የአባይ ግድብ ዲፕሎማሲ አጀንዳ! (ከግርማ ሞገስ )

(ግርማ ሞገስ)

በአለም አቀፍ ደረጃ እንደ አባይ ግድብ አወዛጋቢ የሆኑ ጉዳዮች ተፈጻሚነት የሚያገኙት አለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ትግል በማድረግ አለም አቀፍ ደጋፊ ማብዛት ሲቻል ነው። የዲፕሎማሲ ትግል ደግሞ ሰላማዊ ትግል ትግል በመሆኑ ብስለት እንጂ ክፉ ቃል አይሻም። ቀረርቶ ደጋፊን አስበርግጎ እንደሚያርቅ እና ለባላንጣ የማጥቂያ ቀዳዳ እንደሚከፍት ግልጽ ነው። የሆነው ሆኖ ይኽን ጽሁፍ እንድጽፍ ያነሳሳኝ የህውሃት ውጭ ጉዳይ ቴዎድሮስ እና አቻው የግብጹ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሰኔ 11 ግድም ዲፕሎማሲያዊ ውይይት አደረጉ ከተባለ በኋላ ቴዎድሮስ “አብረን እንዋኛለን ወይንም እንሰምጣለን” ማለቱን ካነበብኩ በኋላ በዚህ ጉዳይ ላይ ከኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ኃይሎች ጋር ውይይት መክፈት ያስፈልጋል የሚል እምነት ስላደረብኝ ነው።

“አብረን እንዋኛለን ወይንም እንሰምጣለን” የሚለው የቴዎድሮስ አባባል “ግብጽ እና ኢትዮጵያ ላይፋቱ ተጋብተዋል” ከሚለው የአምባገነን መሰል አባባል ብዙም የራቀ አይደለም። ሁለቱም ህውሃታዊ አነጋገሮች ናቸው። ስሜት በመቀስቀስ ኢትዮጵያውያንን ለማስከተል እና ስልጣን ለማጠናከር። የቀድሞው የህውሃት ውጭ ጉዳይ ስዩም መስፍን በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት ምን ሲል እንደነበር፣ በመጨረሻ ግን ጦርነቱ እና የባድመ ጉዳይ እንዴት እንዳከተመ እናስታውሳለን። ቴዎድሮስም ከስዩም መስፍን የተለየ አደለም። ትናንት ኤርትራን አስገነጠሉ። በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነትም አብረው ነበሩ። ዛሬም አብረው ናቸው። የሆነው ሆኖ የዲፕሎማሲ ትግል ‘አብረን እንዋኛለን ወይንም እንሰምጣለን” ከሚለው  አባባል ባሻገር እጅግ ሰፋ ያለ ነው። የዲፕሎማሲ ትግል ህግ፣ ፍትህ፣ ታሪክ፣ ሳይንስ፣ ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ፣ ሰበዓዊ እና ግብረገባዊ አድማሶች ያሉት የትንታኔ፣ የክርክር፣ የማግባባት፣ የማሳመን ትግል ነው። በተጨማሪ በኢትዮጵያዊነት መንፈስ ከልብ መደረግም አለበት።

 

ከ1938 እስከ 1945 ዓ.ም.  በነበረው በዚያ በጨለማ ዘመን እንኳን እነ ሎሬንዞ እና አክሊሉ ኃብተ ወልድ ከአለም አቀፍ ህግ አማካሪያቸው ከስፔንሰር ጋር ሆነው ኤርትራን ከኢትዮጵያ ለመቀላቀል ባደረጉት ዲፕሎማሲያዊ ትግል የእነ ካናዳን፣ ህንድን፣ ኖርዌይን፣ ግሪክን እና ሌሎች በርካታ አገሮችን ድጋፍ ሊያገኙ የቻሉት ዲፕሎማሲያዊ ትግላቸው በሳል በመሆኑ ነበር። ከልባቸው ያደረጉትም ትግል ስለነበር ነው። በቅድሚያ በምርምር እና በጥናት የተመሰረተ በሳል የዲፕሎማሲ ትግል አጀንዳዎች በመቅረጻቸው ነበር። ዛሬ ጊዜውም እንደያኔ ጨለማ አይደለም። የኃያላን መንግስታት አስተሳሰብ ከቅኝ ገዥነት በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ተለወጧል። ዛሬ አፍሪካውያን በተባበሩት መንግስታት ከ50 በላይ መቀመጫ አላቸው። ያኔ እነ ሎሬንዞ እና አክሊሉ ኃብተ ወልድ በተባበሩት መንግስታት መድረክ ለኢትዮጵያ ከልባቸው ሲታገሉ መቀመጫ የነበራቸው እና የድጋፍ ድምጽ የሚሰጡዋቸው ኢትዮጵያ እና ላይቤሪያ ብቻ ነበሩ። ለፍትህ የሚደረግ የዲፕሎማሲ ትግል ከዚያ ከጨለማ ዘመን ይልቅ ዛሬ የማሸነፍ እድሉ ከፍተኛ ነው። ሆኖም ግን በሳል የዲፕሎማሲ ትግል አጀንዳዎች መቀመር እና ከልብ መታገል ያስፈልጋል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የኦርቶዶክስ ቤት ክርስቲያንን አንድ ሊያደርግ የሚችል የመፍትሄ ሃሳብ !

