ፓርላማው ያሳለፈውን ያለመከሰስ ውሣኔ በ24 ሰዓታት ልዩነት አጠፈ፤ አቶ ቃሲም እየተፈለጉ ነው

ፓርላማው ያሳለፈውን ያለመከሰስ ውሣኔ በ24 ሰዓታት ልዩነት አጠፈ

አቶ ቃሲምና ሁለት ሌሎች የአስተዳደሩ ባለሰልጣናት እየተፈለጉ ነው

(በፍሬው አበበ)

በአዲስአበባ ከተማ አስተዳደር በመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ሥር የውዝፍ ሥራዎች መስተንግዶ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ የነበሩትና ከአምስት ዓመታት በላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ በመሆን ያገለገሉት አቶ ቃሲም ፊጤ ዳኖ ያለመከሰሰ መብታቸው መነሳት ጉዳይ ላይ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ረቡዕ ሰኔ 26 ቀን 2005 ዓ.ም ተወያይቶ ጥያቄውን ውድቅ ካደረገ በኋላ በማግስቱ በዚሁ ጉዳይ ላይ የቀረበለትን አጀንዳ ተቀብሎ አጸደቀ።በኦሮሚያ ክልል ሲሙ ኮሶ 2 ከሚባል አካባቢ ተመርጠው የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባል የነበሩት አቶ ቃሲም ፊጤ ያለመከሰሰ መብታቸው እንዲነሳ ጥያቄ የቀረበው ከፌዴራል የሥነምግባርና የጸረ ሙስና ኮምሽን ሲሆን ጉዳዩ ለም/ቤቱ የሕግ ፍትህና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮምቴ ቀርቦ ከታየ በኋላ ም/ቤቱ እንዲያጸድቀው ባለፈው ሳምንት ረቡዕ እለት ከሰዓት በኋላ ለም/ቤቱ መቅረቡ ታውቋል።ሆኖም በም/ቤቱ አንዳንድ አባላት በኩል ጥያቄው መቅረብ የነበረበት በፌዴራል የሥነምግባርና የጸረ ሙስና ኮምሽን ሳይሆን በፍትህ ሚኒስቴር በኩል መሆን ነበረበት የሚል አስተያየት የቀረበ ሲሆን በሌላ በኩል በሙስና የሚጠረጠሩ ግለሰቦችን ኮምሽኑ ለም/ቤቱ ማቅረብ ይችላል፣ ከዚህ በፊትም በተመሳሳይ መንገድ የቀረበ ያለመከሰሰ መብት ይነሳ ጥያቄ በም/ቤቱ ማለፉን በመጥቀስ ክርክሮች ከተደረጉ በኋላ በ58 የድጋፍ እና በ111 የተቃውሞ ድምጽ ያለመከሰሰ መብት እንዲነሳ የቀረበውን የውሳኔ ኀሳብ ውድቅ አድርጓል።ይህ የፓርላማው ያልተጠበቀ ውሳኔ የም/ቤቱን የሕግ የፍትህና አስተዳደር ቋሚ ኮምቴ አባላትን ጨምሮ የፌዴራል የሥነምግባርና ጸረ ሙስና ኮምሽንን ያደናገጠ መሆኑን ምንጮቻችን የጠቆሙ ሲሆን በዚህ መንገድ የሰዎች ያለመከሰሰ መብት እንዳይነሳ ውሳኔ የሚተላለፍ ከሆነ የጸረ ሙስና ትግሉን አስቸጋሪ ሊያደርገው ይችላል የሚሉ ሥጋቶች ተሰምተዋል።ሆኖም ፓርላማው በማግስቱ ሰኔ 27 ቀን 2005 ዓ.ም ባካሄደው ስብሰባ ም/ቤቱ ያስተላለፈውን ውሳኔ እንደገና ስለማየት በሚል አጀንዳ ከ24 ሰዓታት በፊት የጣለው አጀንዳ ተመልሶ ቀርቦለት በአብላጫ የድምጽ ውሳኔ በመስጠቱ የአቶ ቃሲም ፊጤ ያለመከሰሰ መብት ሊነሳ ችሏል።አንድ በጉዳዩ ላይ አስተያየት የተጠየቁና ስማቸውን መግለጽ ያልፈገሉ የሕግ ባለሙያ ም/ቤቱ መጀመሪያ ያሳለፈው ውሳኔ ትክክል እንዳልነበር ጠቅሰው ቆይቶም ቢሆን መታረሙ ተገቢ ነው ብለዋል። ም/ቤቱ አንድን የም/ቤት አባል በሙስና ጠርጥሬዋለሁ፣ ሰውየውን ይዤ ለማጣራት የሚያስችል በቂ መረጃ አለኝ እየተባለ፤ በአቀራረብ ፕሮሲጀር ተከትሎ ያልቀረበ ቢሆንም እንኳን አጀንዳውን ውድቅ ሊያደርገው አይገባም። ይህ ማለት እኮ ሌቦች መሸሸጊያ እንዲያገኙ ዕድል መስጠት ነው ሲሉ አስተያታቸውን ሰጥተዋል። የፌዴራል የሥነምግባርና የጸረ ሙስና ኮምሽን የአቶ ቃሲም ያለመከሰሰ መብት በፓርላማው ከተነሳ በኋላ ከፍ/ቤት የመያዣ ትዕዛዝ በማውጣት አቶ ቃሲምንና ሌሎች ከሁለት በላይ ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ ጥረት ያደረገ ቢሆንም ለሕትመት እስከገባንበት ትላንት ከሰዓት በኋላ ድረስ ሰዎቹ በቁጥጥር ሥር እንዳልዋሉ ታውቋል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የኢትዮጵያን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ እና የዲያስፖራውን ሚና በተመለከተ በኖርዌይ ኦስሎ ሕዝባዊ ውይይት ተካሄደ

