይ የተጠመደ ክፍል አለ። ታዲያ እኒህን ክፍሎች ለማስማማት ይመስለኛል የድርድር ሃሳቡ የሚናፈሰው። እስኪ ጠለቅ አድርገን እንመርምረው።
በባህላችን፤ መደራደርና ሽምግልና ሁለት የተለያዩ ክፍሎች ናቸው። የመጀመሪያው በእኩያዎች መካከል፤ የሠጦ መቀበል የእኩልነት ስምምነት ነው። ሁለተኛው ደግሞ በበዳይና በተበዳይ መከካከል ያገሬ ሽማግሌዎች ገብተው ዕርቅ እንዲኖርና ሰላም እንዲከተል፤ በኅብረተሰቡ ስም የሚደረግ ክንውን ነው። በሽምግልናው መስክ፣ ሽማግሌዎች በዳይና ተበዳይን ባንድ አስቀምጠው፤ አንተም ተው! አንቺም ተይ! በማለት ይቅር ሊያባብሉና ሊያስታርቁ ሲነሱ፤ በደሉን ተረድተው፤ በዳይ ማን፣ ተበዳይ ማን እንደሆነ ጠንቅቀው አውቀው ነው። በተጨማሪ ደግሞ፤ ቢታረቁ ሁለቱም የሚያገኙት ጥቅም ከወዲሁ ስለገፋፋቸው ነው ለዕርቁ የሚቀርቡት። ታዲያ በዚህ ግንዛቤ፤ ጥፋተኛው ጥፋቱን ማመኑ፤ ተበዳይ ደግሞ ጥፋቱን ይቅር ብሎ ካሣውን ለመቀበል ፈቃደኝነት አላቸው ማለት ነው። ይህ ፈቃደኝነት የሚመነጨው፤ “አሁን ካለንበት የጠብ ሁኔታ ይልቅ፤ ጠባችንን አጥፍተን አብረን ብንኖር፤ የበለጠ ተጠቃሚዎች እንሆናለን!” የምል ግንዛቤ በመካከላቸው ስላለ ነው። ከሁለቱ መካከል አሻፈረኝ ባይ ካለ፤ ዕርቁ አይሠራም። ሽምግልናው ያስፈልጋል፤ ማስታረቅ እንችላለን ባዮች ሽማግሌዎች ከሌሉ፤ ሽምግልናው አይጀመርም። ለመታረቃቸው ሌላው ምክንያት ደግሞ፤ ከጠቡ በፊት አብረው በሰላም ይኖሩ የነበሩ መሆናቸውና ያ ሁኔታ የገዛቸው መሆኑ ነው። ከጠቡ በፊት በመካከላቸው የነበረው፤ ግንኙነት ሆነ፤ የየራሳቸው ታሪክ፤ ወሳኝ ነው። ከጠቡ በፊት ምንም ዓይነት ግንኙነት ላልነበራቸውና በፊትም ስምምነት ላልነበራቸው፤ ድርድሩ የወግ ነው።
ሽምግልናውን በዚህ መንገድ ስናየው፤ ድርድር የሚለው ከላይ ካሰፈርኩትየማስታረቅ ሂደት፤የተለየ ነው። ድርድር አብላጫውን በንግድ ሙያ የተያዘ የስምምነት መንገድ ሲሆን፤ በሁለት አካላት መካከል የሚካሄድ የሠጥቶ መቀበል ክንውን ነው። ሁለት የሚተማመኑ አካላት፤ በጠረምጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው የሚያደርጉት፤ የእኩልነት ግብይት ነው።እኒህ ሁለት አካላት፤ የሚገዙበት የኅብረተሰብ እውነታ መኖር አለበት።
