አብርሃም ሰሎሞን ግንቦት ፫/፳፻፭ ዓ.ም.
መለያየት ይብቃ፤ ገለልተኛ ሆኖ መቀመጥም ይቅር። ቅዱስ ሲኖዶስ አንድ ነው፤ መንበሩም ያለው ኢትዮጵያ ነው። ሃያ ዓመታት ያስቆጠረው የመለያየት ግድግዳ ይፍረስ፤ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጋር አንድ እንሁን። ልጆቻችንን አንድነት እንጂ መለያየትን አናስተምራቸው፤ አባቶቻችን ያቆዩልንን ሥርዓትም አናጥፋው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከእራስዋ ልጆች ፓትርያርክ ለመሾም የወሰደባት ጊዜ ምን ያህል አድካሚ እንደነበር እናስብ፤ የተከፈለውንም የጊዜ፣ የገንዘብ፣ የጉልበት እና የሕይወት መሥዋዕት አንዝንጋ። ወ.ዘ.ተ. በማለት የደብረ ሰላም መድኃኔዓለም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናት አባቶችና መምህራነ ወንጌል አብይ ጾም ከመግባቱ በፊት በነበሩት ተከታታይ ሳምንታት በአውደ ምሕረት ላይ ስብከት መስበክ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ “ቤተ ክርስቲያናችንን ለወያኔ አሳልፈው ሊሰጡ ነው።” የሚል ዜና አልፎ አልፎ ከመሰማቱ ባሻገር በሚኒሶታ ውስጥ ባሉ የመገናኛ አውታሮች፣ በድረ-ገጽ፣ በኢሜል እና በጽሑፍም ሲሰራጭ ቆይቷል። በተለይም በሰሞነ ሕማማት ጊዜ የጌታን ነገረ ስቅለት እያሰቡ ሰዎች በጾም፣ በጸሎት እና በስግደት ሳምንቱን እያሳለፉ ባሉበት ወቅት የካህናተ ቤተ ክርስቲያኑን ፎቶግራፍ በድረ-ገጽ ላይ እና በኢሜል ላይ አውጥቶ “እሪ በል ሚኒሶታ ቤተ ክርስቲያንህ ለወያኔ ሊሰጥ ነው” በሚል ቅስቀሳ ጽሑፍ መበተኑም አይዘነጋም፤ ሁኔታውም እጅግ ያሳዝናል።
ከላይ በርእሱ ላይ እንደገለጽኩት ማንም ሰው እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባልነቱ ሊቀበለው የሚገባው ጉዳይ እና እውነታ ቢኖር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የደርግ አልነበረችም፤ የወያኔም አይደለችም፤ የቅንጅትም አትሆንም የሚለውን ኃይለ ቃል ነው። ምክንያቱም ቤተ ክርስቲያን ዘመን ተቆጥሮላቸው የሚያልፉ የፖለቲካ ድርጅቶች ወይም የመንግሥት አካሎች ሳትሆን ዘላለማዊት ናትና። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስንም ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ቤተ ክርስቲያን ሲያስተምረው፦ ጴጥሮስ አንተ አለት ነህ በአንተ ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፤ የገሀነም ደጆችም አይችሉአትም ብሎ ተናግሮታል። አንግዲህ ጌታችን ቤተ ክርስቲያኔን እያለ ከተናገረና ካስተማረን ስለ ምንድን ነው ቤተ ክርስቲያንን ለወያኔ ሊሰጡት ነው እየተባለ አባላቱን ግራ ማጋባት የተፈለገው? ቤተ ክርስቲያን ያዘነ የሚጽናናባት፣ የደከመ የሚበረታባት፣ የወደቀ የሚነሳባት፣ ንስሐ የሚገባባት፣ ቅዱስ ሥጋው እና ክቡር ደሙ የሚሰጥባት በአጠቃላይ ነፍስ የሚድንባት እንጂ የምድራዊ ፖለቲካ የሚነግርባት እና የእነእገሌ ድርጅት ናት የምትባል አይደለችም።
