የቁጫ ወረዳ በማንነት ጥያቄ ትርምስ ውስጥ ገብታለች

‘‘ከ500 በላይ ሰዎች ታስረዋል’’ነዋሪዎች
‘‘የታሰሩት ዘጠኝ ብቻ ናቸው’’
የዞኑ ፍትህ መምሪያ
*ከታሰሩት መካከል የኢህአዴግ አባላት ይገኙበታል

በዘሪሁን ሙሉጌታ

በደቡብ የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግስት በጋሞ ጎፋ ዞን በምትገኘው የቁጫ ወረዳ በሕገ-መንግስቱ መሠረት የማንነት ጥያቄአችን አልተመለሰም፣ የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄ አልተሟላንም በሚል ጥያቄ በነዋሪዎቹና በወረዳው አስተዳደር የተፈጠረው ውዝግብ እንደገና አገርሽቷል። በወረዳው ነዋሪዎችና በአስተዳደሩ መካከል በተፈጠረው አለመግባባት ከሰኔ 28 ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ ጥያቄ ያነሱ ግለሰቦች መታሰራቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ለዝግጅት ክፍላችን ገልፀዋል። ነዋሪዎቹ ‘‘እኛ ቁጫ ሆነን ሳለ በጋሞ ጎፋ ብሔረሰብ ስር እንድንጨፈለቅ ተደርገናል። ልጆቻችንም በኢትዮጵያ ህገ-መንግስት እና በተባበሩት መንግስታት በፀደቀው የሰብአዊ መብት ድንጋጌ መሠረት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ አልተደረገም። በዚህም ሳቢያ የመልካም አስተዳደርና የልማት ተጠቃሚ መሆን አልቻልንም’’ ሲሉ ቅሬታ አቅርበዋል። ከዚህ ቀደም ጥያቄአቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ቢያቀርቡም ተቀባይነት ማጣታቸውንና በድጋሚ ትናንት 12 አባላት የሚገኙበት የወረዳው የሀገር ሽማግሌዎችን የሚወክሉ አባላትን ወደ አዲስ አበባ መላካቸውን አስታውቀዋል። የወረዳውና የዞኑ ፖሊስ አግባብነት የሌለው እርምጃ በመውሰድ ታሳሪዎችን መጎዳታቸውንም ገልፀዋል። በአሁኑ ወቅት ከታሰሩት ግለሰቦች መካከል ቀደም ሲል ከወረዳ አስተዳደር ጀምሮ በልዩ ልዩ የመምሪያ ኃላፊነት ደረጃ ሲሰሩ የነበሩ እና እየሰሩ ያሉ የደኢህዴን/ኢህአዴግ የወረዳ አባላት ጭምር እንደሚገኙበት የነዋሪዎቹ ጥቆማ ያስረዳል። በቀጣይም የብሔረሰቡ ተወላጅ ምሁራንና የሀገር ሽማግሌዎች ሊታሰሩ እንደሚችሉ ስጋታቸውን ገልፀዋል። የጋሞ ጎፋ ዞን የፍትህ መምሪያ ኃላፊ አቶ አባይነህ አዴቶ ሁኔታውን በማስመልከት ለሰንደቅ ጋዜጣ በሰጡት ማብራሪያ ባለፈው ቅዳሜ ዘጠኝ የሚሆኑ ሰዎች በቁጥጥር ስር ማዋላቸው ተደውሎ ተነግሮናል ብለዋል። ለጊዜው ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር የዋሉበት ምክንያት እየተጣራ ቢሆንም እስሩ ከማንነት ጥያቄ ጋር መያያዝ አለመያያዙን እያጣራን ነው ሲሉ አስረድተዋል።‘‘በወረዳው 500 ሰው ታስሯል የሚባለው ሐሰት ነው። አሁን በማንነት ዙሪያ ጥያቄውን ለምን አነሳህ ተብሎ የሚታሰር አይመስለኝም። ጥያቄው ተገቢነት እንዳለውና እንደሌለው የሚመለከተው አካል የሚሰጠው ምላሽ ይኖራል። ነገር ግን የተጠረጠሩት ሰራተኞች በአካባቢው አስተዳደር ላይ በፈጠሩት የፀጥታ ችግር በተጨባጭ በህግ አግባብ ተይዘው ምርመራ እየተጣራ መሆኑን ነው ያለኝ መረጃ የሚያመለክተው’’ ሲሉ አቶ አባይነህ ምላሽ ሰጥተዋል። ከሁኔታው ትርፍ ለማግኘት የሚፈልጉ ኃይሎች ያለውን ነገር አጋነው እያቀረቡት ነው ሲሉ የወቀሱት ኃላፊው በታሳሪዎቹም ላይ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ተፈፅሟል መባሉንም አስተባብለዋል። በቁጥጥር ስር ከዋሉት ግለሰቦች መካከል የኢህአዴግ አባላት ይገኙበታል ተብለው የተጠየቁት አቶ አባይነህ በእርግጥም ከታሰሩት ውስጥ የኢህአዴግ አባል የነበሩና አሁንም አባል የሆኑ እንደሚገኙበት አረጋግጠዋል። የታሰሩት ሰዎች ከቴክኖሎጂ ሽግግር ጋር፣ ከማዳበሪያ ስርጭት ጋር በተያያዘ የወረዳ አመራሩ ሕዝብ ሲሰበሰብ ሕዝቡን መሰብሰብ አትችሉም፤ እኛንም መምራት አትችሉም የሚል እንቅስቃሴ ማድረጋቸውን ለዞኑ አመራር ሪፖርት ተደርጓል ብለዋል።ከታሳሪዎቹ መካከል የኢህአዴግ አባላት ጭምር ስለኖሩበት ምክንያት የተጠየቁት የፍትህ መምሪያ ኃላፊው አስተዳደራዊ ብዥታ መኖሩን አምነዋል። ከሰሞኑም ከመልካም አስተዳደር ጋር የተያያዘ ግምገማ ለማካሄድ ዝግጅት መኖሩንም ጠቁመዋል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የምርኮኞች ወግ ከአርበኛ ዘመነ ካሴ ጋር! | አዲሱ ደረበ | ብልፅግና ትርምስምሱ | “የኢጋድ ውድቀት” ሱዳን እና ኢትዮጲያ አምፀዋል!

የዜናው ምንጭ ሰንደቅ ጋዜጣ የዛሬ ጁላይ 10 ዕትም

Share