ችግሩ ወያኔን በማስወገድ ብቻ የሚፈታ አይደለም ! – ካለፈው የቀጠለ

ፈቃዱ በቀለ፣ ዶ/ር     

መስከረም 8፣  2015

መግቢያ

የተፈጠርነው እንደ እንስሳ  ለመኖር ሳይሆን ፣ የትክክለኛውን ዕውቀትና  የታታሪነትን    መንገድ ለማግኘትና ለመቀዳጀት ነው ።“ ዳንቴ

ዳንቴ ይህንን ያለው በ13ኛው ክፍለ-ዘመን የኢጣሊያን ህዝብ በድህነት፣ በተስቦ በሽታና በጦርነት፣ እንዲሁም ኑሮው ሁሉ ስለጨለመበት ደጉን ከክፉ መለየት ባልቻለበት ወቅትና፣ ማንኛውንም ለሰው ልጅ የሚሰቀንን አጸያፊ ድርጊት በሚያደረግበት ዘመን በአንክሮ ከተመለከተ በኋላ ነው። በእሱ ዕምነትም፣ ለዚህ ሁሉ ዋናው ምክንያት የሰው ልጅ አዕምሮ በጊዜው በነበረው ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ በመጣው ባህላዊ የአኗኗር ስልትና በመጥፎ ነገሮች ስለተወጠረና ደጉን ከክፉ ለመለየት የሚያስችለው ዕውቀት ስለሌው ነው። በዚህም ምክንያት የማሰብ ኃይሉ እጅግ ደካማ ስለነበር አርቆ ማሰብና ለምን በእንደዚህ ዐይነት ሁኔታ ውስጥ ለመኖር ተገደድኩ ብሎ ራሱን ለመጠየቅ አይችልም ነበር። በዳንቴ ምርምርና ዕምነት የሰው ልጅ ግን ራሱ በሚሰራው አፀያፊ ሁኔታና አልፎ አልፎ በሚከሰት የተፈጥሮ አደጋ መሰቃየት ያለበት ሳይሆን፣ መንፈሳዊ ኃይል ያለውና የሚኖርበትንም ሁኔታ መለወጥ እንደሚችልና አካባቢውንም ገነት እንደሚያደርጋት የአምላኮች ኮሜዲ በሚለው ግሩም ስነ-ጽሁፉ ውስጥ ያመለክታል።

የዳንቴን ጥቅስ ትምህርታዊ አባባል ለመጥቀስ የተገደድኩበት ዋናው ምክንያት አንዳንድ ጊዜ ከምኖርበት፣ ከዚሁ ከአንድ የምዕራብ አውሮፓ ከተማ ወጣ ብዬ የገጠሩን ህዝብ የኑሮ ሁኔታ ስመለከትና ከአገራችን የገጠር ሁኔታና የህዝባችንን አኗኗር ጋር ሳወዳድር ነው። ራሴንም የምጠይቀው፣ እኛ በእግዚአብሄር አምላክ ተፈጥረናል በምንባለው በጠቅላላው የሰው ልጅ ዘንድ የአስተሳሰብና የድርጊት ለውጥ መኖሩን ሳወጣና ሳወርድ፣ አንደኛው አካባቢውን ወደ ገነትነት መለወጥ ሲችል፣ ሌላው ደግሞ እግዜአብሄር የለገሰውን የተፍጥሮ ጸጋ በማውደም ከእንስሳ ያላነሰ ኑሮ መኖሩን ስመለከትና በጭንቅላቴ ውስጥ ሳወጣ ሳወርድ ነው።  ጀርመን አገር ስኖር ብዙ ዐመታት ባስቆጥርም፣ በመጀመሪያዎቹ አስር ዐመታት ይህንን ያህልም የአገራችንን ሁኔታ ከጀርመኑ ወይም ከአንዳንድ የአውሮፓ አገሮች ጋር ለማወዳደር ሃሳቡም ሆነ ግንዛቤውም አልነበረኝም። ከትምህርቴ ዓለም ባሻገር ራሴን ከተለያዩ ዕውቀቶችና ቲዎሪዎች ጋር የማገናኘትና፣ እስከተወሰነ ደረጃም ድረስ ዕውቀቱን ለመረዳት ዕድል ቢያጋጥመኝም፣ ተጨባጭ ከሆነው የቀን ተቀን ህይወቴ ጋር የተያያዘውን የቤትና የመንገድ አሰራር፣ የመናፈሻና የልጆች መጫወቻ ቦታዎች፣ የመብራትና የውሃ  እንዲሁም የመጸዳጃ  ጉዳይና፣ አያሌ የሰውን ልጅ ህይወት የሚነኩ ጉዳዮችን ጭንቅላቴ ውስጥ አስገብቼ ለማውጣትና ለማውረድ እስከዚህም ድረስ ደንታ አልነበረኝም። ጀርመን አገር ከመጣሁ ከሰላሳ ዐመታት በላይ ሲሆነኝ፣ በእነዚህ ዐመታት ውስጥ አንድም ጊዜ መብራት የተቋረጠበትና የውሃ ዕጥረትም የተከሰተበት ጊዜ በፍጹም አላጋጠመኝም። ቀኑ እየረዘመ ሲሄድ፣ ከቲዎሪ አልፌ በቴዎሪና በተጫባጩ የሰው ልጅ ኑሮ መሀከል ያለውን ሁኔታ ስመለከት የዕውቀት ትርጉሙ የመጨረሻ መጨረሻ ሌላ ነገር ሳይሆን የሰውን ልጅ ኑሮ ማሻሻልና፣  ለዚህ ደግሞ እያንዳንዱ ግለሰብ የመንፈስ ነፃትን በመቀዳጀት በሰማይ ላይ ሳይሆን በምድር ላይ ገነትን መመስረት እንዳለበት ልገነዘብ ችያለሁ።  ስለሆነም፣ ነጩ የአውሮፓና የአሜሪካ ህዝብ ብቻ ሳይሆን፣ ጥቁር አፍሪቃዊም፣ እኛንም ጨምሮ በማሰብ ኃይሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመስራት የኑሮውን ሁኔታ መለወጥና፣ አካባቢውንም ገነት ማድረግ አለበት የሚል ውሳኔ ላይ ከደረስኩኝ ከአስር ዐመታት በላይ ሆኖኛል። ይህ ብቻ ሲሆንም አንድ ግለሰብም ሆነ አንድ ህዝብ ነፃነቱን መቀዳጀት እንደሚችል ለመረዳትና ለመገንዘብ ችያለሁ።  በመሆኑም የሰው ልጅ ከእንስሳ የሚለየው ሞራላዊ፣ ስነ-ምግባራዊ፣ ባህላዊ፣ ጥበባዊና ከዚህም በመነሳት ተዓምር በመስራት በዕቅድና በተቀነባበረ መልክ የኑሮውን ሁኔታ ማሻሻል እንዳለበት በፈላስፋዎችና በሊትሬቸር ሰዎች ተመዝግቧል፤ በተግባርም ታይቷል። ታዲያ እኛን ምን ተሳነን? ምንስ ጎደለን?  የሚለት ጥያቄዎች ሁልጊዜ ያብከነክኑኛል።

ራሴን ከአውሮፓው የህብረተሰብ አወቃቀር ታሪክና ፍልስፍና ጋር ይበልጥ ማስተዋወቅ ከጀመርኩኝ  ከሃያ ዐመታት በላይ ሲሆነኝ፣ በዚያው መጠንም በአገሮች መሀከል ያለውን ልዩነት የማወዳደር ዕድል ይበልጥ አጋጥሞኛል ብል እንደግብዝነት አይቆጠርብኝም። ይሁንና ግን የባህል ሁኔታና የታሪክ ሂደት ለአንድ ህብረተሰብ ዕድገት ወሳኝ ሚናን እንደሚጫወቱ ሙሉ በሙሉ ባምንም፣ በሌላ ወገን ግን ራሴን እንደጠረጥር የሚያስገድደኝ ሁኔታ አለ። አንዳንድ የተበሳጩ ኢትዮጵያውያን ወንድሞቼ ጋር በምጫወትበት ጊዜ በእኔ አባባል ይህንን ያህልም አይረኩም። ምክንያትም እንድደረድርላቸው አይፈልጉም። በምሁር „መፈላሰፍም“ ስለማያራከቸው፣ በነጩና በኛው ዓለም መሀከል ያለውን ልዩነት ለመረዳት የሚፈልጉት በሌላና ብዙም ውጣ ውረድን በማይፈልግ ስሌት ነው። በአብዛኛዎቹ ዕምነት ወይም ግምት የነጭ ዘር ከስልጣኔ ጋር የተወለደ ሲሆን፣ እኛን ደግሞ እግዚአብሄር በድሎናል የሚል ነው። በእዚህ ዐይነቱ ማረጋገጫ የሌለው አባባል ባልስማማም፣ አንዳንድ ውጭ አገር ሰላሳና አርባ ዐመታት ኑረው ወደ አገራቸው የተመለሱ ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው ያላቸውን አመለካከትና ደንታ-ቢስነት ስመለከት ራሴን እንድጠረጥር ተገድጃለሁ። አንድ ሰው ውጭ አገር ሰላሳና አርባ ዐመታት ከተቀመጠ በኋላ የግዴታ የአስተሳሰብ ለውጥ ያመጣል ብዬ ስለማምን፣ ወደ አገሩ በሚመለስበት ጊዜ እስከተወሰነ ደረጃም ድረስ የአገሩ ሁኔታ እንዲቀየር አስተዋጾዖ ሊያበረክት ይችላል የሚል ዕምነት ነበረኝ። ለብዙ ዐመታ ሁኔታዎችን ከተከታተልኩኝና፣ ካወጣሁና ካወረድኩኝ በኋላ የተገነዘብኩት ነገር፣ ከውጭው ዓለም ወደ አገሩ የሚመልስ ኢትዮጵያዊ ራሱን አግሎ ከመኖር በስተቀር ለአገሩ ምንም ዐይነት አስተዋጽዖ እንደማያበረክት ነው።  የማነሳው ጥያቄ፣ ለመሆኑ እኛ ኢትዮጵያውያን  አንድን ነገር ተኮር አድርጎ የመመልከትና የማገናዘብ ኃይል አለን ወይ? ሁለተኛ፣ ከራሳችን ባሻገር ለአገራችን ዕድገትና እንዲሁም ለህዝባችን የኑሮ መሻሻል ምኞትና ፍላጎት አለን ወይ?  መልሱ ባጭሩ በራሳችን ዓለም የምንኖርና ለለውጥም ያልተዘጋጀን ነን የሚል ነው። ይሁንና ግን በሌላ ወገን ኢትዮጵያ አገሬ እያልን መዝሙርም እንዘምራለን፤ ባንዲራውንም ለብሰን እንጎድራደዳለን። እንደሚታወቀው ባንድ በኩል ለአገር ዕድገትና ስልጣኔ ደንታ-ቢስ መሆን፣ በሌላ ወገን ደግሞ ባንዲራ ማውለብለብና አገሬ አገሬ እያሉ መዘመር፣ አብረው ሊሄዱ የሚችሉ ነገሮች አይደሉም።

ስለሆነም ለአገሬ እታገላለሁ የሚልና፣ የዛሬውን አገዛዝ የሚጠላ አገር ወዳድ ነኝ ባይ ኢትዮጵያዊ ማንሳት ያለበት ጉዳይ አለ።  ይኸውም አንድ ሶስት ሺህ ዐመት ታሪክ ያለው አገርና ከአጭር ጊዜ በስተቀር የውጭ አገር ቅኝ ግዛት ያለሆነ ለምን የስልጣኔና የዕድገት ባለቤት ለመሆን አልቻለም? አገራችን ለምንስ ባለፉት አርባ ዐመታት በድህነትና በረሃብ እንድትታወቅ ተገደደች? የሚለውን አንስቶ መወያየት የሚያስፈልግ ይመስለኛል። ወደ አርዕስቱ ጋ ልመለስና፣ አብዛኛዎቻችን ዛሬውኑ ወያኔ ቢወገድ ችግሩ የሚፈታ የሚመስለን አለን። በእግዚአብሄርም ቁጣም ቢሆን የሁላችንም ዕምነት  የዛሬው ሰይጣናዊ አገዛዝ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጫንቃ ላይ እንዲላቀቅ እንመኛለን። መወገድም እንዳለበት ታሪካዊ ግዴታ እንደሆነ ይህ ጸሀፊም ያምናል። ይሁንና ግን መመለስ ያለብን፣ ለመሆኑ የችግሩን ምንጭ በደንብ ተረድተናል ወይ?  ሁለተኛስ፣ ደረጃ በደረጃ ህዝባችን የሚፈልገውን ነገር ለመመለስ በቂ ዝግጅት አድርገናል ወይ?  ችሎታውስ አለን ወይ?  እነዚህን መሰረታዊ ጥያቄዎች መመለስ ያለብን ይመስለኛል። እነዚህን መሰረታዊ ጥያቄዎች መመለስ ሳንችል፣ ይህ አገዛዝ ዛሬውኑ መወገድ አለበት ብንልና እንዳጋጣሚም ቢወገድ ፍጥጫ ውስጥና፣ ሌላ ችግር ውስጥ መውደቃችን አይቀርም። ስለዚህም እነዚህን የመሳሰሉትንና ሌሎችን ለአገር ግንባታ አስፈላጊ ናቸው የምንላቸውን ነገሮች አንስተን መወያየትና መልስም ለመስጠት መዘጋጀት መቻል አለብን ብሎ ይህ ጸሀፊ ያምናል። ይህንን ስናደርግ ብቻም ትግላችን የተሟላና ግቡንም ሊመታ እንደሚችል ግልጽ መሆን አለበት።

በዚህ ረገድ የህብረተሰባችንን ዋና ችግርና ዘለዓለማችንን በድህነትና በረሃብ እንድንታወቅና፣ መሳቂያና መሳለቂያ ያደረጉንን ነገሮች ለመረዳት እንድንችል ዘንድ የሰው ልጅ በጠቅላላው ሃሳብን የማፍለቅ ችሎታ እንዳለው ፣ ይሁንና ግን ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ይህንን ሊያደርግ እንደማይችል ጠጋ ብለን መመልከቱ ግንዛቤ ሊሰጠን ይችላል። በስልጣኔና በህብረተሰብ ዕድገትና ለውጥ ታሪክ ውስጥ ሃሳብን የማፍለቅና ሃሳብን ተግባራዊ ማድረጉ የቱን ያህል ለአንድ ህዝብና አገር በሰላምና በነፃነት መኖር እጅግ አስፈላጊዎች መሆናቸውን በህብረተሰብ ታሪክ ውስጥ የተረጋገጠ መሆኑን መረዳት እንችላለን።  በሌላ ወገን ደግም በየጊዜው አዳዲስ ሃሳቦችን ማፍለቅና በተግባርም መተርጎም የማይችል ህዝብ የድህነትና የኋላ-ቀርነት ሰለባ መሆኑን እንመለከታለን።

ሃሳብን ማፍለቅና ሃሳብን ወደ ተግባር መተርጎም የስልጣኔ ዋናው ቁልፍ መሆኑን የመረዳቱ ጉዳይ !