አሁን የሚሽከረከረው የድርድር ሃሳብ፤ ምን እንደሆነ ከኒህ ከሁለቱ ክስተቶች ጋር እናዛምደው። እግረ መንገዳችንንም፤ ድርድር ያስፈልጋል ባዮች ያቀረቡትን እና ሊያቀርቡ የችሉትን ማስተማመኛና የድርድሩን አስፈላጊነት ማጠናከሪያ ሃሳባቸውን እናጢን።ሁለቱን የተለያዩ ፅንሰ ሃሳቦችን በማዛመድ፤ የሰላም ድርድር በማለት የቀረበው፤ የሁለቱ ክፍሎች ጥቅል ግንዛቤ ነው። እዚህ ላይ እኒህን የሽምግልናና የድርድርን ግንዛቤዎች ባንድ አጠቃለጠው የሚያቀርቡ ሰዎች፤ ልዩነቱ ጠፍቷቸው ሳይሆን፤ ከጭንቀት የተወለደ መውጫ መንገድ ፍለጋ የሄዱበት ነው። ፍላጎታቸው፤ ስምምነት ላይ እንዲደረስ ብቻ ነው። ማሰሪያ አድረገው የተነሱት፤ ተደራዳሪዎቹ፤ “በሽማግሌዎች ፊት፤ ቃሉን ከሠጠኝ አምነዋለሁ!” የሚል ግንዛቤን አዝለው፤ ለመደራደር ይቀርባሉ ብለው ነው። እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት፤ ማይተማመኑ አካላት ለድርድር እንደማያስቡ ነው። በእኩል መንፈስ፤ በመካከላቸው ያለውን ስምምነት እያንዳንዳቸው እኔም ተደራዳሪየም፤ በሥራ ላይ እንውለዋለን ብለው የሚተማመኑ አካላት፤ በቅን መንፈስ ለድርድሩ ይቀርባሉ።
በተወሰነ ደረጃም ቢሆን፤ በዚህ መንገድ፤ ተደራዳሪዎችበድርድሩ ጊዜ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ፤ የኃይል ሚዛን ወሳኝ ነው። ሁለቱ አንድ አጣብቂኝ ሁኔታ ሲገጥማቸውና ማለፍ የማይችሉት አጥር ሲይዛቸው፤ “መቼስ ምን ይደረግ!” በማለት ለድርድሩ ይቀርባሉ። ባለጉልበት፤ የድርድሩን ይዘትና ሂደት ይወስናል። ጉልበት የሌለው ደግሞ፤ የሠጡትን ይቀበላል።
እስኪ በየተራ አሁን ይደራደሩ የምንላቸውን ሁለት አካላት፤ ባህሪያቸውን፣ ታሪካቸውን፤ የታማኝነት ምስክራቸውን እና አንጻራዊ የጉልበት ጥንካሬያቸውን እንመርምር። የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ “ካሁን በኋላ የመጣው ይምጣ! የማጣው የለም!” በማለት ተነስቷል። ወራሪው ወገንተኛ አምባገነኑ የትግሬዎች መንግሥት ደግሞ፤ “እስካሁን እንደ ነበረው መግዛት እፈልጋለሁ። ይሄን የሚቃወም ፀረ-ሰላም፣ ፀረ-ልማትና ሀገር አፍራሽ ነው!” በማለት ቆሟል። በተግባርም ሕዝቡን እየገደለና ንብረቱን እየቀማ ነው። የትግሬዎች መንግሥት የእስካሁን ታሪክ እንመለከት፤
የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር፤ ( የአሁኑ የትግሬዎች መንግሥት ባለቤት፤ )
፩ኛ. የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር፤የሥልጣን ዘመኑን በትክክል አልተጠቀመበትም።
“ከኔ በላይ አዋቂ የለም!” ባይ ነው።“እናም እኔ አዛዥ ናዛዥ ነኝ!” ብሎ ቆሟል።
“ከማንም በላይ ጉልበት ስላለኝ፤ ሁሉን አዛለሁ!” ባይ ነው – በጉልበቱ ይተማመናል።
ተቃዋሚ አያስተናግድም፤ ይልቁንም ተቃዋሚን ጠላት አድርጎ ይመለከታል።
የጊዜ ሂደት አልቀየረውም፤ የበርሃ አመለካከቱና መልስ አሠጣጡ እንዳለ ነው። “ሁሉን በጠመንጃ!”