 

ኢትዮጵያ የምታካሂደው የዲፕሎማሲ ትግል ከግብጽ ሳይንትስቶች፣ መሃንዲሶች፣ የህግ አዋቂዎች እና የዴሞክራሲ ኃይሎች ጋር ውይይት መክፈት ቢችል እና በአለም አቀፍ መድረክ ደግሞ የአፍሪካ ህብረትን፣ የተባበሩት መንግስታትን፣ የአሜሪካን፣ የአውሮፓን፣ የአለም ባንክን፣ የአይ.ኤም.ኤፍን ድጋፍ ማግኘት ቢችል ግንባታው ቀላል ይሆናል። ስለዚህ የዲፕሎማሲ ትግሉ ጥናት ላይ የተመሰረቱ አጀንዳዎች ሊኖሩት ይገባል።  የቀድሞ አባቶቻችንን ድሎች እየጠቀሱ እኛም እንደግመዋለን አይነት አኪያሄድ አይጠቅምም። የሚከተሉት የዲፕሎማሲ አጀንዳዎች ለኢትዮጵያ አባይ ግድብ ግንባታ ዲፕሎማሲ ትግል ሊያገለግሉ ይችላሉ የሚል እምነት አለኝ፥

 

አጀንዳ አንድ (1)፥ ግድቡ በሸለቋማ ቦታ ላይ በመገንባቱ በትነት የሚባክነውን ውሃ ዝቅተኛ ያደርጋል።

 

አጀንዳ ሁለት (2) በግድቡ የሚሰበሰበው ውሃ ቁልቁል ሲለቀቅ መዘውሮችን (Turbines) በመምታት ያመቀውን ኃይል (Energy) ወደ መዘውሮቹ ካስተላለፈ (እንዲሽከረከሩ በማድረግ) በኋላ የሚስፈነጠረው ውሃ ወደ ኢትዮጵያ ሳይሆን ወደ ሱዳን ስለሚፈስ ወደ ግብጽ የሚሄደው የአባይ ውሃ አይቀንስም።

 

አጀንዳ ሶስት (3)፥ ግድቡን ለመሙላት የሚያስፈልገው ውሃ በግብጽ ላይ ስጋት መፍጠር የለበትም። በበጋም ሆነ በክረምት ወደ ግብጽ የሚፈሰው የአባይ ውሃ ግብጽን አልፎ ሜድትራኒያን ባህር ስለሚገባ የኢትዮጵያ፣ የሱዳን እና የግብጽ ሳይንትስቶች እና መሃንዲሶች ከአለም እክስፐርቶች ጋር ሆነው ምን ያህል ውሃ ግድቡ ውስጥ እንዲቀር ማድረግ እንደሚቻል ማስላት ይችላሉ። ግድቡን ለመሙላት ከበጋ ይልቅ በክረምት ከፍ ያለ የውሃ ማስቀረት እንደሚቻል ግልጽ ነው።

 