በመጀመሪያው ጽሁፌ ላይ የአዕምሮንና የመንፈስን ሚና እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ ለመተንተን ሞክሬያለሁ። አዕምሮና መንፈስ በጭንቅላታችን ውስጥ የሚገኙ፣ አውቀንም ሆነ ስናውቅ የተለያዩ ሃሳቦችን ማፍለቅ እንደሚችሉ ለመጠቆም ሞክሬያለሁ። ይሁንና ግን አዕምሮና መንፈስ ዕውቀትንና ጥሩ ሃሳብን የማፍለቅ ችሎታ ቢኖራቸውም፣ በአጠቃላይ ሲታይ የሰው ልጅ በስሜት፣ አልፎ አልፎ ደግሞ በደመ፟-ነፍስ የሚመራ ነው። ይህም ማለት በጣም ጥቂት ሰዎች ብቻ ናቸው በመንፈሳቸው ኃይል በመመራት አርቆ-አሳቢነትን በማስቀደም ደጉን ከክፉ መለየት የሚችሉት። ትክክለኛ ዕውቀትንም በማፍለቅ የሰው ልጅ በመንፈስ ኃይሉ ራሱን ነፃ ማውጣትና የተፈጥሮ አደጋ ሰለባ እንዳይሆን መንገዱን የሚያሳዩት በመንፈሳቸው የበላይነት የሚጠቀሙና አርቆ-አሳቢነትን የሳይንስ ግኝት መሳሪያ ማድረግ የሚችሉ ጥቂት ሰዎች ብቻ ናቸው። የስልጣኔን ታሪክ በምናገላብጥበት ጊዜና፣ ካለብዙ ውጣ ውረድ ራሳችንን ስንጠይቅ የምንገነዘበው ነገር ፍልስፍናንና ጥበብን ማፍለቅ የቻሉት ልዩ ዐይነት ተሰጥዖ ያላቸው ሰዎች ብቻ ናቸው።  በሌላ ውገን ግን እንደፈላስፋዎችም ባይሆን የሰው ልጅ በደመ-ነፍስ በመመራት አዳዲስ መሳሪያዎችን መፍጠር እንደሚችልና የአኗኗር ስልቱን እንደሚለውጥ መገንዘብ ይቻላል።  ይሁንና ግን በአንድ አካባቢ የህዝብ ቁጥር እየጨመረ ሲመጣና ሀብትም በጥቂት ሰዎች ቁጥጥር ሲውል አንድ ህዝብ በመጀመሪያው ዕድገቱ ሊገፋበት አይችልም። ባህላዊ የአኗኗር ልምድና ርዕዮተ-ዓለም፣ በተለይም ደግሞ በተለያዩ ነገሮች ማምለክና፣ የራስንም ዕድል ከአምልኮት ጋር ማያያዝ በአንድ አካባቢ የሚኖር ህዝብ የማሰብ ኃይሉን እንዳይጠቀም አግደው እንደሚይዙት በጥናት የተረጋገጠ ነው። ስለሆነም ከአንድ አካባቢ ወይም ከአንድ የህብረተሰብ-ክፍል የሚፈልቁ ልዩ ልዩ አስተሳሰቦች እንደየጥራታቸውና እንደየአተረጓገማቸው የሰውን ልጅ የማሰብ ኃይል መቆጣጠር ይችላሉ፤ ወይም የማሰብ ኃይሉን በማዳበር ታሪክን እንዲሰራ ያግዙታል። ስለሆነም የሰውን ልጅ ዕውቀት አመጣጥና አፈላለቅ በመረዳትና የተፈጥሮንም ምንነት በመተርጎም ረገድ በፈላስፋዎች ዘንድ ከፈተኛ ክርክር ተካሂዷል። በተለይም በአሁኑ ዘመን የሰው ልጅ ቁጥር በበዛበትና የተለያዩና የተዘበራረቁ ኤንፎርሚሽኖች፣ እንደዚሁም ገንዘብና የፍጆታ አጠቃቀም የሰውን ልጅ አዕምሮና መንፈስ ወጥረው በያዙበት ዘመን በጣም ጥቂት ሰዎች ብቻ ነው በአርቆ-አሳቢነት ሃይል የሚመሩና ራሳቸውን መቆጣጠር የሚችሉት።

ይህ በእንደዚህ እንዳለ፣ የሃሳብን አፈላለቅና ተግባራዊነት መረዳቱ ላለንበት የተወሳሰበ ችግር እስከተወሰነ ደራጃ ድረስ መልስ ሊሰጠን ይችላል ብዬ እገምታለሁ። በፍልስፋና ዓለም ውስጥ ሃሳብ(Idea) ከፍተኛ ትርጉም አለው። ይህም ማለት በአጠቃላይ ሲታይ በተግባር ሊመነዘር የሚችለው ተጨባጭ ነገር ሁሉ ከአዕምሮአችን በመንፈስ ኃይል የሚፈልቅ ነው። ለምሳሌ ካለብዙ መጨነቅ(Intuitively ) የሰው ልጅ የፈጠራቸውን ነገሮች ሁሉ ስንመለከት ከተፈጥሮና በተፈጥሮ ውስጥ ካሉት ነገሮች በስተቀር ሁሉም ነገሮች በሰው ልጅ የማሰብ ኃይል ነው የተፈጠሩት። ለምሳሌ ከብዙ መቶ ሺህ ዐመታት በፊት የሰው ልጅ ዝም ብሎ በጫቃ ውስጥና በዛፍ ላይ በሚኖርበት ዘመን ጎጆ የመቀልበስ ነገር ታየውና ራሱን ከብርድና ከአደጋ ለመከላከል ሲል መጠለያን መስራት ተገደደ። ቀስ በቀስም ሌሎችን ነገሮች መስራት እንደሚችል ሲረዳ የተፈጥሮ ተገዢ ከመሆን ይልቅ እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ ተፈጥሮን እንደሚቆጣጠር ወይም በተፈጥሮ ውስጥ ያሉ ነገሮችን እያወጣና መልክና ቅርጽ በመስጠት ኑሮውን እንደሚያሻሽል ተገነዘበ። እንደዚሁም ጠረቤዛና ወንበር እንዲሁም አልጋ ሳያይ በራሱ የማሰብ ኃይል መፍጠር ቻለ። ባጭሩ፣ ይህ የሚያሳየን የሰው ልጅ ሃሳብን ወይንም ዕውቀትን ከጭንቅላቱ በአዕምሮውና በመንፈስ ኃይሉ ማፍለቅና ሃሳቡንም ወደ ተግባር ለመመንዘር እንደሚችል ነው። በዚህ መልክ የሰው ልጅ የቋንቋ፣ የፊደልና የጽሁፍም አፍላቂ ነው። ስለሆነም ርስ በርሱ በመገናኘትና ሃሳብ ለሃሳብ በመለዋወጥ ከድሮው በተሻለ ሁኔታ አዲስ ህብረተሰብ መፍጠር ይችላል። እንዲህ እያለ እየሄደ አዳዲስ መሳሪያዎችንና የፍጆታ ዕቃዎችን በማምረትና የስራ-ክፍፍልን በማዳበር ወደ ንግድ ልውውጥ የሚያመራና ገንዘብን በመፍጠር የንግድ ግኑኝነትና ልውውጥ እንዲፋጠን የሚያደርግ ነው።  ይህ ሁሉ ነገር የተፈጠረው እንደዛሬው የአካዳሚ ዕውቀትና ዩኒቨርሲቲዎች ባልተስፋፉበት ዘመን ነው።

ይሁንና ግን አንድ ህብረተሰብ የተወሰኑ ነገሮችን ከፈጠረና ወይም ካገኘ በኋላ ከዚያ በላይ ገፍቶ ሊሄድ እንደማይችል ደግሞ በታሪክም የታየ ነው። ለምን አንድኛው ከሌላው ቀድሞ እንደሚሄድ፣ በመጀመሪያ የስልጣኔ ባለቤት የሆነው በሌላው እንደሚቀደምና፣ ኋላ ብቅ ያለው ከፍተኛ ምጥቀትን በማግኘት የተሻለ ህብረተሰብን እንደሚመሰርትና ህግና ስርዓትንም በማውጣትና በመደንገግ ለሰው ልጅ ኑሮ መልክ እንደሚሰጠው በተለያዩ ተመራማሪዎች በተለያየ መልክ ይተረጎማል። በተጨማሪም በተለያዩ ህዝቦችና ህብረተሰቦች ዘንድ የተለያየ የአኗኗር ስልትና ነገሮችን በመረዳት ረገድ ለምን ልዩነት ይኖራል ? በሚለው ሃሳብ ላይ የተለያየ ትርጓሜ ይሰጣል።

በፍልስፍናና የህብረተ-ባህል(Socio-Cultural studies) ጥናት መሰረት ለዚህ የተለዩየ ምክንያቶች ይሰጣሉ። ብዙ ጥናቶች እንደሚያረጋግጡት ከሆነ፣ አንዳንድ ዘረኛ ፈረንጆች እንደሚሉት የዘር ልዩነት ጉዳይ ሳይሆን የተለያዩ ሃሳቦች ሲገናኙና የተለያዩ ህዝቦችም ሲጋቡና ሲዋለዱ የተሻለ ሃሳብና ዕውቀትን ማፍለቅ እንደሚችሉ ነው። እንደሚባለውና እንደተረጋገጠውም የመጀመሪዉ የሰው ልጅ የተገኘው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። ዲዮዶርስ የሚባለው የግሪኩ የታሪክ ጸሀፊ እንደሚነግረን ከሆነ ለግብጽ ስልጣኔ መነሻ ዋናው ምክንያት ኢትዮጵያውያን እንደሆኑና፣ የመጀመሪያውም የግብፅ ፋራዖኖች ከኢትዮጵያ ፈልሰው የሄዱ እንደሆኑ ይነግረናል። የመጀመሪያዎቹ ኢትዮጵያውያን ፋራዖኖች ከኢትዮጵያ ፈልሰው ሲሄዱ ህግንና የሂሳብንም ሆነ ሌሎችን ዕውቀቶችን ይዘው እንደሄዱ በሚገባ ሰፍሯል። ይህ ከሆነ በኋላ ግን ኢትዮጵያ በዚያው እንዳለች ስትቀር የግብጽ ስልጣኔ ከፍተኛ ደረጃ በመድረስ፣ ፍልስፍና፣ አስትሮኖሚና ማቲማቲክስ፣ እንዲሁም የአርክቴክቸር ዕውቀቶች እዚያ ሊዳብሩና ሊስፋፉ ችለዋል። የግብጽ ስልጣኔ ለብዙ ሺህ ዐመታት የበላይነትን ከያዘ በኋላ ውስጡ ባለው የታፈነ ስርዓት የተነሳና ዕውቀት ከቀሳውስጡ ወጥቶ መነጋገሪያና መከራከሪያ እንዲሆን ባለመደረጉና፣ ከዚህ በላይ ደግሞ የህዝቡም ቁጥር አነስተኛ ስለነበር ስልጣኔው በዚያው መልክ ሊቀጥልና ከፍተኛ ደረጃ ላይ ሊደርስ አልቻለም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ክርስቶሳዊ ያልሆነ ክርስቶሳዊነት! 

