በፌደራል መ/ቤቶች ዝርክርክነቱ ተጠናክሮ ቀጥሏል (ሪፖርታዥ)

May 1, 2013
በፌዴራል መ/ቤቶች
 
–   ወደ 1.4 ቢሊየን ብር አልተወራረደም
–   በ30 መ/ቤቶች 353.6 ሚሊየን ብር ደንብና መመሪያን ያልተከተለ ግዥ ተፈጽሟል
–   በ9 መ/ቤቶች 3.5 ቢሊየን ብር ባልተሟላ ሰነድ ወጪ ሆኗል፣3.2 ቢሊየን ብሩ የመከላከያ ወጪ ነው
–   በ27 መ/ቤቶች ከተፈቀደላቸው በጀት በላይ ብር 212.5 ሚሊየን ተጠቅመዋል
ጋዜጠኛ ፍሬው አበበ
የፌዴራልና ዋና ኦዲተር መ/ቤት በ2004 በጀት ዓመት በፌዴራል መንግስት መ/ቤቶች የኦዲት ሥራ አከናውኗል። በትላንትናው ዕለት ዋና ኦዲተሩ አቶ ገመቹ ዱቢሶ 58 ገጽ የያዘውንና በ116 የፌዴራል መንግስት ባለበጀት መ/ቤቶችና በ283 የወረዳና ከተማ አስተዳደር የፋይናንስ ጽ/ቤቶች ላይ መ/ቤታቸው ያካሄደውን የኦዲት ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አቅርበዋል። በዚህ ሪፖርት ውስጥ የተጠቀሱ ዋናዋና ግኝቶች እንደሚከተለው በዝርዝር ቀርበዋል።
በፌዴራል መንግሥት የልዩ ልዩ መ/ቤቶች
የፋይናንስና ሕጋዊነት ኦዲት ወቅት የታዩ ዋና ዋና ግኝቶች
መ/ቤታችን ምክር ቤቱ ያፀደቀው በጀት የፋይናንስ አስተዳደር ሕጉ፣ ደንብና መመሪያ በሚፈቅደው መሠረት በትክክል ሥራ ላይ መዋሉን ለማረጋገጥ በ2004 በጀት ዓመት ሂሳብ ላይ ባከናወነው ኦዲት በርካታ የሂሳብ አያያዝ ግድፈቶች እና የውስጥ ቁጥጥር ድክመቶች፣ እንዲሁም አፈፃፀማቸው ከደንብና መመሪያ ውጪ የሆኑ ሁኔታዎች የተገኙ ሲሆን፤ የም/ቤቱን ትኩረት ሊያገኙ ይገባል ተብሎ የታመነባቸው አንኳር ግኝቶች ብቻ ተለይተው እንደሚከተለው ቀርበዋል።
የጥሬ ገንዘብ ጉድለት
የጥሬ ገንዘብ ሂሳብ አያያዝና አጠባበቅ ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ኦዲት ሲደረግ፣ በ3 መ/ቤቶች ብር 247 ሺ 210 ብር ከ19 ሳንቲም የጥሬ ገንዘብ ጉድለት ተገኝቷል። በመሆኑም በጉድለት የታየው የጥሬ ገንዘብ ሂሳብ እንዲተካ ተገቢው እርምጃ እንዲወሰድ ለየመ/ቤቶቹ በላክነው የስራ አመራር ሪፖርት አሳስበናል።
በተጨማሪም በበጀት ዓመቱ መጨረሻ በሂሳብ መግለጫ ሪፖርት የተደረገውና በቆጠራ የተገኘው ጥሬ ገንዘብ መካከል ልዩነት በ2 መ/ቤቶች ቆጠራው በብር 133ሺ466 ብር ከ99 ሳንቲም በማነስ እና በ9 መ/ቤቶች በብር 3 ሚሊየን 433ሺ 156 ብር ከ03 ሳንቲም በመብለጥ የታየ ሲሆን፤ በአጠቃላይ በ24 መ/ቤቶችም የተለያዩ የጥሬ ገንዘብና የባንክ ሂሳብ አያያዝ ድክመቶች እንደሚታዩ በኦዲታችን ወቅት አረጋግጠናል።
የጥሬ ገንዘብና የባንክ ሂሳቦች ላይ ተገቢ ቁጥጥር አለማድረግ ለገንዘብ ጉድለትና ምዝበራ የሚያጋልጥ በመሆኑ፤ የጥሬ ገንዘብ ሂሳብ በየወቅቱ ተቆጥሮ ከመዝገብ ጋር እንዲመሳከር፣ በሂሳብ መግለጫ ሪፖርት ላይ የተመለከተው የጥሬ ገንዘብ ሂሳብ በቆጠረ ከተገኘው ጋር ሊመዛዘንና ትክክለኛነቱ ሊረጋገጥ እንደሚገባ፤ በማነስና በመብለጥ የታየው ልዩነትም ተጣርቶ እንዲተካ ወይም ተገቢው ማስተካከያ እንዲደረግ እና በ24ቱ መ/ቤቶችም የታዩ የተለያዩ የጥሬ ገንዘብና ባንክ ሂሳብ አያያዝ ድክመቶች እንዲስተካከሉ አሳስበናል።
የውዝፍ ተሰባሳቢ ሂሳብ
