የሰንደቅ ጋዜጣ ገጽ ሶስት፣ የአዲስ ዘመን ገጽ ሶስት መንትያ

በዳዊት ሰለሞን 
 (ምንጭ: ፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ)  http://www.fnotenetsanet.com/?p=4112)

አመታዊ በጀት የተያዘለት፣ባለቤቶቿ ከመጋረጃው በስተጀርባ የሚዘውሯትና እራሷን የነጻ ጋዜጦች ‹‹ምድብ ›› ውስጥ የምትቀላቅለው ‹‹ሰንደቅ›› ጋዜጣ (በነገራችን ላይ ፋናም የግል መሆኗን ወገቧን ገትራ እንደምትከራከርና  አንባቢ መርሳት አይገባውም) ሰርግና ምላሽ ሆኖላታል፡፡ ሰርግና ምላሹም አንድነት ለዴሞክራሲና ፍትህ ፓርቲን በውድቀት አፋፍ እንዳገኘችው ጋዜጣዋ ማመኗን ተከትሎ የተፈጠረ ነው፡፡

ሰንደቅ የሚያዚያ ወር ቁጥር 397 ዕትም ‹‹በቃኝ›› በሚል ርዕስ የአንድነት ፓርቲ አመራር የነበሩት ኢንጅነር ዘለቀ ረዲ የሰጡትን እርስ በእርሱ የተጣረሰ ቃለ ምልልስ፣ የኢንጅነሩን ከአመራርነት መልቀቅ በድጋሚ በዜና መልክና ከአዲስ ዘመን ገጽ ሶስት ተዛምዱ ባለው መልኩ ሰንደቅም በገጽ ሶስቷ ‹‹ኪራይ ሰብሳቢነት ፣በአንድነት ፓርቲ ›› በሚል ዐቢይ ርዕስ ፓርቲው ላይ በማነጣጠር የሳምንቱን አጀንዳዋን አንድነትን አድርጋለች፡፡

ኢንጅነሩ ለምን ‹‹በቃኝ›› ማለታቸውን ሰንደቅ ዘገበች በማለት ለወቀሳ አልቸኩልም፡፡‹‹በቃህ››የተባሉት ሰው ፣ሁሉን ቀድሜ ‹‹በቃኝ›› አልኩኝ ማለታቸውን ለምናውቅ ሰዎችም ጋዜጣዋ ለኢንጅነሩ መድረክ  እንደምትሆን እንጠብቀው የነበረ ነገር እንጂ እንግዳ አይደለም፡፡

በገጽ 3 አንድነትን የገዢውን ፓርቲ ልሳን በመዋስ ‹‹በኪራይ ሰብሳቢነት›› ለመወንጀል ስማቸው ያልተጠቀሰው ‹‹የጋዜጣዋ ሪፖርተር›› ዙራዙሩን ዞረው እርባና ያለው መረጃ ሳያቀርቡ ለፓርቲው በመጨረሻው መጨረሻ አዛኝ ቅቤ አንጓች በመምሰል ‹‹ራሱን ማጽዳት አለበት››በማለት ጽሁፋቸውን ቋጭተዋል፡፡ ሰንደቅ የጋዜጠኞቿን  ሃላፊነት በምትጠቅስበት ግርጌ ‹‹ሪፖርተር ››እንዳላት ባትክድም ስያሜያቸው ‹‹ከፍተኛ ሪፖርተር››እንደሆነ ትነግረናለች፡፡ ገጽ ሶስት ላይ የወጡት ጸሀፊ ግን ‹‹የጋዜጣው ሪፖርተር ነኝ ››ማለታቸውም የሰንደቅንና የአዲስ ዘመንን ቤተሰባዊነት ቅርብ ያደርገዋል፡፡
(እረስቼው ለካ አዲስ ራዕይም ስሙ የተጻፈ ዋና አዘጋጅ የነበራት ቢሆንም ዋና አሰናጇ ግን መለስ ዜናዊ ነበሩ፡፡)

ተጨማሪ ያንብቡ:  “ሣንሞት መቀባበር መቼ ይሆን የሚቆመው?