ወደ ግሪክ ስንመጣ ግን ሁኔታው የተለየ ይሆናል። በመጀመሪያ ደረጃ የመጀመሪያዎች የግሪክ ፈላስፋዎች፣ ፕይታጎራስ፣ ታለስ፣ ሶሎንና ፕላቶ ዕውቀታቸውን ግብፅ ሄደው እንደቀሰሙ ማርቲን በርናልና የሴኔጋሉ ምሁር አንታይ ዲዮፕ በሚገባ አረጋግጠዋል። ሌሎችም እንደዚሁ በዚህ ማስረጃ ይስማማሉ። ይህ በእንደዚህ እንዳለ ከተለያየ ቦታ ፈልሰው የመጡ ህዝቦች የሚገናኙባት አዮን የምትባለው ደሴት ላይ የመጀመሪያው የግሪክ ስልጣኔ መዳበርና አዲስ ዕምርታን እንዳገኘ በታሪክ የተረጋገጠ ነው። በዚህ መልክ የግሪኩ ስልጣኔ የተጠነሰሰው ከህንድና ከግብጽ በመጣው ፍልስፋና አማካይነትና፣ ግሪክም የተለያዩ ህዝቦች መናኸሪያ እንደነበረችና፣ በተለይም ደግሞ ከግብፅ የመጡ ጥቁር አፍሪቃውያን ለስልጣኔው ዕምርታ እንደሰጡት የተረጋገጠ ጉዳይ ነው።

ለግሪክ ስልጣኔ መነሾ ይህ ብቻ አይደለምም ዋናው ምክንያት።  በግብጽ ስልጣኔ ዘመን ዕውቀት ከቀሳውስቱ የሚያልፍ አልነበረም። እንደ ምስጢር የተያዘና ህዝቡ እንዳያውቀው በመደረጉ የግብጽ ስልጣኔ እምርታን ሊያገኝ አልቻለም። ወደ ግሪክ ስንመጣ ግን፣ የግሪክ ፈልሳፎች ፍልስፍናውን ወደ ውጭ በማውጣት ወጣቱን ማስተማሪያና መከራከሪያ አደረጉት። በአንድ ነገር ላይ ብቻ ረክቶ እንዳይቀር ጥያቄን በጥያቄ እንዲያነሳ በማድረግ ዕውነትን  ከውሸት ሊለይ የሚችልበትን ዲያሊክቲካዊ የምርምር ዘዴ እንዲቀዳጅ አደረጉት። ከእንግዲህ ወዲያ በስሜት የሚገፋ መሆኑ ቀርቶ በሎጂክና በምርምር በመመራት የተሻለ ነገር ማግችትና መፍጠር እንደሚችል አስተማሩት።  አንድን ማዕከለኛ ነገር ከአንድ ነገር ነጥሎ በማውጣትና እንደገና ደግሞ በነገሮች መሀከል መተሳሰር እንዳለ በማሳየት ይህ የምርምር ዘዴ ለሳይንስ መሰረት እንዲጥል ተደረገ። ከዚህ በኋላ የግሪክ ሳይንቲስቶች ከዚያ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ አዳዲስ መሳሪያዎችን መፍጠርና ለመጀመሪያ ጊዜ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ጥበባዊ የከተማ ዕቅድ በማውጣት  ዘመናዊ የአኗኗር ዘዴን ፈጠሩ። ለመጀመሪያ ጊዜ መሻሻልና (Progress) ዘመናዊነት (Modernity) በማሰብና በምርምር ኃይል እንደሚደረስባቸው አረጋገጡ። አርኪሜዲስና ከሱ በፊት የነበሩ ሊቃውንት በመንፈስና በማሰብ ኃይል እየተመሩ ከምንም በመነሳት አዳዲስ መሳሪያዎችን ሲፈጥሩና እንደ አሊክሳንደሪያ የመሳሰሉትን ከተማዎች ሲገነቡ ማረጋገጥ የቻሉት ገንዘብ ሳይሆን የዕድገት መነሾ የሰው ልጅ የማሰብ ኃይል መሆኑን ነው። የሰው ልጅ የማሰብ ኃይሉን ማንቀሳቀስ ከቻለና ለመሻሻልም ፍላጎት ካለው ምንም ሳይኖር አዲስ ነገር መፍጠር እንደሚችል የግሪክ ፈላስፎች ማረጋገጥ ችለዋል። ከዚያ በኋላ በጋሊልዮና በኒውተን የተፈጠሩት መሳሪያዎችና ግኝቶች በግሪክ ስልጣኔና፣ በተለይም ደግሞ በአርኪሜዲስ  ዕውቀት ላይ የተመሰረቱ ናቸው። ይሁንና የአውሮፓው ስልጣኔ ከመነሳቱና ዕምርታን ከማግኘቱ በፊት ከክርስቶስ ልደት በኋላ በስምንተኛው ክፍለ-ዘመን ባግዳድ የሳይንስና የፍልስፍና መዲና እንደነበረችና፣ በዚያ ዘመንም አንድ ሚሊዮን ህዝብ ይኖርባት እንደነበር የታወቀ ነው።  የአውሮፓ ስልጣኔ አነሳስ እነዚህን መሰረት ያደረገና እየዳበረ የመጣ ለመሆኑ ቀደም ብለው የወጡም ሆነ አዲስ ጥናቶች ያረጋግጣሉ።

ክዚህና ከአውሮፓው ስልጣኔ የምንማረው ምንድን ነው፟?  በአንድ አካባቢ አዲስ ዕውቀት ወይም ስልጣኔ ቢገኝም ከፍተኛ ዕምርታን ሊቀዳጅና ህብረተሰብአዊ ለውጥ ሊገኝ የሚችለው የተለያዩ ህዝቦች ስልጣኔን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ይዘው ሲሄዱና አዲሱ ቦታ ተቀማጭ ሲሆኑና ከኗሪው ህዝብ ጋር በመጋባት ሲቀላቀሉ ነው።  ይህ እንግዲህ የመጀመሪያው ግሎባላይዜሽን ሲሆን፣ ጤናማ አስተሳሰብ በነበረበትና፣ አንደኛው ህዝብ ሌላውን በበላይነት በመቆጣጠር ሀብቱን በመዝረፍና በመጨቆን ዕድገትን በተወሰነ ቦታና የህብረተሰብ ክፍል ብቻ እንዲሽከረከር በማያደርግበት ዘመን ነበር። በሌላ አነጋገር፣ ተንኮል በማይታሰብበት ዘመንና፣ ጥበብንና ሳይንስን ለሰው ልጁ ሁሉ ማካፈል ያስፈልጋል ተብሎ በሚታሰብበት ጤናማ አስተሳሰብ በሰፈነበት ዘመን ነው። ወደ አውሮፓው ታሪክና ዕድገት ስንመጣ ግን፣ በተለይም እንግሊዝ የበላይነትን መቀዳጀት ስትጀምርና በአዲስ የፍልስፍና አስተሳሰብ ስትመራና የሌሎች አውሮፓን አገሮች ምሁራን ስትመርዝ ዕውቀት በተወሰነ ክልል ብቻ እንዲሽከረከር ይደረጋል። በተለይም ከአስራስምንተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ የዘረኝነት ቲዎሪ በመስፋፋት የጥቁር ዘር ሳይንስንና ፍልስፍናን ሊያፈልቅ አይችልም የሚለው በመስፋፋት የነጭ-ዘር የበላይነት እንዳለው ለማረጋገጥ ጥረት ይደረጋል። ይህ ጉዳይ በሳይንስ ያልተረጋገጠ ቢሆንም የነጭ ዘር እንደ አምላክ እንዲታይ አብቅቶታል። በሁላችንም ዘንድ የህሊና ተጸዕኖ በማሳደር እስከዛሬ ድረስ ሲያሰቃየንና የዝቅተኛ ስሜት እንዲያድርብን በማድረግ ለመሸማቀቅ በቅተናል። በራሳችን ላይ ዕምነት እንዳይኖረን ተደርገናል። በተለይም በአውሮፓው ምድር ውስጥ ብሄረተኝነት(Nationalism) መስፋፋት ከጀመረበት ከ19ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮና የአፍሪቃን የጥሬ-ሀብት ለመቀራመት ስትራቴጂ ከተቀየሰ ወዲህና፣ ብዙ የአፍሪቃ አገሮች በቅኝ-ግዛት አስተዳደር ውስጥ እንዲወድቁ ከተደረጉ በኋላ የተወሰደው እርምጃ ሁሉ የአፍሪቃን ህዝብ የኑሮ ሁኔታ ማዘበራረቅና የማሰብ ኃይሉንም በማዳከም ዘለዓለሙን በዝቅተኝነት ስሜት ወድቆ እንዲኖር ማድረግ ነው። ይህ ዐይነቱ ስትራቴጂ ለኛም በመትረፍ የማሰብ ኃይላችን እንዲጠብና ለዕድገትና ለስልጣኔ የሚሆነውን መሰረት በመጣል ከድህነትና ከረሃብ እንዳንላቀቅ ተደርገናል። በቡሃ ላይ ጆር ደግፍ እንዲሉ ፊዩዳላዊ አስተሳሰብና የተበጣጠሰ የካፒታሊዝም የፍጆታ አጠቃቀምና የምርት ክንዋኔ አንድ ላይ በመጣመር የአስተሳሰብ አድማሳችንን ለማጥበብ በቅተዋል።

 

የማሰብ ነፃነት፣ ሃሳብን መግለጽና የአስተሳሰብ  አንድነት ህብረተስብአዊ ኃይል መሆናቸውን መረዳት !

በአውሮፓ ታሪክ ውስጥ የግሪክ ስልጣኔ ብቅ ካለና ከዳበረ ወዲህ በነጻ ማሰብ፣ ሳይፈሩና ሳይቸሩ ሃሳብን መግለጽ፣ መከራከርና ለማሳመንም ሆነ ለማመን መሞከር፣ ከዚያም በኋላ ወደ አንድ አስተሳሰብ ላይ መድረሰ መሰረታዊ የስልጣኔ ጉዳይ ሆኗል።  ስለሆነም ለሶክራተስም ሆነ ለፕላቶ፣ እንዲሁም ለአርስቲቶለስ በተከታታይ ደቀ መዝሙሮችን ማፋራት ከባድ አልነበረም። በየጊዜው ብቅ የሚሉት ፈላሳፋዎችና ሳይንቲስቶችም በመንፈስ ኃይል ተውጠው የሰውን ልጅና ተፈጥሮን በማገናኘት ሚዛናዊ የሆነ ስርዓት ለመገንባት ችሎታም ሆነ ፍላጎት ነበራቸው። ዋናው ምኞታቸውም ሆነ ምርምራቸው በመጀመሪያ ደረጃ የራሳቸውን ፍላጎት ለሟሟላት ሳይሆን፣ የሰው ልጅ አርቆ-የማሰብ ኃይሉን በመጠቀም በመስማማትና በመተባበር ጤናማና ጥበባዊ ህብረተሰብ ለመገንባት እንደሚችል መንገዱን ማሳየት ነበር። ስለሆነም መንፈሳዊውና የማቴርያላዊ ዓለም አንድ ላይ ሊጓዙ የሚችሉበትና፣ የሰው ልጅም በመንፈስ ኃይል እየተመራ ራሱን በመቆጣጠር አዲስና ሚዛናዊ የሆነ ህብረተሰብ መመስረት እንዳለበት ማስተማር ነበር። በተለያየ ጊዜ ብቅ ባሉት የግሪክ ፈላስፎች ዘንድ የአመለካከት ልዩነት ቢኖርም የሚስማሙበት ነገር አንድ ህብረተሰብ ልክ እንደኮስሞስ የተሰተካከለና በስርዓት የሚመራ ህብረተሰብ መመስረት አለበት በሚለው ላይ ነው። ሌላው የሚስማሙበት ነገር፣  በአጠቃላይ ሲታይ የሰው ልጅ አርቆ-የማሰብ ኃይሉን ለመጠቀምና ራሱን በራሱ ለማግኘት ብዙ መቶ ዐመታት እንደሚፈጁበት ነው። ይሁንና አንድ ህብረተሰብ ትክክለኛውን ዕውቀት ካገኘና አርቆ-የማሰብ-ኃይሉን ካስቀደመ ስልጣኔን በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊቀዳጅ እንደሚችል በአንዳንድ የህብረተሰብ ታሪክ ውስጥ የተረጋገጠ ነው። በሌላ ወገን ግን  በአንድ አገር የሚኖር ህዝብ እንደ አንድ ኃይል የሚታይ ቢሆንም፣ ዋናው መነሻቸው ግለሰብአዊ  ነፃነትና ራስን በራስ ማግኘት የሚለው መሰረተ-ሃሳብ ለስልጣኔ ቁልፍ እንደሆነ ያሰምሩበታል። ይህ ዐይነቱ ግለሰብአዊ ነፃነት ግን ስግብግብነትንና የራስን ፍላጎት ማሟላት የሚለውን የሚያስቀድም ሳይሆን፣ የየግለሰቡን ነፃ አስተሳሰብ አፍላቂነትና የአዕምሮንና የመንፈስን የበላይነት ለማሳየት ነው። በመሆኑም ግለሰቦች ነፃና ሃሳብ አፍላቂዎች እንዲሁም በራሳቸው የሚተማመኑ መሆናቸውን የሚያመለከት ከዕብነ-በረድ የተሰራ የሰው ምስል ሀውልት በግሪክ ስልጣኔም ሆነ በሬናሳንስ ዘመን የተስፋፋ ነበር።

ይህ የማሰብ ነፃነት ግን በካቶሊክ ሃይማኖት የበላይነት ከሰባት መቶ ዐመታት በላይ ይታፈናል። ውጤቱም በአውሮፓ ምድር ውስጥ የተስቦ በሽታ መስፋፋትና በድህነት ዓለም ውስጥ መኖር ነበር። ይህ ሁኔታ ግን በሬናሳንስና በሬፎርሚሽን ኃይል ይለወጣል። በተለይም በጀርመን ምድር ማርቲን ሉተር በመነሳትና የካቶሊክ ኃይማኖትን የበላይነት በመቃወም እያንዳንዱ ግለሰብ መጽሀፍ ቅዱስን ማንበብና በራሱም አርቆ የማሰብ ኃይል መመራት እንዳለበት ያውጃል። ለመጀመሪያ ጊዜም መጽሀፍ ቅዱስን ከላቲን ወደ ጀርመንኛ ተርጉሞ በማሰራጨት ለጀርመን ቋንቋ ከፍተኛ ዕምርታን ይሰጠዋል። እስከ አስራአምስተኛው ክፍለ-ዘመን ድረስ በየክልሉ በራሱ ዲያሌክት ብቻ ይግባባ የነበረውና በሃይማኖት ይበጣበጥ የነበረው የጀርመን ህዝብ አንድ የመግባቢያ ቋንቋ ያገኛል። በጀርመንኛ የተተረጎመውን መጽሀፍ ቅዱስን ሲያነብ የማሰብ ኃይሉ ከፍ ይላል። ዐይኑ ይከፈታል። ዝም ብሎ የሚነዳ ህዝብ ሳይሆን ማሰብ የሚችልና የሚጠይቅ፣ እንዲሁም በምድር ላይ የራሱ ነፃነት ያለው መሆኑን ይገነዘባል።