በሚኒስትሮች ምክር ቤት የፋይናንስ አስተዳደር ደንብ ቁጥር 190/2002 አንቀጽ 32 እስከ 35 በተደነገገው መሠረት ተሰብሳቢ ሂሳብ በወቅቱ መወራረዱ ሲጣራ በ57 መ/ቤቶች ብር 1 ቢሊየን 369 ሚሊየን 377ሺ 900ብር ከ98ሳንቲም በደንቡ መሠረት በወቅቱ ሳይወራረድ ተገኝቷል። ከዚህ ውዝፍ ተሰብሳቢ ሂሳብ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የያዙት የትምህርት ሚኒስቴር ብር 401 ሚሊየን 757ሺ 697 ብር ከ18ሳንቲም፣ የግብርና ሚኒስቴር 64 ሚሊየን 602 ሺ 005ብር ከ48 ሳንቲም፣ የግብርና ቴክኒክ ሙያና ትምህርት ስልጠና ፕሮጀክት ማስተባበሪያ 155 ሚሊየን 597 ሺ 701 ብር ከ70ሳንቲም፤ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር 173 ሚሊየን 756 ሺ 807 ብር ከ75ሳንቲም፤ የመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ብር 159 ሚሊየን 455 ሺ 023 ብር ከ31ሳንቲም፤ የሀገር መከላከያ ሚ/ር ብር 86 ሚሊየን 367 ሺ 964 ብር ከ14ሳንቲም፤ በሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና የፈተናዎች ኤጀንሲ ብር 83 ሚሊየን 081 ሺ 758 ብር ከ27ሳንቲም፤ መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ብር 69ሚሊየን 022 ሺ 422 ብር ከ95ሳንቲም፤ የፌዴራል ፖሊስ 29 ሚሊየን 778 ሺ 302 ብር ከ26 ሳንቲም እና አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ብር 21 ሚሊየን 399 ሺ 805 ብር ከ70 ሳንቲም ይገኝበታል።
በተጨማሪም በተሰብሳቢ ሂሳብ አያያዝ የሚታዩ ዋና ዋና የአሰራር ችግሮች፤ ዕዳው ከማን እንደሚፈለግ ዝርዝር ማስረጃ ባለመኖሩ ከሰራተኛው የሚፈለገውን ቀሪ እዳ ትክክለኛነት ማረጋገጥ አለመቻሉ፤ በአንዳንድ መ/ቤቶች ገንዘቡ ወጪ ተደርጎ ለመሰጠቱ ማስረጃው ባለመቅረቡ የተሰብሳቢ ሂሳቡን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ አለመቻሉ፤ የተሰብሳቢ ሂሳቡ ያልተለመደ ሚዛን /Abnormal Balance/ ማሳየቱ፤ በአንዳንድ መ/ቤቶች የተሰብሳቢ ሂሳብ ሰነዱ ለኦዲት ያልቀረበ መሆኑና ከመቼ ጀምሮ የሚፈልግ ሂሳብ እንደሆነ የሚገልጽ ማስረጃ እና ተቀጽላ ሌጀር ያልተቋቋመ በመሆኑ የሂሳቡን ትክክለኛነት ማረጋገጥ አለመቻሉ ናቸው።
ውዝፍ ተሰብሳቢ ሂሳቡ በየመ/ቤቶቹ የሥራ ማስኬጃ ላይ ተፅዕኖ በማሳደር የሥራ እንቅስቃሴ የሚያዳክምና የበጀት አጠቃቀም ላይ ተጽዕኖ ከመፍጠሩም በላይ ለምዝበራና ለብክነት በር የሚከፍት በመሆኑ መ/ቤቶቹ የፋይናንስ ደንብና መመሪያዎችን ተከትለው እንዲያወራርዱ አሳስበናል።
የገቢ ሂሳብ
የመንግሥት ገቢ በአግባቡ መሰብሰቡን ለማጣራት ኦዲት ሲደረግ ቀጥሎ የተመለከቱት ሁኔታዎች ተገኝተዋል።
በገቢ ግብር፣ ቀረጥና ታክስ አዋጅ፣ ደንብና መመሪያ መሠረት
ሳይሰበሰብ የተገኘ የገቢ ሂሳብ
የገቢ ሰብሳቢ መ/ቤቶችና አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች በገቢ ግብር፣ ቀረጥና ታክስ እንዲሁም በሌሎች ገቢ መሰብሰብን በሚፈቅዱ አዋጆች፤ ደንቦችና መመሪያዎች መሠረት የመንግሥትን ገቢ የሰበሰቡ መሆኑን ለማረጋገጥ ኦዲት ሲደረግ፣ በናሙና በታዩት በ4 መ/ቤቶችና በ6 የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ቅ/ጽ/ቤቶች በድምሩ ብር 29 ሚሊየን 205 ሺ 484 ብር ከ95ሳንቲም  በገቢ ግብር፣ ቀረጥና ታክስ እንዲሁም በሌሎች ገቢ መሰብሰብ በሚፈቅዱ አዋጆች መሠረት ያለተሰበሰበ የገቢ ሂሳብ መኖሩ ታውቋል።