የሕግ ከለላ የማንሳት ጥያቄ ይዘት

በ1987 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቦሌ ክ/ከተማ ወረዳ 3 ውስጥ የሚገኘውን ስፋቱ 500 ካ.ሜ ቦታ ሕንፃ እንዲገነቡበት ለኢንጂነር ግርማ አፈወርቅ በጊዜያዊ ካርታ ቁጥር 35852 ተሰጥቷቸው ግብር ሲከፍሉበት የቆዩ ቢሆንም በቦታው ላይ የነበሩ ኗሪዎች ቦታውን አንለቅም በማለታቸው በአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ግለሰቡ ክስ አቅርበው በጥቅምት 2/1997 ለእርሳቸው በተወሰነው መሰረት ቦታውን ተረክበው ከ09/06/03 እስከ 09/06/08 የሚያገለግል ባለ አስራ ሁለት ፎቅ ሌግዥሪ አፓርትመንት የግንባታ ፈቃድ አውጥተው ስራ ለመጀመር ዝግጅት ማጠናቀቃቸው በተሰበሰበ መረጃ መረጋገጡን፣አቶ ዮሐንስ ደርሰህ የተባሉ በአካባቢው የሚገኙ ባለ ሆቴል ከላይ የተጠቀሰው የኢንጂነር ግርማ ይዞታ እንዲሰጣቸው ለከተማ መስተዳደሩ ጥያቄ አቅርበው የአዲስ አበባ የመሬት አስተዳደርና የግንባታ ፈቃድ አሰጣጥ ባለስልጣን ስራ አስኪያጅ የሆኑት የተከበሩ አቶ ቃሲም ፊጤ ኢንጂነር ግርማ አፈወርቅ ቅድሚያ የማልማት መብት ያላቸው መሆኑን እና ከቦታው ላይ የተነሱ ነዋሪዎችን በራሳቸው ወጭ በሌላ ቦታ ግንባታ ገንብተው ያሰፈሩ መሆኑን የሚያውቁ መሆናቸውን፣አቶ ቃሲም ፊጤ ለመሬት አስተዳደር ቦርድ ያልተሟላ መረጃ በመስጠት እና የሚያውቁትን መረጃ በመደበቅ የኢንጂነር ግርማ አፈወርቅ 500 ካ.ሜ ይዞታ ካርታቸው እንዲመክን ተደርጎ ቦታው ለአቶ ዮሐንስ ደርሰህ እንዲሰጥ ማድረጋቸውን፣አቶ ቃሲም ፊጤ አቶ ዮሐንስ ደርሰህን አላግባብ በሕገወጥ መንገድ ጥቅም እንዲያገኙ በሌላ በኩል ኢንጂነር ግርማ አፈወርቅ ይዞታቸውን እንዲያጡ ማድረጋቸው በማስረጃ መረጋገጡን፣ በመጥቀስ የፌዴራል የስነ ምግባር እና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በጉዳዩ ላይ ምርመራ ለማድረግ እንዲችል ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የአቶ ቃሲም ፊጤ ያለመከሰስ መብት እንዲነሳ ከላይ በተጠቀሰው ቁጥር እና ቀን ተገልጿል።በዚሁ መሰረት የሕግ ፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የአሰራርና የአባላት ስነ ምግባር ደንብ ቁጥር 3/1998 አንቀጽ 5/6/ እንዲሁም በም/ቤቱ መመሪያ ቁጥር 17 አንቀጽ 11/6 መሰረት ከተቋሙ በተፃፈው ደብዳቤ ላይ በቂ ግንዛቤ በመያዝና የኮሚሽኑ መርማሪዎችን ጠርቶ ተጨማሪ የማጣራት ስራ በማከናወን አቶ ቃሲም ፌጤ ዳኖ ያለመከሰስ መብት እንዲነሳና