June 6, 2013
17 mins read

ከግብጾች እንማር – ግርማ ካሳ

 

Muziky68@yahoo.com
ግንቦት 28 ቀን 2005 ዓ.ም

ከካይሮ የጦርነትን ከበሮ እየሰማን ነዉ። ዩኒስ ማዮኡን የተባሉ ወግ አጥባቂዉ የእስላማዊ ፓርቲ መሪ፣ በኢትዮጵያ ያሉ ተቃዋሚና የታጠቁ ሃይሎችን ግብጽ መርዳት አለባት። አለበለዚያ የአባይ ግድብን በእኛዉ እጅ ማፍረሱ የግድ ነዉ» ሲሉ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያላቸውን ንቀት ገልጸዋል። የአቶ ዩኒስ ፓርቲ በፓርላማ ሃያ አምስት በመቶ መቀመጫ የያዘ ነዉ።

በግብጽ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን፣ በኢትዮጵያና በሕዝቧ ላይ የተጀመረዉ የማስፈራራት፣ የዛቻና የጥቃት እንቅስቃሴ የመጀመሪያ ሰለባ እየሆኑ ነዉ። ከፍተኛ ድብደባና እንግልት እየደረሰባቸው ሲሆን፣ ከፍርሃት የተነሳም ከቤታቸው ለሥራ፣ ምግብ ለመግዛት ብዙዎች እንደማይወጡ የሚገልጹ ሪፖርቶች እያነበብን ነዉ። ካይሮ ያለዉ የኢትዮጵያ ኤምባሲም ሳይቀር፣ ከአንዳንድ የሙስሊም ወንድማማች አክራሪዎች ጥቃት እንዳይደርስበት በታንክ ተከቧል። ሞርሲ በአባይ ጉዳይ ላይ፣ ሕዝቡ አንድ ሆኖ እንዲንቀሳቀስ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፣ በቅርቡም ኢትዮጵያን በማዉገዝ ሰላማዊ ሰልፍ በካይሮ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።

ይሄ እንግዲህ ግብጾች «የአገራችን ጥቅም ነዉ» የሚሉትን ለማስጠበቅ ያላቸውን ትብብርና አንድነት የሚያሳይ ነዉ። የግብጽም መንግስት የፓርቲን ጥቅም ከማስጠበቅ አልፎ በመሄድ ከተቃዋሚዎች ጋር ሲመካከር አይተናል።

ግብጾች በአባይ ጉዳይ ኢትዮጵያ ላይ ዘምቻ ሲያደርጉ፣ ከኢትዮጵያዉያን ይጠበቅ የነበረዉ ተመሳሳይ እንቅስቃሴ ነበር። አባይ፣ የፖለቲክ ጉዳይ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያዉያንን ሁሉ አንድ የሚያደርግ አገራዊ ጉዳይ መሆን ነበረበት። አዲስ አበባ ያለዉን ጨምሮ ሰላማዊ ሰልፎች በግብጽ ኤምባሲዎች ሁሉ መደረግ ነበረባቸው። ግን መሆን የነበረበት አልሆነም። እንደዉም የሚያሳዝነው አንዳንዶቻችን የግብጽ «ቃል አቀባዮች» የመሆን ዝንባሌ እየታየብንም እንደሆነ ነዉ።

ለዚህም በዋናነት ተጠያቂ የማደርገዉ ገዢዉን ፓርቲ ነዉ። ከጅምሩ «የአባይ ጉዳይ የኢሕአዴግ ሳይሆን የኢትዮጵያ ሕዝብ ጉዳይ ይሁን። አባይን የመገደብ ሥራ ዴሞክራሲን ባለመገደብ ይታጀብ። ፕሮጀክቱ በሁሉ ተቃዋሚዎች የተወጣጡ ባለሞያዎች ባሉበት ገለልተኛ ኮሚሽን ይመራ። በአባይና በልማት ስም የሰብአዊ መብት ረገጣ ይቁም። ሕዝቡ ደስ ብሎት እንጂ ተገዶና ታንቆ ገንዘብ እንዲያዋጣ አይደረግ። አባይ የፖለቲካ አጀንዳ አይሁን» እያልን ይኸው የአባይ ግድብ ወሬ ከተነሳ ጊዜ ጀምሮ ስንጮህ ነበር።

