ፓርላማው መጠራቱ ለምንድን ነው? – ከነዚህ 3 ምክንያቶች በአንዱ ሊሆን ይችላል

ግርማ ካሳ

547 መቀመጫ ያለው ፓርላማ ከሰኔ 30 ቀን በኋላ መስከረም እስኪጠባ ድረስ የማይሰበሰብ አካል ነው። አባላቱ እረፍት ላይ ነው የሚሆኑት። (እንደ ትምሀርት ቤቶች ማለት ነው)። በሌላውም አገር የፓርላማ አባላት የማይሰበሰቡባቸው ቀናቶች በዛ ይላሉ። ይሄም የሆነበት ምክንያት አለው። አባላቱ በፓርላማ መቀመጥ ብቻ ሳይሆን፣ የሕዝብ ተወካዮች እንደመሆናቸው ከሕዝብ ጋር መነጋገር አለባቸው። በዚህ ወቅት ነው የተለያዩ ስብሰባዎች በተመረጡበት ቦታ እየጠሩ ሕዝቡ ያለውን ብሶት፣ መሻሻል አለባቸው የሚለው እንዲነገራቸው የሚያደርጉት። የበኢትዮጵያ ያሉ የፓርላማ አባላት ግን ከተመረጡ በኋላ መንግስት በአዲስ አበባ ከሚሰጣቸው ቤት ፈቀቅ አይሉም። ይሄ ማለት የሕዝብ ተወካዮች የሚባሉት ሕዝብን እንደማይወኩሉ በገሃድ የሚያረጋግጥ ነው።

 

የፓርላማ ተወካዮች መረጠን የሚሉት ሕዝብ ቢሆንም በተግባር ግን ተጠያቂ የሆኑት ለኢሕአዴግ ፖሊት ቢሮ ነው። በኢህአዴግ ፖሊት ቢሮ ደግሞ ፈላጭ ቆራጩ ሕወሃት ነው። ከ547 የፓርላማ መቀመጫ 38 መቀመጫ ብቻ ያለው ሕወሃት፣ እንዳለ ፓርላማዉን የሚያሽከረከር መሆኑ በኢትዮጵያ የጥቂቶችን ጥቅም ብቻ የሚያስጠብቅ የአፓርታይድ ስርዓት እንዳለ አመላካች ነው።

ይህ ፓርላማ መለስ ዜናዊ ሞቶ እርሱን ለመተካት ነው በ እረፍት ጊዜ የተጠራው። በምን ምክንያት እንደሆነ ዉሉ ባይታወቅም ፓርላማው እንደገና ተጠርቷል። ሊሆን የሚችለው ከሚከተሉት ሶስት ምክንያቶች አንዱ ነው ሊሆን የሚችለው

1. እንደተለመደው ሕወሃት ወስኖ፣ በኢሕአዴግ ፖሊት ቢሮ አጸድቆ በቶሎ ፓርላማው እንዲወስነው የፈለገው ነገር አለ። አንዳንዶች በኤርትራ ላይ ጦርነት ለማወጅ ነው የሚል አስተያየት ይሰጣሉ። እኔ አይመስለኝም።ሕወሃቶች ሞኝ አይደሉም በአሁኑ ወቅት ኤርትራ ላይ ጦርነት የሚያደረጉት። ኤርትራ ምን ስላደረገቻቸው ? ኤርትራ ያሉ ደርጅቶች እኮ ከወሬ ዉጭ ያረጉት ነገር የለም። ይሄን ደግሞ ወያኔዎች ጠንቅቀው ያውቃሉ። ለወያኔዎች ትልቅ ራስ ምታት የሆነው የሕዝቡ እምቢተኝነት ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የሚኒሶታ ደብረሰላም መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን በከፋፋዮች ሴራ አትናወጥም!!! ለአንድነት ከቆሙ ምእመናን

2. ሃይለማሪያም ደሳለኝ እጅግ በጣም ደካማ የሆነ ሰው። የጦር ሃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ሆኖ እንኳን ፣ የኤታ ማጆር ሹሙን ሳሞራ የኑስን ቢሮዬ እንድትመጣ ብሎ ለማዘዝ የሚፈራ ሰው ነው። እንደው እንደሚባለው ህወሃቶች ሙሉ አድርገው እየሰደቡት ያዋርዱታል ሁሉ ይባላል። እንዲህ አይነት የጥቁት ሕወሃቶች መጨፈሪያ የሆነ ጠቅላይ ሚኒስተር አገርን እና ህዝብን እየጎዳ ነው።፡በዚህም ምክንያት ብአዴን እና ኦህዴድ ጡንቻቸውን በማፈርጠም፣ ይሄን ሰው በመቀየር፣ ለሕወሃቶች ታዛዥና አጎብዳጅ ያለሆነ ጠቅላይ ሚኒስተር ለመሾም አስበውም ሊሆን ይችላል።

3. ህወሃትን ጨመሮ እንዳለ ኢሕአዴግ በአገሪቷ ያለው ቀውስ አስቸኳይ መፍትሄ እንደሚያስፈልገው በማመን፣ በፖሊት ቢሮ ደረጃ ኢሕአዴግ ተሰማምቶመሰረታዊ የሆኑ ለዉጦችን በቶሎ በማድረግ አገር ወደ ከፋ ደረጃ እንዳትሄድ አንዳንድ ዉሳኔዎች እንድወሰኑ ይሆናል ፓርላማው የተጠራው። መቼም ትንሽም ቢሆን ጥሩ ነገር ተስፋ ማድረግ አይከፋም። ለምሳሌ የጸረ-ሽብር ሕጉን ለጊዜው ተግባራዊ አይሆንም ብለው ቢሰርዙት፣ እጅግ በጣም ብዙ የሕሊና እስረኞች ይፈታሉ። የብሄራዊ እርቅ የሚያመቻችና የሕግ መንግስቱና የየፌዴራል አከላለልን አጥንቶ ማሻሻያዎች የሚያቀርብ ኮሚሽን ቢያቋቁሙ የወልቃይት ጉዳይ፣ የአዲስ አበባ እና የኦሮሚያ ጉዳይ እንዲሁም ሌሎችም በሂደት ሊፈቱ እንደሚችሉ ለሕዝቡ ተስፋ ሊሰጥ ይችላል።

ለማንኛውም እናያለን።