በጀርመን ምድር የተከሰተው የማሰብ ነፃነትን መቀዳጀት ቀስ በቀስ ለጀርመን ሊትሬቸርና ለአዲሱ የጀርመን አዲያሊስት ፍልስፍና መንገዱን ይከፍታል። የተለያዩ ፈላስፋዎች ብቅ ብቅ በማለት የተፈጥሮንና የህዋን ምንነት በመመርመር ለጀርመን ህዝብ አዲስ የአስተሳሰብና የኑሮ ፈለግ ይቀዱለታል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኑሮ በዘፈቀደ መሆኑ ቀርቶ በአርቆ አስተዋይነት እየታሰበና እየታቀደ፣ መንደሮችም ሆነ ከተማዎች በዕቅድ እየተሰሩ የሰው ልጅ በሰማይ ላይ ሳይሆን በምድር ላይ ገነትን እንደሚመሰርት ያረጋግጣሉ። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ጀርመን የአሳቢዎችና የገጣሚዎች አገር በመሆን አዲስ ዕምርታ ይታይባታል። በተለይም በቫይማር ከተማ ግንባታ የተረጋገጠው ይህ ዐይነቱ የማሰብና የግጥም ኃይል አንድ ላይ በመጣመራቸው ነው። በዚህ ዐይነቱ ሂደት ውስጥ የተለያዩ አስተሳሰቦች ቢከስቱም፣ እነዚህ የተለያዩ አስተሳሰቦች ወደ ርስ በርስ ግጭት ያመሩበት ሁኔታ አልነበረም። በተቻለ መጠን ለመግባባትና ለመደማመጥ መሞከር፣ በዚያም መሰረት በአንድ መሰረታዊና ሳይንሳዊ በሆነ ነገር ላይ በመስማማት ቲዎሪን ወደ ተግባር መመንዘር ነበር። በግሪኩም ሆነ በጀርመኑ የፍልስፍናና የሳይንስ ታሪክ ውስጥ ካለ ፕሪንስፕል መመራት ቦታ አልነበራቸውም። ተንኮለኝነት፣ ምቀኝነትና በሆነው ባልሆነው ወደ ግጭት ማምራት የሚታወቁ አልነበሩም። ማጭበርበርና ለራስ ጥቅም ብቻ መሽቀዳደምና ሌላውን ማዳካም የኑሮአቸው ፍልስፍና አልነበረም።  ሃሳባቸው ወደ እግዚአብሄር የሚጠጋ በመሆኑ በልዩ የመንፈስ ኃይል እየታገዙ ህብረተሰብአዊ ኃላፊነታቸውን መውጣት ነበር ዋናው ዓላማቸው። በአገራችን የተለመደው ዐይነት ሽወዳና እጅግ የደቀቀ አስተሳሰብ እንዲሁም ህብረተሰብን አዘበራርቆ ጥሎ መጥፋት የሚታወቅ አለነበረም። ፈላስፋዎችና ሳይንቲስቶቹ በልዩ መንፈስ የሚመሩ ስለነበር ዘለዓለማዊ ዕምነታቸውና ዓላማቸው የሰውን ልጅ የመንፈስ ኃይል ማዳብርና አርቆ አሳቢም መሆኑን እንዲገነዘብ ማድረግ ነበር። በተለይም የካንትን የህይወት ታሪክና ስራውን ያነበበ ሰው የሚረዳው፣ ይህ ታላቅ ፈላስፋ በእርግጥም ህይወቱን በሙሉ በምርምር ያሳለፈና፣ የህይወት ዕቅዱም ስነ-ስርዓትን የያዘና በሌላ ዓለም ውስጥ ይኖር የሚያስመስለው ነበር። የላይብኒዝም የሞናድ(Monad) ቲዎሪ የሚያረጋግጠው የሰውን ልጅ የማሰብ ኃይል ነው። በተለይም የእንግሊዝ ኤምፕሪሲስቶችን ወይም በዛሬው አባባል የሊበራል አስተሳሰብ ያላቸውን ምሁሮች የተሳሳተ አመለካከት ለመጣል የደረሰበት ማረጋገጫ የሰው ልጅ ጭንቅላት ውስጣዊ-ኃይል እንዳለውና ራሱን በራሱ በማንቀሳቀሰ አንድን ነገር እንደሚፈጥር ነው። ስለሆነም በእሱ የሞናድ ቲዎር መሰረት ትንሿ ህዋስ ብትሆንም ውስጣዊ-ኃይል ያላትና በራሷ ውስጣዊ የመንቀሳቀስ ኃይል ከሌለች ህዋሶች ጋር በመተሳሰር ልዩ ነገር እንደምትፈጥር ነው ለማረጋገጥ የቻለው። በሌላ አነጋገር ዕውቀት ከውጭ ወደ ወደ አዕምሮአችን ውስጥ የሚገባ ሳይሆን በማሰብ ኃይልና በምርምር ከውስጥ የሚፈልቅ ነው። የላይብኒዝ የሞናድ ቲዎሪ የፕላቶንን የዕውቀት አፈላለቅ ያረጋገጠ ነው ማለት ይቻላል።

ከዚህ ሁሉ የምንረዳው ምንድ ነው? በመጀመሪያ የሃሳብ ነፃነት በማንም ኃይል የሚሰጥ ሳይሆን ከሰው ልጅ ጋር የተፈጠረ ነው። ስለዚህም የሰው ልጅ የሚናገርበትና ሃሳቡን የሚገልጽበት አንደበት አለው። ሁለተኛ፣ ማንኛውም ሰው በአርቆ-አሳቢነትና በፕሪንስፕል በመመራት ወደ አንድ የጋራ አስተሳሰብ ላይ መድረስ ይችላል። በሳይንስና በፍልስፍና ዓለም ውስጥ የተለያዩ ሀቆች ወይም ዕውነተኛ ነገሮች የሉም። ሁል ጊዜ ሊኖር የሚችለው አንድ ሀቅ ወይም አንድ ዕውነት ብቻ ነው። ይሁንና ግን የተለያዩ ፈላስፋዎች የሃሳብና የዕውቀትን የመፍለቅ ጉዳይ በተለያየ መልክ ስለሚተረጉሙትና፣ በሃሳብ ወይም በዕውቀት ምንጭ ላይ ስምምነት ስለሌለ የሃሳብ ልዩነቶች ይፈጠራሉ። ለምሳሌ የሰው ልጅ ከዕውቀት ጋር የተፈጠረ ነው፣ ይህንንም በማሰብ ኃይሉ ወደ ውጭ ማውጣት አለበት በሚለው ፕላቶናዊ አስተሳሰብና፣ የለም የሰው ልጅ ዕውቀት ከውጭ በሚታየው ነገር ላይ የተመሰረተና እሱም ወደ አዕምሮ ውስጥ በመግባትና በመብላላት እንደገና ወደ ዕውቀት የሚመነዘር ነው በሚለው ላይ የአስተሳሰብ ልዩነት ይኖራል። ይህ ጉዳይ በተለይም በአስራስድስተኛውና በአስራሰባተኛው ከፍለ-ዘመንና፣ ከዚያም በኋላ እስከ አስራዘጠነኛው ክፍለ-ዘመን ድረስ ፈላስፋዎችን ሲያከራክር የቆየና፣ የመጨረሻ መጨራሻም በካፒታሊዝም አሸናፊነት የሶፊስቶች የበላይነት የነገሰበትን ሁኔታ እነመለከታለን። ይህ ማለት ግን ሶፊስቶች ወይም የማቴርያላዊ ዓለም ትክክለኛ ነው ማለት ሳይሆን፣ በኃይል አሰላለፍ ለውጥ የተነሳ የበላይነትን የተቀዳጀው ኃይልና ከሱ ጋር ያበሩ ወይም ጠበቃ የቆሙ ምሁሮች ሌላውን የህብረተሰብ ክፍል ተገዢያቸው ለማድረግ  የሚጠቀሙበት መሳሪያና በዓለም አቀፍ ደረጃ አማራጭ የሌለው ሆኖ የተወሰደ ነው። ዛሬ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን ድህነት መስፋፋት፣ የሀብት ዘረፋና ጦርነት፣ እንዲሁም የህዝቦችን መፈናቀል ስንመለከት በዓለም አቀፍ ደረጃ ላይ የተስፋፉት አገዛዞች በዚህ ዐይነቱ የሰውን ነፃነት በሚያፍን ሶፊስቲያዊ አስተሳሰብ ስለሚመሩ ነው። በዚህ አመለካከት ማንኛውም ግለሰብ እንደ አንድ ግለሰብ የሚታይና የራሱም ውስ|ጣዊ ነፃነት እንዳለው አይወሰድም።  ማንኛውም ግለሰብ በአንድ አካል የሚወጣ ህግንና ደንብና እንዲሁም አስተሳሰብን ጥያቂ ሳይቀርብና ሳይከራከር ዝም ብሎ መቀበል አለበት። የየአገሮችን ህገ-መንግስት ስንመለከት የምንገነዘበው፣ ህገ-መንግስቶች በየአገሩ የሰፈኑትን የኃይል አሰላለፎች የሚያንፀባርቁ እንጂ በምንም ዐይነት የህዝብን ጥቅምና ፍላጎት እንዲሁም ዕውነተኛ ነፃነት የሚያስቀድሙ አይደሉም። በዚህም ምክንያት ራሱ ህገ-መንግስት የተዛባ የሀብት ክፍፍልና ክምችት እንዲሁም የድህነት ምንጭ በመሆን በየአገሩ የተስተካከለ ዕድገት እንዳይመጣ እንቅፋት ሆናል ማለት ይቻላል።

አስቸጋሪውን የኢትዮጵያ ሁኔታና የህዝብ አስተሳሰብ የመረዳት ጉዳይና አስፈላጊነት !

በአውሮፓ የህብረተሰብ ታሪክ ውስጥ አንድ የተለመደ አሰራር አለ። ከግሪክ ስልጣኔ ጀምሮ ብቅ ያሉት ምሁራን ጥረታቸው ሁሉ በጊዜው የነበረውን የየህብረተሰባቸውን የተመሰቃቀለ የኑሮ ሁኔታና የገዢ መደቦችን ባህርይ በቅጡ መረዳት ነበር። ከዚያም በመነሳት ከጨለማ በመውጣት እንዴት ብርሃንን ማየት ይቻላል? ብለው የተቻላቸውን ጥረት ማድረግ ነበር። ደጋግሜ ለማሳየት እንደ ሞከርኩት፣ አሁንም ቢሆን አዕምሮና መንፈስ ያላቸውን ልዩ ቦታ በመረዳትና የነበረውን አስቸጋሪ ሁኔታ በሳይንስ የትንተና ዘዴ በመጋፈጥ፣ አገዛዙና ህዝቡ በዘልማድ ላይ ከተመሰረተ ኑሮ ተላቀው የማሰብ ኃይላቸውን በመጠቀም አዲስ ህብረተሰብ ለመፍጠር ያልተቆጠበ ትግል ማድረግ ነበር።  በዚህም መሰረት የአውሮፓ ምሁራን ህይወታቸውን ለዕውቀት በመሰዋት ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ ዕድገት መሰረት መጣል ችለዋል ማለት ይቻላል። ይሁንና ግን በአስተሳሰባቸው ውስጥ ሳይንስንና ቴክኖሎጂን የተረዱትና የፈጠሩትም የሰውን ልጅ ከጨለማ ኑሮ ለማላቀቅና ኑሮውን ለማሻሻል እንጂ ወደ መጨቆኛ መሳሪያ በመለወጥ ጦርነት እንዲስፋፋ አይደለም። ይህ ዐይነቱ አስተሳሰብ ግን በካፒታሊዝም ዕድገትና በኃይል የአሰላለፍ ለውጥ የተነሳ ልዩ ባህርይና መልክ እየያዘ ይመጣል። ሳይንስና ቴክኖሎጂ የጥቂት አገሮች ሞኖፖሊ በመሆን ዓለምን መበወዣና ጦርነትን ማስፋፊያ ሊሆኑ በቅተዋል። የዕድገትና የስልጣኔ ምንጮችና መሰረቶች ከመሆን ይልቅ የአገዛዝ መሳሪያዎች በመሆን ህዝብን ማፈናቀያና ሀብቱንም መዝረፊያ ሊሆኑ በቅተዋል ማለት ይቻላል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  መሬት የማነው? - ከፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም

ወደ አገራችን ሁኔታ ስንመጣ እስከዛሬ ድረስ የህብረተሰብአችንን ኋላ-ቀርነት፣ የሳይንስና የቴክኖሎጂ መሰረት እንዳይጣልና፣ ህዝባችንም የስልጣኔ ቀማሽ እንዳይሆን አግደው የያዙትን ነገሮች ለማጥናት የሞከረ የለም ብል እንደ ግብዝነት አይቆጠርብኝም። በመጀመሪያው እትሜ ላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት፣ የፊዩዳሉ ስርዓትና ሃይማኖት ማነቆ በመሆን ለአዲስ አስተሳሰብና የአኗኗር ስልት መፈናፈኛ መንገድ ለመስጠት እንዳልቻሉ ነው። ይህንን አጥብቄ የማነሳው በዚያው በድሮው መልክ መኖር የለብንም፣ መሻሻል አለብን የምንል ከሆነ ብቻ ነው። የለም በዚያው በዘልማዳችን መኖር እንፈልጋለን የምንል ከሆነ ደግሞ ምንም መከራከር አያስፈልግም። ስርዓቱንና ሃይማኖትን በጥያቄ ውስጥ ማስቀመጥ የለበንም። በሌላ በኩል ግን ሃይማኖት በራሱ የሰው ልጅ ኑርውን ማሻሻል የለበትም አይልም። የትም ቦታ አልተጻፈም። በብሉይ ኪዳንም ሆነ በአዲሱ መጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ የሰው ልጅ በእግዚአብሄር አምሳል የተፈጠረና ራሱንም መለወጥ እንዳለበት ያመለክታል። ለምሳሌ በብሉይ ኪዳን ውስጥ፣ „ብዙ ተባዙ ተፈጥሮንም በቁጥጥራችሁ ስር አድርጓት ይላል።“ በዚህ አባባል ሙሉ በሙሉ ባልስማም፣ የሰው ልጅ በማሰብ ኃይሉና በስራው ኑሮውን እንደሚያሻሽል  መጽሀፍ ቅዱሱ ያስተምረናል። ሌላው ደግሞ በመጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ እንደመሰረታዊ ነገር የተጻፈው፣ „ጠይቅ ይመለስልሃል፣ ፈልግ ታገኛለህ፣ አንኳኳ በሩ ይከፈትልሃል፣“ የሚሉት አባባሎች የሚያረጋግጡት መጽሀፍ ቅዱስ በራሱ የሰውን ልጅ የማሰብና የመፍጠር ኃይል በፍጹም እንደማይቃወም ነው። የሰው ልጅም በእግዚአብሄር አምሳል ነው የተፈጠረው ብሎ ቁልጭ አድርጎ ይነግረናል። ይህም ማለት በማሰብ ኃይላችን ገነትን መስራት እንደምንችል ነው የሚያረጋግጥልን።  አስቸጋሪው ግን የተወሰኑ ነገሮች ብቻ ተወስደው እንደ ቀኖና ሲደገሙና፣ የሰው አዕምሮ ውስጥ ሲገቡ የሰው ልጅ መሰረታዊ ነገሮችን እንዲረሳና፣ ጭንቅላቱ በባልባሌ ነገሮች እንዲጠመድ ይደረጋል። የኖይሮ ባይሎጂና የሶስዮሎጂ ምሁራን እንደሚያስተምሩን ከሆነ፣ በመሰረቱ የሰው ልጅ አዕምሮ ወግ-አጥባቂ (Conservativ) ነው። የተወሰኑ ነገሮችን እንደዶግማ ከተቀበለ በኋላ ከዚያ አልፎ ራሱን ለመጠየቅም ሆነ ራሱን ለማስጨነቅ አይፈልግም። በዚህም ምክንያት የራሱ ውስን አስተሳሰብ ተገዢ በመሆን በድንቁርና ዓለም ውስጥ እንዲኖር ይገደዳል። ፍልስፋና ከክርስትና ሃይማኖት የቀደመ ቢሆንም የሰው ልጅ ራሱን በመፈላሰፍ ከማስጨነቅ ይልቅ ብዙም ማረጋገጫ የማይጠይቀውን የተወሰኑ ነገሮችን ብቻ ከመጽሀፍ-ቅዱስ ውስጥ በመውሰድ የኖሮው መመሪያ ያደርጋቸዋል። ስለዚህም መጽሀፍ ቅዱስና ሃይማኖት በራሳቸው ሳይሆኑ የሰውን የማሰብ ኃይል የሚያግዱት፣ እንዴት እንደሚተረጎሙና በተግባርም እንደሚውሉ ነው። በተጨማሪም በሰው ልጅ በተወሰኑ ነገሮች ብቻ በመርካትና ራስን ካለማስጨነቅ የተነሳ ነው ህብረተሰባዊ ችግሮች ሊፈጠሩ የሚችሉት።

ያም ሆነ ይህ በአውሮፓ ታሪክ ውስጥ የፊዩዳሉ ስርዓት የራሱ የሆነና በአወቃቀሩ የተወሰነ ውስጠ-ኃይል ስለነበረው እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ ለአስተሳሰበ ለውጥ መፈናፈኛ ስጥቷል ማለት ይቻላል። በተለይም ስርዓቱ ከኛው ጋር ሲወዳደር በጣም ጨቋኝ ስለነበር የግዴታ ገበሬው እንዲያምጽና እንዲደራደርም አስችሎታል። ከዚህም በላይ በተለይም አንዳንድ የሃይማኖት መሪዎች ራሳቸውም ምርምር ስለሚያደርጉና በምድራዊና በመንፈሳዊ ዓለም ያለውን የቀሳውስት አኗኗር እንዲለይ ይጎተጎቱ ስለነበር፣ ሃማኖት ከውስጥ ቅራኔ ተነስቶበታል ማለት ይቻላል። በተጨማሪም፣ በሩቅ ንግድ አማካይነት በአንድ በኩል ወደ ውስጥ የገንዘብ ሀብት መከማቸት፣ በሌላ ወገን ደግሞ አሪስቶክራሲውና የባላባቱ መደብ ከአዲስ የፍጆታ አጠቃቀም ጋር መተዋወቅና፣ ራሱ የባላባቱ መደብ በዕዳ መተብተብ የግዴታ ስርዓቱን ላላ እንዲያደርገውና ለአዳዲስ ኃይሎችና አስተሳሰብ በሩን እንዲከፍት ማድረግ ተገዷል። ከዚህም ባሻገር ገንዘብ ማካበት የጀመረው በሩቅ ንግድ የተሰማራው ነጋዴ ወደ ውስጥ የዕደ-ጥበብ ስራን መቆጣጠር ይጀምራል። አንጥረኛው ከነጋዴው የሚመጣለትን ትዕዛዝ በመቀበልና ምርትን በማምረት(Putting-Out System) የፍጆታ አጠቃቀም እንዲለወጥና የውስጥ ንግድም እንዲስፋፋ ያደርጋል ። ለአውሮፓው የካፒታሊዝም ዕድገት መዓት የተጋጠጠሙና እንደምክንያት የሆኑ ነገሮች ስላሉ በእነሱ ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ለመስጠት አልፈልግም።

ወደ አገራችን ስንመጣ ስርዓቱ ይህንን ሁሉ ዕድል አላገኘም። ከውስጥ አንጥረኛው ከነጋዴው ጋር የመገናኘት ዕድል አልነበረውም። በውጭ ንግደ ላይ የተሰማራው ነጋዴ ወደ ውስጥ ተቀማጭና የሰራ-ክፍፍልን የሚያዳብር አልነበረም። ከዚህም በላይ በባላባቱ ስርዓት ንግድና የዕደ-ጥበብ ስራዎች እንደ አፀያፊ ተግባራት ነበር የሚቆጠሩት። በዚህም ምክንያት በንግድና በዕደ-ጥበብ ሙያ የተሰማሩት „የህብረተሰብ ክፍሎች“ ከክርስቲያኑ ህዝብ ጋር በጋብቻም ሆነ በሌላ ነገር የሚጋቡና የሚገናኙ አለነበሩም። ይህም በራሱ ህብረተሰቡ አዳዲስ አስተሳሰብ እንዳያፈልቅና እንዳይስፋፋ አድርጎታል ማለት ይቻላል። ከውጭም የሚመጣ አስተሳሰብም ስላልነበረ ስርዓቱ ለብዙ መቶ ዐመታት ተንሰራፍቶ የመኖር ዕድል አጋጥሞታል። እንደነ ማርቲን ሉተርና ካንትን የመሳሰሉ ስዎች ብቅ ማለትም ስላልቻሉ አዲስ ፍልስፍናና ሳይንሳዊ አስተሳሰብ ሊዳብሩ አልቻሉም።  በዚህ ላይ፣ የርስት መሬት የተሰጠው የክርስቲያኑ ገበሬ ባለው ረክቶ የሚኖር ስለነበር የተቃውሞ ባህል ማዳበር አልቻለም። ግፋ ቢል የሚያደርገው በተናጠለ መሸፈት ነበር። ይህ ጉዳይ እስከዛሬ ድረስ እንደ ባህል ተወስዶ ምሁሩም ሲመረው ወደ ውጭ የሚሽሽና ከውጭ ሆኖ ለመታገል የሚጥር አድርጎታል። በሌላ አነጋገር፣ ከውስጥ ሆኖ ስርዓቱን በምሁራዊ ኃይል ለመጋፈጥ የሚያስችል ባህል ስላልተመደ ስርዓቱ ራሱ ካለብዙ ግፊት ለብዙ መቶ ዐመታት እንዲቆይና ኋላ-ቀርነትና ድህነት መለዮአችን እንዲሆን ለማድረግ ችሏል ማለት ይቻላል። ከዚህ በተረፈ የገበሬው የማምረት ኃይል ደካማ ስለነበር ብዙ በማምረት ወደ ገበያ አውጥቶ የመሸጥ ኃይል አልነበረውም። ለባላባቱና ለቤተክርስቲያን ከገበሬው የሚሰጠው ድርሻ ከራስ ጥቅም ስለማያልፍ በአጠቃላይ ሲታይ ሀብት እንዳይከማችና እንደገና ለመዋዕለ-ነዋይ እንዳይውል አግዶታል። በፖለቲካ-ኢኮኖሚክስ ህግ መሰረት ከፍጆታ በላይ ተጨማሪ ምርት(Surplus-product) የማያመርቱ ህዝቦች ለማደግ አይችሉም። በሌላ አነጋገር፣ ከእጅ ወደ አፍ ብቻ በሚውል የአሰራርም ሆነ የአስተራረስ ዘዴ የሚኖር ህዝብ የማደግ ኃይሉ በጣም ደካማ ነው ማለት ነው።  በሌላ ወገን ግን በአገራችን ውስጥ ምንም ዐይነት ቴክኖሎጂያዊ ወይም የአሰተሳሰብ ለውጥ የለም ብሎ መናገር በፍጹም አይቻልም። ለምሳሌ የጠላ፣ የጠጅንና የካቲካላን አጠማመቅ ካለብዙ ውጣ ውረድ ስንመረመር እናቶቻችን በደመ-ነፍስ እየተመሩ አዲስ የአኗኗር ስልትን ማዳበር እንደቻሉ ነው የምናየው። በመሰረቱ፣ በተለይም የካቲካላ አጠማመቅ ባይሎጂያዊ፣ የኬሚካላዊና የፊዚክስ ክንውን ነው። ከምርት ክንዋኔ እስከ ብቅል ማብቀልና ድፍድፍ መስራትና ይህንንን በእሳት አማካይነት ወደ ፈሳሽነት መለወጥ ሳይንሳዊ ክንዋኔ ለመሆኑ የተረጋገጠ  ጉዳይ ነው። ይህ ሁሉ ሊሆን የቻለው እናቶቻችን ምንም ዐይነት ሳይማሩ በደመ-ነፍስ በመማራቸውና እስከተወሰነ ደረጃም ድረስ የማሰብ ኃይላቸውን መጠቀም በመቻላቸው ነው።  እንደዚህ ዐይነቱ አመራረትም በአውሮፓ ምድር ውስጥም በማዕከለኛው ዘመን  የተለመደ ነበር። እነሱ ግን መመራመርና መፍጠር ስለቻሉ ቴክኖሎጂውና የአሰራር ዘዴው በዚያው ሊቀር አልቻለም። የሽማኔንም ባህል ስንመለከት እናቶቻችንና አባቶቻችን ከውጭው ዓለም ጋር ሳይገናኙ በራሳቸው የማሰብ ኃይል የልብስ አሰራር ቴክኒክን ሊያዳብሩና፣ እስከዛሬ ድረስ ይህ እንደ ባህል ሊወሰድና መለዮአችንም ሊሆን በቅቷል።፡ ይህም የሚያመለክተው የተለያዩ ህበረተሰቦች በራሳቸው የማሰብ ኃይል አንደኛው ከሌላው ሳይኮርጅ የተወሰነ ቴኮኖሎጂያዊ ለውጥንና የአመራረት ሁኔታን እንደሚፈጥርና እንደሚያዳብር ነው።

እዚህ ላይ መተንተን ያለበት ሌላ መሰረታዊ ነገር አለ። በመጀመሪያ ማንም ሰው ፊይዳል ልሁን ብሎ አይነሳም። ፊዩዳሊዝም የህብረተሰብአዊ ክንውን ውጤት ሲሆን፣ በስ13ኛው ክፍለ-ዘመን በአሸናፊነት ከወጣው የሰለሞናዊው አገዛዝ ጋር በጥብቅ የተያያዘ ስርዓት ነው። አዲሱ ንጉሳዊ አገዛዝ ህብረተሰቡን ለመቆጣጠርና ለማስተዳደር ሲል መሬትን ለባላባቱ መደብና ለገበሬው እንደየህብረተሰብአዊ አቀማመጣቸው አከፋፈለ። በዚህ ዐይነቱ የመሬት አደላደልና ህብረተስብአዊ አወቃቀር ቤተክርስቲያን የራሷ ድርሻ ተሰጣት። በዚህ መልክ የህብረተሰቡ የርስ በርስ ግኑኝነት መሬትን በሚቆጣጠሩና ከመሬት በሚገኝ ሀብት በሚተዳደሩና አርሶ በሚያድረውና፣ ጠቅላላውን የአገዛዘ አወቃቀር በሚደግፈው ሰፊ ገበሬ መሀከል የሚገለጽ ነበር። እንደዚህ ዐይነቱ ስርዓት በገዢና ተገዢ፣ በአስገባሪና በገባሪ መሀከል የሚገለጽ ስለነበር ገበሬው መጠየቅ የሚችልና ለመብቱም የሚከራከረ አልነበርም። ስርዓቱ ተፈጥሮአዊ ሆኖ በመወሰዱ የህብረተሰቡን ኑሮና አስተሳሰቡን የሚደነግግና የምርት ኃይሎችም እዚያው ባሉበት ቀጭጨው እንዲቀሩ የማድረግ ኃይሉ ከፍተኛ ነበር ማለት  ይቻላል። ስለሆነም የሰው የማሰብ ኃይል ውስንና በራሱ የማሰብ ኃይል የኑሮውን ሁኔታ ማሻሻልና መለወጥ የማይችል ሆኖ ይሰማው ነበር። በህብረተሰቡ ውስጥ የሚከሰቱ ማንኛውም ቀውሶች፣ ረሃብ፣ የወረርሽኝ በሽታና ሌሎችም እንደ እግዚአብሄር ቁጣ የሚታዩና በጸሎት ሊወገዱ የሚችሉ መስሎ የሚታይበት ሁኔታ ለብዙ መቶ ዐመታት ስፍኗል።  ከዚህ በተጨማሪም፣ በሆነው ባልሆነው ነገር ማመንና በፍርሃት መዋጥ የህብረተሰቡ የማሰብ አካልና አስተሳሰቡንም ወጥሮ የያዘው ነበር። ስለዚህም የገበሬውም ሆነ የአገዛዙ በተለያየ መልክ የሚገለጹ ባህሪዎች በሚሆንና በማይሆን ነገሮች የተጠመዱና ለሳይንስንና ለቴክኖሎጂ ፈጠራ የማያመቹ አስተሳሰቦች ነበሩ።