አጀንዳ አራት (4)፥ ከአባይ ወንዝ ውሃ በተጨማሪ ከሱዳን የኤሌክትሪክ መስመሮች ጋር በመተሳሰር ግብጽ የምታገኘው ተጨማሪ ጠቀሜታ እንዳለም የግብጽ እና የአለም ህዝብ እንዲያውቅ ዲፕሎማሲያዊ ቅስቀሳ መደረግ አለበት። ለምሳሌ ግብጽ እና ጆርዳን የኤሊክትሪክ መስመራቸውን አስተሳስረዋል። የኤሌክትሪክ መስመሮቻቸውን ለማስተሳሰር በየብስ ከግብጽ ወደ ጆርዳን በመማዎች ማጓጓዝ ስላልቻሉ ከፍተኛ ወጪ አውጥተው መስመሩን በቀይ ባህር ወለል ስር ቀብረው የሁለቱን አገሮች የኤሌክትሪክ መስመሮች አስተሳስረው የኤሊክትሪክ ኃይል ይነጋገዳሉ። በቅርቡ ደግሞ ግብጽ ከሳውዲ ጋር ለማስተሳሰር ስምምነት ጨርሳለች። ግብጽ ለጆርዳን ከምተሸጠው የኤሌክትሪክ ኃይል ውስጥ የተወሰነው የኤሊክትሪክ ኃይል ከኢትዮጵያ የሚፈሰው አባይ አስዋን ግድብ ላይ ከሚፈጥረው 2 ሺ አንድ መቶ ሜጋ ዋት መሆኑን አንባቢ ልብ ይበል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የጦርነቱ ፍትሀዊነት እና ፋይዳ! - ከናፍቆት ገላው

 

አጀንዳ አምስት (5) 09 JUNE 2013 ሪፖርተር ጋዜጣ ከቀድሞ ዲፕሎማት አምባሳደር ኃይሉ ወልደ ጊዮርጊስ ጋር ባደረገችው  ቆይታ የውሃ አጠቃቀምን አለም አቀፍ ህግ አስመልክታ ላቀረበችላቸው ጥያቄ አምባሳደሩ መልስ “በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስብሰባ ላይ 101 የድምፅ ድጋፍ፣ በሦስት ተቃውሞና 27 ድምፀ ተአቅቦ ያለፈው የውኃ ኮንቬንሽን የኢትዮጵያን አቋም የሚደግፍ ነው፡፡” ይህን ሁሉ የግብጽ ህዝብ እንዲያውቅ ይደረግ።

 

አጀንዳ ስድስት (6)፥ ግብጽ ከመቶ አመቶች በኋላ የህዝቤ ብዛት 3 መቶ ሚሊዮን ወይንም ከዚያ በላይ ሊሆን ይችላል ከሚል የተደበቀ ስሌት አባይ ይለቀቅልኝ ማለት እንደማትችል ግልጽ መሆን አለበት። 

 

አጀንዳ ሰባት (7)፥ የቅኝ አገዛዝ ዘመንን ውል ኢትዮጵያ እንደማትቀበል በጠዋት ግልጽ መደረግ አለበት። የአባይ ውሃ ባለቤትነት እና የመጠቀም መብታችንን ለድርድር እንደማናቃረብ ህግን፣ ታሪክን፣ ፖለቲካን፣ ኢኮኖሚን እና ግብረገብነትን መሰረት ያደረጉ ትንታኔዎች ማቅረብ።

 

አጀንዳ ስምንት (8)፥ ግብጽ የሚገባው ነጭ አባይ 85% ያህሉን ውሃ የሚያገኘው ከኢትዮጵያ ወደ ሱዳን ከሚፈሱት ጥቁር አባይ (70%)፣ ተከዜ (5%) እና ባሮ (10%) ወንዞች ነው። እነዚህ ሶስት አውራ ወንዞች የሚፈጠሩት በኢትዮጵያ ከተለያዩ ቦታዎች ከሚነሱ በርካታ ገባር ወንዞች ነው። ግብጽ በጸበኛነት የምትቀጥል ከሆነ ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብ ከየአካባቢው የሚነሱትን ትናንሽ ገባር ወንዞች አቅጣጫ ይቀይራል። ከኢትዮጵያ ወደ ሱዳን የሚፈሰው ውሃ መጠን እጅግ ዝቅ ይላል። ግብጽ በወታደራዊ ኃይል የባሮ ወንዝ ከሚገኝበት ደቡብ ምዕራብ ጀምሮ እስከ ሰሜን ምዕራብ ድረስ ሁልጊዜ መዋጋት አትችልም። ይኽን ሃቅ ግብጾች፣ አሜሪካ፣ አውሮፓ፣ የአለም ባንክ፣ አይ.ኤም.ኤፍ. ሁሉ እንዲገነዘቡት እና የግብጽ ጸበኛነት የማያዋጣ መሆኑ ወለል ብሎ እንዲታያቸው ማድረግ።

 

አጀንዳ ዘጠኝ (9)፥ ግብጽ ጦርነት ከመረጠችም ከምታገኘው ጥቅም ይልቅ የሚደርስባት ኪሳራ ብዙ ነው። ጦርነት ለማኪያሄድ የምታወጣው እና በጦርነት ጀማሪነት እንዲሁም ለደረሰችው ጉዳት የተባበሩት መንግስታት ይቀጣታል።  

