ሊቀ ትጉሃን አስታጥቄ አባተ ተከሰሱ

(ዘ-ሐበሻ)  የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዝዳንት ሊቀ ትጉሃን አስታጥቄ አባተ በከፍተኛ የማታለል ወንጀል ተጠርጥረው ተከሰሱ። ሊቀትጉሃን አስታጥቄ በተመሰረተባቸው ክስ ጠበቆቻቸው ዋስትና ቢጠይቁባቸውም ፍርድ ቤቱ ግን ዋስትና ለመፍቀድ ወይም ላለመፍቀድ ዛሬ ውሳኔ ይሰጣል ቢባልም ዘ-ሐበሻ ይህ ዜና እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ አልደረሳትም።

በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 5ኛ የወንጀል ችሎት የማታለል ወንጀል ክስ የተመሰረተባቸው ሊቀ ትጉሃን አብረዋቸው ሁለት የማህበሩ አመራሮችም ክስ እንደተመሰረተባቸው መንግስታዊ ሚድያዎችም ጭምር ዘግበዋል። ለዘ-ሐበሻ እንደደረሱት መረጃዎች ከሆነ ሊቀትጉሃን በተለያዩ ክሶች የተከሰሱ ሲሆን ከነዚህም መካከል በ1998 ዓ ም ከአዲስ አበባ ከተማ አሰተዳደር ለአቅመ ደካማ ጀግኖች አርበኞች የተሰጠውን 25 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለግል ጥቅማቸውና ለወዳጆቻቸው አከፋፍለዋል የሚለው በዋነኝነት ተጠቅሷል።

የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አንድነት ማህበር ሊቀመንበርና አጋሮቻቸው የማህበሩን ሃብትና ንብረት ያለአግባብ ለግል ጥቅማቸው እያዋሉትና እየመዘበሩት እንደሚገኙ፣ አንዳንድ የማህበሩ አባላት እንደገለጹለት ጠቅሶ አውስትራሊያ የሚገኘው ጋዜጠኛ ቅዱስ ሃብት በላቸው ከወራት በፊት ዘገቦ እንደነበር ይታወሳል።  ጋዜጠኛው  ባጠናቀረው ዜና መሰረት የማህበሩ ሊቀመንበር የሆኑት ሊቀ ትጉሃን አስታጥቄ አባተ ከጥቂት ግብረ አበሮቻቸው ጋር በመሆን ቁጥሩ ቀላል የማይባል ጥሬ ገንዘብና ንብረት ለግል ጥቅማቸው አውለዋል። ከዚህም መካከል በዓመት 800 ሺህ ብር ከሚከራየው ህንፃ 240 ሺህ ብር፣ እንዲሁም ካሳንቺስ አካባቢ የሚገኘው የማህበሩ ንብረት ከሆነው ቡና ቤት ኪራይ የሚገኘው 150 ሺህ ብር የት እንደሚገባ ተለይቶ እንደማይታወቅ የማሕበሩን ም/ፕሬዚዳንት ጨምሮ ሌሎች የማህበሩ አባላት ማስታወቃቸውን፤ ከዚህም በተጨማሪ የአዲስ አበባ መስተዳድር ለአቅመ ደካማ የማህበሩ አባላት እንዲከፋፈል የሰጠው 15 የቀበሌና 30 የኮንዶምኒየም ቤቶች ውስጥም የማህበሩ ፕሬዚዳንትና ጥቂት አመራሮች የግል ቤት እያላቸው ለራሳቸው ከመውሰዳቸውም በተጨማሪ፤ የተቀረውንም ቢሆን አብዛኛውን ለቤተሰቦቻቸውና እነርሱ ለሚቀርቧቸው ጥቂት አባላት ማከፋፈላቸው ታውቋል ሲል ጋዜጠኛ ቅዱስሃብት በላቸው ዘግቦ እንደነበር ይታወሳል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የትግራይን ሕዝብ ጁንታ ብለህ ከጨፈጨፍክ በኋላ አሁን ደግሞ ጃውሳ ብለህ በአማራ ሕዝብ ላይ ሰይፍህን መዘዝክ

የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች ማህበር ከ1928 እስከ 1933 ዓ.ም ድረስ በዱር በገደሉ ተማርተው የፋሺሽት ኢጣሊያን ጦር ድል አድርገው ከአገር ባባረሩ አርበኞች የተቋቋመ ማህበር ነው።

Share