አንድነት ‹‹በሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች ላይ የሚሰነዝረው የኪራይ ሰብሳቢነት ውንጀላ ተቀባይነት የሚኖረው ፓርቲው ከኪራይ ሰብሳቢነት ፣አመለካከት ሙሉ ለሙሉ ራሱን ማጽዳት ሲችል ብቻ መሆኑ ግንዛቤ ሊወሰድ ይገባል፡፡ መልእክቱ ግልጽ፣ ቋንቋውም አንድና አንድ ነው፡፡

እርግጥ ነው አንድነት ገዢውን ፓርቲ በሙሰኝነት ሲከስ ቆይቷል፡፡ ኢህአዴግም ቢሆን በአንድ መድረኩ ‹‹ዋነኛ ችግሬ ኪራይ ሰብሳቢነት ነው፡፡)በማለት ተናግሯል፡፡ አሁን ሰንደቅ አንድነት ሌሎችን በሚከስበት ሚዛን ላይ ሲቀመጥ ቀልሎ ስለ መገኘቱ በሚጮህ ርዕስ ስር አገኘሁ ያለችውን መረጃ አቅርባለች፡፡

ኪራይ ሰብሳቢነትን በአንድነት ቀረበ ከተባለው ማስረጃ አንጻር የሚመዝኑ ሰዎች ‹‹ኪራይ ሰብሳቢዎችን በፓርቲው የማያገኙ በመሆናቸው ጋዜጣዋን መታዘባቸው እንደተጠበቀ ሆኖ የኪራይ ሰብሳቢ ፖለቲካ ኢኮኖሚ ምን ማለት እንደሆነ እንመልከት፡፡

ለኪራይ ሰብሳቢነት አቻ ትርጉም ለመስጠት የሞከሩ ባለሞያዎች የጋራ ስምምነት ላይ በመድረስ አንድ አይነት ድምዳሜ ላይ ባይደርሱም አንድ የሚያደርጋቸውን ትርጓሜ ከመስጠት አልተቆጠቡም፡፡
Rent-Seeking When a company, organization or individual uses their resources to obtain an economic gain from others without reciprocate any benefits back to society through wealth creation.(ኪራይ ሰብሳቢነት፤ አንድ ካምፓኒ፣ድርጅት ወይም ግለሰብ የኢኮኖሚ ጥቅም ከሌሎች ለማግኘት በእጁ  የሚገኘውን ሀብት  ለማህበረሰቡ ምንም አይነት ጥቅም ሳያበረክትበት ሀብቱን ለራሱ ብቻ  ለማከማቸት መፈለግ ነው፡፡) በዚህ ትርጓሚ መነሻነት ሰንደቅ አንድነት ውስጥ ተገኘ ያለችውን ኪራይ ሰብሳቢነት ብንፈልገው ዱካውን እንኳን ማግኘት አንችልም፡፡

የፓርቲው የፋይናንስ ኮሚቴ ለፓርቲው ማጠናከሪያ የገቢ ማሰባሰቢያ እቅድ በመንደፍ በ2004 አንድ ምሽት የእራት ፕሮግራም በማዘጋጀት የትኬት ሽያጭ ያቀርባል፡፡ በዚህም መሰረት እያንዳንዱ የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ 15,000 ብር የሚያወጡ ኩፖኖችን እንዲሸጥና ገንዘቡን ገቢ እንዲያደርግ ያዛል፡፡ (ሰንደቆች የፓርቲው ጸሀፊ 24.000ብር አላስገቡም በማለት መዘገባቸው በዚህ አጋጣሚ ፍጹም ውሸት መሆኑን ከፓርቲው የፋይናንስ ኮሚቴ ማጣራት እንደሚቻል መጠቆም እወዳለሁ፡፡) ኮሚቴው በቅርቡ ይፋ ባደረገው ሪፖርቱ ከኩፖን ሽያጭ ገቢ መደረግ ከነበረበት ውስጥ የተወሰነው ተሟልቶ አለመግባቱን በመጠቆም ያልተሸጠ ኩፖን በእጁ የሚገኝ አመራር ያልተሸጠውን ኩፖን ገቢ እንዲያደርግ ጠይቋል፡፡ እንግዲህ ሰንደቅ ይህንን ሪፖርት በመውሰድ ‹‹አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ በኪራይ ሰብሳቢነት ተጨማልቋል›› ለማለት የደፈረችው፡፡
(በነገራችን ላይ ከፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የፋይናንስ እንቅስቃሴውን በውጪ ኦዲተር በማስመርመር ከምርጫ ቦርድ የምስክር ወረቀት ያገኘ አንድነት ብቻ መሆኑን ሰንደቆች ያውቁ ይሆን?)