በአዋጁ መሠረት ገቢ ካልሰበሰቡት መ/ቤቶች መካከል ምስራቅ አዲስ አበባ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ቅ/ጽ/ቤት ብር 25 ሚሊየን 090 ሺ 951 ብር ከ15 ሳንቲም እና ውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ብር 1 ሚሊየን 066 ሺ 483 ብር ከ48 ሳንቲም ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
በመሆኑም መ/ቤቶች ለወደፊቱ የመንግሥት ገቢ ሕግና ደንብ በሚፈቅደው መሠረት መሰብሰብ እንዳለባቸው፣ በተለያዩ ምክንያቶች ያልተሰበሰበውም ገቢ እንዲሰበሰብ በላክነው ሪፖርት አሳስበናል።
ያልተሰበሰበ ውዝፍ የገቢ ሂሣብ
ገቢ ሰብሳቢ መ/ቤቶችና አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች በወጣው ሕግና ደንብ መሠረት የመንግሥት ገቢ በወቅቱና በአግባቡ መሰብሰባቸውን ለማረጋገጥ ኦዲት ሲደረግ፤ በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና መ/ቤትና በስሩ ባሉ ስድስት ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ከውዝፍ ግብር፤ ወለድ እና ቅጣት መሰብሰብ የሚገባው ብር 853 ሚሊየን 920 ሺ 158 ብር ከ83 ሳንቲም እና በሌሎች 6 መ/ቤቶች ብር 12 ሚሊየን 250 ሺ 953 ብር ከ19 ሳንቲም በድምሩ ብር 866 ሚሊየን 171 ሺ112 ብር ከ02 ሳንቲም ያልተሰበሰበ ውዝፍ ገቢ መኖሩ ተረጋግጧል።
በመሆኑም የሚሰበሰበው ገቢ መንግስት ለሚያከናውናቸው የልማትና ማኅበራዊ አገልግሎቶች መስፋፋት እንዲሁም ለሀገሪቱ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መሳካት ወሳኝ በመሆኑ፤ ለገቢ አሰባሰቡ ትኩረት ተሰጥቶት የመንግሥት ሕግና ደንብ ተከብሮ እንዲሠራ፣ ያልተሰበሰበውም ውዝፍ ገቢ እንዲሰበሰብ በሪፖርታችን አሳስበናል።
በገቢ ሂሳብ ሪፖርት ውስጥ ያልተካተተ ገቢ
በበጀት ዓመቱ በተለያዩ የመንግሥት መ/ቤቶች የተሰበሰበው ገቢ በትክክል ተመዝግቦና በሂሳብ ሪፖርታቸው ተካቶ ለገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር መቅረቡን ለማረጋገጥ ኦዲት ሲደረግ፤ በ5 መ/ቤቶች የሰበሰቡት የውስጥ ገቢ ብር 24 ሚሊየን 606 ሺ 079 ብር ከ30 ሳንቲም ባቀረቡት ዓመታዊ የገቢ ሂሳብ ሪፖርት ውስጥ ሳይካተት ተገኝቷል።
በሌላ በኩል 15 መ/ቤቶች ከልዩ ልዩ የገቢ ማስገኛ ምንጮች ገቢ የሚሰበስቡ ቢሆንም፤ የገቢ ሪፖርት የማያዘጋጁ በመሆኑ ሂሳቡን ኦዲት ማድረግ አልተቻለም። በተጨማሪም 5 መ/ቤቶች የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚ/ር ሳያስፈቅዱ የገቢ ደረሰኝ አሳትመው ገቢ እንደሚሰበስቡ ታውቋል።
ይህ አሰራር በመ/ቤቶች የሚዘጋጁት የሂሳብ መግለጫዎች ትክክለኛውን የገቢ ሂሳብ እንቅስቃሴ የማያሳይና የመንግስት አጠቃላይ ገቢና ወጪም ትክክለኛውን ገጽታ እንዳያሳይ ስለሚያደርግ መ/ቤቶች የሚሰበስቡትን ማንኛውም የመንግስት ገቢ ሕጋዊ በሆነ መንገድ በታተሙ ደረሰኞች ብቻ በመጠቀም እንዲሰበስቡና በሂሳብ መግለጫዎቻቸውም በመካተት ለገ/ኢ/ል/ሚ/ር ሪፖርት ሊያደርጉ እንደሚገባ አሳስበናል።
የወጪ ሂሳብ