ቅዱስ ዳዊት አእምሮ ያለው ክቡር ሰው እንደሚጠፋ እንስሳ መሰለ ብሎ እንደተናገረው ተነጋግረን መግባባት ስንችል ውይይትን እንደ ጦር ፈርተነው “ከተነጋገርን እንለያያለን፤ እንበታተናለን” በሚል ፍራቻ ገለልተኛ እንደሆንን እንቀመጥ ማለቱ አግባብ አይደለም። እኛ እንደ ሰውነታችን “ከተነጋገርን እንግባባለን፤ እንስማማለን” ብለን በማሰብ ለውይይት መቀመጥ ይኖርብናል። ከቤተ ክርስቲያን ሕይወት የተለየ አመለካከት ከሌለው ሰው በቀር መንፈስ ቅዱስ ሆይ አንተ እርዳን ሕፃናት የሚያድጉባት፣ ልጆች የሚማሩባት፣ ሃይማኖት የሚሰበክባት እና ፍጹም ኦርቶዶክሳዊት አስተምህሮ የሚሰጥባትን ቤተ ክርስቲያንህን ልንሠራ ተዘጋጅተናልና በአንዲት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ልዩነትን አጥፍተን በአንድነት የምንጓዝበትን መንገድ አቅናልን ብለን በተሰበረ ልብ ለውይይት ከተቀመጥን ከሳሻችን ዲያብሎስ ያፍራል፤ እግዚአብሔር በግብራችን ይደሰታል። አላማችን ግን የፖለቲካ አመለካከትን ከቤተ ክርስቲያን አመለካከት ጋር አንድ አድርገን እናራምዳለን ከሆነ ሁለት የማይገናኙ ሐሳቦችን ለማገናኘት እየተሞከረ በመሆኑ ድካማችን ከንቱ ይሆናል፤ ጥረታችንም ይመክናል። ዓለም በምድራዊ ፖለቲካ ትመራለች፤ በዓለማችን ውስጥም ፖለቲካ የእራሱ የሆነ መንገድ እና ግንዛቤ ኖሮት በትምህርት ታግዞ ብዙኻን እየሠሩበት ይገኛል። በመሆኑም ፖለቲካ በቦታው መልካም እንደሆነ እናምናለን፤ ተቃውሞም አይኖረንም። በየትኛውም ቦታ ያሉ አካላት ግን ቤተ ክርስቲያንን የፖለቲካ ድል ማግኛ ሊያደርጉ አስበው ከሆነ ትክክለኛ መንገድ ላይ አለመሆናቸውን ሊረዱት ይገባል። ምክንያቱም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፖለቲካ እና ጫማ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መግባት የለበትም።
ኢትዮጵያ ለጠላት ያልተንበረከከች አገር እንደሆነች ታሪክ ሲያስተምረን ቆይቶ በርስ በርስ ጦርነት ግን ስትጠፋ አየናት። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም ባለ ታሪክ ሆና ከሐዋርያት ጀምሮ ትክክለኛውን መንገድ ስትመራ ቆይታ አሁን ዘመን ሰለጠነ ሲባል ልጆቿ ከሰላም ይልቅ ጦርን ከአንድነት ይልቅ መለያየትን መርጠን የአገር ውስጥ እና የውጭ ሲኖዶስ በማለት ተለያየን። ቤተ ክርስቲያንን መደበቂያ አድርገው ፖለቲካቸውን ለማስፋፋት የሚሞክሩትን ሁሉ ልብና ኩላሊትን የሚመረምር አምላክ መልሱን ይሰጣቸዋል። በቅንነት ቤተ ክርስቲያን ተገፍታለች ልናድናትና ልንደርስላት ይገባናል ብለው ለተነሱትም እግዚአብሔር ያግዛቸዋል። የሰው ዝምታ ፍርሐት መስሎ ሊታይ ይችላል፤ የእግዚአብሔር ዝምታ ግን ያስፈራል። ለቤተ ክርስቲያን አምላክዋ ነውና ቤተ ክርስቲያን ስትገፋ ዕለት ዕለትም ስትታወክ ያለ መልስ ዝም አይልም። እግዚአብሔር ሲወረውር አይታይም ሲጥል ግን ይታያል። የሰላም መድረክ እንዳይፈጠር ስምን ደብቆ በብዕር ስም መዋጋት አይጠቅምም። ሁላችን ከአንድ ገበታ ቆርሰን የበላን ወንድማማቾች እና እኅትማማቾች ሆነን ሳለ እንደ ጠላት ልንተያይ የምንዘጋጅበት ወቅት መሆንም ባልተገባ ነበር። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በግልጽ ካልተነጋገርን በየትኛው ስፍራ ተወያይተን ወደ አንድነት እንመጣለን? አንተ ማነህ? አንቺ ማነሽ? እናንተስ ማናችሁ? እኛስ ማነን? ሳንደባበቅ በገሐድ እንወያይና ቤተ ክርስቲንን የሰላም ቤት እናድርጋት።
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በገላትያ መልእክቱ ነገር ግን እርስ በርሳችሁ ብትነካከሱ ብትበላሉ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ። ያለው ቃል እንዲፈጸምብን አያስፈልገንም። ጌታችን በወንጌል እንዳስተማረን እንደ እባብ ልባሞች እንደ ርግብም የዋሆች ልንሆን ይገባል። ልባሞች ብቻ ሆነን የዋህነትን ሳናክልበት ከቀረን አስተዋይ እንደ እኛ ከየት ይመጣል በሚል ትዕቢት እንወድቃለን። የዋሆችም ብቻ ሆነን ሥርዓት ሲፈርስ፣ ሃይማኖት ሲጠፋ፣ ፍርድ ሲሳሳት እና ፍትህ ሲመዘበር ዝም ካልን ቤታችንን እናፈርሳለን። በመሆኑም እርስ በርሳችን ስንነካከስ እንዳንጠፋፋ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በሚመራት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከጸሎት ጋር የተሰበረው እንዲጠገን፣ የተበላሸው እንዲስተካከል፣ የተጣመመው እንዲቃና እና የተለያየው አንድ እንዲሆን በውጭ ሆነን ሳይሆን በውስጥ ገብተን ተሰልፈን ቤተ ክርስቲያንን ወደ ቀደመ ክብርዋ እንመልሳት። ይኽም ማለት በውስጥዋ አባት እና ልጆች ተከባብረውባት፣ ወንድማማቾችና እኅትማማቾች ተፈቃቅረውባት እንመልከታት ማለት ነው። ቀርበን ሳንወያይ በስማ በለው ብቻ አንተ እንዲህ ነህ፤ አንቺ እንዲያ ነሽ ብንባባል የሰይጣን ዲያብሎስ መሳለቂያ ከመሆን በቀር ሌላ አንዳች ነገር አናመጣም። እውነት ገንዘባችን ሃይማኖት ከሆነ ስለ ምንድን ነው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለውይይት ቀርበን ችግራችንን ተነጋግረን ቤተ ክርስቲያንን ለተተኪው ትውልድ በፍቅር ለማስረከብ የማንዘጋጀው? ነቢዩ ኢሳይያስ ከትውልዱ ማን አስተዋለ? ብሎ የተናገረው ቃል በገሐድ ሲፈጸም እያየነው ዛሬም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች ብቻ በእኛ የርስ በርስ ችኩቻ አዛውንቱ፣ ወጣቱ እና ታዳጊ ሕፃናቱ በመናፍቃን ሲወሰዱ እየሰማን ብቻ ሳይሆን እያየንም ባለንበት ሰዓት የእነእገሌ ሐሳብ እኛን አያሸንፈንም ተባብለን በእልህ መንገድ ስንጓዝ ቤቱ ባዶውን እንዳይቀር ያስፈራል። ሁለት ሰዎች ሳይነጋገሩ ተፈራርተው ብቻ ያኛውም መጣብኝ ብሎ ወደ ኋላው ሲያፈገፍግ ይኽኛውም ያጠቃኛል ብሎ አስቦ አካባቢውን ሲለቅ ምድሪቱ ብቻዋን ያለ ሰው ቀረች ይባላል። እኛም ተፈራርተን የእኛ ሰዎች እነእገሌ ብቻ ናቸው ስንባባል በመሐል ሃይማኖታችን፣ ፍቅራችንን እና አንድነታችን አጥተን እንኖራለን።