ከጊዜ ወደ ጊዜ ዕብሪቱ እየበዛ የሄደ ድርጅት ነው።
ሀገር የሚያስተዳደር ሳይሆን፤ ሀገርን የሚዘርፍ ድርጅት ነው።
፪ኛ. የትግሬዎች መንግሥት፤የድርድር ታሪኩ አያኮራም፤ ይልቁንም ያሳፍራል። እንኳንስ አሁን ጉልበት አለኝ ብሎ ራሱን ባገዘፈበት ሰዓት ይቅርና፤ እስካሁን ያለው ታሪኩ ያስደነግጣል።ለአንድ ኢትዮጵያዊ/ት ይሄን ታሪክ ዘርዝሮ ማቅረቡ ስድብ ስለሚሆን እንዲያው ድርድር ሊያደርግ አቅርቦ፤ ያላገጠባቸው ስም ብቻ ልዘርዝር፤
ከትግራይ ነፃ አውጪ ግንባር ጋር፤
ለድርድር ጠርቶ፤ አመራሩን በሙሉ ሌሊት ገድሎ፤ ድርጅቱን አጠፋው። በሕይወት ያሉ የድርጅቱ አባላት አሁንም እዚሁ በመካከላችን አሉ፤ ይመሰክራሉ።
ከኢሕአፓ/ኢሕአሠ ጋር፤
ይህን ድርጅት ከትግራይ ለማስወጣትና ትግራይን ለብቻው ለመቆጣጠር፤ ጦርነት ክፍቶ ብዙ ገድሏል። ተከትሎም ድርጅቱ በገባበት በመግባትና ሰላዮቹን በመካከል በመሰግሰግ፤ ለድርጅቱ ድክመት ምክንያት ሆኗል። መስካሪ አባላት ሞልተዋል።
ከኢዲዩ ጋር፤
ይህን ድርጅት በማጥፋት በኩል፤ ክፍተኛውን ሚና ተጫውቷል። ብዙዎቹን አባላቱን ገድሏል።
የዚህ ድርጅት የቀድሞ አባላት በመካከላችን አሉ።
ከኢሕድን ጋር፤
ይህን ድርጅት ብዙ ዋሽቶለት፤ በመጨረሻ ከሀገር አቀ ድርጅት ወደ የአማራ ወካይ ነኝ ባይነት ቀይሮታል። ባሁን ሰዓት የአማራ ተቀካይ ነኝ ባዩ፤ ብአዴን ነው።
ከኦነግ ጋር፤
ለንደን ላይ በምዕራባዊያን መንግሥታት መካከል ስምምነት አድርጎ፤ ሀገር ከገቡ በኋላ፤ ወታደሩን ስብስቦ ጨርሶታል። አባላቱ ይመሰክራሉ።
ከቅንጅት ጋር፤
በተደጋጋሚ በውጪ ሀገር መንግሥታት ታዛቢነት የገባውን ቃል አጥፎ፤ መሪዎችን ለእስር ዳርጎ፤ ድርጅቱን እንዲከስም አድርጓል። መስካሪዎች ሞልተዋል።
ከመድረክ ጋር፤
ልክ እንደቅንጅቱ፤ ከዓመት ዓመት፤ ባንድ በኩል፤ “ነፍስ ያለው ተቃዋሚ የለም እያለ፤ በሌላ በኩል ደግሞ መድረክ መድረክ እንዳይኖረው በማድረግ፤ እንደ እስስት እየተለዋወጠ፤ ድርጅቱን ፊርማ ሠጪ አድርጎታል። አሁንም በመድረክ ስም የሚንቀሳቀሱ አዲስ አበባ አሉ።
፫ኛ. የትግሬዎች መንግሥት፤ገዢ መተክል የለውም። እንዳሻውና አስፈለጊ ሆኖ እንዳገኘው ይለዋውጠዋል።
መርኀ-ግብሩን ቀያይሯል።
ሲጀምር ማርክሲስት ሌኒኒስት ነበር። ቀጥሎ ነፋሱ ወዳዘመመው ነጉዷል። አሁን የያዘው ቅይጥ የሆነው እንቶ ፈንቶ፤ “ዴሞክራቲክ ሴንተራሊዝም!” ይለዋል። ነገሩ በመንግሥትነት፤ ከሰው ነፍስ እስከ መሬቱ ድረስ በመሪዎቹ ቁጥጥር ሥር ሀገሪቱን በማድረግ፤ የንብረቱ ሁሉ ባለቤት መሪዎቹ መሆናቸው ነው። ይህ ሥርዓት ትክክለኛ ስም፤ “የገዥዎች ነጠቃ!”የሙስና ንቅዘት ነው። ( ከዶክተር ሰዒድ ሃሰን የወሰድኩት )
