በኢትዮጵያ ውስጥ አገዛዙ የሚያካሂደው አፈና ተጠናክሮ ቀጥሏል – ሸንጎ

ጥር 16፣ 2007

ለአስቸኳይ ስርጭት

የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ (ሸንጎ) እራሱን በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የጫነው አገዛዝ በተቃዋሚ ድርጅቶች ላይ አፈናውን አጠናክሮ የቀጠለ መሆኑን ለመረዳት ችሏል።  በነገው ዕለት (ጥር 17 ቀን 2007 ዓ. ም) በአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትኅ ፓርቲ (አንድነት) አስተባባሪነት ሊደረግ ከታሰበው ሰላማዊ ሰልፍ አስቀድሞ የአገዛዙ የፀጥታ ኃይሎች ቢያንስ አራት የአንድነት ፓርቲ የአመራር አባላትን ማሰራቸውን ሸንጎ ተገንዝቧል።  ከታሰሩት ውስጥ፦

  1. አቶ አሥራት አብርሃም – የአንድነት የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ
  2. አቶ ሰለሞን ሥዩም – የአንድነት የ”ሚሊዮኖች ድምጽ” የኢዲቶሪያል ቦርድ አባል
  3. አቶ ስንታየሁ ቸኮል – የአዲስ አበባ የወጣቶች ክፍል ሃላፊ
  4. አቶ ነዋይ ገበየሁ – የአንድነት የሕዝብ ግንኙነት ም/ሃላፊ እንደሚገኙበት ለመረዳት ተችሏል።

በነገው ዕለት በአዲስ አበባ፤ በባሕር ዳር፤ በአርባ ምንጭና በሌሎችም ቦታዎች ሊካሄድ የታሰበው የተቃውሞ ሰልፍ አገዛዙና የምርጫ ቦርድ ተበዬው የአንድነትና የመኢአድ ድርጅቶችን በግንቦት ወር ሊደረግ ከታሰበው ሀገራዊ ምርጫ ውጪ እንዲሆኑ ለማድረግ እየተሸረበ ያለውን ሤራ በመቃወም ነው።

የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ የዓለምአቀፉ ማህበረሰቡ፣ በተለይም ለጋሽ ሀገሮች፣ ኢትዮጵያውያን ሕጋዊ መብቶቻቸው ለማስከበር በሰላማዊ መንገድ በሚያደርጉት ትግል ምክንያት አገዛዙ እየፈጸመባቸው ያለውንና ሊያባብሰው የሚችለውን አፈና፤ እስራትና የግፍ ተግባር  በመገንዘብ  ይህ ኢሰባአዊ ተግባር እንዳይፈጸም ተጽዕኖ በማድረግ ከአሁኑ እርምጃ እንዲወስዱ ለማሳሰብ ይወዳል።

ገዢው ፓርቲም በዜጎቹ ላይ ከሚፈጽመው የማሳደድ፤ የማሰርና ሌሎችም የግፍ ተግባሮች  በአስቸኳይ እንዲታቀብ እናሳስባለን።

ሸንጎ መሠረታዊ መብቶቹን ለማስከበር ከሚታገለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን ይቆማል። ለነዚህም መብቶች እውን መሆን ከሚታገሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ያለውን የትግል አጋርነት ያረጋግጣል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ‹‹ብሔራዊ ምክክሩ አገር ለመታደግ ቁልፍ መፍትሄ ነው›› -አቶ ክርስቲያን ታደለ

በያንዳንዱ ፖለቲካ ድርጅት ላይ የሚካሄድ ሴራና ረገጣ በሁሉም ላይ የሚካሄድ ሴራ መሆኑን በመገንዘብ  የፖለቲካ ድርጅቶች በጋራ በመቆም በህዝብና በተቃዋሚዎች ላይ የተቃጣውን ጥቃት እንዲቋቋሙ  ጥሪ እናደርጋለን።

መሠረታዊ መብቶችን ለማስከበር ትግሉ ይቀጥላል!

 

 

Share