መ/ቤቶች የተፈቀደላቸውን በጀት በፋይናንስ አስተዳደር አዋጅ፣ ደንብና መመሪያዎች መሠረት በአግባቡ መጠቀማቸውን፣ ተገቢው ማስረጃ መቅረቡንና ሂሳቡም በትክክል መመዝገቡን ለማጣራት ኦዲት ሲደረግ ቀጥሎ የተመለከቱት ሁኔታዎች ተገኝተዋል።
የተሟላ የወጪ ማስረጃ ሳይቀርብ በውጪ ተመዝግቦ የተገኘ ሂሳብ
በወጪ ለተመዘገቡ ሂሳቦች የተሟላ ማስረጃ መቅረቡን ለማረጋገጥ ኦዲት ሲደረግ፣ በ13 መ/ቤቶች የተሟላ ማስረጃ ሳይቀርብ ብር 132 ሚሊየን 364 ሺ 911 ብር ከ31 ሳንቲም በወጪ ተመዝግቦ ተገኝቷል።
ተሟልተው ካልቀረቡት ማስረጃዎች መካከል፣ የተከናወነውን ሥራ በሚያሳይ ዝርዝር ማስረጃ ሳይደገፍ በቀረበው ጥያቄ ብቻ የተፈፀመ ክፍያ፤ በባንክ በኩል ገንዘቡ ተልኮ ሥራ ላይ መዋሉን የሚገልጽ የወጪ ማስረጃ ሳይቀርብ በወጪ የተመዘገቡ ሂሳቦች ጎላ ያሉት ናቸው።
ማንኛውም ሂሳብ በወጪ ከመመዝገቡ በፊት በፋይናንስ አስተዳደር አዋጁ፣ ደንቡና መመሪያ መሠረት ማስረጃዎች መሟላታቸው እንዲረጋገጥ፣ ያልተሟሉት ማስረጃዎች እንዲሟሉና ለወደፊቱም ተገቢው ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት አሳስበናል።
የወጪ ማስረጃ ያልቀረበለት ሂሳብ
በወጪ የተመዘገቡ ክፍያዎች ሕጋዊ ማስረጃ የቀረበላቸው መሆኑን ለማረጋገጥ ኦዲት ሲደረግ፣ በ22 መ/ቤቶች ብር 13 ሚሊየን 803 ሺ 411 ብር ከ08 ሳንቲም ማስረጃ ሳይኖረው በወጪ ተመዝግቦ ተገኝቷል።
በመሆኑም የወጪ ማስረጃ ያልቀረበለት ሂሳብ በቂ ማስረጃ እንዲቀርብለት፣ አለበለዚያ ገንዘቡ ለመንግስት ካዝና ተመላሽ እንዱደረግ፤ ለወደፊቱም ማንኛውም ወጪ ከመመዝገቡ በፊት ተገቢው ማስረጃ መቅረቡን በማረጋገጥ እንዲመዘገብ አሳስበናል።
የግዢ አዋጅ፤ ደንብና መመሪያ ሳይከተሉ የተፈፀሙ ግዢዎች
የዕቃና አገልግሎት ግዢ በመንግሥት ደንብና መመሪያ መሠረት የተፈፀመ መሆኑን ለማጣራት ኦዲት ሲደረግ፣ በ30 መ/ቤቶች ብር 353 ሚሊየን 568ሺ 759 ብር ከ15 ሳንቲም የመንግሥትን የግዢ አዋጅ፤ ደንብና መመሪያ ያልተከተለ ግዢ ተፈጽሞ ተገኝቷል።
ከደንብና መመሪያዎች ውጭ ግዥ ከፈፀሙ መ/ቤቶች መካከል ጅማ ዩኒቨርሲቲ ብር 240 ሚሊየን 221 ሺ 573 ብር ከ63 ሳንቲም ፤ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ብር 36 ሚሊየን 198 ሺ 641 ብር ከ27 ሳንቲም፤ መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ብር 20 ሚሊየን 341 ሺ 230 ብር ከ59 ሳንቲም ፤ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ብር 14 ሚሊየን 082 ሺ 063 ብር ከ07 ሳንቲም ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ብር 8 ሚሊየን 755 ሺ 250 ብር ከ38 ሳንቲም፣ ወሎ ዩኒቨርሲቲ ብር 6 ሚሊየን 745 ሺ 462 ብር ከ35 ሳንቲም ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
ካልተከተሏቸው የግዥ ደንብና መመሪያዎች ውስጥ የጨረታ ማስታወቂያ በማውጣት ሊፈፀሙ የሚገባቸው ግዥዎች ያለጨረታ ማስታወቂያ በመግዛት፣ በዋጋ ማወዳደሪያ /ፕሮፎርማ/ መፈፀም ያለበትን ግዥ ውድድር ሳይደረግ መፈፀም እና በውስን ጨረታው የግዥ ዘዴ በቂ አቅራቢዎች ሳይጋብዙ ግዥን ማከናወን የሚሉት ይገኙበታል።
የግዢ መመሪያን ሳይከተሉ ግዢ መፈፀም ለምዝበራና ለጥራት መጓደል የሚያጋልጥ በመሆኑ የመንግሥት ግዢ ደንብና መመሪያን አክብረው በማይሰሩ መ/ቤቶች ላይ የተጠናከረ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል።
