ሸንጎ ከጎንደር ሕዝብ ጎን መሆኑን አስታወቀ – “የሕዝብ መብት የማያከብር መንግሥት በሕዝብ አመፅ ይወገዳል”

የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ (ሸንጎ)
Ethiopian People’s Congress for United Struggle (Shengo) www.ethioshengo.org shengo.derbiaber@gmail.com
ሐምሌ 6 ቀን 2008 ዓ. ም ጁላይ 13, 2016

ላለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ሥልጣኑን በጉልበት ወስዶ፣ የሕዝቡን መብት ገፎ፣ ያገሪቱን ሃብትና ንብረት የሚዘርፈው ቡድን ሥልጣኑና አድራጎቱ ዝንተ-ዓለማዊ እንደማይሆን ከወደቁትና ከተወገዱት ተመሳሳይ መንግሥታት ታሪክ ገና አልተማረም። ከፋፍዬ እኖራለሁ የሚለው ስልቱ እየተጋለጠ በየአቅጣጫው በሕዝብ ተቃውሞ እየተዋከበ ይገኛል። ወደ ታሪክ መቃብር የሚገባበት ቀን እያጠረ መጥቷል። አሁን በጎንደር ቀደም ሲል በሸዋ,በተለያዩ ያኦሮሚያ ክልል አካባቢወች በጋምቤላና በሌሎቹም ያገሪቱ ክፍሎች የተነሳው ሕዝባዊ አመፅ ይህን የሚያመላክቱና ውድቀቱን የሚያፋጥኑ ተቃውሞዎች ናቸው።
የአሁኑን የሕዝብ ተቃውሞ ከሌላው ጊዜ የተለየ የሚያደርገው ባዶ እጁን ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በአደባባይ የሚያደርገው ትግል አሁን እንደ ፀጥታ ኃይሎቹ በመሣሪያ የተደገፈ ትግል የሚካሄድ መሆኑ ነው። መንግሥት ተብየው ትዕቢተኛና ጎሰኛ ቡድን ለሌላው ዜጋ ብቻ ሳይሆን እወክለዋለሁ የሚለውን የትግራይ ሕዝብ፣ በኢትዮጵያዊነቱ ኮርቶ በፈለገው የአገሪቱ መሬት ሠርቶ ማደር እንዳይችል እስረኛ ከማድረጉም በላይ ባላስፈላጊ ግጭት ውስጥ ገብቶ ደሙን እንዲያፈስላቸው የጥላቻና የሽብር ፕሮፓጋንዳ በመርጨት ላይ ይገኛል። የትግራይ ተወላጅ በሚረጨው የጥላቻ ቅስቀሳ ሳይታለል በስሙና በልጆቹ ደም ሥልጣን ላይ ያሉትን የበለጸጉ አምባገነኖች ማስወገድ ይጠበቅበታል። ለዘመናት ከሌሎቹ ወገኖቹ ጋር ተባብሮና ነፃነቷን አስከብሮ የኖረችውን አገር አሁንም ተባብሮ ድንበሯን እየቆረሰ ለባዕዳን የሚሰጠውን ወንጀለኛና አገር አጥፊ ቡድን በቃህ ሊለው ይገባል። ዳር ድንበሯን ለማስከበር እምቢ ላገሬ ብሎ መነሳት፣ በወገኖቹ ጋር አላስፈላጊ ግጭት ፈጥሮ ደም ከመቃባት፣ ደም ሊያቃባው የሚጥረውን ቡድን ከሥልጣኑ ሊያስወግደው በሚችለው ሕዝባዊ ትግል ውስጥ የድርሻውን ማበርከት ይጠበቅበታል። በአገዛዙ ዙሪያ የተሰበሰቡት ለውጥ ፈላጊዎችና አገር ወዳዶች ሰልፋቸውን ከሕዝቡ ጋር ቢያደርጉ ሊደርስባቸው ከሚችለው የህሊና ጸጸት ሊድኑ ይችላሉ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሁለተኛውን ዙር የሚሊየኖች ድምጽ እንቅስቃሴን በመደገፍ: ላስ ቬጋስ የአዲስ አበባዉን – አትላንታዎች አዋሳን -ዴንቨሮች ደሴን - ቃሌ እና ደብተራው ቁጫንና ድሬደዋን ስፖንሰር አደረጉ !