ስሙን ቀያይሯል።
ይሄ ዝርዝሩ ብዙ ነው። ሆኖም ግን፤ እንደ እስስት በየሄደበትና ቀለሙ ለጊዜው በሚደምቀው ስም እየያዘ ኖሯል። ወያኔ እንዲባል ምንጭ የሆነው፤ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ ከሚለው እስከ ኢሕአዴግ ድረስ ብዙ ስሞች አሉት።
ግቡን ቀያይሯል።
ሲነሳ፤ ትግራይን ገንጥሎ በአማራው መቃብር ላይ የትግራይን ሩፑብሊክ ሊመሰርት ነበር። ቀጠለና አዲስ አበባ ዘሎ ገብቶ፤ የትግራይን የበላይነት በኢትዮጵያ ማሰፈኑን ተያያዘው።
ወዳጆቹን ክዷል።
ከግለሰቦች እስከድርጅቶችና መንግሥታት፤ ክህደቱ የተዘገበ ነው። ኤርትራ፣ ሱዳን፣ በግልናበድርጅቶች ላይ የነበሩ ሰዎች፣ የራሱ የድርጅት አባላቱ ሳይቀር የዚህ ሰለባዎች ናቸው።
ደጋግሞ ዋሽቷል።
የራሱን ጥቅም ማስገኛ ጊዜያዊ መንገድ ለማግኘት፤ ለዕለቱ የሚያስኬደውን ሁሉ ይጠቀማል። ለሕዝቡ፤ ለእስረኞች፣ ለውጪ መንግሥታት፣ ለሽማግሌዎች፣ ለወላጆች፣ ለራሱ ወታደሮች፣ ለመንግሥት ሠራተኞች፣ ለግል ባለንብረቶች፤ ዋሽቷል በዚህ ያልተነካ ማንም የለም።
፬ኛ. የትግሬዎች መንግሥት ባሁኑ ሰዓት የሚያምነው ጉልበቱን ብቻ ነው።
ለማንኛውም ጥያቄ መልሱ በለው ነው።
እሱ የሚፈልገውን ማድረግ እንጂ፤ የሕግ የበላይነትን አይቀበልም።
የመንግሥት መስሪያ ቤቶችንና ሁሉንም በሀገራችን ያሉ ተቋሞች፤ የስለላ ማዕከሎች አድርጓቸዋል።
በውጪ ሀገር ያሉ ኤምባሲዎች፤ ባሉበት ሀገር ያሉ ስደተኛ ኢትዮጵያዊያንን መሰለልና በነሱ ላይ ዘገባ ማቅረብ ሆኗል ዋናው ሥራቸው።
የትምህርት ተቋሞች በሙሉ በመፈራረስ ላይ ናቸው።
የፍትኅና ርትኅ መስሪያ ቤት፤ የገዥው አንድ ቅርንጫፍ ሆኖ፤ ሕዝብን በመቀጥቀጥ እያገለገለ ነው።
ጉቦና ሙስና፤ በሀገራችን ለዕለት ተዕለት መንቀሳቀስ፤ ግዴታ ሀቆች ሆነዋል።
፭ኛ. የትግሬዎች መንግሥት ፈሪ ነው።
ባዶ እጃቸውን ለሰልፍ በወጡ ሰላማዊ ሕዝብ ላይ አረመኔያዊ ግድያ ፈጽሟል።
ሕፃናትንና አዛውንትን ገድሏል።
የሱዳን ወታደሮችን በጎንደር አስገብቶ በአማራው ሕዝብ ላይ ግድያ አስፈጽሟል።
ለሱዳንና ለግብፅ አጎብድዷል፤ በፍርሃትም ይሁን በውለታ ከኢትዮጵያ ይልቅ የነሱን ጥቅም ያስቀድማል።
ለሙን የሀገራችንን መሬት ለውጭ ሀገር ሽርከኞቹ አድሏል።
፮ኛ. የትግሬዎች መንግሥትበአሁኑ ሰዓት ማዕከል የሌለው የግል ንጉሶች የበዙበት ቡድን ነው።
ከመለስ ሞት ወዲህ፤ አባላቱ የየራሳቸውን ኪስ ማሳበጥና፤ የየራሳቸው ጦር የሚያዘጋጁ ይመስላሉ።
