አንድነት “የፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ የኢህአዴግ የዕድሜ ማራዘሚያና መጠቀሚያ ከመሆን በዘለለ ፋይዳ አለው ብለን አናምንም” አለ

የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ “የፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ የኢህአዴግ የዕድሜ ማራዘሚያና መጠቀሚያ ከመሆን በዘለለ ፋይዳ አለው ብለን አናምንም” ሲል ትናንት በነአንዷአለም አራጌ ላይ የወሰነውን የፍርድ ውሳኔ አጥብቆ አወገዘ። ፓርቲው ለዘ-ሐበሻ በላከው መግለጫው “አሁንም የፖለቲካና የህሊና እስረኞች በአፋጣኝ እንዲፈቱ እንጠይቃለን!!!” ብሏል። ሙሉ መግለጫው እንደሚከተለው ቀርቧል።

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ(አንድነት) የተሰጠ መግለጫ

ፓርቲያችን አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) በሰላማዊና ህጋዊ የትግል መንገድ ለውጥ ማምጣት ይቻላላል፤ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እንፈጥራለን፤ ስልጣንም በግለሰቦች ወይም በቡድኖች ይሁንታ የሚገኝ ሳይሆን በህዝቡ በልካም ፈቃድ ይሆናል የሚል ጠንካራ እምነት በመያዝ ከአምባገነኑ ስርዓት ጋር እየታገለ የሚገኝ ነው፡፡

ይሄ ጠንካራ የትግል መነሳሳታችን እና ያለን የህዝብ ድጋፍ ጠንካራ ተቃዋሚ በዓይኑ ማየት የማይፈልገው ገዥ ፓርቲ ጥርስ ውስጥ የከተተን በምስረታችን ማግስት ጀምሮ ነው፡፡ በርካታ አባሎቻችንንና አመራሮቻችንን ተልካሻ ምክንያት እየተለጠፈባቸው ታስረዋል፣ ተሳድደዋል፣ ተደብደበዋል፡፡

በተለይ ከቅርብ አመታት ወዲህ ደግሞ ጠንካራ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎችና ተቃውሞዎች ሁሉ የሚሰጣቸው ስም ሽብርተኝነት የሚል ነው፡፡ የስርዓቱ የስልጣን ማቆያ፣ የሀቀኛ ተቀናቃኞችና ስርዓቱን የሚተቹ ጋዜጠኞች ማሸማቀቂያ ብሎም ማስወገጃ መሳሪያ ሽብርተኝነት ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡

ፓርቲያችን አንድነትም ጠኋትና ማታ እየተጠቀሰ ዜጎች እንዲሸማቀቁ የሚደረግበትና የፖለቲካ አመራሮች የሚታሰሩበት የፀረ-ሽብርተኝነት ህግ ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት ተቃውሞውን አሰምቷል፡፡ ሰኔ 18 ቀን 2001 ዓ.ም የፀረ ሽብር ህጉ ገና ረቂቅ አዋጅ እንደነበረ ለማፈን እየተሰናዳ መሆኑን በመጥቀስ ‹‹የፀረ-ሽብርተኝነት ረቂቅ አዋጅ በዜጎች ላይ ሽብር ፈጣሪ ነው›› በሚል ርዕስ ባወጣነው መግለጫችን ረቂቅ አዋጁ እንዳይፀድቅ የሚሰማ ባይኖርም አበክረን ጩኸታችንን አሰምተን ነበር፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ልዩ መረጃዎች! "እነ ዶ/ር ይልቃል አኩራፊነትና ግለኝነት አለባችሁ" - ዐቢይ | ስለ ፋኖ የተያዘው ዕቅድ ተጋለጠ!

ወዲያው ህግ ሆኖ እንደወጣም የፀረ ሽብርተኝነት ትግልን ሽፋን በማደረግ የገዥው ፓርቲ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የማፈን ድብቅ ፍላጎት ተግባራዊ መሆን ጀመረ፡፡ የመጀመሪያው ሰለባ አንድነት ፓርቲ ነው ብንል ማጋነን አይደለም፡፡ አንዱአለም አራጌንና ናትናኤል መኮነንን የመሰሉ ከፍተኛ የፓርቲ አመራሮችንና ሌሎችን የፓርቲያችን አባሎች በእስር አጥተናል፡፡ እነዚህ በማናለብኝነት የሚፈፀሙ የገዥው ፓርቲ ሸፍጦች ትግላችንን የበለጠ የሚያጠናክሩና አፈናውን ለመስበር ጉልበት የሚሆኑን ናቸው እንጂ አንገታችንን አያስደፉንም፡፡ የፍትህ ተቋማት ላይ እምነት መጥፋቱ፣ ከላይ እስከታች ያለው የአፈና ቋንቋ ተመሳሳይ መሆኑና የገዥው ፓርቲ እጅ መርዘም ትግሉን ማፋፋምና አጠናክሮ መቀጠል ዋና መፍትሄ እንደሆነ የሚጠቁመን ነው፡፡