ስለዚህም የቤተ ክርስቲያናችን ሽማግሌዎች አሁን ወቅቱ ልዩነትን አጠንክራችሁ የምትሰብኩበት እና የምትነጋገሩበት ሳይሆን በቀሪው ዕድሜአችን ለወጣቱ ምን እናስተምረው የምትሉበት በመሆኑ በምትገናኙበት ሁሉ ስለ ሰላም መክራችሁ ቤተ ክርስቲያንን የሰላም መድረክ ለማድረግ ተዘጋጁ። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በኤፌሶን መልእክቱ በቁጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ፥ ለዲያብሎስም ፈንታ አትስጡት። ብሎ እንዳስተማረን በቁጣችሁ ላይ ፀሐይ አይጥለቅባችሁ። የቃሉ ምስጢር ጠዋት ጀምበር ሲወጣ የተጣላን ማታ ጀምበር ሳይጠልቅ በአንድ ቀን ውስጥ እንታረቅ ሳይሆን ሞት መጥቶ ሳይወስደን እና ለዘላለም ጀምበር ሳይጠልቅብን እንታረቅ ማለት ነው። ስንቶች አባቶቻችን፣ እናቶቻችን፣ ወንድሞቻችን እና እኅቶቻችን የጥሪያቸው ቀን ደርሶ ቤተ ክርስቲያን እንደተለያየች ጀምበር ጠለቀባቸው!!!! ይኽ ሊያሳዝነን ይገባልና አሁንም ልባሞች ሆነን በዚሁ ትውልድ ወደ ሰላም መንገድ እናቅና። የዕድሜ ባለፀጋ አባቶቻችን በዚህ ነገር እርዱን። እንባችሁ እንደ ራሔል እንባ ፀባኦት የሚደርስ እናቶቻችን ከጸሎት እና ከልመናችሁ ባሻገር የቤተ ክርስቲያን ውስጥ መለያየት እንዲወገድ በየቤታችሁና በያላችሁበት ተነጋገሩ። የእምነት ጽናታችሁ የሚለካበት ሚዛን የሚሰፈርበት መስፈሪያ የለውምና። ወጣቶች ሁላችሁ እንደየዕድሜ ደረጃችሁ የመለያየት ነገር በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ምን ያህል እንዳቆሰላችሁ ታውቁታላችሁና ምንም እንኳን መንገዱ አልጋ በአልጋ ሆኖ ያረማምደናል ብለን ባናስብም ለዘመናት ተለያይተን ያመጣነው ነገር ስለሌለ ቤተ ክርስቲያንን ሌላ አንዳች ነገር ሳንጨምርባት እንደ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ተመልክተናት በቀኖናም፣ በሥርዓትም፣ በዶግማም፣ በዶክትሪንም አንድ ሆነን መራመድ የምንችልበትን ጉዳይ አጥብቃችሁ እሹ። ሕፃናቱ በእጃችን ስለወደቁ የሕፃናቱን ነገር እኛ እናስብላቸው፤ ያልተለያየች ቤተ ክርስቲያን ተመልክተው በጳጳስ ተባርከው ይኑሩ። ይኼንን ባናደርግላቸው ለውደቅታቸው ምክንያት እኛ መሆናችንን አንዘንጋው። አገራችን ኢትዮጵያ ፈተና ገጥሟታል፤ ልጆች ሞተውባታል፣ የንጹሐን ደም ፈስሶባታል፤ በእስር ቤት ውስጥ ያለ ፍርድ የተዘጉ ኢትዮጵያውያን ሞልተውባታል። ለዚህና ይኼን ለመሳሰለው ሁሉ የቤተ ክርስቲያን ልጆች እናዝናለን። ሆኖም ከችግር ለመውጣት ከቤተ ክርስቲያን አንድነት ተለይቶ ለብቻ መሆን መፍትሔ አያመጣም። መለያየት የሥጋ ሥራ ነውና እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት እንጓዝ። ይቆየን!!