ነገር ግን የገዢው ፓርቲ ባለስልጣናት ሕዝቡን እየገፉት፣ እያዋረዱት፣ እያስጨነቁት ሊደግፈው ይገባ የነበረን ፕሮጀክት እንዲቃወመው እያደረጉት ነዉ። «ማር ሲበዛ ይመራል» አሉ አባቶች ሲተርቱ። ደግመዉ ፣ ደጋግመዉ ፣ ጠዋት፣ ማት፣ ሰኞ፣ ማክሰኖ፣ መስክረም ሰኔ፣ «አባይ ፣ አባይ» እያሉ ሕዝቡን አሰለቸቱት። ሕዝቡ ጣፋጭ የነበረው ነገር መረረዉ።

እዚህ ላይ በአባይ ዙሪያ የሚነሱ ተቃዉሞዎች፣ አባይ እንዳይገነባ ከመፈለግ የመነጩ ሳይሆኑ የአገዛዙ ብሶትና ግፍ የወለዳቸው ተቃዉሞዎች መሆናቸውን ቸል ማለት የለብንም። እንደዉም በቅርቡ በሲዘርላንድ የተደረገዉን የቦንድ ግዢ በመቃወም ሰልፍ የወጡ ኢትዮጵያዉያን ያሰሙት ከነበሩት መፈክሮች መካከል ጥቂቶቹን ብንመለከት ፡ «አባይ እንዲገነባ እንፈልጋለን። አባይ በተባባረ ክንዳችን ይገነባል። ከአባይ ግንባት በፊት ግን ዘረኝነት ይገደብ። የመብት ረገጣ ይገደብ» የሚሉትን እናገኛለን።

The Nile River has become a point of contention between Egypt and Ethiopia.
ከግብጾች እንማር - ግርማ ካሳ 1

ግብጾች ምን ለማድረግ እንደሚይስቡ ይኸው አሳዉቀዉናል። የሚያስፈራዉና የሚያሳዝነዉ ግን፣ ግብጽ በኢትዮጵያ ላይ ጥቃት ብትሰነዝር፣ ግብጽን መመከት የምንችልበት አቅም፣ ጉልበትና የሕዝብ ድጋፍ አለመኖሩ ነዉ። ደርግ አምስት መቶ ሺህ ጦር ይዞ የተሸነፈው፣ የሕዝብ ድጋፍ በማጣቱና በሕዝብ በመተፋቱ ነበር። በባድመ ጦርነት ጊዜ ሻእቢያ የተመታዉ፣ የኢሕአደግ ሰራዊት በልጦት ሳይሆን፣ ከኢሕአዴግ ጎን ሕዝቡ በመሰለፉ ነበር። ግብጽ የተባባረዉን የኢትዮጵያዉያን ክንድ መግጠም እንደማትችል እኛም እነርሱም እናወቀዋለን። አዲስ ነገር አይደለም፤ ከዚህ በፊት ሞከረዉ በጉንደትና በጉራ(አሁን ኤርትራ ዉስጥ ያሉ ከተሞች) ተዋርደው ነዉ የተመለሱት።

ያኔ የነበረዉ የሕዝብ አንድነትና መነቃቃት ግን አሁን የለም። ይሄንንም ባለስልጣናቱ እራሳቸው ያዉቁታል። እንደዉም የሕዝብን አንድነት እንተወዉና፣ በኢሕአዴግ ዉስጥ እራሱ አንድነትና መስማማት የለም። በአቶ መለስ ጊዜ የተለያዩ ሃሳቦች ቢሰነዘሩም በመጨረሻ አቶ መለስ ይወስኑ ነበር። አሁን ግን በአስተዳደር ላይ ማነቆ የሆነ፣ የቡድን አመራር ነዉ ያለዉ። ወታደሩን እና ደህንነቱን የሚቆጣጠረው፣ «ከበስተጀርባ ፈላጭ ቆራጭ እርሱ ነዉ» የሚባለዉ ሕወሃት፣ ለአቶ መለስ የቸረዉን ስልጣን ከአቶ ኃይለማርያም ላይ ቀንሶ እንደ አገር መሪ እንዳይንቀሳቀሱ ያደረጋቸው ይመስላል። የቡድን አመራር በሚል ፈሊጥ፣ አቶ ኃይለማርያም በነጻነት ለአገር የሚበጅ ዉሳኔዎችን እንዳያሳልፉ አስሯቸዋል። ደፍሮ ዉሳኔ የሚሰጥ አካል የለም። ባለስልጣናቱ ይፈራራሉ። አንዱ ሌላዉን አያምንም። ታዲያ ይሄ አይነት አመራር ነውን የኢትዮጵያን ሕዝብ አስተባብሮ፣ ከግብጽ የሚመጣን ወታደራዊም ሆነ ዲፕሎማቲክ ጥቃት ለመመከት የሚችለው ?