በመቀሌ ራሱን የቻለ በሚባል ሁኔታ፤ ሀገሪቱን እገዛለሁ የሚል የአባይ ወልዱ ቡድን አለ።
በአዲስ አበባ የብዙ ንጉሶች ስብስብ አለ። ደብረጽዮን፣ አርከበ፣ ስብሃት ነጋ፣ አዜብ፣ ቴዎድሮስ፣ የየራሳቸው ማዕከል ያላቸው ይመስል።
ምንም እንኳ እንደበረከት ያሉ ሰው በላዎች አለን ብለው ቢፎክሩም፤ የአማራውን ክፍል ገዥዎቹ እኒሁ ትግሬዎቹ ናቸው። በተመሳሳይ መልኩ ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ ሽፈራውና ሌሎች የክልል ንጉስ ነን ባዮች ራሳቸውን ቢያንቆለጳጵሱም፤ በየራሳቸው የተሸከሟቸው የትግሬ ገዥ ንጉሶች አሏቸው።
፯ኛ. የትግሬዎች መንግሥት፤ ታማኝ አደራዳሪ የለውም።
ሀገር ለማስተዳደር ብቁ ስላልሆነና ማንንም ስለማያምን፤ ሁሉንም ነገር በሽፍንፍንና በሚስጥር ያካሂዳል።
የውጪ ሀገር መንግሥታት የራሳቸውን ጥቅም አስጠባቂ አሽከር ስላገኙ፤ ለሱ አባሪዎች እንጂ፤ ታማኝ አደራዳር ሊሆኑ አይችሉም። ትክክለኞችን የውጭ ሀገር አደራዳሪዎች አያምንም፤ አይቀበልም።
እሱ የሚኮለኩላቸው ያገር ሰዎች፤ በፍርሃት የተዋጡና በጥቅም የታሰሩ ስለሆኑ፤ ታማኝ አደራዳሪ ሊሆኑ አይችሉም። ትክክለኞቹን የሀገር ውስጥ አደራዳሪዎችን አያምንም፤ አይቀበልም።
እንግዲህ ይሄን ሁሉ ስለ ትግሬዎች መንግሥት ካልሁ በኋላ፤ የሰላም ድርድር እንዲደረግ የሚፈልጉ ግለሰቦች ለምን እንደተነሳሱ ምክንያታቸውን ላቅርብ። ፍጹም ቅን ሆነው ድርድር እንዲደረግ የሚፈጉ ሰዎች የሚከተሉትን ነጥቦች ያነሳሉ፤
፩ኛ. ብዙ ሰዎች እንዳያልቁ፤
፪ኛ. ብዙ ንብረት እንዳይወድም፤
፫ኛ. በሕዝብ መካከል ቁርሾ እንዳይኖርና ተሽከርካሪ የጥፋት ሂደቶች እንዳይከታተሉ፤
፬ኛ. ከታሪክ ተጠያቂነት እንድንድን፤
፭ኛ. ሀገራችን ወደ ኋላ እንዳትጎተት፤
እኒህ እውነተኛና ተጨባጭ ምክንያቶች ናቸው። በያንዳንዳቸው ላይ ብዙ መተረክ ይቻላል። መፈተሽ ያለበት ግን፤ እኒህን ነጥቦች እያዳንዳቸውን በሚመለከት፤ ተደራዳሪ ወገኖች፤ እንዴት ይመለከቷቸዋል? ነው። ያ የአመለካከት አንድነት ከሌለ፤ ይደራደሩ ብሎ መጣሩ፤ እንዲያው መዳከር ነው የሚሆነው።
፩ኛ. ባሁኑ ሰዓት ብዙዎችን እየጨረሰ ያለው ማን ነው?
፪ኛ. ባሁኑ ሰዓት የሀገራችንን ሀብት በቁጥጥሩ ሥር አውሎ፤ ንብረት እያቃጠለ ያለው ማነው?
፫ኛ. ሕዝቡን ከፋፍሎ፤ እርስ በርሱ እንዲጠፋፋ መንገድ ያዘጋጀው ማነው?
፬ኛ. ታሪክን ክዶ አዲስ ታሪክ በመጻፍ፤ አዲስ ኢትዮጵያ እየፈጠረ ያለው ማነው?
፭ኛ. ሀገራችንን ከሥልጣኔ ወደኋላ እንድትቀር ያደረጋትና፤ አሁን የቴክኖሎጂ የመጨረሻዋ ሀገር ያደረጋት ማነው?
