June 10, 2013
14 mins read

ወቅታዊው የአባይ ወንዝ ዲፖሎማሲ፣ ፖለቲካዊ ብዥታውና እንደምታው (ዶ/ር ዘላለም ተክሉ)

 

ካለፉት ጥቂት ሳምንታት ወዲህ ከሃገራችን፣በምስራቅና ሰሜን አፍሪካ እስከ መካከለኛው ምስራቅ ድረስ የሚሰማው የጂኦ ፖለቲካ ትኩሳት በዓባይ ወንዝ ተፋሰስ ልማት ላይ ያተኮረ መሆኑ ለሁላችንም ግልጽ ነው:: በተለይ ደግሞ  ወያኔ “ታላቁን የህዳሴ ግድብ” ግንባታ በማካሄድ ረገድ የወንዙን ተፈጥሮአዊ አቅጣጫ ማስቀየሩን በፕሮፖጋንዳ ማሽኖቹ እንደ “ትልቅ ድል” መለፈፍ ከጀመረ በኋላ የግብጽ መንግስትና ህዝቧን አስቆጥቷል፣ የወታደራዊና ፖለቲካዊ ብቀላና ጥቃት እርምጃ አማራጮችም በኢትዮጵያ ላይ ለመውሰድ ምክክሩ ተጧጡፏል:: በኢትዮጵያ በኩልም ገዢው መንግስት ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም በአንድ በኩል ግብጽ ልማታችንን ልታሰናክል እየጣረች ነው፣ተቀዋሚዎችም የግብጽ ተባባሪ እየሆኑ ነው ብሎ በማላከክ እየተፋፋመ የመጣውን የህዝብ የለውጥ ንቅናቄ ለማርገብ እያሴር ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የግብጽን መንግስት ግድቡን በተመለከተ “Win –Win Diplomacy” እንደሚከተል በመደጋገም እየተለማመጠ ይገኛል::

የእኔን ትኩረት የሳበው በተለይ ከአገዛዙ በቀጥታም  ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ተጠቃሚ በሆኑትና በየዋህነት ድጋፋቸውን የሚገልጹት (ከሊቅ እስከ ደቂቅ ያሉ) ወገኖቻችን ዓባይን በተመለከተ “Win –Win” የተባለውን ዲፕሎማሲያዊ አማራጭ ግብጽ ጦርነትም ከመረጠች ድባቅ እናደርጋታለን ከሚል ስሜት ጋር እየደበላለቁ መጠቀም እንደፋሽን አይሉት እንደልማድ በስፋት መያያዛቸው ነው::.

ለመሆኑ Win-Win የሚባል ዲፕሎማሲያው ቃል ምን ማለት ነው?

ይህ ቃል መሰረቱ የመጣው Game theory ከሚባል ሳይንሳዊ የጥናትና ምርምር ዘዴ ነው:: ይህ ዘዴ ተቃራኒ የሆኑ ቡድኖች/ ግለሰቦች የጋራ ጥቅማቸውን (Pay-Off) ለማስጠበቅ የሚወስዱት ስትራቴጂያዊ እርምጃ የሚቀነባበርበት ሞዴል ነው:: ይህም ስትራዴጂያዊ ውሳኔ በ ጨዋታ (Game) መልክ የሚቀመር ሲሆን ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ ተጫዋቾች (Players or Decision Makers) ሁለትና ከዚያ በላይ ስትራቴጂዎችን እየመረጡ በመወሰን ከፍተኛ ጥቅማቸውን እንዲያገኙ ይረዳቸዋል:: ይህን ሂሳባዊ ሞዴል ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ወታደራዊ ድሎችን ተዋዳድሮ ለማሸነፍ ጥቅም ላይ ይውላል:: አገራትን አቋርጦ የሚሄድን ውሃ (Transboundary River) በጋራ ለመጠቀም የሚደረግን ግጭት ለመፍታት ለሚደረግ ዲፕሎማሲያዊ ውሳኔ መስጫ መሳሪያነትም ፖለቲከኖችና ኢኮኖሚስቶች የሚጠቁበት ሞዴል ነው::

 

በዚህ ጨዋታ የሚሳተፉ ተጫዋቾች በሚመርጡት ስትራቴጂ መጣጣምና መለያየት የሚያገኙት ጥቅም ሊያንስ፣ ሊበዛ፣ ወይ ለብቻቸው ጠቅልለው ሊወስዱት ወይም ደግሞ ጠቅልለው ሊያጡት ይችላሉ:: በጨዋታው የመረጡት ስትራቴጂ ሁሉንም ተጫዋቾች ተጠቃሚ ካደረገ “ Win- Win” ጨዋታ ሲባል፣ ከተቃራኒ ተጫዋቾች ውስጥ አንዱ ብቻ ተጠቅሞ ሌሎቹ ምንም ካልተጣቀሙ “Zeo-Sum-Game” ይባላል::

የአባይን አጠቃቀም በተመለከተ እስካሁን ያለው የጨዋታ ሁኔታ:

ይህን ጥያቄ ለመመለስ በ Madani et al. ከታተመ የጥናት ጽሁፍ ውስጥ የተጠቀሱትን ስትራቴጂዎች ተጠቅሜያለሁ:: በዚህጥናትመሰረት የአባይን ተፋስስ የሚጋሩትን አሥር አገሮች ባላቸው ተጽእኖ ደረጃ በአራት ተጫዋቾች ተከፍለው ተቀምጠዋል:: እነሱም ኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ግብጽና ሌሎች የላይኛው ተፋሰስ ሃገሮች ናቸው:: ውሃውን ለልማት ተግባር በማዋል ረገድ እየተከተሉ ያለው ስትራቴጂም 1) በግጽና ሱዳን ብቻ እ.ኤ.አ በ 1959 የተፈራረሙትን ስምምነት አክብሮ መቀመጥ፣ 2)  በ1999 የተቋቋመውን የአባይን ተፋሰስ ኢኒሺዬቲቭ (Nile Basin Initiative) ተቀብሎና ተስማምቶ ውሃውን ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ተካፍሎ ማልማት፣ 3) እያንዳንዱ ሃገር በተናጠል ወንዙን ገድቦ ለመጠቀም መሞከርና በግብጽ በኩልም ይህን አማራጭ ሊጠቀሙ ባሰቡት ሃገራት ላይ ኢኮኖሚያዊ ፣ ፖለቲካዊና ወታደራዊ ጥቃት መሰንዘር ናቸው::  ኢትዮጵያና ሌሎች የላይኛው ተፋሰሱ ሃገራት በነበራቸው ደካማ ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ አቋም የተነሳ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የነበረው የጨዋታ ሁኔታም የ 1959 ስምምነት በውድም ይሁን በግድ ተቀብሎ ካለባቸው የውሃ ችግር ጋር መኖር ነበር:: ይህም “Zeo-Sum-Game” የሚባለውን የጨዋታ ዓይነት ያመለክታል::

ከቅርብ ጊዜ  ወዲህ የአባይን አጠቃቀም በተመለከተ እየታየ ያለው የጨዋታ ሁኔታ:

በ 2010 የላይኛው ተፋሰስ ሃገሮች የአባይ ተፋሰስ ኢኒሺዬቲቭ ፍሬምወርክን ከተፈረረሙ ወዲህ የታችኛውን ተፋሰስ ሃገሮች የበላይነት የሚፈታተኑ እርምጃዎች መታየት ጀምረዋል:: በተለይ ኢትዮጵያ የግብጽን ስምምነት ሳትጠብቅ 63 ሚሊዮን ሜትር ኩብ ሊይዝ የሚችል ትልቅ ግድብ ለመገንባት ከወሰነች በኋላ ግብጽ ይህንን ግንባታ ለማስቆም እስከ ሃይል መጠቀም የሚደርስ የማስፈራራት እርምጃ እየዛተች ትገኛለች:: እንግዲህ በዚህ አስጊ ሁኔታ ኢትዮጵያ ግድቡን ገንብታ የወንዙን ውሃ መሙላት ከጀመረች፣ በማለሙያዎች ግምት መሰረት ለሚቀጥሉት 5  ዓመታት ግብጽ ታገኝ ከነበረው 55 ቢሊዮን ኩዩቢ ሜትር ውሃ ውስጥ 20 በመቶውን ታጣለች ማለት ነው:: ይህም በግብጾች በኩል ተቀባይነት ስለማይኖረው ግጭት ያስከትላል፣ በዚህ ግጭትም ግብጽና ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆኑ ሱዳንና ሌሎችም የተፋሰሱ አገራትን ተጠቂ ይሆናሉ:: በዚህ ፍጥጫ አንጻር የሚገነባው “ታላቁ የህዳሴ ግድብ”  እንግዲህ “ Win- Win” ሳይሆን “Zeo-Sum-Game” የሚያስከትል ድፕሎማሲያዊ እንደምታ ይኖረዋል ማለት ነው::

በሁሉም የተፋሰሱ ሃገራት አሸናፊ የሆነ “ Win- Win” ጨዋታ ለመጫወት ከተፈለገ ሁሉም ሃገራት የአባይ ተፋሰስ ኢኒሺዬቲቭ ፍሬምወርክን ተፈራርመው ውሃውን እኩልና ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ተከፋፍለው መጠቀም ሲችሉ ነው:: በእርግጥ ኢትዮጵያ “ታላቁን የህዳሴ ግድብ” ለመገንባት ቆርጣ መነሳቷ ግብጽን ለስምምነት ወደጠረጴዛ ዙሪያ  እንድትመጣ ሊያስገድዳት ይችላል:: ነገር ግን ግብጽ ተስማማችም አልተስማማችም ግድቡን እንገነባለን የሚለው የኢትዮጵያ የተናጠል አካሄድ ከሆ ነ በረጅም ጊዜ ወደ “Zeo-Sum-Game” ይወስደናል ማለት ነው::

