(በፍሬው አበበ)
በቅጽል ስማቸው አይ ኤም አፍ በመባል የሚታወቁትና በገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ዐቃቤ ሕግ ከዛሬ አራት ዓመታት በፊት በአራጣ ማበደር ክስ ተመስርቶባቸው በማረሚያ ቤት ይገኙ የነበሩት አቶ አየለ ደበላ ባደረባቸው ሕመም በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ሰኔ 30 ቀን 2005 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። የቀብራቸው ስነስርዓት ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበት ትላንት በቅድስት ስላሴ ቤ/ክ ተፈጽሟል።አቶ አየለ ደበላ በሕመም ላይ እንደነበሩና የፌዴራል ማረሚያ ቤቱም አስፈላጊውን ሕክምና በአገር ውስጥ ሆስፒታሎች እንዲያገኙ ሲያደርግ መቆየቱን ጠቁሞ ሰኔ 30 ቀን 2005 ሕይወታቸው ማለፉን ለሰንደቅ ጋዜጣ አረጋግጧል። የአቶ አየለ አስከሬን ከማረሚያ ቤት ትላንት ቤተሰቦቻቸው በመረከብ የቀብር ሥነሥርዓቱን በቅድስት ስላሴ ቤተክርስቲያን መፈጸሙን የደረሰን መረጃ ይጠቁማል።
ስለአቶ አየለ ደበላ የክስ ጭብጥ ዳራ
የኢትዮጽያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ከአራጣ ማበደር ተግባር ጋር ተያይዞ በአቶ አየለ ደበላ ላይ ክስ ያቀረበው ግለሰቡ ለባንክ ብቻ የተፈቀደውን አገልግሎት ሲሰጡ ተገኝተዋል፣ የገቢ ግብር አዋጅን በመጣስ የተጨማሪ እሴት ታክስ ሳይከፍሉ ቀርተዋል፣ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብን ሕጋዊ አስመስለው በማቅረብ ገቢ ሰብሳቢ መ/ቤቱን አሳስተዋል በሚል ነው። የባለስልጣኑ ዐቃቤ ሕግ በአቶ አየለ ላይ 10 ያህል የወንጀል ክሶችን በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት 11ኛ ወንጀል ችሎት በወቅቱ ያቀረበ ሲሆን ፍ/ቤቱም ክሱን ለአራት ወራት ያህል ሲመለከት ከቆየ በኋላ ሐምሌ 13 ቀን 2002 ዓ.ም በዋለው ችሎት በሰጠው ቅጣት አቶ አየለ ደበላ በ22 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኗል። በተጨማሪም ለቀሪዎቹ ስምንት ክሶች በድምሩ 308 ሺ ብር ቅጣት እንዲከፍሉ፣ እንዲሁም በንብ ባንክ በዝግ አካውንት አስቀምጠውት የነበረ ብር 12 ሚሊየን፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለከተማ የሚገኝ አንድ መኖሪያ ቤት እንዲሁም ሁለት ተሸከርካሪዎች የሶስተኛ ወገኖች መብት ተጠብቆ እንዲወረሱ ሲል ውሳኔ መስጠቱ ይታወሳል።
ምንጭ፡ ሰንደቅ ጋዜጣ የዛሬ ጁላይ 10 ዕትም።