ደንብና መመሪያን ሳይከተሉ ያለአግባብ የተፈፀሙ ክፍያዎች
ኦዲት በተደረጉት መ/ቤቶች ደንብና መመሪያ ተጠብቆ ክፍያ መፈፀሙ ሲጣራ በ21 መ/ቤቶች ብር 137 ሚሊየን 363 ሺ 575 ብር ከ83 ሳንቲም ከደንብና መመሪያ ውጭ ተከፍሎ ተገኝቷል።
በግንባታ ቦታ ላይ ላሉ ዕቃዎች materials on site)፤ ከሚመለከተው አካል ሳይፈቀድ የትርፍ ሰዓት ክፍያ በመፈፀም፤ ሰራተኞች መስክ ሳይወጡ የውሎ አበል በመክፈልና የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር ሳይፈቅድ የኃላፊነት አበል ለዩኒቨርሲቲ የስራ አመራሮች ክፍያ በመሳሰሉት ምክንያቶች በጅማ ዩኒቨርሲቲ ብር 77 ሚሊየን 611 ሺ 944 ብር ከ97 ሳንቲም፣ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ብር 34 ሚሊየን 771 ሺ 018 ብር ከ34 ሳንቲም እና ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ብር 10 ሚሊየን 825 ሺ 188 ብር ከ84 ሳንቲም ወጪ ያደረጉ መሆናቸው በኦዲቱ ተረጋግጧል።
በተጨማሪም የቀድሞው የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን በቁጥር መ30/ጠ/ጠ13137/820 በቀን 5/13/2001 ዓ.ም በተፃፈ ሰርኩላር የትርፍ ሰዓት ክፍያ ተግባራዊ እንዳይሆን መመሪያ ያስተላለፈ ቢሆንም፤ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ሳያስፈቅድ በሁሉም ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች በ2004 በጀት ዓመት ለትርፍ ሰዓት ክፍያ ፈጽሞ ተገኝቷል።
በመሆኑም ከደንብና መመሪያ ውጪ ያለአግባብ የተከፈለው ሂሳብ ተመላሽ እንዲሆንና ለወደፊቱም ደንብና መመሪያዎች ተከብረው መሰራት እንዳለበት ኦዲት ለተደረጉት መ/ቤቶች አሳስበናል።
በተሰብሳቢ ሂሳብ መመዝገብ ሲገባው በወጪ የተመዘገበ
የቅድሚያ ክፍያ ሂሳብ የተገኘባቸው መ/ቤቶች
በበጀት ዓመቱ በመንግሥት መ/ቤቶች በወጪ የተመዘገበው ሂሳብ በደንብና በመመሪያ መሠረት መሆኑን ለማረጋገጥ ኦዲት ሲደረግ፣ በ12 መ/ቤቶች ለልዩ ልዩ ኮንትራታዊ አገልግሎቶች የተከፈለ ቅድሚያ ክፍያ ብር 546 ሚሊየን 599 ሺ 723 ብር ከ27 ሳንቲም በተሰብሳቢ ሂሳብ መመዝገብ ሲገባው በወጪ ተመዝግቦ ተገኝቷል።
ቅድሚያ ክፍያን በወጪ ከመዘገቡት መ/ቤቶች መካከል ውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ብር 302 ሚሊየን 924 ሺ 907 ብር ከ46 ሳንቲም ፣ ጅማ ዩኒቨርሲቲ ብር 123 ሚሊየን 905 ሺ 491 ብር ከ52 ሳንቲም፣ ትምህርት ሚኒስቴር ብር 47 ሚሊየን 988 ሺ 495 ብር ከ21 ሳንቲም እና ማዕድን ሚኒስቴር ብር 28 ሚሊየን 630 ሺ 317 ብር ከ74 ሳንቲም ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
መሆኑም የመንግሥት ሂሳብ አያያዝ በሚያዘው መሠረት አስፈላጊውን ማስተካከያ በማድረግ፤ ቅድሚያ ክፍያው ሥራው ተጠናቆ በቂ ማስረጃ እስከሚቀርብለት ድረስ በተሰብሳቢ ሂሳብ እንዲመዘገብ በሪፖርታችን አሳስበናል።
በብልጫ የተከፈለ ወጪ