ከዚህ ተነስቶ ፍርድ መሥጠት ይቻላል።ማለትም፤ የትግሬዎችን መንግሥት ተው በማለት ብቻ ይሄ ሁሉ እንዲቀር ማድረግ ይቻላል መለት ነው።
እስኪ በሕዝቡ በኩል ወግኖ የሚታገለውን ክፍል ደግሞ፤ በትክክል እንመልከት። በሕዝቡ በኩል ወግኖ የሚታገለው ክፍል አንድ ማዕከል የለውም። ምንም እንኳን ከሞላ ጎደል ግባቸው አንድ ቢሆንም፤ ማለትም፤ “በሥልጣን ላይ ያለውን ፀረ-ኢትዮጵያ ቡድን ደምስሶ በቦታው ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን መገንባት!” ይሄን ተቀብለው፤ ሁሉም በአንድነት እየተጓዙ አይደሉም። ራሱ ይሄን ግብ ደግሞ አተረጓጎማቸው ለየቅል ነው። ይህ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ምን ማለት ነው? አሁንም እንደ ትግሬዎቹ መንግሥት የትግሬ ዞን፣ የኦሮሞ ዞን፣ የአማራ ዞን፣ የደቡብ ዞን፣ የሶማሌ ዞን፣ የአፋር ዞን፣ የአኙዋክ ዞን፣ የቤንሻንጉል ዞን፣ የአዲስ አበባ ዞን እያልን ልንቀጥል ነው? ወይንስ እያንዳንዱ/ዷ ኢትዮጵያዊ/ት አንድ ግለሰብ ዜጋ በመሆን በፖለቲካ ማኅደሩ የሚሳተፉበት ሥርዓት ለማምጣት ነው?
ይህ ብቻ አይደለም። ከነዚህ አንዱ ላይ ስምምነት ቢደረስስ፤ ይህ በምን መንገድ ነው በተግባር ላይ የሚውለው? አሁንስ ከመጀመሪያው፤ ይሄን ፀረ-ኢትዮጵያ ቡድን እንዴት ነው ከሥልጣኑ የሚባረረው? ይህስ ከታለፈ፤ ምን ዓይነት የሽግግር መንግሥት ነው የሚመሰረተው? ለዚህ ቀድሞ የተዘጋጀ ምን አለ? እኒህ ሁሉ ከወዲሁ መመለስ ያለባቸው ጥያቄዎች ናቸው። ለዚህ መልስ ለመሥጠት፤ ዝግጅቱ በቦታው አልተጀመረም። መጀመር ያለበት ደግሞ፤ ለትግሉ አንድ ማዕከል መፈጠሩ አስፈላጊ መሆኑን በመቀበል ነው። በአንዳንድ ነገሮች ልዩነቶች ይኖራሉ። መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ስምምነት ከሌለ ግን፤ አንድ ትግል ሳይሆን፤ የብዙ ትግሎችን እናት ነው የያዝነው ማለት ነው። ይህ ምስቅልቅል ነው ወደፊት እንዳንሄድ አንቅፋት የሆነብን። እናም በበኩሌ፤ የተለያዩ ሕዝባዊ ድርጅቶች በአንድ የሚሰባሰቡበት መንገድ መፈለግ አለበት እላለሁ። በርግጥ ይሄን ዘፈን ያልሰማ የለም። ተቀብሎም ያላጨበጨበ የለም። ነገር ግን ለተግባሩ የቆመ የለም። ስለዚህ፤ ድርድሩ ሊታሰብም አይችልም። ባቋራጭ ቀዳዳ ፈላጊዎችና አጋጣሚውን ለመጠቀም ከሚሯሯጡት በስተቀር፤ ከሕዝቡ ጎን የሚታገለው ክፍል፤ ሕዝቡን ወክሎ የሚደራደር እንደሌለ ያውቀዋል።
አሁን በተጨባጭ በሀገር ቤት ባለው ሕዝባዊ ታጋዩ ወገን፤ አመራሩን እየሠጠ ያለ ክፍል አለ። ይህ ክፍል ብዙ ጥሩና ትክክለኛ ጎኖች አሉት። ከላይ እንደገለጽኩት፤ አንድ አይደለም። ወደ አንድ መሰብሰብ አለበት። በውጪ ያለነው መርዳት አለብን። ይሄን ለማድረግ፤ አመቺ ሁነኢታው በጃችን ነውና፤ በውጪ የምንኖር ኢትዮጵያዊያን፤ በድርጅት ውስጥ ያሉም ሆነ በድርጅት ውስጥ ያልተካተትን፤ በአንድነት ከሕዝቡ ወገን ለመቆም፤ ሕዝባዊ ንቅናቄውን ለመርዳት፤ ባንድ መቆም አለብን። እንዳልኩት ብዙ ተደርቶበታልኅ በተጨባጭ ተግባራዊ ለመሆን፤ በየትኛውም ሕዝባዊ መዘገቢያ፤ ይሄ ይቀንቀን።