 

አጀንዳ አስር (10)፥ ኢትዮጵያ እራስዋን የመከላከል መብቷ የተከበረ መሆኑንም የዲፕሎማሲው ትግል ጨምሮ ይገልጻ።     

 

እነኚህ አስር (10) አጀንዳዎች ቢተነተኑ ትልቅ ሰነድ እንደሚወጣቸው ግልጽ ነው። እነዚኽን አሳቦች ካለቀረርቶ ለግብጻውያንም ሆነ ለአለም ህዝብ ወዝ እና ቁርጣኛነት በግልጽ በሚታይበት አነጋገር በማቅረብ ቢያንስ የግብጽን የተወሰነውን የዴሞክራሲ ኃይል ድጋፍ ማግኘት እና አለም አቀፍ ደጋፊዎችን ብዛት ማሳደግ እንደሚቻልም ግልጽ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ኢታርእየኒ ሙስናሃ ለኢትዮጵያ (የኢትዮጵያን ጥፋቷን አታሳየኝ) - ከይኄይስ እውነቱ

 

የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ኃይሎች ዲፕሎማሲያዊ ትግላቸውን እንዴት ማኪያሄድ ይችላሉ? በብዙ መንገዶች ማኪያሄድ ይችላሉ። በአገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ምሁራን የሚዘጋጁ የበሰሉ የምርምር ጽሑፎችን እና የዲፕሎማሲ ትግሉን ሂደት ደረጃዎች እየተከታተሉ እነ አንድነት ፓርቲ፣ ሰማያዊዎች እና ሌሎች የዴሞክራሲ ኃይሎች የሚያወጧቸውን መግለጫዎች በየድረገጹ በማቅረብ። ድረገጾቹ ለግብጽ ዴሞክራሲ ኃይሎች፣ ለአሜሪካ፣ ለአውሮፓ ዲፕሎማቶች እና የቀድሞው የዓለም አቀፍ አቶሚክ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ለነበረው ለነ መሐመድ አልባራዳይ አይነቱ የግብጽ ዴሞክራሲ ኃይሎች ተደራሽነት ቢኖራቸው ጥሩ ነው። የቀድሞው የዓለም አቀፍ አቶሚክ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር የነበረውን መሐመድ አልባራዳይ እና ሌሎች ግብጻውያንን በመጋበዝ ህዝብ ለህዝብ የሚሉ ጉባኤዎች በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ አዘጋጅቶ መነጋገርም ይቻላል። ተደጋጋሚ ቢሆን ጥሩ ነው። በአለም ውስጥ የተሰራጩት ኢምባሲዎች ይኽን አይነቱን ዲፕሎማሲያዊ ቅስቀሳ ቀደም ብለው ማድረግ ነበረባቸው። ችግሩ ህውሃት (ቴዎድሮስ አድሃኖም እና ገብረ ክርስቶስ ) ያላዘዛዋቸውን አያደርጉም።

 

ስለዚህ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ኃይሎች በአባይ እና በአገራቸው ጉዳይ የዲፕሎማሲ ትግሉ ባለቤት መሆን አለባቸው። አንድ ነገር በግልጽ መታወቅ አለበት። የኢትዮጵያ ዲሞክራሲ ኃይሎች በራሳቸው አነሳሽነት መራመድ ካልጀመሩ ህውሃት የዲፕሎማሲ ትግል አጋር እንዲሆኑም ሆነ ወደፊት በሚደረጉ ምርጫዎች በነፃ ተፎካክረው ስልጣን እንዲጋሩት ወይንም አሸንፈውት አገር እንዲያስተዳድሩ ፍጹም አይፈልግም። የዴሞክራሲ ኃይሎች ከዳር ቆሞ ተመልካችነትን ከመረጡ የኢትዮጵያ ህዝብም በአባይ ጉዳይ ሆነ በሌሎች ጉዳዮች ያለኝ ጠበቃ እና ጠባቂ ህውሃት ብቻ ነው የሚል አደገኛ እምነት ሊፈጠር ይችላል። የህውሃትም ፍላጎት የኢትዮጵያ ህዝብ በህውሃት ላይ እንዲያመልክ ማድረግ ነው። ስለዚኽ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ኃይሎች የአባይም ሆነ የኢትዮጵያ ባለቤትነታቸውን እና ሌሎች የሚጠበቁባቸውን ህዝብ የመምራት ግዴታዎች ለመወጣት ህውሃት የዘጋባቸውን በር እስኪከፍትላቸው መጠበቅ የለባቸውም። የመግለጫ ጋጋታም ህውሃት የዘጋውን በር አይከፍትልህም። የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ሰራዊት ህውሃት የዘጋውን በር እራስህ ከፍተህ በአገርህ ጉዳይ በአቻነት መሳተፍ መጀመር አለብህ! በህዝብህም ዘንድ ሆነ በአለም አቀፍ ደረጃ መታወቅን እና ክብርን የሚያስገኝልህ ብሎም ፕሮግራምህን ተፈጻሚ ማድረግ የምትችለው እንደነዚህ አይነት ስራዎች ስትሰራ ብቻ ነው!