በወጪ የተመዘገቡት ሂሳቦች በፋይናንስ አስተዳደር አዋጅ እና ደንብ መሰረት በአግባቡ የተፈፀሙ፤ እንዲሁም መ/ቤቶቹ ላገኙት አገልግሎት የተፈፀመ መሆኑን ለማጣራት ኦዲት ሲደረግ፤ በ7 መ/ቤቶች ለተለያዩ ግዢዎች ብር 542 ሺ 220 ብር ከ60 ሳንቲም እና ለውሎ አበልና ሌሎች ክፍያዎች በ4 መ/ቤቶች ብር 851 ሺ 589 ብር ከ66 ሳንቲም  በድምሩ ብር 1 ሚሊየን 393 ሺ 810 ብር ከ26 ሳንቲም በብልጫ ተከፍሎ ተገኝቷል።
በብልጫ የተከፈለው ሂሳብም በግዢ ሂደት ያለበቂ ምክንያት ዝቅተኛ ዋጋ ያቀረቡ እያሉ ከፍተኛ ዋጋ ከቀረቡት ድርጅቶች ግዢ በመፈፀም፤ በድጋሚ ወጪ በማድረግ ወይም ከተገባው ውል ውጭ በመክፈልና ከውሎ አበል ተመንና የትርፍ ሰዓት ክፍያ በላይ በመክፈል የሚሉት ይገኙበታል።
በመሆኑም መ/ቤቶች የግዢና ፊይናንስ አስተዳደር ስርዓቱን ተከትለው መፈፀም እንደሚገባቸውና በብልጫ የተከፈለውም ገንዘብ ለመንግስት ካዝና ተመላሽ እንዲሆን አስፈላጊ እርምጃ እንዲወሰድ በሪፖርታችን አሳስበናል።
የንብረት ገቢ ደረሰኝ ያልቀረበለት
የመንግስት ገንዘብ ወጪ ሆኖ የተገዛው ንብረት ለመ/ቤቱ ገቢ ለመሆኑ የንብረት ገቢ ደረሰኝ የተቆረጠለት መሆኑን ለማረጋገጥ ኦዲት ሲደረግ፤ በ6 መ/ቤቶች በብር 20 ሚሊየን 240 ሺ 407 ብር ከ36 ሳንቲም የተገዙ ዕቃዎች የንብረት ገቢ ደረሰኝ ሳይቆረጥላቸው ሂሳቡ በወጪ ተመዝግቦ ተገኝቷል።
ከዚህም ውስጥ ጂማ ዩኒቨርሲቲ ብር 18 ሚሊየን 870 ሺ 460 ብር ከ03 ሳንቲም እና መደወላቡ ዩኒቨርሲቲ ብር 1 ሚሊየን 325 ሺ 755 ብር ከ75 ሳንቲም ለተገዛው ዕቃና ንብረት የንብረት ገቢ ደረሰኝ ካልቆረጡት ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
በተጨማሪም በኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ከውጪ ሀገር በድምሩ በአሜሪካን ዶላር 832 ሺ 255 ከ80ሳንቲም ተገዝተው የመጡ የተለያዩ ማሽነሪዎች ገቢ ያልተደረጉ መሆኑ ታውቋል።
የዚህ ዓይነት አሰራር ለንብረት ብክነት ስለሚያጋልጥ ለወደፊቱ ተመሳሳይ ሁኔታ እንዳይከሰት ጥንቃቄ ሊደረግና የንብረት ገቢ ደረሰኝ ያልቀረበላቸው ንብረቶች ለየመ/ቤቶቹ አገልግሎት ለመዋላቸው በማስረጃ እንዲረጋገጥ ለመ/ቤቶቹ በላክነው ሪፖርት አሳስበናል።
የወጪውን ትክክለኛነት ማረጋገጥ ያልተቻለ ሂሳብ
በበደች ዓመቱ መ/ቤቶች የፈፀሙት ክፍያ ትክክለኛነቱን ለማጣራት ኦዲት ሲደረግ፣ በ9 መ/ቤቶች በተለያየ ምክንያት ማስረጀ ባለመቅረቡ የወጪውን ትክክለኛነት ማረጋገጥ ያልተቻለ ሂሳብ ብር 3 ቢሊየን 507 ሚሊየን 062 ሺ 927 ብር ከ60 ሳንቲም ተገኝቷል።
የወጪውን ትክክለኛነት ማረጋገጥ ካልተቻለው ሂሳብ ውስጥ የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር ብር 3 ቢሊየን 169 ሚሊየን 110 ሺ 595 ብር ከ13 ሳንቲም፣ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ብር 187 ሚሊየን 857ሺ 058 ብር ከ5 ሳንቲም፤ ወሎ ዩኒቨርሲቲ ብር 41 ሚሊየን 288 ሺ 852 ብር ከ19 ሳንቲም፤ ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ብር 29 ሚሊየን 790 ሺ 947 ብር ከ40 ሳንቲም እና ሰመራ ዩኒቨርሲቲ ብር 14 ሚሊየን ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