ያም ሆነ ይህ የፊዩዳሉ ስርዓት አ.አ እስከ 1974 ድረስ መቆየቱና፣ ራሱ ደግሞ እጅግ ተሰበጣጥሮ የገባው በተለይም በገንዘብና በፍጆታ አጠቃቀም የሚገለጸው ካፒታሊዝም የማሰብ ኃይላችንን ሊወስነው ችሏል። ይህም ማለት በረቀቀና በተወሳሰበ መልክ እንዳናስብ፣ ሎጂካዊና አርቆ አስተሳሰብን እንዳናዳብር፣ ንቃተ-ህሊናችንን በማዳበር ለህብረተሰባችን ኃላፊነት እንዳይሰማን፣ በአገራችንና በራሳችን ላይ ከመመካት ይልቅ በውጭው ዓለም ላይ ጥገኛ እንድንሆን ለማድረግ በቅቷል ማለት ይቻላል። በተጨማሪም ሂስን ለመቀበልና ለመሰንዘርም ዝግጁ መሆን አልቻልንም። ካለምንም ውጣ ውረድ አንድ „ከበድ ያለ ሰው“ ስናይ በሱ ሃሳብ መመራት አስቸጋሪው ባህርያችን እየሆነ መጥቷል። ይህም ማለት ዕውቀትንና ጥበብን አሳዳጆች ሳንሆን ሰውን በማሳደድና በሱ ጥገኛ በመሆን የአዳዲስ አስተሳሰብና የዕድገት እንቅፋት ለመሆን በቅተናል።  በዚህ ላይ ደግሞ በዕምነትና በፕሪንስፕል ላይ አለመመራትና አለመስራት፣ እንዲሁም ተንኮልና አድርባይነት አስቸጋሪው ባህርያችን በመሆን ለችግራችን ልዩ ገጽታ በመስጠት ህብረተሰብአችን እንዲመሰቃቀል አድርገውታል። ስለሆነም፣ ለፈጠራ የሚያመቹ አዳዲስ ሃሳብን የማፍለቅና ችግርን የመፍታት ባህልን ማዳበር አልቻልንም። በአንድ ሃሳብ ዙሪያ ለመደራጀት አለመቻል፣ በዕቅድ መመራትና የተሰጠንን ኃላፊነት በስራ ላይ ማዋል አለመቻል፣ ተጠያቂ መሆንና በአጠቃላይ ሲታይ ለህብረተሰብአችን ኃላፊነት እንዳለበን አለመረዳት ሌላውና አስቸጋሪው ባህርያችን ሆነዋል። በተለይም የተለያዩ የፍልስፍናና የሳይንስ አስተሳሰቦች እንደመከራከሪያ ነጥቦች ስለማይቀርቡና ጥናትም ስለማይካሄድ አብዛኛዎቻችን የተሰማራናው ብዙም ጥያቄን ወደ ማያስከትለው ግን ደግሞ ለአንድ ህብረተሰብ የመኖርና ያለመኖር ወሳኝ በሆነው  ፖለቲካ(ቦለቲካ) በሚባለው ነገር ላይ ነው።

እንዲሁም የአንድን ህብረተሰብ ዕድገት የሚጎትቱና ህብረተሰባዊ ትርምስም እንዲፈጠር የሚያድረጉ አስተሳሰቦች በመስፋፋት የማሰብ ኃይላችንን ለመቆጣጠር በቅተዋል። ይህ በራሱ ደግሞ በጠቅላላው በአደረጃጀት፣ በዕቅድ ላይና በጠቅላላው ለህብረተሰብ ዕድገት በሚያስፈልጉ ነገሮች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ በማድረግ ለዛሬው ትርምስ ምክንያት ሆነዋል ማለት ይቻላል። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ሁሉም በየፊናው የሚሮጥ እንጂ ለመተባበር የሚፈልግ አይደለም። ሁሉም ስልጣን ላይ ቁጥጥ ለማለት የሚፈልግ እንጂ ለማስተማርና ደቀ-መዝሙሮችን ለማፍራት የሚፍልግ አይደለም። እያንዳንዱ ግለሰብም ሆነ ድርጅት አለኝ የሚል በራሱ ብቻ ኢትዮጵያን የመሰለ ትልቅ አገር የሚገነባ ነው የሚመስለው። ብዙ ዕውቀትና ኃይል እንዲሁም መቻቻል ለአገር ግንባታ አስፈለጊዎችና መሰረተ-ሃስቦች እንደሆኑ አይረዳም። ኢትዮጵያ ትላንትና የሃምሳ ሚሊዮን ህዝብ አገር፣ ዛሬ ደግሞ የዘጠና ሚሊዮን ህዝብ አገር እንደሆነች የሚረዳው በጣም ጥቂቱ ብቻ ነው። የህዝብ ቁጥር በዚህ መልክ እየጨመረ ሲሄድ የግዴታ አዳዲስ ፍላጎቶችም እንደሚከሰቱና፣ እየጨመረ የመጣውን የህዝብ ቁጥር ለማስተናገድ በየጊዜው ማሰብና ማቀድ አስፈላጊ መሆኑን የሚረዳው በጣት የሚቆጠር ነው።  ስለሆነም አንድን አገር ለመገንባት ኃይልንና ሃሳብን መሰበሰብና በጋራ ለመሰራት አስፈላጊ መሆኑን የተገነዘብን አይመስለኝም። በተለይም ባለፈው አርባ ዐመታት ቡዳናዊ ስሜት አይሎ በመውጣቱና፣ በዚህ ላይ ደግሞ እንደ ሃይማኖትና የብሄረሰብ ጥያቄዎች ተጨማሪ አጀንዳ ሆነው በመወሰዳቸው አስተሳሰባችን ችግርን ለመፍታት ወደ ሚያስፈልጉ ነገሮች ላይ ከማዘንበል ይልቅ በችግራችን ላይ ችግርን በመጨመር ወደ ትርምስና መፍቻ ወደ ማይገኝለት ዓለም ውስጥ የምንጓዝ ለመሆን በቅተናል። እስከዛሬ ድረስ ሁላችንም ቢሆን ችግራችንና የችግራችንን ምንጭ ከሳይንስና ከፍልስፍና አንፃር መመርመር አልቻልንም። ሁላችንም ብንሆን ይበልጥ የምንመራው በስሜታዊነት እየተገፋን እንጂ የማሰብ ኃይላችንን በማንቀሳቃስ  አይደለም። እንደ አንድ ጥቁር ህዝብና የተወሳሰበ ችግር እንዳለበት በአንድ መንፈስና በአንድ ዓላማ ከመነሳትና ከመመራት ይልቅ ቡድናዊ ስሜትን በማዳብርና ሳይንሳዊ መሰረት የሌላቸውን ነገሮች በማንሳት በምስኪኑ ህዝብ ላይ እናሾፍበታለን። ለምሳሌ ከሳይንስና ከፍልስፍና አንፃር የምርምር መሰረተ-ሃሳቦች የሰው ልጅ፣ ተፈጥሮና ኮስሞስ ብቻ ናቸው። ስለሆነም የሰውን ልጅ የማሰብ ኃይል በማዳበር የሰው ልጅና ተፈጥሮ በመደጋገፍ በምድር ላይ ሚዛናዊ ስርዓት መመስረት የሚለው የሳይንስና የፍልስፍና መሰረተ-ሃሳቦች ናቸው። እኛ ግን ሳይንሳዊ መሰረት የሌለውን የብሄረሰብ ጥያቄን በመፍጠር ለችግራችን ልዩ ዕምርታን ሰጥተነዋል።  በአስራሰባተኛው፣ በአስራስምንተኛውና በአስራዘጠነኛው ክፍለ-ዘመን ብቅ ያሉት የአውሮፓ ምሁራን ልክ ዛሬ እኛ እንደምናስበውና እንደምንጨቃጨቅበት ትግላቸውን ቢጀምሩ ኖሮ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ዓለምን ባላየን ነበር። ጫካ ውስጥ እየተተራመስን የምንኖር ነበርን። ስለሆነም የሰውን ልጅና ተፈጥሮን እንደመፈላሰፊያ ነጥብ የወሰዱት የአውሮፓ ምሁራን የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት ለመሆን ሲበቁ፣ እኛ ደግሞ ከሳይንስና ከፍልስፍና ውጭ የማይሆን ነገር በመፍጠር በመጠራጠርና በመፈራራት ዓለም ውስጥ እንኖራለን። የሰው ልጅ ሌላውን አምሳሉንና በእግዚአብሄር አምሳል የተፈጠረውን እንዲጠላና እንዲገደል እናደርጋለን። የዕውቀትና የአስተሳሰብ ችግር መሆኑን ከመረዳት ይልቅ ችግሩ ሁሉ ከአንድ ብሄረሰብ የተፈጠረ በማስመስል ህብረተስብአዊና ባህላዊ ትርምስ እንፈጥራለን። ይህም የሚያረጋግጠው ምንድ ነው፟? የቀጨጨ አስተሳሰብ ያለንና አምላክ የለገሰንን የማሰብና የመመራመር ኃይል ሁሉ ለመጠቀም እንደማንችል ነው።   ስለሆነም፣ እኛው ራሳችን የረሃብና የድህነት ምክንያቶች ልንሆን በቅተናል። ዕድገትና ስልጣኔ እንዳይኖር እንቅፋት በመሆን የጥቁር ህዝብ በጨለማ ዓለም ውስጥ እንዲኖር ባለማወቅ የምንሰራው ስራ ሁሉ የታሪክ ወንጅል እየሆነ መጥቷል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ፍሬ አልባ ደረቅ ዛፍ ላይ ድንጋይ ማባከን ለምን ?

ሌላው አስቸጋሪው ጉዳይ ደግሞ ሁሉም ፖለቲከኛ ሆኖ ለመታየት መፈለጉና ስለሚሯሯጥም አስቸጋሪ ሁኔታን እየፈጠረ ነው። እስከሚገባኝ ድረስ ፖለቲካ እንደማንኛውም የትምህርት ዘርፍ ዕውቀትን ይጠይቃል። እንደ ፊዚክስ፣ ኬሚስትሪ ባይሎጂና እንደህክምናና ሌሎችም ችግር መፍቻ ዘዴዎች የሆኑት እንደ ኢንጂነሪግ የመሳሰሉት ዕውቀቶች ሁሉ ፖለቲካ ሰፋ ያለ ዕውቀትን የሚጠይቅ ነው። ለምሳሌ አንድ ሰው የፓይለት ኮርስ ወስዶ በደንብ ሳይሰለጥንና ፈተናውን ሳያልፍ አውሮፕላን መንዳት እንደማይችል ሁሉ ፖለቲካ አንድን ህብረተሰብ ማስተዳደሪያና አገርን መገንቢያ መሳሪያ እንደመሆኑ መጠን ማንኛውም በፖለቲካ ዓለም ውስጥ እሳተፋለሁ የሚል አስፈላጊውን ጥናትና ምርምር ማድረግና በተግባርም ለማሳየት መቻል አለበት። ማንም እየተነሳ ፖለቲከኛ ነኝ የሚል ከሆነ ፖለቲካ የወንበዴዎችና የገዳዮች መጫወቻ ይሆናል ማለት ነው። ይህ ዐይነቱ በአገራችን የተስፋፋ አጉል ባህል እስካልተወገደ ድረስና፣ ፖለቲካም ሳይንሳዊና ፍልስፍናዊ፣ ሶሶይሎጂያዊና ሳይኮሎጂያዊ፣ እንዲሁም ልዩ ልዩ ዕውቀቶችን መሰረት ያደረገ መሆኑ እስካልታየ ድረስ ሁሉም ፖለቲከኛ ነን እያለ ህዝብን ይበጠብጣል።  ስለሆነም ሁሉም በየዝንባሌውና በሰለጠነው ፊልድ ቢሰራና አስተዋፅዖ ቢያደርግ ለአገርና ለህዝብ ይበጃል።  እስካሁን የማይገባኝ ነገር፣ ለምሳሌ ፊዚክስ ወይም ባይሎጂ የተማሩ ምሁራን በዚህ ጠለቅ ያለ ምርምር ከማድረግና ለአገራቸውም ዕድገት አስተዋፅዖ ከማበርከት ይልቅ ፖለቲካ ዓለም ውስጥ ገብተው ዕውቀታቸውን እንድሚያባክኑ ነው።

ይህ ሁሉ የሚያረጋግጠ ምንድነው ? የሃሳብ ነፃነት ተሰምቶን ሃሳብን የምናፈልቅና በሱ ላይ ክርክር ለማድረግ የማንችል መሆናችንን ነው። የሌላውንም ሃሳብ የማናዳምጥና በንቀት የምናይ ነን። እንደ አ.አ በ1906 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ የሄደ ጀርመናዊና አዲስ አበባና አርሲ እስከ ጣሊያን ጦር መጨረሻ ድረስ የኖረ ጀርመናዊ የኢትዮጵያ አገር ወዳድ በቅጡ ባህርያችንን እንደተመለከተው፣ አብሲኒያኖች 1ኛ) መመልከትና መኮረጅ አይችሉም፣ 2ኛ) የሰውን ንግግር ሳይሆን የራሳቸውን ንግግር ብቻ ነው የሚያዳምጡት ያለው እስከዛሬ ድረስ ቋሚነት አለው። ልዩ ዐይነት ባህርያችንና ለውዝግብ አንዱ ምክንያት ነው ማለት ይቻላል። ሃሳብን ማፍለቅ አለመቻል ብቻ ሳይሆን ማዳመጥና መደማመጥንም አንችልም። ይህ ዐይነቱ ባህርይ እስካለ ድረስ ደግሞ ስለ አገርና ዕድገት ማሰብም ሆነ ማውራት አንችልም። ከዚህ ስንነሳ የግዴታ ሁለንተናዊ  የአስተሳሰብ ለውጥ ለማድረግ መቻል አለብን። ራሳችንን እየመላለስን ለመጠየቅና ለመመርምር ዝግጁ መሆን አለብን። ይህ እስካለሆነ ድረስ  የወያኔ መወገድ በራሱ ብቻ ምንም ለውጥ ሊያመጣ የሚችለው ነገር የለም።  ከዚህ በመነሳት ደግሞ ወደ ሌላው አስቸጋሪው ነገር እንሻገር።

ለምን ዐይነት ህብረተሰብ እንደምንታገል ያለማወቁ ጉዳይ !!

