ሁለት የአረና ለትግራይ ሥራ አስፈጻሚ አባላት ከፓርቲው ለቀቁ

አቶ ግዑሽና አቶ አስራት (ዘ-ሐበሻ) ለረዥም ጊዜ መድረክ ወደ ውህደት እንዲመጣ ሲለፉና ሲታገሉ የነበሩት ሁለት ለአረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ለሉአላዊነት ሥራ አስፈጻሚ አባላት ከፓርቲው ራሳቸውን ማግለላቸውን ለድርጅቱ በጻፉት ግልጽ ደብዳቤ አስታወቁ። አስራት አብርሃም የተባሉ የዓረና የስራ አስፈፃሚ አባልና የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ እንዲሁም፤ ጉዕሽ ገብረፃዲቅ የዓረና የስራ አስፈፃሚ አባልና የድርጅት ጉዳይ ሀላፊ የሆኑት እነዚህ ሁለት የድርጅቱ አመራር አባላት ከድርጅቱ ለመልቀቅ ለምን እንደወሰኑ በጻፉት ግልጽ ደብዳቤ ላይ “እኛ ፓርቲውን ለመመስረት ከታሰበበት ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች እስካሁን እየሰራን መቆየታችን የሚታወቅ ነው። ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመድረክ ውስጥ እየተከሰተ ባለው ፖለቲካዊ ድባብና በሌሎች ከዚህ ጋር ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ፓርቲው ሁኔታውን ገምግሞ፣ “መድረክ ከዚህ በኋላ ወደ ምንፈልገው ግብ ያደርሰናል ወይስ አያደርሰንም? በእኛ በእኩል መድረክ ወደ እሚፈለገው ግብ እንዲደርስ ምን ዓይነት እስትራቴጂና የትግል ስልት እንከተል?” የሚሉ ጉዳዮች በጥልቀት ለማየትና የእስትራቴጂ ማስተካኪያ ለማድረግ ያለው ፍላጎት ዝቅተኛ መሆኑን በመገንዘብ፤ ከዚህም በተጨማሪ በዓረና ውስጥ እየተስተዋሉ ባሉት እንግዳ ሁኔታዎች ምክንያት ፓርቲው እንዲከፋፈልና እንዲዳከም የሚያደርጉ መሆናቸውን በመገንዘብ፤ ይህን ሁኔታ ለማረም ደግሞ በሌሎች የስራ አስፈፃሚ አባላት ዘንድ ዳተኝነት መኖሩ ግልፅ እየሆነ በመምጣቱ፤ የዚህ አካል ላለመሆንና ፓርቲውን ደግሞ የበለጠ እንዳይከፋፈል በማሰብ፣ ይህ ደብዳቤ ከተፃፈበት ዕለት ጀምሮ ፓርቲውን ለመልቀቅ የወሰንን መሆናችንን በአክብሮት ለማሳወቅ እንወዳለን።” ብለዋል።
“ለዓረና/መድረክ አባላትና ደጋፊዎች በሙሉ ስላሳለፍነው ጥሩ የአብሮነት ጊዜ ማመስገን እንፈልጋለን። ብዙ የትግል ልምድ ካለው አመራር ጋር አብሮ መስራት በራሱ እንደ አንድ ትልቅ እድል ነው ምናየው። ለዓላማ የመኖር ፅናት፣ ትዕግስትና ፖለቲካዊ ተሞክሮ አግኝተንበታል። ከዚህ በተጨማሪም ስለአገራችን ፖለቲካ በተወሰነ መልኩም ቢሆን ለመረዳት እድል ፈጥሮልናል። በእዚያ ባሳለፍነው አስቸጋሪ የፖለቲካ ጉዞ ውስጥ ስብዕናህን የሚፈታተኑ፣ ትግል የምታደርግበትን ምክንያት እስኪጠፋህ ድረስ የሚያደርሱና ፀጉር የሚያቆሙ ብዙ አስቸጋሪ ሁኔታዎች የነበሩበት ቢሆንም፤ የዚያው ያህል ደግሞ ብዙ የተማርንበት፣ አቅምና ክህሎት ያገኘንበት፣ ከአገር ውስጥም ከውጭም ብዙ ለአገርና ለወገን ተቆርቋሪ የሆኑ ዜጎች ለመተዋወቅ ዕድል የፈጠረልን በመሆኑ ሁላችሁም እናመሰግናለን።” ያሉት አቶ አስራት አብርሃም እና ጉ ዕሽ ገብረጻዲቅ “ከሁሉም በላይ ደግሞ ዓረና የፖለቲካ ጥርሳችን የነቀልንበት፣ ስለሀገር፣ ስለሰው ልጅ፣ ስለስልጣን ምንነት፣ ስለሁሉም ነገር በጥልቀት እንድናውቅ ዕድል የሰጠን ፓርቲ በመሆኑ በህይወታችን ሁሉ ስናስታውሰው የሚኖር ነው። ባለፉት ስድስት ዓመታት የተማርነው ነገር ብዙ ነው፤ አገራችን የብዙ ችግሮች ባለቤት መሆኗም ተገንዝበናል። ይህ ሁሉ ችግር ለማቃለልም አሁንም ቢሆን እልህ አስጨራሽ ትግል ማድረግ ግድ የሚል መሆኑን እንረዳለን፤ ከዚሁ ትግል ደግሞ እኛ ወደኋላ እንል ዘንድ ስብዕናችንና ተፈጥሯዊ ባህርያችን የሚፈቅድልን አይደለም።” ብለዋል።