ሜዲያ ጋዜጣ ወዘተረፈ በታፈነበት ሁኔታ፣ በአንድ ድርጅት ብቻ በተጠራ፣ ለሶስት ሳምንታት ብቻ በተደረገ ዝግጅት፣ በመቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዉያን ተቃዉሟቸውን ሲያሰሙ አይተናል። ሰልፉም በአገዛዙና በሕዝቡ መካከል ከፍተኛ መቃቃሩ እየጨመረ ለመሆኑን ግልጽ አመላካች ነዉ። « ያኔ በባድመ ጊዜ አንድ እንሁን ፣ የጋራ ጠላታችንን እንዋጋ ሲሉን፣ አብረናቸው ተሰለፍን። ጦርነቱ ሲያልቅ ግን ጦራቸውን በኛ ላይ አዘመቱ። በዉጭ ወራሪዎች ላይ መቀሰር የነበረባቸው የመሳሪያዎች አፈሙዝ እኛ ላይ አነጣጠሩ። ግንባር ግንባራችን እየቀለቡ አረገፉን» እያለ ሕዝቡ በአገዛዙ ላይ ከዉጭ ወራሪዎች ባልተናነሰ ጥላቻ እያደረበት ነዉ።

እንግዲህ የሕዝብን አመለካከት መቀየሩ ቁልፍ ነዉ። ሕዝብን በማንኛዉ አገራዊ አጀንዳ ከጎን ለማሰለፍ ከተፈለገ፣ በቀዳሚነት ሕዝብን ማክበር ያስፈልጋል። ሰልፍ ያደረጉ በመቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዉያን በአዲስ አበባ ድምጻቸው ያስተጋቡበትን ታሪካዊ ሰልፍን ብንመለከት፣ አንድም ሰው ሳይጎዳ፣ አንድም ሱቅ ሳይዘረፍ፣ በሰላም የተደረገ፣ የኢትዮጵያዊ ጨዋነት የሰፈነበት ሰልፍ ነበር። ነገር ግን ይሄን ሰልፍ የጥቂት ሽብርተኞችና አክራሪዎች ሰልፍ በማለት አቶ ሬድዋን እና አቶ ሸመልስ ከማል አጣጥለዉታል። ይሄም ኢሕአዴግን እራሱ የሚጎዳዉና ያቀለለ ትልቅ ስህተት ነዉ። እርግጠኛ ነኝ እንደ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ አቶ ደመቀ መኮንን፣ ዶር ቴዎድርስ አዳኖም ያሉ በሳል የአመራር አባላት፣ የነዚህን ሰዎች አስተያየት አይጋሩም። እንደነዚህ አይነት የእንስሳ አይምሮ ያላቸውን ካድሬዎች ኢሕአዴግ ማባረር አለበት። ኢሕአዴግን ወደ መቃብሩ ይዘዉት የሚሄዱ መዥገሮች ናቸው። «ጥጋብ ክብርን ይራባል፣ የሚያገኘው ግን ዉርደትን ነዉ» እንዳሉት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም፣ ከጥጋብና ከእልህ ፖለቲካ ተወጥቶ ለአገርና ለሕዝብ የሚጠቅምን ነገር ማድረግ ያስፈልጋል።

ለማጠቃለል ሁለት ነገር ጣል አድርጌ ላቁም፡

አንደኛ፡ በመቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዉያን ሰልፍ አድርገው የጠየቁት ጥያቄዎች አለ። በጣም ቀላልና ጠቃሚ ጥያቄዎች ናቸው። ለነርሱም አዎንታዊ መልስ ቢሰጥ መልካም ነዉ እላለሁ። ጥያቄዎችን መመለስ ከምንም በላይ የሚጠቅመው ኢሕአዴግን እራሱ ነዉና።