ድሮም ሆነ ዛሬ ሲያተራምሰን የኖረው ለምን ህብረተስብ እንደምንታገል ያለማወቃችን ነው። ለምሳሌ በአውሮፓ ህብረተሰብ የትግል ታሪክ ውስጥ ከግሪኩ ስልጣኔ ጀምሮ በየኤፖኩ ብቅ ያሉት ምሁራን ምን ምን ነገሮች እንደሚፈልጉና ምን ዐይነትስ ህበረተሰብ መመስረት እንዳለበት በደንብ የተገነዘቡ ነበር። ስለሆነም ከመንግሰት አወቃቀር ጀምሮ፣ እስከ ፖለቲካ ምንንነትና ሞራልና ስነ-ምግባር መወያያ ነጥቦች ነበሩ። በግሪክ ስልጣኔም ሂደት ውስጥ ለአንድ ህብረተሰብ መኖርና ማበብ የግዴታ የስራ ክፍፍልና የንግድ ልውውጥ አስፈላጊው መሰረተ-ሃሳቦች እንደሆኑ ክርክር ይደረግ ነበር።

ኋላ ደግም ወደ አውሮፓ ስንመጣ የመንግስትን ሚና በኢኮኖሚ ውስጥና፣ የነቁ የህብረተስብ ክፍልሎችን በሃስባና በቁሳቁስ መርዳት፣ እንዲሁም ደግሞ ማኑፋክቱርና የውስጥ ንግድ እንዲስፋፋ አስፈላጊው እርምጃዎች ስለመወሰዳቸው ጉዳይ በምሁራን ዘንድ በሰፊው ውይይትና ክርክር ይደረግባቸው ነበር። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ለአንድ ህዝብ መሰባሰብ የግዴታ መንደሮችና ከተማዎች በዕቅድ መስራት እንዳለባቸውና፣ ምን ምን እርምጃዎች መወሰድ እንዳለባቸው፣ እንዴትስ ገንዘብንና የሰውን ኃይል መሰብሰብና ማደራጀት እንደሚያስፈልግ ሌላው መነገጋሪያ ነጥብ ነበር። ከተማዎች፣ መንደሮች፣ የመናፈሻ ቦታዎች፣ የገበያ አዳራሾችና ልዩ ልዩ ለአንድ አገር የሚያስፈልጉ ነገሮች ሳይነጠፉና ሳይሰተካከሉ ስለ ኢኮኖሚና ስለአንድ ህብረተሰብ ማውራት እንደማይቻል ለአውሮፖው ምሁራን ግልጽ ነበር። ስለሆነም የአውሮፓው ምሁራን አስተሳሰብ ሁለንታዊና፣ አንዱ ነገር ከሌላው ተነጥሎ ሊታይ እንደማይችል መመሪያ ዘዴና የአሰራር ባህል ነበር።

ወደ አገራችን ስንመጣ ግን፣ በተለይም ወያኔ ስልጣን ከጨበጠ ወዲህ ተቃዋሚ ነኝ ከሚለውና መጠኑ ከማይታወቀው ኃይል፣ ህዝባችን ምን ዐይነት ስርዓት እንደሚያሰፈልገውና በምንስ መልክ እንደሚደራጅ ግልጽ ውይይት ሲካሄድ ታይቶ አይታወቅም። ከአብዮቱ በፊትና በአብዮቱ ወቅት በዚያን ጊዜ ተራማጅ ነኝ ይል ከነበረው ኃይል ዘንድ ቢያንስ አንድ ዐይነት ስምምነት ነበር። ወዛደሩንና ገበሬውን ያቀፈ ዲሞክራሲያዊና ሶሻሊስታዊ ስርዓት መገንባት ያስፈልጋል የሚለው ላይ ስምምነት ነበር። በዚያን ጊዜ ከተማሪው ንቅናቄ የወጡ ተራማጅ ኃይሎች በጊዜው የነበረውን ስርዓት ከመመረመሩ በኋላ የደረሱበት መደምደሚያ ዲሞክራሲያዊና ሶሻሊስታዊ ስርዓት ነው የሚያስፈለገው የሚል ነበር። ይህ ዐይነቱ ግምገማና ድምዳሜ ትክክል ነው ትክክል አይደለም በሚለው ላይ መነታረኩ ከዚህ ጽሁፍ አቅም በላይ ነው። ለማለት የተፈለገው አንድን አገዛዝ እቃወማለህ ስንል አገዛዙን ብቻ ሳይሆን የስርዓቱንም ምንነት መረዳትና፣ ለምንስ ህብረተሰብ እንደምንታገልና፣ ምን ምንስ እርምጃዎች ተግባራዊ መሆን እንዳለባቸው ማመልከት ያስፈልጋል።

በተቃዋሚው ዘንድ ያለው ሌላው አስቸጋሪ ነገር ወያኔ ስልጣን ከጨበጠ ጀምሮ የዘረጋውን ስርዓት በሚገባ አለመመርመር ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ በአብዛኞቻችን ዘንድ አገዛዙ እስከዛሬ ድረስ የተከተለውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ አለመመርመርና ለመረዳት አለመቻል ለወደፊቱ ህብረተሰብአዊ ፕሮጀክት አስቸጋሪ ሁኔታ መፍጠር ችሏል። እንደሚታወቀው ለአንድ አገር ነፃነት እታገላለሁ የሚል ድርጅትም ሆነ ድርጅቶች የስርዓቱን ምንነትና ስንኩልነት በሚገባ መረዳት አለባቸው። ለምሳሌ ሲያመን  ሃኪም ቤት በምንሄድበት ጊዜ ሀኪሙ ምርመራ ከመጀመሩ በፊት ምንና የት ቦታ እንደሚያመን፣ ከመቸስ ጀምሮ እንደሚያመን ሲጠይቀን መመለስ እንዳለብን ሁሉ፣ ለአገራችንም እንታገላለን ስንል በቅድሚያ በሽታውንና ለዕድገት ማነቆ የሆነውን ሁኔታ በሚገባ መመርመርና ወደ ውጭ አውጥተን መወያየትና መከራከር አለብን። እንዲያው በደፈናው ነፃነት ነው የሚያስፈልገን፤ ሌላውን ከዚያ በኋላ እንወያይበታለን የሚለው አባባል ለችግራችን መፍትሄ ሊሆን የሚችል አይደለም። በተለይም ደግሞ ከህብረተስብ ግንባታ፣ ፈጠራና በሳይንስና በቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም ደግሞ ውብ ውብ ከመሳሰሉ ከተሞች አንፃር ስንነሳ በቅድሚያ የዛሬውን የአገራችንን ሁኔታ፣ የአገዛዙን ፖሊሲና ከውጭ ኃይሎች ጋር ተቆላልፎ ለዕድገትና ለስልጣኔ ከፍተኛ ጠንቅ መሆኑን እያነሱ መወያየት ያስፈልጋል። ከዚህ ስንነሳ ለምንድን ነው ይህንን አገዛዝ የምንታገለው?  ብለን ጥያቄ ማቅረብ አለብን።

በአጭሩ ይህንን አገዛዝ የምንታገለው ፋሺሽታዊ መዋቅር በመዘርጋት ህዝባችንን ርስ በርሱ እንዲጫረስ የተቻለውን ሁሉ ስለሚያደርግ ነው። የውጭ ኃይሎች ታዛዥ፣ በተለይም የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ታዛዥ በመሆንና የጦር ካምፕ እንዲቋቋም በማድረግ የውክልና ጦርነት በማካሄድ የጥቁር ህዝብ ርስ በርሱ እንዲጫረስና ለዘለዓለሙ የስልጣኔ ባለቤት እንዳይሆን ስለሚያደርግ ነው። አገራችን ብቻ ሳይሆን፣ በአካባቢው ያለው ጠቅላላው ጥቁር ህዝብ ስልጣኔን እንዳያይ በጦርነት ታምሶ እንዲኖር ስለሚያደርግ ነው። አገራችን ታሪክ እንዳይሰራባት፣ ህዝቦቿ የቀን ብርሃንን እንዳያዩና ዘለዓለም ተመጽዋች ሆነው እንዲኖሩ ስለሚያደርግ ነው። ባጭሩ የአገዛዙ ተልዕኮ ፀረ-ስልጣኔ፣ ፀረ-ሳይንስና ፀረ-ቴክኖሎጂ፣ ፀረ-ህዝብና የተፈጥሮ ጠንቅ ስለሆነ ነው አጥብቀን የምንዋጋው። ስለሆነም ትግላችን የዛሬው እጅግ አስከፊ ስርዓት እንዲወገድና ህዝባችንም ዲሞክራሲያዊ ነፃነቱን እንዲቀዳጅና ታሪክን ለመስራት እንዲችል ነው ደፋ ቀና ይምንለው። ባጭሩ የዛሬው አገዛዝ የድህነት፣ የረሀብ፣ የጦርነት፣ የስደት፣ የትርምስና ያለመረጋጋት ምንጭ ስለሆነ አጥበቀን እንታገለዋለን። አገዛዙን የምንታገለው በትግሬዎች ስለሚመራ ሳይሆን ይህንን እንደ ሽፋን በመጠቀም በጠቅላላው ህዝባችን ላይ ስለዘመተ ነው። የትግሬን ኤሊት የበላይነት አሰፍናለሁ በሚል የራሱንና ከሱ ጋር በጥቅም የተሳሰሩ ጥቂት ሰዎችን ጥቅም የሚያሰጠብቅ ነው። በዚህም ምክንያት በአገሪቱ ውስጥ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ሰፋ ያለና ጠቅላላውን ህዝብ የሚጠቅም ኢኮኖሚ እንዳይዳብር አግዶ ይዟል። ሰፋ ያለ ህዝቡን ሊያስተሳሰር የሚችልና በሳይንስ የተጠና ባህል እንዳይዳብርና አገራዊና ብሄራዊ ስሜት እንዳያድጉ በዕውቅ ይሰራል።  አገዛዙ  የውጭ ቅምጥ ስለሆነና በነሱም ስለሚደገፍ የኢትዮጵያ ህዝብ ጠላት ብቻ ሳይሆን የጠቅላላው ጥቁር ህዝብ ጠላት ማለት ይቻላል።

ስለሆነም የኛ ትግል ደግሞ የሰለጠነችና በቴክኖሎጂና እንዲሁም በሳይንስ ላይ የተደገፈች ኢትዮጵያን መገንባት ይሆናል። ውብ ውብ ከተማዎችና መንደሮችን በመገንባት ህዝባችን ዕውነተኛ ነፃነቱን ሊጎናጸፍበት የሚችልባትን ኢትዮጵያ ለመገንባትና ለመጭው ትውልድ ለማስተላለፍ ነው ዋናው ትግላችን። በዚህም ሺህ በሺህ የሚቆጠሩ የሊትሬቸርና የፈላስፋ ስዎች፣ እንዲሁም የሳይንስና የቴክኖሎጂ ፈጣሪዎች የሚበቅሉባትና የሚስፋፉባት አገር ለመመስረት ነው። ይህ ዐይነቱ ህብረተሰብ በመንግስት፣ በህብረተሰቡና በግል ተሳትፎ የሚገነባና የሚደጋገፍ፣ ግን ደግሞ የገበያን ኢኮኖሚ የማይጻረር፣ የገበያ ኢኮኖሚ ጤናማ በሆነ መልክ ሊገነባ የሚችልበትን መሰረት ለመጣል የሚያስችል መሆን አለበት። ህዝባችን ከድህነትና ከረሃብ የሚላቀቀውና ዕውነተኛ ነፃነቱን ሊቀዳጅ የሚችለው በሳይንስና በቴክኖሎጂ አማካይነት ብቻ መሆኑን በመረዳታችን ለዚህ ለተቀደሰ ዓላማ እንታገላለን። ዋናው ትግላችንም የተከበረችና የምትፈራ፣ እንዲሁም ብሄራዊ ነፃነቷ በማንም ኃይል የማይደፈር ኢትዮጵያን መገንባት ይሆናል።