“ዛሬ ከፓርቲው በዚህ ሁኔታ ብንለይም ፓርቲው እስከ አሁን ይዞት የመጣውን ለመርህ የመገዛት፣ በጋራ አመራር የማመንና ተግባብቶ የመስራት ባህሉ መቀጠልና መጠናከር አለበት እንላለን። ውስንነት ቢኖረውም ውስጣዊ ልዩነቶችን አቻችሎ የሚጓዝበት፣ ችግሮች ሲከሰቱ ደግሞ በሰከነ ሁኔታ የሚፈታበት መንገድ ለሌሎችም ትምህርት ሊሆን የሚችል ነው። ይህ ልምድም መጠበቅ አለበት። በአንፃሩ ደግሞ ጎጂ የሆኑ ዝንባሌዎች ማለትም ወግ አጥባቂነትን፣ ቡድናዊነትን፣ ግላዊ ጥቅመኝነትንና ስልጣን ወዳድነትን ሥር እንዳይሰዱ ነቅቶ መጠበቅና መታገል የሚገባ ነገር ነው።” ሲሉ በደብዳቤያቸው ላይ ያተቱት የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚዎች “በተለይ ደግሞ መድረክ አሁን ካለበት የተሻለ አደረጃጀትና አሰራር እንዲኖረው፣ በአባል ፓርቲዎች መሀከል ያሉትን ጥቃቅን ልዩነቶች በማቀራረብና በማመቻመች የተሻለ መተማመንና አብሮ መስራት የሚቻልበት ብሎም ወደ ውህደት የሚመጣበትን መንገድ እንዲፈጠር ጠንክሮ መስራቱ ለሁሉም የሚበጅ ነው የሚሆነው። ዓረና በዚህም በእኩል ከሸምጋይነት ሚናው ወጥቶ የበኩሉን አስተዋፅኦ ማድረግ የሚጠበቅበት ነው። ጠብ እና አለመተማመን በመርህ፣ ብሎም ተቀራርቦ በመስራት ይፈታሉ እንጂ የመርህ ችግር በሽምግልና የሚፈታ አይደለም።” ሲሉ አስረድተዋል።
“መድረክ የአመራር ዳይናሚዝም ለመፍጠር የሚያስችል አሰራር መከተል፣ ብቃት ያላቸው አዳዲስ አመራሮች ማብቃና ወደፊት ማምጣት ይጠበቅበታል። ነባርና ልምድ ያለው አመራር መኖር ለአንድ ፓርቲ እጅግ ጠቃሚ ቢሆንም የተለየ እንቅስቃሴ ማድረግ ግድ ለሚለው የሀገራችን ፖለቲካዊ ሁኔታ የሚመጥን ፖለቲካዊ አመራር መስጠት ባልተቻለበት ሰዓት ግን “የማርያም መንገድ አለኝ” ለሚል አዲስ አመራር ዕድል መስጠት ተገቢ ይሆናል። ደግሞም አመራርነት በብቃትና በአባላቱ ዘንድ በሚኖረው ቅቡልነት ላይ የተመሰረተ መሆን ይገባዋል እንላለን።” በሚል የተነተኑት እነዚህ ሁለት አመራር አባላት “ውድ የዓረና/መድረክ አባላትና ደጋፊዎች፣ እኛ ዜጋ በዜግነቱ የሚከበርባት፣ ፍትሃዊትና ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እስክትፈጠር ድረስ ፖለቲካዊ ትግሉን የምናቆም አይደለንም። ከዚህ በኋላም ቢሆን በሀሳብና በተግባር በአጠቃላዩ የሀገራችን የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ መኖራችን የሚቀጥል ነው የሚሆነው። እኛ የትግራይ ህዝብ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወገኑ ጋር ተስማምቶና ተግባብቶ ለመኖር ያለውን መልካም ፍላጎት ከማንፀባረቅና ከማሳየት ውጪ ሌላ ዓላማ የለንም። ከአሁን በኋላም ቢሆን ይህን ጉዳይ ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ ከመግለፅና ከማሳየት ወደኋላ የምንል አይደለንም። ከሁሉም በላይ ደግሞ በአገሪቱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፍትህ፣ ፖለቲካዊ እኩልነትና ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ማንነቱ፣ መብቱና ክብሩ እኩል ተጠብቆለት፣ በአገሪቱ ውስጥ እንደ ዜጋ በሙሉ ነፃነት የመንቀሳቀስ እና ሰርቶ የመኖር መብቱ ካለምንም ቅድመ ሁኔታ ሙሉ ለሙሉ እንዲከበር በምንችለው አቅም ሁሉ ከመታገል ወደኋላ አንልም።” ሲሉ የወደፊቱን የትግል አቅጣጫቸውን አስምረውበታል።