የሥርዓቱ አገልጋይና ተከታይ የሆነውም ወገን አገሪቱ ያለችበትን ሁኔታና ሊከሰት የሚችለውን አደጋ አጢኖ ለችግሩ ምክንያት የሆነውን መንግሥት ተብዬ ቡድን ለማስወገድ በሚደረገው ትግል ሊሳተፍ ይገባዋል። ምርጫውን ሊያስተካክል የግድ ይላል፤ ከሚወድቀው አገዛዝ ጋር አብሮ መውደቅ ወይም ከሚተካው ሕዝባዊ ሥርዓት ጋር አብሮ መነሳት! ሌላ ምርጫ የለም። የመከላከያ ጦርና ፖሊስም የሕዝቡን ድምፅ ለማፈንና ሕዝቡን በጦር ለመምታት ከአገዛዙ የሚሰጠውን ትዕዛዝ እንዳይቀበልና ከሕዝቡ ጎን እንዲሰለፍ እናሳስባለን።

የተለያዩት የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች የእርስ በርስ ንትርክን አቁመው የተቀጣጠለው ትግል በድል እንዲደመደም ተባብረው አመራር ሊሰጡት ይገባል። ትግሉ የአማራ፣ የኦሮሞ፣ የወልቃይት፣ የትግሬ፣ የደቡብ…ወዘተ ከመሆን አልፎ አገራዊ መልክና ዓላማ እንዲይዝ የማድረግ ሃላፊነት እንዳለባቸው አውቀው በዚያ መልክ ሊንቀሳቀሱ ይገባል። በግርግር ክልሌን ይዤ የራሴን መንግሥት እመሠርታለሁ በማለት ለዚያ መታገል አገሪቱን ለበለጠ ቀውስ ይዳርጋታል። የሥርዓቱ ደጋፊ የሆኑት የውስጥ የውጭና ኃይሎች የመጨረሻ የመዳኛ ስልት የወታደራዊ መንግሥት ቦታውን እንዲረከብ ማድረግ ሊሆን እንደሚችል ከግብፅና ከሌሎቹ አገሮች ተመክሮ መማርና መጠንቀቅ ይገባል። ስለዚህም በቀጣይ ጨቋኝና አምባገነን ሥርዓት ሲረገጡ መኖር እንዳይከተል ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል።
በየአካባቢው ታምቆ የቆየው ሕዝባዊ ብሶትና ብቅ እልም ሲል የነበረው ሕዝባዊ ትግል አሁን በጎንደር የተከፈተው የድል በር እንዳይዘጋ ተባብሮ መቆም ይገባዋል። የጎንደር ሕዝብ እያሳየ ያለው ትግልና መስዋዕትነት የሚደነቅና ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከጎኑ ቆሞ አብሮት ሊታገል የሚገባው ነው። ስለሆነም ታጋዩ የአንድነት ኃይል ትግሉን አቀነባብሮ እንዲታገል ጥሪያችንን እናቀርባለን። በዚሁ አጋጣሚም ኢትዮጵያውያን አገዛዙ ሕዝብ ከሕዝብ ጋር እንዲጋጭ ለሚፈጥረው ተንኮልና ሤራ ሰለባ እንዳይሆኑ ጥንቃቄ እንዲደረግ እናሳስባለን።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የታማኝ በየነ ንግግር በሎሳንጀለስ (አዲስ ቪዲዮ)

የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ (ሸንጎ) አገዛዙ በጎንደር ነዋሪዎች ላይ የወሰደውን የኃይል እርምጃና ግድያ በጥብቅ እያወገዘ በመቀጣጠል ላይ ያለው ሕዝባዊ አመጽ ብሶት የወለደው መሆኑን ያምናል፤ ይደግፋል፤ የትግል አጋርነቱንም ይገልጻል። ትግሉ ይበልጥ ፍሬያማና የለውጥ ኃይል እንዲሆን የተያያዘ አመራርና አገር አቀፍ ዓላማ ያለው እንዲሆን ያሳስባል።

የስርአቱ ባለስልጣኖች በህዝብ ላይ የሚያካሂዱት የግፍ ተግባር አሁኑኑ እንዲያቆሙ ፣ አጥብቆ ይጠይቃል። በጎንደር ህይወታቸውን ላጡ ወገኖቻችን ቤተሰቦች፣ ወዳጅና ዘመዶችም የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ይገልጣል

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!
Tel: 44 7937600756 , +1 9168486790 E-mail : shengo.derbiaber@gmail.com

Share