ከዚህ ስነሳ የሚቸግረኝ ነገር  የወያኔን ባህርይ የማወቁ ጉዳይ ሳይሆን ተቃዋሚው ኃይል ምን እንደሚፈልግና ለምንስ ህበረተሰብ እንደሚታገል ለመረዳት አለመቻሌ ነው። ይህ ዐይነቱ ግልጽ የትግል አካሄድ ከምን የመነጨ ነው? በእኔ ዕምነት የተቃዋሚው ኃይል የሚመራበት ፍልስፍናና ሳይንስ የለውም። በመሆኑም በቅጡ የአገዛዙን ባህርይም ሆነ ስርዓቱን፣ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ኮሙኒቲው የተደገሰልንን የጥፋት ፖለቲካ በሚገባ የተገነዘበና ሊገነዘብም የሚፈልግ አይደለም። እንዲያው በደፈናው ብቻ እኛ ስልጣን ከጨበጥን ሁኔታውን እንለወጠዋለን የሚል አጉል ፖለቲካ በማካሄድ ስፊውን ህዝብና፣ በተለይም ደግሞ ወጣቱን እያዘናጋውና እያታለለው ነው። ይህ ከሆነ ደግሞ ለምንስ ወያኔን እንደምታገል ግልጽ አይደለም። ለምንስ ዕድሜዬን በሙሉ እኔ ብቻ ሳልሆን የኢትዮጵያ ህዝብም እንደሚሰቃይ አይገባኝም። ስለሆነም የስርዓቱን ምንነት ብቻ ሳይሆን ጠላቶቹንም ጠንቅቆ ማወቅ የሚያስፈልግ ይመስለኛል። ለዕድገታችን ጠንቅ የሆኑ ኃይሎችን በሚገባ መረዳት ከቻልንና፣ በቲዎሪ ደረጃ ተንትነን ማስረዳት ከቻልን ለችግሩ መፍትሄ አንድ መልስ አገኘን ማለት ነው።

ሌላው አስቸጋሪው ጉዳይ ደግሞ የተሰበጣጠሩ ኃይሎችና ዓላማቸውስ ምን እንደሆኑ የማይታወቁ በትግል ውስጥ እንሳተፋለን ስለሚሉና እዚህና እዚያ ስለሚሯሯጡ የአገራችንን ሁኔታ እንዳንረዳና ርዕይም እንዳይኖረን ለማድረግ በቅቷል። በተለይም ውጭ አገር የሚኖረውና እዚህና እዚያ የሚሯሯጠውና፣ ይኸኛውን ወይም ያኛውን ድርጅት እደግፋለሁ ወይም አባል ነኝ የሚል በዓለም ውስጥ ምን ነገር እንደሚካሄድ የሚያውቅ አይመስለኝም። ከዘጠና በመቶ በላይ የሚሆነው በውጭ አገር የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ከሊትሬችሮችና ከጋዜጦች ጋር ግኑኝነት የለውም። ይህ ዐይነቱ ኃይል ነው ልባችንን የሚያደርቀውና ለትግሉ እንቅፋት የሚሆነው። በዚህ መልክ ደግሞ አገርን ነፃ ማውጣትና ጠንካራ አገር መገንባት አይቻልም። ስለሆነም ትግሉ የግዴታ ጥራት ማግኘት አለበት። ለዚህ ደግሞ ሰፊ ጥናት ማካሄድ ያስፈልጋል። መንፈስን የሚያድስና ጥራትን የሚያመጣ የፍልስፍናና የሳይንስ መመሪያ ሊኖረን ይገባል። ይህ ሲሆን ብቻ ነው የታሪክ አስተዋፅዖአችንን ልንወጣ የምንችለው። አገራችንና ህዝባችን ታሪክ እንዲሰራ መንገዱን ማሳየት ብቻ ሳይሆን የምናግዘውም የጠራ አስተሳሰብና፣ አነሰም በዛም አንድ ሁላችንንም ሊያሰራ የሚችል የጋር አመለካከት ያፈለቅንና እንደመመሪያ መውሰድ ከቻልን ብቻ  ነው። ፕሉራሊዝምና ሊበራሊዝም የሚባሉት የቅንጦት ፅንሰ-ሃሳቦች ለችግራችን መፍትሄ ሊሆኑ አይችሉም። የአውሮፓው ህዝብም በነዚህ ፅንሰ-ሃሳቦች ወደ ጠንካራ ህብረተሰብና ህብረ-ብሄር አልተሽጋገረም። ይህ ማለት ግን የሃሳብ ነፃነት አይኑር ማለቴ አይደለም። ወደድንም ጠላንም ፕሉራሊዝም የተፈጥሮ ህግ ነው። በሌላ ወገን ግን አንድ ድርጅትም ሆነ አንድ ግለሰብ የጠራና መፍትሄ አምጭ አስተሳሰብ ሳይኖረው ስለፕሩላሪዝምና ሊበራሊዝም ቢሰብክ ውዠንብርን ብቻ ነው የሚነዛው። ህዝባዊ ፍላጎትን ሳይሆን የራሱን ጥቅም ብቻ ነው ተግባራዊ ለማድረግ የሚታገለው። አሁን ባለው የአገራችን የተወሳሰበና የተመሰቃቀለ ሁኔታ የግዴታ ስራ ሊያስራና መፍቴሄ ሊሰጥ የሚችል የሁላችንም መመሪያ የሆነ የጋራ ሃሳብ ማዳበር የሚያስፈልግ ይመስለኛል።

በመሆኑም ማንኛውም ስለ አገሬ ያገባኛል የሚል ግለሰብም ሆነ የፖለቲካ ድርጅት ማንሳትና መመለስ የሚገባቸው ጥያቄዎች አሉ። 1ኛ) በአገራችን የተንሰራፋውን ረሃብና እንደ ባህል የተወሰደውን እንዴት አድርጎ በአምስት ዐመት ጊዜ ማጥፋት ይቻላል? ብሎ መመለስ ያስፈልጋል። 2ኛ) ከዚህ በመቀጠል በምን ዘዴና መሳሪያ ድህነትን በሃያ ዐመት ጊዜ ውስጥ ማስወገድ ይቻላል? ብሎ መጠየቅና ተገቢውን መልስ ለመስጠት መዘጋጅተ ያስፈልጋል። 3ኛ) እንዴት አድርጎ ቀስ በቀስ ለላይኛው ጥያቄዎች መልስ ሊሰጡ የሚችሉ ቀልጣፋ ኢንስቲቱሽኖች መገንባት ይቻላል ? የሰው ኃይልንም እንዴት ማሰልጠንና ማሰማራት ይቻላል ? በሚለው ላይ በበቂው መነጋገር ያሻል። 4ኛ) ከዚህ ስንነሳ እንዴት አድርጎ ያሉትን የሰውም ሆነ የተፈጥሮ ሀብቶችን በማንቀሳቀስ አንድ ጠንካራ ህብረተሰብ ገንባት ይቻላል? ብሎ መጠየቅና ለመልስ መዘጋጅት የማይታለፍ መሰረታዊ ሃሳብ ነው። 5ኛ) ከዚህ ስንነሳ በመንግስት፣ በህብረት ስራና በግለሰብ ተሳትፎ መሀከል የስራ-ክፍፍል በመፍጠር እንዴት አድርጎ የተሳሰረ ኢኮኖሚ መገንባት ይቻላል? ለሚለው በቂ መልስ መስጠት የምሁሩ የቤት ስራ ነው። 6ኛ) መንደሮችን፣ ከተማዎችናን የመኖሪያ ቦታዎችንና ልዩ ልዩ ለንግድና ለፋብሪካ የሚሆኑ ቤቶችንና መደብሮችን በምን ኃይልና በምን ሀብት መስራት እንችላለን?  በሚለው ላይ መነጋገሩ ሌላው አንገብጋቢ ጥያቄ ነው። ባጭሩ በሰላሳና በሃምሳ ዐመታት ውስጥ ልዩ መልክ የምትይዝና ውስጠ-ኃይሏ ጠንካራ የሆነ  ኢትዮጵያን በምን ዘዴና በምን ኃይል፣ እንዲሁም ሀብት መገንባት ይቻላል፟? የሚለውን ጥያቄ ተቃዋሚው ኃይል መመለስ ያለበት ይመስለኛል።  በዚህ መልክ ብቻ ትግላችን መልክ ሊይዝ ይችላል። መልካም ንባብ !!

 

ፈቃዱ በቀለ

                                                                                 fekadubekele@gmx.de

 

የጠቢባን አባባል፣     ጓደኛህን ንገረኝና ማንነትህን እነግርሃለሁ !!

                                                               

 

5 Comments

  1. ዽር ፈቃዱ

    Ethiopia le achir Gizem behon be nech altegezachim !!!

    5 amet ke talyan gar yeneberew,,,Gize ye Filmeya weqt neber !!!!

    yehen neger keyet ametut ??????? !!!!!!

  2. ** ኢህአዴግ ፳፪ ዩኒቨርስቲ ከፍቶ መምሕራኖቼ ሀገር በታኝና ትውልድ አጥፊ ዘሮችን ፡ጎጠኝነትን ጠባብነትን የሃይማኖት አክራሪነትን እያስተማሩልኝ ነው በማለት በጠ/ሚ ማዕረግ የህወአት ወንበር ጠባቂ አቶ ኀይለመለስ ደስአለኝ.. አርስት ፈጥረው ማጯጯህ ጀምረዋል…
    *** ይህ ሁሉም በአንድ የፖለቲካ ጥላ ሥር የማጎር አባዜ! አንድ ሓሳብና አመለካከት ..አንድ የዜና ምንጭ!..አንድ የሙት ራዕይ የማስቀጠል እርብርብ! ሀገሪቷንም፣ ያለውንም የሚመጣውንም ትውልድ ከማባከንና ከማምክን …የዱላ ቆረጣ የደቦ አመራር ሳይሆን የሚያወጣውና ዘላቂ የኅብርተሰብ ለውጥ የሚመጣው ..የአስተሳሳብ ነፃነት! የመናገር የመጠየቅ መልስ የማግኘት መብት! እንደሰው መከበርና የመደመጥ! መልካም አስተዳዳርና ፍትህ! ለማሟላት ሕዝብ በተለይም ወጣቱ ከትርክሚርኪ የሬዲዮ፣ የጋዜጣ፣ የቲቪ፣ አንድ ዓይነት የወሬ ሰላባ ሆኖ አድራቂና አፍራሽ የውጭ ባሕል እየቀዳ ዓይኑን አፍጦ ማንነቱና ምንነቱን ከሚያጣ፣ቁጭ ብሎ ከሚያማርር፣ በአማራጭ የሚዲያ አውታሮች ዶ/ር ፈቃዱ በቀለና ሌሎችም ምሁራን ለረጅም ዓመት በተለያየ አርዕስቶች የሚያስነብቧቸው እጅግ ጠቃሚ ድንቅ! ፅሑፎች በሚዲያ ላይ ለትውልድ ማስተማር ቢቻል ቢያንስ ባላፈው ፲ ዓመት ለሀገር አሳቢና ከሌላው ሀገር ሕዝብ እኩል ሰው መሆኑን የሚያምንና እኩል ሊያደርግ የሚችል ጥሩ ዜጋ ማፍራት በተቻለ ነበር። ይህ እንዳይሆን እስኪወራ የሚጠብቅ…የተነገረውን እንዳለ እየገለበጠ የሚያወራ… በአንድ አናጢ የተቀረፀ ፈሪ (አድናቂ) ትወልድ እንዲሆን ተፈርዶበታል!? ነበረን አንጂ አለን ብሎ ለሀገርና ለሕዝብ ተጨናቂ ሳይሆን ለግለሰቦች ኑሮ አዳማቂ ‘ተከልክሎና ተከልሎ’ ተለጣፊ(ጭፍን ተደጋፊ) ሆኖ መኖርን በመፈቃቀርና በመፈቃቀድ ላይ በተመሠረተ ማኒፌስቶን በፀጋ ተቀብሎ መቀጠሉ ያሳዝናል! ያስቆጫል! ያሳፍራል! ግን እስከመቼ? “ያዢ ያጣች ሀገር!” አሉ አባቴ ሠላም ለሁሉም በቸር ይግጠመን

  3. ትክክል! የወያኔ መወገድ ብቻ በራሱ ለኢትዮጵያ ህዝብ ለውጥ ሊሆን አይችልም ነገር ግን በኢትዮጵያ ውስጥ የአስተሳሰብ ለዉጥ እንዳይመጣ እንቅፋት የሆነዉ የትግሬዉ ነጻ አውጪ ክፉ ቡድን በሚቻለው መንገድ ሁሉ መወገድ የግድ ይላል:: የጀርመን ሀገር የዛሬዋ እድገት ያለ ሂትለር መወገድ እዉን ሊሆን ከቶ እንደማይቻለዉ በኢትዮጵያም ወያኔ ሳይወገድ የአስተሳሰብ ለዉጥም እድገትም እዉን ሊሆን ከቶ አይቻልም::

  4. Tplf,min alk? Lemehonu anchi manesh demo,lemayawiqish tategni.neqe nen bakish,hijina eza le dhadio ,nigeriw
    .weyim kefelegish le high definetion amakiriw.enkuan tenafitesh sititenefishiw,enawiqishalen,yalteboka lit enjera new bilesh sitaweri,hoodish yinefal enji,yanchi bado buhaqa man enjera yiliweal bilesh new.

  5. Thank you mr belew.i think you are right and 100 better.this guy seem nervous about what about to happen to tplf.you the write of tplf advocater through writing techinics ,do not wast time
    .hey 24 years is tplf is murderer ,then any one who is a victime chase after tplf cadre all over.

Comments are closed.

Share