ሚያዚያ 24 ቀን 2005 ዓ.ም ይግባኝ ሰሚ ችሎት በነ አንዷለም አራጌ ፍርድ ላይ በአንድ መዝገብ ከተከሰሱት መካከል የአንዱን ጥቂት ዓመታት ከመቀነስ ባለፈ የስረኛውን ፍ/ቤት ውሳኔ ትክክል ነው ብሏል፡፡ ይሄ ፍርድ የሚያስታውሰን የኪሊማንጃሮ ኢንተርናሽናል ኮርፖሬሽን ሊሚትድ በዓለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ ከፀረ ሙስና ኮሚሽን ጋር በመተባበር ይፋ ያደረገውን ጥናት ነው፡፡ በ27 የመንግስት ተቋማት ላይ በተደረገ ጥናት ‹‹በከፍተኛ ደረጃ የህዝብ አመኔታ ያጡ ተቋማት›› በሚል ርዕስ ስር በመጀመሪያ ደረጃ የተቀመጡት ፍ/ቤቶች ናቸው፡፡ ይሄ የሚያሳየው ፍ/ቤቶች የገዥው ፓርቲ ጉዳይ አስፈፃሚዎች እንጅ ገለልተኛ ተቋማት አለመሆናቸውን ነው፡፡

ከፍተኛው ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ወጣቱን ፖለቲከኛና ከፍተኛ አመራር አንዱአለም አራጌና ናትናኤል መኮንን ሽብርተኞች እንደሆኑና በሰላማዊ ትግል ሽፋን ሽብርተኝነትን እንሚያራምዱ ተደርጎ የቀረበው ሀተታ የፓርቲያችንን ጠንካራ መዋቅር ያላገናዘበ፣ የፓርቲያችንን መልካም ስም የሚያጎድፍ ነው፡፡ እነ አንዷለምም ሰላማዊ ታጋዮች እንጅ ሽብርተኞች አይደሉም፡፡ ሽብርተኝነት በኮሃራም ናይጀሪያ፣ በፓኪስታንና አፍጋኒስታን በየዕለቱ የምንሰማው እንጅ የኢትዮጵያ ችግር አይደለም፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ፋኖ በድጋሚ ድል ሰራ | 4 ኪሎ እና አመራሮቹ ተናወጡ | ብልጽግና በአማራ ክልል ፈርሷል' | የአማራ ክልል ባለስልጣናት ሹመት |

በአጠቃላይም የፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ የኢህአዴግ የዕድሜ ማራዘሚያና መጠቀሚያ ከመሆን በዘለለ ፋይዳ አለው ብለን አናምንም፡፡ የአመራሮቻችንንና አባሎቻችንን መታሰር አጥብቀን እንቃወማለን፡፡ አሁንም ደግመን ደጋግመን የምንለው በሽብርተኝነት ስም ዜጎችን ማሰር ይቁም፤ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሽብርተኝነት አይደለም፤ የፖለቲካና የህሊና እስረኞ በአስቸኳይ ይፈቱ፡፡

ትግላችን እስከለውጥ ድረስ ይቀጥላል!!!

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ(አንድነት)

ሚያዝያ 25 ቀን 2005 ዓ.ም

አዲስ አበባ

3 Comments

  1. Andnet should learn by now that sending protest letters to fascist Tigre liberation front officials, time after time, won’t achieve anything. It is just a pointless gesture to appear to be doing something. Stop playing games and do something practical. You are supposed to be a political party with strategies and plans

  2. Do these Andinet guys seriously think that the woyane junta will gave their letter a damn. It is a joke. Wise up and get your brain working.

  3. ህገመንግስቱ ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ ይፈቅዳል;; ታዲያ ይህን ማድረግ ትክክለኛ መንገድ ሆኖ ሳለ የወረቀት ነብር መሆን ምን ይጠቅማል? ክዚህ በፊት ብዙ መግለጫ አውጥታችሁ ነበር;; አንዳች መልስ ግን አልተገኘም;; ታዲያ እናንተ እንደምትሉት ህዝቡን በምን ሁኔታ ነው የሰልጣኑ ባለቤት የምታረጉት? በዐሁኑ ጊዜ ወያኔ-አኢሃአዲግ በሰባዊመብት ጥስት ምክንያት ባለም ላይ ውግዘት እየደረሰበት ይገኛል;;እናንተ አጋጣሚውን ተጠቀሙበት;; አለበለዚያ ሁሌ መግለጫ ይደብራል;;

Comments are closed.

Share