በተጠረጠሩበት ወንጀል የፌዴራል የስነ ምግባር እና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የጀመረውን የሙስና ወንጀል ምርመራ ስራ ለማጠናቀቅ እንዲችል ያቀረበውን ጥያቄ ቋሚ ኮሚቴው ከላይ በተጠቀሰው የምክር ቤቱ ደንብና መመሪያ መሰረት አስፈላጊውን መረጃ በመያዝና በማጣራት ለድርጊቱ መፈፀም አመላካች ሁኔታዎች መኖራቸውን አረጋግጦ አባሉ በተጠረጠሩበት ጉዳይ ቀርበው ቃላቸውን እንዲሰጡ ያለመከሰስ መብታቸው እንዲነሳ ኮሚቴው የውሳኔ ሃሳብ አቅርቦ እንደነበር ይታወሳል።ነገር ግን የፌደራል የስነ ምግባር እና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ያቀረበው የሕግ ከለላ የይነሳልኝ ጥያቄ ተጨማሪ መታየት ያለባቸው ጉዳዮች በማጋጠማቸው ጊዜ ሰጥቶ ማየቱ የተሻለ ነው በሚል ያለመከሰስ መብታቸው ከመነሳት እንዲዘገይ ጠይቋል።በዚህ መሰረት ኮሚሽኑ እስከአሁን ሲያጣራ የቆየ ቢሆንም አስቀድሞ የቀረበውን ጥያቄ ሊያስለውጥ የሚችል ማስረጃ ማግኘት አለመቻሉን በመጥቀስ በቁጥር 40/መመ1-መ/4/ ሰኔ 13 ቀን 2003 ዓ.ም በተፃፈ ደብዳቤ የአቶ ቃሲም ፊጤ ዳኖ ያለመከሰስ መብት እንዲነሳ በድጋሚ ምክር ቤቱን ጠይቋል። ለቋሚ ኮሚቴውም በዚህ ጉዳይ ላይ የውሳኔ ሃሳብ እንዲያቀርብ ከክቡር አፈጉባኤ በድጋሚ ተመርቶለት ምርመራ በማካሄድ የሚከተለውን ውሳኔ ሃሳብ አቅርቧል።የውሳኔ ሃሳብኮሚቴው የፌዴራል የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የተከበሩ አቶ ቃሲም ፊጤ ዳኖ ያለመከሰስ መብት እንዲነሳ ዳግም የቀረበውን ጥያቄ የኮሚሽኑ መርማሪዎችን እና አቶ ቃሲም ፊጤ ዳኖን ጠርቶ በተናጠል በማነጋገር እንዲሁም አስፈላጊ ማስረጃ በመመልከት በዝርዝር የመረመረ ሲሆን፤ የፌዴራል የስነ ምግባር ፀረ ሙስና ኮሚሽን የጀመረው የሙስና ወንጀል ምርመራ ስራ ለማጠናቀቅ እንዲችል ያቀረበው ያለ መከሰስ መብት ይነሳ ጥያቄ በምክር ቤቱ የአሰራርና የአባላት ስነ ምግባር ደንብ ቁጥር 3/1998 አንቀጽ 6 መሰረት እንዲሁም በምክር ቤቱ መመሪያ ቁጥር 17 መሰረት ለድርጊቱ መፈፀም አመላካች ሁኔታዎች መኖራቸውን አረጋግጧል።በዚህ መሰረት አባሉ በተጠረጠሩበት ጉዳይ ቀርበው ቃላቸውን እንዲሰጡ ያለመከሰስ መብታቸው እንዲነሳ ኮሚቴው በሙሉ ድምፅ ተቀብሎታል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የትነበርሽ ንጉሴ ዝምታውን ሰበረችው አክራሪ ኦሮሞ ሀገር ከማፍረስ ሰከን ቢሉ ይሻላል:: አለማየት ወንጀል አይደለም አለማስተዋል ግን ስህተት ነው

ምንጭ – ሰንደቅ የዛሬ ረቡዕ እትም

Share