ተጨማሪ ያንብቡ:  በእንቆቅልሽ ኖሮ በእንቆሽልሽ ያረፈው ድምፃዊ ጥላሁን ገሰሰ

እኛ አገር ሁሉም ነገር በራስ አረዳድና በአድርባይነት ከታመነለት ወገን ፍላጎት በመነሳት ትርጉም የሚሰጠው በመሆኑ ኪራይ ሰብሳቢነት ወይም (Rent-Seeking)ሁሉንም አይነት ትርጉም በመያዝ ውዥንብር እየፈጠረ ይገኛል፡፡ በአንድ ወቅት ታዋቂው አትሌት ሻለቃ ሃይሌ ገ/ስላሴ ‹‹ህንጻ በመስራት እያከራየሁ ገቢ አገኛለሁ፣እና እኔ ኪራይ ሰብሳቢ ነኝ ›› በማለት መጠየቁን ሰምቼ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ሰንደቅ ተሸጦ ይሁን ሳይሸጥ ገቢ ያልተደረገበትን ምክንያት ያልታወቀ ኩፖን በስራ አስፈጻሚዎቹ እንደተበላ በመቁጠር ‹‹በትንሹ ያልታመኑት አንድነቶች በትልቁ እንዴት ይታመናሉ፡፡›› በማለት ለመሳለቅ ትሞክራለች፡፡ ለመሆኑ በሰነድ ደረጃ የሚገኝን ኩፖን እንደ ገንዘብ በመውሰድ ድምር ወጥቶለት እንዴት ለኪራይ ሰብሳቢነት ውሏል ይባላል? እርግጥ ነው የፋይናንስ ኮሚቴው በሪፖርቱ ገንዘቡና ያልተሸጠው ኩፖን ገቢ ይደረግ ብሏል፡፡

ሰንደቅ እነዚህን እውነታዎች በተጣረሰ መልኩ የራሷንና የጌቶቿን የቃላት ፍቺ በመጠቀም‹‹ኪራይ ሰብሳቢነት በአንድነት ነግሷል ትላለች፡፡
ግጥምጥሞሹ ለአንዳንድ የዋሃን የአጋጣሚ ሊመስላቸው ቢችልም የአዲስ ዘመን ገጽ ሶስትና የሰንደቅ ገጽ ሶስት ድብቅ አላማን በማንገብ ተመሳሳይ ውጤት ላይ ለመድረስ ብዕራቸውን ከወረቀት ባገናኙ ዙምቢዎች ሀሳብ እንዲሞሉ ተደርገዋል፡፡

 