ማንኛውም የመንግስት ባለበጀት መ/ቤት የፌዴራል መንግስት የፋይናንስ አስተደደር አዋጅ ደንብና የመንግሥት የሂሳብ አያያዝ መመሪያዎችን ተከትሎ ሂሳቡን መያዝና ኦዲት ማስደረግ ስላለበት እነኚህ መ/ቤቶች ለወደፊቱ ተገቢውን የማስተካከያ እርምጃ በመውሰድ የተሟላ ሰነድ በማደራጀት ሂሳባቸውን እንዲያስመረምሩ አሳስበናል።
በወጪ ሂሳብ ሪፖርት ያልተካተተ
ከውስጥ ገቢ እንዲጠቀሙ የተፈቀደላቸው መ/ቤቶች ከውስጥ ገቢያቸው ያወጡትን ወጪ በወጪ ሂሳብ ሪፖርት አካተው ለገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር የሚያቀርቡ መሆኑን ለማረጋገጥ ኦዲት ሲደረግ፤ በ6 መ/ቤቶች የብር 159 ሚሊየን 482 ሺ 075 ብር ከ35 ሳንቲም ወጪ በወጪ ሂሳብ ሪፖርት ተካቶ በሕጉ መሠረት ለሚኒስቴር መ/ቤቱ ሪፖርት ያልተደረገ መሆኑ ታውቋል። ከዚህም በተጨማሪ የውስጥ ገቢ ሂሳባቸውን በገቢ ሂሳብ ሪፖርት የማያካትቱ 15 የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በገንዘብ መጠን ያልታወቀ ወጪ በወጪ ሂሳብ ሪፖርት የማያካትቱ በመሆኑ ሂሳቡን ኦዲት ማድረግ አልተቻለም።
ይህ አሰራር የዘመኑ የፌዴራል መንግስት ዓመታዊ ገቢና ወጪ ሂሳብ መግለጫን የሚያዛባ ከመሆኑም በላይ ሕገወጥ በመሆኑ እንዲስተካከል ባለፉት ዓመታት ሪፖርታችን ብናሳስብም ሊስተካከል አልቻለም። ስለሆነም ሊሰበሰብ የሚገባው የመንግሥት ገቢ በአግባቡ እንዲሰበሰብ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ከሚመለከታቸው ጋር በመሆን ተገቢውን የማስተካከያ እርምጃ በመውሰድ ለተከበረው ም/ቤት ሪፖርት እንዲያቀርብ ሊደረግ ይገባል።
የተከፋይ ሂሣብ
በወቅቱ ያልተከፈለ ተከፋይ ሂሳብ
በገ/ኢ/ል/ሚ/ር መመሪያ መሠረት በበጀት ዓመቱ በተከፋይ ሂሳብ የተያዙት ሂሳቦች በተገቢው ጊዜ ውስጥ መከፈላቸውን ለማረጋገጥ ኦዲት ሲደረግ በ29 መ/ቤቶች ብር 491 ሚሊየን 128 ሺ 467 ብር ከ58 ሳንቲም በወቅቱ ያልተከፈለ ተከፋይ ሂሳብ ተገኝቷል።
በወቅቱ ያልተከፈለ ተከፋይ ሂሳብ ከታየባቸው መ/ቤቶች ሀገር መከላከያ ሚኒስቴር ብር 173 ሚሊየን 824 ሺ 549 ብር ከ10 ሳንቲም፤ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ብር 159 ሚሊየን 330 ሺ 268 ብር ከ77 ሳንቲም፤ ትምህርት ሚኒስቴር ብር 64 ሚሊየን 327 ሺ 615 ብር ከ57 ሳንቲም፤ ጅማ ዩኒቨርሲቲ ብር 25 ሚሊየን 010 ሺ 347 ብር ከ 22 ሳንቲም እና የግብርናና ቴክኒክ ሙያ ማሰልጠኛ ማስተባበሪያ ብር 23 ሚሊየን 125 ሺ 504 ብር ከ24 ሳንቲም ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
በሀገር መከላከያ ሚኒስቴር በሰኔ 30/2004 ከሠራዊት ደመወዝ ተመላሽ ተብሎ ሪፖርት የተደረገው ብር 163 ሚሊየን 504 ሺ 599 ብር ከ94 ሳንቲም የሠራዊቱ አባላት ደመወዝ ባለመውሰዳቸው ለረጅም ዓመታት በተከፋይ ሂሳብ የተያዘና መጠኑም እያደገ የመጣ ከመሆኑም በላይ ክፍያው ሳይፈፀም ሂሳቡ በወጪ የተመዘገበ ሲሆን፤ ቀሪው ብር 10 ሚሊየን 319 ሺ 949 ብር ከ16 ሳንቲም ለበርካታ ዓመታት በተከፋይ የተያዘና ለማን እንደሚከፈል የማይታወቅ መሆኑ ታውቋል። አሰራሩ ከመንግሥት የሂሳብ አሰራር ውጭ በመሆኑ እንደማንኛውም የፌዴራል መንግሥት መ/ቤት ያልተከፈለ ደመወዝ በቀጣዩ ወር መጀመሪያ ለገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ፈሰስ መደረግ እንዳለበት ደመወዝ ካልተከፈላቸው አባላት ጥያቄ ሲቀርብ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር እየተጠየቀ እንዲከፈልና ሌሎችም መ/ቤቶችም በወቅቱ ያልተከፈለውን ተከፋይ ሂሳብ የፋይናንስ አስተዳደር ሕጉን ተከትለው ለሚመለከተው አካል እንዲከፍሉ አሳስበናል።