4 Comments

  1. Ethiopian Leaders must use this type of matured wisdom.
    we must organize.
    Great.

  2. ደገመው በለው! ግርማ ሞገስ ያለው ምክር ነው።
    ለእውነት ለመናገር :
    *የወያኔ ሀገርን በፓርቲ መተዳደሪያ ደንብና (በቡድን ) በክልል ልጅ፣ ባምቻ ጋብቻ፣ በዘርና ጎሳ፣ መምራት ።
    *አሁንም በኀይለመልስ (የኅብረት አመራር)(የደቦ) የቀረበ፣ የቻለ መልስ ይስጥ! …የኢነርጂ ሚ/ር የመንገድ ትራንስፖርት ኃላፊ ! የኮምንኬስን ሚ/ር የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ! የጤና ሚ/ር የዕድገትና ትራንሰፎርሜሽን ዋና ፀሐፊ! የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚ/ር የብድርና ቁጠባ የልማት ዘርፍ በቻይና ተወካይ ሲሆን (ዞሮ ህወአት) ብቻ ሲሆን…በፕሮፓጋንዳና ቅስቀሳ ሰድብና ዝልፊያ የተጨቆኑና ማንነታቸውን ላለፉት ፳፪ ዓመት ፈልገው ያገኙ መጠቀሚያ መሳቂያ መሳለቂያ ሲአደርጓቸው። እንደሚያናድደኝ ሁሉ፤
    **ተቃዋሚው አንድነት ይልና ፲፩ባንዲራ ይዞ ይጮሃል…የፖለቲካ ምህዳር ጠበበ ይልና ሰፊውን የትግል ዘርፍ ይዘነገዋል…ኅብረት ይሉና የአማራ ልጅ፣የቀድሞው ባለሥልጣናት ትውልዶች፣ የኦሮሞ ዘር፣ የቋንቋ አደረጃጀትና አሰላለፍ ይላል…ችግሩ ያለው “የሚናገሩበት ቋንቋ ላይ ሳይሆን”…. “የሚናገሩት ነገር ምን ፍሬ አለው? ? ?”

    ዛሬም እንደወትሮው የተከበሩ ግርማ ሞገስ ለተፎካካሪ ፓርቲዋች ጠቃሚ ሥራን ጠቁመዋል፤ያለው መንግስት አድበስብሶ የጦርነት ነገሪት ይጎሸም ያለው ጨርሶ ከእውነት የራቀ፣ የቁራ ጩኸት ነው!፤ለመሆኑ በአንድ ሳምንት የተስማሙት በምንድነው? “የአባይ ጉዳይ የዛፍ ላይ እንቅልፍ የሆነባት ግብፅና ለሥልጣን ፀብ ጫሪው ህወአት” በሚለው ፅሑፋቸው ላይ የሰጠሁትን አስተያየት ያንብቡ ከምስጋና ጋር!

    ይህ መንግስት ተብዬ ኢህአዴግ በሥልጣን እስካለ ድረስ ከማናቸውም ጎረቤት ሀገር ፀብ የለም! አይኖርም! ችግር ሲፈጠር ግን እራሱ ወያኔ አሁን በሰው ላይ የደፈደፋትን የማጥቃት፣ የማፍረስ፣ የማተራመስ፣ የማሸበር ፣ወሬ ሁሉ እራሱ ተመለሶ የሀገር ጠላት! የትውልድ ጠንቅ!አካባቢው አተራማሽ ለመሆን የብጥብጥ አውድማን አሁን እየለቀለቀልህ ነው ከወዲሁ ከመወቃትህ በፊት ተጠንቀቅ በለው!በቸር ይግጠመን ከሀገረ ካናዳ ይቀጥላል>>>>

  3. Nothing new this is idea has been written by ethiopian government .please my dear respect for copy right .

Comments are closed.

Share