1 Comment

  1. ዳዊት ሰለሞን እዚህም እዚያም የሚረግጠውን ጹሑፍዎን አነበብኩት፡፡መነሻዎ ልክ እንደአለቆችዎ ሰንደቅ ጋዜጣ ለምን የአንድነትን ጉድፍ (ገመናችንን) ዘገበች የሚል ነው፡፡ለምን ባዕድ ድምጽ ተሰማ፣ለምን የማንወደው፣የማንፈቅደው ነገር ተነገረ፣ለምን ሰዎች ኀሳባቸውን በነጻነት ገለጹ የሚል ነው፡፡ የተከበሩ ፕሮፖጋንዲስት ዳዊት፤ ሰንደቅ ከፍኖተ ነጻነት ጋዜጣ የምትለይበት ትልቁ ነጥብ ይህ ነውና እውነቱን እየተናነቅዎትም ቢሆን ይቀበሉት (ይቅርታ፤ ፕሮፖጋንዲስት ያልኩት የፓርቲ ልሳን ላይ የሚሰራ ሰውን ጋዜጠኛ ማለት ስለማይቻል ነው)፡፡ ፍኖተ ነጻነት የፓርቲ ልሳን ነው፡፡ልሳን ደግሞ ከቆመለት ፓርቲ ውጪ ሊናገርበት የሚችልበት ነጻነት ሆነ ቋንቋ ሊኖረው አይችልም፡፡(እዚህ ላይ የፓርቲ ልሳኗ ፍኖተ ነጻነት ነጻ ጋዜጣ ነኝ፣ እመኑኝ እያለች በምትምልና በምትገዘትበት በዚህ ወቅት ሰንደቅ ነጻ ጋዜጣ አይደለችም የሚል ሙግት መጀመርዎም ሲበዛ ያስገርማል፤ያስተዛዝባልም፡፡በኔ ይሁንብዎ፤ በእርስዎ ሚዛን የነጻ ጋዜጣን ካባ ለመደረብ እንደፍኖተ ነጻነት የአንድነት ልሳን መሆን ነበረባችሁ እያሉን ይሆን!? ይገርማል! ቂቂቂቂቂቂቂ…..)
    እናም የተከበሩ…ዳዊት በበሉበት መጮኸዎ ተለክቶ የተሰጥዎ የልሳን ግዴታዎ ነውና አይደንቅም፡፡ሰንደቅ ግን በገዥው ፓርቲም ይሁን በተቃዋሚው ጎራ ያሉትን የሚወደድም ይሁን የማይወደድ ተጨባጭ ወሬዎችን ለመዘገብ ምንም የሚያግዳታት ነገር የለም፤ፍኖተ ነጻነት ጋዜጣ አይደለችምና፡፡እናም ልክ በፍኖተ ነጻነት ልክ ካልተሰፋችሁ አዲስዘመን ናችሁ ዓይነት ሙግት ስልችት ያለ፣ የቆረፈደ፣የጠነዛ ሙግት ነው፡፡(በነገራችን ላይ ይህ ዛሬ ደፍረው ሊያጣጥሉት ከሞከሩት የሰንደቅ ጋዜጣ “ሥራችሁን እናደንቃለን፣ልምዳችሁን አካፍሉን” በሚል በደብዳቤ ጠይቃችሁ ደርዘን የፍኖተ ነጻነት ሰዎች መምጣታችሁንስ እንደምን ሊዘነጉት ቻሉ?…ያን ግዜ ሰንደቅ የአዲስዘመን ገጽ ሶስት አቻ መሆኑ አልተከሰተላችሁም ነበር ማለት ነው!..ቂቂቂቂቂ….) ከዚህ ጉንጭ አልፋ ክርክር ይልቅ ሰንደቅ ወደዘገበችው ጉዳይ መጥተው አንድነትን የሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ከቻሉ መልስ ይስጡና እባክዎ ያሳፍሩን፡፡
    የአንድነት አመራር አባል የነበሩት ኢ/ር ዘለቀ የፓርቲው አመራሮች አምባገነን ናቸው ብለዋል፡፡ከዲያስፖራው የሚመጣው ገንዘብ ወጪና ገቢው አይታወቅም ብለዋል፡፡የግለሰቦች ፈላጭ ቆራጭነት እንጂ ዴሞክራሲያዊ አሰራር በፓርቲው ውስጥ አለመኖሩን ጠቅሰዋል፡፡ ለምን? ለምን? ለምን?…..እባክዎ ይመልሱልን ፡፡
    በእራት ምሽት ገንዘብ ለማሰባሰብ ታቅዶ ያልተሰበሰበውን ገንዘብ በተመለከተ ኪራይ ሰብሳቢ ተባልን ብለው ምርር ብለው እንደሕጻን ልጅ ከሚያለቅሱ ግለሰቦች እጅ ላይ ለምን የፓርቲው ገንዘብ ሊቆይ ቻለ ብለው ይጠይቁ፡፡ሰዎቹ ሪፖርት እስኪቀርብባቸው ድረስ ገንዘቡን ገቢ ሊያደርጉ ያልፈለጉት ለምን እንደሆነ ያስረዱን፤የሚጠቅመው ይህ ነውና፡፡
    በተረፈ ተጨባጭ ትችት ሲቀርብ ተንደርድሮ አቅራቢውን ለመዝለፍ አፍን መክፈት ባዶ ጭንቅላትን ከማሳየት ያለፈ ፋይዳ የለውም፡፡ከዚህ ይልቅ በጎ ትችቶችን ወስዶ በራስ ውስጥ ያለውን ጉድፍ መመልከቱ መሰልጠን መሆኑን በዚሁ አጋጣሚ ለፕሮፖጋንዲስቱ ዳዊት ሰለሞን ላስታውሳቸው እወዳለሁ፡፡
    አክባሪዎ

Comments are closed.

Share