በተጨማሪም በ12 መ/ቤቶች የተለያዩ የተከፋይ ሂሳብ አያያዝ ችግር ያለባቸው፤ ያለበቂ ማስረጃ በተከፋይ ሂሳብ የተመዘገቡ፤ ለማን እንደሚከፈል የሚያመለክት ዝርዝር ማስረጃ ባለመቅረቡ ትክክለኛነታቸውን ማረጋገጥ ያልተቻለ፤ በተከፋይ ሂሳብ መግለጫ ያልተካተቱ፤ እንዲሁም ያልተለመደ የሂሳብ ሚዛን የሚያሳዩ ተከፋይ ሂሳቦች ተገኝተው አስፈላጊው ማስረጃ እንዲቀርብና ተገቢው ማስተካከያ እንዲደረግላቸው ለየመ/ቤቶቹ በላክነው ሪፖርት አሳስበናል።
የበጀት አጠቃቀም
ከተደለደለው በጀት በላይ ወጪ የሆነ ሂሳብ
መ/ቤቶች የተፈቀደላቸውን በጀት በአግባቡ መጠቀማቸውን ለማረጋገጥ በተደረገው ኦዲት በ27 መ/ቤቶች ለልዩ ልዩ የሂሳብ መደቦች ከተፈቀደላቸው በጀት በላይ በደንቡ መሠረት ሳያስፈቅዱ ሥራ ላይ የዋለ ብር 212 ሚሊየን 476 ሺ 799 ብር ከ01 ሳንቲም ተገኝቷል።
ከበጀት በላይ ወጪ ካደረጉ መ/ቤቶች ባሕርዳር ዩኒቨርስቲ ብር 40 ሚሊየን 976 ሺ939 ብር ከ3 ሳንቲም፣ ሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ብር 30 ሚሊየን 910 ሺ 509 ብር ከ49 ሳንቲም፣ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ብር 28 ሚሊየን 217 ሺ 838ብር ከ81፣ ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ብር 22 ሚሊየን 225 ሺ 409 ብር እና በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የቆላ ዝንብ ማጥፊያ ፕሮጀክት ብር 21 ሚሊየን 636 ሺ 005 ብር ከ12 ሳንቲም ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
በመሆኑም መ/ቤቶች በፋይናንስ አስተዳደር አዋጅና ደንብ መሠረት የተፈቀደላቸውን በጀት በተገቢው መንገድ የበጀት ዝውውር በማድረግ አስፈቅደው ሥራ ላይ ማዋል እንዳለባቸው አሳስበናል።¾
ምንጭ የዛሬው ሰንደቅ ጋዜጣ (ሜይ 1 ቀን 2013)
Previous Story

ኢትዮጵያ በርግጥ ዴሞክራሲ ይገባታል ወይ?

0
Next Story

“ኢሕአዴግን ጥለን እኛ እዚህ የምንቧቀስ ከሆነ ኢሕአዴግ ባይወድቅ ደስ ይለኛል” – ግርማ ሰይፉ (የፓርላማው አባል)

Latest from Blog

አዲስአበባ ተኩስ ተከፈተ “ለመደራደር ዝግጁ ነን” አረጋ ከበደ | አብይ አደገኛውን ካርድ መዘዙ | አዲሱ አዋጅና የቀረበበት ተቃውሞ “የሞተም ሰው ንብረት ይጣራል | ጌታቸው ያጋለጠው ጸብ

አዲስአበባ ተኩስ ተከፈተ “ለመደራደር ዝግጁ ነን” አረጋ ከበደ\  አዲሱ አዋጅና የቀረበበት ተቃውሞ “የሞተም ሰው ንብረት ይጣራል አብይ አደገኛውን ካርድ መዘዙ ጌታቸው ያጋለጠው ጸብ

ከመጠምጠም መማርን እናስቀድም!

;በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com) አብዛኛው አንባቢ ተገንዝቧል ብዬ እንደምገምተው ሕዝብ ለቡና ቲራቲም፣ ለግብዣ፣ ለበዓል፣ ለሰረግ፣ ለሐዘን፣ ለእድር፣ ለእቁብ ለውይይትና ለሌሎችም ማህበረሰባዊ ጉዳዮች ሲገናኝ የሚበዛው አድማጭ ሳይሆን ተናጋሪ  ወይም ደግሞ ለመናገር  መቀመጫውን ከወንበር ወይም
Go toTop