“በአንድ መንገድ ይሁን በሌላ፣ ለሁላችንም የምትስማማ፣ የተሻለች አገር ለመፍጠር መታገላችን እስከቀጠልን ድረስ ተለያየን አንልም። የእኛ እና የሌሎች በተለያዩ አቅጣጫዎች የሚደረጉ ትግሎች ተደማምሮ ነው ውጤት ሊመጣ የሚችለው።” የሚሉት አቶ አስራት እና አቶ ጉዕሽ “እንግዲህ በዚሁ ስንሰናበት ሀዘናችን በጣም ጥልቅ ነው። ስትለያይ ሀዘን መኖሩ፣ ቅር ማለቱ ያለና የማይቀር ነገር ቢሆንም ሀዘናችን እጅግ በጣም ጥልቅ እንዲሆን የሚያደርገው በዚህ ሁኔታ መለያየታችን ነው። ብፆት ሰላም ኹኑ! ድል ለዴሞክራሲያውያን ታጋዮች! ድል አዲሱ ኢትዮጵያዊ ትውልድ!” በማለት ለድርጅታቸው የጻፉትን ግልጽ ደብዳቤ ቋጭተዋል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የተመድ የሰብዓዊ መብት ም/ቤት በአማራ ጉዳይ | “ተፀፅችያለሁ ይቅርታ ለመጠየቅ እፈልጋለሁ” አብይ | የመራዊ ፖሊስ ጣቢያው ሙሉ በሙሉ በእሳት ጋየ

ይህ በ እንዲህ እንዳለ አቶ አስራት አብርሃም እና ጉዕሽ ገብረፃዲቅ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲን ይቀላቀላሉ ተብሎ በሰፊው እየተወራ ነው።

4 Comments

  1. This is a great failure to Merara and Endeshaw. As the two members said MEDREK can’t reform itself to current political situation of the country. Still, they don’t understand the people’s demand. Simply they are tied to ethnical ideology like Weyane. The Ethiopian people either Muslims or Christians need unity in diversity but MEDREK leaders stand contrary of that. Some of them wishes the Spanish Latino alphabet based Oromo language to be a national language. Also, some of them need the Raya-Kobo people to be included in the map of greater Oromia. This is simply waste of time not a struggle. God bless Ethiopia.

  2. Matured personality. God bless you both. I’m glad we are wintessing capable new generation poleticials and activists. We are sick of the old gurus.

  3. Weyane is behind them and the evil wolf Nege Sibaht are their new dirctor I mean compas..
    Monay is take under this gangster Tigria

Comments are closed.

Share