ጋዜጠኖች፣ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች፣ የሙስሊም ችግር መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት በሙሉ በአስቸኳይ ይፈቱ። የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር የዲሞክራሲ ተቋማትን ማሻሻል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ቅንነት የሞላበት ድርድር ይደረግ። ለአረቦችና ለሕንዶች የሚሰጠው ለምለም መሬት ባለበት ይቁማና፣ ስምምነቶች በሙሉ እንደገና በገለልተኛ አካል ይጠኑ። እንደ ኤፈርት ያሉ ድርጅቶች ኦዲት ይደረጉ። በወታደር ደሞዝ ፎቅ የሰሩ ጀነራሎች ከየት አምጥተዉ ፎቅ እንደሰሩ ይመርመሩ። «የአሳ ግማቱ ከጭንቅላቱ» እንደተባላ ታች ያሉትን በሙስና ማሰር ሳይሆን፣ ቱባ ቱባ የሚያህሉ፣ ከላይ የተቀመጡ መዝባሪዎችና ደም መጣጮች ይጋለጡ። ሕዝቡ ለአባይ በጉልበት እንዲከፍል የሚደረገዉ በአስቸኳይ ይቁም። በባለሞያተኖች፣ ጠበቃዎች፣ የዲፕሎማሲ ጠበብት ያሉበት የአባይን ግድብ ስራ የሚመራ፣ ገለልተኛ እና በግልጽነት የሚሰራ የአባይ ኮሚሽን ይቋቋም። ይሄ የግንባታዉን ጊዜ ሊያራዝመው ይችላል። ግድ የለም ይራዘም። በጥራትና በጥንቃቄ መሄዱ ይሻላል።( ደግሞም ለአባይ ግድብ የሚያስፈልገዉን ሃይቅ ዉሃ ለመሙላት ሰፊ ጊዜ እንዲኖርም ያደርጋል። ያም ከግብጽ ጋር ያለዉን መቃቃር ሊያበርደው ይችላል፤ ለምን ግብጾች ሃይቁን ለመሙላት በአንድ ጊዜ ብዙ ዉሃ ይወሰድብናል በሚል ያላቸውን ፍርሃት ስለሚቀንስ )በዚህም መልክ አባይን የአገዛዙ ፕሮጀክት ሳይሆን የኢትዮጵያ ሕዝብ ፕሮጀክት ማድረግ ይቻላል።

ሁለተኛ፡ እርግጥ ነዉ ያገዛዙ የግፍ ቀንበር አፍንጫችን ላይ እየደረሰ ነዉ። ነገር ግን አሁን ባሉን የፖለቲካ ልዩነቶች ምክንያት ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ጎን መሰለፍ ግን ነዉር ነዉ። ለግብጾች መጠቀሚያ መሆን የለብንም። እርስ በርስ እንጣላ፣ ግን ጠላቶቻችን ፊት አንድ እንሁን። በተለይም ከተቃዋሚ መሪዎችና ከተቃዋሚ ሜዲያዎች፣ በአገራዊ ጉድዮች ላይ ትልቅ ማስተዋልና ሃላፊነት ይጠበቃል። አርቀን ከተራራና ከጊዜዉ ስሜታዊነት ባሻገር ማየት መቻል አለብን። የአገር ጉዳይ የሳይበር ስፔስ ጨዋታ አይደለም። «The Nile is Egypt and Egypt is the Nile» የሚለዉን የአንድ የግሪክ ፈላስፋ አባባል ግብጾች ሲይስተጋቡ እየሰማን ነዉ። እኛም «አባይ አባይ ያገር ሲሳይ» ወይም « The Nile is Ethiopia and Ethiopia is the Nile» እያልን ኢትዮጵያ የአባይን ወንዝ የመጠቀም ሙሉ መብት እንዳላት ማስተጋባት አለብን። ኢትዮጵያዊያን ኢትዮጵያዊን መሆን አለብን።

Latest from Blog

መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። ) “ገብርዬ ነበረ

ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ?

January 3, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ዛሬ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ጥር 1ቀን 2025 ዓ/ም ነው ። አውሮፓውያኑ አዲስ ዓመትን “ሀ” ብለው ጀምረዋል ። አዲሱን ዓመት ሲጀምሩም ከልክ ባለፈ ፈንጠዚያ ነው ። ርቺቱ ፣ ምጉቡና መጠጡ

ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። )

Go toTop