በጨዋታው የተዘነጋ ትልቅ ስትራቴጂ:

በኢትዮጵያ በኩል መካተት ከሚገባቸው የጨዋታው ስትራቴጂዎች ውስጥ የተዘነጋ  አንድ ትልቅ ቁም ነገር አለ:: በግብጽ በኩል ህዝቡ፣ ተቃዋሚ የፖለቲካ ሃይሎችና የሲቪል ማህበረሰቦች ሁሉ በወንዙ አጠቃቀምና ከተፈሳሱ ሃገራት ጋር ስላለው ፍጥጫ አንድ አቋም ይዘው፣ “ውሃችን ከተነካ ህልውናችን የለችም”፣ “በናይል የመጣ በብሄራዊ ደህንነታችን የመጣ ነው” እያሉ ከፍተኛና የተቀናጀ እንቅስቃሴ እያደረጉ ናቸው:: በኢትዮጵያ በኩል ግን መንግስት ግድቡን ከማቀድ ጀምሮ፣ ስራውን እስካስጀመረበት ጊዜ ድረስ የተናጠል የወያኔ ጥንስስና ጥንቅር አድርጎታል:: ህዝቡን በፍላጎት ሳይሆን በግዴታ ገንዘብ እንዲያዋጣ እያደረገው ይገኛል:: እስካሁን ከህዝቡ የተሰበሰበውን ገንዘብ ግልጽነትና ተጠያቂነት በጎደለው አኳኋን እያተስተዳደረው ይገኛል:: በግድቡ ላይ ስትራቴጂያዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ጥያቄ ያነሱ ወገኖቻችን እንደ ፀረ-ኢትዮጵያ፣ አሸባሪ፣ የኤርትራ ተላለኪ፣ ፀረ-ልማትና የመሰሰሉት ብሎ በመፈረጅ ማስፈራራት፣ማሳደድና ማሰር ስራዬ ብሎ ተያይዞታል:: በዚሁም የተነሳ ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆኑ በሃገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ግድቡ ከልማት ይልቅ የወያኔን አገዛዝ እድሜ ለማራዘም የታቀደ ሴራ ነው በማለት ተቃውሞ እያኪያሄዱ ይገኛል:: በቅርቡ በተለያዩ ምዕራባዊያን ሃገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በማሳተፍ ሊካሄዱ የታቀዱት የገንዘብ መዋጮና የቦንድ ሽያጭ ዘመቻዎች በተቃውሞ ስኬታማ ሳይሆኑ መቅረት ለዚህ እብቢተኝነት ትልቅ ምሳሌ ነው::

ወያኔ ከህዝቡ የሚፈልገውን መውሰድ ብቻ ሳይሆ ህዝቡ እንዲከበርለት የሚጠይቀውን መብትና ነጻነት እስላልሰጠው ድረስ የሚገደበው ግድብ የኔ ነው ብሎ እንደባለቤትነት አይመለከተውም:: ግድቡ የህዝቡን ነጻ ተሳትፎ፣ ፍላጎትና ጥቅም ባልጠበቀ ሁኔታ ቢገነባ ዘላቂነቱ አስተማማኝ አይደለም:: ሁሉም ኢትዮጵያዊ አምኖበትና ተስማምቶበት የሚገነባ ግድብ ቢሆን ኖሮ ለግንባታው የሚያስፈልገው 5 ቢሊዮን ዶላር ከሃገር ውጭ ባሉት ኢትዮጵያውያን ብቻ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በተሰበሰበ ነበር:: በዚህ ታላቅ ግድብ ግንባታ ዙሪያ ሁሉም ተቃዋሚ ሃይሎች ቢሳተፉ ኖሮ ለግብጽ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሻጥርና ወታደራዊ ጥቃት ተባባሪ ይሆናሉ የሚለውን ስጋት ሙሉ በሙሉ መድፈን በተቻለ ነበር:: በአጠቃላይ የግድብ ግንባታውን ለአፍራሽ ፖለቲካ ከመጠቀም ይልቅ ሁሉን አቀፍና ቀና በሆነ መልኩ ቢካሄድ ኖሮ ኢትዮጵያ ከተያያዘችው “Zeo-Sum-Game” ወደ “ Win -Win” ጨዋታ በተዘዋወረች ነበር::

የኢሳቱ ሬዲዮ መሳይ አሳምሮ እንደሚለው “ አገራችን ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር”!!!!!

Latest from Blog

መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። ) “ገብርዬ ነበረ

ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ?

January 3, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ዛሬ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ጥር 1ቀን 2025 ዓ/ም ነው ። አውሮፓውያኑ አዲስ ዓመትን “ሀ” ብለው ጀምረዋል ። አዲሱን ዓመት ሲጀምሩም ከልክ ባለፈ ፈንጠዚያ ነው ። ርቺቱ ፣ ምጉቡና መጠጡ

ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። )

Go toTop